Saturday, 06 January 2024 21:12

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ለምን ውዝግ አስነሳ?

Written by  -ሪፖርታዥ-
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች፣ ኢትዮጵያን ለ50 ዓመታት የባህር ጠረፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረማቸውን ተከትሎ፣ በቀጠናው አዲስ የጂኦ ፖለቲካ ውዝግብ መፈጠሩ እየተነገረ ነው።
እስካሁን ድረስ በሱማሌላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል በህግ የሚፀና ስምምነት ባይካሄድም እንኳንም  በቀጠናው ውዝግብ ማስከተሉ አልቀረም ። በሁለቱም መንግሥስታት መካከል የተፈረመው ለመግባቢያ ሰነድ የሚሆን መደራደርያ መነሻ ነጥብ  ሲሆን፣ ስምምነቱ በታቀደው መሰረት ከተጠናቀቀ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ ቀንድ አዲስ የታሪክ እጥፋት እንደሚሆን  የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ።
በእርስ በርስ ግጭትና በበረታ የኢኮኖሚ ቀውስ እየታመሰች ያለችው ኢትዮጵያ ፤ ከፊቷ የሚጠብቃትን ተግዳሮት ለመወጣት ያለችበትን ቁመና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ አስተያየት ሰጪዎችም አልጠፉም -ከውስጥም ከውጭም፡፡  የመግባቢያ ስምምነቱ፤ 20ኪሜ በ90 ኪሜ  የሚሆን የባህር ሀይል ሰፈርና የበርበራ ወደብን ለመጠቀም የ50 ዓመታት የሊዝ ኪራይ ስምምነት መሆኑ ታውቋል። ከሰሞኑም በሶማሊላንድ ሀርጌሳ የመግባቢያ ሰነዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና በሙሴ ባሂ አብዲ መፈረሙ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ፣ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍና  የደስታ መግለጫ ትዕይንት ተደርጓልም።


በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መስማማቷን የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ለሰላሳ አመታት ከሶማሊያ ተነጥላ ለቆየችው ሶማሊላንድ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ተወስዷል። ሶማሊያ፤ ስምምነቱን “የተቀባይነት የሌለውና ሉዐላዊነቴን የሚዳፈር ነው፤ ለዚህም አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ አልልም” ብትልም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል፣ “የመግባቢያ ሰምምነቱ ማንንም የማይጎዳና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ”  መሆኑን እየተነገረ ይገኛል።
 የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ፤ “አዲሱ ስምምነት አልሸባብ እንዲያንሰራራ በር ይከፍታል” ሲሉም ሰሞኑን  ለፓርላማቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ፤ የግብፅና  የኳታር አቻቸው ዘንድ ስልክ   ደውለው  የአጋርነት  ድጋፍ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል ተብሏል።  ሀሰን ሼክ መሐመድ፤ የአፍሪካ ህብረት፣  የፀጥታው ምክር ቤትና የአረብ ሊግ እንዲሁም ኢጋድ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉም መጠየቃቸውን የሱማሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።


በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመውን የመግባብያ ስምምነት  ተከትሎም፣  ዓለማቀፍ ተቋማትና አገራት የየራሳቸውን አቋም እየገለፁ ነው።
በቀጠናው እያንዣበበ ያለውን ጂኦ ፖለቲካዊ ውጥረት አስመልክቶ አዲስ አድማስ ጋዜጣ  የዘርፉ ምሁራንን አነጋግራለች። በዲላ ዩኒቨርስቲ የታሪክና አለማቀፍ ግንኙነት መምህር  ዶ/ር  አብዱ መሐመድ አሊ፤ በኢትዮጵያና በሱማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባብያ ሰነድ አሉታዊም አዎንታዊም መልኮች ያለው መሆኑን በመግለፅ፤ ከህግ አንፃር የአፍረካ ህብረት የማይቀበለው በመሆኑ በአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ  ለምታደርጋቸው ግንኝነቶች አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው እንደሚችል ያስረዳሉ። በተለይም ኢትዮጵያ  ከፈረመችው የቬይና  ስምምነት አንፃር “የሚፃረር” ነገር እንዳለው ይገልፃሉ ። የቬይና ስምምነት አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ የሚችሉት ከአቻ አገራት ጋር መሆን እንዳለበት የሚገልጽ  አንቀፅ ሰፍሮ ይገኛል ።ዶክተር አብዱ መሐመድ አክለውም፤ አገራቱ ቆየት ላለው መልካም ጉርብትናቸው ሲባልም አሁን ላይ ተፈጥሯል የሚባለውን አለመግባባት በውይይት የሚፈቱበት ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እየተሰጡ ያሉ ማብራርያዎችን የሱማሊያ መንግሥት በዝግታ እንዲያጤነው ማድረግን ጨምሮ አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ሥራዎች መስራት ከኢትዮጵያ  መንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው ባይ ናቸው ።


