Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 12:29

የተሸከምነው ክብደት ፍቅር ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሙሉነት ተሰማኝ፡፡ የመጉድል ፍላጐት በፅኑ አደረብኝ፤ ለመፃፍ ተነሳሁ፡፡ መጉደል ማለት ማጣት አይደለም፡፡ የሀሳብ ደም በመጉደል የሚተካ ነው፡፡ መሆኑ ራሱ የፍቅር ባህርይ አለው፡፡ 
መቶ ቢሊዮን ፀሐዮች በእኛ ጋላክሲ ውስጥ፣ መቶ ቢሊዮን የኒውሮን ህዋሶች ደግሞ በእኔ የራስ ቅል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ምን ያህል የተራራቅን እና የተለያየን ነገሮች እንደሆንን ፀሐይ እና እኔ ወይንም ጋላክሲዋ (ሚልኪ ዌይ) አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ሙሉነት እንደዚህም ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡ ሙሉነት የተነጣጠሉ ማንነቶችን እና ተቃርኗቸውን በአንድነት የሚሽር ልዕለ ተአምር ነው፡፡ የተአምሩ ስም “ፍቅር” ይባላል፡፡

የተሰማኝን ሙሉነት ለመግለፅ ፍቅርን በቁንፅል መረዳት ሳይሆን በጥቅል ስፋቱ ማወቅ አለብኝ፤ አልኩኝ፡፡ በጥቅል ስፋቱ ስል፤ ሁሉንም የተነጣጠለ እውቀቴን በአንድ ውል ማሰር እንዲችል አድርጌ ልገነዘበው ከቻልኩ ማለቴ ነው፡፡ 
“ፍቅር ያሸንፋል” ይለናል ወጣቱ የዘመናችን ዘፋኝ፡፡ ነገሩ ገብቶታል፡፡ ነገሩ ቢገባውም ግን ነገሩን (ሐሊዮቱን) ከተግባሩ ነጣጥሎ በመናገሩ ስህተት ፈፅሟል፤ እላለሁ እኔ፡፡ ፍቅር ተግባሩ ነው፤ “ፍቅር ያሸንፋል” ሳይሆን መፈክሩ “እያሸነፈ ያለው ፍቅር ነው” መሆን አለበት፡፡
እያሸነፈ ያለው ብቻ ሳይሆን በህልውና እየኖረ ያለው ነገር ሁሉ በፍቅር የተሸነፈ ነው፡፡ ሙሉነት ሲሰፍን፤ ፍቅር የበላዩን ቦታ ተቆጣጥሯል ማለት ነው፡፡ ፍቅር መስጠት እና መቀበል ነው፡፡ የሰጠውም አልተጐዳም የተቀበለውም አላተረፈም፡፡ ሙሉነትን ለመመዘን ጐዶሎ ማነፃፀሪያዎች አያገለግሉም፡፡
እናት ልጇን ወልዳ ስትንከባከብ፤ ፍቅር እየሰጠችው ነው፡፡ እየሰጠች እንደሆነ ሳታውቅም የሙሉነት እንጂ የመጉደል ስሜት አይሰማትም፡፡ እንዲያውም፤ በተቃራኒው፤ ልጇን ወልዳ ፍቅርን አለመስጠቷ እሷን ጐዶሎ ስሜት ውስጥ ይጥላታል፡፡ አለመስጠቷ እሷን ደስታ ያጐድልባታል፡፡ . . . መስጠት መጉደል ሳይሆን መሙላት ነው፡፡ ይህም የፍቅር (ከፍተኛ) ትርጉም ነው፡፡
እቺ ሁሉም ነገራችን የሆነችውን ፀሀይ፤ በግጥማችን የምንቀኝላት፣ በጥበባችን የምንጠበብላት እኮ፤ የፀሀይ ብርሐንን ስለምትሰጠን አይደለም፡፡ ጀምበር ማለዳ ስትወጣ ተመልክቶ፣ የፈጠነቀችው የጮራ ውለታ እንደ (ገንዘብ) እዳ የሚሰማው ሰው የለም፡፡ ፀሀይን የምወደው ለህይወቴ መሰረታዊ ነገር ስለሆነኝ ነው፤ “ብርሐኗን እንዳትነፍገኝ ነው በመውደድ እማባብላት” የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡
ፍቅር ህያው ነው፡፡ በሰው ልጆች ላይ ደግሞ የተለየ ባህሪ ይላበሳል፡፡ የሰው ልጅ ከእፅዋት ወይንም ከእንስሳት አለም የሚለየው ራሱን በራሱ በመገንዘቡ ምክንያት ነው፡፡ እውቀት ሰውን ግለሰብ ያደርገዋል፡፡ የግለሰብ ማንነቱን በእውቀት ከነጠለ በኋላ ወደ ጥቅሉ እውነታ መልሶ መቀላቀል ካልቻለ፤ ህዋን በሚያክል ስፋት ውስጥ ያለ አላማ እንደሚንገላወድ ብናኝ ጠፍቶ ይቀራል፡፡ ከየት እንደመጣሁ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም እንደማለት፡፡ የብቸኝነቱን ባዶ ህዋ ከነጠለበት ሙሉነት መልሶ እንዲያዋህድ የሚደርገው ሀይል “ፍቅር” ነው፡፡ . . . በፍቅር አየር ውስጥ እየኖረ አተነፋፈሱን እስካልተማረ ታፍኖ ይሞታል፡፡ ግለሰብነቱን ከሙሉኤ ኩሉው ጋር ላስተሳሰረ፤ በኖ ይጠፋል፡፡
ህፃን ልጅ ሲወለድ ፍቅርን ሆኖ ነው፡፡ ለእሱ ሁሉም ነገር አንድ ነው፡፡ ራሱን ከእናቱ ነጥሎ ገና ማወቅ አልጀመረም፡፡ ፍቅር ለህፃኑ ተፈጥሮአዊ ነገር ነው፡፡ መውደድ እና መጥላትን አልተማረም፡፡ እያደገ ሲመጣ ቀላል የነበረው ፍቅር ከባድ እየሆነ መምጣት ይጀምራል፡፡ . . . ነብስ አወቀ ማለት የራሱን ማንነት ከሌሎቹ ነጠለ ማለት ነው፡፡ እንደ እናቱ አይነት በሁለት አካል አንድ ማንነት ከእንግዲህ ለማግኘት ይከብደዋል፡፡ . . . ፍቅርን ለመረዳት ወይንም ለማግኘት እድሜ ልኩን ሲሞክር ይኖራል፡፡ . . . የህይወት ሸክሙ ፍቅር ነው፡፡…እውቀትን ከየዋህነት ጋር ለማዋሐድ መሞከሩ ነው ሸክሙ፡፡
የህይወት ሸክሙ ፍቅር የሚሆነው ነጠላ ማንነትን ከሌላ ነጠላ ፆታ ጋር ወይንም ማህበረሰብ ጋር፣ ተፈጥሮ ጋር . . . ወይንም በጥቅሉ ራስን ከሌላው ጋር ለማስተሳሰር በሚደረገው የእድሜ ልክ ሙከራ ነው፡፡
አለን ጂንስበርግ የ Beat generation ቁንጮ ገጣሚ ነበር፡፡ ከግጥሞቹ በሙሉ ለእኔ ስኬታማ (ሙሉ) የሆነችዋ “የአለም ሸክም” የተሰኘችዋ ነች፡፡ ፍቅርን የሙሉነት መጨረሻ መሆኑን እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡
The weight of the world is love
under the burden of solitude
under the burden of dissatisfaction
the weight, the weight we carry is love
who can deny? In dreams it touches the body In thought constructs a miracle
in imagination anguishes till born in human looks out of the heart burning with purity
for the burden of life is love...
