Monday, 15 January 2024 13:11

”ሠላሳዎቹ” - ከጽንሰቱ እስከ ውልደቱ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ዮናስ ታረቀኝ ይባላል፡፡ በጀርመን ባህል ማዕከል የቤተ መፃህፍትና የመረጃ ሃላፊ ነው፡፡ ከአስር በላይ የተለያዩ መጻሕፍትን ከጀርመንኛና ከእንግሊዝኛ በመተርጎም ለአንባቢ ማድረሱን ይናገራል፡፡ በቅርቡ ለንባብ በበቃውና በጀርመን ባህል ተቋም ሙሉ ድጋፍ በታተመው “ሠላሳዎቹ” የተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ላይ ከሃሳብ ማመንጨት እስከ ማስተባበር ድረስ ተሳትፏል፡፡ በአጭሩ የፕሮጀክቱ መሪ ነበር፡፡ ለዮናስ ታረቀኝ “ሠላሳዎቹ” በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድበልዙሪያ አንዳንድ ጥያቄዎችን ላቀርብለት እንደምፈልግ ስነግረው ምንም ሳያቅማማና ለደቂቃ ማሰብ ሳያስፈልገው ፈጣን ምላሹንበመስጠቱ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ከዚያም በላይ ግን ሥራዎቻቸው በመፅሐፉ የተካተተላቸው ደራስያንም የመጠየቅና ሃሳባቸውንየመግለጽ እድል ያገኙ ዘንድ ያቀረበልኝ ሃሳብ አስደምሞኛል፡፡ እውነቱንም ነው፡፡ በዚህ መሰረት በቀጣይ ሳምንታት ከጥቂቶቹጋር ቆይታ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ለዛሬ ግን ከደራሲና ተርጓሚ ዮናስ ታረቀኝ ጋር በ“ሰላሳዎች” መድበል ዙሪያ ያደረግነውን አጭር ቃለ ምልልስ እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡



           “ሠላሳዎቹ” የተሰኘውን የአጫጭር ልብወለዶች መድበል የማሳተም ሃሳቡ እንዴት ተጠነሰሰ? መቼና በማን ?
የጀርመን ባህል ማዕከል ባለፉት  አስርት ዓመታት በሀገራችን ውስጥ የንባብ ባህል እንዲዳብር የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፡- ወርሃዊ የመጽሐፍ ውይይቶች (በአካልም በኦንላይንም)፣ ሀገር አቀፍ የንባብ ፌስቲቫሎች (አዲስ አበባ ታንብብ፣ ኢትዮጵያ ታንብብ)፣ የተረት ሳምንት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ በየቤተ መጻሕፍቱ ከደራሲያን ጋር  የሚደረግ የንባብና የልምድ ማካፈል (ንባብን ባህላችን እናድርግ በሚል መርህ ስር)፣ በንባብ ለህይወት የመጽሐፍ አውደ ርዕይ ላይ በመሳተፍ ደራሲያንን ከታዳሚያን ጋር የማገናኘትና የማስፈረም እንዲሁም በተለያዩ ስነ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት የማካሄድ መርሃ ግብሮችን ማከናወን፣ የጀርመን ደራሲያንን ስራ በንባብ፣ በውይይት እንዲሁም ስራዎቹ እንዲታተሙ በማድረግ ማስተዋወቅ የመሳሰሉት ይገኛሉ። “ሠላሳዎቹ” የእነዚህ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውጤት ነው።  ገፊ ምክንያቶቹ፣ አሁን ሀገራችን ውስጥ ባለው ሁኔታ መጽሐፍ ማሳተም እጅግ ፈታኝ መሆኑ፤ የሀገራችን ወጣት ጸሐፍት የህትመት ብርሃን እንዲያገኙላቸው የሚፈልጓቸው ርዕሰ ጉዳዮች ምንድናቸው? ምን ያሳስባቸዋል? ስለምን መጻፍ ይፈልጋሉ? ይህንንስ እንዴት ባለ ስነ ጽሑፋዊ ለዛ ያቀርቡታል? የሚሉ ጥያቄዎች፤ እንዲሁም እጅግ በጣም በጥቂቱ ቢሆንም የኢትዮጵያዊ ወጣት ስራዎችን ቢያንስ ወደ ጀርመንኛ አፍ መልሶ ለጀርመን ማህበረሰብ የማቅረብ ፍላጎቶች ናቸው። መነሻ ሃሳቡን እኔ ያነሳሁት ቢሆንም እንዲዳብር በማድረግ የተሳተፉ ወዳጆቼ ብዙ ናቸው። የጀርመን ባህል ተቋም ደሞ ተቀብሎትና አምኖበት፣ በጀት መድቦ የተካሄደ ነው።    
ጸሃፊዎቹ ካልተሳሳትኩ አዳዲሶች ናቸው--- በአጭር ልብወለድ ሥራዎቻቸው  የምናውቃቸው ጸሃፍት አልተሳተፉም ብዬ ነው? ሆን ብላችሁነ ነው?
