Saturday, 23 March 2024 20:41

ወይ አዲስ አበባ …!

Written by  ብርሃነ ዓለሙ ገሣ-
Rate this item
(2 votes)

 አዲስ አበባ፡፡ “ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ፣ አገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ?” የክረምቱ ዳመና ዝናቡን ወደ መሬት ሊደፋ ተንጠልጥሏል፡፡ የአዲስ አበባ መተላለፊያ መንገዶች ውኃ አቁረው ጭቃ በጭቃ ሆነዋል፡፡ ላቁጠዋል፡፡ ያኔ ኮብልስቶን ብሎ ነገር የለማ፡፡
ከሰባት ቤት ተወርውሬ አዲስ አበባ ላይ አረፍኩ፡፡ የሐምሌ 1964 ክረምትና አዲስ አበባ፡፡ አዲስ አበባ አይኗን ለመግለጥ ክንብንቡዋን እያነሳች ነበረች፡፡ የወቅቱ መሪ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁሉም በእጃቸው፣ ሁሉም በደጃቸው ነበር፡፡ እዚህም እዚያም ጉርምርምታዎችና እሮሮዎች  ቢኖሩም፣ የስልጣን ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በኋላ በ1967 ዓ.ም መጀመሪያ ያበቃል ብሎ የገመተም ሆነ የተነበየ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ምክንያቱም መለኮታዊ ስልጣን የተጎናጸፉ ናቸው ተብሎ ይታመን ስለነበር ነው፡፡


ክፉና ደጉን መለየት እንደ ጀመርኩ ጃንሆይን በተደጋጋሚ ሥማቸውን መስማት ጀመርኩ፡፡ የአባቴ እናት (አያቴ) ወ/ሮ ኬረዢ ወማ፣ ቡና ተፈልቶ እንደወረደ ሁሌም ይመርቃሉ፡፡ “ጃንሆይ የዋሮም የግቦ” (ጃንሆይ በሰላም ውለው ይግቡ እንደ ማለት)፡፡ ለጃንሆይ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማቸው ከተማጸኑ በኋላ ወደ ቤታችን ይመለሳሉ፡፡ ሸረኛ ምቀኛ ዝም ጸጥና ለጥ እንዲል ይመኛሉ፡፡ አያቴ ሲመርቁ ጀማው በኅብረት፣ “አሜን!” ይላል፡፡
የእኔ ትኩረት ግን የቡና ቁርሱ ላይ ነው፡፡ እንደ ወተት የሚጣፍጥ የ“አወዳወ” ገብስ ቆሎ ይቀርባል፡፡ ወ/ሮ ኬረዢ የነኩት ሁሉ የሚጣፍጥላቸው አጅየት (ሴት ወይዘሮ) ነበሩ፡፡ ከእሳቸው እጅ ምግብ ለመቀበል እንሻማ ነበር፡፡ መቼስ ትዝታ አያረጅም፤ ዕድሜ መስተዋት ነው፡፡ እያደር አያቴ ዘወትር ጧትና ማታ በቡና ሥነ ሥርአት ላይ ሥማቸውን የሚያነሷቸው ጃንሆይ የሚመርዋት አገር ዋና ከተማ አዲስ አበባ መጥቼ፣ መኖሪያቸው የሆነውን ቤተ መንግሥት ከአጥር ውጭ ለማየት በቃሁ፡፡ ቀኃሥ የሚል የተበየደበት አጥር፡፡


