Sunday, 18 February 2024 00:00

የአብ ኩላሊት ማዕከል አገልግሎት መቋረጥ ህይወታቸውን ለአደጋ እንዳጋለጠውታካሚዎች ገለፁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በመንግስት ተቋማቱ ጫና አገልግሎቱን ለማቆም ተገደናል - የማዕከሉ መስራች
“ከገባነው ውል ያጎደልነው የለም” - አዲስ አበባ ጤና ቢሮ እና ምንሊክ ሆስፒታል


ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያዊቷ ዲያስፖራ ትዕግስት አበበ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮና በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ትብብር ለኩላሊት ታማሚዎች ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአብ ሜዲካል ሴንተርና ሪሀብሊቴሽን ሊሚትድ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ ህይወታቸው ለአደጋ መጋለጡን ችግር ላይ መውደቃቸውን ታካሚዎች ለአዲስ ድማስ ገለፁ።
ህይወታችንን ለማቆየት ትግል ላይ በነበርንት ወቅት አብ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተከፍቶ እፎይ አልን ስንል  “የግብአት እጥረት አጋጥሟል” በሚል ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ካቆመ ሶስት ሳምንት አልፎታል ያሉት ታካሚዎች፤ ግማሾቻችን ወደ ልመናና ወዳጅ ዘመድ ማስቸገር፣ ከፊሎቻችን የቀረችንን ጥሪት ወደ መሸጥ፣ ይህን ያልቻልን ፊታችን ከተደቀነው ሞት ጋር መፋጠጥ ዕጣ ፈንታችን ሆኗል ሲሉ አማርረዋል።
“ወዳጅ ዘመድ የሚደግፈን ወደ ግል የኩላሊት እጥበት ማዕከል አገልግሎት ፍለጋ ስንሄድ፣ ከምኒልክ ከመጣችሁ አናስተናግድም የሚል ተግዳሮት እየገጠመን ነው” ሲሉ ከወጣት እስከ ዛውንት የእድሜ ክልል የሚገኙ የማዕከሉ ተጠቃሚ ታካሚዎች ለአዲስ አድማስ ገልጸው፤ የሚመለከተው የመንግስት አካል አስቸኳይ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ገቢ ውስጥ የሚገኘውና በአንድ ጊዜ 30 ታካሚዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ማዕከሉ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለ120 ታካሚዎች ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር የሚገልፁት የማዕከሉ መሥራች ትዕግስት አበበ፤ ለማዕከሉ ታካሚዎች፤ አገልግሎት  መስጠት ካቆመ ሦስት ሳምንታት ማስቆጠሩንና በዚህ ሳቢያ ከሞት ጋር ትንቅንቅ የገጠሙ ታካሚዎች እንዳሉ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
“ሳይንሱ የሚያዘው አንድ ኩላሊት እጥበት የጀመረ ታካሚ በሳምንት ሶስት ቀን ዲያሊሲስ ማድረግ እንዳለበት ነው ያሉት ታካሚዎቹ፤ “ይህ ማዕከል ከመከፈቱ በፊት በግል የኩላሊት እጥበት ማዕከላት አገልግሎት ለማግኘት በወር እስከ 40ሺህ ብር ለመክፈል ቤት ንብረት ከመሸጥም ባለፈ ወዳጅ ዘመድ እያስቸገርን፤  የሌለን  ደግሞ ጎዳና ወጥተን እየለመንን ነበር” ብለዋል።
