Saturday, 23 December 2023 11:19

”የዘጠኝ ሞት” ፊልም ሥነልቦናዊ ዳሰሳ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ዘጠኝ ሞት ጥንቅቅ ተደርጎ የተሰራ ስነልቦናዊ ድራማ ነው። ይዞ የተነሳው ዓለማቀፋዊ ጭብጥ፣ የገጸ ባህርይ አሳሳልና የተዋንያኑ ብቃት እንዲሁም የሲኒማው የላቀ ደረጃ ተወዳጅ አድርገውታል። በዚህ ዳሰሳበፊልሙ የተነሳው ስነ-ልቦናዊ ጭብጥ ላይ በማተኮር ስለ ሞት፣ ስለ ሀዘን፣ እውነታን በመካድ ራስን ስለ መደለልና ስለ ለቅሶ ባህላችን በወፍ በረር እንመለከታለን።
          ዶ/ር ዮናስ ላቀው፤ የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስትና የአማኑኤል ሆስፒታል ታሪኮች መጽሐፍ ደራሲ


       ሞት-ታላቁ ምስጢር
በዘጠኝ ሞት ላይ የተነሳው  ጭብጥ  የሁሉንም ሰው ልብ የሚያንኳኳ፣ ሁሉም ሰው ላይ የሚደርስ ነገር ስለሆነ “ይሄ ጉዳይ አይመለከተኝም” የሚል ሰው አይኖርም።  ሁላችንም የምንወዳቸውን ሰዎች በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ማጣታችን አይቀርም።  በጅምላ ዋናውን ከመሞታችን በፊት ደግሞ ትንንሽ የችርቻሮ ሞቶች ሁልጊዜ ዙሪያችን አሉ። ከሚወዱት ሰው መለየት፣ ከሀገር መሰደድ፣ ጤና የሚነሱ ህመሞች፣ ተቀብረው የቀሩ እምቅ ችሎታዎች… ወዘተ። ዘጠኝ ሞት እነዚህን ሁላችንም አዳፍነን ይዘናቸው የምንዘራቸውን ጥያቄዎች የሚቆሰቁስ ፊልም ነው።  በነባሪያዊ የስነ-ልቦና ህክምና (ጽንሰ ሀሳብ) መሰረት፤ ሰዎች ሁሉ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎች ጭንቀት ይፈጥሩብናል። እነዚህም ብቸኝነት፣  ነፃነት፣ የህይወት ትርጉምና ሞት ናቸው። ሞት ቢያስቡት ቢያስቡት የሚገባ ነገር አይደለም። እንደውም አተኩረው ካዩት እንደ ቀትር ጸሀይ ማጥበርበርና ግራ ማጋባት  ይጀምራል።
በአንድ መንደር የሚኖር ልጅ እናቱ ትሞትና ለብዙ ሳምንታት አምርሮ ያለቅስ ነበር። ቤተሰቦቹና ጎረቤቶቹ ሊያጽናኑት ሞክረው አልሆን ሲላቸው ለሃይማኖት አባት ይናገራሉ። እሳቸውም ልጁን፤ “ሀዘን ማብዛት ደግ አይደለም። ፈጣሪም አይወደውም” ይሉና  ይገስጹታል። ልጁም ተግሳጹን ፈርቶ ማልቀሱን ይተዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የእሳቸው እናት ሞቱና እሳቸው አልቅሰው አልቅሰው አላቆም አሉ። ልጁ ሄዶ፤ “ምነው ሀዘን ማብዛት ደግ አይደለም ብለውኝ አልነበር?” ሲላቸው፤ “የኔ ልዩ ነው” አሉት ይባላል። ስለሞት ሲወራ ብንሰማም በኛ  ከደረሰብን ግን ልዩ ነው። ህዳር አበጋዝን እየመከረችው ነበር። “ለብሌን ንገራት፤ መዋሸት ጥሩ አይደለም” ስትለው ነበር። በራሷ ሲደርስ ግን “ልዩ” ሆነባት።
