Monday, 15 April 2024 09:32

የደግ ሰው መንገድ

Written by  በጸጋዬ አዳም ምልከታ
Rate this item
(2 votes)

 የመፅሐፉ ርዕስ -  ግርባብ  [ያ ደግ ሰው]
ደራሲ -ፍቃዱ አየልኝ
ስነ ፅሁፉዊ ዘውጉ -prose poetry fable
የገፅ ብዛት - 237  
የሕትመት ዘመን - 2016 ዓ.ም

[በሀሳብና በልብ ሀገር ላይ እየተመላለሰ የሕይወትን፣ የጊዜን  የነፍስንና  የፍጥረትን ተነፃፃሪ መልክ ለመፍታት እንዲኹም ውላቸውን ለመጨበጥ... ጥያቄዎችን አንስቶ እንዲኹ ጠይቆ ለመደመም..
አቃተን ያልናቸውን ሀሳቦችና በምን ተረድተናቸው ያልናቸው ሁነቶች ...  እንደ ተወለወለ ጥሩ መስታየት ነፀብራቅ በማያደናግር መልክና በለስላሳ ወንድማዊ ጨዋታ እንድንመለከት አምኃ (ስጦታ) የኾነን ግርባብ መጽሐፍ በእኔ  ንባብ ይሄን መሳይ መልክ ተመልክቼበታለኹ፡፡] 
ግርባብ  በ [prose poetry fable]  መልክ (literary gener) የተፃፈ ኾኖ  ጥልቅ የሐሳብ መጠይቁ[ profundity]ው ደግሞ በ ያ ደግ ሰው አፈ ቀላጤነት  የሚጠየቁት የፍልስፍና ‘ ሐሳቦች የተሳፈሩበት፣ በአተራረኩ [ ደግሞ በሁለተኛ መደብና በሦስተኛ መደብ ሁሉን አወቅ የተተረከልን  ግሩም ስራ ነው...  
በእርግጥ  ደራሲው  ያንን  ነኝ ለማለት ይሄንን የሚተው ወይም ወዲህ ያለውን ለመጨበጥ ከወዲያ ያለውን የሚለቅ አይነት ባይኾንም፣ ትረካዎችን አዛንቆ በማጫወት  እስከዛሬ ካየኋቸው በአማርኛ ቋንቋ  ከተፃፉ መጻሕፍት የተለየ፣ የተለያዩ ጀነራዎችን በማዛነቅ (hybrid ) መልክን ቀምሮ  አስመልክቶኛል፡፡ .
እንግዲህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንከታተላቸው ደራሲዎች ፀሐፊዎችና ገጣሚያን  የተለየ ቅርፅ በመፍጠር (experimental ) ስራዎችን ሰርተን አዲስ ነገር እናመጣለን በሚል የሙከራ መከራ ውስጥ እንደወደቁና classic የኾነው የቀደሙት ጣፋጭ ዓይነትኛ ስራዎች በካልቾ ተመተው አዋራ እየለበሱ መኾኑን አንባቢ ልብ ይሏል.. ይሄ ባለበት ሁኔታ  እንደዚህ ያለ ጥዑም አተራረክ ያለው ስራ ማግኘት የሚያስደንቅ ነው:: 
አይንን ገርበብ አድርገው እንዲኹ እንደዋዛ የጀመሩት መፅሐፍ፣ “ወረቀት ከአድማስ እንደሚሰፋ” እያስረዳ ‘ና ልጓም በሌለው ንፋስ ጀርባ ኮርቻ እንደተጫነች ላባ እብስ አድርጎ ወስዶ የመጨረሻውን ገፅ ጨርሰው ካልዘጉት በስተቀረ ለበኋላዬ ይትረፈኝ ብለው የሚያስቀምጡት መፅሐፍ አይደለም...
ምናልባት ዘግተው ቢያስቀምጡት እንኳን እንደ አንድ ሰበዝ የሳቧትን ሀሳብ እንደ ጠገበ ገኛ ሲያመሰኩባት ቢውሉ እንጂ በዋዛ የምትለቅ መች ኾና....  
