Saturday, 15 October 2011 12:24

የሃሳብ ምግቦች

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

ተረት ማህበረሰባዊ እውነታን በቀላል እና የዋህ ዘዬ የሚቀርብበት የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ቀጥሎ በምትመለከቷቸው ተረቶች ውስጥ የተገለፁ እውነቶች ደረጃቸውና መገለጫቸው የተለያየ ቢሆንም በህይወታችን ውስጥ በየቀኑ የሚገጥሙንና በዝንጋኤ የሚታለፉ ደረቅ እውነቶችን የሚያጎሉ የሃሳብ ምግቦች ናቸው፡፡ እስኪ እንብቧቸው፡፡  
የነብሩ ጅራት

አንድ ገበሬ የሩዝ እርሻውን ሲያርስ ውሎ ሲመሽ ወደቤቱ ይሄዳል፡፡ በጣም ደክሞትም ስለነበር እቤቱ ገብቶ ሲጋደም፣ እሚጣፍጠውን ሩዝ ሲበላ፣ ከቤቱ አቅራቢያ ካለው ጉብታ ቁጭ ብሎ ዋሽንት ሲነፋ እየታየው ማጭዱን በእጁ ይዞ ወደቤቱ ያዘግማል፡፡ እያዘገመ ሄዶ ትላልቅ ቋጥኝ ካለበት ሥፍራ ደረሰ፡፡ አይኑን ወደቋጥኙ ወርወር ቢያደርግ በአለቶቹ መሃል ውን ውን የሚል አንድ ነገር ተመለከተ፡፡ “ምንድን ነው የሚታየኝ?” አለ፡፡ ቀረብ ሲል የነብር ጅራት እንደሆነ አወቀ፡፡ “አሃ ነብ ይሄማ ትልቅ ነብር ነው” ብሎ በፍርሃት ተንቀጠቀጠ፡፡ ከዚያም በሩጫ አልፎ ወደ መንደሩ መሄድ ፈለገ፡፡ ነገር ግን በቋጥኙ በኩል እጥፍ ሲል ዘሎ እንደሚያንቀው አስቦ ፈራ፡፡ ወዲያው ሀሳቡን ቀይሮ ማጭዱን ጥሎ እያደባ ቀረበና የነብሩን ጅራት ለቀም አደረገ፡፡  
ከዚያም ከነብሩ ጋር ግብግብ ገጠሙ፡፡ ነብሩ ወደፊት ይሳባል፤ ገበሬው ወደኋላ ይጎትታል፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ቆዩ፡፡ ነብሩ በቁጣ እየጮኸ መሬቱን በጥፍሩ ይቧጥጣል፡፡ ገበሬው ደከመው፤ ላብ በላብ ሆነ፤ በጣም ተጨነቀ፡፡
በዚህ ጊዜ በመንገዱ የሚመጣ አንድ መነኩሴ አየ፡፡ “እግዚሃር ነው እርሶን የላከልኝ፤ በሉ አሁን እዚያ የጣልኩት ማጭድ ያንሱና እኔ እንደያዝኩት ነብሩን ይግደሉልኝ” አለ ገበሬው፡፡
መነኩሴው ገበሬውን ትክ ብለው ካዩት በኋላ “አይ እኔ አልገድልም ይህን ለማድረግ እምነቴ አይፈቅድልኝም” አሉት፡፡
