Saturday, 24 February 2024 20:14

የቱርክና የሶማሊያ ወታደራዊ ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ስጋት የሚጋርጥ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ኢትዮጵያ የአገራቱ ስምምነት እንቅልፍ እንደማይነሳት ገልፃለች
- በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ

ሶማሊያ በቅርቡ ከቱርክ ጋር የፈፀመችውና የሶማሊያ ፓርላማ ሰሞኑን  ያጸደቀው ወታደራዊ ስምምነት፣ ለአጎራባች አገራት በተለይም ለኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት እንደሚጋርጥ ምሁራን ገለፁ። በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነቱ የተፈረመው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ፣ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ በገባች  ማግስት መሆኑ ደግሞ ስጋቱን የባሰ ያደርገዋል  ተብሏል።
ለ10 ዓመታት እንደሚዘልቅ በተነገረለት በዚህ ወታደራዊ ስምምነት፣ ቱርክ ለሶማሊያ የባህር ሃይል ሥልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ ተዘግቧል።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ የተፈረመውን ስምምነት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ቁጥራቸው በውል ያልተገለጹ የቱርክ የባሕር ኃይል መርከቦችና ወታደሮች በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ውስጥ ሆነው ለአገሪቱ ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ የሶማሊያ ባሕር ኃይልን መልሶ የማደራጀት ሥራም እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።
 “የቱርክ ወንድሞቻችን በስምምነቱ መሰረት፣ ባህሮቻችንን ለ10 አመታት ይጠብቃሉ፤ ከ10 አመት በኋላ ጠንካራ የባህር ሃይል እንፈጥራለን” ብለዋል-ፕሬዚዳንቱ።
የስምምነቱ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም ቱርክ የሶማሊያን ባህል ሃይል በማሰልጠን የምታስታጥቅ ሲሆን የሶማሊያን የባህር ጠረፍም ለመጠበቅም የራሷን ባህር ሃይል በአካባቢው ታሰማራለች ተብሏል። ስምምነት   በቅርቡ ከአገሪቱ ጋር ውዝግብ ለገባችው ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት እንደሚፈጥር የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ። የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ያለባትን  ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት ዕድል ባላገኘችበት በዚህ ወቅት   ሌላ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ መግባቷ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉ ተችተዋል።  በተለይ  በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ባጠላበት በአሁኑ ወቅት፣  አገሪቱ ከቱርክ መንግስት ጋር የፈጸመችው ወታደራዊ ስምምነት ስጋቱን ይበልጥ የሚያባባስ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለው የመግባቢያ ሠነድ መፈረሙን ተከትሎ፣ በሶማሊያና በሶማሊላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው የጠቆሙት ዶ/ር አንተነህ፤    በተለይም  የሶማሊላንድ  ሁለተኛ  ትልቋ   ከተማ በሆነችው ቦርኦ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ   የአካል ጉዳት ለማድረስ፣ ንብረት ለመዝረፍና፣ ቤታቸውን በእሳት ለማቃጠል ሙከራ ተደርጓል  ብለዋል። በሶማሊኛ ቋንቋ “ኢትዮጵያዊ ላይ በተገኘበት እርምጃ ይወሰድበት” የሚል አደገኛ በራሪ ጽሑፍ በሐርጌሳ ከተማ እየተበተነ መሆኑን ተናግረዋል-ወቅቱ  በሶማሊላንድ ለሚገኙ ወደ 50 ሺ የሚጠጉ  ኢትዮጵያውያን እጅግ አደገኛ መሆኑን በመግለፅ።ይህ በእንዲህ እያለ፣  የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ተፈጻሚ መኾኑ እንደማይቀር ለአገራቸው መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። “ሶማሊያ ቱርክን ወይም ግብጽን አጋሯ አድርጋ ብታመጣም፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም፤ “ሶማሊያና ቱርክ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን መግባቢያ ስምምት ሊጎዳ አይችልም” ብለዋል።
“ሶማሊያም ሆነች ቱርክ ሉአላዊ አገር ናቸው፤ የፈለጉትን ስምምነት ከየትኛውም አገር ጋር የማድረግ መብት አላቸው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አላት፤ ይህ ወታደራዊ ስምምነት እንቅልፍ አይነሳንም” ብለዋል።

Read 912 times