Saturday, 09 March 2024 20:08

የሴቶች ቀን በእናቶች ሲቀነቀን

Written by  -ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(1 Vote)

በፈረንጅ ማርች 8 ትናንት ነበር፤ ሴቶቹ የሚንቆለጳጰሱበት፤ ጥቅማቸው አለመከበሩ (አፋዊ ቢሆንም) የሚያንገበግብበቱ፤ ዘለሰኛ ስለ ሴቶች የሚዜምበቱ--

የኢፌዲሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ ቀን ሲቀረው የተጨነቀ፣ የተጠበበትን መፈክር አሰምቷል፡፡ ”ሴቶችን እናብቃ፣ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ!”

”ጥሩ“ ብለን እንቀጥል ---

እንግዲህ ሴቶች ለወንዶቹ ሁለመና ናቸው ማለት ግድ ነው፡፡ እናት ሆነው ይወልዳሉ፤ ያሳድጋሉ፤ ሚስት ሆነው ከእናት ይረከባሉ፤ለወግ ያበቃሉ፤ወግ ያሳያሉ፤ በስተመጨረሻ፤ የልጅነት ፍቅር ለማጥገብ ከእኛው ይፈለቀቃሉ፡፡ እንግዲህ አክስትና የአክስት ልጅ እየሆኑ መምጣታቸውን ሳንቆጥር ማለት ነው፤አያትም ይሆናሉ እኮ፡፡ ኸረ እህትነትም አለ፡፡

--- እኛ ከዚህ ሁሉ የሴቶች ለወንዶች ጸጋ ውስጥ ለዛሬ እናትነትን መዝዘን እናስወክላለን፡፡ ስለ እናትነት ምን ተባለ? እናቶችስ በማይገሰስ ጸጋቸው ምን አደረጉ?

ስለ እናትነት ካህሊል ጅብራን ካህሊል እንዲህ ይላል፡- “በእናትነት ጽንፍ ውስጥ ሁሉም ነገር አለ፡፡ በሃዘን ጊዜ መጽናናትን ፣ በችግር ጊዜ ተስፋ፣ በመረታት ወቅት ጽናትም አለ፡፡ እናቱን ያጣ ሰው በህይወት ከሚባርከውና ከሚጠብቀው ጽዱ ነፍስ የተናጠበ ይሆናል፡፡

“ተፈጥሮ ውስጥ የሚያስተጋባው ይሄው የእናትነት እውነት ነው፡፡ ጸሃይ ምድርን ሙቀት የምታጠባት እናቷ ናት፡፡ ጭንቅላቷን እየዳበሰች በወፎቿ፣ በወንዞቿና በጥልቅ ባህሮቿ እሹሩሩ እስክታሸልባት ወዴትም ጥላት አትሄድም፡፡ ምድርም በፈንታዋ የዛፎቿና የአበባዎቿ ወላጅ ናት፡፡ ታፈራቸዋለች፤ ትንከባከባቸዋለች፡፡ እናት ጨቅላ ልጇን ድንች አላሽቃ እንደምታጎርስ፣ ምድርም ለልጆቿ እንዲያ ናት፡፡ ዛፎችና አበቦችም ለፍሬዎቻቸውና ለዘሮቻቸው እሩሁሩህ እናቶች ናቸው፡፡ እናም እንዲህ እያለ የህይወት እናት እስከሆነችው እስከ ዘላለማዊቷ መንፈስ ድረስ ምሳሌነቱ ይቀጥላል፡፡ በጸዳልና በፍቅር የተሞላች ዘላለማዊቷ መንፈስ፡፡”

ከዚህ በላይ እናትነትን ማን አሸበራርቆ ያቀርባል? ለመሆኑ የጂብራንን ሙገሳ “በዛ“ያለ ይኖር ይሆን?
“በዛ”  የሚል ቢመጣም በዚህ ድርሳን ውስጥ አናካትተውም፡፡ ማንኳሰስ (ቢያንስ) የዛሬ ዓላማችን አይደለማ፡፡

“እናት ለልጇ ወልይ ናት” የሚለውን አባባል የሰማሁ ዕለት፣ ፊት ለፊቴ ድቅን ያሉ እናቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር እናት ”ወለላይ” (እሱ እንደሚጠራቸው) ናቸው፡፡ ገና የስምንትና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ የስብሐትን ባህርይ አጢነው፣ ለአንተ የሚሆንህ ሀገር አዲስ አበባ ነው፤ እዚህ (እርባ ገረድ) ፍየል ጠብቀህ መኖር አትችልም፡፡ እዚያ ሂድ እንዳሉት ስብሀት ይዘክራል፡፡ ከዚህ በላይ ወልይነት አለ?

