Tuesday, 20 February 2024 10:48

“የአፍሪካ ወንድማማችነት”፣ ከብሔረሰብ ፖለቲካ ጋር ምን አገናኘው?

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

አውሮፓዊና አፍሪካዊ በሚሉ ፍረጃዎች የጠላትና የወዳጅ ጎራ እየፈጠርን እናወራለን። “አፍሪካዊያንን ያስማማል” ብለን እናስባለን።
የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላስ? “ከሰሀራ በላይና ከሰሀራ በታች”፣ “ጥቁር አፍሪካዊና ዐረብ አፍሪካዊ”፣ “እንግሊዝኛ ተናጋሪና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ” እያልን ተቀናቃኝ ጎራ እንፈጥራለን።
ከዚያስ? ጎረቤት ከጎረቤት ጋር ይሆናል ጸቡ። “እነዚያ አበሾች፣ በውኃ ጥም ሊጨርሱን ነው” እያለ ግብፃውያንን የሚያነሳሳ ሁከተኛና ዐመፀኛ አይጠፋም። አለ እንጂ። ግብፃዊያንን ያስማማል ብሎ ያስባል። “አነዚያ ግብፆች፣ ዘላለም ኢትዮጵያ ላይ ተንኮል የሚሸርቡ ሤረኞች!›” እያለ የሚሰብክም ይኖራል - ኢትዮጵያውያንን የሚያስማማ እየመሰለው።
ችግሩ ግን፣ በጎረቤት ላይ ጭፍን ጥላቻና የጅምላ ፍረጃ በማንኛውም ሰበብ ከተለመደ በኋላ፣ በአገር ውስጥ በዘርና በሃይማኖት እያቧደኑ ማጋጨት ለሚፈልጉ መጥፎ ሰዎች አመቺ ጥርጊያ መንገድ ይከፍትላቸዋል።


የባሕር በርና የአባይ ወንዝ፣ የወደብና የሕዳሴ ግድብ ጉዳዮችን እያነሳን በቁጭት ስንነጋገር ከርመናል። አንዳንዴም የኢትዮጵያውያን ቁጭት እንደ ቁጣ እየተቆጠረ፣ “የግጭትና የጦርነት ሰበብ” እንዳይሆን ስጋት ያደረባቸው አልጠፉም። በዙሪያችን በሚገኙ አገራትና በጎረቤቶቻችን ላይ ቂም ይዘን የምናወራ የሚመስላቸውም ይኖሩ ይሆናል። ሰሞኑን ደግሞ፣ ስለ አፍሪካ ሕብረት ስብሰባ እየተነጋገርን ስለ ወንድማማችነት እናወራለን።
በእርግጥ፣ ወንድማማችነት የሚለው ቃል ነፍስ የሚዘራው፣ ጠላት ስናበጅለት ነው። የነጮች ወረራ፣ የቅኝ ግዛት ሤራ፣ የአውሮፓውያን እብሪተኛና ዘረኛ የበላይነት ስሜት” እያልን በየጣልቃው ስንጨምርበት፣ የአፍሪካዊያን የወንድማማችነት ፍቅር የሚጨምር፣ ሙቀት አግኝቶ የሚግል ይመስለናል። ለዚያውም የአውሮፓ ባለሥልጣናትን በታዛቢነት ወደ ስብሰባ እየጋበዝን ነው፣ ያንን ሁሉ የምንራገመው፣ የምንደነፋው።
በእርግጥ፣ የሆነ ዘመን ላይ የተከናወኑ የታሪክ ክስተቶችንና ሂደቶችን ማስታወስ፣ ካስፈለገም መናገር ችግር የለውም። ነገር ግን፣ ሁሉም “ነጭ”፣ የያኔውም የዛሬውም አውሮፓዊ፣ የቅኝ ግዛት ሤረኛ አድርገን ባንናገር ጥሩ ነው። ያኔ ከ80 ዓመት በፊት፣ የቅኝ ግዛት ፖለቲካን፣ የባርነትና የዘረኝነት በሽታን እየተቃወሙ የነጻነት አስተሳሰብ እንዲስፋፋ ሲተጉ የነበሩ አውሮፓውያን ጥቂት እንዳልሆኑ ማስታወስ ጥሩ ነው። የአድዋውን ድል በማድነቅ የዘገቡና የጻፉ የአውሮፓ ጋዜጦችንም ብናስታውስ አይከፋም።
