Monday, 15 April 2024 09:16

ምዕራባውያን ፈላስፎች ዠን-ፖል ሳትረ

Written by  መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(1 Vote)

(ክፍል አንድ)

ሕይወት እና ሥራዎች
ዠን-ፖል ሳትረ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ ፈላስፎች መካከል አንዱ ነወዉ፡፡ ይህ ፈላስፋ የዘመናዊዉ ኤግዚስቴንሻሊዝም ዋናው ደቀመዝሙር ሲሆን፤ ይህ ፍልስፍናዊ ንቅናቄ ወደ ፈረንሳይ የገባውና ገናና የሆነዉም በእሱ አማካኝነት ነበር፡፡ በኖረበት ክፍለ ዘመን የእሱን ያህል እጅግ ታዋቂ ፈላስፋ ዓለም ላይ አልነበረም፡፡ የጃዝ ሙዚቃ አፍቃሪው ሳትረ፤ ፈላስፋ ብቻ አይደለም፣ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ጸሐፌ ተዉኔት፣ የፖለቲካ ተዋሪ፣ የፖለቲካ አክቲቪስት፣ የሥነ ልቡና ልሂቅና የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ነዉ፡፡
ሳትረ የተወለደው ግንቦት 21 ቀን 1905 ዓ.ም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ዉስጥ ነበር፡፡ ገጠር መኖር ይጠላ የነበረው ሳርተር፤ አብዛኛውን ዘመኑን የኖረው በትውልድ ከተማው ፓሪስ ዉስጥ ነበር፡፡ ገና የአንድ ዓመት ህጻን ሳለ የባህር ኃይል መኮንን ወላጅ አባቱን ዠን-ባብቲስት ሳትረ ሞት ስለነጠቀበት ያደገው በእናቱ አን-ሜሪ ሹታይዘር ነዉ፡፡ ሳትረ የወላጆቹ ብቸኛ ልጅ ነበር፡፡ በ1913 ዓ.ም በስምንት ዓመቱ ፓሪስ ውስጥ በሚገኘው ሞንታንያ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ 1914 ዓ.ም ተማረ፡፡

በ1915 ዓ.ም ደግሞ እዛው ፓሪስ ውስጥ በሚገኘው ሄነሪ 4ኛ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ 1917 ዓ.ም ተማረ፡፡ በ1917 ዓ.ም እናቱ ሁለተኛ ባሏን መሀንዲሱን ጆሴፍ ማንሲ አግብታ ከነመላ ቤተሰቧ ፓሪስን ለቃ ወደ ላ ሮሻል አቀናች፡፡ ሳርተር ፓሪስን እጅግ ይወድ ስለ ነበር፣ ላ ሮሻል ውስጥ ሲማር ደስተኛ አልነበረም፡፡ በ1920 ዓ.ም ከእናቱ ጋር ወደ ፓሪስ በመመለሳቸው የሚወደው ትምህርት ቤት ሄነሪ 4ኛ ተመልሶ ገብቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አገባደደ፡፡ የኮሌጅ መሰናዶ ትምህርቱን ከ1922 ዓ.ም እስከ 1924 ዓ.ም ሉዊ-ል-ግራን ትምህርት ቤት ውስጥ ተማረ፡፡   

                       
ሳትረ በልጅ እድሜው መጽሐፍትን እንዲወድ የረዳዉ አያቱ ቻርልስ ሽዋይዘር ነበር፡፡ የታዋቂውን ፈረንሳዊ ደራሲ ጉስታቭ ፉሎባር መዳም ቦቫሪ የተሰኘዉን ልብ ወለድ ያነበበዉ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ በ1924 ዓ.ም በአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ከጓደኛው ፖል ኒዛን ጋር ፓሪስ ውስጥ ወደሚገኘዉ ኢኮል ኖርማል ሱፐሪየር ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ፍልስፍናን በማጥናት በ1929 ዓ.