Saturday, 06 January 2024 21:15

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፣ ባሕር ያስፈልጋታል ግን ትልቁን ቁምነገር ካልዘነጋን ነው

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 የባሕር በር የማግኘት ጅምር፣ የኢትዮጵያ ታሪክን የሚያድስ ጥሩ መነሻ እርምጃ ሊሆን ይችላል። በትዕግሥትና በጥበብ ከተጓዝንበት፣ አገራችንን ከትርጉም የለሽ አጥፊ ግጭቶችና ጦርነቶች አላቅቀን፣ የሰላም ምድር ብቻ ሳትሆን ሕግናና ሥርዓትን እየገነባች የምትገሠግሥ፣ ሥራ ወዳድነትና ትጋት፣ የሥራ ፍሬና የንብረት ባለቤትነት የተከበረባት፣ እያደገችና እየበለጸገች የምጓዝ ዜጎቿ የሚተማመኑባት አገር እንድትሆን ከዕውቀት ከልብ ከጣርን… የሚያስቆማት ኃይል አይኖርም።
ከሩቅም ከቅርብም፣ ከጎረቤትም ከባሕር ማዶም፣ ወዳጅና ተባባሪ ይበረክትላታል። ደግሞስ ለምን አይበረክትላትም? የሌሎችን በማጉደል አይደለም የሚሞላላት። የአንድ አገር ስኬት ለሌሎችም ይተርፋል። ስኬታማ አገር ጎረቤት መሆን፣ በምኞት የማይገኝ ዕድል ነው። የድኻ አገር ጎረቤት መሆን ነው አለመታደል።
የኢትዮጵያ ታሪክን የሚያድስ አንድ ጉልህ ሥራ በተግባር አይተናል። የአባይ ውኃ ላይ የሕዳሴ ግድብ ከሕልም ተነሥቶ እውን ለመሆን በቅቷል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሕዳሴ ግድብ ጋር ስማቸው ሲነሣ፣ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ደግሞ፣ ከባሕር በር ታሪክ ጋር ስማቸው ይነሣ ይሆናል - የዛሬው ጅምር በጥበብና በትጋት በዓመታት ጥረት የባሕር በር ባለቤትነት እንዲጸና እንዲሰፋ።
ታዲያ፣ በአባይ ውኃና በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በተለይ በግብፅ መንግሥት መሪነት ከፍተኛ ዓለማቀፍ ጫናና ዛቻ እንደተፈጠረው ሁሉ፣ በባሕር በር ጉዳይ ዙሪያም ዓለማቀፍ ወከባዎች መምጣታቸው አይቀርም። የግብፅ መንግሥት አላስፈላጊ የባላንጣነት ስሜትና ዛቻ፣ አንዳንዴ ወደለየለት ግጭትና ጦርነት ያዘነበለበት መጥፎ ጊዜዎችና አጋጣሚዎች እንደተከሰቱም ማስታወስ ይቻላል።
ደግነቱ፣ የሕዳሴ ግድብ የተገነባው የአስዋን ግድብን በመሰወር አይደለም። የሕዳሴ ግድብ ውኃ የሞላው የአስዋን ግድብን በማጉደል አይደለም። ወደፊትም፣ ለሱዳንና ለግብፅ ተጨማሪ ጥቅም ያስገኝላቸው እንደሆነ እንጂ፣ ከቁጥር የሚገባ ጉዳት አያመጣባቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ በአመዛኙ የታየው መንፈስ ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም።
አዎ፣ ኢትዮጵያ የእልህና የባላንጣነት አሉታዊ ስሜት አልነበረም አይባልም። ነበረ። ግን፣ ሕዳሴን ለመገንባት እንጂ የጎረቤቶችን የመመኘት ወይም የመመቅኘት የቅናት ስሜት ብዙም ቦታ አላገኘም - አገራችን ውስጥ። በእርግጥም፣ አወንታዊ መንፈስ፣ አላስፈላጊ ጥላቻችንና የጦርነት አደጋዎችን ለመከላከል ረድቷል ማለት ይቻላል። ይደተቀናቃ ውነት
የባሕር በር ጉዳይም በዚሁ ቅኝት መታየት አለበት። የጎረቤቶችን የባሕር በር የመመኘት፣ የመውሰድ ወይም የመመቅኘት ስሜት ሳይሆን፣ ተጨማሪ የባሕር በር የመክፈት ጉዳይ የኢትዮጵያ የዘመናችን ታሪካዊ ቅኝት ሊሆን ይገባል። በሌላ አነጋገር፣ ትልቁን ቁምነገር መዘንጋት የለብንም። የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት፣ በእልህ መንፈስ ወይም የጎረቤቶችን በመመኘት ስሜት አይደለም።  የሕልውናና የሰላም ጉዳይም ነው። በተለይ ደግሞ፣ የኢኮኖሚና የኑሮ ጉዳይ ነው። ለምን?