ጃንሆይ፣ በየሣምንቱ ቅዳሜ ቢሾፍቱ ይሄዱ ስለነበር ሰው ተሰልፎ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለተሰለፈው ሕዝባቸው በአጋፋሪያቸው አማካይነት የቃሊቲው የኮነናል ቤ ዳቦ ሲወረወር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለእኔ ዳቦ ባይደርሰኝም፣ ለወሬው ግን ባይተዋር አልነበርኩም፡፡
ዝነኛው የቃሊቲ ኮነናል ቤ ዳቦ ጣት ያስቆረጥም ነበር፡፡ አባቴ ጧት፣ ጧት ከቃሊቲ ሆቴል ወተት አዝዞልኝ ከበላሁ፣ ምሣ ብውልም ግድ አልነበረኝም፡፡ ቃሊቲ ሆቴል በወቅቱ ዝነኛ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን ያየሁትም እዚህ ነው፡፡ የተመረጡ ሴትኛ አዳሪዎችም ለሆቴሉ ተጨማሪ ውበትና ድምቀት እንደነበሩ መካድ አይቻልም፡፡
ይህ ታሪክ በሚከወንበት ሰዓት የኮነናል ቤ ዳቦ ዋጋ አስር ሣንቲም፣ ለስላሳ አስራ አምስት ሣንቲም፣ ቤንዚን 42 ሣንቲም፣ ናፍጣ 38 ሣንቲም፣ ከወልቂጤ አዲስ አበባ (መናኸሪያ ተክለኃይማኖት እያለ) የትራንስፖርት ዋጋ ብር 3.10 እንደነበር አንጋፎች ነግረውኛል፡፡
ወይ አዲስ አበባ …
ዛሬስ? ዛሬማ ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ አለ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ሆኖ በቅርቡ ያጋጠመኝን ባካፍላችሁ ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ሰሞን አጎቴ ስላረፈ ገጠር ዘልቄ አንድ ቀን አድሬ ተመለስኩ፡፡ ከእኔ ጋር የነበሩ ተሳፋሪዎች ተንጠባጠቡ፡፡ ቀድመን የተገኘነው ኮንትራት የያዝነው መኪናችን ጭቃ ይዞት ስለነበር “ግፉ” አለን - ሾፌር፡፡ መግፋት ጀመርን፡፡ “ኧረ ግፉ ገና ነው፡፡ ግፉ፣ ግፉ …” አለን፡፡ እኛም ሳንለግም ገፋን፡፡ ለካ እኔ ስገፋ ተጎድቻለሁ፡፡ ወገቤን ማለት አበዛሁ፡፡ ከአሁን አሁን ይተወኛል ብዬ ተስፋ ባደርግም አልሆነም፡፡ ወገቤ ተወለካክፎ ኖሮ ጊዜ ጠብቆ ይነሳብኝ ጀመር፡፡
ለባለቤቴ፣ “ወገቤን” ብዬ በተደጋጋሚ አስተዛዝኜ ነገርኳት፡፡ “ልሽህ” ሳይሆን “ታሸው!” አለችኝ፤ ዓይኗን ግድግዳው ላይ ሰክታ፡፡ እንዲሁ እያመነታሁ ሳታሸኝም፣ ሳልታሽም፣ ሳታሳሸሽኝም ዓመታት እንደ ወንዝ ዳር አፈር እየተሸረሸሩ እንደዘበት አለፉ፡፡ የኋላ ኋላ እያሰለሰ ሲሰቀስቀኝ አስበዳሪ ማፈላለጉ የግድ ሆነብኝ፡፡ ከራስ በላይ ነፋስ ብዬ ለመታሸት ቆረጥኩ፡፡ ቦሌ አካባቢ አለ ስላሉኝ ማልጄ ወጣሁና ፈልጌ አስፈልጌ ሐኪም ቤቱን አገኘሁት፡፡ የሚፈልጉትን ተቀበሉኝና እንዴት እንደ ጀመረኝ በወረቀት ሪፖርት አቅርብ አሉኝ፡፡ አቀረብኩ፡፡ የወረቀቱ ስላልበቃቸው ኢንተርቪው አደረጉኝ፡፡
“እንዴት ጀመረህ?”
“ያለ አቅሜ መኪና ገፍቼ”
“እዚህ አገር ያለአቅም የሚገፋ ነገር ይበዛል ልበል?”  
ማንና ከየት እንደሆነ ማወቅ ፈለግኩ፡፡ ለማሽተት የሰነግኩትን አፍንጫዬን ከፈትኩ፡፡ ተናግሮ ከሚያናግር እንዲሰውረኝ ደጋግሜ አማተብኩ፡፡
“ምነው?” አለኝ፤ ባለ ነጭ ጋውኑ፡፡
“ሕመሜን እያዳመጥኩ ነው”
ብዙ አናግሮ ከባለደንታዎች ጋር ሊያጣላኝ መሆኑ ሲገባኝ ፊት ነሳሁት፡፡ በብጥሌ ወረቀት ላይ በሐኪምኛ ጽፎ ወደ ባልደረባው ዘንድ ሰደደኝ፡፡ ተባብረውና ደማምረው ለሰባት ሺህ - ሁለት መቶ አምሳ ጉዳይ ወሰዱብኝና “ደምና ውኃ ሽንት” እንፈልጋለን አሉኝ፡፡ ነርሷ ክንዴን ወግታ ሳትሰስት ደሜን ቀዳች፡፡ ሽንቴንም በፊንጃል ወሰደች፡፡ የሚገርመው ክንዴን ወግታ፣ ደምን ያህል ውድ ነገር ወስዳብኝ አመስግኛት ወጣሁ፡፡ ተወግቶ የሚያመሰግን ከእኔ ሌላ በምድር ላይ ተፈጥሮ ይሆን?
ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ የደምና የሽንት ውጤት ደረሰ ተባልኩ፡፡ ውጤት በኦን ላየን የተላከለት ነጭ ጋውን የለበሰው ሐኪም መሳይ ሰው፣ ሰፋ ያለ ፕሬዘንቴሽን ሰጥቶኝ ሲያበቃ፣ በመስቀለኛ ጥያቄ አጣደፈኝ፡፡ ፖሊስ ጣቢያ እንጂ ሐኪም ቤት አልመስልህ አለኝ፡፡ ምቾት እንዳልተሰማኝ ሲገባው፣ “እኔ እኮ ጠቅላላ ሐኪም ነኝ” ብሎ ወገቤን ይነካካ ጀመር፡፡ ጥቂት ነካክቶ ወረቀት ሰጥቶ ለዳግም ክፍያ ወደ ካዝናው መራኝ፡፡


