Saturday, 23 December 2023 11:15

የሄርሜቲክ ፍልስፍና (Hermetic Philosophy) አንድ እርምጃ…To The Unknown

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(0 votes)


          ዛሬ ከጭንቅላታችን ጀምረን ከሁለንታ(Universe) ላይ ነጥረን እንድንመለስ ወደድኩ፡፡ በእናንተና በመላው አለማት መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት ላይ የሚያትተውንና የአለማትን ስርዓት ስለሚያስተዳድረው የተፈጥሮ ህግ ላይ መሰረት አድርጎ ሀሳብ የሚያነሳውን አንደኛውን የጥበብ መንገድ ይዤላችሁ መጥቻለሁ፡፡ አዕምሯችሁን ነፃ አድርጋችሁ ተከተሉኝ፡፡
ስለአንድ ሰው…(አማልዕክት) ሚስጥራዊ የአስተሳሰብ ስልት ላወራችሁ ነው፡፡
ስለዚህ ሰው ብዙ ተነግሯል፡፡ ሰው ይሁን አማልዕክት…ጥርት ያለ መረጃ የለም፡፡ ሆኖም ጥናቴ የመራኝ ድረስ ስለማንነቱ ሁሉንም ባላትት በጥቂቱ ለማስረዳ ልሞክር፡፡ ስሙ ህርም ትራስሚገስተስ ይባላል (Hermes Trismegistus) ፡፡ ጥንታዊዋ ሄለን ውስጥ በስፋት ስሙ የሚጠራለት ሰው ነው፡፡ በሌላም መልኩ ህርም ቶዝ (THOTH) ከሚባለው አማልዕክት ጋርም የሚያመሳስሉት አሉ፡፡ ይህን ጥርት ያለ መልስ ማግኘት ያልተቻለው በህርምስ ስም ብዙ ፀሀፊያን ስለፃፉም ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡
እንደ የግብፅ የታሪክ ተመራማሪዎች ትንተና፤ በዚህ ሊቃውንት ስም 36000 መፅሀፍት እንደተፃፉ ነው የሚነገረን፡፡ መፅሀፍቱ ከሚያነሱት ሀሳቦች መካከል ስለ ነፍስ አፈጣጠር እና አሰራር፣ የስነ ፍጥረታት አሰራርና መርሆች፣ የስነ-ከዋክብት ጥበብ፣ አልኬሚ፣ ምትሀት የመስራት ጥበብ፣ ህክምና ላይ እና ሌሎችም ጠለቅ ያሉ ሀሳቦች ላይ ነው፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ መፅሀፍት የት እንዳሉ መድረሻቸው አይታወቅም፡፡ ምናልባትም በዚህ ዘመን ላይ በሚስጥራዊ እውቀት ላይ ጥናት የሚያደርጉ ጠቢባን ሊያገኙዋቸው የሚችሏቸው መፅሀፍት Emerald Tablet of Hermes Trismegistus - Origins of Alchemy and Hermetic Philosophy እና The Kybalion የሚባሉት ብቻ ናቸው ነው ተብሎ የሚታሰበው፡፡
የዚህን ሰው ወይም አማልዕህት ወይም ሀሳብ ባለቤት ሆነው… በሚስጥራዊ ማህበሮቻቸው ውስጥ መርሆቹን ከሚተገብሩት የሄርሜቲክ ሚስጥራዊ ማህበራትም መካከል ሮዚክሩሺያንስ፣ ፍሪሜሰንስ እና ሄርሜቲክ ኦርደር ኦፍ ጎልደል ዶን በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በ1945 በግብፅ ናግ ሃማዲ ውስጥ እንደ አዲስ ሊገኝ የቻለው የዚህ የጥበብ መዝገብ በአዲስ መልክ ለዚህ ዘመን የሰው ልጆች ፍልስፍናው እንዲሰራጭ ምክንያት ሆኖታል፡፡
የህርምስን ፍልስፍና በሁለት አይነት መንገድ በትነን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በቲዮሪ የሚገለፀውና በፍልስፍና ደረጃ ብቻ የሚተረከው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተግባራዊው የፍልስፍና መንገድ ነው…ይህም በውስጡ ምትሀት መስራትን እና ከመናፍስት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ማድረግን የሚጠቁመን ነው፡፡ የዚህን ጥበበኛ ሰው የማንነት መሰረት ላይ ጥናት በራሳችሁ እንድታደርጉ ጠቁሜ፣ ከፃፋቸው መፅሀፍት አንዱን በመንቀስ ለዚህ አምድ በሚመጥን መልኩ ለማቅረብ ልሞክር፡፡ የመፅሀፉ ርዕስ The Kybalion የሚል ነው፡፡ በውስጡም የምንመለከተውን የሁለንታ አለም የሚመራው ህግ ላይ መሰረት አድርጎ ፍልስፍናውን የሚጀምር ሲሆን ያንንም ህግ ህይወታችን ውስጥም ሆነ የሰው ህይወት ውስጥ በጥንቃቄ እንዴት አድርገን እንደምንተገብረው እንማከርበታለን፡፡ በመርህ ደረጃ ሰባት መርሆች ተጠቅሰው እንመለከታለን፡፡ እያንዳንዱ መርህ አንዱ ከአንዱ በቅርፅ ይለያዩ እንጂ በዲግሪ ሰባቱንም አንድ የሚያደርጋቸውም ነገር አለ፡፡ እሱም ተፈጥሮ ነው፡፡
 እንጀምር…
 The Principle of Mentalism
‘The All is Mind: The Universe is Mental’ – The Kybalion.