በእውቀት ወይም ተሞክሮ የነጣጠልነውን እውነታ መልሶ ለማስተሳሰር ከምንጠቀምባቸው ዋነኛ መሳሪያ አንዱ ጥበብ ነው፡፡ ሌላኛው:- ሀይማኖት ቢሆንም ለጊዜው ግን እኔን አይመለከተኝም፡፡ አቅጣጫቸው ለእየቅል ቢሆንም ሁለቱም “ፍቅርን” የመሆኛ/ የማግኛ ሰውኛ ዘዴዎች ናቸው፡፡ ሙሉነትን መፈለጊያ ጐዶሎ ዘዴዎቻችን፡፡
የጥበብ፣ አላማ ከአንድ ቅንጣት (Particular) በመነሳት ጥቅሉ ነገር ላይ በጥበበኛው ምርጫ እና ሚዛን አማካኝነት መድረስ ነው፡፡ ለጥበበኛው፤ ጥበቡ የከፍታ ሁሉ መጨረሻ እንደሆነው፤ ለሀይማኖተኛው ደግሞ እምነቱ ወደ ፈጣሪው መድረሻ ብቸኛ መሰላል ነው፡፡ አልፋና ኦሜጋ የሁሉም ነገር ማጠቃለያ ከሆነ፣ የሰው ልጅ ገለፃ በጥበብም ሆነ በሀይማኖት አልፋና ኦሜጋውን በተነካ ፀሎቱም ሆነ በተሳካ ጥበብ መቀላቀል ነው ሙከራው፡፡ ስለዚህ ጥበብም ሆነ ፀሎት ፍቅርን በተለያየ አቅጣጫ ለማነጋገር የሚሞክሩ አውታሮች ናቸው፡፡ አልፋና ኦሜጋ ፍቅር ነው፡፡
በሁለቱ አይኖቼ የተመለከትኩት እይታ ሁለት የተነጣጠለ ሳይሆን አንድ ምስል እንደሚሰጠኝ ሁሉ፤ በፍቅር እይታም የተለያዩ ነገሮች በአንድነት ይተሳሰራል፡፡ በፍቅር እይታ ልዩነት በእኩልነት ሚዛናዊ ሆኖ ይስማማል፡፡ በአካል፣ በአምሳል እና በግብር የተለያዩ መሆናቸው በእውቀት (የአእምሮ አይን) የታወቁ ነገሮች በፍቅር አይን አንድ እና እኩል ይሆናሉ፡፡
ወንድ ልጅ ለሴቷ ፍቅሩን በአካሉ አማካኝነት ሲያቀርብ እና ሴቷ ስትቀበል፤ ማን አገልጋይ ማንኛው ደግሞ ተገልጋይ እንደሆነ መናገር አይቻልም፡፡ የአንዱ የገላ ትርጉም ፍቺ የሚያገኘው ሌላኛው ላይ ነው፡፡ በልዩነት ሚዛን ላይ አንድ የሚያደርጋቸው ፍቅር ነው፡፡ ሁሉም አንድ ናቸው፤ አንዱም ደግሞ ሁሉንም ይሆናል፡፡ የእኩልነት ትርጉም ይሄ ነው፡፡ የእኩልነት ትርጉም ተመሳሳይነት አይደለም፡፡ የፍቅር ከፍተኛ ትርጉም እኩልነት እንጂ ተመሳሳይነት አይደለም፡፡ ተመሳሳይነት የፍቅርን ተፈጥሮአዊ ተአምር ወደ ሰው ሰራሽ አስማት ለመቀየር የሚደረግ ማጭበርበር ነው፡፡ ተመሳሳይነቱ አገልግሎት ካለውም ከማህበረሰብ ህሊና ላለማፈንገጥ የሚደረግ፣ ከመንጋ ያለመነጠል ፍቅር ላይ መሰረት ያደረጉ ይሆናል፡፡ ጥቅልነትም ሆነ ጥልቀት የለውም፡፡
ጥበብ እና ፀሎት ሙሉኤኩሉውን ለመድረስ የተደረጉ እስከሆኑ ድረስ ከህይወት በላይ ናቸው፡፡ ህይወት ላይ ለመኖር ስንል ተመሳሳይ አይነት ልብስ ልንለብስ እንችላለን፣ ተመሳሳይ ቋንቋ መናገር …፡፡ ሀይማኖተኛው ፈጣሪውን፣ ጥበበኛው ፍቅርን ጠቅልሎ ለመግለጽ ሲሞክር ግን በምንም አይነት ከማንም ጋር ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም፡፡ ነጠላ ማንነቱን ይዞ ነው ሙሉ ከሆነው እውነት ፊት ፀሎት ወይንም ጥበቡን ይዞ የሚቀርበው፡፡ ጥበቡም ሆነ ፀሎቱ ከህይወት በላይ ናቸው፡፡ ከህይወት አገልግሎት (Function) ውጭ የሆነ ፍቅርን የመጨበጥ ተሻጋሪ ሙከራ በሙሉ “ውበት” አለው፡፡ ሁሉም ውበት በልዩነት ሚዛንም ላይ ቢመዘን እኩል ነው፡፡ በህይወት ላይ ብቻ አገልግሎቱ የተወሰነ ነገር ሊመዘን የሚችለው በህይወት ሚዛን ነው፡፡ በህይወት ሚዛን ላይ ፍቅር በገንዘብ ሊገዛ እና የሚሸጥ አገልግሎት ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን ይህ ቁንፅሉ ፍቅር ነው፡፡ ወደየትም የማያደርስ ነጠላ እና ተመሳሳይ የሆነው፡፡ ጥቅሉ ፍቅር ጨረቃን ከአምፖል የበለጠ እንድንወድ ያደርጋል፡፡ በአገልግሎት የማይገናኙትን ልዩነቶች በፍቅር አንድ ያደርጋል፡፡
The weight is too heavy… must give for no return
as thought is given in solitude/
in all the excellence of its excess...
ጥበብ እና ፍቅር ነፃ ናቸው፡፡ ለፍቅራቸው እና ለጥበባቸው (ምናልባትም ለፀሎታቸው) የሚያስከፍሉ ሰዎች የፍቅርን ጽንሰ ሀሳብ ከገበያ ሐልዮት ጋር አምታተዋል፡፡ ውበትን ከአገልግሎት ጋር፡፡
ከጥቅሉ ተፈጥሮ ወይንም ከህዋ ጋር የሚያስተሳስረውን ፍቅር ለማግኘት ምናባዊ ማፈንገጥ ያስፈልጋል፡፡ ግን በህይወትም ላይ ቅርብ ያለውን የፆታ አንድነት ፍለጋ ሰዎች በፍቅር መውደቅን ይመኛሉ፡፡ ወይንም እንመኛለን (አባይ ውስጥ ሆነን አጠጣጡን ባለማወቅ ውሃ ይጠማናል)...፡፡ በውበት እንጠመዳለን...በፍቅር እንወድቃለን...ፍቅሩን ለማቆየት ትዳር ውስጥ እንገባለን፡፡
ትዳር ከውበቱ አገልግሎቱ ይበረታል፡፡ ሴት ሚስት እና እናት፣ ወንድ አባት እና ባል የመሆን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ፍቅሩ የት እንደጠፋ ግራ በመጋባት ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ አገልግሎት ውበትን ወደ ህይወት መጠን በመቀየር እንደሚገድለው ማወቅ ተስኗቸው...፡፡ ፀሎት እና ጥበብን ለኑሮ አገልግሎት ማዋል የሚያስቸግረው ለዚህ ይሆናል፡፡
አገልግሎት ብቻውን ግን ጥቅሉን ፍቅር አይተካም፡፡ በግብርና አብዮት ዘመን ጥሩ ሚስት ማለት:- ብዙ ልጆች መውለድ፣ ብዙ መንገድ እቃ ተሸክማ መጓዝ፣ ምግብ አጣፍጣ ለቤተሰቧ ማቅረብ የምትችል… ልትሆን ትችላለች፡፡ ወንዱም ይህንን እሴቶች የተላበሰች ሴት “ፍቅር” የሚል ስሜት ብትቀሰቅስበት አይገርምም፡፡ . . . ዘመናዊው ወንድ ሮማንቲክ ፍቅርን እንደ ዋና ነገር ይቆጥራል፡፡ . . . ቆንጆ፣ የተማረች፣ የገንዘብ ችግር የሌለባት . . . ፌስ ቡክላይ በብዛት የምትገኝ . . . ወዘተ፡፡ . . . ፍቅር ሳይሆን ኑሮ ነው፡፡ እሴቶቹ በሙሉ የአንዱ የመስጠት እና የሌላኛው የመቀበል ፍላጐት ላይ የተመሰረተ functional እስከሆኑ ድረስ ውስን ናቸው፡፡ ከዘላለም ጋር ቅጽበትን አያገናኙም፡፡ ህይወትን እንጂ ከዛ በላይ ሩቅ የመድረስ አቅም የላቸውም፡፡ . . . ልክ ስለ ኑሮ ዘዴ የሚጨቀጭቅ “ኪስህ ነው ዘመድህ” የሚል የዘፈን ጥበብ ከኪስ ቦርሳ መጠነ አለም የተሻለ ተስፋ እንደማይሰጠው ማለት . . . ፡፡