ወረቀት የተላከላት አንዲት እንስት፣ ምኑን ከምን ጋር ቀላቅላ እንደደማመረችው አላውቅም ኪሴን አልቦ የሚያደርግ ክፍያ በድጋሚ ጠየቀችኝ፡፡  “የእኔ እመቤት ለአሁኑ ሕመሜ ብቻ ነው ወይስ ወደፊትም የምታሸው ታስቦ ነው?” ክፉኛ አፈጠጥኩባት፡፡ ይኸ ሰው በቁሜ (መለመላዬን) ሳይበላኝ መሸሽ እንዳለብኝ ልቡሰ ጥላዬ ነገረኝ፡፡ ቀደም ሲል ከከፈልኩት ላይ የነበረኝ መልስ እንኳ ሳልቀበል ከከተማው ሕዝብ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በላይ መቀጠል አልችልም፤ ኪሴ ባዶ ነውና፡፡ “አባብያት ባለቤቴ ብታሸኝ ይሻላል” ብዬ ወስኜ ወደ ቤቴ ሎሚ ሜዳ ሮጥኩ፡፡


አሁን አሁን የአዲስ አበባ ሕዝብ ሳየው በአስማት የሚኖር ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል የአዲስ አበባ ገበያን የተወሰኑ ዕቃዎች  (የጥቂቶቹን) ዋጋ እንመልከት፡፡ ሥጋ አንድ ኪሎ ብር 1,600.00፣ ጤፍ 100 ኪሎ ብር 16,000.00፣ ስኳር አንድ ኪሎ ብር 130.00፣ ዘይት 5 ሊትር ብር 1,100.00፣ አንድ የአበሻ ዕንቁላል  ብር 15.00፣ ሽንኩርት አንድ ኪሎ (አሁን ለጊዜው ከብር 150.00 ቀንሶ) ብር 85.00 ወዘተ. ፡፡ የውኃ፣ የመብራት፣ የግብር፣ የትምህርት ቤት፣ የቀሩት አስቤዛዎች … እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥትና የፓርቲ ወገብ የሚቆምጡ ክፍያዎችን ትተን ተራ ወጪዎችን መሸፈን መቻል በራሱ የሚደንቅ ነው፡፡ አንዳንዴ ሰው ከብረት ይጠነክራል የሚሉት ብሂል እውነት ኖሯል ለካ! ኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) በተአምር የሚኖርባት አገር ሆናለች፡፡


የኑሮ ውድነቱን ያወሳሰበው ገበያችን ሲቃኝ በዚህች ምድር ላይ አንዳች የፈጣሪ ተአምር እንዳለ በግልጽ ይታያል፡፡ ገበያው መረንና ጠረን ካጣና ለሕግ አልገዛም ብሎ መቅኖ ካጣ በጣም ቆይቷል፡፡ እኛ በቁስ ቆጠራ ላይ ተጠምደን  ቁስላችንን ዘንግተነዋል፡፡ ለካስ ድምጻዊው ቢቸግረው ነው “ጩህ ጩህ ይለኛል” ብሎ የዘፈነው፡፡ ኧረ እኛም እንጮሃለን፡፡
በደርግ ዘመን ዕቃ አስወደዱ በሚል አሻጥረኛና አድሃሪ ተብለው የታሰሩ፣ የተገደሉና ከንግዱ ዘርፍ የተባረሩ በርካቶች ናቸው፡፡ በኢሕአዴግም ኪራይ ሰብሳቢ፣ ሙሰኛ ወዘተ. የሚል ሥም ተሰጥቷቸው ተወሰደ ያልተባለ የእርምት እርምጃ የለም፡፡
 አገሬው አይቶ አይቶ ተስፋ ቆረጠና በአዝማሪ አማካይነት ግጥም አስገጠመ፡፡ “አስራ ሰባት ዓመት ቢነፋ ቢያናፋ፣ ከሰማይ ደመና ከምድር ሰው ጠፋ፡፡” በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ ግጥም ተሰማ፡፡ “በኃይለሥላሴ የተራባችሁ፣ ደርጉ እንጀራ ይዞ ሲፈልግ አጣችሁ፡፡”


አሁን ግን ለመግጠምም  ሆነ ለማስገጠም ከባድ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ገበያው በሥርአትም ሆነ በሕግ የሚመራ ስላልሆነ እኛ አዲስ አበባውያን ከመርግ የከበደ ጭነት ለመሸከም ተገድደናል፡፡ “ከቤቱ የወጣ እቤቱ እስኪመለስ፣ ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ” ብለን እናንጎራጉር እንዴ?  

Read 700 times