Monday, 19 February 2024 08:04

“ታላቅየው ሲመቸው፣ ታናሽየው ሳይድህ በእግሩ ይሄዳል”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ፖርቹጋል ገናና በነበረችበት ወቅት የነበሩ የአንድ ንጉሥ አፈ-ታሪክ አለ፡፡
ለዘመናት በወራሪነት የኖሩ ንጉሥ፣ በምርኮ የያዙዋቸውን አገሮች አቀናለሁ እያሉ ብዙ ብር ያፈሱባቸዋል፡፡ ከዚያም በዓመት አንድ ጊዜ ህዝቡን ሰብስበው፤
“ዕድሜ ለእኔ በሉ ነፃ አወጣኋችሁ” ይላሉ፡፡ህዝቡ በጭብጨባ ስለንግግራቸውና ስለቸርነታቸው ያለውን አድናቆት ይገልፃል፡፡
ቀጥለውም ንጉሡ፤ “ዛሬ በገዛ ደግነቴ፤ ለሀገራችሁ ዕድገት፣ ለህዝባችሁ ደህንነት ስል አንድ ተጨማሪ በጎ-አድራጎት እፈፅማለሁ፡፡ ይኸውም፤ ነፃ የወጣችሁበትን ቀን በዓመት አንድ ቀን ታከብሩ ዘንድ ፈቅጄላችኋለሁ፡፡”
ህዝቡ በጭብጨባ አድናቆቱን ይገልፃል፡፡፡
ከዚያ እንደተለመደው፤
“ጥያቄ ካላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ” ይላሉ፡፡
ከሰው መካከል በተራ በተራ እየተነሱ ተወካዮች ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡ የህፃናቱ ተወካይ፤ “ንጉሥ ሆይ! መዋዕለ - ህፃናት ይሰራላችኋል ከተባልን ብዙ ዓመት አለፈን፡፡ በጦርነቱ እናት አባታቸውን ያጡ አያሌ ህፃናት የሚኖሩበት አላገኙም፡፡”
ቀጥሎ የወጣቱ ተወካይ ይነሳል፡፡
“ንጉሥ ሆይ! ከሁሉም በጦርነቱ የተጎዳው ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ የሚያነብበት ቤተ -መፃሕፍት፣ የሚዝናናበት ኳስ ሜዳ፣ የሚወያይበት አዳራሽ የለውም፡፡ ስለዚህ የእርሶን እርዳታና ረድኤት እንሻለን” ንጉሥ- “መልካም፡፡ የእናንተም በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በቀጣይ የተያዘ ስለሆነ ይፈፀማል” አሉ፡፡
በተከታታይ የሴቶች ተወካይ፣ የሽማግሌ ተወካይ፣ የሠራተኛ ተወካይ፣ የተማሪ ተወካይ ወዘተ…. ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡
ንጉሡም “በቀጣይ ተይዟል” ሲሉ መለሱ፡፡
በመጨረሻም የምርኮኞቹ ወታደሮች ተወካይ፤
“ንጉሥ ሆይ! ከሁሉም የተጎዳን እኛ ወታደሮች ነን፡፡ ይኸው ያለ ጦርነት ተቀምጠን ስንትና ስንት ዓመት  ተሰቃየን፡፡ ወይ ከእንግዲህ ጦርነት የለምና ተበተኑ በሉን፡፡ አለበለዚያ ደግሞ በአስቸኳይ ጦርነት ይፈጠርልንና በቶሎ ተግባር ላይ እንሰማራ፡፡ ንጉሥ ሆይ! ቃታ እንስብበታለን ያልነው ጣታችን ለስልሶ የወርቅ ቀለበት ማሰሪያ ሆነ፡፡ ለሬዲዮ መገናኛ የተሠጠን መሳሪያ የሙዚቃ ማዳመጫ ሆኖ ሰነበተ፡፡ ስንት ዳገት ቁልቁለት ይወጣል ይወርዳል፤ የት ይደርሳል የተባለው ሰውነታችን በተጠረገ መንገድ መምነሽነሽ፤ በሚሞቅ አልጋ ላይ መተኛት የሁልጊዜ ፀባዩ ሆነ፡፡ ምቾት በዛ ንጉሥ ሆይ? ያ በሥልጠና ላይ የተነገረን ጦርነት የታለ?  እንደ-ምጽዓት ቀን ራቀብን’ኮ፡፡ ኧረ አንድ መላ ይፈጠርልን ንጉስ ሆይ!” ሲል ተማጠነ፡፡
ንጉሡም፤ “እኔም ይህን ችግራችሁን በጣም አስቤበታለሁ፡፡ ሥቃያችሁ ያሰቃየኛል፡፡ ህመማችሁ ያመኛል፡፡ ስለዚህም የናንተ ጉዳይ ከማንም በፊት በቀዳሚነት በቀጣይ ተይዟል” አሉ፡፡
እኒያ ንጉሥ ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ እለተ - ሞታቸው ድረስ መጠሪያ ስማቸው “ንጉሥ በቀጣይ” የሚል ሆነ፡፡
አገራቸውም፤ ከዓመት ዓመት ጦርነት በቀጣይ እያስተናገደች፤ አያሌ ቅኝ-ግዛቶቿን እስክታጣ ድረስ ስትዋጋ ኖረች፡፡
***
ህዝቦችን በተስፋ ብቻ በማሰር ለመሰንበት  የሚሞክር እንደ ፖርቹጋሉ ንጉሥ ያለ መሪ፤ ህዝቦቹ የለበጣ የሚገዙለት፤ በሀሳዊ-ጭብጨባ እንዲገበዝ የሚያደርጉት ነው፡፡ ከቶውንም ምርኮኞቹን ነፃ እንዳወጣቸው ማሰቡና፤ እንዲያስቡም ለማስገደድ መሞከሩ፤ ጊዜያዊ የአሸናፊነት ስሜትን እንጂ ዘላቂ ሥርዓትን ለመገንባት የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡
ህዝብ የተታለለ ሲመስል የእድር አለቃውም፣ የቀበሌ ሹሙም፣ የቢሮ ኃላፊውም፣ የቢሮክራሲ አባ-ወራውም፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪውም…. አዕምሮውን ሰብሰብ አድርጎ፣ ማናቸውንም ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሁለት ሶስቴ አስቦ፤ ከምወስደው እርምጃ ጠቀሜታና ህዝቡ ከሚያገኘው ፋይዳ የትኛው ሚዛን ይደፋል? ብሎ ሁኔታዎችን ማውጠንጠን እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የገባሁት የተስፋ ቃል ከታጠፈ ካፌ የሚወጣው ሁሉ ወደ አለመታመን ማምራቱ አይቀርም ብሎ የማያስብ የበላይ፤ የኮቴውን ድምፅ ያህል እንኳ የሚታወስ ፍሬ የሌለው ነው፡፡
የኒውዚላንድ ህዝቦች ሲተርቱ “አሮጌ ቃል - ኪዳን ወደ ኋላ ይቀራል” እንደሚሉት፤ በአዲስ ቃል-ኪዳን ወይም እንደ ፖርቹጋሉ የአፈ -ታሪክ ንጉስ በቀጣይ ቃል-ኪዳን ይተካል ብንል፤ ጊዜን መሸጋገራችን እንጂ ረብ ያለው ድርጊት አልፈፀምንም፡፡
ጆርጅ ፓድሞር የተባለው ትሬኒዳዳዊ የምርጫ ተወዳዳሪ “አፍሪካውያን በቃል--ኪዳን በመተማመን ረዥም ጊዜ ኖረዋል፡፡ አሁን ማየት የሚፈልጉት ጥቂት ተጨባጭ ተግባራትን ብቻ ነው፡፡ አንገታቸው ላይ የሎሌነት ሰንሰለት አጥልቀውም ስለ “ዲሞክራሲ” እና ስለ “ነፃነት” የሚሰበኩ ሃይማኖት አከል ውዳሴዎችን ማዳመጥ ደክሟቸዋል፤ ታክቷቸዋል” ያለው በከንቱ አይደለም፡፡ የብዙ ፖለቲካዊ ቀውሶች መንስዔዎች የታጠፉ ቃሎች ናቸው፡፡
ሌት ተቀን አውጥተን አውርደን፣ አዋቂ ጠይቀን፤ የውጪ አጥኚ አሰማርተን ይሄን ችግር በቅርቡ እንፈታዋለን ብለን ስናበቃ፣ መልሰን በቅርቡ ያልነውን ላልተወሰነ ጊዜ አሸጋግረነዋል ካልን፣ ከቃል ማጠፍ የማይተናነስ ተግባር ፈፅመናልና ችግሩን አዘገየነው እንጂ የመፍታት ሙከራ አላደረግንም፡፡ የሚዋዥቀውን ወይም ትርጉም ባለው መልኩ ለውጥ ያልታየበትን ኢኮኖሚ፣ አድጓል ተመንድጓል፣ነገ ደግሞ የእጥፍ-እጥፍ ያድጋል ብለን ቃል-ብንገባ፣ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ሰልፍ አስመርሮኛል የሚለውን ሰው በቅጡ ማሳመን የሚቻል አይሆንም፡፡ ነባራዊውም ሆነ ህሊናዊው ሁኔታ የማያግዙት ሙግት፤ አፍአዊ እንጂ ልባዊ ብሎም ተግባራዊ ለመሆን ይሳነዋል፡፡
የላይኛው እንዳፈተተው ሲናገር የታችኛው ለማስተጋባት የበለጠ መጮሁ አግባብ ያለው ሥርዓት በሚመስልበት፣ እንደ ውሃ በመሬት ስበት ኃይል ከላይ ወደታች እንደሚወርድ የዕዝ-ሠንሠለት የተዋቀረ በሚመስል አካሄድ ውስጥ፤ “አሳታፊ ዲሞክራሲ”፣ “የውድድር ኢኮኖሚ”፣ “ልማት-ተኮር ራዕይ”፣ “ፍትሕ-ርትዕ የሰፈነበት ማህበራዊ መርሕ” እያልን ብናንቆለጳጵሰው፤ ለስልት እንጂ ለስሌት አያግዘንም፡፡  ዞሮ ዞሮ  ከላይ ወደታች የሚወርድ አንድ አሸንዳ ውስጥ ያለ ፍሰት የመሰለ ፖለቲካዊ ሥርዓት፤ “ታላቅየው ሲመቸው፣ ታናሽየው ሳይድህ በእግሩ ይሄዳል” እንደሚባለው ያለ ነው፡፡

Read 1049 times