በዚያ ላይ ደግሞ፣ እዚሁ አፍሪካ እርስ በርስ በጦርነት የመጠፋፋት፣ በጭካኔ የመጨፋጨፍ አስቀያሚ ክስተቶችንም መዘንጋት የለብንም። ክፉና መጥፎ የመሆን ጉዳይ፣ ነጭ ወይም ጥቁር የመሆን ጉዳይ፣ አውሮፓዊ ወይም አፍሪካዊ የመሆን ጉዳይ እንዳልሆነ ካላወቅን፣ ጉዳቱ ለራሳችን ነው።
በጅምላ፣ አውሮፓዊና አፍሪካዊ በሚሉ ፍረጃዎች አማካኝነት፣… የጠላትና የወዳጅ ጎራ ለመፍጠር የምንሞክር ከሆነ፣ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ፣ “ከሰሀራ በላይና ከሰሀራ በታች”፣ “ጥቁር አፍሪካዊና ዐረብ አፍሪካዊ”፣ “እንግሊዝኛ ተናጋሪና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ” እያልን መጠፋፋታችን አይቀርም። ከዚያም፣ ጎረቤት ከጎረቤት ጋር ይሆናል ጸቡ።
በዚሁ አያበቃም። በጭፍን መፈረጅ የለመደ አንደበት፣ ሁልጊዜ ስለ ጎረቤት አገራት ብቻ ሊያወራ አይችልም። እዚያው አገር ውስጥ፣ በሰፈርና በመንደር፣ በብሔረሰብና በሃይማኖት ሰዎችን እያቧደነ፣ የጅምላ ጥላቻዎችን መስበኩ አይቀርም። እንደማይቀርም ከዓመት ዓመት ለዘመናት አይተነዋል። በየዕለቱ ቀንና ሌሊትም እያየነው ነው።
ከጎረቤት አገራት ጋር በሰላም ለመኖር ከፈለግክ፣ የአገር ውስጥ ሰላም ይኑርህ ይባላል።
በሌላ በኩልም ግን፣ የአገር ውስጥ ሰላም እንዲኖርህ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላም ይኑርህ ብንል ትክክል ነው። ከጎረቤት አገራት ጋር ሲሆን ጭፍን ጥላቻና የጅምላ ፍረጃዎችን ማዘውተር ከለመድን፣ በማግስቱ እርስ በርስ በጭፍን ተቧድነን በጥላቻ መጠፋፋት አይቀርልንም።
ለዚህም ነው፣ ስለ ወደብና ስለ ሕዳሴ ግድብ፣ ስለ ባሕር በርና ስለ አባይ ወንዝ ስናወራ፣ ጎረቤቶቻችን ላይ የጅምላ ውንጀላ በመሰንዘር ወይም በጭፍን ጣት በመቀሰር የማይሆነው። ከሆነም ስህተት ነው። ጎረቤቶቻችንን በጭፍን በመወንጀልና በጭፍን ጣት በመቀሰር መሆን የለበትም ለአገራችን መልካም የምንመኘው።።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
ሌሎች አገራት የወደብ ባለቤት ቢሆኑ፣ ኢኮኖሚያቸው እየተመነደገ ቢገሠግሥ፣ ኑሯቸው ቢሻሻልና ቢበለጽግ፣ የባሕር በራቸው ቢደራ፣ ፋብሪካዎቻቸውንና ከተሞቻቸውን በኤሌክትሪክ ኃይል ቢያሟሙቁና ቢያደምቁ… “ዕሠይ… ዕሠይ፣ ያዝልቅላቸው! ለከርሞም ይጨምርላቸው!” ብለን ደስታችንንና መልካም ምኞታችንን መግለጽ አለብን። የለብንም?
ከቻልንም ምርቃት ብናክልበት አይከፋም።
መቼም፣ ይብዛም ይነስ፣ በጥበብና በትጋት እንጂ፣ እንዲሁ በዋዛ የሚገኝ ሲሳይ የለም። የጥረታቸውን ያህል ሕይወታቸው ቢለመልም፣ “ዕሠዬው” በማለት መልካም ስሜትን መግለጽ ከማንም ሰው ይጠበቃል። ከኛም ጭምር ማለቴ ነው። ሰው አይደለንም እንዴ?
