Monday, 22 January 2024 08:51

”ሠላሳዎቹ” - በወጣት ጸሃፍቱ አንደበት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ጎተ የአጭር ልቦለድ ቡፌ ነው ያቀረበልን“


መስዑድ ጀማል እባላለሁ፡፡ በ“ሠላሳዎቹ“ መድበል ውስጥ “ወሎ ሎጂ“ የተሰኘ ሥራዬ ታትሞልኛል፡፡ በሙያዬ በአማራ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን (አሚኮ) ጋዜጠኛ ነኝ፡፡
ድርሰትህ በ“ሠላሳዎቹ“ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ውስጥ በመካተቱ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ? ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞህ ያውቃል? የራስህን መጽሃፍስ አሳትመሃል?
ልዩ ደስታ ነው የሚሰማህ። እስከዛሬ ትደሰተው ከነበረው ደስታ ከፍ ያለ።ትንሽ ኩራትም ቀልቀል ያለበት። ቀደም ሲል በመፅሐፍ መልክ የወጣ ሥራ የለኝም። በሌላ የጥበብ ቅርፅ ግን አለ። ከዚህ በፊት ደራሲ ሜሪ ፈለቀ  የአጭር ፊልም ወድድር አወዳድራ ነበር። ‘ሀቅ’ በሚል አጭር ፊልም ተወዳድሬ 1ኛ በመውጣት 50,000 ብር አሸንፌያለሁ። ያው ስለሚያያዝ  ብዬ ነው። በመፅሐፍ ግን ይህ የመጀመሪያዬ ነው።
የአጫጭር ልብወለዶች ስብስቡን   እንዴት አገኘኸው?
 በጎተ ፅሁፌ ከተመረጠ በኋላ መፅሐፉ ከመታተሙ በላይ በጉጉት ስጠብቀው የነበረው መፅሐፉ ወጥቶ 29 ታሪኮችን እስካነብ ነበር። መፅሐፉ ወጥቶ 29ኙን ታሪኮች ካነበብኩ በኋላም መጓጓቴ ልክ እንደነበረ ነው የገባኝ። ጎተ የአጭር ልቦለድ ቡፌ ነው ያቀረበልን። የተለያየ መልክ፣ መዓዛና ጣዕም ያላቸው አጫጭር ልቦለዶችን ነበር ያገኘሁት።  የመጣንበት አካባቢያዊ ዳራ ደግሞ ድርሰቶቹ በመቼት እንዳይገደቡ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያን በሁሉም መአዘን ትቃኛታለህ። ወደ ወሎ፣ ትግራይ፣ አርባምንጭ፣ ጅማ... የማትሄድበት ሀገር፤ሄደህም የምታጣው ነገር የለም። ራሳቸው ወደቆረቆሩት የምናብ ሀገር የሚወስዱህም አሉ። “ሠላሳዎቹ“ መፅሐፍ በህብረ ቀለማት ያጌጠ እንደምንለው፣ “በህብረ ታሪኮች” ያሸበረቀ መፅሐፍ ነው ማለት እንችላለን። በቋንቋ አጠቃቀም፣በአተራረክ፣በጭብጥ፣በገፀ ባህሪ አሳሳል፣በትልም አጎናጎን፣በአተያይ፣በአፃፃፍ ፍልስፍና ሁሉም የራሱን ቦይ እየቀደደ እንድትፈስ ያደርግሀል። ከአንዱ ታሪክ ወደ ሌላው ታሪክ ስትሄድ በጉጉት ነው፤ “ይሄኛው ደሞ ስለምን ይሆን?” እያልክ ነው። በሁሉም ድርሰቶች የምትደመምበት አንዳች ነገር አታጣም።
የወጣት ጸሃፍት ሥራዎች እንዲህ ተሰባስበው በጋራ መታተማቸው ምን ፋይዳ አለው ብለህ ታስባለህ?
አብዛኛው የመፅሐፉ ደራሲ “ማነህ?” በሚል ጥያቄ  በጥበብ ሸንጎ ቆሞ ነፃ ለመውጣት እየተሰቃየ ባለበት ሰዓት ጎተ  ደርሶ “እሱ እከሌ ነው...ደራሲ ነው” ብሎ ምስክር ሆኖ፣ ነፃነትና ማንነት እንደሰጠን አምናለሁ።