ማዕከሉ ምን ችግር ገጠመው በሚል ትላንት ረፋድ ወደ ምንሊክ ሆስፒታል አቅንተን የማዕከሉ መስራች  ትውልደ ኢትዮጵያዊቷን ትዕግስት አበበን ጠይቀን  ታካሚዎቹ በነፃ በሰጡን ምላሽ፤  ላለፉት 2 ዓመታት 120 ታካሚዎች በነጻ ኩላሊታቸውን በሳምንት ሶስት ቀን  እንዲታጠቡ  በማድረግ መቆየታቸውን ይናገራሉ።  ኑሯቸውን ለረጅም ዓመታት በአትላንታ ጆርጂያ ያደረጉት የማዕከሉ መስራች ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የጤና ባለሙያ፤ በዚሁ የህክምና ዘርፍ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ለ19 ዓመታት በሜዲካል ሚሽን ትሪፕ ወደ አገራቸው እየመጡ እያገለገሉ ይመለሱ እንደነበር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ዲያስፖራው ማህበራሰብ ባለው አቅምና ሙያ ሀገሩን እንዲደግፍ ባደረጉት ጥሪ መሰረት፣ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ ይህን ማዕከል በመክፈት ወገንን ለማገልገል ሙያቸውን ይዘው እንደመጡ ይናገራሉ።
ከዚም በኋላ በክብርት ከንቲባዋ አዳነች አበቤ ትብብር ጉዳዩ ተቀላጥፎ ከሁለት ዓመት በፊት በ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማዕከሉ ደረጃውን ጠብቆ መከፈቱን 60 ያህል ሰራተኞች መቅጠሩንና አዲስ አበባ ጤና ቢሮና ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል አስፈላጊውን ድጋፍ ባለማድረጋቸው ህክምና አሰጣጡ መስተጓጎሉን የገለፁት የማዕከሉ መስራች ትዕግስት አበበ፤ ማዕከሉ በቀን እስከ 120 ታካሚዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሆኖ በድንገተኛ የሚመጡ አራትና አምስት ታካሚዎችን በሳምንት እየተቀበለ ሲያክም እንደቆየ አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ ህክምና መስጠት ስንጀምር የነበረው የታካሚዎቹ የአላቂ እቃ ዋጋ በአራት እጥፍና ከዚያ በላይ በመጨመሩ ከአቅም በላይ ሆኖብን ከ4 ወር  በፊት ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት አቁሞ እንደነበር ገልጸዋል። ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ገብቶ ረጅም ሂደት ወስደን የገዛነውን የህክምና እቃ የአውሮፕላን ተከፍሎ መምጣቱን ተናግረዋል። እንደ ማዕከሉ መስራች ገለፃ፤ ሀገራችንንና ወገናችንን ለማገልገል ካለን ጥልቅ ፍላጎት አንፃር በኩላሊት እጥበት ሥራ በጣም አስፈላጊውንና ዋናውን እቃ (አሲድ) እዚሁ አገራችን ማምረት ጀምረን፣ እንኳን ለማዕከላችን ለሌሎች ሆስፒታሎችም በጣም በቅናሽ ዋጋ ማቅረብ ጀምረናል፤ ዋናው ችግራችን ግን ወዲህ ነው ብለዋል።
“የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለን ስንመጣ ከተደላደለና ከሞቀ ኑሯችን ወጥተን ነው” የሚሉት ሃላፊዋ፣ በስምምነታችን መሰረት ከተማ መስተዳድሩ የጤና ቢሮ ሃላፊዎችንና ምንሊክ ሆስፒታል መስተዳድሮችን ይህን አድርጉልን ይሁን አሟሉልን ስንል  ከአራት ወር በፊት  በ90 ቀናት ውስጥ “ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ ውጡ” የሚል ከአንድ ትልቅ የጤና ቢሮ ሃላፊ የማይጠበቅ ምላሽ ሰጥተውናል ብለዋል።
ወ/ሮ ትዕግስት አክለውም፤ ይህን ስራ ከጀመርንበት ከአንደኛው  ቀን ጀምሮ በሁለቱ ተቋማት ሃላፊዎች እየተበደልን ወገን ለማገልገል ብንታገስም፣ አሁን ግን በደረሰብን ጫና አገልግሎት መስጠት አቁመን ለ10 ዓመት የተፈራረምነውን ውል፣ በሁለት ዓመቱ ላይ ለማቋረጥ ደብዳቤ ፅፈናል ሲሉ ለምንሊክ ሆስፒታል የፃፉትን የውል ማቋረጫ ደብዳቤ በዋቢነት አቅርበዋል።
