Saturday, 08 October 2011 09:52

ደሴን ያያችሁ... የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ረድኤት መስፍን
Rate this item
(0 votes)

...በአሁኑ ሠዓት እንኳ የሬዲዮናችሁን ጆሮ እየጠመዘዛችሁ ጣቢያ ብትቀይሩ አንድ የወሎ ጣዕመ ዜማ አታጡም፡፡ ከፈለጋችሁ የመጽሐፍት መደርደሪያችሁን በርብሩት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ስለ ደሴ ውበት የሚተነትን ሽራፊ ገፅ አይጠፋም፡፡ ደሴ እድለኛ አገር ናት፡፡ የማያቁት አገር አይናፍቅም የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ፉርሽ አድርጋለች፡፡ በተለይ እንደ እኔ ወጣት ወንድ ከሆኑ ልብዎ መንጠልጠሉ አይቀርም፡፡ እዚያ የእየሩሳሌምን ቆነጃጅት የመሠሉ እንስቶች እንዳሉ ተነግሮኛል፡፡

የውበት ምንጭ የሆነ ቦርከና የሚባል ጠበል ለዘመናት እንደሚረጭ ተተርኮልኛል፡፡ ባቲ የተሠኘ የጀሮ ቅባ ቅዱስ እንደሚጐረስ ተቀንቅኖልኛል፡፡ ሎካሉንና ቪአይፒውን የማይነጣጠል አይጠየፍ የሚሉት ማዕደ ሞሠብ እንዳላቸውም ተሠብኮልኛል፡፡ ባይገርማችሁ ጠፍቶ የተገኘ የመድሀኒያለም ታቦት ሲገኝ |ለአላህ ምን ይሳነዋል´ ብሎ የሚደሠት ሙስሊም አለ ብለው አጫውተውኛል፡፡ እውነት ለመናገር ከተማዋን ለማየት የዩኒቨርሲቲ ጥሪውን እንደሚጠብቅ አዲስ ተማሪ ጓጉቼ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ተሳካልኝ፡፡ ደሴን አየኋት፡፡ ደሴ የለችም፡፡ ወይም ደብቀውኛል፡፡ ጦጣ ተራራ ወጥቼ ለጋበዙኝ የካምፓስ ጓደኞቼ እንዲህ አልኳቸው፡፡ “ደሴን ያያችሁ...ው...” እነርሱም መለሱልኝ... “አላየንም እባካችሁ...ው...”
ሀገርን ፍለጋ
የማቱሳላን ዕድሜ የተሸከመ ከተማ አሁን የት ገባ ይባላል? ማንንስ ምን ተብሎ ይጠየቃል?
ከአዲስ አበባ በኮተቤ ደብረ ብርሀን መንገድ ስትነኩት፣ አስፓልቱና መልክዓ ምድሩ ምቾት የሚነሳ አይደለም፡፡ ደብረ ሲና ላይ ያሉትን አስፈሪ ዋሻዎች ካለፉ በኋላ ለምሳ መቆም ግድ ነው፡፡ በእርሥዎ ትዕዛዝ እንዳይመስልዎ፡፡ በሾፌሮቹ ነው፡፡ የተፈቀደው 20 ደቂቃ ነው ይላል፤ ረዳቱ ሌባ ጣቱን እየነቀነቀ፡፡ እንደ ገጠር ሠርግ እንግዶች የሚበዙባት ደብረ ሲና የቋጠረችውን ስንቅ ፈታ ማቋደስ ታውቅበታለች፡፡ የምግብ ጥራቱ የልብ ካላደረሠ ደግሞ የእነአብራሽ ቆሎ አለ - እጅ የሚያስቆረጥም፡፡ ይሉኝታ-ቢስ ከሆኑ በቅምሻ ብቻ ጠግበው ወደ መኪናዎ ይመለሳሉ፡፡
ጉዞው ቀጥሏል፡፡ ከደጋው የሸዋ ምድር ወደ ሙቀቱ የሸዋ ሮቢት ቀርበናል፡፡ ከደገኞቹ ወደ ቆለኞቹ ሠፈር ሠዎች ተቀላቅለናል፡፡ ብርቱካን መግዛት ፈልገዋል? እጅ ካላጠረ መግዛት ይችላሉ፡፡ እንዴት እንደሚጣፋጥ ባዩት፡፡ ከሚሴ ደረስን፡፡ አሁን ሹፌሩን አንድ ነገር ይዘዙት፡፡ እባክህ ሙዚቃውን ከፍ አድርገው በሉት፡፡ አለበለዚያ ሙቀቱ መከራ ነው፡፡ በራፐሮቹ “ሬጌ ከሚሴ” ዜማ ኮምቦልቻን እንለፍና ሙዚቃ እንቀይራለን፡፡ ካልሆነ የገራዶ ጠመዝማዛ መንገድ ፈተና ነው፡፡  
