Saturday, 30 December 2023 20:30

ህልም ሲተነፍስ…

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል-
Rate this item
(0 votes)

 አንድ እንግዳ የሆነ ታሪክ ልነግራችሁ ነው….
ህልም ብዙ አይነት ገፆች አሉት፡፡ በነፍስና በስጋ መካከል ባለ ብርማ ቀለም ውስጥ ብዙ ገጠመኞችንና በትካዜ ተረግዘው የተወለዱ ሀሳቦችን ይዟል፡፡ እኛ በመካከል ነን…ህልም ውስጥ ስንኖር፡፡ ሆኖም እንጠይቃለን… አሁን ባሉን የስሜት ህዋሶች ከምንለማመደው ህይወት ውጭ የሆነን ህይወት እንዴት አድርጎ አዕምሯችን አስሶ ደረሰበት? እንዴት ሆኖ አማራጭ ህልውና ተሰጠን? ህልማችን ውስጥ ያለው ራሳችንን በምን አይነት ሚስጥር ነው አሁን ካለነው…ቆሞ ከሚያስበው ማንነታችን ጋር አጣምረነው ትርጉም ያለው እውነት ማምጣት የምንችለው? ብዙ ጥያቄዎች በተፈጠሩ ልክ ብዙ መልሶች እየተሳቡ በህሊናችን ውስጥ መማሰናቸው አይቀርም… ሆኖም ይህን ንትርክ ቅርፅ ለማስያዝ ታሪክ እንፈልጋለን …. ልክ እንደህልማችን አወዛግቦን ትርጉምን የሚያስማስነን ታሪክ እንፈልጋለን….
አንድ እንግዳ የሆነ ታሪክ ልነግራችሁ ነው….
ስሙ እያዩ ነው፡፡ እጅግ ሲበዛ ሀብታም ነው፡፡ ከሀብቱ ግን ጎልቶ የሚታየው ፊቱ ላይ ያለው ንቀት ነው…ከነዋዩ ጎልቶ የሚሰማው ስድቡና ዘለፋው ነው፡፡ በአጭሩ መጥፎ ሰው ነው ብል ይቀለኛል፡፡ ባለው ሀብት ተሳክሮ በቅጥሩ ውስጥ ያሉትን ሰራተኞች ሳይሳደብና መንፈሳቸውን ረብሾ ወደ አልጋቸው ሳይሰዳቸው ወደ መኝታው አይሄድም፡፡
የእሱም ሰራተኞች ቢሆኑ አይወዱትም፡፡ ገና ሲጠራቸው ነፍሳቸው በሚረብሽ ንዝረት ትርዳለች፡፡ ሁሌም ሲጠራቸው በዛ ግቢ ውስጥ የመጨረሻ ቀናቸው እንደሆነ አስበው ነው ከፊቱ የሚቀርቡት፡፡ ጠዋት ተነስቶ ቀልቡ ያልወደደውን ተጣርቶ ያባርራል፡፡ የሰው ልጅን የሚያየው ከሚያሳድጋቸው ውሾች አሳንሶ ነው፡፡ እያዩ ማለት ይሄ ነው፡፡ ከራሱ ጋር ተጠፋፍቶ ምስኪን ነፍሶችን እያደነ፣ በቃላቱና ስለትን በሚያስንቁ አይኖቹ በጣጥሶ ይጥላል፡፡ በአጭሩ እሱን የሚወደው ሰው እንደሌለ ሁሉ እሱም የሚወደውና የልቤ የሚለው ሰው የለውም፡፡ ጊዜውን የሚያባክነው ግቢው ውስጥ የሚጠላቸውን ሰዎች ሰብስቦ እነሱኑን በመጥላት ነው፡፡ እያዩ ማለት ይሄ ነው፡፡
አንድ ቀን በተንጣለለው የፎቁ በረንዳ ላይ ሆኖ ቁልቁል መናፈሻውን የሚያፀዱትን ሰራተኞች ሲመለከት ከቆየ በኋላ አንዲት ሴት ላይ አይኖቹ አረፉ፡፡ ልጅቷ እጅግ ከመክሳቷ የተነሳ እየተራመደች ሳይሆን እየተንሳፈፈች የምትሄድ ነው የምትመስለው፡፡ የህይወት ፍርቱና ባለፀግነትን ብቻ ሳይሆን የምድርንም ስበት የነፈገቻት ሴት ነው የምትመስለው፡፡ አጎንብሳ በሀሳብ ጭልጥ ብላለች፡፡ ታሪኳን ለማንበብ አተኩሮ አይኖቿ ላይ አይኖቹን ጣለ፡፡ ምንም ሊያገኝባት አልቻለም፡፡ ባዶ ህይወት፤ ባዶ ሰውነት ውስጥ በባዶ እንቅስቃሴ ሲወዛወዝ ተመለከተ፡፡ ጠላት፡፡ በደንብ አድርጎ ጠላት፡፡ ሁሌ አጠገቡ ለምትቆመው ሎሌው ልጅቷን እንድትጠራለት ነገራት፡፡