ሰው ከዋክብትን ተመልክቶ ይመሰጣል፡፡ ተከፍሎት አይደለም የተመሰጠባቸው፤ ተከፍሏቸው አይደለም በማታ ወጥተው አፅናፍ በሌለው ሰማይ ላይ እነሱም የተሰጡት፡፡ ተመልካቹ ለእሱ ደስታ የሚያብለጨልጩ አለመሆናቸውን ቢያውቅም የራሱን ማንነት ከእነሱ መነጠል አይችልም፡፡ ራሱን ከክዋክብቶቹ አንዱ አድርጐ መቁጠር ይችላል፡፡ ያኔ ተመልካቹ ከፍተኛውን የፍቅር ትርጉም በዝምታ መረዳት ጀምሮአል፡፡ ምናልባትም ከፍተኛውን የጥበብ ትርጉም፡፡
የኔ መቶ ቢሊዮን የአንጐል ኒውሮን ህዋሶች፤ ከመቶ ቢሊዮኑ የጋላክሲያችን ፀሀዮች ጋር መግባባት መተዋወቅ የመጀመራቸው ሂደት… እውቀት ተብሎ ከተጠራ . . . እኔ አዋቂው እና ያወቅሁት ነገር በልዩነታችን ውስጥ አንድነትን መስርተናል፡፡ ከልዩነት ሚዛን እኩልነትን በፍቅር አማካኝነት ለክቻለሁ፡፡ ፍቅር በግለሰብ ፍለጋ የሚገኝ ሙሉነት ነው፡፡
በግሪኮቹ የሚነገረውን አፈ ታሪክ እንደ ምሳሌ ከወሰድን የሙሉነትን ፍለጋ መረዳት እንችላለን፡፡ አፈ-ታሪኩ በሴት እና ወንድ ሙሉነት ፍለጋ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ሰውና ጥቅሉ እውነታ ለመተሳሰር የሚያደርጉትን የእውቀት እና መግባባት ፍለጋም ሊመስልልን ይችላል፡፡
ሰው ሲፈጠር መጀመሪያ ወንዱና ሴቷ አንድ ላይ ተጣብቀው ነበር፡፡ ሙሉ ስነለነበሩ ስራ ፈቱ፤ ፈጣሪን ከተቀመጠበት ለማውረድ መዶለት ጀመሩ፡፡ ፈጣሪ ሊያጠፋቸው ስላልፈለገ ሁለት አድርጐ ሰነጠቃቸው፡፡ ለያያቸው፡፡ . . . የተነጣጠለውን የአካል ክፍላቸውን ፍለጋ የሚያደርጉት የሙሉነት ሙከራ የእድሜ ልክ ሸክም ሆነባቸው . . .፡፡ ሸክሙን ግን የምንሸከመው በሙሉ ፍቃደኝነት እና ደስታ ነው፡፡ ተሸካሚዎቹም አንጐዳም፤ አሸካሚውም አይጠቀምም፡፡
But we carry the weight we wearily and so must rest in the arms of love, at last
must rest in the arms of love . . . No rest without love
no sleep without dreams of love . . .
be mad or chill obsessed with angels or machines, the final wish is love
can not be bitter, cannot deny
cannot withhold if denied: the weight is too heavy
Allen Ginsberg

 

Read 4151 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:33