Tuesday, 02 April 2024 16:03

አንጋፋው ሠዓሊ ጥበበ ተርፋ አረፉ !

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ጥበበ ተርፋ ማመጫ፤ በሐረር ከተማ በ1941 ዓ.ም ተወለዱ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር መድኃኒዓለም ት/ቤት እንዳጠናቀቁ ወደ አዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት) በመግባት ተመርቀዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ልምምድ ውስጥ ተዋጽዖአቸው ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ነበረ:: የሥዕል ሥራቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለዕይታ ያበቁ ሲሆን፣ በሙያው ስምና ዝና ያፈሩ አንጋፋ ሙያተኛ ነበሩ::

አቶ ጥበበ ተርፋ የሥራቸው አቅጣጫ ተወልደው ባደጉበት ሐረር ላይ በማተኮር የትላንቱንና የዛሬውን ገጿን በቀለማት እንቅስቃሴ ይገልጹ ነበረ። አቶ ታዬ ታደሰ ባዘጋጁት የሠዓልያን ታሪክ ውስጥ ጥበበ "የተለያዩ ቴክኒኮችን የሚጠቀሙ ሲሆኑ፤ የሚያደንቁት ግን ኤክስፕሬሽኒዝምን ነው" በማለት መጻፋቸው ይታወሳል::

ሠዓሊ ጥበበ ተርፋ ማመጫ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ሰምተናል:: ለመላው ቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለአለ_የሥነጥበብ_ት/ቤት ማህበረሰብ፣ ለሙያ ጓዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናት እንዲሆንላቸው እንመኛለን።

ቀብራቸው ነገ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በየካ ሚካኤል ቤተክርስትያን ከቀኑ 8:30 የሚፈጸም ይሆናል። ነፍስ ይማር።

(አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ)

Read 902 times