Monday, 08 January 2024 20:05

“የሳህለ ሥላሴ ትውፊታዊ ቅርሶች”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 (ክፍል አንድ)
                        


        ( አየህ ከድርሰት አቅራቢዎች ወገን ብቻ ሳልሆን እኔም አንባቢ ነኝ - ድርሰት ሞልቷል ባይ ነኝ፡፡ በአማርኛ አያሌ ደራሲያን ይጽፋሉ እኮ፣ ብዙ አሉ…የስንቱን ስም ልጥቀስልህ፡፡
 በተለይ ተጽፈውየተቀመጡና ያልታተሙ እጅግ ጥሩ-ጥሩ መጻሕፍት እንዳሉ አጋጥሞኛል፣ አውቃለሁም፡፡ ችግራችን የደራሲያን ሳይሆን በአንባቢያን በኩል ነው፡፡
 ስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ አንዳች የጎደለ ነገር ይኖር ወይ እላለሁ?፡፡ አንድ ሰው ተምሮ መጻሕፍትን ካላነበበ ምንድነው ፋይዳው? ግቡ ምንድን ነው? ይቅርታ ይደረግልኝና የተማሩ መሃይሞች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ፈተና ለማለፍ ብቻ የሚደረግ ዓይነት ትምህርት ከሆነ ይህ ለኔ ትራጂክ ነገር ነው የምለው፡፡
 ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ፈቃደኛ ከሆነ የተለየ ከፍተኛ ሚና ሊኖረው ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዓመቱ ውስጥ ታትመው ከሚወጡት መጻሕፍት ውስጥ ምርጥ- ምርጥ ናቸው የሚላቸውን ወስዶ/ከእያንዳንዱ 10 ሺህ ኮፒ/ እንኳን ቢያሰራጭ ተማሪዎቹ ደረጃ በደረጃ ወደ አንባቢነት ሊመጡ ይችላሉ፡፡
ይህን ጊዜ ደራሲና ህብረተሰቡ ተገናኙ ማለት ነው፡፡ የእውቀት መንገዱ እኮ ብዙ ነው፡፡ሪፖርተር መጽሔት. ጥር.1992)
የዘመናችን የታሪክ ልሂቃን በአሁኑ ወቅት የደረሱበትን ዘመናዊ የሳይንስ ጥበብ መሰረት በማድረግ፤ የታሪክ መረጃ ዓይነቶችን እና ምንጮቻቸውን በሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡
እነርሱም “የስነ ልሳን - የቋንቋ ሳይንስ መረጃዎች”፤ “የሰነድ - የጽሁፍ የስዕል የቅርፅ መረጃዎች”፤ “የትውፊት - ባህላዊ የአፈ’ታሪክ ወይም የኪነ‘ቃል መረጃዎች”…በማለት፡፡ ከዚህም ተነስተው ያለፉትን ዘመናት ታሪካዊ ልምዶች ከወቅቱ ተጨባጭ እውነታ ጋር በማገናዘብ የሰው ልጆችን ቀጣይ የዕድገት አካሄድ፤ አቅጣጫ እና አዝማሚያ መርምሮ መጠቆም ይቻላል ብለውም ያምናሉ፡፡ እኛም ይህን ታሪካዊና ጥናታዊ እውነታ መሰረት በማድረግ በተለይ ሶስተኛውን መዘን ትውፊታዊውን በመነጠል፤የአገራችንን ነባር የሆነውን የጉራጌን ህዝብ ባህልና እምነት፣ የእርሻ እና የከብት እርባታ፣ የስልተ ምርት ግንኙነት እና የምርት ክፍፍል፣ የዕደ ጥበብ ዕውቀት እና ክምችትን በጥቅሉ እንዲሁም በዝርዝር ለማወቅ እና ለመገንዘብ እንዲረዳን በደራሲና ተርጓሚ ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም ትውፊታዊ ይዘት ባላቸው ሁለት ድርሳናት “ዘ-አፈርሳታ እና የሺንጋ መንደር” በኩል፤ በሳቸው መነጽር አጮልቀን የጉራጌን ባህል ለመመርመርና ለማጤን እንሞክራለን፡፡ ታዲያ የብሄሩ ቱባ ጥናት የሆነው “የጉራጌ ባህል እና ታሪክ”ን ተጨማሪ ዋቢ ማድረጉን ሳንዘነጋ በዚህ በክፍል አንድ አንኳር ነጥባችን ወደ ሆነው ወደ ዘ-አፈርሳታ እናመራለን፡፡
