Sunday, 28 April 2024 21:10

የሁለቱም ድል ወይስ የሁለቱም ኪሳራ?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

 በጎ በጎውን ያሰማን ብለን በቀኝ ጎናችን ብንነሳ፣ የግል ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን የአገራችን ጦርነቶችን፣ የዓለም ችግሮችም ጭምር የሚጠፉ ቢሆን እንዴት መልካም ነበር። ምን ዋጋ አለው? አይሆንም። ባይሆንም ግን…
ነገሮችን በበጎ ለማየት ልባችን ከፈቀደ፣ ብዙ በጎ ነገር ማየት እንችላለን። አዎ በጎ ያልሆኑ ነገሮች እልፍ ናቸው። ብዙ ሰዎች ይታመማሉ። ይሄ በጎ አይደለም። ግን በደህና አድረው በጤና የማለዳዋን ፀሐይ ለማየት የታደሉ ሰዎችም ብዙ ናቸው። እንዲህ ማሰብ ነው በበጎ በጎውን ማየት ማለት?
አስቸጋሪ ነው። እስቲ ስለ ጦርነት እንዴት እንዴት አድርገን በጎ ነገር ልናስብ እንችላለን? የአገራችን ጦርነቶች ላይ ብናወራ ጥሩ ነበር። ግን ይቅርብን። ብዙ ሰዎች ስለ አገራችን ጦርነት ለማውራት ሲሞክሩ፣ ነገሩን ማባባስ እየሆነባቸው ተቸግረዋል። ትንሽ ከተነጋገሩ በኋላ፣ ሳይታወቃቸው ወደ ንትርክ ይገባሉ። ስድብና ዛቻ መወራወር ይጀምራሉ። በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ነው። የአገራችንን ጦርነት ለዛሬ እንተወው።
ይሄ… የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት እንዴት ነው? ጦርነቱ ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ፣ የየመን የሁቲ ታጣቂ ቡድን ተጨመረበት። በሮኬትና በድሮን ቀይ ባሕርን ሲያናውጥ ስንት ወሩ! ይሄም ሳያንስ፣ ኢራንና እስራኤል በተዘዋዋሪ ሲያካሂዱት የነበረው ጸብ በቀጥታ ገቡበት ተባለ። ይሄ ሁሉ በጭራሽ በጎ አይደለም።
ሰሞኑን ግን ትንሽ ረግቧል።  የኢራንና የእስራኤል የጥቃትና የዐጸፋ ምልልስ አሁን ለጊዜው የተረጋጋ ይመስላል። ተመስጌን ነው። ሰላም እንደማያወርዱኮ ልባችን ይነግረናል። ቢሆንም በሰላም መሰንበታቸው ተመስጌን ነው። የሁለቱ ግጭት ከሰሞኑ ቢረግብም ጸባቸው እየተካረረ እንደሆነኮ ይታወቃል። ቢሆንም ግን፣ ባለፉት ሰባት ቀናት በቀጥታ ስላልተታኮሱ፣ በጎ በጎውን በማየት “እስቲ ያዝልቅላቸው” እንላለን።
ሁለቱም ራሳቸውን እንደ ድል አድራጊ ለመቁጠር መሞከራቸውን ስንሰማ፣ የጸብ ስሜታቸው እንደተጋጋለ እንጂ እንዳልበረደ መረዳታችን አይቀርም። ቢሆንም ግን፣ በበጎ ጎኑ ልናየው ብንሞክር፣ ተመስጌን የሚያስበል ሰበብ አናጣበትም።
ሚሳዬል ተወራውረው፣ ድሮኖችን ለጥቃት አሰማርተው፣ ተታኩሰው አፈንድተው በማግስቱ በየፊናቸው በድል አድራጊነት ከዘፈኑ ምን ማለት እንችላለን?
“የእውነት ግን ድል አድራጊው ማን ነው?” ብለን አስቸጋሪ ጥያቄ ከምናነሣ “ይሁንላችሁ” ብንላቸው ምን ችግር አለው?
