Sunday, 14 April 2024 20:28

አንጋፋው ሙዚቀኛ ሙሉቀን መለሠና ሥነ ቃል

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

በ1946 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አንድ ሥጦታ ተከሰተ….
…ሙሉቀን መለሠን ምድር እጇን ዘርግታ ተቀበለች፤ ጎጃም፣ ደብረማርቆስ ከተማ አጠገብ በምትገኝ አነስተኛ መንደር ተወልዶ፣ የምውት ልጅ ነውና አዲስ አበባ ኮልፌ አጎቱ ዘንድ ተከተተ፤ ኑሮ አልሆነውም…
…ተመልሶ ወደ ጎጃም ተመመ፤ የካ ሚካኤል ትኖር የነበረች አክስቱ ይዛው ትመለሳለች፤ አሁንም ፈተናው ብዙ ኖሯል፤ ሻይ አሳላፊ ሆኖ ብዙ ፏጨረ፤ ኮሬንቲ እየነዘረው ይፈታተነው ገባ፤ ወላ በስድተኛው ወር ጣጥሎ ውቤ በረሃ ከሚገኝ ‹‹ፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ›› አመለከተ፤ በደስታ ተቀበሉት፤ ፖሊስ ኦርኬስትራ ተማረከና በ1958 ዓ.ም. አንከብክቦ አመጣውና ቀጠረው…
…የሙዚቃ ሕይወቱ እንዲህ ተጀመረ…
….በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዎችን ክፍያ በማሻሻል፣ በድምጻዊነት፣ በግጥምና ዜማ ደራሲነትና በአቀናባሪነት/በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት የምናውቀው፤ ሙዚቀኛ ሙሉቀን መለሠ በርካታ ሥራዎችን ሰጥቶናል። በ1961 ዓ.ም. በሰለሞን ተሰማ ተደርሶ በፖሊስ ኦርኬስትራ የተቀናበረውን ‹‹የዘላለም እንቅልፍ›› ለመጀመሪያ ጊዜ አቀንቅኖ ተወዳጅነትን አገኘ፤ አቡበከር አሽኬ ደግሞ ‹‹ያላየነው የለም››ን ጀባ አለው፤ በማስከተል ተስፋዬ አበበ ‹‹ልጅነት››፣ ‹‹እምቧይ ሎሚ መስሎ›› እና ‹‹እናቴ ስትወልደኝ››ን ደረሱለትና በፖሊስ ኦርኬስትራ ታጅቦ ለመሰማት በቃ።  
ሙሉቀን መለሠ ድራመር ነው፤ ከዳሕላክ ባንድ ጋር በመሆን ሙላቱ አስታጥቄን በቅንብር ያግዘው ነበር፤ ግጥምና ዜማ ደራሲ ነው፤ ‹‹ያይኔ ነገርማ››፣ ‹‹አካል ገላ›› እና ሌሎች ሥራዎች ላይ የግጥም ማሻሻያዎችን አድርጓል፤ ‹‹እንዴት ልቻለው›› ሙዚቃ የዜማ ድርሰቱ ነው፤ ‹‹ሰውነቷ›› አልበም ላይ በርካታ የዜማ ድርሰቶችን ሠርቷል፤ ባለቤቱ አሥራት አንለይ ደግሞ ‹‹ወተቴ ማሬ›› እና ‹‹ፀሐይ›› የተሰኙ ዘፈኖችን ደርሳለታለች።
ከሠራቸው ሥራዎች መካከል፣ በግጥምና በዜማ ረገድ ለ‹‹ሰውነቷ›› እና ‹‹ሆዴ ነው ጠላትሽ›› ልዩ ፍቅር አለው፤ በቅንብር ረገድ ደግሞ ‹‹ቼ በለው›› እና ‹‹ውቢት››ን አብልጦ ይወዳቸው ነበር። ከላይ በተዘረዘሩ ዘፈኖች ውስጥ በድርሰትና ቅንብር ረገድ የሙሉቀን አሻራ አለ። የ‹‹ቼ በለው›› ደራሲ ተስፋዬ ለማ ናቸው፤ ቅንብር ደግሞ ‹‹ኢኩዌተርስ ባንድ›› ነው፣ 1967 ዓ.ም.።
በአድማጭ ዓይነ-ሕሊና ውስጥ የዘፈንን ጽንሰ-ሀሳብ በመሳል ሙሉቀንን የሚያክል አይገኝም፤ ለዚህ ደግሞ የዓለምፀሐይ ወዳጆ የግጥም ድርሰት እና የዮናስ ሙላቱ የዜማ ድርሰት የሆነው ‹‹የብርሃን ኮከብ›› ደህና ማሳያ ነው፡-
‹‹ዓይኗ ሲያንጸባርቅ፣ እንደ ኮከብ ደምቆ፤
ሽንጧ ሲውረገረግ፣ ባካሄዷ ረቆ፤
ከጠሩት ዓይኖቿ፣ ብርሃን ይመነጫል፤
ሽንጧ ሲተራመስ፣ ጸጉሯ ይጫወታል፤››
ሲለን አንዲት መልከመልካም ሴት በአጠገባችን ስታልፍና፣ እንቅስቃሴዋን እያየን ስንደመም እንገኛለን፤ ሕያው የተላበሰች እንስት ነው የሚያስተዋውቀን፤ ዘፈኑን በድምጽ ብንሰማውም ምስል ያለው እስኪመስል ጥርት ብሎ ይታየናል!