ም ከሰባ ስድስት ተማሪዎች አንደኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡ ከሳትረ ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የተመረቀችዉ የሕይወት ዘመን ፍቅረኛዉ ሲሞን ደ ቡቩዋር ነበረች፡፡ ደ ቡቩዋር በ1949 ዓ.ም የታተመው ታላቅ የፍልስፍና ሥራ ዘ ሰከንድ ሴክስ ጸሐፊ ናት፡፡ ይህ ሥራ የእንስታዊነት ፍልስፍና የማዕዘን ድንጋይ ነዉ፡፡
ኢኮል ኖርማል ሱፐሪየር በናፖሊዮን የአገዛዝ ዘመን የተቋቋመ፣ ከሳትረ እና ደ ቡቩዋር በተጨማሪ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ ፈላስፎችን ሄነሪ በርግሰን፣ ሬይሞንድ አሮንና ሞሪስ ሜርሉ-ፖንቲን ያፈራ፤ ፈረንሳይ ዉስጥ ካሉ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች በግንባር ቀደምትነት የሚቀመጥ ዩኒቨርሲቲ ነዉ፡፡       
ሳትረ እና ደ ቡቩዋር የተገናኙት በ1929 ዓ.ም ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ ነዉ፡፡ እነዚህ ፍቅረኞች በትዳር ሳይጣመሩ አምሳ አንድ ዓመታትን በፍቅር መዝለቅ ችለዋል፡፡ ጥንዶቹ ጎጆ ያልቀለሱት፣ ትዳር አርነትን የሚገድብ የቡርዧዎች ተቋም ነዉ በሚል ምክንያት ነበር፡፡ ጥንዶቹ ሌሎች የፍቅር ወዳጅ ነበራቸዉ፡፡ ደ ቡቩዋር ከሁለቱም ፆታዎች ጋር ወሲባዊ ተራክቦ የምትፈፅም ስለነበረች እርስ በርስ ፍቅረኞቻቸዉን ይጋሩ ነበር፡፡ ሳትረ እና ደ ቡቩዋር በይፋ ያስተምሯቸዉ ከነበሩ ተማሪዎቻቸዉ ጋር አንሶላ ይጋፈፉ ነበር፡፡ ሳትረ ከደ ቡቩዋር በተጨማሪ ታዋቂዎቹን ፈላስፎች ሞሪስ ሜርሉ-ፖንቲን እና ሬይሞንድ አሮንን የተዋወቀዉ ኢኮል ኖርማል ሱፐሪየር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ነዉ፡፡ እነዚህ አራት ፈረንሳዊያን ፈላስፎች ኋላ ላይ በፈረንሳይኛ ለ ቶ ምዴርን የተሰኘ ዝነኛ የፖለቲካ፣ የሥነ ጽሑፍ እና የፍልስፍና ጥናታዊ መጽሔት ለመመስረት በቅተዋል፡፡ የእዚህ ጥናታዊ መጽሔት ስያሜ መነሻ ሞደርን ታይምስ የተሰኘው የእንግሊዛዊው ፊልም ተዋናይ ቻርሊ ቻፕሊን የፊልም ሥራ ነዉ፡፡
ሳትረ ወደ ፍልስፍና የተሳበው በአፍላ ዕድሜዉ የፈረንሳዊውን ፈላስፋ ሄነሪ በርግሰንን ታይም ኤንድ ፍሪዊል የተሰኘ የፍልስፍና ሥራ በማንበቡ ነበር፡፡ ልጅ ሳለ ከሌሎች ልጆች የተገለለ እጅግ ሀዘንተኛና ባይተዋር ነበር፡፡ የእድሜ እኩያ ባልንጀራ አልነበረውም፤ የእሱ የቅርብ ወዳጅ መጻሕፍት ነበሩ፡፡ ሳትረ በልጅነቱ የአያቱን ቻርልስ ሽዋይዘርን ጥብቅ ቁጥጥር እጅግ ይጠላ ነበር፡፡ ቻርልስ ሽዋይዘር የታዋቂዉ የሥነ መለኮት ሊቅ፣ ሙዚቀኛና የፕሮቴስታንት ሚሲዮን አልበርት ሽዋይዘር  አጎት ነበር፡፡
