Thursday, 09 May 2024 17:12

ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ የተመሰረተበትን የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓል በይፋ ማክበር ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
  ባለፉት 50 ዓመታት ከ8ሚ. በላይ ዜጎችን መድረስ ችሏል

  በአሁኑ ወቅት 700ሺ ዜጎች የፕሮጀክቱ  ተጠቃሚዎች ናቸው

  ትልቅ የሀገር ሃብት ነውና መከበርና መጠበቅ አለበት ተብሏል



ላለፉት አምስት አሰርት ዓመታት የቤተሰባቸውን እንክብካቤ ያጡና የቤተሰባቸውን እንክብካቤ ለማጣት በአደጋ ላይ ያሉ ህፃናትን የቤተሰብ እንክብካቤና ጥበቃ አግኝተው እንዲያድጉ ለሁለንተናዊ ዕድገታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በማሟላት እንክብካቤ በመስጠት የሚታወቀው ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ፤ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል  በይፋ ማከበር ጀመረ።

ድርጅቱ በእነዚህ አመታት፤ በአማራጭ የቤተሰብ ክብካቤ፣ በቤተሰብና ማህበረሰብ አቅም ግንባታ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲሁም በትምህርት በጤናና በወጣቶች ማብቂያ ፕሮግራሞች ከ8ሚ. በላይ ዜጎችን መድረስ እንደቻለ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡  

ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ የተመሰረተበትን የ50ኛ ዓመት ክብረ-በዓል  አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ በድርጅቱ ዋና መ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኤስ ኦ ኤስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ ክብረ-በዓሉን አስመልክተው ሲናገሩ፤ ”ለ50 ዓመታት በቁርጠኝነት ፣በፍቅርና በብዙ ለውጦች የታጀበውን ክብረ በዓል ለማክበር በመብቃታችን ታላቅ ኩራት ይሰማናል።” ብለዋል፡፡

“ድርጅቱ ዛሬ የደረሰበት የስኬት ምዕራፍ የሰራተኞቻችን፣ የለጋሾቻችን፣ አጋሮቻችንና የምናገለግላቸው ማህበረሰቦች የጋራ ጥረትና የማያቋርጥ ድጋፍን የሚያንፀባርቅ ነው። በራስ መተማመንና በጥንካሬ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች ሁሉ አልፈው የትናንት ህፃናት የዛሬዎቹን ብርቱ ወጣቶች ማሳያ ነው።” ሲሉም አክለዋል፡፡


ያለፉት ዓመታት የልማት ስራዎቹንና ስኬቶቹን ለመዘከር ዓመቱን ሙሉ የሚከወኑ የተለያዩ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀቱን የገለፀው ኤስ ኦ ኤስ፤ ክብረ በዓሉ የድርጅቱን  ስኬቶችን ለማንፀባረቅ፣ ያበረከተውን  አስተዋፅኦ በጉልህ ለማሳየት፣ ድርጅቱን ያገለገሉትን ሰራተኞችና ደጋፊዎቹን ዕውቅና ለመስጠት እንዲሁም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ህፃናት ለማገልገል ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ዕድል እንደሚሰጠውም አመልክቷል።

በ1966 ዓ.ም በአገራችን ለተከሰተው ድርቅ ከመንግስት ለቀረበለት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ፣ የመጀመሪያ ሥራውን በመቀሌ የጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ አገልግሎቱን አስፋፍቶ በ 9 ክልሎች ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ፣ “ህፃናት በፍቅር በሰላምና በሙሉ ዋስትና ሲያድጉ ማየት” የሚል ራዕይ ያነገበ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ምንም እንኳን ዋና  የትኩረት አቅጣጫዎቹ ህፃናት ቢሆኑም ቅሉ በአሁኑ ወቅት በማህበረሰብ ልማት ላይ በስፋት ተሰማርቶ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በአንድ የኢመርጀንሲ ፕሮጀክት ወደ ስራ የገባው ድርጅቱ፤ ዛሬ 41 ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ እንደሚገኝና  ከእነዚህ ውስጥ 7ቱ ብቻ የህፃናት ፕሮጀክቶች እንደሆነ ይገልፃል። የኤስ ኦ ኤስ ዳይሬክተር እንዳስረዱት፤ የቀሩት የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው።



 ድርጅቱ በህፃናትና ቤተሰብ ላይ አተኩሮ ከሚያከናውናቸው ጉልህ ስራዎች ጎን ለጎንም፣ የወጣቶች ልማትና የስራ ፈጠራ፣ የአደጋ ጊዜ እርዳታ፣ የትምህርትና ጤና ስራዎችም ላይ በስፋት እንደሚሳተፍ ለማወቅ ተችሏል።

የኤስ ኦ ኤስ አመራሮች የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እንዲሁም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተወክለው የተገኙ ሃላፊዎች ስለ ድርጅቱ በጎ ሥራዎች  ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በአገሪቱ ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ከሚንቀሳቀሱ 5ሺ የሚደርሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ኤስ ኦ ኤስ ተጠቃሽ ነው ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን  ም/ዳይሬክተር ፤ድርጅቱ በስራውም በምግባሩም የተከበረና የተደነቀ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያው ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች  በግዙፍነቱ በአለማቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ ነው ያሉት ም/ ዳይሬክተሩ፤ ትልቅ የአገር ሃብትና ተቋም በመሆኑ መከበርና መጠበቅ አለበት ብለዋል።

 ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ህፃናት በፍቅር የተሞላ ቤተሰብ ሲሰጥ የቆየው የዓለማቀፉ የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ፌዴሬሽን አካል ነው።  ኤስ ኦ ኤስ በመላው ዓለም በ132 አገራት የሚንቀሳቀስ ሲሆን በዓለማቀፍ ደረጃ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት  እያከበረ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
Read 599 times