Monday, 18 March 2024 20:18

‹መልሶ ማልማት፡ መልሶ ማድማት…›

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሰሞኑን አዲስ አበባ እጅጉን ተዋክባለች፡፡ በተስፋና በስጋት ማዕበል እየተናጠች ነው፡፡ ተስፋው ከተማውን በማደስ ላይ በሚገኙት የመንግሥት ኃላፊዎች ፊት ላይ ሲታይ፣ ስጋቱ ደግሞ ቦታው በሚፈርስባቸው አካላትና በአልፎ ሂያጁ መንገደኛ ላይ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ መገናኛ፣ ቦሌና የመሳሰሉት አካባቢዎች  የነውጥና የለውጥ አየር እየነፈሰባቸው ነው፡፡ አዲስ አበባን እንደ አዲስ ለመሥራት፣ መልሶ እራሷን ለማዋለድ እየተደረገ ያለው ይህ እሽቅድምድም፣ ፍጥነቱም ክብደቱም፣ ለእኔ ቢጤው ድንገቴ ነው፡፡ አዲስ አበባችን ተዋክባለች፡፡ ሁለ ነገሯ፣ ‹አሁኑኑ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ!› የምትል ሆናለች፡፡
ዘንድሮም አዲስ አበባ ለድሆች ‹ከወዲሁ ቦታችሁን ፈልጉ!› እያለች ነው፡፡ ‹ጠጋ በሉ!› እያለች ጥግ ያስያዘቻቸውና ‹ጫፍ ላይ ወራጅ አለ› ብላ ገፍትራ የጣለቻቸው ልጆቿ ቁጥር ጨምሯል፡፡ ‹እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም!› ሆኗል የዘፈን ምርጫዋ፡፡ አታስቆማቸውም፤ አታስቀምጣቸውም፤ ምናልባት  እንዲጎበኟት የመመላለሻ ፍቃድ ትሰጣቸው ይሆናል፡፡ ኮሪደሩ ግን የእነሱ አይደለም፡፡
ደግሞም ታሪክ እንደ ዘበት የተሳለማቸውና  ዘመን ያስቆጠሩ ቅርሶቿን በጥንቃቄ ሰንዳ  እንዳላስቀመጠች ያስታውቅባታል፡፡ ለእሷ አሮጌ ነገር ሁሉ አይጠቅምም፡፡
‹የገዛኸውን አዲስ ባልዲ ውሃ መያዝ አለመያዙን ሳታረጋግጥ አሮጌውን ባልዲ አትጣል!› የሚለው ብሂል ለአዲስ አበባ የሚሠራ አይመስልም፡፡
የተበጠሰው ነገር፣ ተበጥሶም እንደ አዲስ የተቀጠለው ነገር ብዙ ነው፡፡
ከእንግዲህ የምናውቃቸው ሰፈሮች እንደማናውቃቸው ሆነዋል፡፡  በነጋችን ውስጥ እነሱ የሉም፡፡ ከእንግዲህ ስማቸውና የቀደመ ምስላቸው ብቻ ነው በአንደበቶቻችን የሚደመጡት፣ በዕይታችን የሚመላለሱት፡፡ ከእንግዲህ ከላይ በተጠቀሱ ቦታዎች የተሠሩ የዘፈን ክሊፖች፣ ሥዕሎች እና ምስሎች ቅርስ ይሆናሉ፤ ከንፈር እየተመጠጡ የሚታዩ፤ ‹ለካስ ነበር እንዲህ ኖሯልና ቅርብ› የሚያስብሉ፡፡
ከእንግዲህ የዓለማየሁ ገላጋይ  ‹አጥቢያ› ልቦለድ፣ የመሀመድ ሰልማን ‹ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ› እና እነዚህን መሰል ድርሰቶች ልቦለዶች ብቻ አይደሉም፤ በራሮታዊ ስሜት የሚነበቡ መዘክሮችም ጭምር እንጂ! ሰሞኑን፣ ‹ኧረ ጎበዝ ምን እየተደረገ ነው?› ብለው ለሚጠይቁ መንግሥት፣ ‹ስጨርስ የማደርገውን ታያላችሁ› እያለ ይመስላል፡፡ እንዲህ ያለው ጉርምርምታ በፊትም ነበር፤ ወደፊትም ይኖራል፤ ነበር ይኖራልም ማለት ግን የጥያቄውን ዕድሜ ይናገራል እንጂ የአፍራሹንም የገንቢውንም ልክነት አያሳይም፡፡  ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ‹የትውልድ አደራ› በሚለው መጽሐፋቸው፣ የቦሌን አይሮፕላን ማረፊያ ሜዳ ሲከልሉ ስላጋጠማቸው ችግር ሲያስታውሱ፣ ‹‹…ብዙዎቹ ጓደኞቼ የመሬቱ ባለቤቶች ነበሩ፤ መንገዱ በመቶ ሜትር ስፋት፣ አራት ኪሎ ሜትር ሲሄድ፣ የብዙዎቹን መሬት እየቆራረጠ መሄዱ አይጠረጠርም፡፡ በሀሜት መልክ ይሁን በወቀሳ መልክ ይሁን ‹ይሄ ስንዝር መሬት የሌለው ትግሬ እኮ መጥቶ ርስታችንን በሙሉ ነቀለን› የሚሉበትም ጊዜ ነበር፡፡ እኔም በዚሁ በቀልድና በዋዛ መልስ ‹አዎን ዛሬ ታለቅሳላችሁ፤ ነገ ግን የልጅ ልጆቻችሁ የሚደሰቱበት ሳይሆን አይቀርም፡፡ /…/ ላገሪቱ ደግሞ ታላቅ ሃብትና ለሕዝቡም ዕድገት ደህና መንገድ ሊሆንይችላል…እላቸው ነበር›› ብለዋል፡፡
መንግሥት አገር እየሠራሁ ነው፣ ነው የሚለው፤ ‹ከተማዋን እያበለጸግሁ!›፡፡ ለሚከፉበትም ከላይ ልዑል ራስ መንገሻ የመለሱት ዓይነት መልስ ነው የሚሰጠው፡፡
እርግጥ በፈረሱ ቦታዎች ያማሩ ነገሮች እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ሆኖም ያ ያማረ ነገር ለማየት ተብሎ ደሃ የበደለኞችና የሀብታሞች መሸጋገርያ ድልድይ እንዲሆን መፍቀድ ተገቢ አይደለም፡፡ ምን ተደረገለት ነው? ጥያቄው፡፡ አቤቱታው የት ወደቀ?
መውደቂያቸውን ሳያዘጋጁ፣ ሳይዘጋጅላቸው፣ አዋክቦ ማስወጣት ‹ምን እንዳታመጡ!› የሚል ድምጸት አለው፡፡ ይሄ ደግሞ ውጤቱ ግልጽ ነው፡፡ የተበዳይን ጩኸት የማይሰማ መንግሥት አንድም የነቃፊውን ቁጥር ያበዛል፤ አንድም የህልሙን ተጋሪ ዜጎች  በፈቃዱ ያሰናብታል፡፡
ትልቁ ነገር ሰፈር ብቻውን እንደማይፈርስ መገንዘቡ ላይ ነው፡፡ ሰፈር ቋተ ብዙ፡፡  ሰፈር መስፈርያም መሳፈርያም ነው፡፡ ራሱን በሰፈሩ ቁና የሚሰፍር ጥቂት አይደለም፡፡ በሰፈሩ ወደ ሚፈልገው ዓለም ኳትኖ የሚመለስ ተሳፋሪም ጥቂት አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ደግሞ ሰው የሚሠራው መጀመርያ ቤቱ ውስጥ ነው፤ ቀጥሎ ሰፈሩ፤ ቀጥሎ ቤተ እምነቱ፤ ቀጥሎ ቤተ ትምህርቱ፡፡ የሰፈሩ ግን ጥብቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ የአንድ አካባቢ ሰው ሲነሳ ጎረቤታማሞች ሳይነጣጠሉ በአንድ ሰፈር ቢሰፍሩ ይሻላል የሚባለው፤ ዕድሩም ማኅበሩም ተጠናክሮ እንዲቀጥል፡፡
አንዳንዱ እንኳንስ የተወለደበትና ያደገበት፣ የሚውልበት ሰፈር መፍረሱ ሲነገረው ሰውነቱ የመፍረስ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ይሄ ሰውኛ ባህርይ ነው፡፡ ፈልገህ አታመጣውም፤ አስገድደህ አታባርረውም፡፡ ሰፈሩ እየፈረሰበት፣ ትልቅ ታሪካዊ ነገር ሊገነባበት ነው ሲባል፣ ነፍሱ ‹ጉሮ ወሸባዬ› እያለች አታዜምለትም፡፡ ምን ቢለወጥ፣ ምን ቢታደስ ባይነኩበት የሚመርጣቸው ጥቂት እጅግ በጣም ጥቂት ነገሮች ይኖሩታልና ሊከበሩለት ይገባል፡፡
አንድ ሰፈር በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ይፍረስ  ሲባል፣ ምንም ጥርጥር የለውም፣ መንግሥት ለተሻለ ነገር ቦታውን አጭቼዋለሁ ማለቱ ነው፡፡ ሰፈሩ ጨለማም፣ ኮተታም፣ የድህነት ጎተራና ማፈርያ ስለመሰለውም ጭምር ነው፡፡ ራሱን የሚያይበትና ለሌላው (በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ) ራሱን ሊያሳይበት የሚፈልገው መስታወቱ እንዲሆን በመመኘቱ ነው፡፡  የመጣው የሄደው መንግሥት ሁሉ ማኅተሙን ከሚሰፍርባቸው ሥፍራዎች መካከል ከተሞች ዋነኛው ናቸውና እንዲህ ቢሰማው ስህተት አይሆንም፡፡
ጉዳዩ፣ የሚፈርስበት ቤተሰብ አዕምሮው እንዲዘጋጅ ተደርጓል ወይ? ነው፡፡ ምነው ቢባል የሰው ልጅ ከጊዜና ከቦታ ጋር ያለው ቁርኝት ከባድ ነው፡፡
አንዳንዱ ባይጠቀምበትም ባይጠቅመውም አሮጌ ዕቃውን አይጥለውም፤ ዕቃው ትናንትናን የሚያይበት መነጽሩ ነው፡፡ ለማንም ግልጽ እንደሚሆነው፣ ለልማት ከቦታቸው ከመነሳታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ተነሺው ቤተሰብ አዕምሮው ዝግጁ እንዲሆን ሊደረግ ይገባል፡፡ ተከታታይ የማነቃቃት ሥራ ከተሰራ እያንዳንዱ የልማት ተነሺ ነገ ከነገ ወዲያ ወደተዘጋጀለት ስፍራ ሲያቀና አይወናበድም፡፡ እንደሰው ተቆጥሮ፣ እንደ ዜጋ ተመድቦ ወደተዘጋጀለት ስፍራ እንዲያቀና ሊጋበዝ ይገባል፡፡ በተጨማሪም፣ ቦታው ላይ ምን ዓይነት ልማት ሊከናወን እንደታሰበ በዝርዝር ቢነገረው፣ ‹ታዲያ እኔ እዚህ በመዘግየቴ ለውጡን ለምን አደናቅፈዋለሁ?› ማስባል ነበረበት፡፡
ይህ የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ መልሶ ማድማት ሲሆን አስተውለናል፤ ብዙ ተብሎለታል፤ ከየቦታው የተነሱ ሰዎች ማኅበራዊ ሕይወታቸው ተመሳቅሎዋል፤ እሴታቸውን በግድ ተነጥቀዋል፤ ያልተገባ የካሳ ክፍያ እንዲቀበሉ ተገደዋል፤ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ከተከበሩበት ቦታ ተነስተው ወደ ባዶነት የተሸጋገሩ፣ በዝቅተኛነት መደብ የኖሩ ብዙ ናቸው፡፡
ዜጋ ዜጋ ነው፤ አንድም ይሁን አስራ አንድ፣ ሰባ ሰባትም ሆነ ሰባት መቶ ሰባ ሰባት ያው ነው፡፡ ቁጥር አይደለም ጉዳዩ፡፡ እናም የማንም ሰብዓዊ መብት መረገጥ የለበትም፤ ማንም ለጭንቀት መዳረግ የለበትም፤ የእሱ ክፉኛ መጎዳት እኔንም ይመለከተኛል፤ ውሎዬን ያጨልመዋል ብሎ ማሰቡ ነው የሚያዋጣው፡፡
ሌላው ጉዳይ -ከምንም ነገር በላይ - እነዚህ ከየቦታው በልማት ሰበብ የተነሱ ቤተሰቦች ሰማዕታት ናቸውና በቂ ዕውቅና/ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ እምናለሁ! ወደድንም ጠላንም እነሱ ባይነሱ፣ እነሱ ዋጋ ባይከፍሉ፣ በውድም ሆነ በግድ ተነሱ ሲባሉ እሺ ባይሉ፣ ለሁከት ቢነሳሱ የምናያቸውን ነገሮች አናያቸውም ነበር፡፡ ‹እንበለ ደም ሰማዕትነት› የሚባል ነገር አለ በሃይማኖት ትምህርት፡፡ እኔ እንደገባኝ ‹እንበለ ደም ሰማዕት› የሚባሉት በሰደፍ ባይመቱም፣ በሰይፍ ባይቀሉም ከሰማዕትነት እኩል ሊያስቆጥር የሚችል ተጋድሎ የፈጸሙ ናቸው፡፡ እነዚህ በየስፍራው በልማት ተነሺነት ተመዝግበው ኑሯቸውን የቀጠሉ፣ የሰፈሩበት ቦታ ምቹ ስሜት ያልፈጠረባቸው፣ በግድም ቢሆን ከራሳቸው ቀንሰው ሰጥተዋልና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
**

ሲጮሁ “ያልተሰሙት” የቤተክርስቲያን ደወሎች!

 

 


ከአዘጋጁ፡-
 እንዳለጌታ ከበደ፤  የ14 መጻሕፍት ደራሲ ሲሆን፣  ከሥራዎቹ መካከል፣ ‹ከጥቁር ሰማይ ሥር›፣ ‹ደርሶ መልስ›፣  ‹በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ› እና  ‹ኬር  ሻዶ›.  ይጠቀሳሉ፤  የዛጎል የመጻሕፍት ባንክ መሥራች፣  የነገረ መጻሕፍት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፤ የፎክሎርና የሥነጽሑፍ ተመራማሪም ነው፡፡

Read 1218 times Last modified on Monday, 18 March 2024 20:26