 ግንኙነቱና ስምምነቱ እንዲሳካም በውጭ ግንኙነት ስራ ላይ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው የዲፕሎማት ልኡካን በየአገራቱ በማሰማራት ዲፕሎማሲያዊ  ስራዎችን እንዲሰሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን  ያብራራሉ። አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የኢትዮጵያ የዲፕሎማቶች ቅርፅና አቅም ግን በእጅጉ የፖለቲካ መዳፍ ያረፈበት በመሆኑ በስኬታማነቱ ዙርያ ጥርጣሬ አላቸው።
የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታው ከበደ ደሲሳ በበኩላቸው፤ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራት ከሱማሊላንድ ጋር ከዚህ ቀደም ሲፈራረሙ አለም ምንም ያላለ፣ ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ግን ይህ ሁሉ ጫጫታ መሰማቱ እንዳስገረማቸው ገልፀዋል ። ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘቷ ጉዳይ በመንግሥት በኩል የረጅም ጊዜ ውጥን መሆኑን ያብራራሉ ። ሚኒስትር ደኤታው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር የባለቤትነት ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ “መደመር” በተሰኘው መፅሐፋቸው በሰፊው እንደተቀመጠ አስረድተዋል። ሆኖም ፣የሱማሊላንድ   ህጋዊነትን  በተመለከተ በርከት ያሉ ጥያቄዎች እንደሚነሱበት  ባለሞያዎች ይናገራሉ።
በሶማሊላንድ ሀርጌሳ የመግባቢያ ሰነዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ሙሴ ባሂ አብዲ መፈረሙ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍና የአደባባይ የደስታ መግለጫ እየተደረገ ነው። በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መስማማቷን፣ የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ለሰላሳ አመታት ከሶማሊያ ተነጥላ ለቆየችው ሶማሊላንድ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ተወስዷል።
ሌላኛው አዲስ አድማስ ያነጋገቻረቸው የፖለቲካ ሳይንስ ሙሁሩ በፍቃዱ ዳባ እንደሚሉት፣ አሜሪካና ቻይና በሶማሊላንድ ጉዳይ የተለያየ አቋም ያላቸው በመሆኑ፣ይህ  ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት አጋዥም ፈታኝም ነው። የአፍሪቃ ህብረት በተደጋጋሚ የተጠየቀውን የሶማሊላንድ የዕውቅና ጥያቄ ያልተቀበለ በመሆኑም የኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ  ዕውቅና መስጠት በአፍሪቃ አህጉር አዲስ መስመር ሆኖ ይመዘገባል ባይ ናቸው ።
ስምምነቱ በታቀደው መሰረት ከተጠናቀቀ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ ቀንድ አዲስ የፓለቲካና የታሪክ መስመር እንደሚሆን ባለሞያው ያስረዳሉ።