ልጅቷ እንደተጠራች አንገቷን አቀርቅራ እየሮጠች ወደ እያዩ ፊት ቀረበች፡፡ አሁንም ምንም ሳይናገር በጥልቀት ሊመለከታት ሞከረ፡፡ ምንም ስሜት የሌለባት በስጋና አጥንት ብቻ የተሰራች…ነፍሷ የተዘረፈ…ስጋዋ የናቃት…ለህይወትም ለሞትም ትርጉም የማትሰጥ ሴት እንደሆነች አመነ፡፡ ጥላቻው ወደ አልገባው ንዴት መራው፡፡ ከቁጥጥር ውጭ ሆነ፡፡
አይኖቹን አፍጥጦ “ማነው እኔ ጋ የቀጠረሽ?”ብሎ ጠየቃት፡፡
አንገቷን እንዳጎነበሰች መለሰችለት፤ “እርስዎ ነዎት  የቀጠሩኝ፡፡” አለች፡፡
“ምን ጎሎኝ…ምን ገዶኝ ነው አንቺን የመሰለች…እንዲሁ ሳይሽ ድካም ነው እየተሰማኝ ያለው…”
ልጅቱ ምንም ሳትናገር እንዳቀረቀረች ዝም ብላለች፡፡
“…በምንም አይነት ስካር ውስጥ ብሆን እንዳንቺ አይነት ሴት ልቀጥር አልችልም፡፡ ወይ ደግሞ ሞቼ እሬሳዬ ነው ሊቀጥርሽ የሚችለው….እሬሳዬም ላይቀጥርሽ ይችላል፡፡ ሳይሽ እኮ የሞትኩ ነው እየመሰለኝ ያለው…..”
ልጅቱ ምንም ሳትናገር እንዳቀረቀረች ዝም ብላለች፡፡
“…አሁኑኑ ከዚህ ግቢ ሰብስበሽ ካመጣሻቸው ኮተቶችሽ ጋር ውጪ! የሰው መልክ እንደዚህ አስፈርቶኝ አያውቅም፡፡ አሁኑኑ ትወገድልኝ!”
ካጠገቡ ያለችው ሴት እያመናጨቀች አስወጣቻት፡፡ ልጅቱ ያላትን ሁለት ልብስ በጥቁር ፌስታል ውስጥ አድርጋ ግቢውን በመልቀቅ ላይ እያለች በእያንዳንዱ ሰራተኛ ላይ የሀዘን መንፈስ ሲሰለጥንባቸው እያዩ ተመለከተ፡፡ ሁሉን በአንድ ላይ ጠላቸው፡፡ ሁሉንም በዚሁ ቅፅበት ቢያባርራቸው በወደደ ነበር፡፡ ሆኖም ዝም ብሎ ትኩረቱን ልጅቱ ላይ ብቻ አደረገ፡፡ ልጅቱ ልትወጣ ስትል ቆም አለች፡፡ እያዩ እየገረመው ተመለከታት፡፡ አንድ ጊዜ ዞራ ተመለከተችው፡፡  ድንገት አንዳች ነገር ሰውነቱን ሲወረው ተሰማው፡፡ እሱ ራሱ ሊያስረዳውና ሊረዳው የማይችለው የማንነቱ ክፍል ሲነቃ ተሰማው፡፡ ሆኖም አሁንም ያ ጥላቻውና ንቀቱ እንዳሉ ናቸው፡፡ አሁን በሚያስበው ሀሳብ ውስጥ የተለየ እያዩ እየተወነ እንዳልሆነ ያውቀዋል፡፡ ሁሉም ነገር ባለበት እንዳለ ነው፡፡ የልጅቷ አይኖች ግን እየቀጠሩት ያሉ መሰለው፡፡ የት እንደሚያውቃት ባያውቅም ለዘመናት አብራው የነበረች ሴት እንደሆነች ሊያምን ሲል እጁ ላይ ይዞት የነበረው የቶስካኖ ሲጃራ ጭስ ባይኑ ውስጥ ገብቶ አባነነው፡፡ አይኖቹን አሽቶ ተመልሶ ወደ ልጅቷ ሲመለከት የለችም፡፡
መሸ፡፡: እያዩም እየዞረ የምስኪን ነፍሳትን እረፍት እረበሸ፡፡ በራሱ እረክቶ ወደ አልጋው ሸሸ፡፡ አልጋው ውስጥ ሆኖ ያባረራትን ልጅ መልክ ለማስታወስ ሞከረ፡፡ እያንዳንዱ ነገሯ ከድብቁ ህሊናው ውስጥ ከተፍ አለበት፡፡ ያቺን የመሰለች…ሞት የሸሻት…ህይወት የተሰወረችባት… ቀናቶቿ በበርባሮስ ጨለማ የተደፈኑባት…ይህችን ሴት እንዴት አድርጎ ግቢው ውስጥ እንዳስገባት አስቦ በንዴት አይኖቹን ጨፈናቸው፡፡  እንቅልፉ ውስጥ ሆኖ ከተኛበት ነቃ፡፡ እያዩ፡፡
