የጋዜጠኞች ማህበራት ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ቢሞክሩ ያዋጣቸዋል!
ኤልፓ ለአርጀንቲና የኤሌክትሪክ ኃይል ለምን አይሸጥም?

ባለፈው ሳምንት ሁለት እምብዛም የማላውቃቸው የአገሬ የጋዜጠኞች ማህበራት ፕሬዚዳንቶች ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሰጡትን ቃለምልልስ አንብቤ እንዴት እንደኮራሁ ልገልፅላችሁ አልችልም፡፡ የኩራቴ ምንጭ ግን በጋዜጠኞች ማህበር መሪነታቸው አይደለም። እኔ የኮራሁት በሌላ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንደኛው ማህበር ፕሬዚዳንት ማህበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ምን እንደሰራ ሲጠየቅ “ታሪካችን መፅሃፍ ነው፤ተነብቦ አያልቅም” ሲል የመለሰው በእጅጉ ነው ያስደመመኝ፡፡ ይኸው ሳምንት ሙሉ እኮ ንግግሩ ከልቤ አልወጣም፡፡ (አንደበተ ርቱዕ አይጥፋ አቦ!)
የሌላኛው ማህበር መሪ ደግሞ በሽብርተኝነት ተከስሶ የታሰረውን ጋዜጠኛ ውብሸትን ለማስፈታት ማህበራቸው ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ሁሉም ነገር ሊያልቅ ሲል፣ሲፒጄ ውብሸትን የተመለከተ ሪፖርት በማውጣቱ ጥረታቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ገልጿል፡፡ ግን እንዴት--አልገባኝም። መንግስት ጋዜጠኛውን ለመፍታት ከተስማማ በኋላ፣ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ እልህ ውስጥ ገብቶ  ሃሳቡን ቀየረ ማለት ነው፡፡ መቼም እውነቱ ይሄ ከሆነ ስቄም አላባራ! ይሄን ኩሩ ህዝብ የመምራት አደራ የተሰጠው መንግስት፣ እንዴት ከአንድ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ጋር እልህ ውስጥ ይገባል? (ማን ነበር “ለጠብም እኩያ ያስፈልጋል” ያለው?)  ከቃለምልልሱ ውስጥ ብዙ ጋዜጠኞችን ግራ ያጋባው ነገር ምን  መሰላችሁ? የአንደኛው ማህበር ፕሬዚዳንት ስንት አባላት እንዳላቸው ሲጠየቁ “700 አባላት አሉን” ያሉት ነገር ነው፡፡ (የህዝብ ግንኙነቶችም አባል ናቸው እንዴ?)
እኔ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ብሆን ኖሮ የማህበራቱን መሪዎች “ጋዜጠኛ ለሚለው ቃል ፍቺያችሁ ምንድነው?” ብዬ እጠይቃቸው ነበር፡፡ ልክ ነዋ --- በፍቺው ካልተስማማን እኮ አንግባባም፡፡ እኔ የምለው --- የማህበራቱ መሪዎች በቃለምልልሳቸው  “ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም” (ይቅርታ “በሙያው ሳቢያ ነው” ያሉት!) ብለዋል---አይደል? ባለፈው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም መጠናቀቂያ ላይ በሰጡት የጋራ  መግለጫ ደግሞ “የፕሬስ ነፃነት ከየትኛውም የአፍሪካ አገር በተሻለ መልኩ በአገራችን  ተከብሯል” ማለታቸው አይዘነጋም - ኢህአዴግ ቢስቅባቸውም፡፡ ግን ግዴለም እነሱ እንዳሉት ይሁንና “እሺ ተከብሯል!” እንበላቸው፡፡ ታዲያ እነሱ እዚህ አገር ምን ይሰራሉ? ምናልባት ኢህአዴግን አያምኑት ይሆናል፡፡ እንዴት አትሉም --- አሳቻ ጊዜ ጠብቆ  የፕሬስ ነፃነት  መልሶ እንዳይነጥቀን ይሰጉ ይሆናላ! (እንኳን እነሱ እኛም አንሰጋ!)
እናላችሁ --- ማህበራቱ ደጋግመው እንደነገሩን ----  ጦቢያ  ጋዜጠኛ የማይሰደድባት፣የማይዋከብባት፣ የማይታሰርባትና እንዳሻው በነፃነት የሚፅፍባት የዲሞክራሲ አገር ናት ብለን እንመንላቸው፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ ---- የጋዜጠኞች መብት “ተሟጋች ነን” ለሚሉ ማህበራት ብዙም ሥራ የለም ማለት ነው። (ለአንድም ጋዜጠኛ ተከራክረናል አላሉማ!) እናም ለእነዚህ ማህበራት ምን አሰብኩላቸው መሰላችሁ? እዚህ ሥራ ከሚፈቱ ለምን ወደ ጎረቤት አገራት --- ለምሳሌ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ተሻግረው የጀማሪዎቹን አገራት የጋዜጠኞች መብት አያስከብሩም  አልኩ፡፡ ተንኮል አስቤ ግን  እንዳይመስላችሁ፡፡ ለእነሱው አስቤ ነው (ለወገን ማሰብ አይቻልም እንዴ?) አያችሁ --- ወደ ጎረቤት አገር ሄደው ሲንቀሳቀሱ እግረመንገዳቸውንም የራሳቸውንና የማህበራቸውን ሲቪ ያበለፅጉታል - ከ“ሎካል” የጋዜጠኞች ማህበርነት ወደ አህጉራዊ የጋዜጠኞች ማህበርነት ያድጋሉ (“ያልተገላበጠ ያራል” አሉ!) ብልጥ ከሆኑና  ከበረቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ከመሆን የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ (“ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” አለ ፈረንጅ!) እናም--- ቀስ በቀስ የኒውዮርኩን ሲፒጄ ሊገለብጡት ይችላሉ፡፡ (የጋዜጠኞች ማህበር ኩዴታ ተከልክሏል እንዴ?) ይሄ ከተሳካላቸው እኮ --- ኢህአዴግም ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰቃየት በእነሲፒጄ እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከመወቀስና  ከመወንጀል ዳነ ማለት ነው፡፡ እዚያ ሳይደርሱ ግን  ሲፒጄ ስለኢትዮጵያ አያገባውም ማለት ብዙም ውሃ አያነሳም፡፡ አያችሁ ---- ማህበራቱ እንዲህ ቢዚ ከሆኑ  “ሲፒጄ የወሮበሎች ቡድን ነው” ምናምን እያሉ ለመዝለፍ ጊዜም አይኖራቸው። (“ዘለፋ ለአገር ገፅ ግንባታ ወሳኝ ነው” የሚል ጥናት ወጣ እንዴ?)  
