Monday, 26 February 2024 19:58

አልፎ ያላለፈው የአብዮቱ ወላፈን

Written by  -አብርሃም ገብሬ ደቢ
Rate this item
(0 votes)

“--ሌላው የአብዮቱ ትልቁ ‘ውጤት’ ደግሞ በተለይ አዲስ አይነት ማህበራዊ ስርዓትና ግንኙነት እንዲፈጠር ማስቻሉ ነው፡፡ይህ
አዲሱ ማህበረ-ፖለቲካዊ ስርዓት በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ዘውግን (ethnicity) መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት ያዋቀረ
ሲሆን፤ ይህም በ66ቱ አብዮት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ተተግባሪ ለመሆን ችሏል፡፡--”


የ1966ቱ የየካቲት አብዮት በአንድ ወቅት የተከሰተ ታላቅ ኩነት ወይም ንቅናቄ ብቻ አይደለም፡፡ ሃምሳ ዓመቱን የደፈነው ይህ አብዮት፤ አዲስ አይነት ዕውቀትና እውነትን ያነጸ፣ ከነባሩ እጅግ የተለየ ሌላ ማህበረ-ፖለቲካዊ መንገድ የቀየሰ አብዮት ነው፡፡ የሀገራችንን ታሪክ የምንረዳበትን መንገድ፣ ማህበራዊ ግንኙነታችንን፣ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራችንን፣ ፖለቲካዊ እሳቤያችንንና ዓለምን የምንገነዘብበትን መንገድ የቀነበበልን ስር ነቀል አብዮት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ስለ 66ቱ አብዮት ለማወቅ ሃሰሳ ማድረግ ማለት፣ በአንድ ወቅት ስለተከሰተው ታሪካዊ ኩነት ማወቅ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ የሄድንበትና እየሄድንበት ያለውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ መንገድ ማወቅ እንጂ፡፡ ስለ አብዮቱ ለማወቅ መጣር ማለት፤ ባለፉት ሃምሳ አመታት የተጓዝንባቸውን የቀውስም እንበለው የሰላም፣ የድህነትም እንበለው የእድገት፣ የመነጣጠልም እንበለው የአንድነት፣ የመገዳደልም እንበለው የመፈቃቀር…ጉዟችንን ከስር መሰረቱ ለመገንዘብ መሞከር ማለት ነው፡፡   እውቁ የፖለቲካ ሳይንቲስት ሳሙኤል ሃንቲንግተን፤ ‘Political Order in Changing Societies’ በተሰኘው መጽሐፉ እንዳሰፈረው፤ “አብዮት በባህሪው ግብታዊ፣ በቀውስና በግጭት የታጀበ ሲሆን፤ የማህበረሰቡን ነባር እሴቶች፣ ሚቶች፣ ማህበራዊ መዋቅሮችና ፖለቲካዊ ተቋማትን አፈራርሶ በሌላ ይተካል፡፡ እንዲሁም የአመራርና የፖሊሲ ለውጦችን በማድረግ አዲስ ማህበራዊ ስርዓትን (social order’ን) ያዋቅራል፡፡ (“A revolution is a rapid, fundamental, and violent domestic change in the dominant values and myths of society, in its political institutions, social structure, leadership, and government activity and policies.”)፡፡ በሌላ አገላለጽ አብዮት፣ አንዲት ሃገር ለዘመናት የተጓዘችበትና እየተጓዘች ያለችበትን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መንገድ ‘ቀጥ አድርጎ በማቆም’ በሌላ አቅጣጫ እንድትጓዝ ያደርጋል፤ አዲስ አይነት ማህበረ-ፖለቲካዊ ስርዓትም ያንጻል፡፡ የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በአንድም ሆነ በሌላ የፈጸመው ይህንኑ ተግባር ነው፡፡
ሀንቲንግተን፤በዓለም ታሪክ ውስጥ ስር-ነቀል የማህበራዊ አብዮት ማድረግ ብዙም የተለመደ አይደለም ይላል፡፡ በእርግጥ በዘመናዊ የዓለም ታሪክ ውስጥ በተለይ ማህበራዊ አብዮት ያደረጉ ሃገራት በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
 በኢትዮጵያ አብዮት ዙሪያ ምርምር ያደረጉ ምሁራንም የሚስማሙበት አንድ ትልቅ ጉዳይ ቢኖር፣ የ66ቱ አብዮት፣ ዓለም ላይ ከተካሄዱ ጥቂት ብሉይ የማህበራዊ አብዮቶች (Classical Social Revolutions) ጎራ የሚመደብ መሆኑ ላይ ነው፡፡     
የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት የታሪክ ተመራማሪው ክርስቶፈር ክላፋም (ፕ/ር)፤ የ66ቱ የኢትዮጵያ አብዮትና አብዮቱ ያስከተላቸው ውጤቶችን የሚያትት ‘Transformation and Continuity in Revolutionary Ethiopia’ የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ክላፋም በዚህ መጽሐፉ፤ የኢትዮጵያ አብዮት ብሉይ የማህበራዊ አብዮቶች ተብለው ከሚጠቀሱት የ1789ኙ የፈረንሳይ፣ የ1917ቱ የሩስያና የ1949ኙ የቻይና አብዮቶች ጋር መድቦታል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጠው፣ በአንድ በኩል አብዮቱ ፖለቲካዊ አብዮት ብቻ ሳይሆን አዲስ አይነት ማህበራዊ ስርዓት የማዋቀር ዓላማ ይዞ መነሳቱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ሥር-ነቀል (radical) አብዮት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ነው፡፡
ክላፋም እጅግ ሥር-ነቀል መሆኑን ላሰመረበት የ66ቱ አብዮት፣ ከሌሎች ብሉይ የማህበራዊ አብዮቶች የሚጋራቸው መሰረታዊ ባህሪያትን በማሳያነት አስቀምጧል፡፡ በዚህም አብዮቱ ለሰባት መቶ ዓመታት ገደማ በሰለሞናዊ ስርወ-መንግስት ስም ሃገር ሲያስተዳድር የነበረውን ዘውዳዊው ስርዓት መጣሉን፣ ስር ነቀል አብዮት ባካሄዱ ሌሎች ሃገራት ላይ እንደታየው ዘውዳዊው ስርዓት በወታደራዊ አገዛዝ መተካቱ፣ አብዮቱን ተከትሎ የውጭ ወረራ መከሰቱ (የ1969ኙ የሶማሊያው የዚያድ ባሬን ወረራ ልብ ይሏል)፣ መሬት ላራሹ ‘መታወጁ’ን ተከትሎ የኢትዮጵያ የመሬት ስሪት ላይ መሰረታዊ ሽግሽግ መፈጠሩ፣ የ”ሶሻሊዝም” ርዕዮተ-ዓለም መታወጁ፣ በዲፕሎማሲያዊ መድረክ ላይ የምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ‘ጥገኛ’ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ምዕራባውያን ወደ ነበረችው ሶቪየት ህብረት ጎራ ሙሉ በሙሉ መቀላቀሏን በማሳያነት ጠቅሷል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች ብሉይ ማህበራዊ አብዮቶች ላይ የሚታዩ መሰረታዊ የጋራ መገለጫዎች ናቸው፡፡
እዚህ’ጋ ግን አንድ ጉዳይ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አብዮቱ ‘ስር ነቀል ነበር’ ሲባል፣ ሁሉንም ነገር አፈራርሶ በአዳዲስ ነገሮች ተክቷል ማለት አይደለም፡፡ ለአብነትም በፖለቲካ አውድ ውስጥ ጉዳዩን ብንመለከተው፣ የስልጣን-ወ-ሃይል (power) አረዳዳችንና አተገባበሩ እንደማህበረሰብ ብዙም ለውጦታል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የአካሄድና የቅርጽ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር በመሰረታዊነት የስልጣን-ወ-ሃይል ምንነትና ተፈጥሮ አልተቀየረም፡፡
እንዲሁም ከአብዮቱ በፊት የነበረው የቢሮክራሲ ተቋማትና ተግባራት በአብዮቱ ማግስትም ቀጥሏል፡፡ በእርግጥ እንደ ቀበሌ ያሉ አዳዲስ አደረጃጀቶች ከአብዮቱ ጋር ተያይዘው የመጡ መሆናቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አብዮቱ ሁሉንም አፍርሶ ነገሮችን እንደ አዲስ የጀመረ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ሆኖም ከአብዮቱ በኋላ የኢትዮጵያ ማህበረ-ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ተቋማት ላይ ግን መሰረታዊ ለውጦችን ማስከተሉ  ሊሰመርበት ይገባል፡፡   
እሌኒ ዘለቀ (ዶ/ር)፤ ‘Ethiopia in Theory: Revolution and Knowledge Production, 1964-2016’ በተሰኘው መጽሐፏ፣ ከአብዮቱ በኋላ የኢትዮጵያ የእውቀት ምርት (Knowledge Production) እና መሰረቱ ላይ (በተለይ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ) መሰረታዊ ለውጥ መደረጉን ጽፋለች፡፡ ይህ አብዮት፣ ከዚያ በፊት የነበረውን የታሪክ አጻጻፍ ዘዴ (historiography) በመተው ዘውግ ተኮር የታሪክ አጻጻፍ ዘዴና አረዳድ ማስተዋወቁንና ማንበሩንም ትገልጻለች፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ታሪክ ከዘውጋዊ ማንነት አንጻር