እንዲያም ሆኖ ግን፣ ከውጭም ከውስጥም በአንዳች “ምክንያት”፣ በጨፍጋጋ መንፈስ ብንወረርና ቢከነክነን፣ የቅናት ወላፈን ቢገርፈን፣ የቁጭት ስሜት ቢያንገበግበን አይገርምም። ይሄማ “የምቀኝነት በሽታ ነው” ብላችሁ ለመፍረድ አትቸኩሉ። የአብዛኞቻችን ቁጭት የምቀኝነት አይደለም። ከምቀኝነት የጸዳ ነው። አይደለም እንዴ? ከተጠራጠራችሁ መቼስ ምን ይደረግ? “ቁጭታችን ከምቀኝነት የጸዳ  መሆን አለበት” በሚል ሐሳብ እንስማማ።
ያኔ በሙሉ ልብ መናገር እንችላለን።
ለአገራችንና ለራሳችን መልካም መመኘታችን እንጂ፣ የሌሎችን ስኬት መጥላታችን አይደለም። እኛ ተርበን ማንም አይበላም” ብለን በምቀኝነት እንጀራቸውን ከእጃቸው ለማስጣል አንፈልግም። የነሱ ስለጎደለ፣ የኛ አይሞላም። ከአፋቸው ነጥቀን ለመጉረስም አናሰፈስፍም። እንዲህ ዐይነት አመል አይነካካንም።
በዐጭሩ፣ የነሱ ሲሳይ  አይደለም የሚያስቆጨን። አንዲያውም፣ ኢኮኖሚያቸው ዕጥፍ ድርብ ከፍ ቢልላቸው፣ ከተሞቻቸው ቢደምቁላቸው፣ ፋብሪካዎቻቸው እንደ መንኮራኩር ቢፈጥኑ እሠየው ነው። ለኛም በተረፉ ነበር። ሀብታም አገሮች ለጎረቤቶቻቸው ጥሩ ገበያ ናቸው።
ይልቅስ ሊያስቆጨን የሚገባው፣ ትልቋ አገር ኢትዮጵያ፣ ለክብሯና ለታሪኳ ከማይመጥን፣ ዜጎቿ በጦርነትና በረሀብ የሚሰቃዩበት አሳዛኝ ሸለቆ ውስጥ ገብታ አለመውጣቷ ነው። በኤሌክትሪክ ዕጥረት የደኸየች፣ የባሕር በር ያጣች፣ በኢኮኖሚ የደከመች መሆኗ ነው የሚቆጠቁጠን።
ትልቅነቷ በጭራሽ አያጠራጥርም። የታሪክ ባለጸጋ መሆኗም አያከራክርም። የሚመጥናት ቦታና ደረጃ ላይ አለመሆኗ ነው እጅግ የሚከነክነን፣ እጅግ የሚቆጨን።
እናም፣ የአባይ ወንዝና የባሕር በር ጉዳይ ላይ በቁጭት መናገራችን አይገርምም። የኑሮ ጉዳይ ነውና። እንዲያም ሆኖ፣ በጸበኛ ስሜት፣ በጭፍን ጥላቻ አይደለም። መሆን የለበትም።
አዎ፣ ኢትዮጵያውያን፣ “ሁሉም” ባይሆኑም እንኳ በአብዛኛው የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ይደግፋሉ። በእርግጥ በወቅቱ ገዢውን ፓርቲ ለመቃወም ሲሉ፣ ግድቡንም የተቃወሙ ፖለቲከኞች አልጠፉም። ቢሆንም አብዛኛው ሰው የሕዳሴ ግድብ ተቆርቋሪ መሆኑን እናውቃለን።
ነገር ግን፣ ለአባይ ወንዝና ለሕዳሴ ግድብ የተቆረቆሩ ኢትዮጵያውያን፣ ግብፅን ይጠምዳሉ ማለት አይደለም። የግብፅ ሰዎች ውኃ እንዳያገኙ ይመቀኛሉ ማለት አይደለም።
ውኃ የመቅዳት እንጂ የማደፍረስ ምኞት ምን ይረባል? የጤና አይሆንማ። ውኃ ለመጠጣትና ኤሌክትሪክ ለማብራት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንም፣ በግብፅ አገር ውኃ እንዲጠፋ ወይም አምፖል እንዲቃጠል ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ነን ማለት ግብፅን በክፉ እናያለን ማለት አይደለም።