አሁን ደግሞ እስቲ ወደ አውራው ፓርቲያችን እንመለስ (ዞሮ ዞሮ ወደ እናት ክፍል አሉ!) እኔ የምለው …ኢህአዴግ አልፎ አልፎ የሚያሳያቸው ድንገተኛ  ለውጦች አያስገርማችሁም? (“23 ዓመት ሙሉ የት ነበር”  ያስብላል እኮ!) ሆኖም ፈዝዞና ደንዝዞ ከመቅረት መነቃቃት ይሻላልና “ጐሽ … አበጀህ!” ነው የምንለው። እስቲ አስቡት ---- ቪኦኤንና የማይጥሙትን ድረ-ገፆች ይዘጋል ወይም ጃም ያደርጋል እየተባለ ሲታማ የከረመው አውራው ፓርቲ ድንገት ተነስቶ የሶሻል ሚዲያ አቀንቃኝ ሲሆን! የማይታመን ቢመስልም እውነት ነው። ኢህአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊቱን ወደ ድረገፆችና ፌስቡክ ያዞረ ይመስላል፡፡    (የግሎባላይዜሽን ተፅእኖ ነው ወይስ አማራጭ ማጣት?) የሆኖ ሆኖ በቅርቡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው የተሾሙት (በሚኒስትርነት ማዕረግ መሆኑን ልብ በሉ!) አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰሞኑን እንደተናገሩት፤ የመንግስት መ/ቤቶች ስለሚያከናውኗቸው ስራዎች ትክክለኛውን መረጃ በድረገጾቻቸው ማሰራጨትና ወቅታዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል (ሳይነገራቸው አይሰሩም ማለት ነው!) ሃላፊውም አክለውም መ/ቤቶቻቸውንና ሥራቸውን  ፌስ ቡክን በመሳሰሉ ሶሻል ሚዲያዎች ላይ በንቃት ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል (ሕዝብ ግንኙነቶች “ነብር አየኝ” ይበሉ!) ሚኒስትሮችም ቢሆኑ  እንደ ውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ንቁ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢህአዴግ “ግሪን ላይት” አሳይቷል የሚል መረጃ ደርሶኛል፡፡ ኢህአዴግ የቴክኖሎጂ “ጋግርቱ” ካልተነሳበትና በዚሁ “ሙድ” ከቀጠለ የ2007 አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ቤት ለቤት ወይም በፈንዲሻ መሆኑ ቀርቶ በፌስቡክ ይሆናል ማለት ነው - በ21ኛው ክ/ዘመን ቴክኖሎጂ!  አንድ ወዳጄ --- የኢህአዴግ ወጣት አባላትም በፌስቡክ ፖለቲካዊ ሃሳባቸውን መግለፅና  በአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ “ሙድ” መያዝ እንደጀመሩ ሲነግረኝ፣እንደ ሥልጣኔ ምልክት ቆጥሬው ደስ አለኝ፡፡ እሱ ግን ሃሳብ ሲያልቅባቸውና የተሸነፉ ሲመስላቸው “የባለቤቱ ልጅ ነን” በሚል ወደ ማስፈራራት እንዳይገቡ እፈራለሁ ሲል ስጋቱን ገለፀልኝ፡፡ ስጋቱን ብጋራውም እምብዛም የሚያሳስብ  አይመስለኝም፡፡ (ማስፈራራት የሰለጠነ ሰው ምግባር አይደለማ!)
እስቲ ለአፍታ ደግሞ ወደ ደቡብ አሜሪካ ልውሰዳችሁና--- በአርጀንቲና ለ15 ቀን በተከሰተ የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ሳቢያ የተፈጠረውን ረብሻ፣ የጐዳና ላይ “ነውጥ”፣ ዝርፊያና ማህበራዊ ምስቅልቅል ላስቃኛችሁ፡፡ (የእኛ አገር መብራት ስንት ዓመት እንደተቋረጠ ቢሰሙ አርፈው ይቀመጡ ነበር!) ለነገሩ አርጀንቲናውያን በአሁኑ ወቅት ችግር ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ እላያቸው ላይ የከተመባቸው ነው የሚመስሉት፡፡ እስቲ አስቡት … የአገሪቱ የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በመሆኑ ህዝቡን አላስቆም አላስቀምጥ ብሎታል፡፡ በዚያ ላይ ይሄን ሙቀት የሚያበርዱበት ውሃ የላቸውም፡፡ የውሃ ፓምፓቸው እንደኛ አገር በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ በመሆኑ ውሃውም ከመብራቱ ጋር ጠፍቷል፡፡
እናም በዚህ ሰበብ -- በአርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስና በግራን ቦነስ አይረስ ከተማ ረብሻ፣ ተቃውሞና በጠራራ ፀሃይ የሚፈፀም ዘረፋ --- የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል፡፡ (ሙቀቱ ብቻውን እኮ አቅል ያስታል!) የሚገርማችሁ ደግሞ ለችግሩ መፍትሔ ከመዘየድ ይልቅ የአገሪቱ መሪዎች እርስ በእርስ መናቆር ይዘዋል። የኤሌክትሪክ መቋረጡን በተመለከተም የአርጀንቲና መንግስት በሃይል ማመንጨት ስራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን ኩባንያዎቹ ደግሞ ጥፋቱ የመንግስት ነው ባይ ናቸው፡፡ (“የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” አሉ!) ኤድኖር እና ኤድሰር የተባሉት የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያዎች እንደሚሉት፤ ባለፉት 20 ዓመታት መንግስት የኤሌክትሪክ መስመሮችን ባለማደሱና በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ኢንቨስት ባለማድረጉ የተከሰተ ችግር ነው፡፡ እኔ የምላችሁ … የአገራችን ኤልፓ ስለመብራት መቆራረጡ ሲደረድርልን የነበረውን ሰበብ ከውጭ አገር ነው እንዴ የቀዳው? (እንደ ፀረ-ሽብር ህጉ ማለቴ ነው!)  የኃይል መቋረጡን በተመለከተ የአርጀንቲና ኩባንያዎች ያሉትን ስሙልኝ -
“የሃይል እጥረት የለብንም፤ ችግሩ የውስጥ ለውስጥ መገናኛ መስመሮች ማርጀትና ከአገልግሎት ውጭ መሆን ነው” (ቁጭ የኤልፓ መግለጫ!) እንግዲህ ወይ አርጀንቲና ከእኛ ቀድታለች አሊያም  እኛ ከሆነ አገር “ቃል በቃል” ቀድተነዋል ማለት ነው (የራሳችንን ሰበብ እንኳ መፍጠር ያቅተን?)
ሌላው የሚያስገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክርስቲና ፈርናንዲዝ ህዝባቸው በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሲዳክር ድምፃቸውን ማጥፋታቸው ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚሉት፤ ፕሬዚዳንቷ እስካሁን በኃይል መቋረጡ ዙሪያ ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም፡፡ (የእኛዎቹ እኮ እውነት አይናገሩም እንጂ ድምፃቸውን አጥፍተውብን አያውቁም!) ይገርማችኋል … የአርጀንቲናዋ መሪ ህዝባቸው ከ40 ድግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በሆነ ሙቀት ሲነፍር፣ እሳቸው ግን ቀዝቀዝ ያለ አየር በሚነፍስባት የኢል ካላፋቴ ግዛት ውስጥ ከሃይቅ ዳርቻ በታነፀው መኖርያ ቤታቸው ውስጥ የሰላም እንቅልፋቸውን እያጣጣሙ ነው፡፡ (አላይም አልሰማም ብለው!)
ሌላው ቀርቶ የተለመደውን የገና በዓል “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት እንኳን ለህዝባቸው አላስተላለፉም (ይሄ ታዲያ ፍራቻ ነው ጥላቻ?) አርጀንቲናውያን ግን አሁንም ሻማና የታሸገ ውሃ ከሱቅ እየገዙ በረብሻ፣ በተቃውሞና በዘረፋ ኑሮአቸውን እየገፉ ነው ተብሏል፡፡ መብራትና ውሃ የሚመጡበት ጊዜ “እንደ ኢየሱስ መምጫ” አልታወቅም ተብሏል (አንድዬ ይሁናቸዋ!) እኔ የምለው ግን … የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ለአርጀንቲና የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ አላሰበም እንዴ? (አያስብም አይባል እኮ!) መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!