ሙሉቀን መለሠ በምሰላ አሃድ፣ በዘይቤ፣ በምሳሌያዊ ንግግር…. እያሰረገ ቅኔአዊነትን የተላበሱ ሥራዎችን ሰጥቶናል፤ በዚህም የሥነ-ውበትንና ሙዚቃን ዝምድና አሳይቷል!
‹‹ይረገም›› ላይ የገዛ ዓይኑን ከመውቀስ ጎን ለጎን፣ ዓይንዬ ስለተባለች የደራሲው ወዳጅ ሲብከነከን እናገኛለን፤ ‹‹እኔስ ተሳስቼ›› በሚል ዘፈን ውስጥ
‹‹ፊሪንባ ላኪልኝ፣ በኪስ አገልግል፤
እኔ አንጀት አልበላም፣ አንቺን ይመስል፤››
በአንጀት ፈንታ ፊሪንባ አምጪ ነው፤ ክብሬን አታዋርጂ ዓይነት መዓት፤ በሌላ ጎን ደግሞ አንጀቴን አትብዪ አታባቢኝ ሲል ይማጠናታል፤ ወረድ ይልና፡-
‹‹ከእንግዲህ አልበላም፣ ብርትኳኔን ልጬ፤
መለየትን ያክል፣ ከጎኔ አስቀምጬ››
በብርትኳን አንድ ሰው ወክሏል፤ መለያየታችን ዕውን እስከሆነ ባልደርስብሽ፣ ባትደርሺብኝ ይሻላል ባይ ነው፤ ቁጭት እንዳይከተል መጠንቀቁ ነው…
‹‹እንዴት አደርጋለሁ፣ የዚያችን ልጅ ነገር፤
ባይኔ ውሃ ሞላ፣ ወንዙን ሳልሻገር››
ሲል ይብሰከሰካል፤ በመንገድ ላይ ሳለ የውሃ ሙላት አናጥቦታል፤ ወላ እንባው በዓይኖቹ ተንጠርብቦ ይፈታተነው ገብቷል፤  
ሙሉቀን መለሠ በተለያዩ ሙዚቃዎቹ ብሶቱን፣ ማጣቱን፣ ጣመኑን፣ ፍዳውንና ሕመሙን ለቤት እንሰሶች ያዋያል፤ መንደርደሪያው የከብት ሥም ነው፤ መማጸኛውም ላም፤ በተለይ ከከብት ጋር ያለው ቁርኝት የሚገርም ነው!
1ኛ. ‹‹እምቧ በይ ላሚቱ››
በዚህ ዘፈን ሙሊዬ፣ ‹‹እምቧ በይ ላሚቱ፤
ኮርማ ወላዲቱ፤….››
በማለት ይንደረደራል፤ እዚህ ላይ ላሚቱን ያዋያታል፤ ችግሩን ይዘከዝክላታል፤ ናፍቆቱን ይነግራታል፤ ምናልባትም ለሰው መንገር ሰልችቶት ይሆናል - ስጋቱ ዘባባች አይታጣምና ነው እንግዲህ!