ወደ ሌላ እናት እንሸጋገር ----

---- የመኮንን ሀብተወልድ፣ የአክሊሉ ኃብተወልድ፣ የአካለወርቅና የመክብብ ሀብተወልድ እናት ናቸው፡፡ ወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ ይባላሉ፡፡ አቶ መኮንን ሃብተወልድ አዲስ አበባ መጥተው የተደላደለ ኑሮ ካቋቋሙ በኋላ ወንድሞቻቸውን ለመውሰድ ወደ ቡልግ ይሄዳሉ፡፡ እናት ግን አልተስማሙም፡፡ ”አይሳካልህም” አሉ፡፡

”እንዴት?“ የመኮንን ጥያቄ ነበር፡፡

“ብትወድም ባትወድም፣ ሥመ ጥሩው (አባታችሁ) አለቃ ሃብተወልድ ተተኪ የሚኖራቸው ከእነዚህ ልጆች መካከል ነው፡፡“

መኮንን የእናታቸው ሁኔታ የማያከራክር ሲሆንባቸው፣ ወደ ነፍስ አባታቸው መምሬ ገብረ ዮሐንስ ዘንድ ሄደው እንዲያግባቡላቸው ይማጠናሉ፡፡ እናት ለነፍስ አባታቸው አልተገበሩም፡፡

“ይስሙኝ አባቴ! እኔ ህይወቴ ቆማ ይሄ አይደረግም“

“እኔ ህይወቴ ቆማ ይሄንን አላይም! እኔ የምመኘውና የምጸልየው፣ የሃብተወልድን ተተኪዎች አይቼ ለመሞት ነው፡፡----“

“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” የሚለው የዘውዴ ረታ መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፤ መኮንን ሃብተወልድ መንድሞቻቸውን መውሰድ ሳይሆንላቸው ቀርቶ ብቻቸውን ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡

ይሁንና “እናት ለልጇ  ወልይ ናት“ የሚለውን የሚያጸና አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ የወይዘሮ ያደግድጉ ነፍስ አባት ለመኮንን የጻፉላቸውን ደብዳቤ እንይ፡-

“እንደምን አድረህ ውለሃል? እኔ በስላሴዎቹ ቸርነት ደህና ነኝ፡፡ ይህን ደብዳቤ የጻፍኩልህ  አንድ የምስራች ልነግርህ ነው፡፡ ያች ጻድቅ እናትህ እመት ያደግድጉ፣ ጥር አሥራ አንድ ለአሥራ ሁለት ለቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ  አንድ ድንቅ ታሪክ  የሆነ ህልም  አይታ፣ ትናንት  እዚህ ድረስ መጥታ ነገረችኝ፡፡  አንተ መኮንን ሃብተወልድ፣ አበደላ ካኔ ቀሚስ አሸብርቀህ ፣ በወርቅ ዘቦ የተጠለፈ ካባ ደርበህ፣ ባርኔጣ አድርገህ፣ ሦስት ወንድሞችህን አስከትለህ፣ ትልቁን ቤተመንግሥት እየዞርክ ቀላድ ስትጥል አይታሃለች፡፡ ህልሟ ግልጽ ነው፡፡ ፈች አያስፈልገውም፡፡ እነዚህ ወንድሞችህ እድላቸው በአንተ እጅ መሆኑን ቸሩ ፈጣሪያችን እንደነገራት ተረድታዋለች፡፡ ባለፈው ጊዜ ነገሩ ሳይገባኝ ያስቀየምኩህን  ይቅርታ አድርግልኝ እያለች፣ ልጆቹን ወስደህ ያሰብከውን እንድታደርግላቸውፈቅዳልሃለች፡፡”