የአፍሪካ 100 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ሰሞኑን ይፋ የተደረጉ ሲሆን የደቡብ አፍሪካዎቹ - ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውንና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ስቴሌንቦስች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ እንደወሰዱ “ፎር አይሲዩ” የተባለው ተቋም አስታወቀ፡፡
የታንዛኒያው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዳሬሰላም በአራተኛነት ጣልቃ ቢገባባቸውም፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኩዋዙሉ ናታል እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃን  ይዘዋል፡፡ የግብጹ ካይሮ ዩኒቨርሲቲ ሰባተኛ፣ የደቡብ አፍሪካዎቹ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዊትዋተርስራንድ እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስተርን ኬፕ ስምንተኛና ዘጠነኛ ደረጃን ሲይዙ የናይጀሪያው ኦባፌሚ አዎሎሎ ዩኒቨርሲቲ አስረኛ ሆኗል፡፡ የአገራችን አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ  የ53ኛ ደረጃ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ግብጽ 20፣ ደቡብ አፍሪካ 19 ዩኒቨርሲቲዎችን በምርጥ መቶዎቹ ውስጥ በማስመረጥ፣ ቀዳሚነቱን የያዙ  ሲሆን  ኬኒያ 6፣ ሱዳን 2 ዩኒቨርስቲዎች ተመርጦላቸዋል፡፡
“ፎር አይሲዩ” የተባለው ተቋም በአህጉራት ደረጃ ምርጥ የሚላቸውን ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች እየመረጠ በየስድስት ወሩ ይፋ ማድረግ የጀመረው እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ ነው፡፡ የዓለም ዩኒቨርስቲዎች የፈጠሩትን ተጽዕኖና በድረ ገጾች ላይ ያላቸውን የመረጃ ሽፋን መሰረት በማድረግ የምርጥ ዩኒቨርሲቲዎችን ዝርዝር ይፋ የሚያደርገው ተቋሙ፣ ተዓማኒ፣ ጠቃሚና መልከ ብዙ መረጃዎችን የመስጠት ዓላማ አለው፡፡ የትምህርትና የምርምር ተቋማት  የህትመት ስራዎችንና የምርምር ውጤቶችን በድረ ገጾች እንዲያሰራጩ የበለጠ ተነሳሽነት የመፍጠር ተጨማሪ አላማ እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ጥበብ

በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት የሚካሄደው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮን ሺፕ (ቻን) ሳምንት ሲቀረው፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአቋሙን ለመፈተሽ ዛሬ በአቡጃ የወዳጅነት ጨዋታ ከናይጄርያ አቻው ጋር ሊያደርግ ነው፡፡  ወደ ደቡብ አፍሪካ ጥር 3 እንደሚጓዝ ይጠበቃል፡፡ ትናንት ወደ ናይጄሪያ የተጓዙት ዋልያዎቹ ዛሬ በአቡጃ የወዳጅነት ጨዋታቸውን ከናይጄሪያ ቻን ቡድን ጋር አድርገው ሰኞ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ፡፡
 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቂ ዝግጅት ባለማድረጉ እና በስብስቡ በርካታ አዳዲስ ልጆች ከማካተቱ ጋር በተያያዘ የሚኖረው ውጤት ለመገመት ያስቸግራል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ  በቻን ላይ በሚኖረው ተሳትፎ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ትኩረት ሊስብ እንደሚችል ሲጠበቅ ይህ ሁኔታ ከፍተኛ መነሳሳት እንደሚፈጥርለት ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያ በቻን ውድድር  ለመጀመርያ ጊዜ   ስትሳተፍ በምድብ 3 ከሊቢያ፤ ከጋና እና ከኮንጎ ብራዛቪል እንደተደለደለች ይታወቃል፡፡ በብሎምፎንቴይን፤ማውጋንግ ከተማ በሚገኘው የፍሪ ስቴት ስታድዬም ሶስቱንም የምድብ ጨዋታዎች የምታደርገው ኢትዮጵያ  የምድቡን የመጀመሪያ  ጨዋታዋን  ጥር 5  ላይ ከሊቢያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ የምትጀምር ሲሆን ሁለተኛ የምድቧን ጨዋታ  አርብ ጥር 9 ላይ ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር እንዲሁም የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ ማክሰኞ ጥር 12 ላይ ከጋና ትጫወታለች፡፡
በዋልያዎቹ ስብስብ  ከዓመት በፊት በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉ እና በዓለም ዋንጫ የማጣርያ ውድድሮች ከፍተኛ ሚና የነበራቸው 13 ተጨወቾች ሲያዙ፤  በሴካፋ ውድድር ላይ የታዩ አዳዲስ ተጨዋቾችም ተካትተውበታል፡፡ በልምዳቸው ለብሄራዊ ቡድኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው እንደሚችል የተነገረላቸው በአገር ውስጥ ክለቦች የሚጫወቱት አዳነ ግርማ፤ በሃይሉ አስፋው፤ ምንያህል ተሾመ፤ ኡመድ ኡክሪ፤ አይናለም ሃይሉ፤ ስዩም ተስፋዬ ዋና ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከአገር ውጭ በመጫወታቸው ወሳኞቹን ሳላዲን ሰኢድ፤ ጌታነህ ከበደ፤ አዲስ ህንፃና ሽመልስ በቀለን  በቻን በሚሳተፈው ብሄራዊ ቡድን ማካተት አልተቻለም፡፡
በአጠቃላይ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው 23 ተጨዋቾች ከፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች መልምለው ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል፡፡በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከነበሩት 13ቱ ተጫዋቾች ብቻ ተካተዋል፡፡ ሲሳይ ባንጫ  ኢትዮጵያ ሩዋንዳ በመለያ ምት ጥላ ስታልፍ ሁለት ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምቶችን ያደነ በረኛ ቢሆንም ወደ ደቡብ አፍሪካ አይጓዝም፡፡
በረኞች– ጀማል ጣሰዉ ከኢትዮጵያ ቡና፤ ታሪክ ጌትነት ከደደቢት ፤ ደረጀ አለሙ ከዳሸን ቢራ
ተከላካዮች –ደጉ ደበበ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣  አሉላ ግርማ፣ አበባዉ ቡታቆና ሳላሀዲን ባረጌቾ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፤ብርሀኑ ቦጋለና ስዩም ተስፋዬ ከደደቢት ፤ አይናለም ሀይሉ ከዳሸን ቢራ ፤ ቶክ ጀምስ ከኢትዮጵያ ቡና
አማካዮች– አዳነ ግርማ፣ምንያህል ተሾመ፣ በሀይሉ አሰፋና ምንተስኖት አዳነ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ፋሲካ አስፋዉና ኤፍሬም አሻሞ ከኢትዮጵያ ቡና፤ታደለ መንገሻ ከደደቢት፤ አስራት መገርሳ ከዳሸን ቢራ
አጥቂዎች– ኡመድ ኡክሪ፣ዳዊት ፍቃዱ ከደደቢት እና ማናዬ ፋንቱ ከመከላከያ
ኢትዮጵያ ባለችበት ምድብ 3 የሚገኘው የጋና ብሄራዊ ቡድን ለቻን በሚያደርገው ዝግጅት ከሳምንት በፊት አክራ ላይ ከማሊ አቻው ጋር ተገናኝቶ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ቡድኑ ለመጨረሻ ዝግጅቱ ባለፈው ሰኞ የደቡብ አፍሪካ ጎረቤት ወደ ሆነችው ናሚቢያ የገባ ሲሆን ዛሬ ከናሚቢያ ጋር ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለቻን የተሰባሰበው ቡድን ለዓለም ዋንጫ ያለፉት የጥቁር ክዋክብቶች ስብስብ እንደሌሉበት  ታውቋል፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ በዓለም 24ኛ ሲሆን ቡድኑን በአሰልጣኝነት የሚመራው የአገሬው ተወላጅ ጄምስ ኬዋሲ ነው፡፡ በሌላ በኩል በምድብ 3 የኢትዮጵያ የመጀመርያ ተጋጣሚ የሆነው የሊቢያ ብሄራዊ ቡድን የሜዲትራንያን አረበኞች በሚለው ቅፅል ስሙ ሲታወቅ በፈረንሳዊው ዋና  አሰልጣኝ ሃቪዬር ክሌሜንቴ ይመራል፡፡ ሊቢያ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ከዓለም 64ኛ ናት፡፡ ቀዮቹ ሰይጣኖች በሚል ስሙ የሚታወቀው የኮንጎ ብራዛቪል ብሄራዊ ቡድን በፊፋ ወርሃዊ እግር ኳስ ደረጃ በዓለም 91ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡

Saturday, 04 January 2014 12:41

የደቡብ ሱዳን አዙሪት…

…ከሪፍረንደም ወደ ደም!
“እኔ ደቡብ ሱዳንን ነፃ አወጣት ዘንድ የተመረጥኩ የኑዌሮች ልጅ ነኝ… ተከተሉኝ ወደ ነፃነት እንሂድ!”
በስተመጨረሻም ሱዳናውያን ከዘመናት የእርስ በርስ ጦርነትና የጎሳ ግጭት ትርፍ እንደሌለ ገባቸው፡፡ ከጠመንጃ የተሻለ አማራጭ ለመውሰድ ፈቃዳቸው ሆነ፡፡ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲና የሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ በፈረሙት የሰላም ስምምነት፣ ከ25 ዓመታት በላይ የዘለቀውን የእርስ በርስ ግጭት መቋጫ አበጁለት - እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም፡፡
ይህን ስምምነት ተከትሎ ሱዳናውያን፣ ዕጣ ፋንታቸውን በፍጥጫ ሳይሆን በምርጫ፣ በደም ሳይሆን በሪፈረንደም ለመወሰን ተስማሙ፡፡ ከአጠቃላዩ የደቡብ ሱዳን ህዝብ 99 በመቶ ያህሉ፣ የሱዳንን ሁለት መሆን ደግፈው ድምጻቸውን ሰጡ።
 ሃምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም፡፡ ይህቺ ቀን ከ11 ሚሊዮን ለሚበልጡት ደቡብ ሱዳናውያን ልዩ ትርጉም አላት፡፡ የዘመናት ደም መፋሰስ የተቋጨባት፣ የአዲስ ንጋት ጮራ የፈለቀባት፣ ነጻነት የታወጀባት ልዩ ቀናቸው ናት - አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን 195ኛዋ  አገር ሆና አለምን የተቀላቀለችበት፡፡
ለሩብ ምዕተ አመት ከዘለቀ የእርስ በርስ ግጭትና ደም መፋሰስ በኋላ፣ ሱዳንን ሰሜን ከደቡብ ለሁለት የሚከፍል ድንበር ተሰመረ፡፡ “የነጻነት ቀን መጣች!!” የሚል መዝሙር ከደቡብ ሱዳን ሰማይ ስር ተዘመረ። ይህ ክስተት ከአለም ፖለቲካዊ ስኬቶች አንዱ እንደሆነ ተነገረለት፡፡ ከደቡብ ሱዳን ሰማይ ስር የሰላም ጀንበር ወጣች ተብሎ አገር በደስታ ፈነጠዘ። ደስታ፣ እልልታና ጭፈራ ሆነ፡፡ የአዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ባንዲራ፣ በነጻነት ዝማሬ ታጅባ ከፍ ብላ ተሰቀለች። ለሁለት አመታት አንጻራዊ የሰላም አየር ከሚነፍስበት ሰማይ ስር በነጻነት ተውለበለበች፡፡ ወደሶስተኛው አመት መንፈቅ ያህል እንደተጓዘች ግን፣ ያልተጠበቀ አውሎንፋስ ሳይታሰብ ከተፍ ብሎ ከወዲያ ወዲህ ያራግባት ጀመር፡፡
ከሱዳን ለመገንጠልና ነጻ ለመውጣት በአንድነት አብረው ለዘመናት ሲዋደቁ የኖሩ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች፣ የጋራ ጠላታቸውን ባሸነፉና ነጻ ወጣን ባሉ በሁለት አመታቸው እርስ በርስ ጦር ለመማዘዝ ተዘጋጁ፡፡ ጎሳ ድንበር ሆኖ አይለያየንም ብለው አብረው ለመኖር የተስማሙ ደቡብ ሱዳናውያን፤ ጎራ ለይተው ሊታኮሱ፣ ጎሳ መድበው ሊጫረሱ፣ ዳግም ለሌላ ጦርነት ክተት አውጀው ተነሱ፡፡ ተነጋግረው ያወረዱትን፣ በቃን ብለው የጣሉትን ደም የለመደ ጠመንጃ ዳግም መልሰው ጨበጡ፡፡ ወደ አደባባይ ወጡና እርስ በርስ ተበጣበጡ፡፡
ከሁለት አመታት በፊት በሪፈረንደም ነጻነታቸውን ያወጁት ደቡብ ሱዳናውያን፣ ከሳምንታት በፊት አዲስ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። አዲሲቷን ደቡብ ሱዳን ይመሩ ዘንድ በምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፣ መንበራቸው ላይ ሶስት አመት ሳይቆዩ ነቅናቂ መጥቶባቸዋል፡፡ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር ናቸው፣ በሳልቫ ኬር ላይ አማጽያንን አስታጥቀው የዘመቱባቸው፡፡
ሲጀመር ስልጣን ፈላጊዎች ያሴሩት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው ተብሎ የተነገረለት የሰሞኑ የአገሪቱ ግጭት፣ እየዋል እያደር ግን የአገሪቱን ጎሳዎች ጎራ ለይቶ ያሰለፈ መረር ያለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄ መሆኑ እየለየ መጥቷል፡፡ ከአገሪቱ ህዝብ አብላጫውን ቁጥር (ከህዝቡ 15 በመቶ) የሚይዙት የዲንቃ ጎሳ አባላት ሲሆኑ፣ የኑዌር ጎሳ አባላት ደግሞ 10 በመቶ በመያዝ በብዛት የሁለተኛነትን ደረጃ ይይዛሉ፡፡ ሳልቫ ኬር ከዲንቃ፣ ማቻር ደግሞ ከኑዌር መሆናቸው የሁለቱን ግጭት የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የጎሳዎች ጉዳይ አድርጎታል እየተባለ ነው፡፡
በአብዛኛው ሳልቫ ኬር የወጡበት የዲንቃ ጎሳ አባላትን የያዘው የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦር፣ ከኑዌር ጎሳ የሆኑት የቀድሞው ምክትል ፕሬዜዳንት አስታጥቀው ያሰለፏቸውን አማጽያን ለመደምሰስ ታጥቆ ተነስቷል፡፡ በአሜሪካ የሰላም ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ፖለቲከኛ ጆን ቴሚን እንደሚሉት፣ ኬርና ማቻር እንዲህ በይፋ ባይታኮሱም በወንበር ጉዳይ በጥርጣሬና በጥላቻ ሲተያዩ የኖሩ የረጅም ጊዜ ባላንጣዎች ናቸው። የግጭቱ ሰበብ ብዙዎች እንደሚሉት ነዳጅ በገፍ የመጥለቅ ጉጉት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ባለስልጣናት መካከል ያለው የስልጣን ሽኩቻና የዘመናት ታሪክ ያለው ያልተፋቀ የጎሳ ልዩነት ነው ባይ ናቸው ፖለቲከኛው፡፡
ሳልቫ ኬር ባለፈው ሃምሌ የቀድሞውን ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻርን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ አባላትን ማባረራቸው፣ ከዘመናት የእርስ በርስ ግጭት ለአፍታ አርፋ የነበረችውን አገር ዳግም ወደከፋ ነገር ሊከታት የሚችል መንገድ ጠርጓል። በአጭር የስልጣን ዘመናቸው ህገመንግስቱን የጣሱ በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል ተብለው የሚታሙት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፣ በካቢኔው ላይ ያሳለፉት ውሳኔ ብዙዎችን አበሳጭቷል፡፡ የወሰዱት እርምጃ የስልጣን ጥመኛነታቸውን ብቻም ሳይሆን ዘረኛነታቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