ኧረ ደሴ ደሴ ገራዶ ገራዶ
አለቀልሽ ልቤ ተንዶ ተንዶ… ያለው አዝማሪ ወዶ አይደለም፡፡
ባለታሪኮቹ እንደነገሩኝ ደሴ የ229 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናት፡፡ ወይም ከባህር ዳር በሁለት እጥፍ አለበለዚያ ከሀዋሳ ከሦስት እጥፍ በላይ ትሸመግላለች፡፡ 1885 ዓ.ም ንጉስ ሚካኤል ላኮመልዛ ብለውም ሰይመዋት ነበር፡፡ ቃሉ የአፋን ኦሮሞ ሲሆን ትርጉሙ |የቆንጆ ማሠሪያ´ ማለት እንደሆነ መረጃ አጣቅሰው አስረድተውኛል፡፡
ደሴ በር (እነርሱ ሸዋ በር ይሉታል) ሲደርሱ ዓይን ቁልቁል ይወረወራል፡፡ የከተማዋ መንደሮች ከዚህ ይጀምራሉ፡፡ |ሰኞ ገበያ´ ይባላል፡፡ ማዘጋጃ ያላያቸው የጨረቃ ቤቶች መናኸሪያ ይመስላል፡፡ ወደ ውስጥ ቀረብ ካሉ የገበያው ሽታ ያስነጥስዎታል፡፡ አፍንጫዎን ቢሸፍኑም የሸንኮራ ዝንቦች አስገድደው ይወርዎታል፡፡ ራስዎን ለመከላከል ወደ አንድ ካፌ ዘለው ይግቡ፡፡ የሴኔጋል አሜሪካዊው ድምፃዊ ኤኮን ፖስት ካርድ ሊያፈጥብዎ ይችላል፡፡ ከጐኑ ሽጉጥ ያላቸው ቸኮሌት እንስት ቀልብዎን ስባ ማነች ብለው ከጠየቁ ግን “የሠፈራችን ልጅ ሮዚና” የሚል ፈጣን መልስ ያገኛሉ፡፡ በነገራችን ላይ ሮዚና ባለፈው ዓመት ወደ ሀገር ቤት ተመልሳ ጦሣ ላይ ችግኝ ተክላለች ብለውኛል  ጓደኛቼ፡፡ ሮዚና የኤኮን ሚስት ስትሆን አንድ ወንድ ልጅም አፍርተዋል፡፡ ሙጋድ፣ ኢራዳና ሸርፍ ተራ የአንድ ሠፈር ስም ናቸው፡፡ የደሴ የልብ ትርታም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ የሀላባ በርበሬ በሚመስሉ ቆርቆሮዎችና አዳዲስ ህንፃዎች የተዥጐረጐረው ይህ መንደር ከወሎ አደስና አርቲ እስከ ወፍጮ ማሽኖች ድረስ ይቸበቸባሉ፡፡ ገበያው ጣራ ከነካብዎ እንውጣና ፒያሳ እንሂድ፡፡ እዚያ አዲሡ የሼክ አል አላሙዲ ህንፃ አለ፡፡ ይሄኛው እንደ አዲስ አበባው በሩን ቆልፎ ሡባዔ አልያዘም፡፡ የተወሠኑት ክፍሎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ፒያሳን ወዲያው ወድጃታለሁ፡፡ በምኗ ይመስላችኋል? ጉያዋ ስር በወተፈችው ት/ቤት ነው፡፡ መንገዱማ በእግረኞች የተወረረ ነው፡፡ ካፌዎቹም ቢሆኑ ዓይን የሚገባ ነገር የላቸውም፡፡ የልብ ወጌሻው ዶ/ር በላይ አበጋዝ በወ/ሮ ስህን ወንበሮች ተቀምጦ የሩህሩህነትን ፊደል ለቅሟል፡፡ ነፍሡን ይማርና መምህርና ገጣሚ ብርሀኑ ገበየሁም የጥበብ ዘር የተጠናወተው እዚሁ ወ/ሮ ሥህን እንደነበር ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ ብታምኑም ባታምኑም የኤርትራው ፕሬዚንዳት ኢሳያስ አፈወርቂም የወ/ሮ ስህን ግርፍ ናቸው፡፡ ኧረ እንደውም የስምንተኛ ክፍል ውጤታቸውን አይተናል፡፡ የአማርኛ ውጤታቸውም ከሠማንያ በላይ ነበር ያሉ የደሴ አዛውንቶች አጋጥመውኛል፡፡
ዛሬ ወ/ሮ ስህን ኮሌጅ ሆኗል፡፡ ጠጋ ብዬ አየሁት፡፡ መክበድ ሲገባው ቀሎብኛል፡፡ ምናልባት ጭርታ ስለወረረው ይሆናል፡፡ ወይም የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን ማስተማር ስላቆመ?