ሀዘን እና  እርም ማውጣት
ሁሉም ሀዘኖች የተለያዩ ናቸው። ሁለት ሰዎች የፈለገ ቢመሳሰሉ የሚያዝኑበት መንገድ አንድ አይነት አይሆንም። የምናዝንበት መንገድ እንደየመልካችን የተለያየ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሞት ጥናት (Thanatology)  ፈር ቀዳጅ የሆነችው  Elisabeth   Kiibler- Ross የነደፈችው ባለ 5 ደረጃዎች ንድፈ ሀሳብ አለ።
1.  ድንጋጤዎች ሞትን አለመቀበል  (shock and denial)
2. ንዴት (anger)    
3. ድርድር ( Bargaining)
4. መቀበል (Acceptance)
5. መከፋት (Deperasion)
 ይሄ ንድፈ ሃሳብ በቅደም ተከተል የተቀመጠ ይሁን እንጂ ሰዎች በእያዳንዱ ደረጃ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜና ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላኛው የሚሻገሩበት ፍጥነት እንደሁኔታውና እንደግለሰቡ ይለያያል።
እውነታው ከባድ ሲሆን አእምሯችን ራስን መደለያ ስልቶችን  በመጠቀም ከሀዘኑ (ለጊዜውም ቢሆን) ይጋርደናል። የምንወዳቸው ሰዎች መሞታቸውን ስንሰማ እንደነዝዛለን። እውነታውን አንቀበለውም። ለቅሶ ሊደርሱ የሚመጡ ሰዎች እንኳን “አልሰማሁም! አልሰማሁም!” እያሉ ቢሆንም በርግጥ ሰምተዋል። ነገር ግን የሰሙትን ነገር ምን ያህል  መቀበል እንደከበዳቸው እየገለጹ ነው።
የህዳርን ሀዘን ያወሳሰቡ የተወሰኑ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ድንገተኛ ሞት መሆኑ ነው። ጠዋት “በኋላ እንገናኛለን” ብላ በሰላም ተለይታ፣ ከስራ ስትወጣ ድንኳን ተደኩኖ መድረስ ከባድ ነው። ሰው ሲታመም አስታሞ፣ ሲሞት ወግ ነው።
ሰዎች ለሀዘኑም አእምሯቸው ስለሚዘጋጅ፣ ሞት ሲከሰት ለመቀበል ብዙ አይከብዳቸውም። ድንገት የሚከሰት ሞት ግን የገነገነ ሀዘን (Hypertrophied grief) ስለሚፈጥር ለመቀበል ከባድ ነው።
ፊልሙ ሲጀምር አካባቢ ህዳር  አበጋዝን፤ ”እናቴ ለኔ እናት ብቻ አይደለችም፤ ሚስጥረኛዬ፣ ጓኛዬም ናት።” ስትለው ይታያል። እናቷን ሚዜ ለማድረግ በቀልድ መልክም ቢሆን ስትናገር ታይቷል።  ጓደኛዋም እህቷም ነበሩ። ለእሷ ብለው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በየፍርድ ቤቱ  ተከራክረዋል። የቆዳ ፋብሪካውን ክበብ ምግብ እንዳትበላ፣ ሌሊት ተነስተው ምሳ የሚቋጥሩላትን  እናቷን ስታጣ ምነው መቀበል አይከብዳት?