እናትነት ያልተደረሰበት ጥልቀት እንዳለው የምንረዳው እንዲህ ያለውን ገድል ስንሰማ ነው፡፡ እመት ያደግድጉ የአራቱም ልጆቻቸው ዕጣፈንታ ፍንትው ብሎ በህልም ተገልፆላቸዋል፡፡ በአፄ ኃ/ሥላለሴ ዘመን ሁሉም ወንድማማቾች በሚንስትርና በጠቅላይ ሚንስትር ደረጃ ያገለገሉ የበላይ ሹማምንት ለመሆን በቅተዋል››

አጀብ ! ብለን ከውጪዎቹ እናቶች ገድል ጥቂት እንጥቀስ….

የማርክ ትዌይን እናት

አሜሪካዊው የብዕር ሰው ማርክ ትዌይን በስተርጅና ዘመኑ የራሱን የህይወትታሪክ  ፅፎ ነበር፡፡ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ስለ እናቱ ስለ ጄን ላምፕተን እንዲህ ይላል፡

‹‹ እናቴ ከስታ አቅመ ቢስ ብትሆንም ከሷ ጋር የማይመጣጠን ሰፊ ልቦና ነበራት ›፡፡ አዎ የማንንም ሀዘንና ደስታ ሳይታክት ተቀብሎ የሚያስተናግድ ሰፊ ልብ ! እስከእርጅና ዘመኔ ድረስ ከማውቃቸው ሁሉ እናቴን የሚለያት ይሄ ነው፡፡ ሰዎች ለጥቂት ነገር ብቻ ቀልባቸውን ይቸራሉ፤ እናቴ ግን በተለይ ወደ መሞቻዋ አካባቢ ለመላው አለምና በውስጡ ላሉት ነገሮች እንዲሁም ሰዎች ሁሉ ግድ የሚሰጣት ሴት ሆና ነበር›› ለማንኛውም ነገርና ሰው ሁሉ አንድ ጆሮና ግማሽ ቀልብ ቸራ አታውቅም፤ እራሷን የምትመለከተው ሰሚ ላጡ፣ ባይተዋርነት ላጠቃቸውና ለተገለሉ ሁሉ እንደተፈጥሮዋዊ ወዳጃቸው ነው፡፡ እንስሳትም ከዚህ የፍቅር በረከቷ አትነሳቸውም፡፡

‹‹ አንድ ጊዜ ሴንት ሉዊስ ውስጥ  በመንግድ ስትጓዝ ነው ፤ አንድ ሰው ፈረሱን በጉማሬ አለንጋ ሲቀጠቅጠው ትደርሳለች፡፡ እናቴ ያንን ሰው ተናንቃ አልንጋውን ከቀማች በኋላ ክፉኛ ገሰፀችው፡፡ ያ ሰው ዳግመኛ እንደዚህ እንደማያደርግ ቃል አስገብታ ነበር፤ የጉማሬውን አለንጋ የመለሰችለት፡፡ እናቴ ለተገፉ እንስሳት የተለየ ፍቅር ታሳይ ነበር፤ ትዝ ይለኛል በ1845 ዓ.ም ላይ እናቴ ከመንገድ እያገኘች የምታስከትላቸው ድመቶች ቤታችንን አጣበውት ነበር፡፡ በዚያ ወቅት 19 ድመቶች ተሰብስበው የቤተሰቡን ኑሮ አናግተውት ነበር፡፡ የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ድመቶች አይጥ አድነው እንዲበሉ አትፈቅድላቸውም ነበር፡፡ እኛንም በወጥመድ አይጥ ይዘን እንዳንጨክን ታስጠነቅቀን ነበር፡፡