ይህ የመመሪያ መንገድ የሚጠቁመን በሁለንታ (Universe) ውስጥ የሚከናወኑት ነገራት በሙላ የሚመነጩት ከአዕምሮ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ Reality መቀነባበር እና ወደ ተግባር መጥቶ ትርጉም መስጠት የሚችለው በአንድ ሰው ጭንቅላት ሲታሰብ እና ሲተገበር ብቻ ነው፡፡
ይህም ሲሆን መረዳት ያለብን ይህ ጭንቅላታችን በህግ መመራቱን ነው፡፡ የዚህ ተጠልቆ የማያልቀው ጭንቅላታችን ባለቤት ከመሆናችንም አንፃር …ምን ማሰብ እንዳለበትና የትኛው የእምነት ጣራ ላይ በብቃት መንጠላጠል እንዲችል የምናደርገው እኛው ራሳችን ብቻ ነን፡፡ በዚህ የአዕምሯችን ክፍል ውስጥ ውበት አለ…ፍፁም የሆነ ውበት፤ ሆኖም በዛው ልክ የአረመኔነትም ሆነ ፍፁም መጥፎ የመሆኛ መንገዱም የሚፈበረከው እዚሁ የአዕምሯችን ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ከሁለቱ የአስተሳሰብ ስልቶች ማምለጥ አንችልም፡፡ ይህም አንዱ የሁለንታ ህግ ነው፡፡
በሄርሜቲክ አስተሳሰብ “He who grasps the truth of the Mental Nature of the Universe is well advanced on The Path to Mastery.” ይባላል፡፡
አንድ ሰው አዕምሮው እንዴት አድርጎ እንደሚሰራ ሊያውቅ የሚችለው በጥልቀት ስለራሱና ስለራሱ ብቻ በቅድሚያ ጥናት ማድረግ ሲችል ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት ከሚጠቅሙን መንገዶች መካከል አርምሞ እና ራስን ጠንቅቆ ማወቅ ናቸው፡፡
በአርምሞ ውስጥ እያለን ሙሉውን የሰውነታችንን አሰራር ማየትና መገንዘብ እንጀምራለን … ይህም እውቀት እጅግ ወደረቀቀው ሚስጥር ይመራናል፡፡ ያም ሚስጥር ሁላችንም ወደ ውስጣችን በተጓዝን ቁጥር ራሱን እየገለጠልን ይመጣል፡፡ የኛ የአስተሳሰብ ስልትና ሞገድም መላው ሁለንታ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ መገንዘብ እንጀምራለን፡፡ ሁሉም አስተሳሰብና አካሄድ መሰረቱ አዕምሮ ብቻ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ አንደኛው የሄርሜቲክ ፍልስፍና እና ራስን ፈልጎ አግኝቶ ከመላው አለማት ጋር እንዴት አድርገን በአርምሞ ብቻ ቀጥታ ግንኙነት ማድረግ እንደምንችል የሚያስረዳን የሀሳብ መንገድ ነው፡፡
ይህም እውቀት ላይ ለመድረስ ሄርሜቲኮች በራሳቸው ቀመር የፈበረኩት የአርምሞ (Meditation) የጥበብ መንገድ አላቸው፡፡ እነሱን ለብቻቸው በሌላ ቀን በታትነን እንመለከታቸዋለን፡፡
ሁሉም የተፈጥሮና የሁለንታ ሚስጥር በጭንቅላታችን ውስጥ ቀድሞ ተመልሶ አልቋል… ከኛ የሚጠበቅብን አስፈላጊውን የአርምሞ መርህ ተከትሎ ምላሾቹን በተፈጥሯችንና በእውቀታችን ስርዓት ልክ መስጥረን መረዳታችንን ማስፋት ነው፡፡
2. The Principle of Correspondence
        “As above, so below; as below, so above.”--The Kybalion.