“ደግሞ እንደዚህ ተብሎ ነገር ከመሀል ይጀምራል”  [መቅድም]
ልብ ስፍራዋን ከመሀል እንዳደረገች ሁሉ፣ ያ ደግ ሰው ነገርን ከመሀል ጀምሮ፣ ሰው በኾንኩት ብሎ የሚመኘው አይነት አመኝ በደረስኩበት ብሎ የሚማልልለትን(የሚመንንበትን) ንፁህና ጠያቂ ማንነቱ ይዞ ያገኘውንና የተገረመበትን ወዳጄና ገንዘቤ በማለት የምን ግዜም አስገራሚ መደነቅ የሞላቸው ጥያቄዎችን ለቀረቡት (ለተወዳጁት) ያቀርባል…
ከእነዚህ መሀልም  ለእኔ ሰባት ጉዳዮች ጥሩ ጥያቄ አንስተው አይነተኛ መልስ ያገኘኹባቸው  ቀድሞ ሸክሞቼ ዛሬ ደግሞ ወረቶቼ (ንብረቶቼ) ናቸው…
1. ፈጣሪን፣ ጊዜ’ና ቦታን፣ ነፍስ፣ ሩህ እና ሞት (Creator .time & space ,ruh. soul.and death )
2  ትፍስህት፤ ሀሴት (plasure), እና ውበት(beauty )
3 ምክንያት (reason) እና ግፊት ስሜት (emotions)
4  ወዳጅነት,(friendship) ትስስር እና ጨዋታዎች (talkings)
5 ደስታ፣ ሀዘን እና ህመም (joy, sorrow,and pain)
6 የመኖር ህግ ‘ና የአኗኗር ብልሀት፣  ቅጣት እንዲኹ ምህረት
7.  ዋጋ እና ሚዛንን (ወደር)፤ (value,&balance  እነዚህንና ሌሎች ወዝና ልዩ መልክ ያላቸው ሀሳቦችን አጣጥሜያለው…
     ለዛሬ በመጀመሪያ ቀጥር ላይ የተነሱትን ሀሳቦች ግርባብ ያ ደግ ሰው እንደምን ጥያቄ አንስቶ በ“ዲያሌክቲክ” ሀሳብ አጋራባቸው የሚለውን እንዝለቅበት…
የደራሲው በምዕናብ ሀገር ላይ እንደ ልብ የመጫወት ብቃት፣ በትልልቆቹ የስነ ፅሁፍና የፍልስፍና ባለሟሎች የተመሰከረ  በመኾኑ በመድገም አንባቢን አናደክምም ... ይልቅስ ደግ ሰው እያንዳንዳችን በየዋህነትና በትህትና የቆምንበትን ወይም የአምላክን ባህሪ የተጋራ ደህንኛ መልካችንን(higher self) ቁርጥ ይመስላል፡፡
እንደ እንግዳ የተቀበልነው ደግ ሰው፣ ሰንብቶ ተላምዶን የሾምነው እንደራሴያችን ይኾናል..
ትንሽ የከረመ እንደኾነ ደግሞ እንደራሴ ያልነውን እኔ ራሴ ልንለው ይዳዳናል!
ደራሲው ለነገዬ ብሎ ሳይሰስት የሰጠንን ስራ ስንመለከት፣ ሌሎች ድርሳናትን ለመስራት የማይደክመውና የብዕር ዕርፍን ጨብጦ አሁንም የሀሳብ ሁዳድ ላይ ወዲህ ወዲያ እያለ እየዘራ  እንደኾነ እናውቃለን....   
በግርባብ ያ ደግ ሰው በታኀዝቦ ከተደነቀባቸው( wonder ካደረገባቸው) ብዙ ሀሳቦችን መሀል ሰባት መስመር ሰጥተናቸው ለመመልከት እንዲመቹን ሰደርናቸው፤ ከእነዚያ መሀል ቀዳሚዎቹ፡-
ፈጣሪ፤,ጊዜ እና ቦታ፣ ሩህ፣ ነፍስ እና ሞት ቀድመው ይመጣሉ
ደራሲው ቀደም ሲሉ በተለያዪ አለማት ለተሰሩ እንደነ [Tao te ching - laozi ] የእነ አቦይ ላዑዙ እና [the art of war -sun Tzu] እና ጋሼ ሰን ዙ  መጻሕፍትና ለእነ አለቃ ኮንፊሺየስ [confucius]  ውዴታ አለው፤ ኾኖም እነዚህ ድርሳናት ከተፈጥሮ ጋር አብሮ ስለመኖር(harmony )የስነ ፍጥረትን መነሾ ሀሳብ (ideal of all existence ) ምኞትን እና መከራን (desire and suffering )
ስነ ባህሪ (disciplines) ጥንቅቅ ብሎ መዘጋጀትን (being prepared ) ታዛዥነትን .