“በጦርነት ሁሉም ይከስራል። ማሸነፍም እንኳ በኪሳራ ነው” ስንል እንደነበር አልረሳነውም። ጦርነት በተፈጥሮው “lose-lose” ነው። ቢሆንም ግን፣ ሁለቱም ጸበኞች በየፊናቸው “አሸንፈናል፤ ትርፍ አግኝተንበታል” ካሉ… ምን ይባላል?
“አሪፍ ነዋ፤ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አዲስ የጦርነት ዐይነት ከተገኘ… ሁሉንም ከሚያከስር ጦርነት ይሻላል” ብለን መጽናናት እንችላለን።
ቢዝነስ ወይም ግብይት… ሁሉንም ይጠቅማል ሲባል ነበር የምንሰማው። win-win እንዲሉ ነው። ዛሬ በዘመናችን በአንዳች ተአምር… “የጦርነት ዊን-ዊን” ከመጣ… ጥሩ ነው እንበል?
የእስራኤል የደኅንነት ኀላፊ ግን በዚህ አልተስማሙም። የእስራኤል የዐጸፋ እርምጃ ደካማና ተልካሻ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። “ሽባ ነው” ሲሉም አናንቀውታል። እውነት ለመናገር፣ “ደካማ” ይመስላል። የእስራኤል የጦር አውሮፕላን ቢበዛ ሦስት ሚሳዬሎችን ወደ ኢራን እንደተኮሰ ነው የተዘገበው። በዚህም በጣት የሚቆጠሩ የኢራን የአየር መከላከያ ሚሳዬሎች ተቃጥለዋል።
ከኢራን ጥቃት ጋር ሲነጻጸር፣ የእስራኤል መንግሥት ዐጸፋ “ከቁጥር አይገባም” ማለት ይቻላል። የኢራን መንግሥትኮ 130 ባሊስቲክ ሚሳዬሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል። 30 ክሩዝ ሚሳዬሎችን አምዘግዝጓል። 170 ድሮኖችን አሰማርቷል። ብዙ ነው። የእስራኤል መንግሥት በዐጸፋው ሦስት ሚሳዬል ብቻ?
በእርግጥ፣ ከኢራን ጥቃት በፊት፣ የእስራኤል መንግሥት ጥቃት ፈጽሞ እንደነበር በማስታወስ የዐጸፋ ቀመሮችን ለማስላትና ሒሳብ ለማወራረድ መሞከር አለብን። ሶሪያ ውስጥ የነበሩ ሁለት የኢራን ጄነራል መኮንኖች ከረዳቶችና ከተባባሪዎች ጋር በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል። የጥቃትና የዐጸፋ ሰንሰለቱ የኋሊት እንምዘዘው ከተባለ በቀላሉ ስለማንዘልቀው ለጊዜው ብንተወው ይሻላል።
ሄዶ ሄዶ፣ የኢራን ድሮኖችና ሚሳዬሎች ላይ ይደርሳል። ከዚያም በዐጸፋው ሦስት የእስራኤል ሚሳዬሎች?
ቢንጡት ቢንጡት አንዳችም በጎ ነገር የሚወጣው አይመስልም። መውጫ የሌለው የጥፋት አዙሪት ነው። በጎ ገጽታ ይኖረው እንደሆነ ፈትሸን ብናጣም ግን፣ አጋጣሚውን ለጠቅላላ እውቀት ልንጠቀምበት አንችልም ማለት አይደለም። ስለ ሚሳዬሎችና ድሮኖች አንድ ሁለት መረጃዎች ብንለዋወጥ ምን ክፋት አለው?