የሱዳን ትሪቢዩኑ ዘጋቢ አቲያን ማጃክ ማሉ እንደሚለው፣ ሳልቫ ኬር ባባረሯቸው የካቢኔ አባላት ምትክ የሾሟቸው አብዛኞቹ ባለስልጣናት፣ በእርስ በርስ ጦርነቱ ጊዜ ከካርቱም ባለስልጣናት ጋር ይሰሩ የነበሩና አሁንም ድረስ ቅርበትና ወዳጅነት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም በሹም ሽሩ ውስጥ የሱዳን እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል ጥርጣሬን በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል፡፡
በዚህ አወዛጋቢና ፍትሃዊ አለመሆኑ የሚነገርለት ሹም ሽር ከምክትል ፕሬዚደንትነታቸው ተነቅለው የተባረሩት ማቻር፣ ቂም ቋጥረው ነበር ወደ ትውልድ ቦታቸው ዩኒቲ ግዛት የሄዱትና የኑዌር ጎሳ አባላትን ለአመጽ የቀሰቀሱት፡፡
“ሳልቫ ኬር የሚሉት አምባገነን የሚመራው የዲንቃ ጎሳ መንግስት፣ ከአገራችን ጠራርጎ ሊያጠፋን ተነስቷል፡፡ እኛ ኑዌሮች በድህነት ስንማቅቅ፣ እነሱ ግን ነዳጅ እየቸበቸቡ ሊንደላቀቁ ማነው የፈቀደላቸው?!... ተነሱ እንጂ ጎበዝ!” ብለው ቀሰቀሱ ማቻር፡፡ ድሮም በመንግስት ስልጣን አናሳ ቦታ ይዘናል፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንም ፍትሃዊ አይደለም ብለው እርር ትክን ይሉ የነበሩት ኑዌሮችና የሌሎች አናሳ ጎሳዎች ወታደሮች ናቸው፣ የማቻርን ጥሪ ሰምተው ነፍጥ ያነገቡት፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ታማኝ የጸጥታ ሃይሎች ጋር የከረረ ግጭት ውስጥ የገቡት፡፡
“ልብ አርጉልኝ!... ማቻር የሚሉት ሴረኛ መንግስቴን ሊፈነቅል ነው!” ሲሉ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ አቤት አሉ ሳልቫ ኬር፡፡ ማቻር በበኩላቸው፣ “ያለ ስሜ ስም እየሰጠኝ ነውና አትስሙት!... ሰውየው እልም ያለ ሙሰኛና አምባገነን ነው!” በማለት ውንጀላውን አስተባበሉ፡፡ ሁለቱም ያሉትን ሲሉ፣ የሁለቱም ጦር ተግቶ መታኮሱን ቀጠለበት፡፡
ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ የመጣው ጦርነት ከአገሪቱ አስር ግዛቶች አምስቱን አዳርሷል፡፡ ታማኝ ምንጮቼ ያላቸውን ጠቅሶ ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው፣ ደቡብ ሱዳናውያን የጎሳ መደባቸው እየታየ ብቻ ግድያና ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መረጃን ዋቢ በማድረግ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ እስካለፈው ማክሰኞ ብቻ በግጭቱ ከ1ሺህ በላይ ዜጎች ሞተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ባሉ የጅምላ መቃብሮች ውስጥ እየተገኙ ያሉ አስከሬኖች የሟቾችን ቁጥር ከፍ እያደረገው ነው ተብሏል፡፡ የዩኒቲ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ቤኒቱ ውስጥ ባለ የመቃብር ስፍራ ብቻ 34 አስከሬኖች ሲገኙ፣ በአቅራቢያዋ ካለ የወንዝ ዳርቻም የሌሎች 20 ሟቾች አስከሬን ወድቆ ተገኝቷል፡፡
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ናቪ ፒላይ በበኩላቸው፤ የማቻር ወታደሮች በተቆጣጠሩት አንድ አካባቢ 75 አስከሬኖች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡ ፍለጋው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥርም ከዚህ በእጅጉ እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡
የመንግስት ጦር ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያለባቸውንና 95 በመቶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሰረተባቸውን በአማጽያኑ በቁጥጥር ውስጥ የገቡ ቤኒቱን የመሳሰሉ ቦታዎች ለማስለቀቅ መታኮስ ከጀመረ ሁለት ሳምንታት አልፈዋል። የአማጽያኑ ጦር የአገሪቱን መዲና ጁባን ለመቆጣጠር 200 ኪሎ ሜትሮች ብቻ እንደቀረው ሲናገር፣ መንግስት በተራው እየጠራረግኋቸው ነው እያለ ይገኛል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በነዳጅ አምራችነቷ ወደምትታወቀው የላይኛው አባይ ግዛት ዋና ከተማ ማላካል የተዛመተው ግጭት፣ ቀስ በቀስ ወደ ቦርና ሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡
በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ከኑሯቸው ተፈናቅለው በርእሰ መዲናዋ ጁባና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ተበትነው ይገኛሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከመጣባቸው መከራ ለማምለጥ ወደ ቢሮው ለመጡ ከ80 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ዜጎች ከለላ ለመስጠት የቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 24 ሺህ ያህል ተፈናቃይ ዜጎች ከመጣው መዓት ለማምለጥ በጫካዎች ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙና፣ ሌሎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩም በአብያተ ክርስቲያናት ቅጽር ግቢ እንደተጠለሉ ዘ ጋርዲያን ባለፈው ማክሰኞ ዘግቧል፡፡
6ሺህ 800 ሰላም አስከባሪዎችን በስፍራው ያሰማራው የተመድ የጸጥታው ምክርቤት፣ ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን በማጤን ተጨማሪ 5ሺህ 500 ወታደሮችን ለማሰማራት ውሳኔ ላይ ደርሷል። ያሰማራቸውን ፖሊሶች ቁጥርም ከ900 ወደ 1ሺህ 323 ከፍ ለማድረግ አቅዷል። ይህ እርምጃ ተፈናቃይ ዜጎችን ለመርዳት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባይካድም፣ የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪሙን ግን፣ ግጭቱ ፖለቲካዊ እንደመሆኑ ፖለቲካዊ እንጂ ወታደራዊ መፍትሄ እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ በአገሪቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የነዳጅ ምርት ስራ በከፍተኛ ሁኔታ እየደናቀፈ ይገኛል፡፡ የደቡብ ሱዳን የፔትሮሊየም ሚንስትር ስቴፈን ዲሁ ዳው እንዳሉት፣ በዩኒቲ ግዛት ይከናወን የነበረው