ሲነቃ እጅግ ክፉኛ የሆነ የጀርባ ህመም አመመው፡፡ ከዚህ ቀደም የጀርባ ህመም የለበትም፡፡ ድንገት ግን አንድ ሰው ሲጣራ ሰማ፡፡ አይኖቹን ገለጣቸው፡፡ የሚያየውን ማመን አቃተው፡፡ ያለበት ቤት የሱ ቤት አይደለም፡፡ በህልምና በእውነታው አለም መካከል የቱ ጋ እንዳለ ማወቅ አልቻለም፡፡ ዝቅ ብሎ ራሱን ተመለከተው…ሰውነቱ በአደፈ ቀሚስ ውስጥ የተጀቦነ የሴት ገላ ለብሶ አየ፡፡ በድንጋጤ ከፍራሹ ላይ ብድግ ብሎ ተነሳ፡፡ እየሆነ ያለውን ነገር ለመተርጎም የሚበቃ እውቀት ጭንቅላቱ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ተሳነው፡፡ ሴት ሆኖ ነው ህልሙ ውስጥ የነቃው፡፡ ህልሙ ውስጥ፡፡
“ኢቶፒ?” የሚል የአንዲት ሴት ድምፅ ካለበት ደሳሳ ቤት ውስጥ ይሰማዋል፡፡
አካባቢውን አይኖቹን በፍርሀት እያንከባለለ ለመመልከት ሞከረ፡፡ እጅግ የሚያስፈራ ደሳሳ የጭቃ ቤት…ትርጉም የማይሰጡ ጣሪያዎች ከላይ ለምልክት የተሰቀሉበት...መሬቱ ተሰነጣጥቆ እንግዳ ምድር ላይ የበቀለ ቤት አስመስሎታል፡፡ ተኝቶበት የነበረውን ፍራሽ ሲመለከት የሳር ፍራሽ ሆኖ ከፍራሽነቱ ይልቅ ሳሩ ላይ ብጣሽ ጨርቅ የተጣለበት ነው የሚመስለው፡፡ ሁሉም ነገር ለማየት ይከብዳልም ይቀፋልም፡፡ ገሀነም ያለ መሰለው፡፡ ሞቶ ያለምንም የፍርድ ስርዓት ፈጣሪ ነፍሱን በሴት ገላ ውስጥ ተምትሞት ባለበት ደሳሳ ውስጥ የወረወረው መሰለው፡፡ ፍርሀትም…ድንጋጤም…ተስፋ መቁረጥም… በጥልቀት ማዘንም...እና…እና…ብዙ ብዙ አስጨናቂ ስሜቶች በሴታዊ ጭንቅላቱ ውስጥ ገብተው ዕረፍት ነሱት፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እረፍት የነሳው ከውጭ ሆና የምትጣራው ሴት ድምፅ ነው፡፡
“ኢቶፒ?” ሴትየዋ አሁንም ትጣራለች፡፡ እሱን እየጠራችው መሆኑን ያወቀው ለምንምነት ጥቅም የማይሰጠው በሩ ሲንኳኳ ነው፡፡ በፍርሀት በሩ ጋ ተጠግቶ መልስ ለመስጠት ሞከረ፡፡
“እዚህ ነው?” ድምፁ የሴት ነው፡፡ ሆኖም የሚያውቀው የሴት ድምፅ መሰለው፡፡ ነገር ግን የትኛዋ ሴት እንደሆነች ማወቅ አልቻለም፡፡
“ቶሎ ብለሽ ውጭ እንጂ? ያ ያልኩሽ ደላላ በር ላይ እየጠበቀሽ ነው፡፡ ስራ ሳያገኝልሽ አይቀርም፡፡”
ግራ ገባው፡፡ አንድ ጊዜ ራሱን ዳበሰ፡፡ ሁሉም ነገር ህይወት መስሎ ካቆመበት እየቀጠለ ነው፡፡
በሩን ታግሎ ከፈተው፡፡ ለተሸከመው ሰውነት የማይመጥን ክብደት ነበረው…. በሩ፡፡ እንደከፈተው በነጠላ አፏን ሸፍና የቆመች ሴት ጋር አይኖቹ ተገናኙ፡፡ ሴትየዋ አይን ላይ የመፀየፍና የማዘን ስሜት ይታይባታል፡፡ ምን አይነት ሴት ብሆን ነው እንደዚህ የምትፀየፈኝ ብሎ አሰበ፡፡
“መውጫው በር የቱ ጋ  ነው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ ሴትየዋ ግራ ተጋብታ ስትመለከተው ከቆየች በኋላ፤ “ብለሽ ብለሽ በሩ የቱ ጋ ነው ብለሽ ጠየቅሺኝ፡፡ ስንት አመት የኖርሽበትን ግቢ፡፡ ለነገሩ ትላንት እንቅልፍ ሳትተኚ ነው ያደርሺው፡፡”
“ለምን?” ብሎ ጠየቃት፡፡ አሁንም ሴትየዋ በግርምት ነው የምታየው፡፡