“እኛ ወደ መንግስት ሆስፒታል ገብተን ለመስራት የፈለግነው ጉዳዩ የጋራ በመሆኑ የበለጠ መንግስት ሥራችንን ያሳልጣልናል፤ የመጣነው ሀገርን ለማገዝ ነው በሚል ነው ያሉት ሃላፊዋ፣ ነገር ግን በአንዱ ስንለው በሌላው፣ አንዱን ስንፈታ ሌላ ጉዳይ እየታሰረብን በቀን 240 ሰው ማከም ስንችል 120 ሰው ላይ ተቸክለን ቀርተናል ብለዋል።” መሥራቿ  ለአዲስ አድማስ የገጠማቸውን ተግዳሮት ሲያስረዱ።
“ከዚህ ግቢ ጓዛችሁን ጠቅላላችሁ” ውጡ ለሚባለውም ነገር ይህ ማዕከል ሲቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የቀድሞዋ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰና ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ የደከሙበትና ወገንን የሚያገለግል ማዕከል እንደመሆኑ፣ በህግና በስነስርዓት እንደገባነው ሁሉ አዲስ አበባ ጤና ቢሮና ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ያጠፋነው ያጎደልነው ካለ ገልጸውልን፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አውቀው በህግና በስርዓት ለመልቀቅ ዝግጁ ነን፣ ለሀገራችንና ለወገናችን ለመድረስ ብዙ ጥረናል፤ ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ አንችልም” ብለዋል።
መግባታቸውን ዙሪያ ያነጋገርናቸው የዳግማዊ ምንሊክ ኮምፕረኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተከተል ጥላሁን፣ ሶስቱ ወገኖች ማለትም የአብ የህክምና ማዕከል፣ ዳግማዊ ምንሊክ ኮምፕረኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በመንግስት የግል አጋርነት ወይም (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) አማካኝነት ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሰው፤ ሶስቱም አካላት በውልና በህግ የተቀመጠ ግዴታና ሀላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ተከተል የሶቱን ተዋዋይ ወገኖች ሀላፊነት ሲገልፁም፤ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የአብ የህክምና ማዕከል ለታካሚዎች የሚሰጠው ህክምና ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን መቆጣጠርና ማረጋገጥ አንዱ ሃላፊነቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአብ ሜዲካል ሴንተር ለሚሰጠው አገልግሎት የህክምና  ባለሙያዎችን ማቅረብና የአብ ለሚሰጠው አገልግሎት ለሚጠይቀው ክፍያ በውሉ መሰረት ክፍያው በተጠየቀ 3 የስራ ቀናት  ውስጥ ክፍያ መፈፀም እንዲሁም የድጋፍ ደብዳቤ መፃፍና የመሳሰሉት ዋና ዋናዎች ናቸው ብለዋል። ዶ/ር ተከተል አክለውም የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በዋናነት የአብ ሜዲካል ሴንተር የድጋፍ ደብዳቤ ሲጠይቀው ህጋዊነቱንና አስፈላጊነቱን አጣርቶ ደብዳቤ መፃፍና ማዕከሉ ከቀረጥ ነፃ እቃዎችን እንዲያስገባ ለሚመለከተው አካል የድጋፍ ደብዳቤ መፃፍ በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ሳይቆራረጥ እንዲሰጥ ማገዝ ነው ይላሉ፡፡