2ኛ. ‹‹እምቧ ዘቢደር››
‹‹እምቧ ዘቢደር፣
ላም አለሽ ወይ ጊደር፤››….
እዚህ ላይ ‹‹እምቧ›› ማጀቢያ ነው፤ በሙዚቃውም ከ20-30 ጊዜ ድረስ ተጠርቷል፤ በተጨማሪ፣ ላም ያላትን/ጊደር ያላትን ሴት እየቋመጠ ነው፤ ጊደር ውብ ሴት ላም ነች፤ ነገ ልጅ የምትሰጥ፤ የምትታለብ፤ ቀጥሎ፡-
‹‹እምቧ ስል አድራለሁ - ግርግዳ ስቧጭር፤
ለዓይነ ከብላላ ልጅ፣ ለቁመተ አጭር፤›› ይለናል፤
ለከጀላት ልጅ እንደ ላሚቱ ይሠራራዋል፤ በላማዊ ባሕሪይ እንደሚትከነከን ይናዘዛል፤ ሲቁነጠነጥና ሲፋጭር እንደሚያድር ያወሳናል! ዘለስ ይልና፡-
‹‹በቅሎዬ ስገሪ፣ እንግባ አገራችን፤
የመጣንበት - ሞልቷል ጉዳያችን፤››
የሚላት ብሂል አለቺው፤ ያሳካው ነገር አለ ማለት ነው፤ የልቡ መሻት ደርሷል፤ የቋመጣትን እንስት አወቃት ይሆን?!
በሙዚቃችን ውስጥ በአንደኛ መደብ (እኔ) እያለ የሚተርክ ባለድምጽ ነው የምናውቀው፤ ነገር ግን የሙሉቀን መለሠ ‹‹አካል ገላ›› የሌላን ተናጋሪ ሀሳብ የሚተርክል ዘፈን ነው፤ በጣም ከምወዳቸው የሕዝብ ለዛ ካላቸው የሙሉቀን ዘፈኖች አንዱ ነው፤ ‹‹አካል ገላ›› ሙሊዬ ከረቀቀባቸው ሥራዎች አንዱ ነው፤ በዲያሎግ መልክ ነው ዘፈኑ የሚቀርበው፤ የከጀላትን ሴት ያናዝዛታል፡-
‹‹አካል ገላ፣ አካል ገላ፣
ምን አለሽ ያ ቆለኛ?
አካል ገላ፣ አካል ገላ፣
ምን አለሽ ያ ደገኛ?...››
እያለ ይጠይቃታል፤ ዲያሎግ ነው የሚያደርጋት፤ ምን እንዳልዋት ይጠይቃል፤ በጣም ማራኪ እና ያልተለመደ የአዘፋፈን እና የአተራረክ ስልት ነው፤ ሄደት ይልና ይመስላል፡-
‹‹ዝንጀሮ እንኳን ባቅሙ፣ ያውቃታል
ወዳጁን፤
የፈለፈለውን - ይሰጣታል የእጁን›› ይላል፤››
አየህ እዚህ ላይ እንኳን እኔና አንቺ ሰዎቹ ቀርተን ዝንጀሮም ይዘያየራልና ዘይሪኝ - ጀባታሽ አይለየኝ - ኧረ አንድ በዪኝ እቱ ነው እያላት ያለው፤ የድሮ ጅንጀና ግን ደስ ሲል! በዚህ ስንኝ ውስጥ የተነፈገው ነገር አለ፤ ማር ሊልስ ቋምጧል፤ ልጅት ግን እንደ ቅራሪ ለማንም አልቀዳም ብላዋለችና ልቧን ሊያርድ የዝንጀሮን ሆደ ባሻነት ይጠቅስላታል!
