Wednesday, 28 February 2024 21:00

ተአምረኛውን ትውልድ ተመልከቱ

Written by  ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ
Rate this item
(0 votes)

ዳሰሳ፡- ዘነበ ወላ
ደራሲ፡- ካፕቴን ዘላለም አንዳርጌ
ርእስ፡- ‘ፀሐይ’
የኢትዮጵያ አቬዬሽን አጀማመር
ማተሚያ ቤት፡- ኢክሊፕስ
አሳታሚ፡- የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ
ገጽ፡- 346
ዋጋ፡- 235 ብር



ካፒቴን ዘላለም አንዳርጌ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ  አብራሪ ነው። ወላጅ አባቱ አቶ አንዳርጌ አበበ ደራሲ ስለነበሩ ልጆቻቸውን በንባብ ፍቅር ኮትኩተው  ነው ያሳደጓቸው። ይህ ፍቅር እየጎለበተ ሄዶ፣ ዘላለም ወደ ጸሀፊነት አሳደገው። ይህን መጽሐፍ ማንም ሰው ቢያነበው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ በተገቢው ሰው እንደተተረከለት  ይገባዋል። ደራሲው ይህንን ጥራዝ ለገጸ ንባብ ለማብቃት በአያሌው ተጉዟል። ጉዳዩ የሚያገባቸውን በርካታ ባለሙያዎች፣ የባለታሪኩን ቤተሰቦች አነጋግሯል። በየቤተ መጻሕፍቱ ያጋጠሙትን ማህደሮች በቅጡ መርምሯል። ይህንን ወሳኝ ጥረት በማድረግ ድንቅ ጥራዝ ለገጸ ንባብ አብቅቷል።
መጽሐፉ በ13 ምዕራፎች፣ በበርካታ ንዑስ ምእራፎች የተከፋፈለ ነው። አንብቤው እንዳጠናቀቅኩ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአንደኛው ስራቸው ላይ የአድዋውን ጦርነት ከፋሽስት ወረራ ጋር አወዳድረው፣ አስተውሎታቸውን ለተደራሲያን ሲያጋሩ ያሉትን አስታውሳለሁ፡፡ “ኢጣሊያኖች መሳሪያቸውንና ስንቃቸውን በአጋሰስ አጓጓዙ፣ እኛም እነዚህን ከብቶች ተጠቅመን ጦር ግንባታ ደረስን። ከአርባ ዓመታት በኋላ ፋሽስቶች በአየር መጡ፣ እኛ ግን እዚያው በከብት ማጓጓዣ ላይ ነን”  ይሉናል። በወቅቱ ይህንን አባባላቸውን ሳነብ “ድንቅ አስተዋሉት” ማለቴን አስታውሳለሁ። አመታት ተቆጥረው  ይህንን የካፕቴን ዘላለምን መጽሐፍ ሳነብና የተደረገውን ጥረት ሳስተውል  ከፕሮፌሰር መስፍን ተቃራኒ ቆሜአለሁ።
ኢትዮጵያ ወደ አቪዬሽን ሳይንስ ለመግባት ጥረቱን ሀ ብላ ስትጀምር፣ በስውርና በግልጽ አያሌ አደናቃፊዎች ነበሩባት። አውራዋ ጣሊያን ስትሆን፣ አባሪ ተባባሪዎቿ እንግሊዝና ፈረንሳይ ነበሩ። ተቀዳሚ ኃይለሥላሴ  በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ሊያርቁት ጥረዋል። የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች እራሷን እንዳትከላከል፣ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ  እንዳታስገባ ያግዳሉ። ምንም አይነት ተዋጊ  ጀት እንዳይኖራትም አደናቅፈዋታል። አስተዋዮቹ አባቶች በድርድሩ ብርቱ ሆነው ነው፤ ለትራንስፖርት፣ ለፖስታ ማመላለሻ በሚል ሰበብ የአቪዬሽኑን መሰረት የጣሉት። የፋሽት ወረራ እስኪከሰት ድረስ  እጹብ ድንቅ  የሚሰኝለትን የአቪዬሽን ታሪክ ተሰርተዋል። በዚያ ሁሉ አደናቃፊዎች የፍጥኝ የመታሰርን ያህል በሚከብድ መንገድ ተጠፍረው በሚያስደንቅ መልኩ፣ ለዛሬው እርሾ ለሆኑት ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ድንቅ መሰረት አኑረዋል። የአብራሪዎቹን ሥራ ስንመረምረው፣ መኳንቶችን  ከአንዱ ጠቅላይ ግዛት ወደ ሌላው  አጓጉዙዋል። የፖስታ ማመላለስ፣ ሕመምተኞችንና እስረኞችን የማጓጓዝ እንዲሁም ከአየር ላይ የጠላትን እንቅስቃሴ ፎቶ በማንሳት ለወገን መረጃ ሰጥተዋል። በክፉው ጊዜ ለሠራዊቱ ትጥቅና ስንቅ  አቅርበዋል። በጦርነቱ ወቅት በሚያስገርም ብቃት የተሰጣቸውን ግዳጅ ተወጥተዋል። ይህንን በማድረግ ሳይወሰኑ ኢትዮጵያውያን አብራሪዎችና  መካኒኮች ዘመኑ አፍርቷል። ይህ ታላቅ ጥረት በጠላት ወረራ ሙሉ ለሙሉ ሲደናቀፍ፣ አብራሪዎቹ መትረየስ ታጥቀው ባቡር እስከ ማጀብ ደርሰዋል። በአጠቃላይ ይህንን ድንቅ ጥረት ስመረምረው፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ልፋት  ወደ ትቢያነት ቀይረው አገሪቱን ወደ ኋላ ቀርነት ለመመለስ በኢትዮጵያ ስልጣኔ ላይ የመጀመሪያውን አብዮት ያፈነዱት ኢጣሊያኖች ናቸው።
በእኔ እምነት፣ ኢትዮጵያ የመጣባትን የመከራ ዘመን ተጋትሮ፣ አገራችንን ወደ ድል አድራጊነት ያሸጋገራት በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የተፈጠረው ወጣት ትውልድ ነው። ይህ ትውልድ በአቪዬሽን ዘርፍ ምን ሰራ ? የካፒቴን ዘላለምን መጽሐፍ ማንበብ ማለፊያ እማኝ ነው። እኔ የትውልዱን ተአምረኝነት በዚህ መጽሐፍ ላይ አስተውያለሁ። ጥረቱ በበረራ መብቃት ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የራሷን አውሮፕላን ለመስራት ተግታለች፡፡ እማኝ የምትሆነን ፀሐይ የተባለችው አውሮፕላን ነች። ይህንን እውን ለማድረግ የጀርመኑ ጠቢብ ቬበር ለንጉሰ ነገሥቱ፣ አውሮፕላን ከውጪ ገዝቶ ከማምጣት ቁሳቁሱን አስመጥቶ አገር ውስጥ መገጣጠም ኢትዮጵያ ውስጥ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እንዲያብብ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ነገራቸው። የቬበር ፋና ወጊነት እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈው፣ ፀሐይ የተባለችው አውሮፕላን እውን ሆናለች። የሚገርመው በጊዜው ጣሊያኖች በሺህ የሚቆጠሩ አውሮፕላኖችን አውደ ውጊያ ላይ ሲያውሉ ለታሪክ አንድም አልተረፈላቸውም፤ ፀሐይ ግን ለታሪክ እማኝነት ዛሬም አለች።
አገራችንን በበረራው ዓለም ታሪክ እንድትሰራ በማድረግ ረገድ የፈረንሳውያኑ ሙሴ ማዬ እና ሙሴ ቬዴል፣ የጀርመናዊው ቬበር፣ የስዊድናዊው ካርል ጉስታፍ ቮን ሮዘር አጋርነት የማይረሳ ነው። አገራችንም ለታታሪ ልጆቿ አስፈላጊውን ሞገስና እውቅና እየሰጠች፣ እውቀቱንም በትጉህ ልጆቿ ለመቅሰም ጥራለች።
የመጀመሪያ አብራሪዎች ምርቃት መቼም የሚዘነጋ አይደለም። ወጣቶቹ ሚሺካ ባቢቼፍ (ግማሽ ጎኑ ሩሲያ ነው) አስፋው አሊ መሰረታዊውን እውቀት አዲስ አበባ እንዲያገኙ ሆኖ በረራውን ለመዋድ ጅግጅጋ ሄደው በመማር አጠናቀቁ። ከዚያም  ወደ መናገሻ ከተማ ዘልቀው ጃንሜዳ ላይ ንጉሰ ነገሥቱና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት መብቃታቸውን አሳዩ። መጀመሪያ በርሮ ያረፈው ሚሺካ ነበር። ይህንን ያስተዋሉ “ግማሽ ጎኑ ፈረንጅ ስለሆነ ነው !” ብለው አንሾካሾኩ። አስፋው አሊ ተራው ደርሶ አብሮ ሲመለስ አየር ላይ ትርኢት አሳይቶ ለንጉሡ ሰላምታ ሰጥቶ አሳረፋት። ሃሜተኛው፣ ሁሉን ፈጠራ ለፈረንጅ የሚሰጠው ፎቃቃ ሁሉ አፉን ዘጋ። የዚህን እለት አንድ ከለፍላፋ ጁሊያን የተባለ ሰው ትልቅ ስህተት ሰራ። ማንንም ሳያስፈቅድ መለማመጃ አውሮፕላኗን አስነስቼ እበራለሁ ሲል ተከሰከሰና ጉዳት አደረሰባት። በዚህም መዘዝ ከአገራችን ተባረረ። ይህንን ሰው ወደ አገራችን እንዲገባ የጋበዘው ዶክተር መላኩ በያን ነው። “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንደሚባለው የኢጣልያ ወረራ ቁርጥ መሆኑን መላኩ ሲገነዘብ አንድ አይነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብሎ ነበር የጋበዘው፤ ይሁን እንጂ እርባና ቢስ ነበር። መላኩ ከዚህ ስህተቱ  በመማሩ በቀጣይ ወደ አገራችን እንዲገባ የመረጠው ጥቁር አሜሪካዊ ጆን ቻርልስ ሮቢንሰን ግን ውሃ የሚያነሳ ተግባር ነው የከወነው። ለዚህ ውለታውም በዘመናችን  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስሙ ቦይንግ ጀት ሰይሞለታል።
በዘመኑ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ የአውሮፕላን በረራን በጣም ወደደው። ይህንንም የሕዝብ ስሜት  በወቅቱ ይታተም የነበረው “ብርሃን እና ሰላም” ጋዜጣ የዘገበው እንዲህ በማለት ነበር፤ “የአየር ባቡር እየደጋገመ ወደ አዲስ አበባ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም ደስ ብሎታል። የአየር ባቡር ሲበር ያየ ሁሉ ማጨብጨቡ፣ በደስታ መዝለሉ የሚያስገርም ነው...”፡፡
***
የፋሽስት ወረራ እውን ሆኖ ጠላት በአገራችን ላይ 500 ሺህ ወታደሮች፤ 6000 መትረየስ፤ 2000 መድፎች፤ 800 ታንክ፤ 450 አውሮፕላኖችና በርካታ መኪናዎች አሰልፋ አገሪቱ ላይ መአቱን  አዘነበች፡፡  በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 6852 በረራዎችን አከናውነዋል። ... ከአየር ላይ 1529 ቶን ቦንቦችንና 346200 የመትረየስ ጥይት ለውጊያው ተጠቅመዋል። በዚህ እልቂት ህዝብ የአውሮፕላን ድምፅ ሲሰማ መግቢያ ይጠፋዋል።
በዚህ የመከራ ወቅት ተሰርታ ለታሪክ ትረፊ ያላት ፀሐይ የተባለችው አውሮፕላን፣ በጣሊያን ተማርካ ሮም ሙዚየም ውስጥ እንደምትገኝ ካፕቴን ዘላለም ሰምቶ፣ ለማየት እናም ለአገሯ ለማብቃት ያደረገው ጥረት ድንቅ ነው፡፡ በአማላጅ፣ በበርካታ ደጅ ጥናት አውሮፕላኗን ከባለቤቱ ከወ/ሮ እስራኤል ጋር አዩዋት። ይህ ደራሲው በህይወቱ እጅግ በጣም የተደሰተበት ወቅት ነው። ጉዳዩ ያገባቸዋል ብሎ ላሰባቸው ወገኖች ሁሉ ያጫውታቸዋል። ለመጥቀስ የሮም የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነቡ አንዷ ናቸው። መንግስት ከካፕቴኑ ሥራ አሊያም ከኤምባሲው ወይም በራሱ ምንጭ ደርሶበት ፀሐይን ለማስማለስ አስፈላጊውን ጥረት ማድረጉ የሚያስደስት ነው። ያም ሆነ ይህ ጣሊያን በአየር የበላይነት ቢኖረውም፣ በብዙ መታፈን እራሱን ሆኖ በመብቀል ላይ የነበረው አየር ኃይላችንና አየር መንገዳችን በጠላት ተደመሰሱ። አብራሪዎች፣ መካኒኮቹም ተበታተኑ። ከአንድ የእጅ ጣቶች የማይበልጡት  አውሮፕላኖች ጋዩ። ያም ተአምረኛ ትውልድ የፋሽስት አብዮትን ተጋትሮ ጥቂቶች ለዘር ተርፈዋል።...