ሳትረ ከኢኮል ኖርማል ሱፐሪየር ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ል አቭራ ዉስጥ የሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዉስጥ የፍልስፍና መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡ ሳትረ ቀደም ብሎ በጻፋቸዉ ሥራዎቹ ስኬታማነት የገንዘብ ነፃነትን ማግኘት በመቻሉ፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተቋጨ በኋላ በገንዘብ አስገዳጅነት ምክንያት ተሰማርቶበት ከነበረዉ የፍልስፍና መምህርነት ሙያው መሰናበት ችሏል፡፡              
ሳትረ ጀርመን በርሊን አቅንቶ ከህዳር 1933 ዓ.ም እስከ ሀምሌ 1934 ዓ.ም ፌኖሜሎጂ የተሰኘውን ፍልስፍና በማርቲን ሃይዲገር ስር አጥንቷል፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ሳትረ የኤግዚስቴንሻሊዝም ዋና ደቀመዝሙር ሆኖ ብቅ አለ፡፡  
ሳትረ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመሳተፉ በፊት “ፖለቲካን በሩቁ” የሚል ፖለቲካ ጠል ነበር፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግን በሳትረ አስተሳሰብ ላይ ለውጥ አመጣ፡፡ በእዚህም ምክንያት፣ በወቅቱ ፈረንሳይን ወሮ የነበረዉን የናዚ አገዛዝ በመቃወም ሚርሉ-ፖንቲ ባቋቋመዉ ሶሻሊዝም ኤንድ ሊብሬሽን በተሰኘዉ የፈረንሳይ ምሁራን የሚታገሉበት ምስጢራዊ ጋዜጣ በመሳተፍ መጠነኛ ሚናዉን ተጫዉቷል፡፡
ሳትረ በፖኒ ጦርነት አገሩ ከጀርመን ጋር በገጠመችበት ወቅት ወደ ግንባር ዘምቶ የአየር ትንበያ ባለሙያ ሆኖ በመሰለፍ ከመስከረም 1939 ዓ.ም እስከ ሰኔ 1940 ዓ.ም ለሃያ ሁለት ወራት ተዋግቷል፡፡ ነገር ግን፣ ሰላሳ አምስተኛ አመቱ በሚከበርበት ዕለት፣ ሰኔ 21 ቀን 1940 ዓ.ም፣ ከሌሎች በሺ የሚቆጠሩ የአገሩ ወታደሮች ጋር በጀርመኖች ተማርኮ ዘጠኝ ወራትን በጀርመን የጦር ምርኮኞች ወህኒ ዉስጥ በእስር አሳልፏል፡፡ ሳትረ የማርቲን ሃይዲገርን ታላቅ የፍልስፍና ሥራ ቢንግ ኤንድ ታይም ያነበበው በጀርመኖች የጦር ምርኮኞች ወህኒ ቤት ዉስጥ እስረኛ ሳለ ነዉ፡፡ በጀርመኖች የጦር ምርኮኞች ወህኒ ቤት ውስጥ ዘጠኝ ወራትን ታስሮ ከቆየ በኋላ መጋቢት 1941 ዓ.ም ሐሰተኛ የህክምና ማስረጃ አቅርቦ ከእስር ተፈቷል፡፡ ከእስር ተፈቶ ወደ ፓሪስ ከተመለሰ በኋላ፣ በኮንዶርሴት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የፍልስፍና መምህር ሆኖ ሠርቷል፡፡       
ሳትረ በ1964 ዓ.ም የኖቤል ሽልማትን በሥነ ጽሑፍ ቢያሸንፍም፣ ሽልማቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ ሽልማቱን ውድቅ ያደረገው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያዉ ምክንያት፣ ማንኛዉንም አይነት ማዕረግ የማይፈልግ ሰዉ መሆኑ ነዉ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት፣ ሽልማቱን የሚሰጠው ተቋም እሱ የሚያወግዘውን የፖለቲካ ርእዮት የሚደግፍ ተቋም በመሆኑ ነው፡፡
ሳትረ የራሱ የሆነ መኖሪያ ቤት ወይም አፓርታማ አልነበረዉም፣ ረጅም ዘመን የኖረዉ ፓሪስ ዉስጥ የነበሩ ሆቴሎችን ተከራይቶ ነበር፡፡ በመሆኑም፣ የነበረዉ የቁስ ጥሪት እጅግ ጥቂት ነበር፡፡ እነዚህም ጥሪቶቹ ሲጋራ፣ የጽሕፈት መሣሪዎችና የሚለብሳቸዉ ልብሶች ነበሩ፡፡
