Saturday, 20 April 2024 10:37

የውጭ ዕዳ የብር ሕትመት ምክንያት አላቸው። ከዚያም ለሌላ ችግር ምክንያት ይሆናሉ።

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

በብር ሕትመት ሳቢያ የዋጋ ንረት ከዓመት ዓመት ይጫወትብናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት የውጭ ዕዳ በአገሪቱ ጫንቃ ላይ ይከመርባታል።
ሁለቱም ምክንያት አላቸው። በእርግማን የሚመጡ አይደሉም።
ጦርነቶች ወይም የመንግሥት ፕሮጀክቶች የበረከቱ ጊዜ፣ ልጓም የበጠሰ የውጭ ዕዳ ሲጋልብ ይመጣል፡፡ መረን የለቀቀ የብር ሕትመት ይፈጠራል።
“የውጭ ዕዳና የዶላር እጥረት” እና “የብር ሕትመትና የዋጋ ንረት”… ምክንያት አላቸው፤ የችግር ውጤቶች ናቸው የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው።
አሳዛኙ ነገር፣ የውጭ ዕዳና የገንዘብ ሕትመት እንደገና በተራቸው አዳዲስ ሕመሞችን ጎትተው የሚያመጡ የችግር ቫይረሶች ይሆኑብናል።
እስቲ የታሪክ መዛግብትን በማገላበጥና የመረጃ ሰንጠረዦችን በመፈተሸ፣ ይህን እውነት ለማረጋገጥ እንሞክር።
የ50 ዓመታትን ጉዞ በአራት ከፍለን እንመልከት። በቅድሚያ የደርግ ዘመንን እናያለን። ከዚያም በኢህአዴግ ዘመን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም የሥልጣን ዓመታትን እንቃኛለን። ከዚያም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ ጅምር ጉዞን እንመለከታለን።
የእርስበርስ ጦርነትና አስፈሪ የውጭ ዕዳ ክምር - በደርግ ዘመን
በደርግ ዘመን፣ አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ፣ በዐሥር ዓመት ልዩነት የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ወደ ዐሥር ዕጥፍ ጨምሯል።
በ1967 ዓ.ም ፡    340 ሚሊዮን ዶላር
በ1972 ዓ.ም ፡    820 ሚሊዮን ዶላር
በ1982 ዓ.ም ፡    8.6 ቢሊዮን ዶላር
የንጉሥ ኃይለሥላሴ መንግሥት የዛሬ 50 ዓመት ከሥልጣን በወረደበት ጊዜ፣ የመንግሥት የውጭ ዕዳ ለእያንዳንዱ ሰው ቢከፋፈል፣ የ10 ዶላር ሸክም ነበር።
በደርግ የሥልጣን ዓመታት ውስጥ የውጭ ዕዳ እጅግ ከመከማቸቱ የተነሳ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሸክም ወደ 180 ዶላር ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል።
በየዓመቱ የውጭ ዕዳ ከነወለዱ ለመክፈል የሚወለው ዶላርም በዐሥር ዐመት ልዩነት ዕጥፍ ድርብ ጨምሯል።
ዓመታዊ የዕዳ ክፍያ ከነወለዱ
በ1967 ዓ.ም ፡    25 ሚሊዮን ዶላር
በ1972 ዓ.ም ፡    45 ሚሊዮን ዶላር
በ1982 ዓ.ም ፡    235 ሚሊዮን ዶላር
በዓመት ከኤክስፖርት የተገኘው ዶላር በሙሉ ለዕዳና ለወለድ ክፍያ ነበር የሚውለው ማለት ይቻላል።
ለምሳሌ በ1980 ከኤክስፖርት አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ለዕዳና ለወለድ ደግሞ ከ ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር  በላይ ተከፍሏል። ምናለፋችሁ! የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልቁል እየተንደረደረ የእንጦሮጦስ አፋፍ ላይ ተንጠልጥሎ ነበር።
ለነገሩ ዘመኑም ነው ችግሩ። የበርካታ አገራት ኢኮኖሚ ልክ እንደ ኢትዮጵያ በሶሻሊዝምና በጦርነት ምክንያት እየተፍረከረከ በዕዳ ክምር ሥር እየተንኮታኮተ ነበር ማለት ይቻላል። የዕዳ ምሕረትና  የብድር ስረዛ የሚል ዘመቻ ዋና የዓለማችን አጀንዳ እስከመሆን የደረሰውም ያኔ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
የሆነ ሆኖ፣ አገሪቱ ጦርነትም፣ የኢኮኖሚ ቀውስም፣ የውጭ ዕዳ ጫናም ተደማምሮባት ድቅቅ ያለችበት እጅግ ክፉ ጊዜ የትኛው ነው የሚል ጥያቄ ቢመጣ፣ “የደርግ የማብቂያ ዘመን” ብለን መልስ መስጠት እንችላለን።
የመጀመሪያዎቹ የኢህአዴግ ዓመታት - ድክምክም ያሉ ዓመታት ናቸው።
በኢህአዴግ ዘመን ለተወሰኑ ዓመታት የመንግሥት የውጭ ዕዳ ብዙም አልጨመረም። በኋላ ነው ችግር የመጣው።
በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አገሪቱ ለተጨማሪ ብድር የሚሆን ዐቅም ስላልነበራት፣ እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ የብድር ሩጫ አልታየም።
የመንግሥት የውጭ ዕዳ በሰባት ዓመት ልዩነት ምን እንደሚመስል ተመልከቱ።
በ1983 ዓ.ም ፡    9.3 ቢሊዮን ዶላር
በ1990 ዓ.ም ፡    10.3 ቢሊዮን ዶላር
ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ ታሪክ መጥቷል። በተከታታይ ዓመታት ለድኻ አገራት የዕዳ ስረዛ ስለተደረገ፣ ተከምሮ የቆየው የዕዳ ሸክም በአብዛኛው ተቃልሏል ማለት ይቻላል።
ዐሥር ቢሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረው የውጭ ዕዳ ክምችት ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወርዷል።
ከዚያስ፣ ከዚያማ እንደገና ሽቅብ መጋለብ ጀመረ።
የመንግሥት ፕሮጀክቶች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን
    