ጽሑፎቹን ለመሰብሰብ የታሰበው በውድድር መልክ ስለነበር፣ መስፈርቶች መውጣት ነበረባቸው። ስለዚህ አንዱ ያደረግነው የዕድሜ ገደብ ማስቀመጥ ነው። ይኸውም ከ18 እስከ 35 ዓመት የሚል ነበር፤ ከ-እሰከው ትንሽ ሰፋ ያለ ቢሆንም፡፡ ስለዚህ ምንም አንኳን ጥቂት ከዚህ በፊት የታተሙ ስራዎች የነበሯቸው ጸሐፍት ቢኖሩም፣ አብዛኛዎቹ አዳዲሶች ናቸው። እድሉን መስጠት የፈለግነውም በተቻለ መጠን ለጀማሪና አዳዲስ ጸሐፍት ነበር። ዋናው ትኩረታችን የነበረው ግን ያቀረቡት ስራ አዲስነት ላይ ነበር።   
ልምድ ከሌላቸውና ከጀማሪ  አዳዲስ ጸሐፍት ለህትመት ብቁ የሆኑ  ታሪኮችን  በቀላሉ ማግኘት አያስቸግርም ?  አድካሚስ አይሆንም ?
የማይታወቅና ልምድ የሌለው ጸሐፊ ለህትመት የሚበቃ ምርጥ ስራ ሊያቀርብ አይችልም የሚል እምነት የለኝም። ብዙ “ዋው” ያስባሉን፤ እጃችንን አፋችን ላይ ያስጫኑን፣ ከዚህ በፊት የማናውቃቸው ጸሐፍት ስራዎችን አንብበናል። እነዚህን ስራዎች ያቀረቡልን ግን ሳይደክሙ አልነበረም። ልምድ ደሞ ያለ ድካም አይገኝም። ወደ እኛ ጉዳይ ስመጣም ተመሳሳይ ነው።  መጀመሪያ እድሉን መስጠት ነው የፈለግነው፣ በራሳቸው ተማምነው ስራዎቻቸውን የላኩትን በሙሉ አድንቀን ነው የተቀበልነው። በውድድሩ መስፈርት (ለምሳሌ የተመጠነ የገፅ ብዛት) እና ሌሎችም፣ በዳኞች በተቀመጠ ስነ ጽሑፋዊ መመዘኛ መሰረት ከቀረቡልን 103 አጫጭር ልቦለድ ታሪኮች ውስጥ በዳኞች መካከል ከተካሄደ የከረረ ውይይት በኋላ 30 አጫጭር ልቦለዶችን ብቻ ማውጣት፣ ማድከሙ አይቀሬ ነው። የተመረጡት 30 ስራዎች እንዳሉ አይደለም ለህትመት የበቁት። ለጸሐፍቱ ከስራዎቻቸው በመነሳት ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ጎኖች የተዳሰሱበት፣ መሻሻል የሚኖሩባቸው ነገሮች የተመለከቱበት፣ መሰረታዊ የስነ ጽሑፍ ጉዳዮች የተጠቆሙበትና ልምዶች የተካፈሉበት፣ የሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል። በመቀጠል ፀሐፍቱ ከተሰጣቸው ስልጠና በመነሳት ጽሑፎቻቸውን መልሰው እንዲያዩ፣ እንዲያሻሸሉ፣ እንዲጨምሩ እንዲቀንሱ ሰፊ እድል እንዲሰጣቸው ተደርጓል። በመጨረሻም ከአርታኢያቸው ጋር በመሆን ለሕትመት ብቁ እስኪሆን ድረስ ተግተዋል። አርታኢውም በጣም ለፍቷል። ጥያቄህ አያደክምም ወይ አልነበር? ቀላል ያደከማል!