ሳትረ ፉንጋና ሸዉራራ የነበረ ቢሆንም ሴቶችን እንደ መግነጢስ የሚስብ ኃይልን የታደለ ነበር፡፡ ይህ ፈላስፋ ከእጁ ሲጋራ የማይለይ ሱሰኛ አጫሽ ነበር፡፡  
ሳትረ ካፌ ዉስጥ ተቀምጦ መጻፍ እጅግ ይወድ ነበር፡፡ ያዘወትራቸዉ የነበሩት ቡና ቤቶች ካፌ ደ ፍሎር እና ካፌ ለስ ደክስ ማጎትስ የተባሉ ዝነኛዉ የፓሪስ ቡና ቤቶች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ቡና ቤቶች ከሳትረ በተጨማሪ የእነ ሲሞን ደ ቡቩዋር፣ አልበርት ካሙ፣ ፓብሎ ፒካሶ፣ ሳልቫዶር ዳሊና ሌሎች በወቅቱ ታዋቂ የነበሩ ፈላስፎች፣ ደራሲያንና ሠዐሊያን መናኸሪያ ነበሩ፡፡ ሳትረ የሥራ ቦታዉን ወደ ካፌ ለስ ደክስ ማጎትስ ከማዛወሩ በፊት ሥራዎቹን ይጽፍ የነበረዉ በካፌ ደ ፍሎር ዉስጥ ነበር፤ ሆኖም ግን ብዙ ጎብኝዎች እሱን ካፌ ደፍሎር ዉስጥ ተቀምጦ ሲጽፍ ለመመልከት ይተሙ ስለነበር የሥራ ቦታዉን ወደ ካፌ ለስ ደክስ ማጎትስ ሊለዉጥ ተገዷል፡፡
ሳትረ የሰዉ ልጅ አርነት ጠበቃ ነበር፡፡ በሰዉ ልጅ ላይ የሚደረግን ጭቆና አጥብቆ ይኮንን ነበር፡፡ በመሆኑም፣ አፍሪካዊቷ አገር አልጀሪያ ከእናት አገሩ ፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ቀንበር ነፃ ለመውጣት ታደርገዉ የነበረዉን ብርቱ ትግል ይደግፍ ነበር፡፡ ይኸን አቋሙን ያልወደደዱለት የአገሩ ሰዎች የግድያ ሙከራ አድርገውበት (የመኖሪ አፓርታማዉ ሁለት ጊዜ በቦምብ ተመቷል) ከሞት ተርፏል፡፡ የወቅቱ የፈረንሳይ መሪ ደጎል፣ “ሳትረ አዲሱ የፈረንሳይ ቮልቴር ነዉ” በሚል ህዝቡ በአገር መክዳት ወንጀል እንዲታሰር ያቀረበለትን ጥያቄ ዉድቅ አድርጎታል፡፡
በ1948 ዓ.ም የኢ-አማኙ ሳትረ የፍልስፍና ሥራዎች፣ የፈጣሪን በህልውና አለመኖር የሚሰብኩ በመሆናቸዉ እንዳይነበቡ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተወገዙ ሥራዎች ዝርዝር ዉስጥ ሰፈሩ፡፡  
ሳትረ እጅግ ትጉህ ጸሐፊ ነበር፡፡ በቀን ቢያንስ ስድስት ሰአት ያህሉን የሚያውለው ለጽሑፍ ሥራው ነበር፡፡
የሳትረ የመጀመሪያ ሥራ በ1936 ዓ.ም ያሳተመው ኢማጅኔሽን፡ ኤ ሳይኮሎጅካል ክሪቲክ የተሰኘዉ ሥራዉ ነዉ፡፡ ይህ ሥራ ኤ ስኬች ፎር ኤ ቲኦሪ ኦፍ ዘ ኢሞሽንስ በሚል ርዕስ በ1940 ዓ.ም በአዲስ መልክ ታትሟል፡፡ በእዚሁ ዓመት ያሳተመዉ ሌላኛው ሥራዉ ዘ ትራንሰንደንስ ኦፍ ዘ ኢጎ፡ ኤ ስኬች ፎር ኤ ፌኖሜኖሎጅካል ዲስክርፕሽን ነዉ፡፡ በ1938 ዓ.ም ያሳተመዉ ኖዚያ የተሰኘዉ የበኩር ልብወለድ ሥራዉ ዝናዉ እንዲናኝ አድርጎታል፡፡ ይህ ሥራ በ1950ዎቹ የግማሽ ክፍለ ዘመኑ የፈረንሳይ ታላላቅ የልብ ወለድ ሥራዎች ተብለው ከተመረጡ ስድስት ልብ ወለዶች መካከል አንዱ ሆኖ የተመረጠ ሥራ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ኖዚያ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ኤግዚስቴንሻሊስት ልብ ወለድ ነው፡፡
