Sunday, 28 January 2024 20:31

ኢትዮ ቴሌኮም በመንፈቅ ዓመቱ 42.86 ቢ. ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮው መንፈቅ ዓመት 42.86 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንና አጠቃላይ የደንበኞቹ ብዛት 74.6 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ይህን ያስታወቀው ሰሞኑን  በስካይ ላይት ሆቴል የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለመገናኛ ብዙኃን ባቀረበበት ወቅት ሲሆን፤ ሪፖርቱ ከሐምሌ 2015 እስከ ታህሳስ 2016 በጀት ዓመት ያለውን የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል፡፡  
በመንፈቅ አመቱ አጠቃላይ የደንበኞቹ  ብዛት 74.6 ሚሊዮን መድረሱን የጠቆመው ኩባንያው፤ ይህም  ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ4.7  ሚሊዮን ወይም የ6.7% እድገት ማሳየቱን እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98.3% ውጤት መመዝገቡን አመልክቷል፡፡
በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 71.7 ሚሊዮን፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 36.4 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድ ባንድ 688.3 ሺህ እንዲሁም የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 834 ሺህ ሲሆኑ፤ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 68.5% ማድረስ ተችሏል ብሏል፤ኢትዮ ቴሌኮም፡፡


”የደንበኞችን ቁጥር ለማሳደግ የተቻለው፣ ተሞክሯቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ተደራሽነትን ለማስፋት፤ ተጨማሪ የሞባይልና የመደበኛ ኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራዎች በመሰራታቸው፣ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትና የምርትና አገልግሎት አጋሮች በማካተት አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ በመቅረባቸው፣ የ5ጂ አገልግሎት በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 114 (64 አዳዲስ እና 50 ነባር) የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች በመቅረባቸው ነው፡፡” ብሏል፤ ኩባንያው በመግለጫው፡፡ የአገልግሎት ጥራትን እንዲሁም የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ከማሳደግ አንጻር የኔትወርክ ማስፋፊያ የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲሆኑ ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical)፣ በተመሳሳይ ወቅት(real time) መከናወን ለሚያስፈልጋቸው አገልግሎቶች እና internet of things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችለውን 5G የሞባይል ቴክኖሎጂ አገልግሎት በተወሰኑ ከተሞች ለገበያ ማቅረቡንም አመልክቷል፡፡


 በግማሽ ዓመቱ በተደረገ የኔትወርክ ማስፋፊያ በ3G 678.2 ሺህ፣ በ4G 1.1 ሚሊየን እና በ5G 148.2 ሺህ በድምሩ 1.9 ሚሊየን ተጨማሪ ደንበኛ የሚያስተናግድ አቅም መፈጠሩን የጠቆመው ኩባንያው፤ በዚህም አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኛ ማስተናገድ አቅሙን 81 ሚሊየን ለማድረስ እንደቻለ ነው የገለጸው፡፡


በመንፈቅ አመቱ ከተሰሩ  የሞባይል ማስፋፊያዎች መካከል ለገጠር ቀበሌዎች የሚውል በ10 ክልሎች፣ ለ41 ወረዳዎች፣ 229 ሺህ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችሉ 41 የሞባይል ጣቢያዎች ተተክለው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን እንዲሁም  በገጠር አካባቢ ባሉ 92 ነባር ጣቢያዎች ላይ የ3G ማስፋፊያ ስራዎች ተከናውነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አስታውቋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፤ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት፣ ቀጣይነት ያለው የደንበኞቹን አቅም ያገናዘበ አዳዲስና የተሻሻሉ ምርትና አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የተለያዩ የሞባይል ፋይናንስና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ በመንፈቅ ዓመቱ 42.86 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 98% ማሳካቱን አስታውቆ፤ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8.86 ቢሊዮን ብር ወይም የ26% ብልጫ እንዳለው ጠቁሟል፡፡ ”የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ፤ የድምጽ አገልግሎት 41.8% ድርሻ ሲኖረው፣ ዳታና ኢንተርኔት 25.7%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9.3%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 8.7%፣ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሽያጭ 5%፣ ቴሌብር 2.5%፣ የመሰረተ ልማት ኪራይ 1.1%፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 5.9% ድርሻ አላቸው፡፡” ብሏል፤ የኩባንያው መግለጫ፡፡
 የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 84.7 ሚ. ዶላር መገኘቱንና ይህም የእቅዱን 109% ያሳካ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡
 የቴሌብር አገልግሎት ከ41 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የዕቅዱን 104% ማሳካቱን በመግለጫው ያመለከተው ኩባንያው፤  የግብይት መጠኑን  910.7 ቢሊዮን ብር በማድረስ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁሟል፡፡  የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረ አንስቶም በአጠቃላይ 1.7 ትሪሊየን ብር በኢኮኖሚው ላይ እያንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አክሎ ገልጧል፡፡


በግማሽ ዓመቱ ከዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ጋር በተያያዘ 602 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የአገልግሎት የክፍያ ስርዓታቸውን ከቴሌ ብር ጋር እንዲያስተሳስሩ  መደረጉንም ኩባንያው በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በመንፈቅ ዓመቱ ያጋጠሙትንም ተግዳሮቶች የዘረዘረ ሲሆን፤ በተለያዩ የሀገሪቱ  ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣በኔትዎርክ ሀብት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ቴሌኮም ማጭበርበር፣ የግንባታ ስራ ግብአቶች እጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋትና የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡




Read 468 times