Saturday, 30 March 2024 19:25

“ከሸኘኸኝ አይቀር መቃብሩን አሳልፈኝ”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

በቀድሞው ዘመን አንድ የወረዳ ገዢ ነበሩ፡፡ መቶ አለቃ ናቸው፡፡ ዛሬ እንደ ተረት ሊወሱ አንድ ሐሙስ ነው የቀራቸው፡፡
አንድ ቀን የወረዳውን ህዝብ በሙሉ ጠርተው “ንቃት ልንሰጣችሁ ነውና አንድ ሰው እንዳይቀር፤ የቀረ ወዮለት” የሚል ማስፈራሪያ - አዘል ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ህዝቡ በነቂስ ወጣ፡፡ ባይወጣ ምን እንደሚከተለው አሳምሮ ያውቃል፡፡
ለተሰበሰበው ህዝብ እንዲህ ሲሉ ንግግር አደረጉ፡-
“አብዮታችን በደረሰበት ደረጃ ይህ የዛሬው የንቃተ-ህሊና ማዳበሪያ ስብሰባ ቁልፍ ሚና  እንደሚጫወት ጠላቶችን ባይገባቸውም፣ በወገኖቻችን ዘንድ አንዳችም የጥርጣሬ መንፈስ የማይፈጥር ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ዛሬ የተሰበሰብነው ስለማንኛውም የሀገራችን ጉዳይ ያለንን አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ሌላ ማንኛውም ግንዛቤ የማስጨበጫ ሀሳብ እንድትሰጡና በእኔና በጓዶቼ በኩል ማናችንም ጥያቄ ለመመለስ የሚቻለንን ሁሉ እንድናደርግ በማሰብ ነው። የጓድ ሊቀመንበር አመራር የተመሰገነ ይሁንና፣ ንቃተ - ህሊናችሁ ከፍ እንደሚል ጠንካራ ዕምነት አለን፡፡ በዚህ መሰረት አሁን የምናድለውን ወረቀት ትወስዱና ስለ አብዮታችን ለመጠየቅ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ ትጽፉልናላችሁ፡፡”
በተነገረው መሰረት ወረቀት ታደለ፡፡ ጥያቄ መጠየቅ የፈለገ ሁሉ ስሙን ሳይጽፍ አቀረበ፡፡
መቶ አለቃው የመጡትን በርካታ ጥያቄዎች እየተመለከቱ ለየሚመለከተው የፖለቲካ ኃላፊዎች መደቡ፡፡ ከሳቸው አጠገብ የወጣቶች ተጠሪ፣ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ፣ የሠራተኛ ማህበር ተወካይ ወዘተ ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ መቶ አለቃ ለእነዚህ የፖለቲካ አጋሮቻቸው ጥያቄዎቹን አከፋፈሉ። ስለወጣቶቹ ከተጠየቀ ለወጣቱ ተጠሪ፣ ስለሴቶች ከሆነ ለሴቶች ጉዳይ ኃላፊዋ - በየዘርፋቸው አከፋፈሉ ማለት ነው፡፡ ኃላፊዎቹም በበኩላቸው የፖለቲካ ገለጻ አደረጉ፡፡ ከየአንዳንዱ ገለጻ በኋላም ተገቢው ጭብጨባ ተበረከተላቸው፡፡
በመጨረሻ የራሳቸው የመቶ አለቃ ተራ ደረሰ፡፡ “በዕውነቱ ሁሉም ጓዶች ተገቢውን ዕውቀትና ንቃት እንዳስጨበጡዋችሁ ከፍተኛ ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ አሁን ደግሞ በእኔ በኩል ለደረሰኝ ጥያቄ እንደሌሎቹ ጓዶች መልስና ማብራሪያ እሰጣችኋለሁ” አሉና ተደላድለው ተቀመጡ፡፡ ከዚያ ቃለ-ምልልስ በሚያደርግ ሰው ቅላፄ ቀጠሉ፡-
“ለእኔ የመጣው ጥያቄ ከዋና ዋና የፖለቲካ ጥያቄዎች ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ ይኸውም “የፓሪስ ኮሚዩን ለምን ፈረሰ?” የሚል ነው፡፡ እኔ ለዚህ ያለኝ መልስ”… አሉና ድምፃቸው በድንገት ወደ ቁጣ ተለወጠ፤
“የፓሪስ ኮሚዩን፤ ፈረሰ ፈረሰ! በቃ ምን መጨቃጨቅ ያስፈልጋል? ጨርሻለሁ” አሉና ተቀመጡ፡፡
