Monday, 19 February 2024 08:21

“ባይተዋሩ ልዑል”ን በወፍ በረር

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(2 votes)

በአንድ ወቅት በነበረ ግጭት “ዜጎቻችን ስለሞቱብን ቦታው ለኛ ይገባል” ብለው እንግሊዞች ፍርድ ሊጠይቁ ወደ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መጡ፡፡ ምኒልክም የሚፈርዱት ለጊዜው ቢቸግራቸው ወደ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ዳኝነት ያገኙ ዘንድ መሯቸው፡፡ አቤቱታ አቅራቢ እንግሊዞችም “ዜጎቻችን በሥፍራው ስለተገደሉብን አጽማቸው ያረፈበት ቦታ ይሠጠን ለኛ ይገባል” ሲሉ አመለከቱ፡፡ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስም “ልክ ብላችኋል ቦታው ለናንተ ይገባል፡፡ እንሰጣችኋለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን የቀድሞ ንጉሠነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ አጽም ያረፈበትን ዊንድሶርን ለኛ ስጡን” አሏቸው፡፡ እንግሊዞችም በዚያ አፍረውና ተደናግጠው ጥያቄአቸውን አቆሙ ይባላል፡፡ ግዛት ቆርሶ ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራም ከሸፈ፡፡ በነገራችን ላይ የዛሬ15 ዓመት ግድም የኢትዮጵያ መንግሥት የልዑል ዓለማየሁ አጽም ይመለስልኝ ብሎ እንግሊዝን ጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም የእንግሊዝ መንግሥት “የሌሎች ብዙዎችን ማረፊያ ሳያናጉ የልዑሉን አጽም ማንቀሳቀስ አይቻልም” ብሎ እ.አ.አ በ2023 የአንሰጥም ምላሽ ሰጥቷል-የፀጉሩ ቁንዳላ እና ሌሎች ጥቂት ቅርሳቅርስ ለኢትዮጵያ ቢመለሱም፡፡
ከዚህ የልዑሉ ታሪክ ብዙም ሳንርቅ በታሪካዊ ልቦለድ የብርሃኑ ዘርይሁንን “የታንጉት ምስጢር”ን ታስታሳላችሁ፡፡ ይህንን መጽሐፍ ካነበብኩት በጣም ረዥም ጊዜ ቢሆነኝም በተለይም ፊታውራሪ ገብርዬን፣ ራሳቸው አፄ ቴዎድሮስን እነ ጋረድን አልረሳም፡፡
ከ “ታንጉት ምስጢር” በፊትም ሆነ በኋላ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች እና የታሪክ ድርሳናት፣ በአፄ ቴዎድሮስ፣ በንግሥናቸው፣ በግርማዊነታቸው ጊዜ ስለነበረች ኢትዮጵያ፣ ስለ ቤተሰቦቻቸው ተጽፏል፡፡
ባለፈው ጥር ወር 2016ዓ.ም አጋማሽ ደግሞ ስለ ልጃቸው ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አንድ የሥነጽሑፍ ሥራ በአማርኛ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡  ብሪታንያዊቷ ጸሐፊ ኤልዛቤት ሊያርድ “The Prince Who Walked With Lions”ን መጽሐፍ ወደ አማርኛ “ባይተዋሩ ልዑል” ሲል የመለሰው ጋዜጠኛ ዮሴፍ ዳርዮስ ነው፡፡ ባለ 147 ገፅ ( ያልተጻፈባቸው 