ከላይ ያነበባችሁት ጥቅስ ላይ ለብቻው ጊዜ ሰጥተን እንወያይበታለን፡፡ በውስጡ ያመቀው ሚስጥር ሰፊ ስለሆነ፡፡
ለጊዜው ግን ከሄንሞቲክ ፍልስፍና አንፃር ለመመልከት እንሞክር፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ስልት ብዙ ውስብስብ የሆኑ ሚስጥራትን ነው የሚፈታልን፡፡ ከእይታችንም ሆነ ከመረዳታችን በላይ የሚገኙ ፍጥረታትም ሆኑ የተፈጥሮ ቀመሮች ከበውን ተቀምጠዋል፡፡ ሆኖም ይህን መመሪየ መጠቀም ስንጀምር የተሸፈነው በሙላ ገሀድ መውጣት ይጀምራል፡፡ በፍፁም ሊገባኝ አይችልም ያልሺውም ነገር በሙላ ትርጉም መስጠት ይጀምራል፡፡ በቁሶች ላይ፣ በጭንቃላታችን ውስጥ እና በመንፈሳዊው አለም ውስጥ ያሉትን ሚስጥራዊ እውቀቶችም ላይ ትኩረት ሰጥተን ብናሰላስልበት ህይወት የሚመስል ነገር እናገኝበታለን፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው…
ሄርሜቲስቶች እንደሚሉት፤ እንደ የጂኦሜትሪ መርህ የሰው ልጅ ባለበት ተቀምጦ የፀሀይን ርዝማኔና እንቅስቃሴዎቿን እንዲረዳ እንደሚያደርገው ሁሉ ይህን መርህ በመጠቀምም የሰው ዘር እስከዛሬ ድረስ ተደብቆበት የከረመውን ድብቅ ሚስጥራት ባለበት ሆኖ የትም ሳይደርስ እንዲረዳው ያደርገዋል፡፡
ሄርሜቲኮች ይህን ጥበብ ተጠቅመው የአስትሮሎጂ እውቀታቸውን አስፍተውበታል፡፡ በሰማይ ላይ የሚብለጨለጩት ከዋክብት የሰማይ ላይ ጌጥ ከመምሰል በተረፈ ከሰው ልጅ እጣ ፈንታና የአስተሳሰቡ ስልት ጋር ቀጥታ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ነው የሚናገሩት፡፡ በሌላም ምሳሌ ብንመለከተው በፀሀይ ዙሪያ የሚሽከረከሩት ፕላኔቶች ላይ የሚሰራው ህግ አቶምና በዙሪያው ከሚዞሩት ኤሌክትሮኖች ጋር ቀጥታ የሆነ መመሳሰል እንዳላቸው እንመለከታለን፡፡
ይህም መመሪያ ነባራዊው አለምን የሚመራውን ህግ በጥልቀት እንድንረዳው ያደርገናል፡፡ በአይን ልናየው የማንችለውን የዩኒቨርስ አሰራር ከአዕምሯችን አሰራር ጋር አማክረንና አመሳጥረን በሁለቱ መካከል ልዩነት እንደሌለም እንደርስበታለን፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ያለው አሰራር በመላው አለምም ላይ እየሰራ ነው፡፡ እኛና መላው ዩኒቨርስ አንድ ነን፡፡
3. The Principle of Vibration
“Nothing rests; everything moves; everything vibrates.”--The Kybalion.
