Saturday, 06 January 2024 21:35

“ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ናቸው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የገና ትውስታ-የዛሬ 24ዓመት


        “በነቢያት ጥሪ መሰረት እጅ መንሻ እንዲያቀርቡ የተጠሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው” ሲሉ አለቃ አያሌው ገለፁ፡፡
ትክክለኛው የዘመን አቆጣጠርም የኢትዮጵያውያን መሆኑን አስታወቁ፡፡
ከብሉይ ኪዳን መፃህፍት የተለያዩ ምዕራፎች አስረጅ እየጠቀሱ እጅ መንሻ እንዲያቀርቡ የተጠሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚሉት አለቃ አያሌው፤ “ኢትዮጵያውያን የትንቢት ጥሪ፣ የትንቢት ቀጠሮ አላቸው፡፡ ይህን ትንቢት ሲጠብቁ ኖሩ፡፡ ጊዜው ደረሰ፡፡ ኮከብም ወጣ፡፡ አምላክ ተወለደ፡፡
 በኮከብም እየተመሩ ሄደው መባዕ ይዘው ሰግደውለታል፡፡ ይህን ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
 አክለውም፤ “ከክርስቶስ ልደት ቀደም ሲል የኢትዮጵያውያን አባት የሚባለው ታላቁ ፈላስፋ ዥረ ጀሽት ይኸው ትንቢት ተገልፆለት ድንግል ህፃኗን እንደታቀፈች የሚያሳይ ምስል ክብረት ቀርፆ ነበር” ሲሉ አለቃ አያሌው አብራርተዋል፡፡በመቀጠልም፤ በውሃ ዳር ተቀምጦ ክዋክብትን ሲመረምር ማሪያም ልጇን እንደታቀፈች በኮከብ ላይ ታትሞ በማየቱ ትንቢቱ ተገልጦለት፣ “የሚወለደው የሰላም አባት ስለሆነ ሄዳችሁ ስገዱለት” ብሎ ማዘዙንና በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያውያኑ በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሄም እንደ ሄዱ አለቃ አያሌው ይናገራሉ፡፡
ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ ግርጎሪ የተባለው ሊቀ ጳጳሳት የቀመረው የዘመን አቆጣጠር የተሳሳተ መሆኑን አብራርተው፤ “እንኳን ለአውሮፓውያን ለአይሁድም የክርስቶስን መወለድ የነገሯቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው” ያሉት አለቃ አያሌው፤  “ኢትዮጵያውያ ለአምላክ ምስክር ናቸውና ከነሱ የበለጠ ሊጠየቅ የሚገባው የለም” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵውያን የዘመን አቆጣጠራቸው የተፋለሰው ክርስቶስ ከተወለደ ከ8 ዓመት በኋላ ዘግይተው ስለሰሙ ነው” የሚለውን አስታውሰው፣ “ይህ የፌዘኞች አባባል ነው፡፡ መጠየቅ የሚገባቸውስ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ አይሁድ እያወቁት አልተቀበሉትም፡፡ አውሮፓውያንም አያውቁትም፡፡ ክርስቶስን ስለማያውቁ ቢጠይቁ ነውር የለውም፡፡ ለዕውቀቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ናቸው መሰረቶቹ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፡- (አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ነሃሴ 28 ቀን 1992፤ የመጀመሪያው ዕትም)

Read 1728 times