***
“ፈረሰ ፈረሰ!” የሚል መሪ ወይ አለቃ ካጋጠመን ዕድለኞች አይደለንም ማለት ነው፡፡ የፈረሰው “ለምን ፈረሰ?”፣ “በፈረሰው ቦታ ምን ይተካ?”፣ “እንዴትስ ይህን ጥያቄ የህዝቡ ጥያቄ መሆኑን ማስገንዘብ ይቻላል?” መባል አለበት፡፡ ይህን የሚጠይቅ ሀላፊ ያስፈልገናል፡፡ ነገ የተሻለ ህይወት ይኖር ዘንድ የወደቀው እንዲነሳ፣ የፈረሰው እንዲገነባ፣ አወዳደቁንና አፈራረሱን ማወቅና ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡
“ታማኝ ነው ያሉት የስለት ዕቃ ይሰርቃል” ይባላልና የሚተማመኑበት መሪ ቀን አይቶ ይከዳል የሚል ጥርጣሬ ከህዝብ አዕምሮ አይጠፋም፡፡ ይህን ጥርጣሬ በጊዜ ካላስወገዱ ደግሞ ጥርጣሬ አድጎ ወደ ተቃውሞ፣ አድሮም ወደ ጠንካራ ፍጭት እንዳይለወጥ መጠንቀቅ የግድ ይሆናል። የሥልጣን  ሁሉ ጥልቅ ተዓምር ተለዋዋጭነቱ፣ ተሸርሻሪነቱ ከርሞም ጠዋት ያሉትን ማታ ለመካድ መመቸቱ ነው፡፡ ሥልጣን ለዚህ ኃይል ያጎናጽፋል፡፡ ስለዚህም ህዝብ ሁሌ መጠራጠሩና ለጥርጣሬው ተጨባጭ መፍቻ ካላገኘ አገር ችግር ላይ መውደቅ ጀመረች ማለት ነው፡፡ እንደ ድርቅ ሙስናና አስተዳደራዊ ኢ-ፍትሃዊነት ያለ ጎጂ ባህል ሲታከልበት፣ በችግሩ እሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ይሆናል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ለመፍታት የበርካታ ድርጅቶችን፣ ፓርቲዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን ርብርብ ይጠይቃል። በዓላማና በጠባይ ባይመሳሰሉም፣ የደም የአጥንት ቂም ቢኖራቸውም፣ ዕድሜ ልካቸውን የሚታረቁ ባይመስላቸውም፣ የችግሩ ጥልቀት ያግባባቸዋል - የግዳቸውን! የዛሬው ዕውነታ ወደድንም ጠላንም ይሄው ነው!
ሁሌ እሥር ቤት የሚያስታርቃቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ማየት አገራችን ሳትታክት አልቀረችም፡፡ “የመቀመጥ ብዛት የደረቀ ቁስል ያስፍቃል” እንዲሉ ብዙ ተቀምጠው የቆዩ ፖለቲከኞች ዋና ችግር የተረሳ ጉዳይን እየቀሰቀሱ መናቆር ነው፡፡ ይሄ ሊያበቃ ግድ ነው፡፡ ጊዜ ሳያልፍ፣ ሌላ ዕድል ሳያመልጥ፣ ጀንበር ሳትጠልቅ የአገራችንን ችግር በጥሞና ማስተዋል እጅግ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ውጤቱ፡-
“ውሎ ይደር ያሉት ነገር ዕዳ ይሆናል፤ እባብ እቤት ገብቶ ዘንዶ ይሆናል” የሚለው ተረት ነው።
መከራውን ወደ መከር ለመለወጥ ጨክኖ መታገስን ይጠይቃል፡፡ ጨክኖ መከባበርን ይጠይቃል፡፡ ጨክኖ መቻቻልን ይጠይቃል፡፡ ከማንኛውም ጉዳይ፣ ከማንኛውም ወገን፣ ከማንኛውም ሰው በላይ አገርን ለማየት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ ማግኘት ዛሬ እንደመለኮታዊ ፀጋ የሚቆጠር ሆኗል፡፡ ከችግሮቻችን ማለትም ከአስተዳደራዊ አሽክላችን፣ ከሙስናዊ ምዝበራችን፣ ከሀሳዊ-ዲሞክራሲያችን፣ ከየአሥር ዓመት የድርቅ ልደታችን፣ ከእርስ በርስ ግጭቶቻችን፣ ከየማን-አለብኝ ዕብሪታችን ሁሉ ለመገላገል ቢቆረቁረንም፣ ቢያጎሰቋቁለንም፣ በእልህ ቢያቃጥለንም---ከሁሉ ባሻገር ያለውን ተስፋ ለመጨበጥ ሁሉን በትዕግስት ተቀብሎ አገርን ማዳን ዛሬ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡
 በአሁኑ ሰዓት፤
“ከሸኘኸኝ አይቀር መቃብሩን አሳልፈኝ” የሚለው የሁላችንም ጥሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ መቃብሩን በሰላም ለመሻገር ያብቃን! አሜን!

የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 1324 times Last modified on Monday, 01 April 2024 07:59