Monday, 26 February 2024 20:25

ሞት በቅኔ ሲያፍር!

Written by  -ሲራክ ወንድሙ-
Rate this item
(2 votes)

“አልሞትም!
አልልም።  
              እንደ አማሟቱ ነው፣
              እንደ አፈር አልባሱ . . .
በቀሉም የሚያምር፣
              በዘሪ ʻጅ - ተዘግኖ፣
             ሲበተን - ተረጭቶ . . . እንደማይፈለግ - እንደሚጣል ነገር።
እንደ ቀባሪው ነው፣
እንደ ገበሬው ስልት . . .
ሞቶም በቃይ ቶሎ፤
እስቲ እኔም ልሙተው!
ሞቴ ለምን ይቅር!? . . .
ያልሞተ መች በቅሎ።
አልሞትም
አልልም።”
የጊዜው ቁጥር 1950 ነበር። የተወለደው  ”ቢስሚላሂ በስማም - በስማም ቢስሚላሂ
አብሮነትስ ወሎ ማሪያምን ወላሂ” በምትባልበት የወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ ወረኢሉ አውራጃ ታክል ከተማ ውስጥ ነበር። ልጅነት ድምቀቱን፣ ፍካቱን ወዝና ጣዕሙን ባልነሳበት ለጋ አእምሮው፣ አባቱ ለጉዳይ አዲስ አበባ ሲመላለሱ ቃርመው በሚያመጡለት መጻሕፍት አማካኝነት ንባብን ተዋወቀ።  ካቤ በምትባል መንደሩ ከላምባ ጭስ ጋር እየታገለ ራሱን ለማጎልበት በቃ። በእናትና አባቱ ትዳር አለመስመር ሳቢያ የተፈጠረበትን የስነ ልቦና ጫናና የእንጀራ እናቱን አይን ሽሽት፣ መከፋቱን ሀዘንና ሳቁን በፊደል የቃል አንቀፅ ጠቅልሎ ሊደብቅ ሲል፣ ብዕርና ወረቀቱ ጋር የእድሜ ዘመኑን ባልንጀርነት አሀዱ ብሎ ጀመረ።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዝነኛው ደሴ ወይዘሮ ስኅን ትምህርት ቤት አጠናቆ፣ በ1971 ዓ.ም በደብረ ዘይት የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ገባ። መንፈሳዊ ግጥሞችን ይጫጭር የጀመረው ይህን ጊዜ ነበር። ከደብረ ዘይት የእንስሳት ህክምና ተመርቆ እንደወጣ የስራ ቅጥሩ ወደ አርሲ ይዞት በመሄድ፣ ዘጠኝ ዓመት ከግማሽ አከረመው። ወንድዬ በአርሲ ቆይታው የብርቱ ገጣሚነት ምስሉን ይዞ ብቅ እንዳለ ብዙዎች ይስማማሉ። የዚህ ምስክሩ ደግሞ በ1984 ዓ.ም የታተመችው የመጀመሪያ የግጥም መድበሉ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ኮተቤን ጨምሮ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነፅሁፍ ክፍል ለማስተማሪያነት  በካሪኩለሙ ውስጥ የተካተተችው ዝነኛዋ “ወፌ ቆመች” መፅሐፉ ነች።