የውጭ ዕዳ ክምችት
በ1998 ዓ.ም    2.2 ቢሊዮን ዶላር
በ1999 ዓ.ም    2.6 ቢሊዮን ዶላር
በ2000 ዓ.ም    5.4 ቢሊዮን ዶላር
በ2001 ዓ.ም    7.3 ቢሊዮን ዶላር
በ2002 ዓ.ም    8.6 ቢሊዮን ዶላር
በ2003 ዓ.ም    10.5 ቢሊዮን ዶላር

የመንግሥት የውጭ ዕዳ ለጊዜው በብድር ስረዛ ቢቃለልም፣ እንደገና በዐጭር ዓመታት ውስጥ በፍጥነት እንደጨመረ የዓለም ባንክ መረጃዎች ያሳያሉ።
በእርግጥ፣ የውጭ ዕዳ እንደገና መከማቸት የጀመረው፣ በወቅቱ የግጭትና የጦርነት ቀውስ ስለተፈጠረ አይደለም። ጦርነት አልነበረም።
ነገር ግን የመንግሥት ፕሮጀክቶች እጅግ የተስፋፉበት ዘመን እንደሆነ ማስታወስ ይቻላል።
10 የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ ለስኳር አገዳ እርሻ የግድብና የመስኖ ሥራዎች…
ከ3.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጁ የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች…
ከግልገል ጊቤ 3 ግንባታ በተጨማሪ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚጠይቅ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግንባታ…
ከዚያም የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት…
ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ድንገት የተበራከቱበት ዘመን ነው ማለት ይቻላል (1998 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ)።
የውጭ ዕዳም በዚያው ፍጥነት በአራት ዕጥፍ ጨምሯል።
ይህም ብቻ አይደለም።
የብር ሕትመትም በፍጥነት ጨምሯል።
በአገሪቱ ውስጥ የነበረው የብር መጠን፣ በአምስት ዓመት ልዩነት ሦስት ዕጥፍ ሆኗል።
    
የብር ብዛት
1998    24 ቢ
1999    27 ቢ
2000    35 ቢ
2001    45 ቢ
2002    50 ቢ
2003    70 ቢ


በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመንም፣ የውጭ ብድር በክምር በክምር ሲከማች እንደነበር ነው የዓለም ባንክ መረጃ የሚያሳየን።
የብር ሕትመትም ስላልረገበ፣ የብር ብዛት በአምስት ዓመት ልዩነት ከዕጥፍ በላይ ሆኗል።
     የብር ብዛት  
2005    75 ቢ
2006    90 ቢ
2007    100 ቢ
2008    120 ቢ
2009    145 ቢ
2010    175 ቢ


ይህም ብቻ አይደለም።
የውጭ ዕዳ ከ10 ቢሊዮን ዶላር ተነስቶ ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል (በስድስት ዓመታት ልዩነት)።
    
የውጭ ዕዳ ክምችት
2005    12.5 ቢ ዶላር
2006    17 ቢ ዶላር
2007    20.5 ቢ ዶላር
2008    23.5 ቢ ዶላር
2009    26 ቢ ዶላር
2010    27.8 ቢ ዶላር


በተለይ ደግሞ በ2007 ዓ.ም ከግል አበዳሪዎች የመጣው የ1 ቢሊዮን ዶላር ብድር፣ እጅግ ከባድ ስህተት እንደነበር ያኔ በጊዜው ብዙዎች ተናግረው እንደነበር ዛሬ ድረስ ያስታውሳሉ።
“አገርን በቦንድ እንደ ማስያዝ ነው የሚቆጠረው” በማለት አምርረው የተቹም ነበሩ። በ6.6 በመቶ ወለድ የመጣው “የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ብድር”፣ በእርግጥም “ከባድ ስህተት” እንደሆነ አያጠራጥርም። መጠራጠር ካማረን፣ እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ ምን ዐይነት ሸክም እንዳስከተለና አሁንም ቅንጣት ታክል እንዳልተቃለለ በማየት ማረጋገጥ እንችላለን።
በዓመት 66 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ይከፈልበታል።
እስከዛሬ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወለድ ተከፍሏል።
1 ቢሊዮን ዶላሩ ብድር ግን እስካሁን ቅንጣት ሳይቃለል፣ እንደያኔው ዛሬም አለ - “የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ብድር ዕዳ”።
ካለፈው ሐምሌ ወዲህ ግን መንግሥት ይህንኑን ወለድ መክፈል አቁሟል። ለምን? የወለዱ መጠን እንዲቀንሱለት ለማስገደድ ወይም ለመደራደር የፈለገ ይመስላል። አበዳሪዎቹ ግን እስካሁን ምንም የድርድር ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም።
ቀላል ውዝግብ አይደለም። መጨረሻው ምን እንደሚሆን ከወዲሁ ለማወቅ ቢያስቸግርም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ምኞት ጉዳዩ በድርድር ወይም በሽምግልና እንዲያልቅ ነው። የወለድ ክፍያ እንዲሻሻልለት ማለት ነው። አለበለዚያ ደግሞ አበዳሪዎች በዓለማቀፍ ተጽዕኖ ወይም በክስ ክፍያቸውን ለማስከበር ይሞክሩ ይሆናል።
መጨረሻው ምንም ሆነ ምን፣ “የውጭ ዕዳ ክምችት” በጣም አስቸጋሪ ሸክም እንደሆነ ከዚህችው የ1 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መረዳት አይከብድም።
ለባቡር መስመር፣ ለስኳር ፋብሪካና ለሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ከቻይና፣ ከቱርክና ከህንድ መንግሥታት የተገኙ ብድሮችም ትልቅ ሸክም ናቸው።
ባለፉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ ለውጭ ዕዳና ለወለድ 15 ቢሊዮን ዶላር መንግሥት እንደከፈለ አስቡት።
ከዚህ ውስጥ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የተከፈለው፣ ለወለድ ነው።
በተገኘው ብድር ምን ተሠርቶበት ምን ትርፍ ተገኝቶበት ነው ይሄ ሁሉ ወለድ የተከፈለበት?
መንግሥት በብድር ሠርቶ ትርፍ ሊያገኝ? ያማ ቀልድ ነው። እንዲያውም በብድር የተጀመሩት በርካታ ፕሮጀክቶች ገና አልተጠናቀቁም። የወለድ ክፍያ፣ ከንቱ ኪሳራ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ የባሰም አለ።
ብድር ለጦርነት ሲሆን ኪሳራው ድርብ ይሆናል። በብድር በተገዛ መሣሪያ እርስ በርስ እንገዳደላለን። ሀብት እናወድማለን። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን አናሰናክላለን። ከዚያ ደግሞ ብድር ከነወለዱ የመመለስ ሸክም ይጠብቀናል።
በእርግጥ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከውጭ የተገኘው ብድር እንደድሮው አይደለም። ትንሽ ነው። ለጦር መሣሪያ ግዢ የሚተርፍ አይደለም። የብድር ምንጮች በገፍ መልቀቅ ትተዋል። ብዙዎቹ አገራት በየራሳቸው ጣጣ ተጠምደዋል።
በዚያ ላይ፣ የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በርካታ ለጋሾችንና አበዳሪዎችን አስኮርፏል። ሙሉ ለሙሉ ፊት ባይነሱንም፣ ብድር መስጠታቸው ባይቀርም መጠኑ ቀንሷል። በጭልፋ ሳይሆን በማንኪያ ሆኗል።
ለዕዳና ለወለድ መንግሥት በየዓመቱ የሚያወጣው ገንዘብ ይበልጣል - በብድር ከሚያገኘው ገንዘብ ይልቅ። በዚህም ምክንያት የመንግሥት የውጭ ዕዳ ባለፉት ስድስት ዓመታት አልጨመረም ማለት ይቻላል።
እስካለፈው ጥር ድረስ የመንግሥት የውጭ ዕዳ 29 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ በቅርቡ የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርት ይገልጻል።
ነገር ግን፣ በጦርነት የተመሳቀለና እየተጎሳቆለ የሚገኝ አገር፣ ወይ የውጭ ዕዳ ይከመርበታል። ወይ ደግሞ በገንዘብ ሕትመት የዋጋ ንረት ይጫወትበታል ብለን የለ?
ከውጭ ዕዳ ክምር ብናመልጥም፣ ከብር ሕትመትና ከዋጋ ንረት ግን አላመለጥንም።
በአራት ዓመት ልዩነት ውስጥ፣ የአገሪቱ የገንዘብ ብዛት ከ200 ቢሊዮን ብር ወደ 480 ቢሊዮን ብር ንሯል።
    