ህዳር “እናቷን ይኸውልሽ አግቢ አግቢ ብለሽኝ ብኋላ ብቻሽን እንድትቆራመጂ” ስትላቸው “ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በተኮነንኩኝ” ሲሏት፣ አእምሮዋ ላይ  መጥፎ ይሆን? የክበብ ምግብ ስትበላ  እናቷ የሚቋጥሩላት ትዝ እያላት አልበላ ብሏት ይሆን? ለእናቷ ቃል የገባችው፤ “የብረት መዝጊያ”  አማች ማምጣት እሳቸው ከሞቱ በኋላ ትርጉም የለሽ ነገር ሆኖባት ይሆን? የባኞ ቤቱን ገንዳ ባለማስተካከሌ፣ እኔ ነኝ እናቴን የገደልኳት ብላ ራሷን  እየወቀሰች ይሆን? ምስኪን ህዳር! እውነታውን መቀበል ቢከብዳት አይገርምም።
ፊልሙ ሊያልቅ ሲል ህዳር የእናቷን ሞት መቀበሏን አይተናል። ሆኖም እስክትወጣ ግን ብዙ የሚቀራት ይመስለኛል። ደስ ሲላት ለእናቷ ለመንገር ስልክ ታወጣ ይሆናል። ሰርግ ለማድረግ ከወሰነች ሰርጓ መሃል የምትተክዝ ይመስለኛል። በአል ሲመጣ  ሆድ ሳይብሳት አይቀርም ሀዘን እረጅም ሂደት ነው።
የለቅሶ ባህላችንና እውነታን መካድ
 ሞት አለማቀፋዊ ይሁን እንጅ የሀዘንና የለቅሶ ስነስርዓቶች በባህል የተቀኙ ናቸው። ምእራባውያን ጥቁር ሱፍና ከረባት አድርገው ጥቂት ሰዎች በተገኙበት ቀብር አስፈጽመው ወደየቤታቸው ይሄዳሉ። እንግሊዞች ጋ “እዬዬ” ብሎ ማልቀስ የለም። ኮምጨጭ ብለው (with stiff upper lip) ንግግር  ያደርጉ ይሆናል እንጂ ድምጽ አውጥቶ ማልቀስ የተለመደ አይደለም። የኛ ሀገር ሰው የእንግሊዞችን ቀብር ቢመለከት “ምን አይነት ልበ ድንጋዮች ናቸው?” ሳይል አይቀርም። በኛ አገር ደግሞ ሀዘን ሲያጋጥም ጎረቤት፣ የእድር ሰዎች፣ የስራ ባልደረቦች፣ * በጣም የሚቀርቡን  ስምንት መቶ ሰዎች ለማስተዛዘን ይመጣሉ።
*  የቀብር ስነስርዓት ላይ ሙሾ  ማውረድ፣ ደረት መምታት፣ አብሬ ካልተቀበርኩ ማለት ሊኖር ይችላል። አንድ እንግሊዛዊ የቀብር ስነ-ስርዓታችንን ቢመለከት፣ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ስተው (mass hysteria)ሊመስለው ይችላል።
ፊልሙ ላይ እንደተቀመጠው የዶርዜዎች የለቅሶ ባህል ደግሞ የሞተውን ሰው በጭፈራ መሸኘት ሊኖር ይችላል።
እድር፣ ጎረቤትና ዘመዶች በለቅሶ ጊዜ  የስሜት  እንዲሁም ተግባራዊ እገዛ ያደርጋሉ። ዋናው ሀዘንተኛ እንግዶችን “እንዴት  ላስተናግድ?” ብሎ አይጨነቅም። ሰጥ ለጥ  አድርገው ያስተናግዳሉ።
በሌላ መልኩ ሀዘን ላይ ያሉ ሰዎች እርም እንዳያወጡ የሚያደርጉ ክስተቶችም አሉ። ሰዎች  ስለሀዘናቸው ማውራት ሲጀምሩ አንዳንድ ሰዎች ስለሚጨንቃቸው “ያው  የፈጣሪ ስራ ነው።” ወይ “ሁላችንም ወደዚያው ነን። ምን ይደረጋል?”  የሚባሉት ጠቅለል ያሉት የማጽናኛ ንግግሮች ሀዘኑን ስለሚደፋፍኑት፣ ሀዘን ውስጥ ያለው ሰው ብቸኝነት እንዲሰማውና ስሜቱን አፍኖ እንዲይዝ ያደርጋል።  