ማዕከሉ ምን ያህል ታካሚዎችን እያገለገለ ነበር ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ፤ እኛ የምናውቀው ለሚያገኙት አገልግሎት ክፍያ የምንፈፅምላቸው 104 ናቸው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ማዕከሉ 120 ናቸው ቢልም 16ቱን ግን አናውቅም ብለዋል፡፡ የአብ ሜዲካል ሴንተር በነፃ ህክምና እሰጣለሁ ቢልም ለታካሚዎች የአገልግሎት ክፍያ ለማዕከሉ የሚከፍለውና ለህክምና ባለሙያዎች ደሞዝ የሚከፍለው ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ነው ብለዋል፡፡ ይህም በውሉ ላይ የተቀመጠና በማስረጃ የሚረጋገጥ ነው ይላሉ፡፡ ከአራት ወር በፊት በግብአት እጥረት ለምን ህክምና ተቆራረጠ የአብ የህክምና ማከል ለጠየቀው የዋጋ ማሻሻያ ለምን ምላሽ አልተሰጠም በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ዶ/ር ተከተል ሲመልሱም፤ ለኩላሊት ስንፈት ታካሚዎች ለአንድ ጊዜ አገልግሎት 800 ብር፣ ዘላቂ የኩላሊት ስንፈት ላጋጠማቸው ደግሞ ለአንድ ጊዜ አገልግሎ 1080 (አንድ ሺህ ሰማኒያ ብር) ለማዕከሉ እንከፍል ነበር ያሉት ዶ/ር ተከተል ሆኖም ማዕከሉ የዋጋ ማሻሻያ  ለከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ተመርቶ ከዚያም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አይቶት ሌሎች የዲያሊስስ አገልግሎ የሚሰጡት እንደነ ጳውሎስ ሆስፒታል ያሉ ማዕከላት ያለው ዋጋ ታይቶና የዋጋ ማሻሻያ ጥናት ተደርጎ የሚፀድቅ እንጂ ማዕከሉ ዛሬ ማሻሻያ አድርጉ ስላለ በእኛ ስልጣን የምናሻሽለው አይደለም ካሉ በኋላ፤ “ሆኖም ይህንን ማሻሻያ አስጠንተን እናሻሽላለን እስከዛ ስራው ይቀጥል የሚል ደብዳቤ ብንፅፍም ማዕከሉ ደብዳቤያችንን ውድቅ አድርጎት ከሶስት ሳምንት በፊ የህክምና አገልግሎቱ ተቋርጧል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የህክምና አገልግሎቱ በዋናነት የተቋረጠውም የአብ የህክምና ማዕከል በውሉ መሰረት ስራ ሲጀምር ቢያንስ ከ3-6 ወር የሚበቃ የህክምና ግብአት ስቶክ እንዲይዝ ውል የገባ ቢሆንም አንድም ቀን መጠባበቂያ ስቶክ ይዞ ባለማወቁ ነው ያሉት ዶ/ር ተከተል ይህን ሁሉ ታግሰን ብንቆም ማዕከሉ ግን የግድ ውል ይቋረጥ በማለት አሻፈረኝ ብሏል ብለዋል፡፡
እስካሁን ከውላችን ያጎደልነው የለም ያት ዶ/ር ተከተል፤ የውሃ ቧንቧ ተሰበረ ራውተር ተሰረቀና ሌሎች ቅሬታዎች ማዕከሉ ቢያነሳም የምን ቀበለው የራውተሩን መሰረቅ ነው ያሉ ሲሆን የሆስፒሉ ጥበቃ አውትሶርስ ተደርጎ በጥበቃ ኤጀንሲ የሚሰራ ሲሆን ከዚህም ቀደም የሆስፒታሉ ሌሎች እቃዎች እየጠፉ የጥበቃ ኤጀንሲው እየገዛ እንዲተካ እንደሚደረግና የማዕከሉንም ራውተር የጥበቃ ኤጀንሲው ገዝቶ ለመተካት በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።  ከዚህ ቀደምም ስራው እንዳይቋረጥና አገልግሎቱ እንዲቀጥል ማዕከሉ ከውጪ ገዝቶ ያመጣውን የህክምና ግብአት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከውሉ ውጪ 3 ሚ ብር የአውሮፕላን ከፍሎ ግብአቱ መግባቱንና ህክምና እንዲቀጥል ማድረጉን ጤና ቢሮው ከገባው ውል አንዱንም አላማጉደሉን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 858 times