Saturday, 09 March 2024 20:08

”ሠዓሊትን ፍለጋ“ እንስት ባለሙያዎችን የሚያበቃ ፕሮጀክት ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ግራር፣ የጠቢባን መናኸሪያ ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) – አሽበርግ ፕሮግራም ጋር በመተባበር፣ “ሠዓሊትን ፍለጋ የተሰኘ ሴት ሠዓሊያንን  ማብቃት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት በይፋ አስጀምሯል።
ይህ ፕሮጀክት ሁሉን አቀፍ የሴት የሥነ ጥበብ ሙያተኞችን ብራንዳቸውንና የዲጂታል ሰብዕና ከማጎልበት ባሻገር ሚዛናዊ የባህል ምርቶችና አገልግሎቶች ስርጭት እንዲሁም የአርቲስቶችና የባህል ሙያተኞች ተንቀሳቀሶ የመስራት ዕድሎችን ለማጎልበት አንዲቻል፣ ሴት ሠዓሊያን በብራንዲንግ፣ ዲጂታል አካታችነትና የንቅናቄ መፍጠሪያ መድረኮች ያካተተ ነው።
“ሠዓሊትን ፍለጋ” የዘመኑ የዲጂታል አሰራር የፈጠረውን ዓለም አቀፍና የባሕልና ጥበብ እንዱስትሪ ትስስር ያለውን ዕድል በአግባቡ የተገነዘበ ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም በዚህ ፕሮጀክት የሴት ሠዓሊያንን የብቃት ደረጃ ማጎልበትን፣ መሰረታዊ መብቶቻቸውን ለመጠበቅና በዲጂታል ሥነ ምህዳር ያለውን የተሳትፎ  ክፍተት ማጥበብ፤ የአርቲስቶች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በነፃነት የሚገልፁበትን፣ በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመስራትና ተመጣጣኝ  የገበያ እድሎችን ተደራሽ ማድረግን፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥበቃን እንዲሁም ፍትሃዊ ክፍያ ለጥበብ የፈጠራ ስራዎች እንዲኖር  አስተዋጽኦ ያበረክታል  ተብሏል። ይህ ፕሮጀክት የዲጂታል ክህሎት ስልጠናን በመስጠት የ20 ሴት ሠዓሊያንን በዲጂታል ስርዓት ውስጥ ያለውን የሥርዓተ ጾታ  ኢ-ፍትሃዊነት በማጥበብ፣ ስኬታማ የሙያ እድገት እንዲኖራቸው  እንደሚያስችል ተገልጿል ።
በፕሮጀክቱ  ለ20ዎቹ ሴት ሠዓሊያን ጋር በቅርበት በሚሰሩና ድጋፍ በሚያደርጉ ባለሙያዎች  በብራንዲንግ፣ በማህበራዊ ሚዲያ አመራር፣ ድረ ገጽ አጠቃቀም የይዘት ዝግጅትና የገበያ ልማት ስልቶች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች  እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህም ሠዓሊያኑ ስራዎቻቸውን ለታዳሚ ለማቅረብ ለሰፊው የጥበብ አፍቃሪው ማህበረሰብ ተደራሽ ለመሆንና በዓለም አቀፍ የዲጂታል ሥነ ምህዳር ውስጥ ያሉ አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለመጠቀም ያስችላቸዋል።
ፕሮጀክቱ በፈጣን እድገት ላይ የዲጂታል ሽግግርና የሰብዕና ግንባታ ያለውን ሚና በመገንዘብ የሴት የጥበብ ሙያተኞችን ተሰሚነትን ከማጎልበት ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህል ምርቶች ማስፋፋትና የባህል ትውውቅን ለማጎልበት ይሰራል።
በተጨማሪም ሠዓሊትን ፍለጋ ለ100 በጥበብ ና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድሎች የሚፈጥር ነው። ፕሮጀክቱ እያደጉ  የመጡ የቴክኖሎጂና ፈጠራ አቅሞችን በመገንዘብ፣ ቀጣዩን ትውልድ ለፈጠራ ማነሳሳትን ታሳቢ አድርጎ ይሰራል ተብሏል። ይህ ፕሮጀክት የባህልና የጥበብ ዘርፉ ላይ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የፈጠራና ጥበባትን ስራዎች በማበረታታት፣ ብዝሃ ባህልን የሚያጎለብቱ ስራዎች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት  በተግባር የሚያሳይበት እንደሆነም ተነግሯል ፡፡
የግራር፣ የጠቢባን መናኸሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሴሚናስ ሀደራ እንደገለፁት፤ “ ሠዓሊትን ፍለጋ ፕሮጀክት ሴት ሠዓሊያን ያላቸው ፈጠራና ተሰጥኦ ተገቢውን እውቅና አንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮጀክት  ሲሆን   ግራር፣ የጠቢባን መናኸሪያ  ከዩኔስኮ - አሽበርግ ፕሮግራም ጋር በመተባበር  ሴት የሥነ ጥበብ ሙያተኞችን አቅም ለማጎልበትና ለማብቃት እንሰራለን ብለዋል ።
በዚህ ፕሮጀክት የዲጂታል ክህሎት ስልጠናን በመስጠት፣ የዲጂታል ሰብዕና መገንቢያ አሰራሮችን በማልማትና በመተግበር የሴት ሠዓሊያ በዲጂታል ስርዓት ውስጥ ያለውን የሥርዓተ ጾታ ኢፍትሃዊነት በማጥበብ እንዲሁም አካታች እና ፍትሃዊ የጥበብ እና ፈጠራ ሥነ ምህዳር እንዲጎለተ በመስራት ሴት ሠዓሊያኑ በዘመናዊው የዲጂታል ዓለም ውስጥ ጉልህ ድርሻ አንዲኖራቸው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡

Read 409 times