2 ገፆችን ሳይጨምር) መጽሐፍ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን ሰብእና በፈጠራ ጽሑፍ ጭምር ያሳየናል፡፡ በወሳኝ ፎቶግራፎችም የታገዘ ነው፡፡ በቀዳሚ ገፆች እንደተጠቀሰው በልጆች መጽሐፍነት ቢዘጋጅም ከዚያም ዕድሜ በላይ ያሉ ሊያነቡ የሚችሉት ነው፡፡ በውስጡ የተጠቀሱትም ሰዎች በገሃዱ ዓለም የነበሩ ናቸው፡፡ ሆኖም የራግቢ ትምህርት ቤት የልዑሉ ጓደኞች የፈጠራ ውጤቶች ናቸው እንጂ ግዘፍ ነስተው በአካል የነበሩ አይደሉም፡፡
ዮሴፍ መጽሐፉን ለመተርጎም ምክንያት የሆነው የእናቱ  ልዑል ዓለማየሁን  በሀገረ እንግሊዝ መንከራተት አስመልክቶ አሳዝኗቸው ለልጃቸው ለዮሴፍ መናገራቸው ነው፡፡  እና የዛሬ 12 ዓመት ግድም እ.ኤ.አ በ2012 የታተመውን የኤልዛቤት ሊያርድ The Prince Who Walked With Lions”ን መጽሐፍን ወደ አማርኛ እንዲመልስ ሆኗል፡፡
መጽሐፉ የሚጀምረው የልዑል አለማየሁ ሕይወትን አስመልክቶ ተማጽኖ በማቅረብ ነው፡፡ “ልዑል ዓለማየሁ በልጅነት ከሀገር ወጥቶ ከመሰደዱ ውጪ በዚያ የልጅነት ዘመን ስላሳፈው ውጣ ውረድ በበቂው ልክም ባይሆን በምናብ እንዲህ ቢሆንስ ለማለት ያህል በጥቂቱ ያሳይ እንደሁ በሚል የልጅ ድፍረት መነሳቴን አውቃችሁ ስታነቡ ያልጣማችሁ እንደሁ አርሙኝ…” ይላል ተርጓሚው፡፡ ትረካውም የሚጀምረው ልዑሉ እንግሊዝ ባለ ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ ተራኪው ልዑል ዓለማየሁ ራሱ “እኔ” እያለ በሚተርክበት አንደኛ መደብ የትረካ አንጻር ሲሆን አተራረኩም በአብዛኛው በምልሰት (flashback) ነው፡፡ ምልልስ (dialogue) እና የመቼት ገለጻም ሌሎችም ስልቶች ተቀናጅተውበታል በአማርኛው “ባይተዋሩ ልዑል”፡፡ዮሴፍ የእንግሊዝኛ መጽሐፉን እንዴት ተረጎመው የሚል ንጽጽራዊ ትንተና (comparative analysis) ማቅረብ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ የጽሑፉ ዓላማ “ባይተዋሩ ልዑል”ን በአጭሩ መቃኘት፣ልዑል ዓለማየሁን በስሱ  በምናብ መጎብኘት ነው፡፡
በዚህ መጽሐፍ አፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን ልዑሉን ክልባቸው እንደሚወዱ በምናብ ተቀምጧል፡፡ በነገሥታት ወግ ያደገውም አስተማሪ ተቀጥሮለት የተማረውም  ቤተመንግሥት ውስጥ ነበር፡፡ እናቱ እቴጌ ጥሩወርቅም ሆኑ ሞግዚቱ አበበች በጣም ይንከባከቡት ነበር፡፡ እናቱ ልዑል አያለቅስም ይሉት እንደነበር ሞግዚቷ አባቱ አፄ ቴዎድሮስ ሲጠሩት አለባበሱን አስተካክላ እስከምታቀርበው ይጣደፍ እንደነበርም ልዑሉ ያስታውሳል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ እንግሊዞችን በማሰራቸው ከእንግሊዝ ጋር ስለተገባው ,እሰጥ አገባ፣ እነሱን ለማስፈታት ጀነራል ናፒየር ወደ ኢትዮጵያ ስለመምጣታቸውና አፄ ቴዎድሮስ መሞታቸውን እና አስከሬናቸውን በሌላ ክፍል መደረጉን ማየቱን እንደሚያስታውስ፣ በምርኮኝነት ስደት ላይ የነበሩት እናቱ ከመሞታቸው በፊት ለሻምበል ስፒዲ (ባሻ ፈለቀ) አደራ እንዳሉት፣ ልዑሉ እንደ አባት ስለሚቆጥረው ሻምበል ስፒዲ (ባሻ ፈለቀ) ከሌሎች ይልቅ ከሱ ጋር ሲሆን አንደሚደሰትም ያወሳል፡፡ ስለ እንግሊዝ ስደቱ እና በአካባቢው ጥቁር እሱ ብቻ ስለነበረ ባይተዋርነት እንደሚሰማው፣ ልዑል ዓለማየሁ  ንግሥት ቪክቶርያን በኢትዮጵያውያት ንግሥታት ልክ አይቶ የተንቆጠቆጠ ጌጣጌጥ እና ልብስ ሲጠብቅ ንግሥቲቱን በተራ ልብስ ማየቱ ከጠበቀው ውጪ እንደሆነበትም ተተርኳል፡፡ ምን እንደገጠመው መጽሐፉን ሲያነቡ የሚያገኙት ነው፡፡
ንግሥቲቱ ግን አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉለት ወደ ትምህርት ቤት መግባቱ እና ከዚያ በኋላ ምን እንደገጠመውም በመጽሐፉ ተጠቅሷል፡፡ በዚህች ምድር ለ19 ዓመታት (18 የሚሉም አሉ) ብቻ ኖሮ ስላለፈው ልዑል ገና በርካታ የምርምር ጽሑፍ እና የፈጠራ ድርሰቶች ይጻፋሉ፡፡ አሁን ያነሳው ግን ስለሱ ሰሞኑን ለኅትመት የበቃውን የዮሴፍ ዳርዮስ ሞዲ “ባይተዋሩ ልዑል” መጽሐፍ በመጠኑ ነው፡፡ ስለ መጽሐፉ ከተነሳ ስለ ኅትመቱ ጥቂት ማለት የግድ ይላል፡፡
ኅትመቱ
ተርጓሚው ማሳተሚያ አንዳችም ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ያለውን አጠራቅሞ ለማሳተም ቢያስብም ከዐቅም በላይ  ሆነ፡፡  በነጻ አባዝቶ ለሚያውቃቸው “አንብቡ ሌሎችንም አስነብቡ” ብሎ ሰጠ፡፡ ረቂቁ የደረሳቸው ጋዜጠኞቹ እነ ሁሴን ከድር፣ ስመኝ ግዛው እና ዙቤይዳ አወል እንዲሁም ሌላው ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን በነፃማ አይሰራጭም ብለው የሚታተምበትን ዘዴ አውጠነጠኑ፡፡  “የቴምር ቡድን” በመባል እየታወቁ የመጡት እኒሁ ጋዜጠኞች ካሁን ቀደምም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በተለይ በፌስቡክ ሰዎች አስተባብረው መጽሐፍ በማሳተም ይታወቃሉ፡፡ አሁንም ገና መጽሐፉ ሳይታተም አንባቢያን መጽሐፉን አንዲገዙ አደረጉ፡፡ ከነዚህ ጋዜጠኞች በተለይ የወሰንሰገድ ገብረኪዳን ሚና የጎላ እንደነበር ተርጓሚው ዮሴፍ  “በተለይ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ወሰንሠገድ ገብረኪዳን ይህ መጽሐፍ አንዲታተም እየተቆጣ ጭምር ብዙ መንገድ አምጥቶኛል፡፡ ለሥሙ እርማት ይባላል እንጂ በድጋሜ የመጻፍ ያህል አርትዖቱን የሠራውም እርሱው ራሱ ነው፡፡” ሲል ገልጾታል፡፡እናንተም ሌሎች አንባቢዎች ታሪክ ከፈጠራ የተሰናሰሉበትን “ባይተዋሩ ልዑል” ን አንብባችሁ አስተያየታችሁን ለሌሎች አንባቢዎችና ለተርጓሚው እንዲሁም ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደምትሰጡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 409 times