ዋናውን የአዲስ አበባ መቀሌ መንገድ ወደ ታች ወረድኩ፡፡ በግራና በቀኝ የሀብታም ቤት አጥር የሚያክሉ ረጃጅም ህንፃዎች ተደርድረዋል፡፡ ሼል፣ ቅዳሜ ገበያ፣ ሆጤ፣ መናፈሻ፣ ፔፕሲ፣  አሬራ /ዕውቀት ጢቅ ሰፈር/ ውልሎ፣ ሮቢት፣ ቧንቧ ውሃ፣ ዶልፊን... እና ሌሎች ስማቸው ያልተነገረኝ የደሴ ሠፈሮችን ገብቼ ወጣሁባቸዉ፡፡ ቆሜ ቆዘምኩባቸው፡፡ ተቀምጬ አሠላሠልኩባቸው፡፡ ውበታቸው የሚደነቅ ነው ወይም በዕድገት ጐዳና እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ ብል ራሴን ማታለል ይሆንብኛል፡፡ ኧረ እንደውም በወገኖቼ ላይ ማላገጥ ነው፡፡ ስለዚህ ደሴና ሰፈሮቿ ቆሽሸዋል ልል ነው፡፡ አዎ ደሴ መንገዶቿ በብጥቅጣቂ ጨርቆችና ብጥሥጣሽ ወረቀቶች ተሸፍኗል፡፡ ቦያቸውን ጥሰው በወጡ የሽንትና የውሀ ፍሳሾች ውሀ ተከቧል፡፡ አደባባዮቹ በደረቁ እንጨቶች እና በተቆራረጡ ሽቦዎች ታጥሯል፡፡ ምሽቶቿ የመንገድ መብራት አንሷቸዋል፡፡ ደሴ ጨልማለች፡፡
የቅዳሜ ገበያ ሠፈርተኞች እንደ ደረቅ ዳቦ በተፈረካከሠው አዲስ መንገድ ተማረዋል፡፡ የቧንቧ ውሀ መንደርተኞች የውሀ ነገር ስሙ ብቻ እንዳይቀራቸው ሀሣብ ገብቷቸዋል፡፡ ሞልቶለት የማያውቀው ማዘጋጃ ቤትም የብዙዎችን ጨጓራ መላጡን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባይገርማችሁ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ራሡ የችግሩ አንዱ ሰለባ ነው፡፡ የቦሩ ሜዳ ጐረቤቶቹ ረግረጋማው መሬት ሊያሠምጠው ነው ብለውኛል፡፡
በተጨማሪም ጓደኞቼ የሚከተለውን ጭራ አልባ ወሬ ነገሩኝ፡፡ ...በአንድ ወቅት አንድ ፈረንጅ ወደ ደሴ መጣ መሽቶበታል፡፡ ለማደር ወሠነ ይሁን እንጂ ነጭ ተጠራጣሪ ነውና የጦጣ ተራራውን ፈራው፡፡ እንዴት ይህን ግዙፍ ድንጋይ ተንተርሶ ሠው እንቅልፍ ይወስደዋል? ፎቶ አነሳው፡፡ አልበቃውም፡፡ ቪዲዮ ቀረፀ፡፡ አልተደሠተም፡፡ በመጨረሻም የብረት እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹን ሸክፎ ወደ ተራራው ስራ አመራ፡፡ ከተወሠኑ የምልከታና የምርምር ጊዜ በኋላ ነጩ ዜጋ ደሴ አላድርም አለ፡፡ ቢለመን ቢባል፡፡ አሻፈረኝ አለ፡፡ ሞቼ እገኛለሁ፡፡ በኋላ ለምን? የሚል ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ...ጦሳ ተራራ ብዙ ውሀ ቋጥሯል፡፡ ይህም ውሀ ሊፈነዳ የቀረው አጭር ሠዓት በመሆኑ መልቀቅ አለብኝ፡፡ አለበለዚያ ከተማዋን ሊያጥለቀልቃትና ሊያጠፋት የሚችል ብዛትና ጉልበት አለው አለ አሉ፡፡ ዛሬ ፈረንጁ የለም ደሴ ግን አለች፡፡
የደሴ ስደት