አልታከተም፡-
‹‹ሠጋር በቅሎንማ፣ መች አጣሁ ከቤቴ፤
ሳይሽ ፈረስ፣ ፈረስ - ይላል አካላቴ፤››
ብሏት እርፍ! ሊጋልባት ያምረዋል! ደግሞ እኮ ቤቱ ሠጋር በቅሎ አስቀምጧል! በእርግጥ እፈራርሳለሁም እያላት ነው፤ ከዚያ ጎን ሊጋልባት መቋመጡንም ይነግረናል።
ፍቅርና ተማጽኖ ይችልበታል፤ ‹‹ባይንሽ ልለፍበት›› በሚል ሙዚቃ በሠራ አካሉ ስትንከላወስ ይነግረናል፤ ሲጽፍ፣ ሲያገድም፣ ሲያዳምጥ… አትቀርም፤ ወላ በጎናው እንድትመላለስ ፈቅዷል፤ ‹‹ሆዴ ነው ጠላትሽ›› ውስጥ ደግሞ፡-
‹‹ቁና ጥሬ ልብላ፣ ዓመት ልመንን፤
እሷን በሱባኤ፣ አገኝ እንደሆን፤›› ይለናል፤  
‹‹አትከብደኝም›› ሲል ደግሞ እሷን ማዘል ማንከብከቡ እንደማይከብደውና እንደማይጎረብጠው ይነግረናል፤ ይልቅ ብትርቅ ፈረሷን ብትጭን እንደሚጣምነው ይናዘዛል፤ ‹‹በርግጥ አገኘሽ ወይ›› ላይ በምን ምክንያት እንደተወቺው ይጠይቃታል፤ ‹‹የኔ ቆንጆ›› ላይ ደግሞ በቆነጃጅት ቢከበብም፣ እንደማያኽሏት የሚተርክበት ዘፈን ነው….
‹‹መቶ ሰው ቢሰለፍ፣ አንቺን የማይመስለኝ፤
ፍቅር ነው ሕመም ነው፣ በይ እስቲ ንገሪኝ፤
ከላይ በተጠቀሱ ዘፈኖች ሀላፊነቱን የሚወስደው እሱ ነው፤ አይወቅስም፤ ዕውነታውን ማወቅ ነው የሚሻው፤ አያላክክም፤ ለበዳይዋ ነው የሚወግነው self-critics ዓይነት ይዘት አላቸው።
‹‹ናኑ ናዬ››፡-
‹‹ወይ ላሚቱ አልሞተች፣ ወይ ጥጃው
አልጠባትም፤
ምን የቆረጠው ነው፣ እንዲህ ያለባት፤››
ሲል ገምዳላ ፈራጅን ይወቅሳል፤ ሙሉቀን ብቻ ብዙ ፍካሬዎች አሉት፤ በቤት እንስሳ ዙሪያ፤ ዐውዱን ማዕከል በማድረግ በቆንጆ፣ ቆንጆ ስንኞች እየታገዘ ያሰግራል፤ ዘይቤአዊነትን ከተካኑ ሙዚቀኞች አንዱ ለእኔ ሙሉቀን መለሠ ነው!
ሥነ-ቃልና ሙሉቀን የተቆራኙ ናቸው፤ የሕዝብን ቱባ ሥነ-ቃል በሙዚቃው አዘምኖና አሻሽሎ በማቅረብ፣ ትውፊታችንን ቀጣይ ያደርገዋል፤ በዚህ ረገድ የሚተካከለው የለም፤ ባሕልን በሚገባ ያስተዋውቃል…
‹‹ቀይ የወደደና እባብ የነከሰው
ሕልም ስልም ይላል፣ አያዋይም ለሰው፤››
ገብስ እሸት ፈትገን፣ ቁይልን ብንላት፤
ይህቺ የባላገር ልጅ፣ የምታምሰው ናት፤››
ሠጋር በቅሎንማ፣ መች አጣሁ ከቤቴ፤
ሳይሽ ፈረስ፣ ፈረስ ይላል አካላቴ፤››
ሙሉቀን አሻሽሎ ከዘፈናቸው ዘፈኖች መካከል፣ ‹‹አካል ገላ››፣ ‹‹እንቧ ዘቢደር››፣ ‹‹አልማዜዋ›› እና ‹‹ናኑ ናዬ›› ይገኙበታል፤ በእነዚህ ዘፈኖች የሕዝብን ሥነ-ቃል በሚገባ በዜማ አዋህዶ ያቀነቅናል፤ ያዘምናቸዋል።
ታዲያ፣ እንዲህ እንዲህ እያለ፣ ሙሉቀን መለሠ ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በተወለደ በ70 ዓመቱ የዘላለም እንቅልፉን ተኝቷል! ነፍስ ይማር!!
ከአዘጋጁ

ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 187 times