የነዳጅ ምርት፣ ግጭቱ መከሰቱን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል፡፡ ይህም 250 ሺህ በርሜል ከነበረው የአገሪቱ ዕለታዊ የነዳጅ ምርት 45 ሺህ በርሜል ያህል ቅናሽ አስከትሏል፡፡ ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለም የአገሪቱን የነዳጅ ምርት ክፉኛ እንደሚጎዳው ይጠበቃል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ግጭት አገሪቱ ለአለማቀፍ ገበያ በምታቀርበው የነዳጅ ድፍድፍ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል በሚል ስጋት፣ የተለያዩ ኩባንያዎች ባለፈው ማክሰኞ በነዳጅ ዋጋቸው ላይ የተወሰነ ጭማሪ አድርገዋል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት በጉዳዩ ላይ የተለያየ አቋም መያዛቸው እየተነገረ ነው፡፡ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ የአሸባሪዎች ስፖንሰር ከምትላት ሱዳን ተገንጥላ ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች አገር መሆኗን አጥብቃ ስትደግፍ ነው የኖረችው፡፡ ለወደፊት ከነዳጇ የመቋደስ ዕድል ይኖረኛል ብላ የምታስበዋ አሜሪካ፣ ደቡብ ሱዳን ወደ ሌላ ጦርነት እንድትገባ አትፈልግም፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም፤ ኬርና ማቻር ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ ጥሪያቸውን ልከዋል፡፡ ድርድሩን የሚያመቻች ልዩ ልኡክና ዜጎችን ከአደጋው የሚያተርፉ 150 ያህል ልዩ የባህርና የአየር ሃይል አባላትንም በጅቡቲና ኡጋንዳ በኩል ወደዚያው ልከዋል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኡጋንዳና ኬኒያን የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸውን ከደቡብ ሱዳን ለማስወጣት እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን 380 አሜሪካውያንና 300 የሌሎች አገራት ዜጎች በአፋጣኝ ከደቡብ ሱዳን እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ቀውስ እንዲህ እንደዋዛ በአጭር ጊዜ እልባት አግኝቶ የሚበርድ አለመሆኑን የሚናገሩ ተንታኞች ብዙ ናቸው፡፡
በወቅታዊ አለማቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ሱፍያን ቢን ኡዝያር፣ ጉዳዩ የስልጣን ብቻ ሳይሆን ስር የሰደደ የጎሳ ጥያቄ ጭምር መሆኑ አሳሳቢና የበለጠ አስከፊ እንደሚያደርገው ይናገራል፡፡ ሳልቫ ኬር ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለተቀናቃኞቻቸው የማይተኙና ወንበራቸውን ላለማስነካት ታጥቀው የቆሙ መሆናቸውን የገለጸው ኡዝያር፣ ማቻር በበኩላቸው ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የመሆን አላማ እንዳላቸው በአደባባይ ሲናገሩ መሰማቱን ጠቁሟል፡፡ መለሳለስ የማይታይበት የሁለቱ ሰዎች አቋም ነገሩን የበለጠ እንደሚያከረውም ተናግሯል፡፡
አሜሪካ፣ ኖርዌይና ኢትዮጵያ የሚመሩት ቡድንም ወደ አገሪቱ በማምራት ችግሩ በሰላማዊ ድርድር የሚፈታበትን መላ ለመፈለግ የራሱን ጥረት አድርጓል፡፡ አሜሪካ ወደ ደቡብ ሱዳን የላከችውን ልዩ ልኡክ በመምራት ወደ ጁባ ያመሩት ዶናልድ ቡዝ፣ ሁለቱን አካላት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ለማግባባት ጥረት አድርገዋል፡፡ ኬርና ማቻርም ለውይይት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ ነገሩ ከልብ አይመስልም፡፡ ማቻር ውይይቱን ማድረግ የምችለው በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አጋሮቼ ሲፈቱ ብቻ ነው ሲሉ፣ ኬር በበኩላቸው ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ አልፈልግም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ቆራጥ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ መቀጠላቸውም ሆነ፣ የአማጽያኑን ጦር የሚመሩት ማቻር አዲስ ወታደራዊ መንግስት በመመስረት ላይ እንደሚገኙ ፍንጭ መስጠታቸው፣ በዚች አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም የመውረድ ተስፋ እንደሌለ ያመላክታል ብሏል ኡዝያር። ይልቁንም አገሪቱ ወደባሰ የእርስ በርስ ጦርነት የመግባት ዕድሏ ሰፊ ነው ባይ ነው፡፡
ከአለማቀፍ ሰሞንኛ መነጋገሪያ የቀውስ አጀንዳዎች አንዱ የሆነው የሁለቱ ሃይሎች ግጭት፣ በብዙዎች የተለያየ ትንተና እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ ድህነት፣ የጎሳ ፖለቲካ፣ አምባገነንነት፣ ኢ- ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የስልጣን ጥም፣ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት… እና ሌሎችም ጉዳዮች ለደቡብ ሱዳን ግጭት መነሻ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
የሱዳን ትሪቡዩኑ ዘጋቢ የአቲያን ማጃክ ማሉ ብያኔ፣ ‘ሌሎችም’ ከሚለው መደብ ውስጥ ይፈረጃል፡፡ ማሉ እንደሚለው፣ የሰሞኑ የደቡብ ሱዳን ግጭት ንጉንዲንግ ከተባሉት የኑዌር ነብይ ትንቢት የመነጨ፣ የማቻር ቅዠት ነው፡፡ ከመቶ አመታት በፊት በህይወት የነበሩት እኒህ የኑዌር ጎሳ አባል የሆኑ የተከበሩ ነብይ፣ በአንድ ወቅት “ከኑዌር ጎሳ የሆነ ጥርሰ ፍንጭትና ግራኝ ሰው ደቡብ ሱዳንን ነጻ ያወጣታል፣ ህዝቧንም በወጉ ይመራል” የሚል ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ ትንቢቱ ከተነገረ ከዘመናት በኋላ፣ ሬክ ማቻር ወደራሱ ተመለከተ፡፡
እሱ የኑዌር ጎሳ አባል ነው፡፡
እሱ ጥርሰ ፍንጭት ነው፡፡
እሱ ግራኝ ነው፡፡
ማቻር፤ በኑዌሮች መካከል ግራ እጁን ወደላይ ከፍ አድርጎ በፍንጭት ጥርሱ እየተፍለቀለቀ እንዲህ ሲል ተናገረ…“እኔ ደቡብ ሱዳንን ነጻ አወጣት፣ ህዝቧንም በወጉ እመራ ዘንድ የተመረጥኩ የኑዌሮች ልጅ ነኝ!!... ተከተሉኝ ወደ ነጻነት እንሂድ!!...”