ደሴ በ1999 የህዝብ ቆጠራ መሠረት 151,094 ነዋሪዎች አቅፋ ይዛለች፡፡ ይህ ቁጥር       15,829 ሄክታር የቆዳ ስፋት ያላትን ከተማ አስጨንቋታል፡፡ በተለይ ጧትና ማታ ደሴ ትንፋሽ ያጥራታል፡፡ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ነው፡፡ ከአቅሟ በላይ የወረሯት ሚኒባሦች አስፓልቱ ጠቧቸዋል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሡት እንግዶቿ የትርምሡ መሪ ተዋንያን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ከተማዋ ወልዳ ያሳደገቻቸውን ወደ ሌሎች የሀገር ውስጥና ውጪ ከተሞች አሳልፋ በመስጠት የሚወዳደራት የለም ይባላል፡፡ በተለይ ሴቶቹን ወደ አረብ ሀገራት መላክ ከጀመረች ቆይታለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ደሴን ከበው የተመሠረቱት እን ሀይቅ-መርሳ-ኩታበር-ወረኢሉ የተባሉ የገጠር ከተሞች ዋነኛ ግብዓት ናቸው፡፡ ይህ ባህል ፊደል ቀመስ ወደሆኑት ወጣቶችም ተሸጋግሯል፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንደነገረኝ ከአምስቱ የመጀመሪያ ድግሪ ተማሪ ዶርም ተጋሪዎቹ መካከል ወደ ደሴ ፊቱን የመለሠው አንዱ ብቻ ነው፡፡ አራቱ በራሳቸው ሲቀልዱ እንዲህ ይላሉ፡፡
ወሎ መውለድ እንጂ ማሳደግ አያውቅም
በረጅም አውቶብስ ይሠደዋል የትም፡፡
የደሴ ሃይማኖት
መምህር አካለወልድና ሼህ ሁሴን ጀብሪል አንድ ማዕድ ይቋደሡ ነበር ብላችሁ ታምናላችሁ? ግን እውነቴን ነው፡፡ እነዚህ ታላላቅ አባቶች በደሴ ትርክት ውስጥ ጉልህ ስፍራ አላቸው፡፡ ሼህ ሁሴን ጀብሪል በ1811 ዓ.ም በወርሂመኖ ተወለዱ፡፡ ለ97 ዓመታት በዚህ ምድር ላይ የቆዩት ሼህ ሁሴን እንደ ነብይ የሚቆጠሩ ሰው ነበሩ፡፡ ሼኪው በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መጪ ሁኔታዎች ላይ የሚሠጧቸው ትንበያቸው መሬት ጠብ አይሉም ነበር ይባላል፡፡ በሌላ በኩል መምህር አካለ ወልድ ለትምህርት ባላቸው ልዩ ፍቅር በአካባቢው ህብረተሠብ ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ በህይወት ዘመናቸው የመሠረቱት ት/ቤትም ዛሬ እስከ መሠናዶ ድረስ ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡ ሁለቱ ሠዎች በጣም ጓደኛ ስለመሆናቸዉ የታሪክ አዋቂዎች ይመሠክራሉ፡፡ እንዲህ ዛሬ ወሎ በሀይማኖት ፍቅር ጨርቋን ባልጣለችበት ወቅት መምህር አካለ ወልድና ሼህ ሁሴን ጀብሪል ቡናቸውን እየጠጡ ሥለ ሀገራቸው እድገትና ተስፋ ሀሣብ ይለዋወጡ ነበር፡፡ ስለ ማህበረሠባቸው ልማትና ስኬት ይጨዋወቱ ነበር፡፡ ትኩስ እንጀራቸውን በወተት እያወራረዱም ኑሮ ያስተማሯቸውን ልምድ ይለዋወጡ ነበር - ነበር - ነበር፡፡