የእመት ጄኒ ላምፕተን ነፍስ በእቅፉ እንዲያኖርልን ፈጣሪን እየለመንን፣ ወደ ሾፐን ሀወር እናት እንሸጋገር፡፡

የአርተር ሾፐንሀወር እናት

የጀርመናዊው ፈላስፋ ሾፐንሀወር (1788-1860 ዓ.ም) የእናቱ ተፅኖ ያረፈበት በተለየ መንገድ ነበር፡፡ ማለትም በመኮን ኃ/ወልድ ሆነ በትዌይን ላይ የተከሰተው አይነት አዎንታዊ መልኩ ሳይሆን በአሉታዊ መንገድ ነበር፡፡ አባቱ በአርበኝነት መንፈስ የተመረዘ ከመሆኑም በላይ ፖላንዶች በወቅቱ ለአገሩ ያሳዩት ድፍረት የሚያትከነክነው፣ የሚያበሳጨውና ለመጥፎ ድርጊት የሚገፋፋው ሰው ነበር፡፡ ሾፐን ሀወር ገና የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ እራሱን በገዛ እጁ ያጠፋል፡፡ ለሾፐን ሀወር ደራሲዋ፣ እናቱም ከአባቱ የተለየች አልሆነችለትም፡፡ አባትህ ተራ ጀብደኛ ነበር›› እያለች በአባቱ ፈንታ ትወቅሰው ነበር፡፡ ለአርበኝነትና ለነፃነት አቅንቃኝት ያላትን ንቀት ከመጥፎ ስሜት ጋር ትቀበለው ነበር ፡፡ ሾፐን ሀወር በእናቱ የተነሳ ኑሮ ክፉኛ ይመረው ጀመር፡፡ የዚህ ስሜቱ ልክፍት እስከመጨረሻ ህይወቱ ድረስ አልተለየውም፡፡ በጀርመን ፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የተመዘገበውም በጨለምተኛ መንፈሳዊ አቋሙ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከዘመዱና ከጓደኛው ከባለቅኔው ባይረን ጋር እየተወያዩ ሳሉ እናቱ ትመታዋለች፡፡ የተለመደ ጭቅጭቋን ጀምራ ልጇን ከላይኛው ክፍል ወደ ታችኛው ቤት በሚወርደው ደረጃ ላይ አምዘግዝጋ ትወረውረዋለች፡፡ ሾፐን ሃወር ከእናቱ ጋር ለመለያየት ያቺ ቀን የመጨረሻው ትሆናለች፡፡ ሲለያትም እንዲህ እንዳላት ይነገራል፡፡

‹‹ያንቺ ደራሲነት የትም የትም አያደርስሽ፣ እስከ ወዲያኛው ትውልድ ድረስ ስምሽን ይዤ የምሸጋገረው እኔ ነኝ፡፡ በእኔ እንጂ እራስሽን አታስጠሪም››

እውነትም ሆነ መሰል …..

 …… ሾፐን ሀወር ይሄን ተናግሮ ከቤት እንደወጣ አልተመለሰም፡፡ ከዚያ በኋላ እናቱ ለ20 ዓመታት ያህል በህይወት ብትቆይም፣ ሾፐን ሃወር ለአንድ ቀን እንኳን መለስ ብሎ አላያትም ፡፡

ኡ ! ኡ! ኡ! ለካ ስለ ለመጥፎዎቹ እናቶች መዝገባችን ላይ አናሰፍርም ብለን ነበር? ይቅርታ !

 ደጋግ እናቶች በደጋግ መንፈሳቸው ማርች 8ን ለማስጠራት ተዘጋጅተው ስለሚገኙ እነሱን ጠቅሳችሁ የጎመዘዘውን ትረካችንን አልሱት፤

መልካም በዓል ሴቶችዬ!
***
ከአዘጋጁ፡-
ጋዜጠኛ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ከአሥር በላይ መጻህፍትን ለህትመት ያበቃ የብዕር ሰው ሲሆን፤ የሚበዙት የህትመት ውጤቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው - ልብወለዶች፡፡ የጋዜጠኝነት ልምድና ተሞክሮ ያካበተው አለማየሁ ገላጋይ፤በሥነጽሁፍ ሃያሲነቱም በእጅጉ ይታወቃል፡፡ ማህበራዊ ሃያሲም ነው፡፡


Read 632 times Last modified on Wednesday, 13 March 2024 20:55