Friday, 29 March 2024 21:08

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃ. የተ. የግል ወኪል አከፋፋይ አሰሪ ማህበር ደረሰብኝ ያለውን በደል ገለጸ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

•  ”የቢጂአይ ኢትዮጵያ አመራር፣ ያሰርነውን ውልና የፍ/ቤት ትዕዛዝ  ጥሷል”
 
•  ”የበለጸጉና የተደራጁ ኤጀንቶችን በአዳዲስ መተካት የሚል አዲስ ስትራቴጂ መጥቷል“

ከተመሰረተ 14 ዓመት ገደማ ማስቆጠሩ የተነገረለት ቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃ. የተ. የግል ወኪል
 አከፋፋይ አሰሪ ማህበር፤ በቢጂአይ ኢትዮጵያ አመራሮች ደረሱብኝ ያላቸውን በደሎች
  ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ ላይ አብራርቷል፡፡  

ማህበሩ በፍርድ ቤት ክስ መሥርቶ ውሳኔ እየተጠባበቀም መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ስንታየሁ ገ/ሥላሴ ሐሙስ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም  በመግለጫው ላይ እንዳብራሩት፤ በመላ አገሪቱ በወኪል አከፋፋይነት የተሰየሙ የማህበሩ አባላት ቁጥር ወደ 36 የሚደርስ ሲሆን፤እኒህ አባላት ወደ 6 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት አፍሰው፣ በቂ የሆኑ መጋዘኖች ገንብተው፣ 40 ቶን የሚሆኑ ትላልቅ መኪኖች ገዝተውና በሥራቸው ወደ 4ሺ ዜጎች ቀጥረው የሚያስተዳድሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ማህበራቸው ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር በፈጠረው የሥራ ግንኙነት፣ መጀመሪያ ያቀረቡት ጥያቄ፣ ቀደም ሲል ለ1ዓመት ብቻ የተሰጠውን ኮንትራት በመገምገም፣ ለዚህ ትልቅ ኢንቨስትመንት ለሚጠይቅ ሰፊ ሥራ የአንድ ዓመት የኮንትራት ውል በቂ ባለመሆኑ የተሻለ የኮንትራት ውል ማሰር አለብን የሚል ነበር፡፡  

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፤ ለዚህ ጥያቄ  ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ያገኙት ምላሽ አዎንታዊ አልነበረም፡፡ እንደውም የ2 ወር ኮንትራት በቂ ነው የሚል የፌዝ የሚመስል ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ፡፡ ደግነቱ በኋላ ላይ እነሱም ጥያቄውን አምነውበት የ2 ዓመት ኮንትራት አስረን ወደ ሥራ ገባን ብለዋል፡፡ በመሃል ብዙ መደነቃቀፎች እንደነበሩ የሚያወሱት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ቢሆንም በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በጋር ለመስራት ወስነን ቀጠልንበት ይላሉ፡፡

የማህበሩ መሰረታዊ ሥራ ቢጂአይ የሚያመርተውን ቢራ ለገበያውና ለሚፈለጉባቸው ሥፍራዎች ማሰራጨት ነው የሚሉት አቶ ስንታየሁ፤ የትራንስፖርት ወጪውን ኩባንያው እንደሚሸፍን ጠቁመው፣ በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ሲመጣ ግን በነባሩ ታሪፍ መሥራት ባለመቻላችን የታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረብን ብለዋል፡፡

ጥያቄያችንን በተደጋጋሚ አቀረብን፤ በግንባር ሄደን አስረዳን፤ ሆኖም ሰሚ ጆሮ አላገኘንም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለአንድ ዓመት ያህል ከ8 ጊዜ በላይ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ሳናገኝ ቀረን ይላሉ፡፡ ”ጭራሽ ችግሩን በማህበር ሳይሆን በየግል ነው የምንፈታው የሚል ነገር አመጡ፤ እንደ ማህበር ዕውቅና ሊሰጡን አልፈለጉም” ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ፡፡

ጥያቄያቸው መልስ ባያገኝምና መፍትሄ ባይሰጣቸውም በኪሳራም ቢሆን አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጠሉበት፡፡ ይህን ያደረግነው በኪሳራም ቢሆን ከድርጅቱ ጋር ያለን የረዥም ጊዜ የሥራ ግንኙነት መቀጠል አለበት በሚል እምነት ነው ይላሉ፤ ፕሬዚዳንቱ፡፡ ነገር ግን እስካሁን በኪሳራ የሰራንበትንም ቢሆን ክፈሉን ብለን ስንጠይቅ፣ ሰባራ ሳንቲም ሳይከፍሉን ቀሩ ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

 የዛሬ 3 ወር ገደማ  የታሪፍ ማሻሻያውን ጉዳይ እናጠናዋለን የሚል ምላሽ ሰጡን የሚሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ይሄ እኮ የሮኬት ሳይንስ አይደለም፤ መንግሥት እንኳን ቤንዚን ሲጨምር የታሪፍ ማሻሻያ ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየሄዱ መምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ስንታየሁ፤ በመሃል ደግሞ ቢጂአይ አዲስ ስትራቴጂ ይዞ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ አዲሱ ስትራቴጂ የደረጁትንና የበለጸጉትን ኤጀንቶች በአዳዲስና ጀማሪ ኤጀንቶች መተካት የሚል ስልት የያዘ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡  ስትራቴጂው የገበያ ሽንሸናንም የሚያካትት ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህንንም ለመተግበር ለ2 ዓመት ያሰርነውን የኮንትራት ውል ጥሰዋል ሲሉ ይከሳሉ፡፡

ኮንትራቱን በመጣስ ወደ አዲስ ገበያ ሽንሸናና ኤጀንት ምልመላ ሲገቡ፣ እኛም  ምርጫ ስላልነበረን ጉዳዩን በጠበቆች አማካኝነት ወደ ፍርድ ቤት ወሰድነው ይላሉ - በቢጂአይ ላይ ክስ መመሥረታቸውን በመግለጽ፡፡ ጉዳዩ በፍ/ቤት ሂደት ላይ እያለም ጥሰቱን ቀጠሉበት፤ ማስፈራራትና ማገድ ሁሉ ጀመሩ ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ በጠበቆች አማካኝነት ለፍ/ቤት አቤት ብለን የህግ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምንም ዓይነት የገበያ ሽንሸናና ኤጀንት ምልመላ እንዳይደረግ ብሎ ፍ/ቤቱ አገደ ይላሉ፡፡  

እንዲያም ሆኖ የድርጅቱ አመራሮች  በጥሰቱ ቀጥለውበታል ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ አሁን ጠቡ ከኛ ጋር ሳይሆን ከአገሪቱ የፍትህ ሥርዓት ጋር ነው ብለዋል፤ ፍ/ቤት ያዘዘውን እየጣሱ መሆናቸውን በመግለጽ፡፡ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም መቅጠሩንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ በሰጠው ጋዜጣዊ  መግለጫ ላይ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ምላሽ ካለው፣ በማንኛውም ጊዜ መድረኩ ክፍት ነው፡፡

Read 696 times