ገበሬው “እንዴት እንዲህ ይላሉ እኔ ይህን የተቆጣ ነብር ብለቀው ደግሞ . . . ትንሽ ከቆየሁ መልቀቄ አይቀርም፤ ያኔ ወደኔ ዞሮ ይገለኛል” አላቸው፡፡ “አይ ወንድሜ የፈለከውን ብትል እኔ አልገልም፤ ሃይማኖቴ ነፍስ ያለው ፍጡር እንዳጠፋ አይፈቅድልኝም” አሉ መነኩሴው፡፡ “ምነው አባ ይሄን ነብር ለቅቄው እኔን ቢበላኝ በኔ ህይወት ተጠያቂ አይሆኑም፤ ከነብርስ ነፍስ የሰው ነፍስ አይበልጥ?” አላቸው “አይ ወንድሜ በዚህ ጫካ ያሉ አራዊት እርስ በእርስ ይበላላሉ፡፡ በዚህ ደግሞ እኔ ተጠያቂ ልሆን አልችልም፡፡ “ገበሬው እጁ ዝሎ ነብሩን ሊለቀው ሆነ፡፡ እናም ገበሬው “ይበሉ እሺ እርሶ ቅዱስ አባት ነዎት እባክዎ ይሄን ጅራት እርሶ ያዙልኝና እኔ ልግደለው” አላቸው፡፡ መነኩሴው ጥቂት አሰቡና “እሺ በመፅሃፉ የነብር ጭራ አትያዝ የሚል አልተፃፈም” ብለው ጭራውን ያዙለት፡፡ “አባቴ አጥብቀው ይዘዋል?“ “አዎ” “በደንብ ይዘዋል” “አዎ ይዣለሁ” ገበሬው ቀስ ብሎ ጭራውን ለቀቀው፡፡ እፎይ ብሎ ተንፍሶ ልብሱን አስተካከለ፣ አቧራውን አራገፈ፤ ከዚያም ኮፍያውን አደረገና ወደ መንደሩ ሊሄድ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ነብሩ ጉልበት ጨምሮ መጎተት ያዘ፡፡ መነኩሴው “ወዴት ትሄዳለህ? ኧረ ገበሬው እባክህ ናና ግደልልኝ እኔ ልለቀው ነው ናና ግደልልኝ” አሉ፡፡ ገበሬውም ፍፁም እረጋ ባለ አኳኋን፡፡ “አባቴ አዩ ቅድም እርሶ ካሉኝ ነገር ተምሬአለሁ፤ መፅሃፉ እንደሚያዘው እኔ ከእንግዲህ ነፍስ አላጠፋም፡፡ እርሶ አጥብቀው ከያዙ በዚህ መንገድ እንደኔና እንደርሶ ያለ እምነት የሌለው አንድ ደግ ሰው መምጣቱ አይቀርም፡፡ እርሱ ነብሩን ይገድልለዎታል” ብሏቸው ሄደ፡፡
መነኩሴው የነብሩን ጅራት ከመያዛቸው በፊትና ከያዙ በኋላ ያላቸው አቋም እምነትና ፍልስፍና ፍፁም ተቃራኒ ነው፡፡ በቃላቸው ያከበሩትን እውነት በግብራቸው ሲያረክሱት እናያለን፡፡ ከዚህ በታች በምታነቧቸው ሁለት ተረቶች ደግሞ እውነትን የሚከልሉ ነገሮች ምን እንደሆኑ የሚያሳዩን ናቸው፡፡ እውነትን መቀበልና በእምነት መኖር ምን አይነት ጀግንነት እንደሆነ ሊያስረዱን የሚችሉ ናቸው፡፡
ንጉስ ካኑቴ እና ባለሟሎቹ
ከዕለታት አንድ ጊዜ በአንድ ሩቅ አገር ትልቅ ግዛት ታላቅና አስተዋይ የሆነ ካኑቴ የሚባል ንጉስ ነበረ፡፡