“አንቺ ልጅ ምን ሆነሻል ዛሬ? ጭራሽ አራስ ልጅሽን እረስተሻት ነው የነቃሽው፡፡ በይ አሁን ለማንኛውም ቶሎ ብለሽ ደላላውን አናግሪው…ያገኘልሽ ስራ ጥሩ ከሆነ ውዝፍ የቤት ኪራይሽን ትከፊያለሽ…ልጅሽንም ማሳከሚያ ታገኛለሽ፡፡”
ምን ብሎ መመለስም ሆነ መጠየቅ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ያልገባው ሀዘን እንደ አዜብ ንፋስ እየተገፋ መጥቶ እንባዎቹን በአይኖቹ መስታወቶች ላይ ድንቅር አደረጋቸው፡፡ የእንባዎቹ ዘለላዎች ድክም እያላቸው ካይኖቹ ላይ መሰደድ  ጀመሩ፡፡ ምንም መናገር አልተቻለውም፡፡ ሰውነቱን ደክሞታል፡፡ እየሆነ ያለውም ነገር አልገባውም፡፡ በር ጋ  ወዳለው ደላላ ማምራት ጀመረ፡፡
ደላላው ከግቢው ፊትለፊት ያለው ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እየጠበቀው ነበር፡፡ እንዳየው ከተቀመጠበት ተነስቶ ያጣድፈው ጀመር፡፡
“ምን ሆነሽ ነው እንደሞላለት ሰው እስካሁን ሰዓት ድረስ የሚያጋድምሽ? በይ አሁን በፍጥነት ተከተይኝ ያበደ ስራ ነው ያገኘሁልሽ?”
እያዩ/ኢቶፕ ምንም መናገር ስላልቻለ ዝም ብሎ ደላላው ወደሚወስደው ቦታ መከተል ጀመረ፡፡ ሰፈሩ ራሱ ነው፡፡ የራሱ ሰፈር፡፡ ጥሪቱን አሟጦ ርስቱን የገነባበት ሰፈር፡፡ እጅግ የሚከበርበትና የሚፈራበት ሰፈር፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ በሚሄድበት ሰፈር አሁን አቀርቅሮ በመራመድ ላይ ነው፡፡ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አሁንም የገባው አንዳችም ነገር የለም፡፡ በህልምና በእውን አለም መካከል ያለው ልዩነት ላይ የሚፈላሰፍበት ጊዜ አላገኘም፡፡ ደላላው እያጣደፈው ነው፡፡
ደላላው የሆነ ነገር እንዲነግረው ፈልጎ ነበር…እንደው የሆነ እውነት የሚመስል ነገር መስማት ፈልጓል፡፡ ሆኖም ደላላው ማቋረጫ የሌለው የስልክ ወሬ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የሚወስደው መንገድ ሁሉ ወደ እሱ ቤት የሚጠቁም ነው፡፡
የፈራውም አልቀረም፤ ደላላው እያንደረደረ ወስዶ መኖሪያ ቤቱ ጋ አቆመው፡፡ ሁሉም ነገር ባለበት ነው፡፡ ምንም የተቀየረ ነገር የለም፡፡ ሆኖም አንድ ቅር ያለው ነገር እስካሁን ምን አይነት መልክ ያላት ሴት ውስጥ እንዳለ አለማወቁ ነው፡፡ ሰውነቱ እንዲህ ከተጎሳቆለ መልኩ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ያን ያህል የሚያስቸግረው አልመሰለውም፡፡ ሆኖም ከዚህ በኋላ ያለው ጊዜው ግን በጣም ያስፈራዋል፡፡ ምን ሊበላ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተመልሶ እዛ አልጋ ላይ ሊተኛ ነው ወይስ ሌላ አማራጭ አለም ይቀርብለታል፡፡ የሆነ ያበደ አምላክ ህልም ውስጥ ያለ መሰለው፡፡
ደላላው የእያዩን በር መጥሪያ ሲጫን በፍጥነት በሩ ተከፈተለት፡፡
“ተከተይኝ?” ብሎት ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡
የራሱ ሰራተኞች…የራሱ ግቢ…የራሱ ሀብት…የቆመበት መሬትን ጨምሮ የራሱ አለም ላይ ባይተዋር ሆኖ ቆመ፡፡ በግቢው ውስጥ ያሉት ሰራተኞች በሀዘኔታ ስሜት ውስጥ ሆነው ነው የሚያዩት፡፡ እሱም ቢሆን ሲያያቸው በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ይሄን የመሰለ ስሜት ተሰምቶት አያውቅም ነበር፡፡ ሆኖም ይህ የማዘን ስሜት ውስጥ ሲገባ የሆነ የድል አድራጊነት ስሜት ውስጥ ነው የከተተው፡፡ ምንን እና ማንን ድል እንደነሳ ግን አያውቀውም፡፡ እንደ ህልም ያለ ስሜት፡፡ ህልማዊ እውቀተ፡፡ ህልማዊ ሀዘን፡፡ ህልም፡፡  
ደላላው ጥሎት ከሄደበት ቦታ ተመልሶ መጥቶ እንዲከተለው በማድረግ ወደ ገዛ ራሱ ቤት ይዞት ዘለቀ፡፡ የራሱን ደረጃዎች ተራምዶ የራሱ ፎቅ ላይ ካለው በረንዳ ላይ ራሱን አገኘው፡፡
“አለቃሽ ሲመጣ አክብሮት አሳዪው? ዝም ብላ የምትዝለፈለፍ ሴት አይወድም፡፡” አላት ደላላው የደላላ ነፍሱን እያሟሟቀ፡፡ እያዩን/ኢቶፕን በዚህ ሰዓት እያስጨነቀው ያለው ነገር በገዛ ቤቴ የሚቀጥረኝ ማነው ብሎ ነው፡፡ ብዙም አልቆየም፤ የገዛ ቤቱ ባለቤት የገዛ ራሱ ሆኖለት መጣ፡፡ ራሱን ተመለከተው፡፡ በሀይል ደነገጠ፡፡ መቆምም ያቃተው መሰለው፡፡ እያየው ያለው ሰው እራሱን ነው፡፡ እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ ራሱን ለመጠየቅ ጊዜ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
“ምነው ደምሴ ደላላው” አለ እያዩ በንዴት ደላላውን እያየው፡፡
“ምን አጠፋሁ ጋሼ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ቀና ብሎ ለመመልከት እንኳን አልደፈረም፡፡
“ምኗን ይዘህብኝ ነው የመጣኸው?” በንቀት ወደ ኢቶፕ/እያዩ/ራሱ/ ተመለከተ፡፡
የገዛ ራሱ ላይ ያየውን ንቀት ሲመለከት ኢቶፕ/እያዩ ንዴቱ ከአቅሙ በላይ ሆነበት፡፡ ማንም እንዲህ አድርጎ አይቶትም አናግሮትም አያውቅም፡፡ ሆኖም ከዚህ ቀደም ባለው ማንነቱ እንዳለው ያለ ንዴት አይደለም የተናደደው፡፡ እንደ ኢቶፕ ሆኖ ነው የተናደደው፡፡ ምንም የማያናግረው ንዴት… በትዝብት ብቻ የሚያሳየው ንዴት…እራስን እንደመውቀስ ያለው ንዴት፡፡
“በል እሺ አሁን ሰራተኛ እስኪገኝ ድረስ እዛ የሚታይህን መናፈሻ ታፅዳልኝ፡፡ አለበለዚያ ዛሬንም የማሳድራት አልመሰለኝም፡፡….“
ድንገት ትዝ አለው …ኢቶፕ/እያዩ….ድንገት ትዝ አለው ልጅ እንዳለው…ድንገት ትዝ አለው ያልከፈለው ውዝፍ የቤት ኪራይ እዳ እንዳለበት፡፡ ልጁን ምን ሊያደርገው ነው፡፡ ሲጀመር ልጁ ወንድ ይሁን ሴት የሚያውቀው ነገር የለም፡፡   የነቃበት አለም ህልም አይመስልም…ሁሉም ነገር እውነት ነው፡፡ ታዲያ አሁን እያየው ያለው የራሱ ሰውነት…እየቀጠረው ያለው…እየናቀው ያለው…እያዩ ማነው? እኔ እያዩን ከሆንኩ ከፊቴ የማየው ሰው ማነው? ብሎ ለራሱ ጠየቀ፡፡ ጭንቅላቱ ትውስታ የለውም፡፡ የገዛ ግቢው ውስጥ በገዛ ራሱ ኢቶፕን ሆኖ ተቀጠረ፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ
ለሁለት ወራት ያህል የመናፈሻው አትክልተኛ ሆኖ ሰራ፡፡ በነዛ ሁለት ወራት ሲሰራ በነበረበት ወቅት ከማንም ጋር ተነጋግሮ አያውቅም… ሆኖም በሁሉም ሰራተኞች ላይ ያለውን መንገላላት አላየሁም ብሎ ማለፍ አይችልም…የሚያድረውም ከመናፈሻው ውስጥ ከተሰራች ትንሽዬ ቤቱ ውስጥ ነው…የወር ደሞዙንም አከራዩ ታማለች ላለችው ልጁ በመላክ አንድም ነገር ለራሱ ሳያስቀምጥ ነው፣ እንዲሁ ልፋት ላይ ያለው፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ ግን መኖር የሚባለው ነገር በሙላ አስጠላው፡፡ የሚስበው አየር ካፍንጫው ውስጥ ሰርጎ ሲገባ ይኮሰኩሰው ጀመር፡፡ አለቃዬ እያለ እየጠራው ያለው ራሱ (እያዩ) ደግሞ ኑሮውን ሲኦል አድርጎበታል፡፡ በትክክል ማሰብ እያቃተው ነው፡፡ ድህነት ውስጥ ያለውን መራራ ጣዕም በገዛ ማንነቱ ሳያወላዳ ለሁለት ወራት ያህል ጥጥት አድርጎታል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ከጭንቀቶች ሁሉ በላይ ጭንቀት የሆነበት ሁለቱንም ወራት እንቅልፍ አለመተኛቱ ነው፡፡ ሳይደክመው ቀርቶ አይደለም፡፡ ሆኖም እንቅልፍ የለም፡፡ አሁን ካለበት የእውነታ አለም ለደቂቃም ቢሆን አርፎ አያውቅም፡፡ ያልወለዳትን ልጁን እያስታወሰ አምሽቶ ፍራሹ ላይ ጋደም እንዳለ በባዶ ትዝታ ውስጥ ሆኖ ያለቅሳል፡፡  ሁለት ወራቱን በሙሉ መልኩን አይቶት አያውቅም፡፡ እንደ እስር ቤት ነፃነቱ ተነፍጎ ከፅድ ዛፍና ከአበቦች ውጭ ምንም የሚያየው ነገር የለውም፡፡ ትውስታው ውስጥ ዛፎችና ሰቀቀን ብቻ ነው ያሉት፡፡
ከሦስት ወራት በኋላ
ከሦስት ወራት በኋላ አስደንጋጭ ዜና ደረሰው፡፡ ልጅህ ጣር ላይ ናት ተባለ፡፡ ከቅርብ ሆኖ የማያውቃትን ልጁን ለመንከባከብ ፍቃድ ቢጠይቅም የገዛ ማንነቱ፤ አለቃው እያዩ እንደማይፈቅድለት ነገረው፡፡ ራሱን ጠላው፡፡ በኢቶፕ ገላ ውስጥ ሆኖ የራሱን የእያዩን ማንነት አምርሮ ረገመው፡፡ እዚህ ድረስ ጨካኝ እንደነበረ…እዚህ ድረስ አረመኔነትን ለመሰልጠን ደሀዎችን ሰብስቦ የሚያሰቃይ አረመኔ መሆኑን…ነገንና አሁንን አዋህዶ ማሰብ የማይችል የገንዘብ እንጂ የመልካም ህሊና ባለቤት እንዳልሆነ በዚያን ቅጽበት ውስጥ ተረዳ፡፡ ሁሉንም ነገር ተረዳ፡፡ ለአመታት በሰው ልጆች ላይ ሲከምር የነበረው መከራ በአምስት ወራት  ውስጥ ኖሮት ተመለከተ፡፡ የነፍሱን ፀጥታ ተመኘ…ተንደርድሮ ሄዶ ራሱን፣ የገዛ ማንነቱን ለመግደል ተመኘ…በግቢው ውስጥ ያሉትን ሰራተኞች በሙሉ  ይቅርታ ለመጠየቅ  ተመኘ፡፡ ሆኖም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በኢቶፕ ገላ ውስጥ ሆኖ ማድረግ አይችልም፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ፈልጎ አለማግኘትን በደንብ አድርጎ ተረዳት፡፡
ከእለታት በአንዱ ቀን  በመናፈሻው ውስጥ ተቀምጦ ተክዞ ባለበት፣ የእያዩ ሰራተኛ መጥታ እያመናጨቀች ጠራችው፡፡
“ጋሼ አንዴ ሊያናግሩሽ ይፈልጋሉ?”