ወንድዬ ከ“ወፌ ቆመች” ሁነኛ ስራው በኋላ የስነ ፅሁፍ መንገዱ ብራ ሆነለት። ጨርቅ ያርግልህ እንደተባለው ሁሉ። በአንዳንድ ባልንጀሮቹ አማካኝነት የግብርና ሚኒስቴርን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ ቃለ ህይወት የስነፅሁፍ ድርጅት በመፅሄት አዘጋጅነት ጠቅልሎ ገባ። ከዚህ ጊዜ ወዲህ ወርቃማ የሚባሉ የስነ ፅሁፍ ጊዜያትን አሳለፈ። በኢትዮጵያ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፉ “በመከራ ያበበች”  እና  “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” የተባሉ በሁለት ቅፅ የተዘጋጁ መጻሕፍትን በ1990 እና 1992 ዓ.ም አከታትሎ አሳተመ። መጻሕፍቱ ይዘው ከመጡት ዝና በላይ የ« Master’s » ዲግሪውን በኬንያ ዴይስታር  ዩኒቨርስቲ እንዲሰራ መንገድ ከፈቱለት።
ልክ በአርባ ዓመቱ ሁለተኛ ዲግሪውን ሊሰራ ትምህርት ቤት ገባ። ሦስት ዓመት ኬንያ በትምህርት ቆይቶ ሁለተኛ ዲግሪውን ይዞ ወደ ሀገሩ በመመለስ የቃለ ህይወት የስነ ፅሁፍ ክፍል ሀላፊ በመሆን ተመደበ። ሆኖም ጋሽ ወንድዬ ከሁለት የአበባየሆሽ የአደይ እድሜ በኋላ የስነ ፅሁፍ ሀላፊነት ቦታውን በመተው፣ በወቅቱ የወጣትና አንጋፋ ደራሲያንን ስራ በማሳተም በስፋት በሚታወቀው ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር  ውስጥ ተቀጠረ።
ማዕከሉ  በ1998 ዓ.ም ባሳተመው “ወንዞች እስኪሞሉ እና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ” ውስጥ “ከሚላ” በምትል ነጠላ ልቦለዱ ተሳተፈ። ይህቺ ከብዙ በጥቂቱ የፖፕሌሽን ሚዲያ ቆይታ ውስጥ የምትጠቀስ ሆነችና  ሁለት ዓመት እንደቆየ ስራውን ለቆ ወደ ሙሉ ጊዜ ፀሀፊነት ተሸጋገረ።
በኢትዮጵያ የስነ - ግጥም ታሪክ ውስጥ የራሱን ቀለም ይዞ ብቅ ከማለቱም ባሻገር “ጊዜን መንዝሮ ለተለያዩ አውዶች በማዋል ከሰለሞን ደሬሳና ከፀጋዬ ገብረ መድህን አቻ ነው።” የሚባልለት ሁለገቡ ወንድዬ አሊ፤ ከ”ወፌ ቆመች“ መፅሐፉ በኋላ በ1998 ›”ህይወትና ውበት“ የተባለ ከቀደመ መፅሐፉ በተሻለ በሀሳብ ደርጅቶ በውበት ቆንጅቶና ተዋዝቶ መጣ። በሁለቱ የግጥም መጻሕፍቱ መካከል ያለው የአስራ አምስት ዓመታት ገደማ እድሜ፣ ወንድዬ ለስነ ግጥም ያለውን ጉልህ ምልከታና አስተዋፅኦ የሚያስረዳ ነው ብዬ አምናለሁ። ከእነዚህ ከሁለቱ ውብ የግጥም መድበሎች ባሻገር፣ ከ25 በላይ የሚሆኑ የተለያየ ይዘት ያላቸው መጻሕፍትን ለአንባቢያን በማድረስ የሚታወቅ የስነ ፅሁፋችን ብርቱ ወዛደር ነው።
ወንድዬ ስነ ግጥምን የሚያይበት መንገድ በበርካታ ፈርጅ ለዚህ ዘመን እንግዳ ነው ብዬ አስባለሁ። በዚህ ፖለቲካው የውጥንቅጥ ማዕከሉ በሆነበት፣ አድሮ እንደ ቅጠል በሚረግፍና የህይወት ንጥፈትን አንደመለያው ይዞ የመጣው የዘመን የግጥም መንፈስ ይከረፋዋል። “ግጥም ያልተሸቀጠ እለት ነው ነብስን የሚያረሰርስ፣ በዘላለም ሸራ ላይ ብሩህ ሆኖ የሚደምቀው” የሚለው የስነ ፅሁፉ ወዛደር፤ ”ችሎታ“ በሚል ግጥሙ እንዲህ በማለት ጩኸቱን ከማሰማት አልተገደበም :-
“አንቺዬ
እንዴት ቢሆን ቻልሽበት
እሳት ከውሃ ማጋባት
እንዴት አድርጎ ሆነልሽ
እርጥብ ደረቁ ተስማማሽ ?
