Saturday, 09 March 2024 19:04

የሚስቴን ወገብ ይዞ የሚጨፍር ሚዜዬ አይደለም

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ዱሮ ኪዩባን ከባቲስታን አምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት እነ ካስትሮና እነ ቼጉቬራ የትጥቅ ትግል ላይ በነበሩበት ዘመን (እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በ1990ዎቹ ውስጥ ) ይነገር የነበረ አንድ ወግ ነበር። አሁን ወደ አፈ-ታሪክነት ሳይለወጥ አልቀረም። የጥንት ተማሪዎች።
“ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማ
እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ” ኢያሱ ይዘምሩለት የነበረ እንቅስቃሴ ማለት ነው።
ወጉ እንዲህ ነው።
 የኪውባው መሪ የነበሩት ፊደል ካስትሮ፣ የባቲስታን አገዛዝ ሊዋጋ ኃይል ሊያደራጅ ወደ ሜክሲኮ ይሄዳል። እዚያም አርጀንቲና የተወለደውንና ኋላ የኪውባ አብዮተኛ የሆነውን ቼ ጉ ቬራን ያገኛል። ሁለቱ ከአንድ ጠንካራ የኪውባ ተዋጊ ወታደር ጋር ጫካ ውስጥ ይመሽጋሉ። የትጥቅ ትግሉን በማፋፋም ላይ ናቸው። ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ከስፔይን ተገላግሎ በአሜሪካ እጅ መውደቅን ለመታገል እየጣሩ ነው።
የአሜሪካ መንግስት አሻንጉሊት የነበረው የባቲስታ ፉልጂኒቺዮ ጦር እጅግ አድርጎ እየበረታ፣ በአንጻሩ የታጋቾቹ ጦር እየተመናመነ ምን ማድረግ እንዳለባቸው  በጨነቃቸው ሰዓት ካስትሮ አንድ ሃሳብ አመጣ ይባላል።
“እንግዲህ ጓዶች ትግሉ እየመረረ፣ የጠላት ኃይል እያየለ እየመጣ ነው። ዕውነተኛ ታጋይነታችን፣ ቆራጥነታችን፣ ለነጻነታችን ከልብ የመቆማችን እውነተኛነት የሚለይበት ሰዓት ደርሷል። ስለዚህ ቃል እንግባ?”
“ምን የሚባል ቃል?” አለ ቼ።
“ምናልባት የጠላት ኃይል ከባድ ጥቃት አድርሶ ድንገት በእጁ ካስገባን፣ የሚያደርስብን ቅጣት፣ እኛ በሱ ላይ ያደረስንበትን ጥቃት ያህል ነው። ያው በእኛ ላይ ያለውን የጥላቻውን መጠን ያህል መሆኑ መቼም ጥርጥር የለውም። ባቲስታ ዓይኑን ካጠፋኸው ዓይንህን ያጠፋሃል። በጥይት ከቆላኀው በጥይት ይቆላሃል። እንዲያውም በዕጥፍ-ድርብ አብዝቶ፣ አንዱን በሺ መንዝሮ ነው ዋጋህን የሚሰጥህ። ስለዚህ ሁላችንም ለዓላማችን ስንል እኩል ጥቃት ማድረሳችን ከሆነ ብቻ ነው። አለበለዚያ ግን ከኛ መካከል ትንሽ ቅጣት የተቀጣ ሰው ዓላማችንን ክዷል ማለት ነው። ስለዚህ ዓላማችንን ላንክድ እንማማል።” ቼጉቬራም፣ ጠንካራው ታጋይም፣ በሃሳቡ ተስማሙ። ተማማሉ።ካስትሮ እንደፈራው ሦስቱም ተዋጊዎች ጠላት እጅ ወደቁ።
ከዚያም ለፍርድ ቀረቡ። ተፈረደባቸው። እንደየጥፋታቸው በቁማቸው እንዲቀበሩ ተወሰነ።አቀነባበራቸው የሚከተለውን ዓይነት ሆነ።
ቼ ጉቬራ ጨርሶ አይታይም። ካስትሮ ጉልበቱ ድረስ ብቻ ነው የተቀበረው። ጠንካራው ተዋጊ ወታደር ግን እደረቱ ድረስ መሬት ተቀብሯል። ይሄ ወታደር የካስትሮን እጉልበቱ ድረስ ብቻ መቀበር ባየ ጊዜ እንዲህ ሲል ወቀሰው።
”ካስትሮ ተማምለን ነበር። ከዳኸኝ። እኔን ደረቴ ድረስ ቀበሩኝ። አንተን ጉልበትህ ድረስ። የእኔን ያህል ጥቃት አላደረስክባቸውም ማለት ነው። ከሀዲ ነህ!”
ካስትሮም እንዲህ ሲል መለሰ!
“የለም የለም! አትሳት ጓድ። ጉልበት ድረስ ብቻ ወደ መሬት የገባሁበትን ምክንያት አላወቅህም። የቆምኩት!ኮ ቼ ጉቬራ ጭንቅላት ላይ ነው።
