Monday, 19 February 2024 08:08

የኢትዮጵያ የአበባ እርሻና የቫላንታይን ቀን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

• የአበባ ዘርፉ ከ50 ሺ በላይ የሥራ ዕድል ፈጥሯል
• ኢትዮጵያ የዓለም 4ኛዋ ትልቋ የአበባ አምራች ናት
• የፍቅረኛሞች ቀን ለአበባ አምራቾች የውጥረት ጊዜ ነው


ባለፈው ረቡዕ ፌብሯሪ 14 ቀን 2024 ዓ.ም በመላው ዓለም የቅዱስ ቫላንታይን ቀን (የፍቅረኛሞች ቀን) ተከብሮ ውሏል- በፅጌረዳ አበባና በሌሎች የፍቅር መግለጫ ስጦታዎች ደምቆና ፈክቶ። በአበባ ምርትና ሽያጭ ላይ ላሉ ወገኖች ግን ከበዓሉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አንስቶ ያሉ ጊዜያትን ጨምሮ በውጥረት የተሞላ ነው- የአበባ ምርቶች በብዛት ለገበያ የሚቀርቡበት ወቅት በመሆኑ፡፡ በአዲስ አበባ ዳርቻ ላይ ለሚገኘው የጋሊካ አበባ ኩባንያም ከዚህ የተለየ አይደለም - ወቅቱ፡፡ ይህን ባለፈው ረቡዕ  በሰፊው የጋሊካ የአበባ እርሻ ግቢ ውስጥ በአካል ተገኝቶ የቃኘው የፈረንሳዩ የቴሌቪዥን ጣቢያ ፍራንስ 24 ነው፡፡ የጣቢያው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ በዕለቱ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ 300 የሚሆኑ የኩባንያው ሠራተኞች በእርሻው ሥፍራ ላይ ደርሰው ነበር፡፡  
በየዓመቱ የኩባንያው 8 ሄክታር የቤት ውስጥ ማልሚያ (ግሪንሃውስ)፣ በመላው ዓለም የሚላኩ 5 ሚሊዮን ገደማ የፅጌረዳ አበቦችን እንደሚያመርት ዘገባው ይጠቁማል፡፡
የቅዱስ ቫላንታይን ቀን መቃረቢያ ጊዜያት ግን ከዓመቱ  ሁሉ እጅጉን ሥራ የሚበዛበት ወቅት ነው። ዛሬ ብቻ (ባለፈው ረቡዕ ማለት ነው) ከ20ሺ በላይ አበቦች ይሰበሰባሉ- ብሏል ዘገባው፡፡
“እዚህ ኡደቱ 80 ቀናት ገደማ ነው” ሲል ያስረዳው  የእርሻው ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ወንድሙ፤ “ፅጌረዳዎቹን የዛሬ 80 ቀን ከተከልካቸው ዛሬ ደርሰው ታገኛቸዋለህ። እናም በተለይ አንዳንዶቹ የፅጌረዳ ዓይነቶች እንዲደርሱ ለማዘጋጀት እንሞክራለን፤ በዋናነት ቀያይ ጽጌረዳዎቹን፡፡ እኛ ሁልጊዜም ከሚፈለገው ያነሰ ነው የምናመርተው።” ብለዋል።
ባለፉት 12 ዓመታት በኢትዮጵያ የአበባ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቆመው ፍራንስ 24፤ እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከምንም ተነስታ 212 ሚ.ዶላር የሚገመት 2 ቢሊዮን ቶን አበባ ለውጭ ገበያ መላኳን ያስታውሳል።
ይኼም አሃዝ ኢትዮጵያን የዓለም አራተኛዋ ትልቋ የአበባ አምራች ሲያደርጋት፤ በአፍሪካ ደግሞ ከኬንያ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል- ይላል ዘገባው።
50ሺ የሥራ ዕድሎች
ምንም እንኳ አብዛኞቹ የአበባ ኩባንያዎች በውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ የአበባ ዘርፍ ከ50ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ከ70 በመቶ የሚልቁት ሠራተኞች ደግሞ ሴቶች ናቸው።
“የምኖረው እዚሁ ጎረቤት ነው፤ ነገር ግን የራሴ መሬት የለኝም። እዚህ  ለመሥራትና በቆጠብኩት ገንዘብ የራሴን ንግድ ለመጀመር ነው ያቀድኩት።” ትላለች፤ በጋሊካ እርሻ ላይ ከሚሰሩት አንዷ የሆነችው ብርቱካን ሚልኬሳ፤ ለፍራንስ 24 ቴሌቪዥን።
“እዚህ በመሥራታችን ትልቅ ጥቅም አለን። ለምሳሌ፡- በየቀኑ ምሳችንን በነጻ እንመገባለን።” ስትልም አክላለች-ብርቱካን።
የኢትዮጵያ አበባ ገበሬዎች ጥብቅ የስነ-ምግባር መመሪያ የሚከተሉ ሲሆን፤ እጅግ ውድድር በበዛበት ገበያ ውስጥ እንደሚሰሩም ይገነዘባሉ።
በጋሊካ እያንዳንዱ ፅጌረዳ በጥንቃቄ ይመረጣል፤ ይደረደራል፤ ከዚያም  ይታሸጋል።
“ወደ መዳረሻቸው ከመላካቸው በፊት ፅጌረዳዎቹ ይታሸጋሉ፤ ውሃ ይጠጣሉ፤ ከዚያም በቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ለአንድ ሌሊት ይቀመጣሉ።” ሲል የጋሊካ ባለቤት ስቲፌን ሞቲየር አስረድቷል፡፡
እርሻው ከ60 በላይ የፅጌረዳ ዝርያዎችን ያመርታል። አዲስ ዲቃላ ቀለማት ሲፈጠሩ ልዩ ስሞች ይወጣላቸዋል።
“የተለያዩ አገራት የተለያዩ ዓይነት ፅጌረዳዎችን ይፈልጋሉ። ይኄኛው ምናልባት ወደ ጃፓን ወይም ደቡብ አፍሪካ ይላካል” አለ ስቴፋን ወደ ነጭ ፅጌረዳ እየጠቆመ፤ “የተቀሩት በተለይም ቀይ ፅጌረዳዎቹ ደግሞ  ወደ ፈረንሳይ ይላካሉ።”
በመጨረሻም አበቦቹን ለመውሰድ ትልቅ መኪና ይመጣል። ከዚያም አበቦቹ በአውሮፕላን ተጭነው በቀጥታ በዓለም ዙሪያ ወደሚገኙ የአበባ መሸጫ ሱቆች በሰዓታቸው ይደርሳሉ - ለፍቅረኛሞች ቀን!!

Read 472 times