ጉግ ማንጉጉን በደረቱ
ቱሪናፋውን በጀርባ
ካህኑን በምኞት ጀልባ
እውሃ ላይ
እመሬት ላይ
አዝለሽም
እየዋኘሽም
እንዴት በአንዴ ሆነልሽ
ሁለት ዛፍ በሁለት እግርሽ....»
.. እያለ ይቀጥላል። የግጥም ዘገባ መምሰል ፤ የሰበካ ቅርፅ መያዝ ለዚህ ዘመን የግጥም መንፈስ መንኮታኮት ምክንያት እንደሆነ የሚያምነው ታላቁ የብዕር ሰው ወንድዬ አሊ፤ በተወለደ በ66 ዓመቱ በአደረበት ህመም ሲረዳ ቆይቶ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለየን የስነ ፅሁፍ አድባር ነው።  ወንድዬ አሊ ከስራው ግዝፈትና ከሰጠን በረከት አንፃር ልንዘምርለት ያልቻልነው ጀግናችን እንደሆነ ይሰማኛል። በእርግጥ በዚህች ሀገር የመወዳደስ ባህላችን መሰረት፣ አንድ ሰው እንዲከበርና እንዲዘከር ግድ እስኪሞት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ እንደ ወንድዬ አሊ ያሉ ዋርካዎቻችን በተነጠቅን ማግስት ወየው ማለታችን የኋላ ኋላ በእቃቃ የሚመራ የጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ የስነ ፅሁፍ መንገድ እንደሚኖረን እሙን ነው። በአንድ መናኛ መፅሐፍ ስሙ እንደግጥም ፈጣሪና ቃላት መስራች የሚታይ ሰው እንደክረምት እንጉዳይ በየአጥቢያው  በፈላባት ኢትዮጵያ፣ ወንድዬ አሊን ያህል አንጋፋ ሰው በሞቱ ማግስት እንዲህ ስንቆጭ ይገርመኛል። ዘመን በእግሩ ቃጤ ካሰመረው አጀባ ማዶ የቆመው በጭብጨባ የገለማን ሰባራ አድናቆት ከእሽሩሩ እኩል ቆጥሮ በስነ ግጥምና ስነ ግጥም ብቻ የገደመ መናኒ የሆነው፣ የዘመኑ ትንፋሽ ባይመቸው ባይደላው ነው እላለሁ። ግጥም ከነብስ ምንጭ የሚገኝ መና ከመሆን አልፎ እንደ ጨውና በርበሬ ለሽያጭ በወጣባት ጊዜ ላይ ተገኝቶ ሁሉን የታዘበ... የአቴቴውን የተማፅኖ ቡራኬ ...የቦግ እልሙ አመል ሲካካውን ደፍቶ ረክቶ ሲመለስ፣ ከሁለተኛው የግጥም መፅሐፉ ከአስራ ሰባት ዓመታት ገደማ በኋላ ሦስተኛ መፅሐፉን የምንናፍቅበት ወቅት ነበር ይሄ...
የህልሙን ከፈፍ የህይወት ውጣ ውረዱን ላቅ አድርጎ የሳለባት ግጥም፣ የሞቱን መሪር ዜማ ስትሰማ በፀጋዬ አፎት ሾልካ :-
« ....
ቃለ – ምንጩን ካልመሰነ፣ ስለቱን ካልጐለደፈ
መቅረዙን ካልተዳፈነ፣ ከፊደሉ ካልነጠፈ
ዐፅመ – ወዙን ካልደረቀ፣ ጧፉን ቀልጦ ካልሰፈፈ
ጡጦ እንደጠፋበት አራስ፣ ቁም ተዝካሩን ካልለፈፈ
ብዕሩ ቀርቶ ምላሱ፣ በሃሜት ካልተንጠፈጠፈ፤
የቃለ – እሳት ነበልባሉ
የድምፀ ብርሃን ፀዳሉ
የኅብረ ቀለማት ኃይሉ
አልባከነምና ውሉ
የዘር – ንድፉ የፊደሉ
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ።²” ሳትል አልቀረችም። በአንድ ራሱ ብዕርም አልሞትም አልልም እኔም እሞታለሁ! እንዳለ ታላቁ የግለ ታሪክ ፀሀፊ፣ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ አርታኢ፣ የቤተክርስቲያናት ታሪክ ፀሀፊ፣ ተመራማሪ፣ አዘጋጅና የመዝሙር ግጥም ፀሀፊ የሆነው የስነ-ፅሁፍ ወዛደሩ የእረፍቱን ዜና ሀገር ሰማው። ሰማይ የክረምት ኪዳኑን በደመና እንደሚያፀና ሁሉ፣ ጊዜ የሞትን ድቤ እየጎሰመ በየማለዳው በየበራፉ የነዋሪን ሆድ ሊያባባ ጥቁር ሳቁን ይለቀዋል። በእያንዳንዱ ፈጋግ ማለዳ መሀል ጭፍግግ የሞት ውሳኔ መዝገብ ሊደመጥ ከሴራው ቢሻረክም ቅሉ፣ በህያው ስራ ሀውልቱን አፅንቶ የሄደ ሞተ ቢባል ማን ያምናል?
