Saturday, 13 January 2024 00:00

አሜሪካና እንግሊዝ በሁቲ አማፅያን ላይ ጥቃት ሰነዘሩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአሜሪካና የእንግሊዝ ወታደራዊ ሃይል በየመን የሁቲ አማፂያን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ከባድ ጥቃት መፈፀማቸው ተገለፀ፡፡
የዓይን እማኞች ጥቃቱን፤ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ለሮይተርስ ያረጋገጡ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳት ጆ ባይደን ከትላንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በቡድኑ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይሉ አስጠንቅቀዋል። “እነዚህ የታለሙ ጥቃቶች አሜሪካና አጋሮ በሰራተኞቻችን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን እንደማይታገሱና የአማፅያኑ የበመርከቦችን ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያደናቅፉ እንደማይፈቅዱ አሳስበዋል፡፡
 ከቀዶ ህክምና በኋላ በገጠማቸው ኢንፌክሽን ለህክምና በሆስፒታል የሚገኙት የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን ባወጡት መግለጫ፤ ከትላንት በስቲያ በአሜሪካና እንግሊዝ ጥምረት የተሰነዘረው ጥቃት፣ ድሮኖችን ባሊስቲክና ክሩዝ ሚሳይልን እንዲሁም ራዳርና የአየር መቆጣጠሪያን ጨምሮ የሁቲ አማፅያን ወታደራዊ አቅሞች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አንድ የሁቲ ባለስልጣን የተፈፀመውን የአየርና የባህር ጥቃት አስመልክቶ ሲናገሩ፤ በዋና ከተማይቱ ሰነአ እንዲሁም በሰአዳና ዳማር ከተሞች “ወረራ” መፈፀሙን አረጋግጠው ጥቃቱ “የአሜሪካን - ፅዮናውያንና ብሪታንያ ወረራ” በሚሏቸው ወገኖች፡፡የዓይን እማኞች ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ የአሜሪካና አጋሮቿ ጥቃት ያነጣጠረው ከሰንአ አየር ማረፊያ አጠገብ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ያለው ወታደራዊ ስፍራ፣ በሆዲይዳህ የሚገኘው የሮውቲ የባህር ሃይል ሰፈር እንዲሁም በሃጃ ግዛት የሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎችን ነበር፡፡
አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት የሁቲ አማፂያን፣ ከሰሞኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ከሚፈፅሙት የድሮንና ሚሳይል ጥቃቶች እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን አሜሪካም ቡድኑ በቀይ ባህር ላይ ጥቃት ከመፈፀም እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋ ተዘግቧል። ሆኖም የአማፂ ቡድኑ አሻፈረኝ ብሎ ጥቃቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል። ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ የሁቲ አማፅያን  በቀይ ባህር 27 መርከቦች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን በዚህም 15 በመቶ የሚሆነው የዓለም የንግድ መርከብ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ተጠቁሟል፡፡  ከትላንት በስቲያ አሜሪካና እንግሊዝ በቡድኑ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ የቡድኑ መሪ፤ አሜሪካ በላይ የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስዱ  ዝተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመግለጫቸው የሁቲ ጥቃት በቀጥታ የአሜሪካ መርከቦችን ያለመ ነው ብለዋል፡፡የአሜሪካ ሪፐብሊካን ኮንግረስ አባላት በአማፂው ቡድን ላይ የተወሰደው እርምጃ ከመዘግየቱ በቀር በአዎንታዊ ጎኑ ተቀብለውታል፡፡ አንዳንድ የዲሞክራት ኮንግረስ አባላት በበኩላቸው አሜሪካ ሌላ የአስር ዓመት ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከትላንት በስቲያ በየመን ላይ የተፈፀመው ጥቃት የሁቲ አማፅያን በቀይ ባህር ላይ ከፍተኛ የተባለውን ጥቃት ከሰነዘሩ ጥቂት ቀናት በኋላ የተከናወነ ነው የተባለ ሲሆን አማፅያኑ ወደ ደቡባዊ ቀይ ባህር የተኮሷቸውን 21 ድሮኖችና ሚሳይሎች የአሜሪካና የእንግሊዝ ባህር ሃይል መትተው ለመጣል መገደዳቸው ተዘግቧል፡፡



Read 958 times