Saturday, 13 January 2024 00:00

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪኮስት

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(2 votes)

  • እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ወጭ ሆኖበታል
      • አዘጋጅ አገር እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል
      • ሞሮኮ ውዱ ብሔራዊ ቡድን በ381.34 ሚሊዮን ዶላር
      • ቪክቶር ኦሲሜሔን ውዱ ተጨዋች በ120.74 ሚሊዮን ዶላር
      • የ24 ብሔራዊ ቡድኖች ተጨዋቾች ስብስብ 2.94 ቢሊየን ዶላር
      • ከ226 በላይ ተጨዋቾች ታላላቅ ሊጎችን ለቅቀው ወደ አፍሪካ ይመለሳሉ
      • ከስፖርት ትጥቅ ኩባንያዎች ገንኖ የወጣውና ኳሷን ያቀረበው ፑማ ነው
      • ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች ፤ በዓለም ዙርያ ከ650 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች


       34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ አይቮሪኮስትና ጊኒ ቢሳዎ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል።   በአምስቱ የአይቮሪኮስት ከተሞች አቢጃን፣ ሳን ፔድሮ፤ ያሙሱኩሩ፣ ቡዋኬና ኮርሐጎ ላይ የሚገኙ 6 ዘመናዊ ስታድየሞች  ጨዋታዎቹ ይካሄዳሉ ። ስታድዬሞቹ ከ20-60 ሺህ ተመልካች የሚይዙ ሲሆን አላሳኔ ኡታራ፤ ፊሊክስ ሑፌት ብዋኜ፤ ቻርልስ ኮናን ባናኒ ፤ አማዱ  ጓው ኩሊባሊ፤ ሎረንት ፖኩና  ስታዴ ዴላ ፓይክስ ስታድየሞች ናቸው። የአይቮሪኮስት እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለሮይተርስ እንደተናገሩት የአፍሪካ ዋንጫው  በአዲስ ስታድየሞች ግንባታና እድሳት፤ በመንገድና ሆስፒታል ግንባታ እንዲሁም በሌሎች መሠረተልማቶች እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበታል። የቻይና መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል። የአፍሪካ ዋንጫው ልዮ ምልክት ሳቂታው ዝሆን አክዋባ Akwaba ሲሆን የአይቮሪኮስትን እንግዳ ተቀባይነት የሚያንፀባርቅ ነው።
የአፍሪካ እግር ኮንፌዴሬሽንና የአይቮሪኮስት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫው መስተንግዶ ያወጡት በጀት ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን ለሽልማት የቀረበው ገንዘብ 40 በመቶ  በማሳደግ 14 ሚሊዮን ዶላር መዘጋጀቱ ታውቋል። ለሻምፒዮኑ ቡድን ከዋንጫው ሽልማት ባሻገር 7 ሚሊየን ዶላር የሚበረከት ሲሆን ለሁለተኛው 4 ሚሊየን ዶላር ፤ በደረጃ ጨዋታ 3ኛና 4ኛ ሆነው የጨረሱት 2.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሩብ ፍፃሜ የሚደርሱት 1.3 ሚሊየን ዶላር ይታሰብላቸዋል።
24 ብሔራዊ ቡድኖችን በ6 ምድቦች ተከፋፍለው በ30 ቀናት ውስጥ 52 ጨዋታዎችን ያደርጉበታል። የዋንጫው ፉክክር በምዕራብና በሰሜን አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል እንደሚሆን ተጠብቋል። አልጄርያ፤ ሞሮኮና ግብፅ ከሰሜን አፍሪካ ሴኔጋል፤ ናይጀሪያና ካሜሮን ከምዕራብ አፍሪካ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ወስደዋል። ከ120ሺ በላይ የስታድየም መግቢያ ትኬቶች መሸጣቸውን ያመለከተው የካፍ ኦፊሴላዊ ገፅ አይቮሪኮስት ከ32 ሺህ በላይ፤  ጊኒ ቢሳዎ ከ28ሺ በላይ፤ኢኳቶሪያል ጊኒ ከ16ሺ በላይ፤ ናይጄሪያ ከ12 ሺ በላይ እንዲሁም ሴኔጋል ከ10ሺ በላይ ትኬቶችን በመግዛት ተከታታይ ደረጃ አግኝተዋል። የአፍሪካካ ዋንጫውን ለመታደም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች አይቮሪኮስት እንደሚገቡ የተጠበቀ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በሚኖረው የብሮድካስት ሽፋን  ከ650 ሚሊዮን በላይ ተመልካች እንደሚያገኝ ተጠብቋል።  
የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት የአገር ገፅታ በመገንባት፤ በቱሪዝምና በስፖንሰርሺፕ ገቢ በመፍጠር  እንዲሁም የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት አስተናጋጁን አገር  ተጠቃሚ ያደርጋል። በ2019 እ.ኤ.አ ላይ ግብፅ 32ኛውን አፍሪካ ዋንጫ በማዘጋጀት 83 ሚሊየን ዶላር በላይ አስገብታለች። ከዚያ በፊት በ2017 እኤአ ላይ 35ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በጋራ ያስተናገዱት ጋቦንና ጊኒም ተመሳሳይ ገቢ አግኝተዋል። በ2021 እኤአ ደግሞ ካሜሩን ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 79.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሆኖ በውድድሩ ታሪክ ክብረወሰን ተመዝግቧል።
የስፖንሰርሽፕ ገበያው ተሟሙቋል እስከ 54.25 ሚ. ዶላር
የአፍሪካ እግር ኳስ  ኮንፌደሬሽን በአፍሪካ ዋንጫ ዙርያ የሚያሰባስበው የስፖንሰርሺፕ ገበያ እየተሟሟቀ መጥቷል። ውድድሩ ከመጀመሩ አንድ ወር በፊት  የመጨረሻውን የውል ስምምነት ከካፍ ጋር ያደረገው  ዓለምአቀፍ ኩባንያው ዮኒሌቨር ነው። ካፍ በተከታታይ የሚያስተናግዳቸው ሁለት አህጉራዊ ውድድሮች ላይ Unilever  በአብይ ስፖንሰርነት  ለመስራት ውል ፈጽሟል። የአይቮሪኮስቱ አፍሪካ ዋንጫንና በሞሮኮ የሚካሄደው  የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ናቸው።  ኩባንያው በአፍሪካ የሚካሄዱትን የእግርኳስ እንቅስቃሴዎችን የመደገፍ እቅድም አለው። ዩኒሌቨር በ190 አገራት የሚንቀሳቀስና በዓመት እስከ 60.1 ሚሊዮን ዶላር ሽያጭ የሚያስመዘግብ ግዙፍ ኩባንያ ነው።
ከአፍሪካ ዋንጫው ኦፊሴላዊ ስፖንሰሮች ዋንኛው ላለፋት 16 ዓመታት ከካፍ ጋር ሲሰራ የቆየው የኤነርጂ ኩባንያ   TotalEnergies ነው። ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ፑማ Puma፤ ዋን ኤክስቤት 1xbet፤ ቪዛ Visa፤  ኦሬንጅስ Oranges እንዲሁም ሬክሶና Rexona ናቸው። ለአፍሪካ  ዋንጫው የገቡ ስፖንሰሮች ደግሞ ኤኮባንክ Ecobank፣ አፕሶኒክ Apsonic፣ ኤር ኮትዲቫሬ Air cotedeivoire ፣ ራዝል Razzle እና  ቴክኖ Tecno ናቸው። አራት የአይቮሪኮስት ኩባንያዎችም ለአፍሪካ ዋንጫው ስፖንሰር ለመሆኑ የበቁ ሲሆን ሤለስቴ celeste ፤ ፖርቲዬ portie ፤ ስማርት smart እና ሎናኪ Lonaci የተባሉት ናቸው።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ከአፍሪካ ዋንጫንና መሰል አህጉራዊ ውድድሮች በማካሄድ  በዓመት ውስጥ 125.2 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል። ከስፖንሰርሺፕ የሚገኘው ገቢ በዓመት ከ54.25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው።
 ከ226 በላይ ተጨዋቾች ታላላቅ ሊጎችን ለቅቀው ወደ አፍሪካ ይመለሳሉ
በአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፉ 24 ብሔራዊ ቡድኖች ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት ከ226 በላይ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ወደ አፍሪካ ይመለሳሉ። በተለይ ከአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች ከፈረንሳይ ሊግ 1፣ ከጣልያን ሴሪኤ፣ ከስፔን ላሊጋ፣ ከጀርመን ቦንደስ ሊጋና ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተጠሩት ታላላቅ  ተጨዋቾች ናቸው። ለአፍሪካ ዋንጫው በርካታ ተጨዋቾችን በመልቀቅ  ግንባር ቀደም የሆነው ክለብ በፈረንሳይ ሊግ 1 የሚወዳደረው ሜትዝ ሲሆን 11  ተጨዋቾችን ወደ ብሔራዊ ቡድኖቻቸው በመላክ ነው። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ኖቲንግሃም  ፎረስት 5 ተጨዋቾችን ወደ አፍሪካ ዋንጫው በመሸኘት  በሁለተኛ ደረጃ  ሲከተል የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ተሳታፊው  ባየር ሌቨርኩዘንና የጣሊያኑ ኡዲኒዜ 4 ተጨዋቾችን በማስመረጥ የሚጠቀሱ ናቸው። በአጠቃላይ ከ38ኛው አፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ የስፔኑ ላሊጋ 88 ተጨዋቾችን በመልቀቅ ቀዳሚው  ነው። የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ 48፣ የጣሊያን ሴሪኤ 37፣ እንዲሁም የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 26 ተጨዋቾችን ከ2 ሳምንት እስከ ወር የሚያጡ ይሆናል።