የብር ብዛት  
2011    200 ቢ
2012    245 ቢ
2013    265 ቢ
2014    360 ቢ
2015    480 ቢ


የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተቀዛቀዘበት ጊዜ፣ የብር ሕትመት እንዲህ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በዕጥፍ ሲትረፍረፍ፣ ብር መርከሱና ኑሮ መወደዱ ምን ይገርማል?
እንግዲህ ቁምነገሩ ምንድነው?
ልጓም ያጣ የውጭ ዕዳ ወይም የብር ሕትመት፣ እንዲሁ ያለ ምክንያት አይመጣም። የመንግሥት ፕሮጀክቶች እንደ አሸን ሲፈሉ ወይም ደግሞ የፖለቲካ ትርምሶችንና ጦርነቶችን ስናበዛ፣ የውጭ ዕዳ ይከመርብናል። መረን በለቀቀ የብር ሕትመት ሳቢያ የዋጋ ንረት ይግለበለባል። የኑሮ ውድነት ይጫወትብናል።
አዎ፣ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እርባታ ለጊዜው ረግቧል። ጦርነቶችን ከማዛመት ግን አልተቆጠብንም። መቼ ነው የሚበቃን?  

Read 634 times Last modified on Saturday, 20 April 2024 12:29

Media

file:///C:/Users/Aster/Desktop/%E1%8A%A8%E1%8B%9A%E1%8B%AB%E1%88%9D-%E1%88%88%E1%88%8C%E1%88%8B-%E1%89%BD%E1%8C%8D%E1%88%AD-%E1%88%9D%E1%8A%AD%E1%8A%95%E1%8B%AB%E1%89%B5-%E1%8B%AD%E1%88%86%E1%8A%93%E1%88%89%E1%8D%A2.html