Saturday, 30 December 2023 20:46

ንብ ባንክ በሃዋሳ በ500 ሚ.ብር ያስገነባውን ህንፃ አስመረቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በሃዋሳ ፒያሳ በ500 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ባለ 12 እና ባለ 15 ወለል መንትያ ህንፃ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙት አስመርቋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አዲሱን ህንፃ ከጎበኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “ንብ ባንክ በሲዳማ ክልልም ሆነ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ለሚያቅዱ ሌሎች አካላት ምሳሌ የሚሆን  ተግባር እያከናወነ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ህንፃው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወለል የተለያዩ ሱቆች፣ ከአራት እስከ ስምንተኛ ወለል የሚከራዩ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን፤ ዘጠነኛ ወለል ላይ የባንኩ ሃዋሳ ዲስትሪክት ፅ/ቤትና ከአንድ መቶ ሰዎች በላይ ሊያስተናግድ የሚችል አዳራሽ ይዟል፡፡ በተጨማሪም በአስረኛ ወለሉ ላይ የማረፊያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ አስራ አንደኛው ወለሉ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ሬስቶራንት እንደያዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡
 የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገነነ ሩጋ በምረቃው ሥነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ንብ ባንክ፣ በባንክ አገልግሎቱ በበርካቶች ዘንድ ተደራሽ ከመሆኑ በተጨማሪ በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች ህንፃዎችን አስገንብቶ ሥራ ላይ በማዋሉ ከራሱ ባሻገር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም ለብዙዎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ባንካችን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይም ይህን ጥረቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
ባንኩ ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በወልቂጤ፣ በዱከምና በሆሳእና የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃዎችን ማስገንባቱ ይታወቃል፡፡

Read 447 times