“ባሊስቲክ ሚሳዬል” ማለት ጠፈር ድረስ ተስወንጭፎ፣ ቁልቁል እንደ ጠላቂ ዋናተኛ ወደ ኢላማው የሚወረወር ሚሳዬል ነው።
ሩቅ ይጓዛል። ፍጥነቱ ለጉድ ነው። 3000 ኪሎሜትር በሰዓት የሚጓዝ የሚሳዬል አረር… ከፈጣን መኪና 10 ዕጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት ኢላማው ላይ ሲወርድበት… ባይፈነዳ እንኳ፣ ያረፈበትን አካባቢ ያፈነዳል።
የአንዳንዶቹ ባሊስቲክ ሚሳዬሎች ፍጥነት እስከ 20ሺ ኪሎሜትር በሰዓት ይደርሳል። ፍንዳታ ሲጨመርበት አስቡት። ትልልቅ “አረሮችን” የመሸከም ዓቅም አለው - ባሊስቲክ ሚሳዬል። አንድ ኩንታል ፈንጂ ሊሆን ይችላል። 10 ኩንታልና ከዚያ በላይ ፈንጂ መሸከም የሚችሉ ባሊስቲክ ሚሳዬሎችም አሉ።
የሆነ ሆኖ፣ በሮኬት ኀይል ወደ ጠፈር ተስወንጭፎ፣ ወደ ኢላማው ቁልቁል እንደ ዐለት በከባድ ፍጥነት የሚወድቅ ትልቅ ፈንጂ እንደማለት ነው - ባሊስቲክ ሚሳዬል።
ከኢራን ድሮኖች ጋር ማነጻጸር ይቻላል። እንደ መንጋ ወደ እስራኤል የተሰማሩት የኢራን ድሮኖች እንደ ትንሽ መኪና በአራት ስሊንደር ሞተር የሚንቀሳቀሱ፣ በሰዓት 185 ኪሎሜትር የሚጓዙ፣ እስከ 50 ኪሎግራም የሚደርስ ፈንጂ የተሸከሙ በራሪዎች ናቸው።
የእያንዳንዳቸው ዋጋ 20 ሺ ዶላር ገደማ ነው ተብሏል።
በእርግጥ፣ ትልልቆቹ የአሜሪካ ድሮኖች 10 እና 20 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ናቸው። የነ ቱርክ ደግሞ ከ5 እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር። ከባባድ ሚሳዬሎችን ይታጠቃሉ።
ምን ቀረ? ክሩዝ ሚሳዬልና ሮኬት?
ክሩዝ ሚሳዬል፣ እንደ ሮኬትም ነው፣ እንደ አውሮፕላንም ነው። የክሩዝ ሚሳዬል ፍጥነት 1ሺ ኪሎሜትር በሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል። ፈጣኖቹ 5ሺ ኪሎ ሜትር በሰዓት ሊምዘገዘጉ ይችላሉ። ከዚያ ባሻገር የሚፈጥኑ “ሀይፐር-ሶኒክ” ክሩዝ ሚሳዬሎች ገና በሙከራ ላይ እንደሆኑ ነው የሚታወቀው - በራሺያ፣ በአሜሪካ፣ በቻይና።
የክሩዝ ሚሳዬሎች መለያ ባህርይ… አንደ አውሮፕላን “በጄት ኢንጂን” የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው። የበረራ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂም ይገጠምላቸዋል።
ነዳጅ እያቃጠሉ የኋሊት ጭስ በመልቀቅ ወደ ኢላማቸው ይምዘገዘጋሉ።
ኢላማቸውን በትክክል ለመምታት፣ አንዳች የማነጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ። ጂፒኤስ ሊሆን ይችላል። ሙቀት የሚያነፈንፍ ቴክኖሎጂም አለ - (ሂት-ሲኪንግ)። ካርታ የሚያነብ ኮምፒዩተርና ካሜራ የተገጠመላቸውም አሉ። የርቀት መቆጣጠሪያ ጭምር ያካተቱም ይኖራሉ።