መቃኘትና መረዳት እያደገ መጥቶ፤ የኋላ ኋላ ዘውጋዊ ማንነት ተፈጥሮአዊና የማይለወጥ (Primordial) ማንነት ስለመሆኑ፣ ህጋዊ እውቅና ጭምር ማግኘቱን ታወሳለች፤ እሌኒ በመጽሐፏ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የካርል ማርክስን የታሪክ አረዳድ (የመደብ ትግል)፣ ከኢትዮጵያ አውድ አንጻር በመጠቀም፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የ”ጨቋኝ” እና የ”ተጨቋኝ” ብሄረሰቦች ታሪክ መሆኑን የሚያትቱ ሃቲቶች (discourses) የዚህ የአብዮቱ ‘ፍሬ’ ናቸው፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ የጨቋኝና ተጨቋኝ ታሪክ አድርጎ በማቅረብ ረገድ ቀዳሚው ቡድን፣ የቤኔቶ ሙሶሊኒ የፋሽስት መንግስት ነው፡፡ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በነበረው የወረራ ዘመን፣ ለኢትዮጵያ ዘውግን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት በማስተዋወቅ፤ እንዲሁም አንዱን “ጨቋኝ”፣ ሌላውን “ተጨቋኝ” አድርጎ የማቅረብ ፖሊሲ በማርቀቅ፣ ተግባራዊ ማድረጉን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አብዮቱን በሚመለከት መነሳት ያለበት ወሳኝ ነጥብ፣ አብዮቱ ዘውዳዊ ስርዓቱን ገርስሶ በቦታው ወታደራዊው የደርግ መንግስት ከተተካ በኋላ፣ የአብዮቱ ነገር እንዳበቃ  አድርጎ የመረዳት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በመሰረቱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ወታደራዊ ደርግ አብዮቱ ላይ የተነሱትን መሰረታዊ ጥያቄዎች “መልሻለሁ” ቢልም፣ በሌላ ጽንፍ ደግሞ ‘የለም! የአብዮቱ ዋነኛ ዓላማና ግብ ይህ አይደለም’ በማለት የትጥቅ ትግል የጀመሩ ሃይሎች የዚሁ የ66ቱ አብዮት አካል ናቸው፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ገብሩ ታረቀ (ፕ/ር)፤ ‘The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa’ በተሰኘው መጽሐፉ አጽንኦት ሰጥቶ ያስገነዘበው አንዱ ርዕሰ-ጉዳይ፤ የህወሃት፣ የሻዕቢያና የሌሎችም ቡድኖች የትጥቅ ትግልና ውጤታቸው የዚሁ የ66ቱ አብዮት ቅጥያ ወይም አካል እንደሆኑ ነው፡፡   እንደሚታወሰው በአጼ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የትጥቅ ትግል ቢጀምሩም፣ ይሄ ነው የሚባል ሃይል ያልነበራቸው የኤርትራ ሃይሎች (አብዮተኞች)፣ ከ66ቱ አብዮት በኋላ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኋላ ኋላም በሻዕቢያ መሪነት ነጻ ሃገር ማወጃቸውና በኢትዮጵያ ቀጣይ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፋቸው የዚሁ የአብዮቱ ‘ውጤት’ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፡፡
ሌላው የአብዮቱ ትልቁ ‘ውጤት’ ደግሞ በተለይ አዲስ አይነት ማህበራዊ ስርዓትና ግንኙነት እንዲፈጠር ማስቻሉ ነው፡፡ይህ አዲሱ ማህበረ-ፖለቲካዊ ስርዓት በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ዘውግን (ethnicity) መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት ያዋቀረ ሲሆን፤ ይህም በ66ቱ አብዮት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ተተግባሪ ለመሆን ችሏል፡፡ እሌኒ በመጽሐፏ አሁን በስራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ህገ-መንግስትን ጭምር ማዕከላዊ የፖለቲካ  የመብት ጥያቄዎቹ የተቀዱት፣ ከዚሁ የየካቲቱ አብዮት መሆኑን አስፍራለች፡፡