ዘ - አፈርሳታ
ከመጽሐፉ የማገኘው እርካታ ነው እንድተረጉም የሚያደርገኝ፡፡ የዚህን ታላቅ ሰው፣ የዚህን ዝነኛ ደራሲ ስራ እኔ ብቻ አንብቤ፣ እኔ ብቻ አድንቄ መቅረት የለብኝም! የኛ አገር አንባቢያን ይህን መጽሐፍ ማንበብ አለባቸው”… በሚል ፅኑ እምነታቸው ምክንያት በተረጎሟቸው መጻሕፍት ትውልድ አስተምረዋል፡፡ በሳህለ ሥላሴ ከደርዘን በላይ በሚሆኑ የትርጉም ስራዎቻቸው ተምሮ ላደገ የኔ ቢጤ፤ እሳቸውን እንዲህ ባለ መልኩ…ወጥ በሆነ ስራቸው ማግኘት መቼም አጀብ ነው፤ ደስም ያሰኛል፡፡ ብዙ ተደራሲያን ሳህለ ሥላሴን በትርጉም እንጂ በወጥ ስራዎቻቸው እምብዛም አናውቃቸውም፡፡ ይሁን እንጂ (ወግ ሞክረው “ሹክታ”ን አቅርበዋል፣ በልቦለድ ዘውግ ደግሞ “ወጣት ይፍረደው”ን አስነብበዋል፣በታሪካዊ ልቦለድ ዘርፍ “ባሻ ቅጣው”ን አስደጉሰዋል) ከትርጉም ባሻገር በጉራጊኛ፣ በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ የደረሷቸው መጻሕፍት አያሌ ናቸው፡፡ ጽፈዋቸው የመታተም እድል ያላገኙ ሌሎችም መጽሐፍት በእጃቸው እንደሚገኝ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ (እድሜና ጤና ይስጣቸው እንጂ ያልታተሙት መታተማቸው አይቀርም) ሳህሌ ለልማዳዊ የጉራጌ ባህል ሁሌም በመሰረታዊነት ታማኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአፈርሳታ ባህልና ዘመናዊነትን በሚዛን ለማስታረቅ በእጅጉ ይጥራል፡፡ ተርጓሚው በኢትዮጵያ የጉራጌ ህብረተሰብ ነባር ባህላዊ አኗኗር ውስጥ የቱን ያህል ስር የሰደደ ማንነት እንዳለው የምናይበት ስራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል በፈርጥ መጽሔት ላይ ያደረገለት ቃለ-ምልልስም ይህንኑ በይበልጥ ያረጋግጥልናል…“እሱ ተወልዶ ያደገበትን ባህልና ሕዝብ ልቅም አድርጎ ያውቃል፡፡
 አጅሬ ታዲያ ትምህርቱን ካደቀቀ በኋላ ስለዚያ ሕዝብ ባህል ብዙ ጽሑፎችን ፅፎ አንጀቱን አርሷል፡፡ ሣህለ ሥላሴ ዘብሔረ ጉራጌ! የ‹‹ሺንጋ ቃያ›› እና ‹‹ዘ - አፈርሳታ›› ከዚህ ከበለፀገ ሕዝብ አኩሪ ባህል ተወለዱ፡፡ (ቁጥር 28. ሰኔ. 1994)
ሳህለ ሥላሴ “ፍኖተ ህይወት” በተሰኘ ግለ-ታሪኩ ውስጥ እንዳሰፈረው ከ1963 - 68 ወንጂ ስኳር ፋብሪካ በህዝብ ግንኙነት ክፍል አገልግሏል፡፡ አሜሪካ አገር የጀመራቸውና ወንጂ ላይ አጠናቆ ያሳተማቸው ሁለት ስራዎቹንም ጠቅሷል፡፡ የመጀመሪያው “ወጣት ይፍረደው” ሲሆን፣ ተከታዩ ደግሞ “ዘ-አፈርሳታ” ነው፡፡ አፈርሳታ አራት ታሪኮች አሉት፡፡ አስቀድሞ የናማጋ ጎጆ የተቃጠለበትን ታሪክ “እሳት በመንደሩ” በሚል ርዕስ ይተርካል፡፡ (የመጽሐፉ አንኳር ጭብጥም ይኸው ነው) በጉራጌ ምድር ከነዋሪው ብዛት አንፃር ህዝቡ የሚኖረው ተጣቦና ተጨናንቆ እንደመሆኑ፤ በዚህ ምክንያት በቂ የእርሻ መሬት ስለሌለው የወርቃማ እጅ ባለቤት የሆኑ ባለሙያዎች፣ አብዛኛው ወጣትና የተቀረው የህብረተሰቡ አባላት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በንግድ ሥራ ለመተዳደር ተገደዋል፡፡ ሳህሌ በዚህ ትረካ ውስጥ ቀደም ሲል የነበረውን የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አነሳስቶ በተለይ በታታሪነቱ፣ በስራ ትጋቱ የታወቀውን የቤተ ጉራጌን ህብረተሰብ ህይወት የገለጸበት ነው፡፡ ሌሎች “የጭሰኛ ልጅ”፣ “የመስቀል በዓል” እና በዋናነት ደግሞ የመጽሐፉ አቢይ ጉዳይ ስለሆነው አውጫጪኝ በመባል የሚጠራው አፈርሳታ የተባለውን ልዩ ባህላዊ የምርመራ ዘዴን ያስቃኛል፡፡ (ሳህለ ሥላሴ አፈርሳታን ለመጀመሪያ ጊዜ ጽፎያስተዋወቀው በእንግሊዘኛ እንደመሆኑ፣ በአፍሪካ ጸሐፊዎች ዝርዝር ውስጥም ተካቶለታል)፡፡ በተለምዶ ባህል ስንል የአንድ ህብረተሰብ የአስተዳደር፣ የአሰራር፣ የአነጋገር፣ የአለባበስ፣ የአዘፋፈን፣ የሰርግና ለቅሶ፣ የፍትህና የፍርድ ስርዓት ወዘተ…አጠቃላይ ልማዳዊ ስርዓቶችን ያካትታል፡፡ ባህል የሰዎች የአስተሳሰብና የአኗኗር ሁኔታ ከመሆኑ አኳያ፣ የጉራጌ ህዝብ ደግሞ የተለያዩ አኩሪ ባህሎች አሉት፡፡ እኚህ የማህበራዊ ህይወታቸው መልካም መገለጫ የሆኑትና ታዋቂ ከሆኑ የጉራጌ ባህሎች መካከል - የጀፎር ሴራ ‹‹የፍትህ ሸንጎ፣ የሸንጎ የሽማግሌዎች መሰብሰቢያ፣ ለለቅሶ የሀዘን መቀመጫ በመሆን እሚገለገሉበት›› በርቸ እና ጡር ‹‹ህዝቡ በመተሳሰብ፣ በመተዛዘን፣ በመከባበርና በመረዳዳት በሰላም እንዲኖር ብልህ የጉራጌ አባቶች የመሰረቷቸው የህሊና ህጎች›› ቂየ ‹‹የሚፈራና የሚከበር የድንበር መጋፋት እንዳይኖር ማስከበሪያ ድንጋይ›› ወኪያ ‹‹ሀብት ያለው ግለሰብ ለደሀ ገበሬ ከብቶች በመስጠት እያረባ ከባለቤቱ ጋር እኩል እንዲካፈሉ ማድረጊያ ስልት›› ጉዳ ወይም ጉርዳ እንዲሁም ቂጫ በመባል የሚታወቁና ሌሎችም…፡፡ የጥንት የጉራጌ አባቶች ይህን መሰል ነባራዊ ባህላዊ እሴት፣ ያልተፃፈ ህግ ለትውልድ ማቆየታቸው ምን ያህልለ ሀገር እና ለወገን  አሳቢ እንደነበሩ በግልጽ ያሳያል፡፡ ከጉራጌ ነባር ትውፊቶች ጋር አብሮ እሚካተት አውጫጪኝ፤ የምርመራ ዘዴ ወይም አፈርሳታን ደርባቸው መሀመድ ገለቱ የተባለው አጥኚ “ጀፎር ጉራጌና ህዝቡ” በተሰኘ መጽሐፋቸው በገጽ 131 ውስጥ እንዲህ ይፈቱታል፣ያፍታቱታል፣ ያብራሩታልም፡፡ ሰውን በግፍ መግደል፣ ቤት ቃጠሎ፣ ባሪያ ፈንጋይነትና የመሳሰሉት ከባድ ወንጀሎች ናቸው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ወንጀሎች ፈጽሞ ሳይያዝ ቢያመልጥ ህዝቡ በሙሉ በአንድነት ተነስቶ፣ ከብቱን ይነዳበታል፤ ሰብሉን ይጨፈጭፍበታል፡፡ የጎሳውን ሀብት ጭምር በአፈርሳታ ስርዓት እያስወጣና እያወጣጣ ይቀጣበታል፡፡…ሳህሌ የአፈርሳታን ስነሥርዓት የሚያስቃኘን በናማጋ በኩል ነው፡፡ ሰላሳ ጎጆዎች በአንድ ሌሊት በተቃጠሉበት ወቅት፤ ሁሉም በከባድ እንቅልፍ ላይ ነበሩ፡፡ በርግጥ ቀደም ብሎም መንደሪቱ የሌቦች መደበቂያ፣ የወንጀለኞች መናኻሪያ ከሆነች ሰነባብታ ነበር፡፡ ከቃጠሎ ባሻገር አያሌ ከብቶችም ተሰርቀዋል፡፡ ነዋሪው በነቂስ ይህን ወንጀልና ሌብነት በአፈርሳታ አጋልጠን መከላከል ይኖርብናል ሲሉ ተነስተዋል፡፡
