Saturday, 16 March 2024 20:19

የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያማክር ተቋም የማስፋፊያ ሥራውን አስጀመረ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በቢዝነስ ማማከርና  በሎጂስቲክ ተግባራት ላይ የተሰማራው “ዋን ስቶፕ“ የተባለ ድርጅት በዛሬው ዕለት የማስፋፊያ  ሥራውን በደንበል ሲቲ  ሴንተር  የጀመረ ሲሆን፤  አዲሱ ቢሮውንም አስመርቋል፡፡

ድርጅቱ  ከ20 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን  የሥራ እድል መፍጠሩ ተነግሯል፡፡

የ“ዋን ስቶፕ” መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሚክያስ አበራ፣ ይህን ተቋም ከመመስረቱ በፊት የባህር ማዶ ባለሀብቶች አገር ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉበትን መንገድ የማመቻቸት ስራዎችን  ሲሰራ እንደቆየ ጠቁሞ፤ በሂደት ግን አንድ ተቋም መስርቶ በተደራጀ መልክ መስራት እንደሚያዋጣ በማመን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ድርጅቱን  እውን ለማድረግ መቻላቸውን ተናግሯል፡፡

በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ተገኝተው፣ እንደ “ዋን ስቶፕ” አይነት ተቋማት ለውጭ ባለሀብቶች የሚያቀርቡት አገልግሎት  ወሳኝነት አለው ብለዋል።

አንድ በአገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚሻ ባለሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የህግ  አሰራር በወጉ ተረድቶ ስራውን ለማከናወን እንዲችል ”ዋን ስቶፕ” ተገቢውን ሙያዊ እገዛ እንደሚሰጥ የገለጸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህም  እቃዎችን  በጉምሩክ በኩል ከማስመጣት ጀምሮ ሀገር ውስጥ እስከሚገቡ ድረስ ያለውን ሙሉ ሂደት መከታተልን እንደሚጨምር ጠቁሟል፡፡

ከቀረጥ ነጻ የሆኑ እቃዎች፣ ፍራንኮ ቫሉታ ኤልሲ የመሳሰሉ ኢንቨስትመንቱን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ስርአቶችን በማሳወቅና ተገቢ ሰነዶች እንዲሟሉ በማድረግ ድርጅቱ  የማማከር ሚናውን በአግባቡ ይወጣል ተብሏል፡፡

በአሁኑ ሰአት የውጭ ኢንቨስተሮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የአማካሪ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩ  ባለሙያዎች ፤ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ የደረጀች እንድትሆንና ባለሀብቱም እንዲመጣ ሀገር ውስጥ ያለው አሰራር በዘመናዊነትና በቅልጥፍና የታጀበ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡  

“ዋን ስቶፕ” ከሚያማክራቸው የኢንቨስትመንት ተቋማት መካከል ኤን ኤች ቤይ ፈርኒቸር፣ አቢሲኒያ ግሩፕ ኦፍ ኢንቨስትመንት፣ የአሊባባ ግሩፕ የሆነው ዌል ክላውድ ይጠቀሳሉ፡፡

(ምንጭ፡-ተወዳጅ የመረጃ ማእከል)

Read 929 times