ባስ ሲል ደግሞ እርስ በራስ ተገናኝቶ የተቋጠረንና ውል የጠፋበትን የሀሳብ አለም ቋጠሮ እየፈቱ እርስ በእርስ ሲደጋገፉና ሲወዳደሱ የነበሩ አሳቢያን ሲኾኑ፤ ለዚህም ኹነኛ ማሳያው ኮንፊሺየስ አቦይ ላዉዙን ለመጎበኘት የሄደበት ሁኔታን ማምጣት ይቻላል…
[the meeting of tow masters] በመባል በሚታወቀው በዚህ የሁለት ታላላቅ ፈላስፋዎች ግንኙነት፣ ኮንፊሺየስ ስለ ላውዙ ይሄንን  ምስክርነት እንዲሰጥ አስችሎታል፡-  “በሰማይ የሚበር ወፍ በወንጭፍ ይወድቃል፤ በጫካ ውስጥ የሚኖር አውሬ ደግሞ በቀስት ወይም በወጥመድ ይታደናል፤ ባህርን ቤቴ ያለ አሳ በመረብ ይጠመዳል.. :-በሰማይ ከደመናው በላይ አልፎ በጀግንነት የሚበርን ነፋስ የማይገታና የማያሸንፈው ደራጎንን ግን ምን ያደርጉታል? እንዴትም ሊያጠምዱት አይቻላቸውም፤ መንገዱም ወደ ገነት ነው!’” [ ልክ እንደዚህ በንግግራቸውም በአሳባቸውም ላቅ ያሉ ዲያሌክቲኮችን በግርባብ መፅሐፍም] እናገኛለን…
ላውዙም በሰማይ የሚበር መንገዱም ወደ ገነት የኾ ደራጎን የሚል ምስክርነት በኮንፊሺየስ ተሰጥቶታል…
[As for dragons, I don›t know if they can arise to the heaven along with a wind. I met with Lao Tzu today. Maybe he is like a dragon!”]  (confucius about lao tzu)
እነ ጋሼ ኮንፊሺየስ  እነዚህን አወዳጅተው ሲያነሱ፤
የነገረ አምላክን (ፈጣሪን) ጉዳይ ያላስተዋሉ እና ወይም የዘነጉ ይመስላል ... በግርባብ መፅሐፍ ደግሞ ደራሲው ይህንን ክፍተት (missing link) ለመሙላት እና ሌሎችም የሀሳብ ዳናዎችን በመምዘዝ፣ መሬታውያንን፤ ሰማያውያንን፤ ሌሎችንም ከየት ወደ የት ናችሁ ብለን እንድንጠይቅ  ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግነው ነው::
1.1»ፈጣሪ “
“ደሞ ሰው እኮ ዝም ሲል አምላክን ይመስላል። ከተናገረ ግን ያው ሰው “ሰው” ነው”፡፡ ይሄ ሀሳብ ለመፅሐፉ መቅድም እንዲኾን ደራሲው የፃፈው ነው...ዝምታ የአምላክ ዋነኛ ባህሪ ነው፤ የቀረው ፍጥረት ሁሉ ደካማ ትርጓሜዎች ናቸው የሚባለውን የቀድሞ አነጋገር እያስታወሰ፣ የፈጣሪን አንድ መልክ ያመላክተናል፡፡
«ያ ደግ ሰው ስለዚህ የጊዜ ቆጣሪ ማሰሪያ ነፍስ ነው እያልህ ነው? ብሎ ሰዓት ሰሪውን ይጠይቀዋል፡፡  ሰዓት ሰሪውም፤  አዎን “አላህ ጊዜ ባህሪዬ ነው ይላል፡፡”