ታሪኮቹን ለማሰባሰብ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባችሁ? በማሰባሰብ ሂደቱ የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምን ነበሩ?
በትክክል ካስታወስኩ ወደ ሁለት ወር ገደማ የወሰደ ይመስለኛል። የሰበሰብነው በኢሚይል እንዲላክ በማድረግ ስለነበር፣ ብዙ ተግዳሮት አልገጠመንም። አልፎ አልፎ ግን መስፈርቱን የማያሟሉ ጽሑፎችና መስፈሩትን የማያሟሉ ጸሐፍት ያጋጥሙን ነበር።
የተለያዩ ጸሃፍት የፈጠራ ሥራዎች በጋራ መውጣታቸው ፋይዳቸው ምንድን ነው?
አንዱ እንደ ቡፌ የተለያየ ጣዕም መፍጠር መቻላቸው ነው። ብዙም ባይሆን ከአዲስ አበባ ውጪ የሚኖሩ ጸሐፍትም የተካተቱበት ነው። ይህ በራሱ የሚሰጠው ነገር ያለ ይመስለኛል። ቀጥታ ከዚህ ጋር መያያዝ ባይኖርበትም፣ በጸሐፍቱ መካከል መተዋወቅና ግንኙነት መፍጠር መቻሉም መልካም ነው ብዬ አስባለሁ። ምናልባት የ“ሠላሳዎቹ” መድበል የህትመት ዋጋ በጀርመን ባህል ተቋም በመሸፈኑ እንጂ፣ አሁን ባለው የህትመት ዋጋ መናር የተለያዩ ጸሐፍት ዋጋውን እየተጋሩ፣ በጋራ ስራዎቻቸውን ማውጣት ቢችሉ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።  
እስቲ  “በሠላሳዎቹ” የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ውስጥ የተካተቱት ታሪኮች ምን እንደሚመስሉ በአጭሩ ጠቅልለህ ንገረን ?
እዚህ ላይ አርታኢው ቴዎድሮስ አጥላው በመጽሐፉ ላይ በመግቢያነት ካሰፈረው ጽሑፍ በላይ ሊያሳይልኝ የሚችል ስለማይኖር እሱኑ እንዳለ ብጠቅስ  ይሻላል።   
‘’በዚህ ሠላሳዎቹ ባልነው ስብስብ ከተካተቱት ሥራዎች አብዛኞቹ የደራሲዎቹን ወይም ድርሰቶቹ የተጻፉበትን ዘመን መንፈስ የሚወክሉ ናቸው። ደራሲዎቹ በጦርነት፣ በጥላቻ፣ ከሥር በመነቀል፣ በመካካድ፣ በአደጋዎች፣ በጭካኔ ድርጊቶች፣ በምንትነት መቃወስና በመሳሰሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት ከተፈጠረው የወል ድባቴ፣ የወል ትሮማ ያመለጡ አይመስሉም። ፊት ለፊት ባይኾንም በሥራዎቻቸው እነዚህን ለመግለጥ ወይም ለማምለጥ የሞከሩም ይመስላሉ። ለሕትመት በመረጥናቸው ሠላሳዎቹም ኾነ በተቀሩት ታሪኮች ውስጥ ሞት፣ የመኪና አደጋ፣ መካካድ፣ መወስለት፣ ድህነት፣ ኀዘን ጎልተው የሚሰሙ ድምጾች ናቸው። ከሁልዮ ኮርታዛር ዝነኛ አገላለጽ ብንዋስ፤ እነዚህ ሠላሳዎቹ የዚህን ዘመን መንፈስ በየራሳቸው መቃን ቀንብበው ያስቀሩ ሠላሳ “ፎቶግራፎች” ሲኾኑ፣ መድበሉ ደግሞ ጥየቃ ለመጣው አንባቢ እንግዳ የቀረበ አልበም ነው። (እንግዳው ፎቶዎቹ መሐል ራሱን መፈለጉ፣ አንዳንዴም ማግኘቱ አይቀርም።