ምንም ሆነ ምን፣ ክሩዝ ሚሳዬሎች ወደ ኢላማቸው አነጣጥረው እንዲምዘገዘጉና በትክክል እንዲመቱ የሚረዳ ቴክኖሎጂ አላቸው።
አለበለዚያ ክሩዝ ሚሳዬል አይደሉም። በሌጣው “ሮኬት” ናቸው።
የማነጣጠሪያ ወይም የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ስለሌላቸው፣ “ሮኬቶች” ለአሠራር ቀላል ናቸው። ዋጋቸውም እንዲሁ። የትንንሾቹ ሮኬቶች ዋጋ ከ100 ዶላር አያልፍም።
የአብዛኞቹ ሮኬቶች አረር ከአንድ ኩንታል በታች ነው። የአንዳንዶቹም ጥቂት ኪሎግራም ሊሆን ይችላል። ለነገሩማ፣ “ባዙቃ” ወይም “አርፒጂ” በሚሉ ስያሜዎች የሚታወቁ መሣሪያዎችም፣ “ሮኬት” በሚል ተርታ የሚመደቡ ናቸው። ከትከሻ ላይ የሚተኮሱ ናቸው። የተተኳሾኩ ክብደት ሁለት ኪሎ ግራም አይሞላም።
በግዙፍ መኪኖች ላይ የጫኑ ትልልቅ ሮኬቶችም አሉ።
በጥቅሉ፣ በሌጣው “ሮኬት” ተብለው ከተጠሩ፣ በቴክኖሎጂና በዋጋ ዝቅ ያሉ መሣሪያዎች ናቸው።
እንግዲህ፣… በጎ በጎውን ለማሰብ ያህል፣ በጦርነት ሰበብ ጥቂት የጠቅላላ እውቀት መረጃ ብናገኝ ይሻላል በሚል ነው የባሊስቲክና የክሩዝ ሚሳዬል ዐይነቶችን፣ የድሮንና የሮኬት ጥቂት መረጃዎችን የተናገርነው።
እንግዲህ… የኢራን መንግሥት እስራኤል የጥቃት ዘመቻ ለማካሄድ፣ በቅድሚያ የድሮን መንጋ በማሰማራት ለምን እንደጀመረ ሦስት ምክንያቶችን መዘርዘር እንችላለን ማለት ነው። ከሚሳዬል ጋር ሲነጻጸር፣ የድሮኖቹ ፍጥነት አነስተኛ ነው። 180 ኪሎሜትር በሰዓት። ስለዚህ ከሚሳዬል ቀድመው ነው ጉዞ መጀመር ያለባቸው። ድሮኖቹ ወደ እስራኤል አካባቢ ለመድረስ ሲቃረቡ፣ ክሩዝ ሚሳዬሎችን ማምዘግዘግ፣ ባሊስቲክ ሚሳዬሎችን ማስወንጨፍ!
ነገር ግን፣ ስላስወነጨፉና ስላምዘገዘጉ፣ አገሬውን ማደባየት ይችላሉ ማለት አይደለም።
የእስራኤል የአየር መከላከያ መሣሪያዎች በጣም የተራቀቁ ናቸው። በዚያ ላይ ድርብርብ የቴክኖሎጂ አጥር ናቸው። የእስራኤል የአየር መከላከያ ቴክኖሎጂዎችን አልፎ ኢላማ መምታት ቀላል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቶ የለ! የመጡበትን ሮኬቶች በአብዛኛው እንደሚያከሽፍ ይታወቃል።
ለዚያም ነው፤ የኢራን መንግሥት ድሮኖችን እንደ መንጋ አስቀድሞ ያሰማራው።
የእስራኤል የአየር መከላከያ የድሮኖችን መንጋ እየመታ ለመጣል ሲዋከብ፣ ክሩዝ ሚሳዬሎችና ባሊስቲክ ሚሳዬሎች ከመከላከያ አጥር አምልጠው ወደ ኢላማ የመግባት ዕድል ያገኙ ይሆናላ! በእርግጥም፣ አምስትም ይሁኑ ዐሥር ጥቂት የኢራን ባሊስቲክ ሚሳዬሎች ወደ ኢላማቸው አካባቢ ደርሰዋል። የኢራን መንግሥት ስሌት ተሳክቷል ማለት ይቻላል።
በእርግጥ ወደ ኢላማቸው አካባቢ የደረሱ ሚሳዬሎች ብዙ ጉዳት አላደረሱም ተብሏል። ደግሞም፣ አብዛኞቹ ሚሳዬሎች እንደከሸፉ ተዘግቧል። ይሄስ ለእስራኤል እንደ ስኬት ይቆጠራል?