እዚህች ጋር አስምርልኝ እንግዲህ፡፡ [ገፅ-68]
በዚህ ዟሪ በተባለ ጽሁፍ ውስጥ ያለ ሰፋሪ  ጊዜ፣ ቆጣሪ የሌለውን ሰአት እንደሚመስል ተናግሮ እኛም ዘላለማዊውን ስፍር የሌለውን ጊዜ ባሰብን ግዜ ባዶ (vacuum)ኾኖ ወደ ሀሳባችን ይገባል፤ ከባዶም ባዶ የኾነውን መቀመጫ የሌለውን ባዶ ለማሰብ በተቸገርን  (ስፍራ የማይዝን ነገር ሰው ለማሰብ ይቸግረዋል)ጊዜ ግን እሱ የአምላክን መልክ እንደሚመስል ይነግረናል፡፡
«ኩብኩባ “በሚል ስም በተፃፈችው መጣጥፉ ውስጥ [ገፅ-10] እናት ዶሮ እና አባት ዶሮ ስለ መፍጠር ይህን ይነጋገራሉ:- “አባት ዶሮ እንቁላሉ አንቺ ሳትኖሪ ቢፈለፈል ራሱ ራሱን የወለደ ይመስለዋል” እንደ እንቁላል ባለች ክብ አለም ውስጥ ስንቱ ነው የራሱ ፈጣሪ እንደኾነ የሚያስበው.? አምላክ ግን እዚህ ውስጥ ሙቀት ሰጪና አቃፊ ኾኖ ይነሳል::
«እናት ዶሮ  አምላክ እንደኔ ላባ አለው ማለት ነው? ያሞቃል? በሽፋኑ ፍጥረት ገምቶ እንዳይቀር ያደርጋል? አለችው”
ይሄ ስለ አምላክ የተነሳ ትልቅ ጥያቄ ነው!
“አባት ዶሮ በአመድ ውስጥ የተቀበረ ፍሬ ሙክክ ብሎ እንደሚበስል፣ ደመናው አመድ ነው ሰው ደግሞ እንዲበስል ተቀብሮ ነው ተጥሎ አይደለም አላት::”  [ገፅ-11]  ቀጥሎ እናት ዶሮ በምን መልኩ ሰማይና የሰማይ እውቀት እንደሚገለጥ  ትናገራለች....   
እንዲኹም “ሳላህ” በሚለው የወዳጆች ጨዋታ ውስጥ [ገፅ-13] ስለ ቡቃያ አንስተው፤ “ የልቦና መድረቅ  ከጨለማ ጥቁረት ከእሳት ግለት እንደሚከፋ አውስቶ  ለዚህም ደራሽ የኾነው መልአክ ገብርኤል ቅዱስ ቃል “በአምላክ ረድኤት” ይዞ እንደሚመጣና ለልቦና መንገድ ማሳያ “ብርሀን ቃል እንደሚያዘንብ እና የሞተች ነፍስ መልሳ እንደምትለመልም ያበስረናል!   ለእውቀት የአምላክን ተራዳኢነት ይነግረናል… ቃል እና ሀሳብም ብርሀን የኾነውን መንገድ ለማግኘት እንደ እግር መብራት ያሉ እንደኾነ ሀሳብ ያመጣል..
ያ ደግ ሰው፣ ከአንዲት ዕጣን ከምትሸጥ ሴት ጋር በሚያደርገው የሀሳብ ልውውጥ ደግሞ፤ ከጥሩ እጣን ጥሩ ስም አብልጦ ሽታው ደስ እንደሚያሰኝ ትነግረዋለች... [ምዑዝ ገፅ-38] ያ ደግ ሰውም ሰባት ሰማያት ያክል ቆሞ የተጠቀለለ ጭስ በልቦናው እያሸተተ ሲሄድ አሰበ እናም “አኹን ከሰማየ ሰማያት የዘለቀ የአምላኬ ጥሩ መዓዛው እየሸተተኝ ነው፤ ልሂድ ልከተለው” አፍንጫውን ወደ ላይ ቀስሮ እያነፈነፈ መንገዱን ይቀጥላል... 