ሀምሌ 1939 ዓ.ም በአንባቢያን ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘለትን ዘ ወል ኤንድ አዘር ስቶሪስ የተሰኘ የአጫጭር ልብ ወለዶች መድበሉን እና ኤ ስኬች ፎር ኤ ቲኦሪ ኦፍ ዘ ኢሞሽንስ የተሰኘ ሥራውን አሳተመ፡፡  በ1943 ዓ.ም የታተመዉ ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ የሳትረ ታላቅ የፍልስፍና ሥራዉ ነዉ፡፡ ይህ ሥራ ለህትመት ሲበቃ ፈረንሳይ በናዚ ቀንበር ስር ነበረች፡፡ ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ከተረጎሙት  አንዷ ሳራ ሪችሞንድ እንደ ተናገረችዉ፤ ከሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ታላላቅ የፍልስፍና ሥራዎች መካከል አንዱ ነዉ፡፡ በእዚሁ ዓመት ዘ ፍላይስ የተሰኘው የተውኔት ሥራው ለመድረክ በቃ፡፡ በቀጣዩ ዓመት 1944 ዓ.ም ለመድረክ የበቃው የተውኔት ሥራው ደግሞ ኖ ኤግዚት፡ ኤ ፕሌይ ኢን ዋን አክት ነዉ፡፡ ይህ ሥራ በ1945 ዓ.ም ለህትመት በቅቷል፡፡ በእዚሁ ዓመት ዘ ሮድስ ቱ ፍሪደም የተሰኘ ተከታታይ ልብ ወለዱን የመጀመሪያ ቅጽ ዘ ኤጅ ኦፍ ሪዝን እና ሁለተኛዉን ቅጽ ዘ ሪፕሪቭ የተሰኙ ልብ ወለዶቹን አሳትሟል፡፡ የእዚህ ልብ ወለድ ሦስተኛ ቅጽ አይረን ኢን ዘ ሶል በ1949 ዓ.ም ለህትመት በቅቷል፡፡ ሜን ዊዝአዉት ሻዶዉስ እና ዘ ሪስፔክትፉል ፕሮስቲቲዉት የተሰኙት የተዉኔት ሥራዎቹ ደግሞ በ1946 ዓ.ም ለመድረክ በቅተዋል፡፡ በእዚሁ ዓመት ያሳተማቸው ሥራዎቹ ደግሞ አንታይ ሴሜት እንድ ጅዉ እና ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም ናቸው፡፡
ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም ሳትረ በ1945 ዓ.ም ፓሪስ ዉስጥ በሚገኘዉ ሜንቴናንት ክለብ ተገኝቶ ኤግዚስቴንሻሊዝም የተሰኘ ፍልስፍናዉ ላይ ከኮሚኒስቶችና ክርስቲያኖች ለተሰነዘረበት ነቀፌታ የመልስ ምት የሰጠበት ሥራ ነዉ፡፡ ይህ ሥራ ሳትረ የሥነ ኑባሬ ትወራውንና የግብረ ገብ ፍልስፍናውን ግልፅ በሆነ መንገድ ያቀረበበት ሥራ ነው፡፡ ይህ ሥራ ለህትመት ሲበቃ ጥቂት መሻሻል ተደርጎበታል፡፡ ዘ ችፕስ አር ዳውን በ1946 ዓ.ም ለህትመት የበቃ ሌላኛው የሳትረ ሥራ ነው፡፡ ዘ ችፕስ አር ዳውን በዠን ዲላኖይ አዘጋጅነት ለፊልም የበቃ የፊልም ጽሑፍ ነው፡፡ በ1947 ዓ.ም ያሳተመው ቦድሌር የተሰኘው ሥራው በታዋቂዉ ገጣሚ ቻርልስ ቦድሌር ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጠጥን ሥራ ነው፡፡ ይህ ሥራ ሥነ ልቦናዊ ፍካሬ ነው፡፡ በእዚሁ ዓመት ሲችዌሽንስ ቅጽ 1 ታተመ፡፡
በ1948 ዓ.ም ደርቲ ሃንድስ የተሰኘዉ ተዉኔቱ ለመድረክ በቅቷል፡፡ በእዚሁ ዓመት የታተሙት ሥራዎቹ ደግሞ ሲችዌሽንስ ቅጽ 2 እና ኢን ዘ ሜሽ ናቸው፡፡ ኢን ዘ ሜሽ ሁለተኛው የሳትረ የፊልም ጽሑፍ ነው፡፡ በ1949 ዓ.ም ሲችዌሽንስ ቅጽ 3 ለህትመት በቃ፡፡ በ1951 ዓ.ም ዘ ዴቭል ኤንድ ዘ ጉድ ሎርድ የተሰኘው ተውኔት ለመድረክ በቃ፡፡