“ውኃ እንዘጋባችኋለን፣ ጎርፍ እንለቅባችኋለን” ብለን የመዛት አንዳች ክፉ ስልጣን  ያምረናል ማለት አይደለም።
ግን በደፈናው ኢትዮጵያውያን ክፋት “አይነካካቸውም”፣ “በባህላቸው የለም” ብለን መመጻደቅም ትልቅ ስህተት ነው። በጅምላና በደፈናው “ቅን ሰዎች ብቻ የሚኖሩበት አገር” የለም። በሁሉም አገር በሁሉም ዘመን በሰዎች መካከል ፀብና ወንጀል ይኖራል። በሁሉም አገር እስር ቤት አለ።
ክፉ ሰዎች ብቻ የሚኖሩበት አገርም የለም። የመጠንና የደረጃ ልዩነት ቢኖርም፣ በሁሉም አገርና በሁሉም ዘመን፣ ክፋትና መልካምነት በየከተማውና በየመንደሩ፣ በቤተሰብ ውስጥም፣ ከወንድማማቾችና ከእህትማማቾች ጎበዝና ሰነፍ፣ ምቀኝነትና ቅንነት መገኘታቸው ዘላለማዊ እውነት ነው። በጅምላና በደፈናው ማሞገስም ሆነ መገሠጽ፣ መደገፍም ሆነ መቃወም ተገቢ የማይሆነውም ከዚህ ዘላለማዊ እውነት ጋር ስለሚቃረን ነው።
እናም፣ ኢትዮጵያውያን ለአባይ ወንዝና ለሕዳሴ ግድብ በቅን ሐሳብና በንፁሕ ልቦና፣ በቃልና በተግባር በፅናት ሲቆሙ፣ የግብፅ ነዋሪዎችን ለመጉዳት ወይም ለማስፈራት አይደለም ስንል፣… የብዙ ሰዎችን ጤናማ አዝማሚያ ለመግለፅ እንጂ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሐሳብና ስሜት አንድ ዓይነት እንዳልሆነ መርሳት የለብንም። ግብፅ ላይ ለመዛትና ቅራኔን ለማካረር የሚፈልጉ አይኖሩም  አይባልም። ይኖራሉ። ሰበብ ደግሞ ሞልቷል።
ግብፅ ውስጥ ደግሞ፣ ሕዳሴ ግድብን እናፈርሳለን ብለው የሚዝቱና የሚያውጁ ፖለቲከኞችና ባለስልጣናት አሉ። ሁሌም ይኖራሉ። ከዚያም አልፈው፣ ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን፤ እንበታትናታለን ብለው ይዝታሉ። ስሜት በማነሳሳት ብዙ ድጋፍ ለማግኘት፣ “ኢትዮጵያ በውሃ ጥም ልትገድለትን ትፈልጋለች” ይላሉ።
እና ምን ይሻላል? ኢትዮጵያ ውኃ ልትዘጋብን ነው እያሉ ጭፍን የጥላቻ ስሜትን ማራገብና የጦርነት እሳት መለኮስ ያዋጣል? በጭራሽ። ፀብና ጦርነት ለሁሉም ኪሳራ ነው። ማሸነፍም እንኳ በኪሳራ ነው።
“ኢትዮጵያ የባሕር በር እፈልጋለሁ ብላ ትወረናለች” እያሉ የጸብ ስሜት ማጋጋልስ ይጠቅማል? በፍጹም አይጠቅምም። እንኳን በጸብ በሰላምም፣ ኑሮ የከበዳቸው አገራት እንዴት ጸብን ይመርጣሉ?
ስለዚህ የሚበጃቸውን አስበውና አውቀው አርፈው ይቀመጡ? የራሳቸው ጉዳይ ነው ብለን እንዳሻን አንሁን? በጭራሽ!