የባሕር በር፣ መተላለፊያ መንቀሳቀሻ ነው።
ከአላስፈላጊ ወጪዎችና ከውጣውረዶች የሚገላግል፣ አስተማማኝና ፈጣን የጉዞ መስመር ከሌለ፣ መንቀሳቀስ ካልተቻለ… የአገር ኢኮኖሚ አያድግም፤ የዜጎች ኑሮ አይሻሻልም። ከዕቃው ዋጋ ይልቅ፣ የማጓጓዣ ክፍያውና ውጣውረዱ የሚበልጥ ከሆነ፣ ምኑን ኖርነው? እና የባሕር በር ባለቤት መሆን የግድ ያስፈልጋል?
ሕግና ሥርዓት እስከተከበረ ድረስ፣ የገበያ አሠራርና ነጻነት እስካልተጣሰ ድረስ፣ በጎረቤት አገራት በኩል መተላለፍና መነገድ፣ በጎረቤት አገራት በኩል የባሕር በር መጠቀም ችግር የለውም። በቅናሽ ዋጋ የላቀ አገልግሎት የመስጠትና የመቀበል አሠራር ነው - የነጻ ገበያ ሥርዓት። ወደቡና መርከቡ የማንም ቢሆን ችግር አያመጣም ነበር።
ነገር ግን፣ የባሕር በርና የአገር ድንበር፣ በገበያ ሥርዓት የሚመሩ አይደሉም። በአብዛኛው የፖለቲካ መጫወቻ፣ የመንግሥት መሣሪያ ሲሆኑ ነው የምናየው። ቀሽም መንግሥታትና ከንቱ ፖለቲከኞች፣ የባሕር በርንና ድንበርን እንደመጫወቻና እንደመሣሪያ እየቆጠሩ፣ የራሳቸውን አገር ይጎዳሉ። ዜጎቻቸውን ያደኸያሉ።
መጽናኛቸው ምንድነው? በጎረቤት አገር ላይ የሚያደርስ ጉዳት ይብሳል ብለው ይጽናናሉ። በጎረቤት አገር ዜጎች ላይ የሚደርሰው እንግል ይበልጣል ብለው ሕዝብን ለማሳመን ይሞክራሉ።
ጎረቤት አገር ከተጎዳ፣ የጎረቤት አገር ሰዎች ከተጎሳቆሉ፣ በአንዳች ተአምር የራሳቸው አገር ልዩ ጥቅም ያገኘ፣ የአገሬው ሕዝብም ኑሮው የሚቃና ይመስላቸዋል። ወይም ያስመስላሉ።
ጠብታ ታክል ውጤት፣ ቅንጣት የሚጨበጥ ፍሬ ባይታያቸው እንኳ፣ የጎረቤት አገር ላይ የሚደርስ ጉዳት በሆነ መንገድ ለራሳቸው አገር ጠቃሚ ሆኖ ይታያቸዋል።
“ቤታችን የሚሞላው የጎረቤት ሲጎድል ነው” ብለው ያስባሉ።
“ቤታችን ሲጎድል፣ የጎረቤት ይሞላል” እንደማለት ነው።
ጎረቤት አገር ከተጠቀመ፣ ያለ ጥርጥር የራሳቸው አገር ክፉኛ እንደተጎዳ፣ እንተሞኘ፣ በየዋህነት ድንበሩን ከፍቶ ራሱን ለጥቃት እንዳጋለጠ ያምናሉ። ያሳምናሉ።   
እናም፣ ድርብርብ የድንበር ቁጥጥሮችን በየጊዜው ይፈበርካሉ። ኬላዎችን በየቦታው እየተከሉ መሰናክል ይደረድራሉ።
በተለዋዋጭ አሰራሮችና እርስ በርስ በሚጋጩ ሕጎች አማካኝነት ሰዎችን ማንገላታት፣ ምርትንና ንግድን ማጉላላት ደግሞ ለመንግሥታት አዲስ ጉዳይ አይደለም።
ሥራን ማደናቀፍና ሰዎችን ቁም ስቅል ማሳየት፣ የመንግሥታት ልዩ ተሰጥኦ ነው።
ለብዙ ፖለቲከኞችም ልዩ መዝናኛ ይሆንላቸዋል።
ታዲያ በዚህ መሀል፣ “በሰው አገር” ለማን አቤት ይባላል? “ተንገላታን፣ አሳር አየን!” ብለው ለአቤቱታ ቢጮኹ፣ በብልጠት ጎረቤት አገራትን ለመበዝበዝ የሚሞከሩ ያስመስላቸዋል እንጂ ሰሚ አያገኙም።