አንዳንድ ጊዜ ሀዘን ውስጥ ያሉ ሰዎች “ግንባር ለማስመታት” መጥቶ  “ሀሙስ አይቻት አልነበር ምን አጋጠማት?” ከሚለው ሰው ሁሉ ጋር እየደጋገሙ መናገሩ ያታክታቸዋል። ከላይ  ከላይ የሆኑ ብዙ ንግግሮችን ከማድረግ የውስጥ ስሜታቸውን ከሚረዷቸው ጥቂት ሰዎች ጋር መወያየት ይመርጡ ይሆናል።
ብዙ ሺህ ህጻናትና ታዳጊዎች ልክ እንደ ብሌን  እናታቸውን እየጠበቁ ነው። አንዳንዶቹ  ሃያዎቹ ውስጥ ደርሰውም አሁንም መጠበቃቸውን ቀጥለዋል። ይህን የሚያደርጉ ወላጆች አንድም ለልጆቻቸው በማሰብ ሲሆን፣ ሁለትም እንዴት እንደሚነግሩ  ግራ ገብቷቸው ነው።
 አእምሯችን አስፈሪና አስጨናቂ ነገሮች ሲያጋጥሙት ከግንዛቤ ውጪ የተለያዩ የመከላከያ ስልቶችን በመጠቀም ጭንቀቱን ለጊዜውም ቢሆን፣ በመጠኑም ቢሆን ለማርገብ ይሞክራል። እነዚህ ነገሮች ከግለሰቡ ግንዛቤ ውጭ የሚካሄዱ ናቸው። በፊልሙ ላይ የተነሳው እውነትን መካድ ገሀዳዊውን ዓለም የምንመለከትበትን መንገድ ስለሚያዛባው እንዲሁም ግለሰቡንም በጣም ስለሚጎዳው ኋላ ቀር ራስን የመደለያ መንገድ ይባላል።
 በህክምና ውስጥ እውነታን መካድ በተለያየ መንገድ ያጋጥመናል። ለምሳሌ አንድን  ሰው እንዴት ነው ብዙ አልኮል ትጠጣለህ ብዬ ብጠይቀው፤  “በየቀኑ ብዙ አልኮል እጠጣለሁ” የሚለው እውነታ የሚያስጨንቅ ስለሆነ፣ ሳያስበው አልፎ አልፎ ከጓደኞቼ ጋር አንድ፣ ሁለት እንላለን። ሊል ይችላል። በተመሳሳይ ሱስ ውስጥ ያለ ሰው፣ ሱስ ስለማቆም ብናወራው “እኔ እኮ ሱስ የለብኝም። ከፈለግሁ ማቆም እችላለሁ።” ሊል ይችላል።
  የስኳር የደም ግፊት ህመምን መቀበል የሚያቅታቸው ሰዎች፤  መድሃኒት ከመጀመር በስፖርት እከላከለዋለሁ” ሲሉ ዜናው ስላስጨነቃቸው አእምሯቸው እውነታውን በመካድ እየደለላቸው ሊሆን ይችላል። ለማጠቃለል ዘጠኝ ሞት  በደንብ ጥናት ተደርጎ የተሰራ ስነ-ልቦናዊ  ፊልም ነው።  ለወደፊትም መታየቱ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለኝም። የስነ-ልቦና ትምህርት ላይ እንደ ማስተማሪያ ሊያገለግል የሚችል፣ የስነ-ልቦና ህክምና ላይ ደግሞ ጠለቅ ያለ ሳይንሳዊ ጥናት እንዲደረግ  የሚጎተጉት ፊልም ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከምንም በላይ ግን ሁላችንም ስለ ህይወትና ስለ መንታ ወንድሙ ሞት  እንድናስብ የሚያደርግ ፊልም ነው።
ስለሞትና ስለሀዘን ሁለት ስነ-ልቦናዊ  መጽሐፍትን እጠቁማለሁ።
 Mourning and Melamcholia by sigmund freud
On Death and Dying by Elisabeth  Kijbler-ross  እንዲሁም የተራዘመ (Prolonged) ወይም የተወሳሰበ (Complicated) ሀዘን ውስጥ  ላላችሁ ደግሞ ሁለት የመጽሐፍ ጥቆማ አለችኝ።
WHO DIES?  By stephen and Dndrea hevine
When bad things happen to good people by harolds. Kushner
ያለ አእምሮ ጤና፣ ጤና የለም!

Read 545 times