«ወራጅ እና ቋሚ” ላይ ደግሞ ደግ ሰው ከአናጢ ጋር ሲነጋገር የአምላክ ዐሳብ ራሱን ችሎ እንጨት ይጎትታል፤ ወራጅና ቋሚ አቁሞ ቤት ይሰራል፤ ገብቶም ይኖርበታል::
እናም ሰው፣ ሰው የአምላክ ዐሳብ ነው የሚመስለኝ ይለዋል::” “ሰጪ አምላክ ንብረቱን ለማን እንደሚያሲዝ ያውቃል”
(እውቀትም ንብረትም አያያዙን ላወቀበት የአምላክ ቸሮታ ነው ...ይለናል [ዓለም ቀን ገፅ-74]
የአምላክ እና የገበሬ መመሳሰል ከ”ሳላህ” ጋር ባደረጉት ጨዋታ እንህ ይነሳል ገበሬ አምላክን መሳይ ከመካከል የተበላሸውን  አረማሞ የወረሰውን፣  እሪያ የበተነውን፣ ጃርት የቦጠቦጠውን እየተወ ለመልካም ቡቃያዎች ግን  ለእናንተ አዲስ ጎተራ አላችሁ ይላቸዋል...”የዛፍ ብስል ወደ መሬት፣ የሰው ብስል ግን ወደ ሰማይ ይወድቃሉ” በዚህም ደራሲው የሰማይን ዜና ለመስማት በልቡ ወደ ሰማይ የወደቀ ነው! 
 እንግዲህ እንዲህ እያጫወተ ደጉ ሰው፣ ስለ ፈጣሪ በ”ነፍስና ዜማ፤ በመቃ፤ በላም እና ገመድ በምዑዝና ሌሎችም አርዕስት በሰጣቸው  ጣፋጭ ወጎቹ ውስጥ” ፈጣሪን ሲያወሳ ተመልክተናል...በተለየ ደግሞ “መድኅኒት”  በምትለው ወግ ውስጥ  ከበሽታ ጋር ተነጋግሮ “አንተም ፈጣሪን ታውቃለህን ? ወይ ብሎ ይጠይቀዋል  [ገፅ-60]
በሽታም፡-”ሳይፈጠር ጊዜ ላይ የሚሰፍር የለም ...እንኳን እኔ ድሮውንም የነበርኩት አንተም እንኳ ባቅምህ አኹን መጥተህ እንደተፈጠርህ ታውቃለህ:: ችግርህ ካልተራመደና ካልበረረ የለም ስለምትል ነው” ብሎ (Existence of GOD )ን እንድንመረምር እንድንረዳ የሚጋብዝ ምላሽ ይሰጠዋል!  በዚህም ሲበርና ሲራመድ ያላየነውን አምላክ በምን ልንመረምር እንደምንችል ያመላክተናል....
ሁሉ ነገር የጀመረው ከነጥብ ነው፤ ነጥብ ደግሞ አንድ ነው:: አንድ ደግሞ አምላክ ነው::(ነቁጥ)  በመጨረሻም አንድ መለዮ ሰሪ ለደጉ ሰው ይህንን ይሉታል ....
“ልብ ማለት ያለብን ግን ሰማይን እንደ ቆርቆሮ ክዳን፣ መሬትን እንደ ወለል አድርገን አምላክን ዉጪ እንዳናሳድረው ነው። ሁሉም የእርሱ ሲኾን “ያ ብቻ ያንተ ብለን አንከለክለውም” በማለት ሁሉን ነገር ለፈጣሪ አሳልፎ ይሰጣል! ያ ደግ ሰው.!