እና ምን ይሻላል? መቼም፣ ወደ ጎረቤት አገራት እየዘመትን፣ ሕግና ሥርዓት እንዲስፋፋ፣ የገበያ አሠራርና ነጻነት እንዲከበር ማድረግ አንችልም። ሐሳቡ አይመጣልንም። የመዝመት ሐሳብ ሊመጣልን ይችላል። ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣ የገበያ አሠራርንና ነጻነትን ማስፋፋት ግን፣ እንደ ቁምነገርም እንደ መፍትሔም አንቆጥረውም። ለራሳችን አገር መች ተጠቀምንበት?
ሌላኛው መፍትሔ፣ ትልቋ አገራችን የባሕር በር ያስፈልጋታል፤ ሊኖራትም ይገባል የሚል ሐሳብ ነው።
ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ስሜትም ነው።
ምኞትን ከእልህ ጋር፣ ፍትሕን ከቅናት የተቀላቀለ ቅይጥ ስሜት ሊሆንብን እንደሚችል አትጠራጠሩ። በክፉ ስሜቶች ያልተበከለ የመልካም ምኞትና የፍትሕ መንፈስ ቢሆን ነው የሚሻለው።
የሆነ ሆኖ፣ በጎም ሆነ ክፉ ስሜት ቢደባለቅበትም፣ “ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፤ የባሕር በር ያስፈልጋታል፤ ሊኖራትም ይገባል” የሚለው ሐሳብ፣ ዘመናትን አሻግሮ ሊያሳይ የሚችል፣ ተገቢ የመፍትሔ ሐሳብ ነው።
ታዲያ፣ የዓመት የሁለት ዓመት ኑሮን ብቻ ሳይሆን፣ ሃያና ሠላሳ ዓመት፣ ከዚያም አልፈንና አስረዝመን ማገናዘብ እስከቻልን ድረስ ነው፣ ለውጤት የምንበቃው። በእለት ተእለት ውዝግብ ውስጥ ካልተዘፈቅን ነው የመፍትሔ ሐሳብ ለፍሬ የሚደርሰው።
መነሻችንንና ቁምነገራችንን ካልዘነጋን ነው፣ የባሕር በር ትርጉም የሚኖረው፣ የሚጨበጥ ፋይዳ የሚያስገኘው።
በሌላ አነጋገር፣ ተደጋጋሚ የድንበር ፍተሻዎችንና ውጣውረዶችን፣ ተደራራቢ ኬላዎችንና የተንዛዙ አላስፈላጊ ቁጥጥሮችን፣ የመሰናክል አጥሮችንና እንቅፋቶችን ለማቃለል ካልተጠቀመ፣ የባሕር በር ባለቤትነት፣ ከስም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።
በዚህ መነጽር፣ የአገራችንን ሁኔታ እንመልከት።
አገር ውስጥ፣ ከክልል አልፎ ወረዳ፣ በየከተማው ዳርቻ፣ በመውጪያና መግቢያ፣ መሸጋገሪያና መተላለፊያ መንገዶች ሁሉ፣ ፍተሻና ኬላ፣ ገደብና ኮታ፣ ቀረጥና  ወረፋ፣ ከዚያም በተጨማሪ እንቅፋትና ክልከላ፣ ከነጭራሹም መንገድ መዝጋት፣ መዝረፍ፣ ንብረት ማቃጠልና ሰው መግደል… ስንቱ ይቆጠራል? የእያንዳንዱን ዜጋ ነጻነትና መብት ከጥቃት የመጠበቅ፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሐላፊነት የተሸከሙ፣ አደራ የተረከቡ የመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናት፣ ከፌደራል እስከ ወረዳ፣ ከክልል እስከ ቀበሌ፣ ሥራቸውን በአግባቡ ሲያከናውኑ ነው፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት፣ ጥረው ግረው ኑሯቸውን መምራትና ማሻሻል የሚችሉት።
