Sunday, 28 April 2024 21:08

እርግማን ንግግር እየመሰለ ይገድላል ጠበል ውሃ እየመሰለ ይምራል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ሁለት ንሥሮች ስለወደፊት ዕጣ-ፈንታቸው ይጨዋወታሉ፡፡ አንደኛው - “እኛ ንሥሮች፤ ሰዎች እንዳያጠቁን በየጊዜው እየተገናኘን መወያየት፣ መነጋገር፣ ደካማ ጎናችንን እያነሳን መፍትሔውን ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ንሥሮች ሰብስበን እንነጋገርና አንድ ዓይነት አቋም እንያዝ”
ሁለተኛው ንሥር - “በዕውነቱ በጣም ቀና ሀሳብ ነው፡፡ ሁሉም እንዲሰበሰቡ ማስታወቂያ እንለጥፍ” አለ፡፡
በዚህ ተስማምተው በዓይነቱ ልዩ ነው የሚባል (Extraordinary) አጠቃላይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ ንሥር- ሜዳ በሚባል ሰፊ ቦታ በተባለው ሰዓት ማንም ንሥር እንዲመጣ፤ የቀረ ከመላው ንሥሮች እንቅስቃሴ ያፈነገጠ፣ ከሀዲ (Saboteur) ነው የሚል ማስጠንቀቂያም ታከለበት፡፡
በተባለው ቦታና ሰዓት የአገሩ ንሥር ሁሉ ተሰበሰበ፡፡ ‘አጀንዳው “ከዛሬ ጀምሮ ሰው እንዳያጠቃን አንድ ዓይነት አቋም ይዘን በጥንቃቄ እንድንንቀሳቀስ ይሁን፣” የሚል ነው፡፡ በመሰረቱ ሰው እኛን መናቁ ያለ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ነገር ከትንሽ ጀምሮ ወደ ትልቅ እንደሚያድግ፣ ከቀላሉ ወደ ውስብስቡ እንደሚሄድ ካለመረዳት የሚመጣ ግብዝነት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም አቅማችን ትንሽ ቢሆን፣ ቀስ በቀስና ከቀን ቀን ስለምንጠነክር ትንሽነት አይሰማችሁ፡፡ ብርታት ከትንንሾች ህብረት የሚመጣ ነው” አለና ንግግር አደረገ፣ ሰብሳቢው ንሥር፡፡ ሁሉም በክንፎቻቸው አጨበጨቡ፡፡ በንሥራዊ ድምጽም እልልታቸውን አሰሙ፡፡ “የንሥሮች ኅብረት ለዘለዓለም ይኑር” የሚል መፈክር በአንድነት አሰገሩ፡፡
ይህ ስብሰባ በተካሄደ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በአንድ ጫካ ውስጥ አንድ አዳኝ ቀስትና ደጋን ይዞ ታየ፡፡ ንሥሮቹ ሁሉ እየተመካከሩ ሸሹ፡፡ አዳኙም ተናዶ ወደ መንደሩ ተመለሰ፡፡ ሌላም ቀን ለአደን መጣ፡፡ ንሥሮቹ ተጠራርተው በረሩ፡፡
አንድ ቀን ግን አዳኙ ንስሮቹ በማያውቁት አቅጣጫ ዞሮ ወደ ጫካው ገባ፡፡ ከንሥሮቹ አንዳቸውም አልጠረጠሩም፡፡ ኮሽታ ታህልም ድምጽ አልሰሙም፡፡
አዳኙ ዓልሞ ወደ አንደኛው ንሥር አነጣጠረ፡፡ ቀስቱን ስቦ ሲለቅቀው አንደኛው ንሥር ልብ ላይ ተተከለ፡፡ ንሥሩ ልቡ ላይ የተተከለው ስል ቀስት በጣም ባሰቃየው ጊዜ፣ በጣሩ ቅጽበት ወደ ኋላ ዞሮ ተመለከተ፡፡ የቀስቱን ጫፍ አየው፡፡ የቀስቱ ጭራ የተሰራው ከንስር ላባ ነው፡፡ ህመሙ በርትቶበት ሊሞት ሲል እንዲህ አለ፡-
“እኛ እራሳችን በሰጠነው መሣሪያ ስንወጋ ነው ለካ፣ ቁስሉ የበለጠ ጥልቀት የሚኖረው”
ከዚያም ለምታስታምመው ንሥር እንዲህ አላት፡-
“ከእንግዲህ ለጠላታችን አለመመቸት ማለት የራሳችንን መሳሪያ አለመስጠት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ወደ እኛ መምጫዎቹን በሮች በሙሉ ጠንቅቆ ማወቅና መዝጋት ነው፡፡ ይህንን ለወገኖቻችን ሁሉ ንገሪ” ብሎ ትንፋሹ አበቃ፡፡
***
መክረው ተመካክረው የሰሩት መንገድ ብዙ ዘመን ያስኬዳል፡፡ የሰው ቤት አያስፈርስም፡፡ የድሃ መተዳደርያ አይነፍግም፡፡ የሰው ድንበር አያስዘልልም፡፡ ማህበራዊ ምስቅልቅል አያስከትልም፡፡ ብዙ ኩርፊያ፣ ብዙ ቅያሜ አይፈጥርም፡፡ ቢሳሳቱ ስንመክር ተሳስተን ነበር፤ ያላየነው - ያላስተዋልነው ነገር ነበር ለማለት አይከብድም፡፡ ራሳችን የሰጠነው መሳሪያ ክፉኛ እንዳቆሰለን ገብቶናል ለማለት ያስችላል፡፡ መሰብሰብ፣ ሸንጎ መዋል የተለመደና የነበረ ነው፡፡ ከዚህ እሳቤ በመነሳት በሀገራችን ከጥንት እስከዛሬ በሽንጎ መምከር ክፉ-ደግ መመርመር የተዘወተረ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ተማሪዎችና መምህራን በዚህ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙ መሆናቸው አሌ አይባልም፡፡ ትምህርት ቤቶች ነጻ የውይይት መድረክ እንዲኖራቸው ብዙ ትግል ተካሂዷል፡፡ ትክክልም ይሁኑ ስህተት በጥቂቶች አነሳሽነት የሚጠሩ ምድር ሰማይ የሚደባልቁ፣ መንግስት የሚነቀንቁ፣ የአገር ዕውነት የሚናገሩ ስብሰባዎች ነበሩ፡፡ ቀስ በቀስም የጎሹት እየጠሩ፣ የጎለደፉት እየተሳሉ፣ የሻከሩት እየለሰለሱ ለሀገር ወደሚበጅ ሁነኛ ጥያቄና መፍትሔ እንዳደጉ አይተናል፡፡ አበው “መንገድና ትውልድ የማያውቅ የተጎዳ ነው” እንዲሉ መንገድ የሚያውቅ፣ በዕውቀት የታነጸ፣ ጠያቂና አስተዋይ ትውልድ ማፍራት ከየዘመኑ ይጠበቃል፡፡ ጊዜ ይጠይቃል እንጂ ፍሬ ያለው ትውልድ ይገኛል፡፡ ቀና ተመኝ ቀና እንድታገኝ ነው፡፡
ከፍተኛ የትውልድ አስተሳሰብ የምናፈልቀው የዕውቀት ምንጭ ከሆነው ት/ቤት ነው፡፡ ለት/ቤት የምንሰጠው ክብር፣ ለዕውቀት የምንጠሰው ክብር ነው፡፡ ለዕውቀት የምንሰጠው ክብር፣ ለትውልድ የምንሰጠው ክብር ነው፡፡  የትምህርት ፖሊሲዎች ጊዜ የተወሰደባቸው፣ ብዙ አዕምሮ የፈሰሰባቸው፣ ለሀገር የማደግ ተስፋን የሚጠምቁ መሆን ይገባቸዋል፡፡  ለመሻሻል እፈልጋለሁ የሚል ዕምነት ያለው ፖሊሲ - ቁራጭ፤ በሂደትና በተመክሮ ስህተት ቢያይ፣ ተከታትሎ ለማረም፤ ተሳስቼ ነበር ለማለት ድፍረት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከእኔ እጅ በሰላም ከወጣ እንደፍጥርጥሩ በሚል ስሜት በተግባር የሚያውሉትን ወገኖች ሌላ አበሳ ውስጥ የሚከትት ከሆነ፣ ችግርን ለመፍታት ችግር ያለበት መፍትሄ እንደ መስጠት ይቆጠራል፡፡ ተመሳሳይ ሰዎች በተመሳሳይ አስተሳሰብ “ልክ ነው” ያሉት ውሳኔ ውሎ አድሮ በተግባር ሲታይ ሌላ ዕዳ ይዞ ይመጣል፡፡ በዳተኝነትም ይሁን በብልጠት እሰይ እሰይ ያሉት ሥራ፣ የማታ ማታ “ሰነፍና ገብሎ ራሳቸውን እንደነቀነቁ ይኖራሉ” የሚለውን ተረት ከማስታወስ በቀር የረባ ለውጥ አያመጣም፡፡
ትላንት የተማርንበት ት/ቤት፣ ዛሬ ተዳክሞ ላለማየት ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ቢያንስ ለመልካም ትዝታችን ቦታ መስጠት፣ የጠንካራን ትውልድ ምንነት ለማጤን ይጠቅማል፡፡ የሠራንበት መስሪያ ቤት ከምናውቀው ተዳክሞ ስናይ፣ የሚሰማን የቁጭት ስሜት የሀገርን መዳከም እንደሚጠቁም ለማየት የአዕምሮ አቅም ማጣት የለብንም፡፡
በተደጋጋሚ የሚወጡ መመሪያዎች፣ ማሻሻያዎች ማጠናከሪያዎች የሚፈጥሩትን እሮሮ፣ እምቢታ፣ የተቃውሞ ምላሽ መመልከት በተለይ እንደኛ ላለ አገር መሰረታዊነትና ተገቢነት አለው፡፡ ብዙ ሰው ተቃውሞ ቀርቶ፣ አልገባንም የሚለውን ጉዳይ ቆም ብሎ አለመመርመር ጎጂ ነው፡፡ ብዙ ሰው የሚያወርደውን እርግማን መናቅ የበለጠ ጎጂነት አለው፡፡ አበው “እርግማን ንግግር እየመሰለ ይገድላል፡፡ ፀበል ውሃ እየመሰለ ይምራል” የሚሉት ለዚህ መሆኑን ልብ ማለት ዋና ነገር ነው፡፡

Read 660 times