Saturday, 17 February 2024 00:00

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በአዲስ መልክ ሥራውን ማከናወን ጀመረ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ታህሣሥ 18 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. የባንኩን ባለአክሲዮኖች 24ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በብሔራዊ ባንክ አመቻችነትና ታዛቢነት ባደረገው ምርጫ የተመረጡት የቦርድ አባላት ዝርዝር ጥር 24 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፀድቋል፡፡ በዚህም መሠረት አዲሱ ቦርድ ባንኩን የማስተዳደር ተግባሩን ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተረክቧል፡፡
አዲሱ ቦርድ ባንኩ ያለበትን ከፍተኛ ተግዳሮት በመገንዘብ ፈጥኖ ወደ ሥራ በመግባት የራሱን አመራር እና የንዑስ ኮሚቴዎችን ድልድል በማካሄድ አቶ ሺሰማ ሸዋነካን በሊቀመንበርነት እንዲሁም ዶ/ር ወንድሙ ተክሌን በምክትል ሊቀመንበርነት መርጧል፡፡ በቀጣይም ቦርዱ፣ ባንኩ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥና ቀን ከሌት መስራትን እንደሚጠይቅ ከግንዛቤ በማስገባት የባንኩን ስምና ዝና  ወደነበረበት መመለስን እንዲሁም የባንኩን ዘለቄታዊ ጥቅም ማስጠበቅን ዋነኛ ግቡ ያደረገውን የባንኩን የመልሶ ማደራጃ የዘጠና ቀናት ዕቅድ (90 days Turnaround Plan) ተልሟል፡፡ ቦርዱ ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት እስከዋና ክፍል ኃላፊ ድረስ  ካሉት የሥራ ኃላፊዎችም ጋር ትውውቅና ውይይት አካሂዷል፡፡ ቦርዱ በተጨማሪም እንደ ባንክ እንዲሰሩ ባሰባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ቦርዱ የተለመውን የመልሶ ማደራጃ ዕቅድ ይፋ በማድረግ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተረጋጋ መንፈስና በጥንቃቄ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ የቦርዱ ንዑሳን ኰሚቴዎችም ጊዜ ሳይሰጡ ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት ጋር በቀረቡ ሪፖርቶችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፤ አቅጣጫም አስቀምጠዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ የካቲት 6 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ከክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ከክቡር አቶ ሰሎሞን ደስታ እና ከሌሎች የባንኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል፡፡
በስብሰባውም ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አዲሱ ቦርድ ከፊቱ የተደቀኑትን ተግዳሮቶች ግዙፍነት በአፅንዖት አስገንዝበው ሃላፊነቱን በልዩ ቁርጠኝነት እና በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት እና ፍጹም ታማኝነት እንዲወጣ በአፅንዖት አሳስበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን ቦርድ የስራ አፈፃፀም በቅርበት እንደሚከታተልና እንደሚገመግም የባንኩ ገዢ በስብሰባው ላይ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡  
በዋነኛነት ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በባንክ ሴክተር ቀደምት እና ጠንካራ ከሆኑት ባንኮች መካከል የሚመደብ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም አዲሱ ቦርድ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደነበረበት ደረጃ በሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጐኑ በመሆን በቅርበት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚሰጠው የባንኩ ገዢ አረጋግጠዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ፤ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ተግዳሮት በገጠመው በዚህ ወቅት ከጐኑ በመሆን ፈተናዎቹን በስኬት እንዲወጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያደረገለት ለቆየው እና ወደፊትም ለሚቀጥለው ሁሉ አቀፍ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ አክብሮቱን እና ላቅ ያለ ምስጋናውን በባንኩ ማህበረሰብ ስም ማቅረብ ይወዳል፡፡

Read 528 times