በአጠቃላይ ግን የ66ቱ አብዮት ምን አይነት ውጤቶችን አምጥቷል? የሚለው ጉዳይ የራሱ የቻለ ትልቅ ርዕሰ-ጉዳይ ነው፡፡ ‘’ሕዝቡን ከጭሰኝነትና ከገባርነት ሥርዓት አላቅቋል፤የብሄርና የሃይማኖት እኩልነት መብት እንዲታወቅ በር ከፍቷል፣ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን (ሴኩላሪዝምን) አስተዋውቋል…” ብለው የሚያምኑ አብዮተኞችና ምሁራን አሉ፡፡ ለምሳሌ አብዮቱ ላይ ትልቅ ተሳትፎ የነበረው አንደርያስ እሸቴ (ፕ/ር)፤ አብዮቱ የኢትዮጵያ ዘመናዊነትን በማዋለድ ሂደት ውስጥ “ቁልፍ ሚና ተጫውቷል” ይላል፤”Modernity: It’s Title to Uniqueness and its Advent in Ethiopia” በተሰኘው ጽሁፉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ‘የለም! የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ በቅጡ ባልመረመሩ፣ ከማህበረሰቡ እሴትና ማህበራዊ ህይወት በተነጠሉ (የምዕራቡ ዓለም ‘ትምህርት’ና የአኗኗር ዘይቤ የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ አድርገው በሚያነበንቡ) ወጣቶች ‘የተመራው’ አብዮት፣ የማህበረሰቡን የአብሮነት ዕሴቶች እንዲሸረሸሩ፤ የዘውግ ጽንፈኝነት እንዲገን፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሥጋት ውስጥ እንዲወድቅና የእርስ በእርስ መጠፋፋት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል’ በሚል፤ የፍልስፍና ምሁሩ መሳይ ከበደ (ፕ/ር)፤ ‘Radicalism and Cultural Dislocation in Ethiopia, 1960-1974’ በተሰኘው መጽሐፉ አጥብቆ ይተቻል፡፡
በአጠቃላይ ግን አብዮቱ በትናንትናው ታሪካችን ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬውን የማህበረ-ፖለቲካዊ ህይወታችንን በመቀንበብ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ስለ አብዮተኛው “ያ ትውልድ” ስናስብም፣ የአብዮተኞቹ ወይም የአብዮቱ ዘመን ትውልድ በፖለቲካው መድረክ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ሳይሆን፣ አብዮተኞቹ ያነሷቸው እሳቤዎች፣ ያስተዋወቋቸው የፖለቲካ ባህሎች፣ የወጠኗቸው የለውጥ ፍላጎቶችና ግቦች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተቋማዊ ገጽታ በመያዛቸው ነው፣ አብዮቱ በዛሬው ህይወታችን ጭምር የጎላ ተጽዕኖ አለው የምለው፡፡ የአብዮቱና የአብዮተኞቹ ዓላማና ግብ ‘ይህ አልነበረም’ የሚሉ ክርክሮች ቢኖሩም፣ ይህን አስተያየት የሚያራምዱ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ዕድሉን አግኝተው የመንግስት ስልጣን ቢይዙ የተለየ የፖለቲካ ባህልና እሳቤ ያንጹ ነበር ለማለት ግን እጅግ ያዳግታል፡፡ሌላው ደግሞ ቅድመ-አብዮት የነበረው የኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምን ይመስሉ ነበር? የሚለው ጉዳይ አብዮቱን ለመረዳት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ለ66ቱ አብዮት መከሰት በቅድመ-አብዮት የነበሩ የኢትዮጵያ መልከ-ብዙ ችግሮች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አብዮቱ ከሆነ ቦታ የወደቀ ድንገቴ ክስተት አልነበረም፡፡ ይህ ጽሁፍም ያለቅጥ እንዳይለጠጥ በሚል የቅድመ-አብዮት የኢትዮጵያ ሁኔታ ከአብዮቱ አውድ አንጻር ባይዳስስም፣ ለማህበራዊ አብዮቱ መከሰት ከአብዮቱ በፊት የነበሩ ችግሮች ሁነኛ ሚና እንደነበራቸው ግን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡     
ለማንኛውም ግን ስለ አብዮቱ ስናስብ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ስለተደረገው አብዮት ብቻ ሳይሆን ስለዛሬው ማህበረ-ፖለቲካዊ ህይወታችን ጭምር እያሰብን መሆናችንን መዘንጋት አይገባም፡፡
ይህ ጽሁፍም የ1966ቱ የየካቲት አብዮት ሃምሳኛውን አመት በማስመልከት የተጻፈ ሲሆን፤ በዋናነት፣ ስለአብዮቱ ምንነትና በዛሬው ማህበረ-ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ላይ ስለተዋቸው በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ይበልጥ መጠየቅና መመርመር እንዳለብን ለማስታወስ የተሰናዳ ነው፡፡



Read 952 times