በስልት ረገድ፣ ከተረኮቹ አንዳንዶቹ ለግል ማስታወሻነት የቀረበ አጻጻፍ አላቸው።የስሜትና የሐሳብ ጥልቀቶቻቸው ከምናብ የተፈጠሩ/የተቀመሩ ሳይኾን በአብዛኛው ከጸሐፊው/ተመክሮ የተቀዱ ያስመስሏቸዋል። ደግሞ አሉላችሁ፡-  በሥነ ልቡና እና በሥነ አእምሯዊ ሰብአዊ ጣጣዎች ላይ የተመሠረቱ፤ስለዚህም በይነዲሲፕሊናዊ ንባብን በተለይም ሳይኮአናሊሲስን የሚጋብዙ። ከጽንሰ ሐሳብ ለመዛመድ እንኳን ባይጻፉ፤ ግጭቶቻቸው፣ ጭብጦቻቸው፣የገጸባሕርያታቸው ጠባያትና ድርጊያዎቻቸው የሥነጽሑፍንና የሌሎች ሙያዎችን ጽንሰ ሐሳቦች በመፈከሪያነት የሚጣሩም አሉባቸው። ኢምክኑያዊ ፍርሓት፣ የአእምሮ ጤና እክል፣ ድባቴ፣ መርሳትና መዘንጋት፣ በራስ እጅ የማለፍ ግፊት፣ ኤዲፐሳዊ ምስቅልቅል፣… በአርእስተ ጉዳይነት ገንነውባቸው የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ሙያዎችን በማናበቢያነት ይጋብዛሉ። ‘’
እስቲ ታሪኮቹን ስታሰባስቡ ከጠየቃችኋቸው መስፈርቶች ሦስቱን ብቻ ጥቀስልኝ.....?
አንዱ እድሜ ነው፤ ቀደም ብዬ ጠቅሼዋለሁ። ሌላው የገፅ መጠኑ ከአምስት ያላነሰ፣ ከአስር ያልበለጠ የሚለው ነው። አንድ ሰው ለውድድር ማቅረብ የሚችለው አንድ ስራ ብቻ ነው የሚልም ነበረበት።
በመድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ታሪኮች ውስጥ አንተ በግልህ የወደድከውና በቀዳሚነት የምታስቀምጠው የትኛውን  ነው?  ደራሲውን ሳትጠቅስ ርዕሱን ብቻ ልትነግረኝ ትችላለህ----?
በዳኝነቱ ውስጥ ባልሳተፍም እኔም ስራዎቹን የማንበብ እድሉ ነበረኝ። አጋጣሚ ሆኖ ወደ ጀርመንኛ እንዲተረጎሙ በዳኞች የተመረጡት ሦስት ስራዎች እኔም ይበልጥ የወደድኳቸው ናቸው። “የክራሩ ክር”፣ “ኩኩ ሉሉ” እና “የማልረሳው መረሳት”።  
ከዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አጭር ልብወለድን ጨምሮ ጠብሰቅ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ተዳክመዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ በዚህ ሃሳብ ትስማማለህ?
ሁልጊዜም ዘመን የራሱ መልክ አለው። የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ከኛ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተጽዕኖው ሁለንተናዊ መሆኑን ልንክደው አይቻለንም። ስለዚህ መፍትሄ የሚሆነው መገዳደር ሳይሆን፣  ይህንን ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ እንዴት አድርጌ ነው እኔ ለምሰራው ጉዳይ የምጠቀምበት፣ ምን አይነት ኦዲየንስ ነው ያለው፣ ወዘተ የሚለው ነው መታሰብ የሚኖርበት። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚወጡ የስነ ጽሑፍ ስራዎች በህትመትም በዲጅታልም እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ሰራዎቻቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያወጡ ቆይተው፣ ምርጥ ምርጥ ስራዎችን ወደ ህትመቱ ገበያ ያመጡ ብዙ ጸሐፍት አሉ።  ስለዚህ በእኔ በኩል መዳከም ሳይሆን ዲጂታል ሚዲያው በሚፈልገው መልኩ የስነ ጽሑፍ ስራ ቅርፁንም ሆነ አቀራረቡን እየቀየረ ነው በሚል መውሰድ ይሻላል ባይ ነኝ።     
በዚህ መድበል ዝግጅት ውስጥ የጀርመን ባህል ተቋም ሚና ምንድን ነው?
ከጽንሰቱ ጀምሮ እስከ ውልደቱ የባህል ተቋሙ ኃላፊነት ነበር። በሃሳብም ሆነ በገንዘብ።


Read 547 times