ከስፖርት ትጥቅ ኩባንያዎች ገንኖ የወጣውና ኳሷን ያቀረበው ፑማ
18 የዓለማችን ትልልቅ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ገብተዋል። ከፍተኛውን ተሳትፎ ያደረገው የጀርመኑ ኩባንያ ፑማ ነው። በ38ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ፑማ “ፖኩ” የተባለቸውን ኳስ ከማቅረቡም በላይ ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የወሰደው ስድስት ብሔራዊ ቡድኖችን በማስታጠቅ ሲሆን ፤ ግብፅ ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ አይቮሪኮስት፣ ሞሮኮና ሴኔጋል ናቸው። የእንግሊዙ አምብሮ ከናሚቢያናና ዲ.ሪ ኮንጎ ቡድኖች ጋር ይሰራል ። የጀርመኑ ኩባንያ አዲዳስ ከአልጀሪያ  እንዲሁም የአሜሪካው ናይኪ ከናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር በትጥቅ አቅራቢነት ተሳታፊ ናቸው። ኢኳቶሪያል ጊኒ ከErrea፤ ጊኒ ቢሳዎ ከGuisport፤ ኬፕቨርዴ ከTempo፤ ሞዛምቢክ ከViper Sportwear፤ ካሜሮን One all sports፣ ጋምቢያ  ከSaller፣ ቡርኪናፋሶ ከTovio፤ አንጎላ ከLacatoni፤  ቱኒዚያ ከKappa ፤ ማሊ ከAirnees፤ ደቡብ አፍሪካ ከLe coq sportif፤ ዛምቢያ  ከKoPa እንዲሁም ታንዛኒያ ከSandaland የስፖርት ትጥቅ ኩባንያዎች ጋር አፍሪካ ዋንጫውን ይሳተፋሉ።
24 ብሔራዊ ቡድኖች  2.94  ቢሊየን ዶላር
(Transfermarkat)
በታዋቂው የጀርመን የእግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ ተንታኝ ድረገፅ Transfermarkt መሰረት በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የሚሳተፉት 24 ብሔራዊ ቡድኖች የተጨዋቾች ስብስብ አጠቃላይ  የዋጋ ተመን 2.94 ቢሊዮን ዶላር  ነው።
 በተጨዋቾች ስብስብ ከፍተኛ የዋጋ ተመን አንደኛ ደረጃ የሚወሰደው በ381.34 ሚሊዮን ዶላር  የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ነው። ናይጀሪያ 367.73፤ አይቮሪኮስት 367.27 ፤ ሴኔጋል 301.2 ፤ ጋና 215.19፤ አልጀሪያ 208.83 ፤ ካሜሮን 154.18፣ ማሊ 151.28 እንዲሁም ግብፅ 149.05 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የተጨዋቾች ስብስባቸው ተተምኖ እስከ 10ኛ ደረጃ ይሰጣቸዋል።
የአፍሪካው ኮከብ ቪክቶር ኦሲሜሔን ውዱ ተጨዋች 120.74 ሚሊዮን ዶላር
በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ከሚሳተፉ ተጨዋቾች መካከል በዝውውር ገበያው ከፍተኛውን የዋጋ ተመን በማግኘት በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው በ2023 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተሸለመው ናይጀሪያዊው ቪክቶር ኦሲሜናህ በ120.74 ሚሊዮን ዶላር ነው። የግብፁ መሐመድ ሳላህ 71.35፣ የሞሮኮው አችረፍ ሃኪሚ 71.35፣ የጋናው መሀመድ ኩዱስ 49.5 እንዲሁም የአይቮሪኮስቱ ኡስማኔ ዲዮማንዴ በ43.9 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ተመን ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ።
የአፍሪካ ዋንጫ ዋጋዋ 139.5 ሺ ዶላር
በዓለም እግር ኳስ የሚሰጡ ዋንጫዎችና ልዮ ሽልማቶችን ዋጋ በማውጣት ደረጃ የሰራው ስፖርት ሰካይዳ (Sportskeeda) እንዳመለከተው የአፍሪካ ዋንጫ በዋጋ ግምቷ 4ኛ ደረጃ  ላይ ናት።  የዓለም ዋጫ 18.7 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ አንደኛ ደረጃ ሲሰጣት፤ የእንግሊዙ ኤፍ ካፕ ዋንጫ 1.1 ሚሊዮን ዶላር፤ የአውሮፓው የወርቅ ኳስ 558ሺ ዶላር፤ የአፍሪካ ዋንጫ 139.5 ዶላር እንዲሁም የጣሊያን ሴሪኤ ስኩዴቶ በ60 ሺ ዶላር የዋጋ ተመን በማግኘት እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

Read 571 times