ይልቅስ፣ የአባይን ውኃ መጠቀምና ግድብ መገንባት፣ መስኖ መዘርጋትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ፈለግን እንጂ፣ ከተሳካም ለጎረቤቶች የሚተርፍ መልካም ፍሬ እንድናገኝበት ተመኘን እንጂ፣ ጎረቤቶችን የመጉዳት መጥፎ ሐሳብም ሆነ ክፉ ስሜት እንደሌለን በመግለጽ የራሳችንን ኀላፊነት መወጣት ይኖርብናል።
የግብፅና የሱዳን ግድቦችን በማጉደል ቅንጣት ጥቅም አናገኝም። ቢሞላላቸው ምኞታችን ነው። እንዲህ የምንለው በብልጣብልጥነት አይደለም። የውሸት እየተናገርን እንሸንግላቸው፤ እንሸውዳቸው ለማለት አይደለም። በትክክለኛ ሐሳብና ከቅን ልቦና እንጂ።
የባሕር በር መፈለግም፣ ከጎረቤት የመንጠቅ ፍላጎት ማለት አይደለም። የባሕር በር በማሳጣት የሚገኝ ጥቅምም የለም። እንዲያውም ብዙ የባሕር በር ቢኖራቸው እሠዬው ነው። ልክ እንደዚያው ኢትዮጵያም የባሕር በር ያስፈልጋታል። ታዲያ በጸብ ስሜት አይደለም።
የጥላቻ ወይም የእልህ ስሜት የማይነካካው ቀና ፍላጎት መሆኑን ሁሌም መግለጽና ማስረዳት፣ የጦርነትና የጸብ ቁስቆሳን ለመከላከል ያግዛል።
ግብፅና ሱዳን ውስጥ፣ “ኢትዮጵያ በውኃ ጥም ልትጨርሰን ነው” እያሉ በጥላቻ የሚቀሰቅሱና የጦርነት ዛቻ የሚሸልሉ ነውጠኞች እንዳይኖሩ መከልከል ባንችልም፣ አብዛኛውን ሰው በስሜት እንዳያጦዙ፣ የመቀስቀሻ ሰበብ ከኛ በኩል እንዳያገኙ መጠንቀቅና መከላከል እንችላለን።
እንዴት? በአገራችን ውስጥ የራሳችንን ድርሻ በመፈፀም፣ አገርን መውደድ ማለት ሌሎች አገራትን መጥላት ማለት እንዳልሆነ መገንዘብና ማስገንዘብ ያቅተናል? አያቅተንም። ፀበኛነት በጭራሽ ጀግንነት እንዳልሆነ ማወቅና ማሳወቅ ይከብደናል? በጭራሽ!
“እነዚህ ግብፆች! ኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት ሸር የሰሩ! ግፍ የፈጸሙ!” የሚል ጭፍን የጅምላ ጥላቻን መከላከል እንችላለን።
በሰላምና በፍቅር፣ በትብብርና በግብይት ተያይዘን የማደግ እንጂ፣ “ለእኛ የተነፈገ ውኃ እናንተም አትቅምሷትም” ለሚል ጭፍን የጥላቻ ስሜት ቦታ እንደማንሰጥ፣ ተያይዘን ገደል የመግባት ክፉ ፍላጎት እንደሌለን ማስረዳት እንችላለን። በትክክለኛ ሐሳብና በልባዊ ስሜት ነው ታዲያ። የውሸትና የሽንገላ ከሆነ፣ የትም አያደርስም።
በጭፍን ለጥላቻና ለጦርነት ቅስቀሳ የሚያገለግሉ ሰበቦችን ለመከላከል የራሳችንን ኃላፊነት ከተወጣን፣ “ኢትዮጵያውያን ሊያጠፉን ነው። ውኃ ዘግተው ሊጨርሱን ነው” የሚል ክፉ ስሜት በግብፅ ውስጥ እንዳይዛመት ለመከላከል ያግዛል። ሳይቀጣጠልና ጦርነት ሳይለኮስ በፊት ማለት ነው።
አገር በጥላቻ ስሜት ከተንቀለቀለ በኋላ፣ በጦርነት እሳት መንደድ ከጀመርን በኋላማ፣ በወጉ ማሰብና በሥርዓት መናገርም ያስፈራል። ጦርነትን ከሩቁ ማስቀረት እንጂ የጦርነትን ነበልባል በየቀኑ እየለኮስን በየዕለቱ ጦርነትን መግታት አንችልም።
እንግዲህ፣ የባሕር በር እና የአባይ ጉዳይ ላይ እንኳ ጦርነት እንዳይፈጠር መከላከል ከቻልን፣ እዚሁ አገር ውስጥ እርስ በርስ በጭፍን የሚያቧድንና በጅምላ የሚያጋጭ ጦርነት እንዳይፈጠር መከላከል እንዴት ያቅተናል?

Read 462 times