ወጣት እንደመሆናችን ብዙ ጥርጣሬዎችና ፍርሀቶች ወስጣችን ይኖራሉ። መመረጣችን፣ ከምናከብራቸው ደራሲዎች ጋር መገናኘታችን ማውራታችንና “ሠላሳዎቹ” መፅሐፍ መታተሙ እነኚህን ፍርሀቶቻችንና ጥርጣሬዎቻችንን እንድንጋፈጥና እንድናሸንፋቸው አድርጎናል። ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ በብዙዎች አልቀመስ ያለውን የመፅሐፍ ህትመት ዋጋ መናርን አልፈን እንድንነበብ ሆነናል። ብዙዎች ይህንን ዕድል አላገኙም። ከዚያ ባለፈ ስራዎቻችን በጋራ መታተማቸው “Gothe 2022 winners” የሚል ቤተሰብ እንዲመሰረት እድል ከፍቷል። አዳዲስ ደራሲዎች ከዚህ በፊት የህትመት ብርሀን ካገኙ ደራሲያን ጋር እንድንተዋወቅና እንድንማማር አድርጓል። ፅሁፎችን መላላክና  አስተያየት እንድንለዋወጥ፣ ቀጣይ ሌሎች ስራዎችን  በጋራ ለመስራት እንድናቅድ አድርጓል።
በጀርመን የባህል ማዕከል ድጋፍ ከተሰጣችሁ አጭር ሥልጠና ምን አዲስ ትምህርት ቀሰምክ?
ስልጠናው ጥሩ ነበር...theory አልነበረም፤ በስልጠናው። የራሳችንን ፅሁፍ እየመዘዙ በጠንካራና በደካማ ጎኖቻችን ነበር ስንሰለጥን የነበረው። ከስልጠናው ስለ ፊደላትና ቃላት አጠቃቀም ብዙ የተማርኩት ነገር አለ። በዘመን ሂደት የተቀየሩ ቋንቋዎች አሉ። “አደረግኩ” ብለን እንፅፋለን፤ “አደረግሁ” ማለት ሲገባን።”ፀሀይ” ነው፣ “ጸሀይ” ብለን መፃፍ ያለብን? ብዙዎቻችን በዚህ ክፍተት ነበረብን። ነገር ግን በስልጠናውም ፤በአርታኢያችን ቴዎድሮስ አጥላው እገዛም የለወጥነው ነገር አለ።
ከአገራችን ወይም ከውጭ አገራት  የአጭር ልብወለድ ጸሃፍት ማንን ታደንቃለህ?
ብዙ የማደንቃቸው የአጭር ልቦለድ ደራስያን አሉ፤ሌሊሳ ግርማ፣አሌክስ አብርሀም...እና አዳም ረታን እመርጣለሁ፡፡ የግድ አንድ ከተባለ አዳም ረታ ምርጫዬ ነው፡፡ አንድን የጥበብ ሰው ስመዝን አይምሮ ውስጥ ተሰንቅረው በሚቀሩ፣ ለትውስታ ቅርብ በሆኑ ስራዎቹ የመመዘን አባዜ አለብኝ። የአዳም ረታ የ”ሎሚ ሽታ” አይምሮዬ ውስጥ የቀረ ታሪክ ነው።ከገፀ ባህሪያቱ እስከ አተራረክ ቴክኒኩ አይምሮዬ ውስጥ አለ። ከውጭ ኦ ኸነሪን  እመርጣለሁ። ያው ቅድም እንዳልኩት ነው። “The last leaf” እያደር የሚደንቀኝ ታሪክ ነው።



ባለፈው ሳምንት የ“ሠላሳዎቹ“ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል የሃሳብ ጠንሳሽና የፕሮጀክቱ መሪ እንዲሁም በጀርመን ባህል ማዕከል የቤተ መፃህፍትና የመረጃ ሃላፊ የሆነውን ዮናስ ታረቀኝ በመጽሐፉ ዝግጅቱ ዙሪያ ማነጋገራችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ድርሰቶቻቸው በመድበሉ የተካተተላቸው ሦስት ወጣት ጸሃፍትን አነጋግረን፣ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡  




”ለአንባቢያን ምርጫን ያሰፋል ብዬ አምናለሁ“

Read 509 times