ባለቅኔነት አይደለም ከሞት ጋር ከዘመን ጋርም የሰመረ የጠጠረ ውል የለውም። ጊዜን በመዳፉ ጠፍጥፎ ሊሰራ ብዕር ያነሳ ሞተ ቢባል እውነት ሞት ነው? አበባው የጀግና ጉሮ ወሸባ እንጂ የእዬዬ መዝሙር ነው? እኔ አይመስለኝም!!
ቀዳሚዎች ሁሌም በቀደሙበት የእርምጃ ልክ ስማቸው ገኖ ይውላል። ዘመን በሚሻገር ህያው ስራዎቻቸው ውስጥ በታሪክ ሲዘከሩ ይኖራሉ።
ዝምታዎቻችንን ላዜሙ ልቦች ...መስቀሎቻችንን ለተሸከሙ ክንዶች የምናለቅሰው ለቅሶ የእዳ ብቻ አይደለም፤ የማይቻለውን በመቻል በነፍሳችን ፅላት ላይ ስለሳሉት ደማቅ ስዕል የመገረም የመቆጨት ምልክቶቻችንን የማሳየትም ጭምር ነው።
ጋሽ ወንድዬ፤ ዘመንህን ሳትሰስት የገበርክለት የኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ሁሌም በበጎ ስራህ ያስታውስሃል። ወጣት ገጣሚያኑ አርአያህን በመከተል መነሻቸው ያደርጉሃል። የአምላክ ፍቃዱ ነውና ዛሬ በመካከላችን የለህም፤ ነፍስህን በአፀደ ገነት ከደጋጎቹ ጎን ያኑርልን። እንወድሃለን ጋሼ!! እናመሰግንሃለን በብዙ። እናከብርሃለን ሁሌም። በልባችን የታተምክ አድባራችን ነህ!

”አልሞትም - አልልም
አልሞትም!
አልልም!!
እኔም እሞታለሁ፣ . . .
ከደንብ ውርስ አልወጣ፣
ካፈር ልብሴ በታች፣
ሽፋኔ በስብሶ፣
ክንብንቤ ፈርሶ . . . በቀሌ እስኪወጣ።
               እሞታለሁ እንጂ፣ . . .
ለምን እኔ ብቻ ልታጣ - ከተርታ?
ደግሞ ትንሣኤዬስ . . . ጽድቅ መከወኛው፣
 የት ብሎ ያግኘኝ!? የቀጠሮ ቦታ።
አልሞትም!
አልልም።  
   እንደ አማሟቱ ነው፣
እንደ አፈር አልባሱ . . .
በቀሉም የሚያምር፣
  በዘሪ ʻጅ - ተዘግኖ፣
  ሲበተን - ተረጭቶ . . . እንደማይፈለግ - እንደሚጣል ነገር።
እንደ ቀባሪው ነው፣
እንደ ገበሬው ስልት . . .
ሞቶም በቃይ ቶሎ፤
እስቲ እኔም ልሙተው!
ሞቴ ለምን ይቅር!? . . .
ያልሞተ መች በቅሎ።
አልሞትም
አልልም።”
...
¹ሙሃመድ ሙፍቲ ( ጀዋድ )
² ፀጋዬ ገ/መድህን ( እሳት ወይ አበባ )

Read 215 times