ጊዜና ቦታ (time and space )
ጊዜን በግርባብ መጽሐፍ ውስጥ ያ ደግ ሰው እንደ ሀገር እና ስፍራ ያነሳዋል:: ጊዜ እንደ ሀገር ከታሰበ ደግሞ ተራራ ሸለቆ ጉድባ በተጨማሪም  ኗሪ ይኖረዋል ...ኗሪዎቹም ሞት እና ዘመዶቹ እንደኾኑ፣ እንቅልፍ የሞት ታላቅ ወንድም፣ እንጉልቻ እና በሽታ የቅርብ ተጠሪዎች እንደኾኑ… ኩርባና ገደል ባለው ግዜ ውስጥ እንዲኹ ከባህር ወደ አየር ዘሎ ወጥቶ ተመልሶ እንደሚገባ አሳ...
የጊዜ ሀገር ላይ ተዘዋውረው ለመምጣት ይቻል እንደኾነ፣ አንድ ሰዓት ሰሪ እና ደግ ሰው ይነጋገራሉ...
ደግ ሰው ጊዜ በጉድባው ላይ የያዛቸውን ነገሮች አራግፎ ምን እንደሚመስሉ ለመመልከት ሲጥር-ጊዜ ያለ ሰፋሪ ቀፎ እንደኾነ ይናገራል፡፡
-ጊዜ   የፈጣሪ ባህሪ እንደኾነ
_የጊዜ ቆጣሪ ማሰሪያ ነፍስ እንደኾነ ያመላክተናል!
_ጊዜ የቆመን ሰው ይመስላል መለመላውን
 ለተመለከተው ደግሞ ዝም ያለውን ነፋስ መትቶ ወዲህ እና ወዲያ የማይንቀሳቀሰውን ዛፍ ይመስላል፡፡
-ጊዜ የሚታሰበው ትልቅ ሰው ሲነሳበት ነው ይለናል፡፡ ትልቅ ሰዎች ጊዜ ስፍራ እንዲይዝ ስራ ያበጁበታል፡፡  ይሄ ድንቅ አተያይ ነው!
1.3 ሩህ እና ነፍስ (ruh and soul)  
ስለ ሩህ እና ነፍስ ልዩነት የሚያጫውተን ደግ ሰው፣ ሩህ ከነፍስ ቀድማ በተገነባ የሰው አካል ውስጥ የምትከተት ማብሪያ (birth of life) ስትኾን፣ ነፍስ ሰውና ቤቱን አንድ ላይ እንደማየት ስትኾን ሩህ ደግሞ ሰውዬውን ለብቻ እንደማየት ነው [ገፅ-130] ይለናል....
 ሰሪ የሩህን ልኬት የሚያውቅ ነውና የአካልን ወርድ እና ቁመት ይወስናል... ያ ደግ ሰው ከአናጢ ጋር ባደረገው ጨዋታ ይህን ይጠይቃል:- “እንደነገርህ ከኾነ የአጭር ሰው ሩህ በረጅም ሰው ጀሰድ(አካል) ውስጥ ብትገባ ሰፊ ጫማ እንዳደረገ ጎተት ጎተት ትላለች። እንዲኹም ሰዎች ራስ ገዝ የማይኾኑት ሩሐቸው በሰፊው አካላቸው ውስጥ ማነሷ ነውን? ይላል..ያ  ግምበኛም:- ምን እሳት እኮ ትንሹ ይበቃል፣ እፍ ካልከው ይፈጋል። ወራጅ እና ቋሚ] ገፅ-146]
አንዳንድ ሰው፣ እሳት ብርሀን የኾነችውን ሩሑን እንደ ማሾ መብራት ጠምዝዞ አያደምቃትም ደግሞ ይገርምሀል ሩህ ፍም መሳይ እፍ ተብላ ካልፈገገች ፤ አካል ውስጥ ያለው ጨለማ የማይገፋ እንደ ተቦካ ሊጥ የዳጎሰ ነው አለው...በዚህም ሩህ የአካል ብርሀን ኾና ትነሳለች...ነፍስ ደግሞ...መልኳን እና ከብደቷን ለማወቅ ደግ ሰው ከአንድ ነጋዴ ጋር ይህቺን ቂሷ ያወጋባታል... 
ያ ነጋዴ :- ነፍስ ወደ ሰማይ ስትሄድ በስንት ግመል ተጭና ነው?
ያ ደግ ሰው :- ነፍስ እኮ ሳትሄድ ነው የምትደርሰው
ያ ነጋዴ :- ሳይሄዱ መድረስ እንዴት ያለ ነው?