ደሴ እምብርት ላይ ቆሜያለሁ፡፡ አጠገቤ የአረብ መስጊድ አለ፡፡ ቀና ካሉ የመድሀኒያለምን ቤተክርስቲያን ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህ የእምነት ተቋማት በትላንት ዓይን ካያችኋቸው በመቻቻል ፍቅራቸው ትቀናላችሁ፡፡ በመረዳዳት ባህላቸው ትደመማላችሁ፡፡ በተመሳሠብ ወጋቸው ትኮራላችሁ፡፡ በዚህ ሠዓት ለሼክ ሁሴን ጀብሪል እና ለመምህር አካለ ወልድ ኮፍያችሁን ከፍ ታደርጋላችሁ፡፡ የዛሬ ልጁ እኔ ደሴ ስደርስ ግን የተቀበለኝ መጥፎ ዜና ነው፡፡ ለተናጋሪውም ሆነ ለሠሚው ምቾት የሚሠጥ አይደለም፡፡ የዘመኖቹ የኔ ቢጤ የደሴ ወጣቶች ማርሽ ቀይረዋል፡፡ ሙድ ለውጠዋል፡፡
የደሴ ፍቅር
ደሴ እንደ ዶሮ ማነቂያና ሠባተኛ ከሞት አፋፍ ላይ የቆሙ ሠፈሮች እናት ነች፡፡ ይሁን እንጂ የተጣመሙትን በሮች በርግደው የሚበሩ ውብ ልጃገረዶች አሏት፡፡ አፍ የሚያስከፍቱ - ልብ የሚያስደነግጡ እና ሆድ የሚያላውሡ የእናቶች ፈገግታና ፍቅር ደሴ አለ፡፡ እውነቴን ነው እንስቶቹ እንደ ወንዶቹ ኮስታራ አይደሉም፡፡ መግባባት ይችሉበታል፡፡ ጨዋታ ያውቃሉ፡፡ እምነታቸውንም ወዲያው ይሠጣሉ፡፡ “ሸጋው ማደርያ ፈልገሀል እንዴ?” ብለውኛል መነሀሪያ ያገኙኝ አንዲት እናት፡፡
በመጨረሻም ደሴ የሆነ አዚም አላት፡፡ አዲስ እንግዳን እያናደደች ቢሆንም ቤተኛ ታደርጋለች፡፡ እያበሳጨችም ቢሆን የግሏ ታደርጋለች፡፡ እያቃጠለችም ቢሆን ታቀዘቅዛለች፡፡ ደሴ ደረቅ ወይራ ገራዶ ቢላን፣
የስንቱ መወክል ለከፈኝ እኔን፡፡… የተባለው እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልጆቿ ግን ግጥሙን ሆነ የተገጠመላትን ከተማ የሚታገሱበት አንጀት ያላቸው አይመስሉም፡፡ ጥለዋት እብስ እያሉ ነው፡፡ ሊቢያ-ጅዳ-ጁባ-አሜሪካ... ከስምንት ዓመት በፊት ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደሴ ተከስቶ ነበር፡፡ ትዝብቱንም በእፍታ የዘጋንባ አስቂኝ ትረካዎች ላይ እንዲህ አስፍሯል፡፡ “...ደሴን ተዘዋውሬ አየኋት አርጅታለች፡፡ በእውነቱ በጣም አርጅታለች፡፡ በተራሮች መሰል የተወተፈችው ደሴ ለከተማ ምቹ ባልሆነ ሥፍራ መመስረቷ ላለማደጓ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም፡፡” እና ያገሬው ሠው |አገር ሲያረጅ ደሴን ይመስላል´ እያለ ይቀልዳል፡፡ ሲዘፈንለት የኖረውን የጦሣን ተራራም አየሁት፡፡ ደሴን ተጭኗታል፡፡
ከደሴ ልመለስ ነው፡፡ አሳዘነችኝ፡፡ ደግሞም አናደደችኝ፡፡ እንደጠበኳት አላየኋትም፡፡ እንደፈለኳት አላገኘኋትም፡፡ እንደናፈቅኳት አልጠገብኳትም፡፡ ግን አልጨከንኩባትም፡፡ በሀገርና በሀገር ልጅ ማን ይጨክናል፡፡ እባካችሁ ደሴን ያያችሁ...
የቦከርና ውሀ እባብ ያንሻልላል
ያንቺ ልብ እንዴት ነው የኔ ይዋልላል፡፡

 

Read 5833 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:01