ይህን አስተሳሰብ አሁን ያሉት ሳይንቲስቶች በብዛት ይናገሩት እንጂ ከሺህ አመታት በፊት በጥንታዊ ግብፅ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሊቃውት ቀድመው ደርሰውበት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለው፡፡ ምንም አይነት ስነፍጥረት ያለ እንቅስቃሴ አንድ ቦታ የተቀመጠ የለም ነው የሚለው የሄርሜቲክ ፍልስፍና፡፡ ቁስ አካል፣ ሀይል፣ አዕምሮ እና መንፈስን ጨምሮ በየራሳቸው የንዝረት ልክ ነው ምንነታቸው ትርጉም እያገኘ የሚሄደው፡፡
 ከአዕምሮ አሰራር ጀምሮ እስከ ቁስ አካል ድረስ ሁሉም የየራሱ ንዝረትን እየተከተለ በስለፍጥረት ህግጋት ውስጥ ራሱን ይገልጣል፡፡ ሆኖም ሁሉም ፍጥረት ተመሳሳይ ንዝረት የለውም፡፡
ፍላጎታችን የራሱ ንዝረት አለው፡፡ የምንበላው ምግብ የራሱ ሞገድ አለው፡፡ የምንሰማው ሙዚቃ በሞገዱ ልክ ነው ሀሳባችንን በደስታና በሀዘን ውስጥ የሚቃኝልን፣ አጠገባችን የሚቀመጥ ሰው የራሱ ወደ እኛ ሞገድ ውስጥ የሚሰድብን ንዝረት አለው….ለዛም ነው ቅዱስ ስፍራዎች የሚባሉት የሀይማኖታዊያን መሰባሰቢያ ቦታ ላይ ስንቆም የምንረጋጋው እና እጅግ የሚጨንቅ ሀሳብና ተግባር የሚፈፀምበት ቦታ ጋ ስንሆን የዛን ስፍራ ሞገድ ሰብስበን ለብቻችን የምንሰቃየው፡፡ የምናወጣው የሀሳብ ሞገድ በዙሪያችን ያሉት ፍጥረታት ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር መረዳት አለብን፡፡
በዚህ መርህ በዘመኑ ይኖሩ የነበሩት ሄርሜቲኮች፤ የአዕምሯቸውን ሞገድ በመጠቀም መልካም የሆነውን ንዝረት ለህይወታቸው ይገብራሉ፡፡ ይህም ወደ ሀይል ይቀየራል፡፡ አዕምሯችን ውስጥ ሰትረን በምናብሰለስለው የሀሳብ ንዝረት ልክ ነው ቀጥለን ስለምናደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት የምናገኘው፡፡ አሁን የት ነን ያለነው? ምን እያዳመጥን ነው? በጠዋት ተነስተን ማግኘት የምንፈልገው ሰው ምን አይነት ሰው ነው? ለየትኛው እውቀትና ህይወት ስንል ነው ደፋ ቀና የምንለው? ለየትኛው አምላክ ነው የምንሰግደው? ሁሉም ነገር ውስጥ ያሉትን ንዝረቶች ባላችሁ ረቂቅ አዕምሮ መርምራችሁ ለመድረስ ሞክሩ፡፡   
“He who understands the Principle of Vibration, has grasped the scepter of power,” ይላሉ ሄርሜቲኮች፡፡ ይህ ማለት የንዝረት ህግን በመረዳት የሀይልን በትር በእጃችን ማድረግ እንደምንችል ነው የሚነግረን፡፡
4. The Principle of Polarity
“Everything is Dual; everything has poles; everything has its pair of opposites; like and unlike are the same; opposites are identical in nature, but different in degree; extremes meet; all truths are but half-truths; all paradoxes may be reconciled.”--The Kybalion.
ይህ ፍልስፍና የሚወስደን መንገድ አለው፡፡
ተከተሉኝ….