ያ ደግ ሰው :-ቀድሞውንም የነበረ አምላክ ሳይሄድ እንደኖረ ይኖራል ! ብሎ በአስተማስሎ ይነግረናል....ነፍስ እንደ ጊዜ ማሰሪያ እንደ ህይወት ማብሪያ፣ በተለያየ ቦታ እየተነሳች ትመጣለች፤ ልስላሴዋ ደግሞ ከውሃም ከጥላም ይልቃል፡፡
ያ ደግ ሰው :- “አሁን የምታየው የሰው አካል  ዐውሎ ነፋስ እንደቆመው ዐቧራ ነው። ነፋሱ አደብ ገዝቶ መረበሹን የተወ ቀን ተንጠልጣይ አፈር ከከፍታው ይዘረገፋል፤ብሎ ነፍስ በአካል ውስጥ ያላትን አስሮ ያዥ ሚና ይነግረናል.፡፡ [ገፅ-78-79 አውድማ]
በእነዚህ እና በሌሎች ወጎች ውስጥ የነፍስን ምንነት፣ የነፍስን አካሄድ፣ የነፍስን ሁነኛ ስፍራ እያዋዛ ለነገረን ደራሲ እጅ ነስተን ምስጋናን ሰድደናል!
1.4  ሞት
በዚህ መፅሐፍ ውስጥ አንድ የሀሳብ ማጠንጠኛ የነገር መወጠኛ ነው...በዚህም ረመጥ የሚል ርዕስ ስር ሞት እና መረሳትን በአንድ ላይ አምጥቶ፣ ነገር ግን በዚህ ባለቤቱ ሞታበት ሁለት አመት ሀዘን ያልወጣለትን አባወራ አምጥቶ  ጓዱ መረሳትን ረስቶ የሄደ ሞት፣ የንግግሯ  ውቅራት ጥሩ የሀሳብ ከተማ ይመስል የነበረውን ሚስቱን እያስታወሰ ስር ለሰደደ ሀዘን የተዳራገውን ሰው፣ የሞትን ህመም ክፋት ተናጋሪ ያደርገዋል ....  [ገፅ -51 ረመጥ]
ሌላም ደግሞ ሞት አገላብጦ አብሳይ፣ ሞት አንዱን ወስዶ ሌላን በተራው አዲስ እንዲቆም የሚያደርግ ኾኖ ተከስቷል፤ በዚህም የዚያ ደግ ሰው ልጆች የኾኑት ውብ አንተ እና ማማሩ ላም እና ገመድ በሚለው አርዕስት ውስጥ በሚለዋወጡት ዐሳብ፤  እውነታ በሚታይ ነገር ላይ ብቻ የሚመሰረት ከኾነ ስምምነትህ ሞትን ያህል ጉድ ያቀፈ ነው ይለዋል፤ መሞት ማለት አለመኖር እንዳልኾነና ስፍራ የመቀየርን ነገር  የማይታይ ነፋስ የሚታይ ቅጠልን መግፋቱን አንስቶ ሞትን በአስተማስሎ(metaphor ) እና በአስረጂ እያዋዛ ይነግረናል...
እዚህ መፅሐፍ ውስጥ ሌሎችም ብዙ እንደ አለት ይከብዳሉ ስንል፣ ደራሲው እንደ ላባ አንስቶ  እንድንነጋገርባቸው የሚያስችሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጪው ጊዜ ቀስ እያልን እነሱ ላይ እንጨዋወታለን…
በመጨረሻም፡- “የማየት ብርሀን በወረቀት ገላጣው ላይ አርፎ፣ ግለቱ ፊደልን እያቃጠለ ዐሳብን ካላተነነ መፅሐፍ ዝግ ከተማ ነውና [ገፅ 109] 
እያነበብን ብርሀን እናምጣ፤ ነገር በደፈናው እዳ ነው! ብሎ ሀሳብ አበጥሮ እንድናብጠረጥር የሰጠንን  ደራሲ ፍቃዱ አየልኝ፣ ምስጋናህን ውሰድ እንላለን .. ሰላም !
                        መልካም  ንባብ!

Read 263 times