የእስራኤል የአየር መከላከያ ቴክኖሎጂዎችና መሣሪያዎች እንደተወራላቸው በጣም “ምርጥ” እንደሆኑ በተግባር አስመስክረዋል ተብለው ተደንቀዋል። እንዲያውም፣ መሣሪያዎቹን ያመረቱ ኩባንያዎች በሚቀጥሉት ዓመታት ብዙ ገበያ ያገኛሉ ተብሎ ስለተገመተ፣ በጥቃቱ ማግሥት የአክሲዮን ዋጋቸው ጨምሯል።
ታዲያ፣ መርሳት የሌለብን ነገር መኖሩን እናስታውስ። ግማሾቹ ድሮኖች ገና ወደ እስራኤል ሳይደርሱ ነው በአሜሪካ አየር ኀይል እየተመቱ የወደቁት። ደርዘን የሚሆኑ ሚሳዬሎችም በአሜሪካና በእንግሊዝ ትብብር ከሽፈዋል። የተወሰኑት ድሮኖች ደግሞ በዮርዳኖስ አየር ኀይል አማካኝነት ወድቀዋል። ያለ እነዚህ ትብብር እስራኤል የኢራንን ጥቃት በብዛት ማክሸፍ ይችል ነበር ወይ የሚል ጥያቄ አይታያችሁም? ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ራሱ እንደ ኪሳራ አይቆጠርም?
እንዲያም ሆኖ፣ የእስራኤል ጦር ኀይል በደርዘን የሚቆጠሩ ድሮኖችና መቶ የሚሆኑ ሚሳዬሎችን ማክሸፍ ነበረበት - ከጉዳት ለማምለጥ። በአብዛኛውም ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል። አለበለዚያ ጉዳቱ ከባድ ሊሆን ይችል ነበር - በሕይወትም፣ በንብረትንም፣ በስነልቦናም።
የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ወዲያውኑ በላይ በላዩ እያከታተሉ ተመሳሳይ መግለጫ ሰጥተዋል። “የኢራን መንግሥት ጥቃት ከሽፏል። ለእስራኤል ድል ነው” በማለት ደጋግመው ተናግረዋል። ይህን ለመናገር የተሽቀዳደሙት፣ “የዐጸፋ እርምጃ አያስፈልግም” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን የኢራንን ጥቃት በዝምታ እንደማያልፉት ነበር የተናገሩት። ለምን?
ኢራን በቀጥታ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽማ አታውቅም። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዚያ ላይ የጥቃቱ ክብደትም ቀላል አይደለም። ለጥቃት የተሰማሩት የድሮኖች ብዛት በታሪክ ታይቶ አይታወቅም።
ለነገሩ፣… ዛሬ ዛሬ “በታሪክ ታይተው የማይታወቁ ነገሮች” ብዙ ናቸው።
ባለፈው ጥቅምት ወር ከ1200 በላይ እስራኤላውያን የተገደሉበት የጥቃት ዘመቻ፣ በእስራኤል ታሪክ ታይቶ አይታወቅም ተብሎ እንደነበር ታስታውሳላችሁ።
በዚሁ የሐማስ ጥቃት ሳቢያ የተጀመረው ጦርነት እስከ ዛሬ አልቆመም። በሐማስ ከታገቱት ሰዎች መካከል ገሚሶቹ አልተመለሱም። በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ ለማረጋገጥም አስቸጋሪ ሆኗል። ለወራት በዘለቀው ጦርነት በመቶ የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን እንደሞቱ ተዘግቧል። 35 ሺ ገደማ የጋዛ ነዋሪ ፍልስጥኤማውያን እንደሞቱም ተገልጿል። ከፊሎቹ የሐማስ ታጣቂዎች ቢሆኑም፣ አብዛኞቹ ሟቾች ግን ሲቪሎች ናቸው።
