Thursday, 29 February 2024 19:59

ከ200 ሚ. ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሆቴል ቅዳሜ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ ከተማ  አዲሱ ገበያ ሸገር መናፈሻ አካባቢ የተገነባውና  ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ  ተደርጎበታል የተባለው  ናሁሰናይ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ ከነገ ወዲያ  ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይመረቃል።

የሆቴሉ ባለቤቶች አቶ እሱባለው ናሁሰናይና  ባለቤታቸው ወ/ሮ ሒሩት ምህረቴ እንዲሁም የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ካሳሁን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ሆቴሉ  ደረጃውን የጠበቀ፣ ምቹ ስፍራ ላይ የተገነባና ለደንበኞቹ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆቴሉ  46 የመኝታ ክፍሎች  ያሉት ሲሆን፤ እንግዶች ምግባቸውን እዚያው እያበሰሉ የሚመገቡበት የተሟላና የተደራጀ የገስት ሃውስ ክፍሎችንም ያካተተ ነው። አገልግሎቱንም  ከአካባቢው አንፃር ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ  በሚያስችል መልኩ መደራጀቱ ተጠቁሟል፡፡

የሆቴሉ ግንባታ  ሦስት ዓመታትን  እንደፈጀ የተገለፀ ሲሆን፤ ናሁሰናይ ኢንተርናሽናል ሆቴል ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ከ70 እስከ 100 ለሚሆኑ  ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡

ሆቴሉ  ከነገ ወዲያ ቅዳሜ  የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል።

Read 368 times