በደል ያንገበገባቸው፣ ጭቆና የሰለቻቸው፣ ደማቸው የፈላባቸው ኑዌሮችም፤ ሌሎች ተበዳይ ጎሳዎችን አግተልትለው፣ የጀግና ልጃቸውን ማቻርን ዱካ ተከትለው፣ ወደ ጁባ ሊተሙ ጠመንጃቸውን ወለወሉ - ይላል አቲያን ማጃክ ማሉ፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፓርላማ የወጣውን ህግ ሲያሻሽል አሁን የመጀመሪይው ነው፡፡ የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደርጐባቸው ነበር፡፡
“በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ላይ የቀረበው የሙስና ክስ መታየት ያለበት በከፍተኛ ፍ/ቤት ነው ወይስ በጠቅላይ ፍ/ቤትን” በሚል ለተነሳው ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ለሰዓታት የተከራከሩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፤ የሚኒስትሮች ክስ በጠቅላይ ፍ/ቤት እንዲታይ የሚደነግገው አንቀጽ ከፀረ ሙስና አዋጁ እንዲሰረዝ በ76 የድጋፍና በ8 የተቃውሞ ድምጽ ወሰኑ፡፡
የሙስና ክሶችን በቀዳሚነት የመዳኘት ስልጣን የከፍተኛ ፍ/ቤት እንደሆነ የሚገልፀው የፀረሙስና አዋጅ፣ ሚኒስትሮች ሊከሰሱ ግን በቀጥታ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት እንደሚቀርብ ይገልፃል፡፡ በ1993 ዓ.ም ኢህአዴግ ውስጥ በተከሰተው ፀብ ከፓርቲው አመራርነት የተባረሩት የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ስዬ አብርሃ፣ በወቅቱ በሙስና መከሰሳቸው የሚታወቅ ሊሆን፣  ጉዳያቸው በቀጥታ በጠቅላይ ፍ/ቤት እንዲታይ መደረጉን ተቃውመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንደሌሎች ተከሳሾች የአቶ ስዬ ክስ በከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲታይ መከራከሪያ ያቀረቡት ጠበቃ፤ አለበለዚያ ግን ይግባኝ የመጠየቅ የተከሳሽ ህገመንግስታዊ መብትን የሚጥስ ይሆናል ብለዋል፡፡  በፀረ ሙስና አዋጅ የተካተተው አንቀጽ ህገመንግስቱን ስለሚቃረን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት የአቶ ስዬ ጠበቃ ቢከራከሩም፤ ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ጥያቄው እንደገና ፍ/ቤት ውስጥ የተነሳው ከአስር አመታት በኋላ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ ሃላፊዎች ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በአንድ በኩል ዋና ዳሬክተሩ አቶ መላኩ ፈንታ በሚኒስትርነት ማዕረግ የተሾሙ በመሆናቸው፣ በፀረ ሙስና አዋጁ መሰረት ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍ/ቤት መታየት ይገባዋል የሚል አስተያየት ቀርቧል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህጐች፣ በበኩላቸው ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደሆነ በህገመንግስት ውስጥ በግልጽ ስለሰፈረ፣ የሁሉም ተከሳሾች ጉዳይ በከፍተኛ ፍ/ቤት መታየት አለበት በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱም፤ የአዋጁ አንቀፆች ከህገመንግስቱ ጋር እንደሚጋጩ ወይም እንደማይጋይጩ የመወሰንና ለዚህ ክርክር እልባት የመስጠት ስልጣን እንደሌለው በመግለጽ ነው፣ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ም/ቤት ያስተላለፈው፡፡  
በፌደሬሽን ምክር ቤት ስር የተቋቋመው የህገመንግስት ጉዳዮች የአጣሪ ጉባኤ፣ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የውሣኔ ሃሳብ ያዘጋጀ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላት ለበርካታ ሰዓታት ተከራክረውበታል፡፡
“በፀረ ሙስና አዋጅ የተካተተው አንቀጽ ህገ መንግስቱን ስለማይፃረር ባለበት ይቀጥል፤ እንዲያውም ህገመንግስቱን የሚያስከብር ነው” በማለት አስተያየት የሰነዘሩ አባላት፤  “ባለስልጣናት በሙስና ሲባልጉ አምነው የተቀበሉትን ህገመንግስት ስለሚጥሱ ይግባኝ በሌለበት ሁኔታ ፍርዳቸው መታየቱ ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው  ጉዳዩ ክብደትና እና ጥልቀት ያለው መሆኑን በመጠቆም ጉዳዩን ለማጤን የተሰጠው ጊዜ አጭር ነው የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ “የይግባኝ መብት የሚጣሰው የአቶ መላኩ ብቻ ሳይሆን የአቃቤ ህግም ነው” በማለት የተከራከሩ አባላት፣ ጉዳዩ በከፍተኛው ፍ/ቤት መታየቱ ሁለቱንም ይጠቅማል ብለዋል፡፡ ይግባኝ በሌለበት ሁኔታ ፍርዳቸው መታየት አለበት በሚል የተሰነዘረውን ሃሳብ በመቃወም  ምላሽ የሰጡት የአጣሪ ጉባኤው አባል አቶ ሚሊዮን አሰፋ “የሚኒስትሮች ክስ ከሌላው ሰው ተነጥሎ ይታይ” የሚል ሃሳብ በዜጐች መካከል የመደብ ልዩነት መኖሩን ከሚያመላክት ፊውዳላዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ በመሆኑ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም፤ አከራካሪው አንቀጽ ህገመንግስቱን ስለሚቃረን ከፀረ ሙስና አዋጅ እንዲሰረዝ በ76 የድጋፍና በ8 የተቃውሞ ድምፅ የተወሰነ ሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ለምክር ቤቱ የመጀመሪያው መሆኑን በመጠቆም ታሪካዊ ውሳኔ ነው በማለት አፈጉባኤው አቶ ካሳ ተክለብርሃን ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

በሐረር ከተማ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በቤቱ ደብቆ የተገኘ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ ተገለፀ፡፡ የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤  የመንግስት ሠራተኛ በሆነው ግለሰብ ቤት ውስጥ 2 ቦንቦች፣ 250 የመትረየስና 168 የስናይፐር ጥይቶች፣ 2 ጠብመንጃ፣ 2 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 21 የልዩ ልዩ የጦር መሣሪያ ካርታዎች እንዲሁም 1 ሣንጃ ደብቆ ተገኝቷል፡፡
ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በግለሰቡ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ፤ የጦር መሣሪያዎቹ ቤት ውስጥ፣ ቦንቦቹና ጥይቶቹ ደግሞ በዘይት ጀሪካን ውስጥ ተደብቀው እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ግለሰቡ በግምት ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውና በከተማው የረዥም ጊዜ ነዋሪ እንደሆነ ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በቅርቡም በሐረር ከተማ ቀበሌ 08 ነዋሪ በነበረ ግለሰብ ቤት ውስጥ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ተደብቀው መገኘታቸውን የጠቆሙት ኮማንደሩ፤ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ፣ በግለሰቡ ላይ ክስ እንደተመሰረተበት ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

በኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ግዢ ከሌሎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የስራ ሃላፊዎች ጋር በመመሳጠር በፈፀሙት የሙስና ወንጀል፣ መንግስትን ከ318 ሚ. ብር በላይ  አሳጥተዋል የተባሉት ሁለት የውጭ ሀገር ዜጐች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ወሰነ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ከፍተኛው ፍ/ቤት ግለሰቦቹ በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ የወሰነው በጋዜጣ የተደረገላቸውን ጥሪ አክብረው ባለመገኘታቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ሚስተር ጂሲስ ባራሶይን እና ሚስተር ናሪሽ ቻንድራ፤ በክስ መዝገቡ ከተካተቱት የኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ከአቶ ሞገስ በላቸው፣ መኮንን ብርሃኔና መስፍን ብርሃኔ ጋር በመመሳጠር ህንድ በሚገኘው “ኮብራ” የተሰኘ ኩባንያቸው አማካይነት ግምታቸው ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ 3520 አሮጌና የቴክኒክ ችግር ያለባቸውን ትራንስፎርመሮች አዲስ በማስመሰል ያቀረቡ ሲሆን በዚህም በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ የጥቅም ተካፋይ ሆነዋል ተብሏል፡፡
የሌሎቹ ተከሳሾች ጠበቆች የተረጋገጠ የሰነድ ማስረጃ ለኮሚሽኑ አቃቤ ህግ እንዲያደርሱ፤  አቃቤ ህግዋ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ባሉት ተከሳሾች በቀረበው የቅድመ ክስ መቃወሚያ ላይ መልስ ይዞ እንዲቀርብ ያዘዘው ፍ/ቤቱ፤ ለጥር 13 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከታናሽ ወንድሙ ጋር ነዳጅ ለመቅዳት ወደ “ኦይል ሊቢያ” የሄደውን የ24 አመት ወጣት ሙባረክ ሱልጣንን በብረት ቀጥቅጠው ገድለዋል በሚል የተጠረጠሩ አምስት የነዳጅ ማደያው ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ሟች ወጣት ሙባረክ፤ ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ከመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ፣ ጳውሎስ ሆስፒታል ፊት ለፊት ወዳለው “ኦይል ሊቢያ” የሄደው የመኪናው ነዳጅ አልቆበት በጀሪካን ለመቅዳት ነበር፡፡ “ቤንዚን በጀሪካን አንቀዳም፣ በሊትር ነው” በሚል በተነሳ ውዝግብ፣ ከነዳጅ ቀጂዎቹ ጋር ጠብ ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ቤተሰቦቹ፤ የነዳጅ ማደያው ሰራተኞች ልጃቸውን በብረት ጭንቅላቱና ጀርባው ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደደበደቡትና ታናሽ ወንድሙ ሊገላግል ሲገባም በያዙት ብረት እሱንም ደብድበው ጉዳት እንደደረሱበት ገልፀዋል፡፡
በድብደባው ክፉኛ የተጐዳውን ልጃቸውን ህይወት ለማትረፍ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል መውሰዳቸውን የጠቆሙት ቤተሰቦች፤ “ከአቅማችን በላይ ነው” የሚል ምላሽ ከሆስፒታሉ በማግኘታቸው፣ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ወስደው እንዳስተኙትና ለሁለት ቀን ህክምና ሲደረግለት ከቆየ በኋላ ህይወቱ እንዳለፈ ተናግረዋል፡፡  
ሟቹ ወጣት፤ ሰው አክባሪና ታታሪ ሰራተኛ እንደነበር ያስታወሱት ቤተሰቦቹ፤ በመልካም ባህሪው ከሠው ጋር ተግባብቶ ከመስራት ውጪ ከማንም ጋር ተጣልቶ እንደማያውቅ መስክረዋል፡፡ በድብደባው ወቅት በኪሱ ይዞት የነበረው ገንዘብና ሞባይሉ መሰረቁን ገልፀው፤ ልጃቸው በገዛ ሀገሩ ላይ በብረት ተቀጥቅጦ መገደሉ ክፉኛ እንዳሳዘናቸው በሃዘን ተሞልተው ተናግረዋል፡፡
ጉለሌ ወደሚገኘው “ኦይል ሊቢያ” ሄደን ነገሩን ለማጣራት ብንሞክርም፤ ባለቤቱን ጨምሮ የማደያው ሰራተኞች በፖሊስ ስለተወሰዱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ፖሊስ ከግድያው ጋር በተያያዘ 5 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያኮሄደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

• የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተቀጥሯል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፍቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ እና በባልደረቦቻቸው ላይ አቃቤ ህግ ከፍ/ቤቱ በታዘዘው መሠረት ክሱን አሻሽሎ አቀረበ፡፡ ቀደም ሲል የቀረበው ክስ አቶ ቃሲም ፊጤ፣ የምርመራና ክስ ኤክስፐርቱ አቶ ተስፋዬ ዘመድኩን፣ የሊዝ አሰባሰብ ክትትል ኦፊሰሩ አቶ ገ/የሱስ ኪዳኔ እንዲሁም የመሬት አቅርቦት አፈፃፀም የስራ መሪ አቶ በቀለ ገብሬ፤ ንብረትነቱ የኢንጅነር ግርማ አፈወርቅ የሆነን 500 ካሬ ሜትር ቦታ በመመሳጠር ለሌላ ግለሰብ እንዲሰጥ አድርገዋል የሚል ሲሆን የተከሳሾቹ ጠበቆች በክሱ ላይ የጉዳቱ መጠን በትክክል አልተገለፀም የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ክሱ እንዲሻሻል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ አቃቤ ህግ ባለፈው ረቡዕ አሻሽሎ ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ፤ በተበዳዩ ላይ ከ342 ሺህ ብር በላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በቦታው ላይ ሊከናወን የታቀደ ፕሮጀክት መስተጓጐሉን አመልክቷል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችም የጉዳቱ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ደንበኞቻቸው ጉዳያቸውን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቁ ሲሆን በተሻሻለው የግምት መጠን መሠረት የመከላከያ ማስረጃችንን በድጋሚ እናቅርብ የሚል ጥያቄም አቅርበዋል፡፡ ከጠበቆቹ ለተነሱት መከላከያዎች አቃቤ ህግ በሰጠው መልስም፤ ግለሰቦቹ አደረሱ የተባለው ጉዳት ትንሽ ነው መባሉ ተቀባይነት እንደሌለውና የተጠቀሰባቸው አንቀጽም ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን በማመልከት፣ ጥያቄአቸው ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው 1ኛ ወንጀል ችሎትም ባስተላለፈው ትዕዛዝ፤ ጉዳዩ ወደ መደበኛ ክርክር ተሻግሮ ማስረጃ እንዲሰማና ሁለቱም ወገኖች የማስረጃ ማሻሻያቸውን እንዲያቀርቡ በማለት፣ የአቃቤ ህግን ማስረጃና ምስክሮች ለመስማት ለጥር 28 ቀን 2006 ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

• በገዳሙ እንክብካቤ እንጂ ጭቆናና እንግልት የለም /የገዳሙ አስተዳደር/

የምስካየ ህዙናን መድሀኒያለም ገዳም ሰራተኞች በቤተ - ክርስቲያኑ አስተዳደር ከፍተኛ ጭቆናና በደል እንደሚደርስባቸው ተናገሩ፡፡ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መላዕከ ገነት አባተክልማርያም አምኜ የገዳሙን ሰራተኛየ ሚያስተዳድሩት እንደመፈንሳዊ አባት ሳይሆን እንደ አምባገነን መሪ ነው ሲሉ ሰራተኞቹ አማረዋል የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ተ/ማርያም አምኜ በበኩላቸው በቤተክርስቲያኒቱ ሁሉም ስርዓትና ደንብን ተከትሎ እንጂ ያለ አግባብ የሚንገላታም የሚጨቆንም የለም ሲሉ መልሰዋል፡፡ “ቤተክርስቲያኑ የሚመራው በፓትሪያርኩ ነው” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ የደሞዝ ማነስን ተከትሎ እንