Saturday, 23 March 2024 20:26

በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዋች

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

· ከ53 አገራት ከ5000 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል፤ በ29 የስፖርት ዓይነቶች 242 ውድድሮች ተደርገዋል፡፡
           · ኢትዮጵያ 15 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ፣ 6 የብርና 4 የነሐስ)
           · በ800 ሜትር በምርኩዝ ዝላይ እና በብስክሌት ፈር ቀዳጅ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
           · ጋና ለመስተንግዶ ያወጣችው አጠቃላይ በጀት እስከ 250 ሚሊየን ዶላር ነው
           · የአፍሪካ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ለኢትዮጵያ እስከ 15 ቢሊየን ብር በጀት ያስፈልጋል፡፡


        በጋና እየተካሄደ የሚገኘው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ ይፈፀማል። የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ወደ የምታስተናግደው 33ኛው ኦሎምፒያድ በሚያሸጋግረው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ 53 የአፍሪካ አገራትን የወከሉ ከ5000 በላይ አትሌቶችን ተሳታፊ ሲሆኑ በ29 የስፖርት አይነቶች 242 ውድድሮች በ15 ቀናት ውስጥ ይከናወኑበታል።
ኢትዮጵያ ከጨዋታዎቹ ፍፃሜ በፊት 15 ሜዳሊያዎች (5 የወርቅ፤ 6 የብርና 4 የነሐስ) በማግኘት በሁሉም ስፖርቶች በሜዳሊያ ስብስብ የደረጃ ሰንጠረዥ ከ41 የአፍሪካ አገራት 10ኛ ስትሆን በአትሌቲክስ ደግሞ ከናይጀርያና ከኬንያ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ ላይ  ተቀምጣለች። በአህጉዊው ውድድር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው  በሴቶች 5000 ሜትርና በወንዶች 10ሺ ሜትር አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የበላይነት ማሳየታቸው፤ በሴቶች 800 ሜትር፤ በምርኩዝ ዝላይ በርምጃ ውድድሮችን በብስክሌት ከወርቅ እስከ  ነሐስ ፈርቀዳጅ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በአፍሪካ ጨዋታዎቹ ፍፃሜ በፊት ለኢትዮጵያ 5 የወርቅ ሜዳሊያዎች የተጎናፀፉት በወንዶች 3000 ሜ. መሰናክል ሳሙኤል ፍሬው ፤ በሴቶች 5000ሜ መዲና ኢሳ፤ በሴቶች 800 ሜ ፅጌ ድጉማ ፤ በወንዶች 10ሺ ሜ ንብረት መላኩ እና በወንዶች 20 ኪሜ የርምጃ ውድድር ምስጋናው ዋቁማ ናቸው። ስድስት የብር ሜዳሊያዎችን  በሴቶች 5000 ሜ ብርቱካን ሞላ፤ በወንዶች 10ሺ ሜ ገመቹ ዲዳ፤ በሴቶች 10ሺ ሜትር ውዴ ክፍሌ፤ በሴቶች 20ኪ ሜ የርምጃ ውድድር ስንተየሁ ማስሬ፤ በግማሽ ማራቶን ዘውዲቱ አደራውና በብስክሌት ሀ-23 የሰዓት ውድድር ከ5 ጎርጎራ ናቸው። አራቱን የነሐስ ሜዳሊያዎች በሴቶች 5000 ሜትር መላክናት ውዱ፤ በሴቶች 10ሺ ሜትር ትካን በርሄ፤ በሴቶች 3000 ሜትር መሠናክል ሎሚ ሙለታና በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ አበራ አለሙ ናቸው።
በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ በዘጠኝ ስፖርቶች 149 ስፖርተኞች ነው ያሳተፈች ሲሆን አምስቱ የኦሊምፒክ ውድድሮችና አራቱ የኦሊምፒክ ውድድር ያልሆኑ ስፖርቶች ናቸው። አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌት፤ ወርልድ ቴኳንዶ ዝላይና ዲስከስ ውርወራ ናቸው።
ከ13ኛው አፍሪካ ጨዋታዎች በፊት
ኢትዮጵያ ከ1965-2019 በተሳተፈችባቸው 12  የአፍሪካ ጨዋታዎች በሁሉም ስፖርቶች ያገኘችው 174 ሜዳሊያዎች  45 የወርቅ ፣ 54 የብርና 75 የነሐስ) የነበረ ሲሆን በምንጊዜም ውጤት ከ50 አገራት 8ኛ ደረጃ ላይ የተመዘገበ ነው። በአትሌቲክስ ደግሞ ከ41 አገራት 4ኛ ደረጃ ይዛ የነበረችው 138 ሜዳሊያዎች 42 የወርቅ ፣44 የብርና 52 የነሐስ ሲሆን ይህም በከፍተኛ ውጤት አራተኛ ላይ የሰፈረ ነው። በተያያዘ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ከአክራው ውድድር ጋር በማያያዝ ባሰራጨው የስታትስቲክስ መዝገብ በኦሎምፒክ ፤ በዓለም ሻምፒዮና፤ በአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች 4 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ከተጎናፀፉ ምርጥ የአፍሪካ አትሌቶች ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ቀነኒሳ በቀለ ፤ መሠረት ደፋርና ደራርቱ ቱሉ ናቸው። ሌሎቹ ካስተር ሴማኒያ ከደቡብ አፍሪካ፤ ማርያ ሞቶላ ከሞዛምቢክ እንዲሁም አስቤል ኪፕሮፕ ከኬንያ ናቸው።

ከጋና በኋላ ግብፅ ከዚያስ?
ጋና  13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት የበቃችው ለመስተንግዶ የተፎካካሪዋቿ የነበሩትን ናይጄሪያና ቡርኪናፋሶ በመርታት ነው፡፡ በ2018 መስተንግዶው ከተሰጣት በኋላ በ2024 ከአፍሪካ ህብረት ጋር ውል በመፈረም አዘጋጆቹን በይፋ ተረክባለች፡፡ የመክፈቻና መዝጊያ ስነስርዓት የተስተናግደው አክራ በሚገኘው እና 40ሺ ተመልካች በሚይዘው በአክራ ስፖርት ስታዲየም ነው፡፡ ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማቶች የጋና ዩኒቨርስቲ ስፖርት ስታዲየም፣ ቦርቴይን የስፖርት ኮምፕሌክስ  ለቤት ውስጥ ውድድሮች፣ ለሆኪ እና ለክሪኬት የሚሆን ሜዳዎችና የቦክስ መጋጠሚያ ናቸው፡፡ የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ እና ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች በመክፈቻው ስነስርዓት መገኘታቸው የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያመለክታል። አህጉራዊ ውድድሩ በ2023 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በውድድሩ አዘጋጆች መካከል በነበረ የገበያ መብቶች አለመግባባት ወደ 2024 ተዘዋውሮ ነው በጋናም መዲና አክራ ላይ ለመካሄድ የበቃው፡፡ ውድድሩን ለማዘጋጀት የጋና መንግስት ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ  በጀት ያወጣ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት፤ የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበርና የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር ትብብር አድርገዋል፡፡ የአፍሪካ ጨዋታዎቹን የጋና ሶስት ከተሞች  አክራ፣ ኩማሲና ኬፕ ኮስት በሚገኙ የስፖርት መሰረተልማቶች  ሲያስተናግዱ በከፍተኛ ወጪ ግንባታ፤ እድሳትና ቁሳቁስ በማዘጋጀት ነው፡፡ የጋናው ሚዲያ ግራፊክ ኦንላይን እንደዘገበው ቦርቴይዋን የተባለው ግዙፍ የስፖርት ኮምፕሌክስ የቤት ውስጥ ስፖርቶችን ለማስተናገድ ሲገነባ 145 ሚሊየን ዶላር ወጪ ሆኖበታል፡፡ የጋና ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በ16 ሚሊየን ዶላር እድሳት የተደረገለት ሲሆን የአትሌቶች መንደር የተገነባው ደግሞ በ148 ሚሊየን ዶላር ነው፡፡  
ኢትዮጵያ በየአራት ዓመቱ የሚካሄደውን የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ለማስተናገድ መፈለጓ ያስደስታል። ከአክራ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በአፍሪካ ጨዋታዎች ቴክኒክ ኮሜቴ ስብሰባ ላይ በ2031 እኤአ ላይ 15ኛውን የመላው አፍሪካ ጨዋታ ለማዘጋጀት በኢትዮጵያ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ከጋና መስተንግዶ ለመረዳት እንደሚቻለው የአፍሪካ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገር እስከ 15 ቢሊየን ብር በጀት ያስፈልገዋል፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን እና የአፍሪካ ህብረት በ2027 እ.አ.አ 14ኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች እንድታስተናግድ የመረጡት የግብፅ መዲና የሆነችው ካይሮ ነው፡፡ 

Read 333 times