Saturday, 13 January 2024 00:00

ዘመን ባንክ በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ የ47.5 ሚ. ብር ድርሻ መያዙን ገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ESX ወደ ሥራ ለመግባት ተጨማሪ 625 ሚ ብር ያስፈልገዋል
                      

       ዘመን ባንክ 47.5 ሚሊዮን ብር በኢትዮጵያን ሴክዊሪቲ ኤክስቼንጅ ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ሴክዊሪት ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለመግባት 625 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል ተብሏል።
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በዘመን ባንክ ዋና መሥርያ ቤት  በተፈረመው የኢንቨስትመንት ውል  መሰረት ዘመን ባንክ በኢትዮጵያን ሴክዊሪቲ ኤክስቼንጅ 5% ድርሻ መያዙ ተረጋግጧል። የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ዘበነ እንደተናገሩት፤ ኢኤስኤክስ ገዢና ሻጭን፤ ፈላጊና ተፈላጊን የማገናኘት ሥራ የሚያከናውን ሲሆን፤ የካፒታል ገበያው እንዲያድግና የአገር ኢኮኖሚ እንዲቀየር በማገዝ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተነግሯል፡፡ የዘመን ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ በኢኤስኤክስ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሲወስን የባንኮችን የኢንቨስትመንት ገደብ ባማከለ መንገድ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘበነ፤ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያለውን የገበያ ስርዓት በኢትዮጵያ እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት በአርአያነት እንደሚከተሉን አምናለሁ ያሉት የባንኩ ሥራ አስፈፃሚ፤ የሴክዊሪቲ  ኤክስቼንጅስ መዋቅር መዘርጋቱ ተቋማት ወደ ገበያ እንዲወጡና ሃብት መፍጠር እንዲችሉ መንገድ  እንደሚያመለክታቸው ተናግረዋል፡፡
”ዘመን ባንክ ከESX ጋር ተባብሮ ለመሥራት ኢንቨስት በማድረግ ከመጀመሪያዎቹ  አንዱ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን፤ የካፒታል ገበያ መስፋፋት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፎች ላይ ለውጥ ያመጣል፣ ስለዚህም በዚህ አስደሳች ጉዞ ውስጥ በመቀላቀላችን ተደስተናል።” ብለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ኩባንያዎች፤ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙም ሆነ ሲስፋፉ አክሲዮኖቻቸውን ይሸጥላቸዋል። ዋናው አገልግሎቱም አዲስ ለሚመሠረቱም ሆነ ለነባር ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን መፍጠር ነው ተብሏል፡፡
የESX ዋና ሥራ  አስፈፃሚ ዶክተር ጥላሁን እሸቱ ካሳሁን በበኩላቸው፤ መ/ቤታቸው የካፒታል ገበያን ለማስተዋወቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ይገልፃሉ። ፈጣን የንግድ መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ፣ አዳዲስ ሠራተኞችን በመቅጠርና የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት  የዘመን ባንክ ኢንቨስትመንት መምጣቱን አመሥግነዋል። የኢትዮጵያን ሴኪዮሪትስ ኤክስቼንጅ በ900 ሚሊየን ብር ካፒታል ለመገንባት መታቀዱን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ዶክተር ጥላሁን እሸቱ፤ ባለፈው ሁለት ዓመት ውስጥ ሃምሣ በመቶ ጊዚያቸውን የወሰደው ስለ ካፒታል ገበያው የማሳመን፤ የማስረዳትና የማስተዋወቅ ስራ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
መንግስትና ሌሎች አጋር ተቋማት እስከ  25 % ድርሻን በመግዛታቸው 225 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የገለፁት ስራ አስፈፃሚው፤ የተቀረውን 625 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመሙላት ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትና ኩባንያዎች እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ከባህርማዶ የፋይናንስ ተቋማት ለመሰ ብሰብ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ብለዋል። አጠቃላይ ሂደቱም መንግስትና የግሉ ዘርፍ አንድ ላይ መሥራት እንደሚችሉ ማሣያ እንደሚሆንም ዶ/ር ጥላሁን ጠቁመዋል፡፡”ከ10 ሚሊየን እስከ 150 ሚሊየን ብር ኢንቨስት በማድረግ የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅስ ድርሻን መግዛት ይቻላል። በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 30 ባንኮችና 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አብረውን እንዲሰሩ  እንፈልጋለን“ ብለዋል፤የESX ዋና ሥራ  አስፈፃሚው፡፡



Read 313 times