መጽሐፉ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ አገራችን በበረራው ዘርፍ ያደረገችውን ታላቅ ጥረት ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። የተሳካን በረራ፣ የደረሰን አደጋ፣ የዘመኑን ታሪካዊ ሂደት ግልጽ በሆነ ቋንቋ ተርኮልናል። ከአንድ አመት በፊት ከዚሁ መጽሐፍ ደራሲ ጋር ተገናኝተን ስናወጋ፣ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ  ጥንቁቅ እንደሆነና በዚህም የግእዝን ደረጃ በጠበቀ መልኩ ሆህያቱን እንደተጠቀመ ሲያወሳኝ፣ ካፕቴን ዘላለም አብራሪ ባይሆን ኖሮ፣ የስነልሳን ባለሙያ ይሆን ነበር ብዬ አብሰልስዬ ነበር። በመጽሐፉ ውስጥ ምንም አይነት የፊደል ግድፈት አላጋጠመኝም። እንዳልምል “እዚያው” ማለት ተፈልጎ “እዛው” ሆኖ ተጽፏል። ይህ አይነት የቃል ግድፈት ከአንድ ጊዜ በላይ አጋጥሞኛል። በሰዋሰው ስርዓት ስንማር አንድ አንቀፅ ለመጻፍ ገባ ብለን እንድንጀምር ህግጋቱ ያዙናል። ከቅርብ  ጊዜ ወዲህ ለህትመት የሚበቁት መጻሕፍት ይህንን ህግ እየጣሱ አንቀጾቹን ገባ ብለው መጀመሩን ትተውታል። ይህ ዘመን አመጣሹን አጻጻፍ ካፒቴን ባይከተል ማለፊያ ነበር። የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ እንዲህ አይነት ማለፊያ መጽሐፍ ሲያስጠርዝ እንዲህ አይነት ህጸጾችን ቢያርማቸው ጥሩ ነበር። ለወደፊቱም መጽሐፉ ለዳግም ህትመት የሚበቃ ከሆነ ያርመዋል ብለን እናምናለን። እኔ ባነበብኩት ደስ ብሎኛል፡፡ እናንተም አንብባችሁ ከደስታዬ ተጋሩኝ።
**
ከአዘጋጁ፡- ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ከ- በላይ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡
 ከጥበባዊና ወጋዊ ጸሃፊነቱ ባሻገርም የህይወት ታሪኮችን (ባዮግራፊስ) በመጻፍም ይታወቃል፡፡ ዘነበ ወላ አርታኢም ነው፡፡ ደራሲውን በኢሜይል አድራሻው፡-  ማግኘት ይቻላል፡፡ EYOB Kassa, [2/21/2024 6:42 PM]
ከአዘጋጁ፡-
 ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ከ6 በላይ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከጥበባዊና ወጋዊ ጸሃፊነቱ ባሻገርም የህይወት ታሪኮችን (ባዮግራፊስ) በመጻፍም ይታወቃል፡፡ ዘነበ ወላ አርታኢም ነው፡፡ ደራሲውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 368 times Last modified on Wednesday, 28 February 2024 21:30