ምድር ላይ ያለም ሆነ ከምድር ውጭ የተፈጠረ ፍጥረት በሙሉ ሁለት ዋልታዎች አሉት ወይም በሌላ አገላለፅ ሁለት ተቃራኒ አካሎች በውስጡ ይዟል፡፡ ምንም ነገር ከሁለትዮሽ ውጭ መሆን አይችልም፡፡ ይህን በምሳሌ ለማስቀመጥ ልሞክር…
ለምሳሌ ንዳድ እና ቅዝቃዜ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ቢመስሉም ነገር ግን አንድ ናቸው፡፡ በምንም አይነት መልኩ አንድ ሰው ፍጹም የሆነ ንዳድ ውስጥም ሆነ ፍፁም የሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ሁለቱም የአንድ ሞገድ ውጤት ናቸው…እሱም ሙቀት ይባላል፡፡ ሙቀት ሁለት ፅንፎች እንዳሉትም በዚህ እንረዳለን፡፡
በሌላም መልኩ እንረዳው ብንል ጨለማ እና ብርሀንን ማንሳት እንችላለን፡፡ መቼ ነው ጨለማ ተወግዶ ብርሀን መምጣት የሚጀምረው? በትልቅና በትንሽ መካከል ምን ልዩነት አለ? በጠንካራ እና በለስላሳ? በጥቁር እና ነጭ? በጩኸት እና በፀጥታ? በከፍታ እና በዝቅታ? በመልካም እና በመጥፎ መካከል ምን ልዩነት አለ? ብለው ሄርሜቲኮች ይጠይቁናል፡፡ እስቲ በጥልቀት እነዚህ ጥያቄዎች ላይ ለማረመም ሞክሩ፡፡ እስከዛሬ ከምታዩትና ከምትተረጉሙት የአስተሳሰብ ስልት ውጭ ወጣ ብላችሁ የነገራትን ምንነት ለመረዳት ሞክሩ፡፡ ምክንያቱም እንደ ሄርሜቲክ እሳቤ፤ ሀሳብ ራሱ ሁለት ነው ዋልታው፡፡ እስከዛሬ በአንዱ ብቻ ስንጠቀም ከርመንም ይሆናል…እስቲ ያልተዳሰሰውን ዳሱት…ያልታየውን እዩት…የትም ሳትሄዱ፤ ራሳችሁ ውስጥ መልሱን ታገኙታላችሁ፡፡
አንድን ሰው እየወደድሺው ይሁን እየጠላሽው እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የሚያቅትሽ ጊዜ አልገጠመሽም? አንተስ ብትሆን አልፈልገውም የምትለው ነገር ላይ በሱስ ተጠምደህ ከዛ አስተሳሰብ ለመውጣትም በዛው ለመቅረትም ብለህ የገዛ ሀሳብህን ፈተና ውስጥ ከተኸው አታውቅም? አዕምሯችን ከዚህም በላይ መሰበጣጠር ይችላል፡፡ አንድ ሀይማኖተኛ የፈጣሪን ቃል በሰበከበት አፉ የፈጣሪን ስራ እና የሚመራውን ሀይማኖት የሚያሳፍር ስራ ሲሰራበት አስተውለናል፡፡ ሆኖም ከፍርድ ውጭ አድርገን የዚህን ግለሰብ አስተሳሰብ ብናጠናው የነዚህ ሁለት ፅንፍ ዋልታዎች ተጠቂ ሆኖ እንደነበር እንረዳለን፡፡
ሆኖም ለሁሉም የሁለንታ አሰራር የራሱ መንገድ መቀየሻ አቅጣጫ አሉት ይሉናል ሄርሜቲኮች፡፡ ጥንታዊ ሄርሜቲስቶች በራሳቸው ቀመር በፈበረኩት የአስተሳሰብ ዘዬ መጥፎን ነገር ወደ መልካምነት የመለወጥን ጥበብ ደርሰውበታል፡፡
ይህም ማለት በህይወታችን የሚገጥሙን እክሎች በሙላ በተፈጥሮ ስህተት የመጡብን መጥፎ ገጠመኞች ሳይሆኑ በሁለንታ ህግና በኛ ነፃ ፈቃድ አማካኝነት የሚከሰቱ የአዕምሮ ውጤቶች እንደሆኑ ነው እንድንረዳ የሚያስፈልገው፡፡ ምንም መጥፎ ነገር ቢደርስብን ያንን መጥፎ ነገር ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ አድርጎ በሀሳብ ከመታገል ፈንታ ያንን መጥፎ ገጠመኝ በህይወታችን እንድንጠነክር የሚያደርገን የተፈጥሮ ማስተማሪያና መንገድ መቀየሻ አሰራር እንደሆነ ተረድተን ነው ለቀጣይ መፍትሄ ራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን፡፡
ጊዜ ሰጥቶም ይህ መርህ ላይ ላረመመ ሰው የራሱን ብቻ ሳይሆን አጠገቡ ያለውንም ሰው አስተሳሰብ መቀየር እንደሚችል ነው የሄርሜቲክ አስተሳሰብ የሚነግረን፡፡ ከዛም ባለፈ የተፈጥሮን ጥልቅና ሚስጥራዊ የእርስ በርስ ግንኙነት በመገንዘብ የትኛውም ሀሳብ ላይ ከፈራጅነት ይልቅ ነገሩን ጠንቅቆ የመረዳትን ጥበብ በማጎልበትና ለሚመጡብን የራስ በራስ መጠይቆች መፍትሄ ፈጣሪዎች እንድንሆን ይረዳናል ፡፡
5. The Principle of Rhythm
 “Everything flows, out and in; everything has its tides; all things rise and fall; the pendulum-swing manifests in everything; the measure of the swing to the right is the
measure of the swing to the left; rhythm compensates.”--The Kybalion.
ይህን ለመረዳት የሁለንታን አሰራር በጥልቀት መረዳት በቂ ነው፡፡ ሁሉም ስነፍጥረት ልክ እንደ ሙዚቃ ኖት ስርዓቱን ጠብቆ ነው የሚሄደው፡፡ ምንም የሚረባበሽ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር በስርዓት እና በስልት ነው የተፈጠሩት፡፡ ተፈጥሯዊ አይደለም የምትለው ነገር በሙሉ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ተፈጥሮ ህጓን አትሽርም፡፡ ለማንም ብላም አሰራሯን አትቀይርም፡፡ ዜማዋን ጠብቃ ነው የምትሄደው፡፡
ይህም ማለት እኛ በዚህ የተፈጥሮ ሙዚቃ ውስጥ ኖታዎች ነን፡፡ ለተፈጥሮ ድምፅና ትርጉም የምንሰራላት እኛው ነን፡፡ ምክንያቱም እኛ ራሳችን ተፈጥሮ ነን፡፡ ከሁሉም ስነፍጥረት ጋር በሚስጥራዊ ሞገድ የተሳሰርን አንድም ሁሉም ነን፡፡
ልክ እንደፔንዱለሙ ውዝዋዜና የውዝዋዜ ፍጥነት… እኛም የራሳችንን ባህሪ እንደዛው መቃኘት እንደምንችል ነው ሄርሜቲኮች የሚነግሩን፡፡ እናም ማንም ራሱን ፈልጎ ያገኘ ሰው እና አዕምሮውን በፈቀደው መልኩ መጠቀም የሚችል ሰው ምናልባት እያልኩ ያለሁት ነገር ሊገባው ይችላል፡፡  
ሀሳብ የራሱ የሆነ ፍጥነት አለው፡፡ እንደ ፍጥነቱ ልክ በህይወታችን ላይ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ላይ ጠንካራ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ራሱን የገዛ ሰው እና እንዴት እና በምን አይነት ቅርፅ እያሰበ እንደሆነ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው፤ ውሳኔዎቹን በአዕምሮው ፍጥነት ልክ ለክቶ ለህይወቱ መፍትሄ እንደሚያመጣ ነው ሄርሜቲኮች የሚነግሩን፡፡
6. The Principle of Cause and Effect
    “Every Cause has its Effect; every Effect has its Cause; everything happens according to Law; Chance is but a name for Law not recognized; there are many planes of causation, but nothing escapes the Law.”--The Kybalion.