ሳትረ በ1952 ዓ.ም ያሳተመዉ ሴንት ጀነት፣ አክተር ኤንድ ማርተር በፈረንሳዊው ጸሐፌ ተውኔት ዠን ጀነት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጠጥን ሥራ ነው፡፡ ሳትረ እና ገነት የተገናኙት በ1944 ዓ.ም ነው፡፡ በ1954 ዓ.ም ኬን፣ ኦር ዲስኦርደር ኤንድ ጂኒየስ የተሰኘ ተውኔቱን አሳተመ፡፡ ይህ ሥራ በእንግሊዛዊው ተዋናይ ኤድመንድ ኬን ሕይወት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በ1955 ዓ.ም ኔክራሶቭ የተሰኘ ተውኔቱ ታተመ፡፡ በ1959 ዓ.ም ዘ ኮንደምንድ ኦፍ አልቶና የተሰኘ የተውኔት ሥራው ለመድረክ በቃ፡፡ ይህ ሥራ በ1960 ዓ.ም ለህትመት በቅቷል፡፡ ክሪቲክ ኦፍ ዲያሌክቲካል ሪዝን ቅጽ 1 በ1960 የታተመ ታላቅ የፍልስፍና ሥራው ነው፡፡ የእዚህ ሥራ ሁለተኛ ቅጽ የታተመው ከሞተ በኋላ በ1985 ዓ.ም ነው፡፡ ሳትረ ይህን መጽሐፍ የጻፈው አምፒታሚን እየወሰደ ነበር፡፡
በ1962 ዓ.ም ማርክሲዝም ኤንድ ኤግዚስቴንሻሊዝም ለህትመት በቃ፡፡ ሳርተር በ1964 ዓ.ም ያሳተመው ወርድስ የተሰኘው ሥራው ግለ ታሪኩ ነዉ፡፡ ይህ ሥራው ልክ እንደ ቦድሌር፣ ሴንት ገነት እና ዘ ፋሚሊ ኢዲየት ሁሉ ኤግዚስቴንሻል ፍካሬ ልቦና የተሰኘ ትወራውን ተግባራዊ ያደረገበት ነው፡፡ በእዚሁ ዓመት ሲችዌሽንስ ቅጽ 4፣ ቅጽ 5 እና ቅጽ 6 ለህትመት በቁ፡፡ በ1965 ዓ.ም ሲችዌሽንስ ቅጽ 7 ለህትመት በቃ፡፡ በ1967 ዓ.ም ሰርች ፎር ኤ ሜተድ ታተመ፡፡ ይህ ሥራ ቀደም ብሎ በ1957 ዓ.ም በወጣው ለ ቶ ምዴርን ጥናታዊ መጽሔት ላይ ታትሟል፡፡ እንደገናም ይኸው ሥራ በ1960 ለህትመት ከበቃው ክሪቲክ ኦፍ ዲያሌክቲካል ሪዝን ቅጽ 1 ጋር አብሮ ታትሟል፡፡
በ1971 ዓ.ም በታዋቂው ደራሲ ጉስታቭ ፉሎባር ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጠጥን ዘ ፋሚሊ ኢዲየት፡ ጉስታቭ ፉሎባር 1821–1857 ቅጽ 1 እና ቅጽ 2 ታተመ፡፡ የእዚህ ሥራ 3ኛ ቅጽ ደግሞ በ1972 ዓ.ም ታተመ፡፡ በእዚሁ ዓመት የታተሙት የሳትረ ሥራዎች ደግሞ ሲችዌሽንስ ቅጽ 8 እና 9 ናቸው፡፡ በ1976 ዓ.ም ሲችዌሽንስ ቅጽ 10 ለህትመት በቃ፡፡ በእዚህ ዓመት ሳትረ ኦን ቴአትር ለህትመት በቃ፡፡   
ሳትረ ከሞተም በኋላ ሥራዎቹ ለህትመት የበቁለት ሰው ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም ኖትቡክስ ፎር አን ኤቲክስ እና ዋር ዲያሪስ ለህትመት በቁ፡፡ በ1984 ዓ.ም ዘ ፍሮይድ ሴናሪዮ ለህትመት በቃ፡፡ በ1989 ዓ.ም ትሩዝ ኤንድ ኤግዚስተንስ ለህትመት በቃ፡፡
ሳትረ በተወለደባትና ለረጅም ዘመን በኖረባት ፓሪስ ከተማ ውስጥ በተወለደ በሰባ አራት አመቱ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 15 1980 ዓ.ም ይኸን ዓለም እስከወዲያኛው ተሰናበተ፡፡ በሥርአተ ቀብሩ ላይ ከሃምሣ ሺህ በላይ ፈረንሳዊያን ተገኝተው ነበር፡፡ የሞቱ ዜና ከተሰማበት ዕለት አንስቶ የፈረንሳይ ቴሌቭዥኖች፣ ሬዲዮኖች እና ጋዜጦች ለወር ያህል ዐቢይ ዜና ሆኖ ስሙ የተወሳ ታላቅ አሳቢ ነበር፡፡ የሳትረን ዜና እረፍት የዘገቡት የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኀን ብቻ አልነበሩም፤ ታዋቂዎቹ የአሜሪካ ጋዜጦች ኒዉ ዮርክ ታይምስ እና ዋሽንግተን ፖስት ጭምር እንጂ፡፡     