እየተንቀጠቀ ወደ ራሱ/ወደ አለቃው ሄደ፡፡ አለቃው በንዴት እያየው ተናገረው….
“ማነው እኔ ጋ  የቀጠረሽ?”
“እርሶ ነዎት…” አለ አንገቱን አቀርቅሮ፡፡
“ምን ጎሎኝ…ምን ገዶኝ ነው አንቺን የመሰለች…እንዲሁ ሳይሽ ድካም ነው የሚሰማኝ…አሁን አሁን ሳይሽ….”
ኢቶፕ/እያዩ ምንም ሳይናገር አንገቱን እንዳቀረቀረ ዝም አለ፡፡
“በምንም አይነት ስካር ውስጥ ብሆን እንዳንቺ አይነት ሴት ልቀጥር አልችልም፡፡ ወይ ደግሞ ሞቼ እሬሳዬ ነው ሊቀጥርሽ የሚችለው...እሬሳዬም ላይቀጥርሽ ይችላል፡፡ ሳይሽ እኮ የሞትኩ ነው እየመሰለኝ ያለው፡፡”
ኢቶፕ/እያዩ ምንም ሳይናገር አንገቱን እንዳቀረቀረ ዝም አለ፡፡
“አሁኑኑ ከዚህ ግቢ ሰብስበሽ ካመጣሻቸው ኮተቶችሽ ጋር  ውጪ፡፡ የሰው መልክ እንደዚህ አስፈርቶኝ አያውቅም፡፡ አሁኑኑ ትወገድልኝ?”
ከቤቱ …ከገዛ ቤቱ ኢቶፕን ሆኖ ተባረረ፡፡ ሆኖም ሊወጣ ሲል የገዛ ማንነቱ የተናገራቸውን ንግግሮች አስታውሶ በንዴት ሊናገረው ፈልጎ እበሩ ጋ ቆመ፡፡ አንድ ጊዜ ዞሮ የገዛ መልኩን ከህንፃው በረንዳ ላይ ተመለከተው፡፡ ፊቱ ላይ ያየውን ጭካኔ እንዳይረሳው አድርጎ በደንብ አስተዋለው፡፡
…..ተመልሶ እዛው ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ገባ…ወራትን አሳለፈ…ያለ ምግብ…ያለ እንቅልፍ…ያለ ሰላም፡፡ በስተመጨረሻም ሰውነቱ መድከም ጀመረ፡፡ እስካሁንም እንዴት አድርጎ በህይወት እንደቆየ ማመን አቅቶታል፡፡ ሞትን እንዲህ ተመኝቶት አያውቅም፡፡ በዚህ ሰዓት እንዲያቅፈው የሚፈልገው የሰው ልጅ የለም…የሞት መልዓክን ክንፍ ብቻ ነው የሚጠብቀው፡፡
…..በአንዱ ቀን በድካም የተከደነውን አይኑን ሲገልጥ ፊትለፊቱ ብዛት ያላቸው አሮጊቶች ከበውት ተመለከተ…
“ዛሬንስ የምታድር አይመስለኝም…የኔ እናት አንድ ቀን እሷም ልጇም ተመችቷቸው ሳይኖሩ ሊነጠቁ ነው…አይ ፈጣሪዬ እኔንስ ምን ታደርገኝ ይሆን…” እነዚህንና ብዙ የእሱን ሞት የሚናገሩ ወሬዎችን አሮጊቶቹ ከበውት በማውራት ላይ ናቸው፡፡
ቀና ብሎ ሊያዋራቸው ፈልጎ ሰውነቱ መታዘዝ እንደማይችል ተረዳ፡፡ የእውነትም የሞት መንፈስ ዙሪያውን ሲዞረው ይታወቀው ጀመር፡፡ ያልወለዳት…አሁንም ድረስ ያላያት ልጁ ልክ ጆሮው ስር ያለች ይመስል የለቅሶ ድምፁዋ ይሰማዋል፡፡  ሆኖም ከሁሉም በፊት አንድ ነገር አድርጎ መሞት አለበት፡፡ እንደምንም ታግሎ ጥያቄውን ለአሮጊቶቹ ለማቅረብ ፈለገ፡፡
“መስታወት አንጡልኝ…?”