 ዋና ገፀ ባህሪ የሆነው ናማጋ የመንደሩ ከበርቴ ነው፡፡ ከሌሎች ጎጆዎች በአመዛኙ በቃጠሎ የወደመው የርሱ እልፍኝ ነው፡፡
 ምርመራው ተጧጡፏል፤ ወንጀለኛውን የሚያውቅ ግን ጠፍቷል፡፡ በናማጋ ማመልከቻ ውስጥ ያሉ ተጠርጣሪዎች ወንጀለኛ መሆን አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ ማህበረሰቡ በሽማግሌዎች የፍርድ ውሳኔ መስማማት ግድ ሆነበት፡፡ የናማጋ መጎዳት ኪሳራው ሁሉንም ነዋሪ ተጠያቂ በማድረግ ሲወራረድ ትረካው ይደመደማል፡፡ በፍርዱ መሠረት ናማጋም ወደ እያንዳንዱ ሰው መኖሪያ በመሄድ ካሳውን ሰብስቦ በመውሰድ ይካሳል፡፡ በሰው ላይ የሚደርስ የትኛውም ወንጀል በማህበረሰቡ የጋራ ቅንጅት ሊወገድእንደሚገባውና ኃላፊነቱም የሁሉም መሆኑን ያስተምራል፡፡…እንደ አፈርሳታው ሁሉ የጉራጌ ትውልድ በፍትህ፣ በፍርድ አሰጣጥ እና በፀጥታ ማስከበር ረገድ በእጅጉ የበረታና የታፈረ ነባር ሌሎች ህጎችም አሉት፡፡ አኚህን ነባራዊ ህጎች ተላልፎ የተገኘ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚጠየቅበት፣ ያለምህረት የሚቀጣበት፡፡ እዚህ ጋ ለማንኛውም የወንጀል አይነት ተመጣጣኝ የሆነ ባህላዊ መቀጮ ያለ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በወንጀል ፈጻሚው ማህበረሰቡ ሳይቀር ስለሚያድምበት፣ መግቢያና መውጫም ስለሚያጣ በገዛ ፈቃዱ እጁን ሰጥቶ ይቀጣል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችም በጥብቅ አስበውበት፣ በብርቱ መክረውበት በባህላዊ ህጉ መሰረት በጉማ ያስታርቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት በሌባ ላይ የሚጣለው ቅጣት የበረታ እንደነበር ደርባቸው በዳሰሳው አያይዞ ዘግቧል፡፡
የጀመሩትን ነገር ጨርሰው ሲያፀኑ የቃል መተማመኛቸውና ማጽኛቸው “እሙረት” ይሉታል፡፡ (እንደ መሀላ ነገር ነው) የ1994 ዓ.ም በስነጽሑፍ ዘርፍ የህይወት ዘመን ተሸላሚ የሆነው ደራሲና ተርጓሚ ሳህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም በልጅነቱ ከገብስ ቆሎ መቆርጠም እስከ ክትፎና ቁርጥ ስጋ አቀላጥፎ መብላትን ያውቅበት ነበር፡፡ በጠንበለል ቁመቱ ቅርጫት ኳስ ተጫውቷል፡፡ በረጃጅም ክናዱ የቡጢ ውድድር ተናርቶበታል፡፡ ዳንስ በጣም ይወድዳል - ውቤ በረሃ ደንበኛ ነበር፡፡
 አሜሪካ ሳለ በርካታ ልቦለዶችን አንብቧል፡፡ በእጅጉ ካነበበውና ከሚያነበው አንዱ የፍልስፍና መጻሕፍትን ነው፡፡ በሰው ልጅ ነፃነት ያምናል፡፡ የዣን ዣክ ሩሶ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ሩሶ ሰው ነፃ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም ባለበት ሁሉ እስረኛ ነው፤ ስለሆነም ምንግዜም ለነፃነቱ መታገል አለበት ምናምን ይላል፡፡ (በቀጣይ ሳምንት በክፍል ሁለት፤ የሺንጋ መንደርን ይዤ እስክመለስ በዘመን አይሽሬዎቹ የጉራጊኛ ባህላዊ ዜማዎች የወራይ ሰመሌ እና ላሌ የ ቦላላን ተጋበዙልኝ፡

Read 337 times