ይሄም ካሁን ቀደም በአካባቢው ታይቶ አይታወቅም ተብሏል።
ለነገሩ በሁቲ ታጣቂ ቡድን አማካኝነት የተፈጠረው አደገኛ የቀይ ባሕር ነውጥስ በታሪክ ታይቶ ያውቃል? ድሮ ጥንት በታጣቂ ሽፍቶች ምክንያት “የአባይ በረሀ” ለተጓዦች በጣም አስፈሪ እንደነበር በታሪክ ይነገራል። አንድ ታጣቂ ቡድን ቀይ ባሕርን  መዝጋት ይችላል ብሎ ማሰብ ግን እስከ ዛሬ አስቸጋሪ ነበር።
ዛሬ ዛሬ አዲስ ታሪክ በዝቷል። በጎ ታሪክ ቢሆን ጥሩ ነበር። ጦርነቶችንና ጥቃቶችን ትተን፣ ቴክኖሎጂውን ብቻ እያየን ለማድነቅ ብንሞክር የሚሳካልን አይመስልም። ቴክኖሎጂው ድንቅ ሊሆን ይችላል። አስደናቂ ቴክኖሎጂ እየታጠቁ መጠፋፋት ወይም የጥቃት ኢላማ መሆን ምኑ ደስ ይላል? ድሮኖችን በ20 ሺ ዶላር፣ ሮኬቶችን ከ100 ዶላር እስከ 1 ሺ ዶላር እየገዙ፣ ከሩቅ እስከ ቅርብ አካባቢን ማናወጥ ይቻላል። ለቀይ ባሕር ጊዜው በጎ አልሆነም።
በየሳምንቱ ከ500 በላይ ትልልቅ መርከቦች በቀይ ባሕር ይተላለፉ ነበር። ከሁቲ ታጣቂዎች ጥቃት በኋላ ግን የመርከቦች ቁጥር በግማሽ ቀንሷል። የሁቲ ታጣቂዎች ይህን እንደ ትልቅ ድል ሊቆጥሩት ይችላሉ። አላማቸው ቀይ ባሕርን ማናወጥ ከሆነ ያለ ጥርጥር ተሳክቶላቸዋል።  
በእርግጥ፣ የተተኮሰ ሮኬት ኢላማውን ይመታል ማለት አይደለም። ፈንጂ የጫነ ድሮን በሙሉ ኢላማውን የማፈንዳት ዕድል ያገኛል ማለት አይደለም። እንዲያውም፣ የሁቲ ታጣቂ ብድን ሮኬቶችና ድሮኖች በአብዛኛው በአየር መከላከያ መሣሪያዎች እየከሸፈ ነው ብለን መናገር እንችላለን። ይሄስ ለአሜሪካ ወይም ለቀይ ባሕር እንደ ድል ይቆጠራል?
ለሁቲ ታጣቂዎችም ለአሜሪካ ጦርም እንደ ድል የሚቆጠር ከሆነ፣ ነገርዬው “ዊን-ዊን” ሊሆን ነው?
የኢራንና የእስራኤል ግጭትም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ባሕርይ አለው።
አዎ፣ የእስራኤል የአየር መከላከያ፣ የሐማስ ሮኬቶችን ሲያከሽፍ ታይቷል። የኢራን ሚሳዬሎችንና ድሮኖችንም በአብዛኛው ማክሸፍ ችሏል። የአሜሪካ የአየር መከላከያም ከሁቲ ታጣቂዎች ወይም ከኢራን የሚመጡ ድሮኖችን፣ ሮኬቶችንና ሚሳዬሎችን በአብዛኛው እያከሸፈ ነው።
ነገር ግን “ማክሸፍ” በነጻ አይገኝም። ዋጋ ይከፈልበታል።
የእስራኤል መንግሥት ከሐማስ የተተኮሱ የ100 ዶላር ወይም የአንድ ሺ ዶላር ሮኬቶችን ለማክሸፍ የ50 ሺ ዶላር ሚሳዬሎችን ይተኩሳል።
የአሜሪካ መንግሥት የ20 ሺ ዶላር ድሮኖችንና ሮኬቶችን ለማክሸፍ የሚሊዮን ዶላር ሚሳዬሎችን ያምዘገዝጋል።
ይሄ፣ ለእስራኤልና ለአሜሪካ ትልቅ ኪሳራ ነው። ታዲያ ለሐማስና ለኢራን እንደ ድል አይቆጠርም? ነው እንጂ።
በእርግጥ ለነሱም ኪሳራ ነው። የኪሳራው መጠን ይለያያል እንጂ፣ የተተኮሰ ሮኬትና ሚሳዬል ማለት፣ የተቃጠለ ሀብት ማለት ነው። መሬት ላይ ተበትኖ፣ ስንዴ ወይም ድንች ሆኖ አይበቅልም።
እየተቃጠሉ ማቃጠል ነው - ጦርነት። ለሁለቱም ኪሳራ ነው።
ዊን-ዊን አይደለም ማለት ነው።

Read 536 times