አሮጊቶቹ ግራ ተጋብተው ከቆዩ በኋላ የቤቷ ባለቤት ከራሷ ቤት መስታወት ይዛለት መጣች፡፡
“በዚህ ሰዓት መስታወት ማየትሽ ምን የሚሉት ነው የኔ ልጅ?” አለች አንዲት አሮጊት፡፡ ሆኖም እያዩ መስታወቱን በትግል በእጁ ይዞት ፊቱ ላይ አስጠጋው፡፡ መልኩን ሲመለከት የሚያየውን ማመን አቃተው፡፡
ወደ እንቅልፉ ከመሄዱ በፊት …የዚያን ቀን ያባረራት ሴት መልክ ነው ያለው፡፡ ሲኖር እና ሲታመም የነበረው ህይወት የራሱን ሰራተኛ ህይወት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር መጨለም ጀመረ፡፡ ሁሉም ነገር፡፡ በጥቂቱ የሚሰማው ነገር ቢኖር የአሮጊቶቹ ዋይታ ብቻ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ጨለመ፡፡
እያዩ በስተመጨረሻ አይኖቹን ሲገልጥ እራሱን መኖሪያ ቤቱ ውስጥ አገኘው፡፡ ኢቶፕ ስትሞት እሱ ካንቀላፋበት ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ነቃ፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉም ነገር ትዝ አለው፡፡ ከአልጋው ላይ ተስፈንጥሮ ተነስቶ እየሮጠ ከግቢው ወጣ፡፡ በህልሙ ውስጥ ያየውን በሙሉ  ስለሚያስታውስ እየተጋጋጠ የኢቶፕ ቤት ጋ ደረሰ፡፡
በሩ ጋር ሲደርስ ያየው ነገር አስደነገጠው፡፡ ከኢቶፕ ግቢ ውስጥ አሮጊቶች የኢቶፕን አስክሬን ይዘው እያለቀሱ በመውጣት ላይ ናቸው፡፡ ምን ያህል ዘመን እንቅልፍ ውስጥ ሆኖ እንደነበር ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ማየትም መስማትም ያቆመ መሰለው፡፡ ነገር ግን የአሮጊትዋ ድምፅ እንደ ድንገት ተሰማው፡፡
“ልጅሽን ለኔ ጥለሽልኝ ሄድሽ የኔ ልጅ… ምን ላድርጋት…ኢቶፕዬ ልጅሽን ምን አባቴ ላድርጋት?”
እያዩ ለአመታት መፈጠራቸውን እንኳን የማያውቃቸው የእንባ ዘለላዎች በጉንጮቹ ላይ ፈሰሱበት፡፡ ማዘን ሲጀምር እርግጠኛ መሆን ያልቻለበት ድል አድራጊነት በውስጡ ተመላለሰበት፡፡ ማዘን መቻሉን ማመን አቃተው፡፡ አለቀሰ…አምርሮ አለቀሰ፡፡
የኢቶፕን ልጅ እንደሚያሳድጋት ያውቃል…የልጅቷንም ስም ኢቶፕ ብሎ እንደሚሰይማት ያውቃል… ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲመለስ ለእያንዳንዱ ሰራተኛ ይቅርታን እንደሚጠይቅ ያውቃል፡፡ እስከዛሬ ሲያወድም የከረመውን ነፍሳት ሰብስቦ ህይወት እንደሚሰጣቸው ያውቃል፡፡  ከሁሉም በላይ ግን ማዘን ቻለ... የሰው ድምፅ ሰምቶ ማሰላሰል ቻለበት… ይሄም ስሜት ድል አድራጊነቱን አበሰረው፡፡ በህልሙ ሰማይ ውስጥ ኢቶፕን ሆኖ ሞቶ በምድር ላይ ሰው የሆነውን እያዩን ፈጠረ….


Read 369 times