፩. ሥነ ኑባሬ
፩.፩. አርነት በሳትረ ሥነ ኑባሬ
በምዕራባውያን ፍልስፍና ታሪክ ዉስጥ ሳትረ የሚታወቀው በአርነት ፈላስፋነቱ ነው፡፡ ስፒግልበርግ እንዳለው፣ ሳትረ የአርነት ጠበቃ ነው (ስፒግልበርግ፣ 1994)፡፡ እንደ እሱ እሳቤ፣ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ፍፁማዊ አርነትን የተቀዳጀ ነው፡፡ ሰው መሆን ነጻ መሆን ነው፡፡    
የሳርተር ፍልስፍና አንኳር ዐሳብ ቀጥሎ በቀረበው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ተጠቃሎ የቀረበ ነው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ ውስጥ የቀረበ ሲሆን፤ ትርሜው እንዲህ የሚል ነው፡ ንቃተ ኅሊናን የተጎናፀፈው የሰው ልጅ ታሪካዊ ኹነቶቹን ቀይሮ ወደ መፃኢው ምዕራፍ የመሻገር ሥልጣን አለው፡፡      
የአርነት ቀንበር                 
በእዚህ ምዕራፍ መግቢያ ሳትረ የአርነት ፈላስፋ ነው ብለናል፡፡ ሳትረ ከፕሌቶ፣ ከባሮን ፖል ሄነሪ ደ’ሆልባች እና ቢ. ኤፍ. ስኪነር በተቃራኒ፣ ለሰው ልጅ አርነት ጥብቅና በመቆም አንዱ የዲበአካል ነባቢ አእምሮ የሆነውን ወሳኛዊነት በፅኑ ከተቹ ፈላስፎች በግንባር ቀደምትነት ስሙ የሚጠቀስ ፈላስፋ ነዉ፡፡ ፕሌቶ፣ ባሮን ፖል ሄነሪ ደ’ሆልባች እና ቢ. ኤፍ. ስኪነር የወሳኛዊነትን ነባቢ አእምሮ የሚያቀነቅኑ ፈላስፎች ናቸው፡፡ እንደ ባሮን ፖል ሄነሪ ደ’ሆልባች (1889) እሳቤ፣ የሰዉ ልጅ በሳቢያ እና ዉጤት ሕግ እግረ ሙቅ የተጠፈነገ ፍጡር ነው፡፡ በመሆኑም፣ አርነት ተረት ነው፡፡     
     የሳትረ የሥነ ኑባሬ ነባቢ አእምሮ የማእዘን ድንጋይ የሆነው ፍፁማዊ ነጻነት ሊሸሹት የማይችሉት የሰው ልዩ ንጥረ ባሕርይ ነው፡፡ ይግረማችሁ ብሎ ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ በተሰኘ ሥራው እንደሚነግርን፣ ሰው የአርነት ሎሌ ነው – ነጻ አለመሆን አይችልም፡፡ ለምን ቢባል ሰው ነጻ እንዲሆን ተኮንኗል (ሳትረ፣ 2018)፡፡
ከላይ በእዚህ ሥራ መቅድም ውስጥ እንደ ጠቀስኩት፣ ህልውና የንጥረ ባሕርይ ወይም ማንነት ቀዳሚ ነዉ የሚለው መፈክር፣ የሳትረ የሥነ ኑባሬ ነባቢ አእምሮ መሠረት ነው፡፡ ይህ አስተምህሮት ኢ-አማኝነቱን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ሳትረ እንደሚነግረን፣ ነጻ ፍጡር የሆነው ሰው ወደ መኖር ከመጣ በኋላ ማንነቱን እንደ ቀራጺ በትልሙ መሠረት የመቅረጽ ኃላፊነት ወድቆበታል፡፡ ይህን ቀንበር መሸሽ አይችልም፡፡
ሰዉ የዕጣ ፈንታው ደራሲ ነው   