ንጉስ ካኑቴ በደን መሃል ባለ ቤተመንግስት ይኖራል፡፡ ትእዛዙን የሚፈፅሙ ብዙ ባለሟሎችም ነበሩት፡፡ እነዚህ ባለሟሎችም ዘወትር በዓለም ውስጥ ወደር የሌለው ታላቅ እና ሃያል ንጉስ መሆኑን እየነገሩ ይሸነግሉታል፡፡
ሲሻቸው “ሃያሉ ንጉስ ሆይ በምድር ላይ ያንተን ትእዛዝ እሺ በጄ ብሎ የማይፈፅም ማንም የለም” ይሉታል፡፡ ሲሻቸው ደግሞ “ማንም ጠላት ሃያሉ ንጉሳችንን ሊደፍረው አይችልም” ይሉት ነበር፡፡
ሆኖም ንጉሱ ፍፁም አስተዋይ ሰው ነበረ፡፡ በምድር ያለ ሰው ምን ሃያል ቢሆን “ካህሌ ኩሉ” አለመሆኑን አሳምሮ ያውቅ ነበር፡፡ ስለሆነም የባለሟሎቹ የዘወትር አሰልቺ ሽንገላ እጅግ ያንገሸግሸው ነበር፡፡
አንድ ቀን ንጉሱና ጥቂት ባለሟሎቹ የወደብ ከተማ ከሚገኝበት የባህር ዳርቻ በወረዱ ጊዜ ከባለሟሎቹ አንዱ በተለመደ የሽንገላ ቃል “ንጉስ ሆይ ያንተ ሃያልነት ዘላለማዊ ነው፡፡ በምድር ላንተ ትእዛዝ የማይገዛ አንድ ፍጡር አይገኝም፡፡ አንተ ያዘዝከውን የማይፈፅም ምድራዊ ፍጥረት የለም፡፡” አለ፡፡ ይሄን የመሰለው የጅል ሽንገላ ያሰለቸውና ያሳመመው ንጉስ ካኖቴም ለባለሟሎቹ ትምህርት ሊሰጣቸው ፈለገ፡፡ ከመንበረ መንግስቱ እንደተቀመጠ ማዕበል ከሚልሰው አሸዋማ የባህር ዳርቻ እንዲወስደው ከባለሟሎቹ አንዱን አዘዘው፡፡ ባለሟሎቹ ንጉሱ ምን ሊሰራ እንደፈለገ ግራ ገብቷቸው እንዳሉ እርሱ በፀጥታ ወደባህሩ ይመለከት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ባለሟሎቹ በየተራ በተለመደ የግነት ቃላቸው ንጉሱን ማሞገስ ያዙ፡፡ “አንተ በምድር የሚስተካከልህ የሌለ ሃያል ነህ፤ ያንተን ትዕዛዝ ላለመፈፀም የሚያንገራግር አይገኝም“ ወዘተ ይሉታል፡፡
ንጉሱም “አሁን ይሄ ባህር ለኔ ትዕዛዝ ይገዛል?“ ሲል ጠየቀ፡፡ እየተንደረደረ ወደእርሱ የሚመጣውንና ወደእግሩ እየቀረበ ያለውን ማዕበል እየተመለከተ፡፡ “አዎ ንጉስ ሆይ እርሶ ብቻ ይዘዙት፡፡” አሉ ጅላጅል ባለሟሎቹ፤ “ይዘዙት እንጂ ትዕዛዞትን ያከብራል”
ከዚያም ንጉስ ካኖቴ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡ አጎብዳጅ ባለሟሎቹን በትዝብት እየተመለከተ እጁን ወደ ባህሩ ዘረጋ፡፡ ከዚያም ድምጹን ጎላ አድርጎ “አንተ ባህር ወደኔ እንዳትጠጋ እዚያው ቁም አንተ ማዕበል መጋለብህን ተው ወደኔ ለመቅረብ አትዳፈር፡፡ እግሬንም እንዳትነካ!”