ታዲያ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በነጻነት በራሱ ጥረት ኑሮውን እንዲመራ፣ የሥራ ፍሬውን እንዲገበያይ እየቻለ ነው ወይ?ከከተማ ወጣ ብሎ መንቀሳቀስ በጣም ያሰጋል። አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ ያስፈራል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የማይሞከር የማይታሰብ ሲሆን አይተናል። ለነገሩ ከተሞች ውስጥ መንቀሳቀስም አስቸጋሪ ሲሆን ተመልክተናል።
ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን መዝጋት ማለት ምንድነው ትርጉሙ? የጂቡቲ መንገድ አደገኛ ከሆነ ምን ማለት ነው?
የሆነ ጊዜ መንግሥት የማታ ጉዞዎች ላይ እገዳ ሲጥል ታስታውሳላችሁ? ደሴ፣ ወልዲያና መቀሌ፣ ደብረማርቆስ፣ ባሕርዳርና ጎንደር፣ አዳማ ናዝሬትና ሐዋሳ፣ ድሬዳዋና ሐረር… የማታ ጉዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተለመደ፣ ተመራጭም እየሆነ የመጣው አለምክንያት አልነበረም። ከመንገድ ጭንቅንቅ ያድናል። ቶሎ ለመድረስ ይረዳል።
ግን ደግሞ፣ የመንገድ መብራት ሳይኖር፣ በጨለማ መጓዝ ለአሽከርካሪዎች ከባድ ነው። በዝግታ ለሚጓዙ የጭነት መኪኖች ብዙም ላያስቸግር ይችላል። በፍጥነት የሚነዱ የሚኒባስና የአይሱዙ አሽከርካሪዎች ግን በተደጋጋሚ ለአደጋ ተጋልጠዋል። ንብረት ወድሟል። ከዚያ በላይ ደግሞ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። የሾፌሮችም የተሳፋሪዎችም።
በተለይ ከደርዘን በላይ ተሳፋሪዎችን የያዘ መኪና፣ በፍጥነት ሲሽከረከር፣ በውድቅት ሌሊት አደጋ ሲደርስበት፣ ጉዳቱ ተደራራቢ ነው። ቶሎ የሕክምና እርዳታ የሚያገኙበት ዕድል አይኖራቸውም።
ይህን ይህን በመጥቀስ ነበር፣ የማታ ጉዞዎች ላይ እገዳ ወይም ክልከላ የተጣለው።
እንዲያም ሆኖ የሚጓዙ አልጠፉም ነበር።
ዛሬ ግን አይሞከርም። ክልከላ ባይኖርም፣ ደፍሮ የሚጓዝ አይገኝም። የትራፊክ አደጋዎችን በመፍራት አይደለም።
ሰውን በመፍራት እንጂ። መንገዶች ሁሉ፣ በእንቅፋት፣ በኬላ፣ በዓመጽ፣ በአደጋ የታጠሩ ሆነዋል።
የባሕር በርና መተላለፊያ ማጣት ከሚያመጣቸው መዘዞች ጋር ይመሳሰላሉ። የባሕር በር የሌለው አገር፣ ኬላ ይበዛበታል።
ነገር ግን፣ በራሱ አገር ውስጥ በየወረዳውና በየቀበሌው እልፍ ኬላዎችን የሚዘረጋና መተላለፊያ መንገዶችን የሚዘጋ ከሆነ፣ ጎረቤት አገራት የባሕር መተላለፊያ ላይ እንቅፋትና ኬላ ሆኑብኝ ብሎ ማማረሩ ምን ትርጉም አለው?


Read 367 times