በሀገር ውስጥ በእርስ በርስ ግጭትና በበረታ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ከፊቷ የሚጠብቃት ተግዳሮት ቀላል የሚባል አለመሆኑን ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
በተለይም በቻይናና በአሜሪካ በኩል ሊኖር የሚችለውን ውጥረት አሁን ላይ አለማቀፍ የፓለቲካ የቅርፅ ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ ማንዣበቡ አይቀሬ ነው ብለውናል። አሜሪካ  ከወራት በፊት ከሶማሊላንድ ጋር የተናጠል ወታደራዊና የፀጥታ ትብብር ማድረግ የሚያስችላትን ህግ በኮንግረስ በኩል ማፅደቋ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም አሁን ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ላደረገችው ስምምነት አጋዥ መከራከሪያ ሊሆን የሚችል ነው። በሌላ በኩል ቻይና በተደጋጋሚ ከታይዋን በኩል እየተነሳባት ካለው ነፃ አገር የመሆን ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና ሱማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባብያ ስምምነት ላትቀበለው ትችላለች የሚል አስተያየት አላቸው። በአንድ ወቅት ታይዋን ከሱማንድ ጋር ጀምራው የነበረውና ያልሰመረ
የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ቻይናን ክፉኛ አስቆጥቷት እንደነበርም አስታውሰዋል ።


በሌላ በኩል ሱማሊላንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲኖራት የሚፈቅድ ስምምነት መሆኑን እየተገለፀ ይገኛል። ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ያስነሳው የሶማሌያ ሉአላዊነት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ወደብ ማግኘት በራሱ በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም፣ ነገር ግን አየር መንገዱ  ያለበትን ገበያ ባማከለ መልኩ  መሆን እንዳለበት ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ሳይንስና የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች እየተናገሩ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም፣ አየር መንገዱን የከረረ ጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ ያለበት ጉዳይ ውስጥ መጣድ ለጥቃት  ሊያጋልጠው ይችላል የሚሉ መላምቶች እየተደመጡ ነው።  
በኢትዮጵያ እና በሱማሌላንድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ማንን ይበልጥ በዘላቂነት ሊጠቅም እንደሚችል ለማወቅ የስምምነቱን ዝርዝር (ምን የመስጠት እና ምን የመቀበል) ጭብጥ በደንብ ማወቅ እንደሚጠይቅ የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው አቶ ዋሲሁን በላይ፤ በመርህ ደረጃ ግን ሁለቱም እጅግ በሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ላይ እንደተገጣጠሙ ይሰማኛል ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ስምምነት በወደፊቱ በ2070ዎቹ ሳይቀር ሁለቱ ሀገራት ሊኖራቸው የሚችለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሳይቀር የሚወስን ነው እየተባለ ይገኛል።
ዋሲሁይ አያይዘው አስተያየታቸውን ሲገለፁ፣ ለሱማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ከኢትዮጵያ ሀ ብሎ መጀመር እና በኢትዮጵያ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኢኮኖሚያዊ አቅም ከፈጠሩ የልማት ድርጅቶች ድርሻ ማግኘትን ከጨመረ ቀላል ጥቅም እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵያ በተመሳሳይ ለመጪው ጊዜ የጦር መንደር ከማግኘት እስከ ነጠላ ክንፍ የወደብ ጥገኝነት (ጅቡቲ) ላይ ለተንጠለጠለው ኢኮኖሚ ሰፊ አማራጭ ማግኘቱ  ቀላል ፋይዳ አይኖረውም ባይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የድርሻ ተጋገሪነት ለኤርትራ መንግሥት ቀርቦለት እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ባለፉት ወራት ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን መግለጿን ተከትሎ፣ ኤርትራን ልትወር ትችላለች በሚል መላ ምት በውጥረት የሰነበቱት ኤርትራውያን እፎይታ እንደተሰማቸው በማህበረዊ መገናኛ ገፆች ሲገልፁ  ተስተውሏል።
በዚህ በሶማሊላንድና ኢትዮጵያ ስምምነት ዙሪያ አስቀድሞ መረጃው የተነገራቸው ጥቂት ሀገራት መኖራቸውን እየተነገረ ነው። ምናልባትም የተባበሩት አረብ ዔምሬትስ ለሶማሊላንድ ዕውቅና በመስጠት ኢትዮጵያን ልትቀላቀል እንደምትችል ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የሱማሊላንድ ሪፐብሊክ የነፃ አገርነት እውቅና የሰጠች የመጀመርያ አገር ሆና ትመዘገባለችም ተብሏል ። በጉዳዩ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በበኩላቸው ሁለቱም አገራት ጉርብትናቸውን አክብረው ችግሮቻቸውን  በንግግር እንዲፈቱ በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።



Read 2154 times