ሆኖም ማዕበሉ ያው እንደወትሮው እየተንደረደረ መምጣቱን ቀጠለ፡፡ እንዲያውም ግልቢያውን አጠንክሮ ይዘል ጀመር፤ ከቅድሙ በባሰ ሁኔታ የባህሩን ዳርቻ ማልበስ ያዘ፡፡ የንጉሱን እግር ብቻ ሳይሆን የካባውን ጫፍ አረጠበው፡፡
ባለሟሎቹ በንጉሱ አድራጎት ግራ ተጋብተው ደነገጡ፡፡ ንጉሱም ወደነሱ ዘወር ብሎ እናንት ባለሟሎቼ እናንተም ሆናችሁ በምድር ያለ ማንኛውም ሰው አሁን ከምታዩት ነገር እውነትን ሊረዳ ይገባል፡፡ ምድራዊ ሰው ከሀሌ ኩሉ እንዳልሆነ እወቁ፡፡ ከሀሌ ኩሉ መባል የሚገባው የሰማይ እና የምድሩ ንጉስ፤ በነሱም ውስጥ የሚመላለስ ፍጥረት ገዢ የሆነው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ አዛዡ ናዛዡ እርሱ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እና ሁሉም ፍጥረት ሊገዛለት የሚገባ ህግ እሱ ብቻ ነው፡፡
ንጉስ ካኑቴ ይህን ተናግሮ በራሱ ላይ ያለውን ዘውድ አወለቀና ዘውዱን ዳግመኛ ካናቱ ላይጭን መሀላ አደረገ፡፡ ይህም ዘውድ በካኑቴ ግዛት ባለ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተሰቅሎ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ ከተንጠለጠለው ከዚሁ ዘውድ በታችም ሰውን ከእግዚአብሄር አብልጠው ለሚያወድሱ መልእክት የያዘ አንድ የብረት ሰሌዳ ይገኛል፡፡ በሰሌዳውም “በሺ 32 ንጉስ ካኑቴ ለባለሟሎቹ ትህትናን አስተማረ“ የሚል ቃል ተፅፏል፡፡
ግፈኛው ንጉሥ
በጥንት ጊዜ ቻይናን የሚገዛ አንድ ግፈኛ ንጉስ ነበረ፡፡ ይህ ንጉስ በቤተ መንግስቱ ፊት ለፊት አንድ ትልቅ ከበሮ አስቀምጦ በሀገሩ ግፍ ተፈፀመብኝ በደል ደረሰብኝ የሚል ሰው ሁሉ እየመጣ ከበሮውን ሲመታ ዳኝነት ለመስማት በዙፋን ችሎት ይሰየማል፡፡ በየጊዜው በደል የደረሰባቸው ሰዎች እየመጡ አቤት ቢሉም፣ ንጉሡ በደላቸውን ሰምቶ ፍትህ በመስጠት ፋንታ በግፍ ላይ ግፍ እየጨመረ ይገርፋቸው ይገላቸው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ባለሟሎቹ “ንጉስ ሆይ ተሳስተዋል” ማለትን ፈርተው በበደሉ እንዲገፋበት ስለፍትህ አዋቂነቱ እየነገሩ ያወድሱታል፡፡ ይህ ንጉስ እሱን የሚቃወም ቃል ደፍሮ የተናገረውን ሰው በቤተመንግስቱ አደባባይ በሚገኝ የአንገት መቁረጫ እያጋደመ ያሳርደው ነበር፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ይህን ግፍ ማየት የሰለቸው አንድ ባለሟሉ እንደሞት የምትፈራ ቃል አጉልቶ በድፍረት ተናገረ፡፡ “ንጉስ ሆይ ተሳስተዋል” ሲል ተናገረ፤ በችሎት የተሰየመውን ንጉሥ አትኩሮ እየተመለከተ፡፡ ከዚህ ሌላ ቃል አልተነፈሰም “ንጉስ ሆይ ተሳስተዋል” አለና ቀጥ ብሎ ወደ አንገት መቁረጫው አግዳሚ አመራ፡፡ አንገቱንም ለሰይፍ አመቻችቶ ሰጠ፡፡
ንጉሡ እንደለመደው ቁረጠው የሚል ትዕዛዝ አልሰጠም፡፡ ይልቅስ እጅግ ደነገጠ፡፡ ሲፈፅመው የቆየው ግፍና በደል ታየው፡፡ ንጉሱን የተቃወመ ሰው ሞት እንደሚፈረድበት የተደነገገ ቢሆንም ጨክኖ ይሄን ሰው አንገቱን ሊያስቆርጠው አልደፈረም፡፡ ይህ ደፋር ባለሟል ሽንገላን አሽቀንጥሮ ጥሎ እውነትን አሳየው፡፡ ንጉሱም በበደሉ ተፀፅቶ እራሱን ሳይሆን ፍትህን አነገሠ፡፡

 

Read 1932 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:27