***
የራሳቸው ጭንቅላት የሌላቸው መሪዎች፣አለቆች፣ ኃላፊዎች በሌሎች ጭንቅላት መኖራቸው የተለመደ ነገር ነው። ሆኖም ውሎ ሲያድር የሌሎቹ ጭንቅላት፣ የሌሎቹ ስም፣ የሌሎቹ ታሪክ ለመኖሪያነት የሚያገለግበት ጊዜ ያልፍና ሁልህም በየራስህ ጭንቅላት ኑር የተባለ እለት የሚይዙት የሚጨብጡት የሚጠፋባቸው አያሌ ይሆናሉ። “አፍረው የተውት፣ ፈርተው የተውት ይመስለዋል” እንዲሉ፣  ለጊዜው የሚመጻደቅ ይኖራል። ቀኑ የደረሰ ጊዜ ግን ሁሉም ወደ ተገቢ ቦታው፣ ወደ ተገቢ ዕሴቱ የሚሄድበት፣ ተፈረካከሰ ያለውም ወደሚበታተንበት አቅጣጫ መጓዙ አይቀሬ ይሆናል።
አምባገነንነት ከልሂቅ እስከ ደቂቅ መከሰቻው ብዙ ነው። የየሰፈሩ ጌታ አለ እንደማለት ነው።
 የመሪ ጌታ አለ፣ የገንዘብ አለ። አምባገነንነትን አስመልክቶ ብሪታኒያዊው ባለሃብትና ታዋቂው ሰው ሪቻርድ ብራንሰን፤ “እኔ በጥሩ አምባገነንነት አምናለሁ። ዋናው ነገር አምባገነኑ እኔ ራሴ መሆን አለብኝ።” ብሏል። አምባገነኑ እኔ መሆን አለብኝ ብለው በይፋ የሚናገሩ አምባገነኖች ብዙ አይደሉም። በየውስጠ-ልቡናቸው የመጨቆን፣ የመግፋት፣ የማፈን፣ የማን-አለብኝ ባህሪ ያላቸው ሙልሙል አምባገነኖች ብቅ ብቅ በሚሉበት ጊዜ አገር ተኮነነች ማለት ነው። ሀሳዊ-ዴሞክራት የማታለያ ስብከትን (Demagogue) ያበዛል። ስሜታዊነትን ከምክንያታዊነት ያስቀድማል። በትንሽ ነገር ኩፍ ይላል-ገፁ ይለዋወጣል።
 ለማገዱ፣ ለማገቱ፣ ለማሰሩ፣ ለመግደሉ ወዘተ ሁሉ ምክንያት ይሰጣል። በየትኛውም ደረጃ ይሄን ባህሪ ይዞ የሚገኝ እሱ አምባገነን ነው። ከእንዲህ ያለው ይሰውረን ዘንድ ነው “ዕውነተኛ ዲሞክራሲ ሆይ፤ ከእኛ አትራቂ” እያልን የምንጸልየው። “የመናገር የመጻፍና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ሆይ፣ ከእኛ አትራቂ” እያልን ሱባዔ የምንገባው ለዚህ ነው። ጉባዔ ሲያቅት ሱባኤ እንዲሉ።ሁሉን በእርጋታ፣ ሁሉን በትዕግስት መከወን፣ የብልህነትና የብስልነት ምልክት ነው ይላሉ። “ተመልሰህ ለምታፍሰው፣ ቸኩለህ አታፍስሰው” ነው ነገሩ። ቸኩሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ፣ ቸኩሎ መውቀስ ቸኩሎ ማወደስ፣ ቸኩሎ መራገም ከንቱ ሆኖ ሳለ፣ ኃይለኛ አለቆችና መሪዎች የዕለት መፈክራቸው ያደርጉታል። ይህ አገርን አያሳድግም። ህዝብን ነፃ አያደርግም። ጥንቃቄ ያሻዋል።ለህዝብ ተቆርቋሪ፣ ለሀገር አሳቢ የሚመስሉ በርካታ ግለሰቦች፣ ቡድኖችም ሆኑ መንግሥታት፣ እንደሚኖሩ አለመርሳት ተገቢ ነው። በርካታ ሃሳዊ-መሢሃን እንዳሉ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
 የበግ ለምድ የለበሰ ቀበሮ ብቻ ሳይሆን፣ የቀበሮ ቆዳ የሚለብስ በግም እንደማይጠፋ ማወቅ ደግ ነው። ከነጋ ለማጨብጨብ ከመሸ ለመሳደብ የማይተኙ በርካታ የአለቃ ሚዜና አጃቢዎች “ሽቶው ውሃ ነው”  እስኪባሉ አንደኛ ማዕረግ ቦታ ሊቀመጡ ይችላሉ። የዛሬ ዕድሜ ግን በውሃ መስላ ሻማ ናት።
በሀገርና ህዝብ ጉዳይ የቲዮሪ አንጓች፣
የፖሊሲ መካሪ፣ የህግ አማካሪ፣ የቅርብ ተጠሪ፣ የሩቅ ተጧሪ የሆኑ ሰዎች፣ ቡድኖች፣  ፓርቲዎች፣ ሀገሮች ፍሬያቸው ብስል መስሎ ጥሬ፣ ምክራቸው አዛኝ መስሎ ገዳይ ከሆነ፣ “የሚስቴን ወገብ ይዞ የሚጨፍር ሚዜዬ አይደለም” የሚል ህዝብ እንዳለ ሊገነዘብ ይገባል።

Read 1103 times