ሳትረ አፅንኦት ሰጥቶ እንደሚሰብከው፣ ከቁስ በተቃራኒ የሰው ልጅ ህልውናው ከንጥረ ባሕርይው ወይም ተፈጥሮው ቀዳሚ ነው፡፡ ዕጣ ፈንታችንን በሥልጣናችን መወሰን የምንችል ፍጡራን የሆነው በእዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንደ ሳትረ እሳቤ፣ ሰው ቋሚ ንጥረ ባሕርይ የሌለው ፍጡር ሆኖ የተገኘው ልክ እሱ የቁሶችን ፈርጅ ቀድሞ አስቦ እንደሚፈበርካቸው የእሱን ዓላማ ቀድሞ ተልሞ ሊያበጅ የሚችል ፈጣሪ በህልውና ባለመኖሩ የተነሳ ነው፡፡ ፈጣሪ ቢኖር ኖሮ የሰው ንጥረ ባሕርይ ከህልውናው ይቀድም ነበር፡፡ ህላዌ ከንጥረ ባሕርይ ከቀደመ ደግሞ ወሳኛዊነት ቅዠት ነው (ሳትረ፣ 2007)፡፡ ሳትረ ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም ውስጥ እንደ ጻፈው፤ ሰዉ የራሱ እግዜር ነው የሚለው አስተምህሮ የመጀመሪያዉ የኤግዚስቴንሻሊዝም መርህ ነው (ሳትረ፣ 2007)፡፡  
     አሜሪካዊው የሥነ ልቦና ልኂቅ ቢ. ኤፍ. ስኪነር፣ ሰው ፍፁማዊ አርነትን የተቀዳጀ ፍጡር ነው የሚለው የሳትረ አተያይ ዋና ተቃዋሚ ነው፡፡ ስኪነር ቢዮንድ ፍሪደም ኤንድ ዲግኒቲ በተሰኘ ሥራው እንደ ጻፈዉ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የትናንት ስሪት በመሆኑ አርነት ተረት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ሰው የትናንት ዉጫዊ ኃይሎች ተፅዕኖ ስሪት ነው (ስኪነር፣ 1971)፡፡
የሰዉ ልጅ ጭንቀት ምንጩ አርነት ነዉ
ሳርተር ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም እና ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ ዉስጥ እንደ ጻፈው፤ የሰው ልጅ በጭንቀት እንዲኖር የተኮነነ ፍጡር ነዉ፡፡ እንዴት? ሳርተር እንደሚነግረን፣ ባይተዋር ፍጥረት የሆነው ሰው የራሱ እግዜር በመሆኑ በሕይወቱ ለሚፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ባለዕዳ ነው፡፡ የጭንቀቱ ምክንያት ይህ ሐቅ ነው፡፡ ሰው ፍፁማዊ አርነቱን በማወቁ ምክንያት የተወለደውን ጭንቀት ለመሸሽ የተጎናፀፈውን አርነቱን ተጠቅሞ ማንነቱን መለወጥ የማይችል ቁስ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ይህን ዘዴ ሳርተር ግብዝነት ብሎ ይጠራዋል፡፡ ግብዝነት የሰው ልጅ የተጎናፀፈውን ፍፁማዊ አርነትና ኃላፊነት በመገንዘቡ ሳቢያ የተፈጠረውን ጭንቀት ለመሸሽ የሚያበጀው ዘዴ ነው፡፡
***
ከአዘጋጁ፡-
መኮንን ደፍሮ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር ድግሪውን በ2009 ዓ.ም፣ የማስተርስ ድግሪዉን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በጅማ፣ በመቐለ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡ ጸሐፊው አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ መጽሔቶች ግጥሞቹንና የልብ ወለድ ሥራዎቹን አሳትሟል፡፡      መኮንን በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡



Read 237 times