በእርግጥም ሁሉም ነገር የሚከሰተው በማይታይ ጥበባዊ ህግ ነው፡፡ በምድር ላይ ገጠመኝ የሚባል ነገር እንደሌለ ነው ሄርሜቲኮች የሚያምኑት፡፡ በተለይ በኛ ማህበረሰብ ውስጥ ያለ የሚገርመኝ የአኗኗር ስልት አለ፡፡ ይህም እርስ በርስ የመተያየትና አንዱ ያደረገውን ለማድረግ የሚካሄድ አሳዛኝ የአስተሳሰብ ስልት ነው፡፡ አንድ ሰው ስለራሱ ከሚጨነቀው በላይ ሰዎች ስለ እሱ ያላቸውን አስተሳሰብ እየገረበ መጨነቁን ይመርጠዋል፡፡ ይህንን የመሰለ አስተሳሰብ ያለው ሰው መውጣት ካለበት የእውቀት እና የንቃት ከፍታ ወርዶ በሀይል ዝቅ ብሎ እየበረረ እንደሆነ ነው የሚያስረዳን፡፡ ራሳችንን ዝቅ አድርገን ማየት የምንጀምረው የሌሎች ሰዎችን የምክንያት ጋጋታ ህይወታች ውስጥ ማስተናገድ ስንጀምርና የነሱ ሀሳብ ውጤት መሆን ስንጀምር ነው፡፡ በሌላ መልኩም በራሱ አስተሳሰብ የፀና ሰው የማህበረሰቡ አስተሳሰብ ውጤት መሆኑ ቀርቶ ማህበረሰብን የሚሰራ መሪ መሆን ይቻለዋል፡፡
የምክንያትና ውጤትን አስተሳሰብ ለመረዳት ብዙም ስለማያለፋ በዚህ ሀሳብ ላይ ብዙም ባልጓዝ ማንንም ቅር የሚያሰኝ አይመስለኝም፡፡  
7. The Principle of Gender
የመጨረሻው የሄርሜቲክ መርህ የሚነግረን ደግሞ ስለ ፆታ ነው፡፡ ይህም የሁለንታ ህግ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሁለት ዋልታዎች እንዳሉት ሁሉ፣
 እያንዳንዱም ነገር ሁለት ፆታዎች ብቻ አሉት፡፡ ይህም ዘር በምድር ላይ እንዲቀጥል የሚያደርግ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ፆታ በሁሉም ውስጥ አለ፡፡ የትኛውም ምድራዊም ሆነ መንፈሳዊ አለማት ውስጥ ያለ ስነ ፍጥረት የራሱ የሆነ የሚገለፅበት ፆታ እንዳለው ነው ሄርሜቲኮች የሚናገሩት፡፡ ሁለትና የተለያዩም ቢመስሉም ግን ሊለያዩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው….ወንድ እና ሴት፡፡
ሆኖም የተፈጥሮን ህግ ለመከተል ወንድ የወንድነትን ምንነት አሰላስሎ ሊደርስበት ይገባል፡፡ ወንድነት ውስጥ ያለ ሀላፊነትም ሆነ የራሱ የሆነ የገዢነት መንፈስ ልክ ሴት ውስጥም እንዳለ ተረድቶ በራሱ ምህዋር ውስጥ ብቸኛው…በምድር ላይ ሌጣ የሆነው ምንነቱን እንደ መፅሀፍ ገልጦና አንብቦ ሊረዳ ይገባዋል፡፡ በሁለንታና በሱ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነትም መገንዘብ አለበት፡፡ ምክንያቱም ሁለንታ እራሱ የራሱ ፆታ ስላለው…
ሴትም ልጅ ህይወትን የምትወልድና የመሸከም አቅም ያላት ፍጥረት ናት፡፡ የዚህ ተፈጥሮ ስርዓት ውጤት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የምታደርግ በራሷ ሀያል ፍጥረት መሆኗን መረዳት አለባት፡፡ አንድ የዛፍ ፍሬ ከዛፉ ላይ ሞቶና ወድቆ ምድር ውስጥ ተመልሶ ህይወት እንደሚሆነው ሁሉ ሴትም ያለወንድ ሆና ወይንም ወንድ ያለሴት ሆኖ ህይወትን ማስቀጠል አይችሉም፡፡ ይህም የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ከዚህም ስርዓት ውጭ ለመውጣት መሞከር ከራስ መራቅንና ምን አይነት ፍጥረት ተደርጎ እንደተሰራ ያለመረዳት ውጤት ነው የሚሆነው፡፡
እንግዲህ በአጭሩና በቀላል መንገድ የሄርሜቲክ ፍልስፍና ሲገለጥ ይህን ይመስላል፡፡ እነዚህ መርሆች ላይ ተመሰጡባቸው፡፡ እያንዳንዱን እሳቤ ነጥላችሁ በማውጣት ራሳችሁን ለመፈተሽ ሞክሩ፡፡ ጥበብ በየትም አለ፤ በሀሳብ ርቀትና ሞገድ ልክ ሁሉንም ሚስጥራት መመስጠር ይቻላል፡፡ የገዛ ጭንቅላትን በእምነት ውስጥ ሸሽጎ እውቀትን መሸሽ ያለነፍስ ስጋችንን ተንቀሳቀስ ብሎ ማስጨነቅ ይመስለኛል፡፡
መልካም የመፈላሰፍና በአዳዲስ ሀሳቦች… ሁለንታ ላይ የመራቀቅ ሳምንት ይሁንላችሁ እያልኩ ወደ ራሴ ሀሳብ ውስጥ ልስመጥ፡፡

Read 393 times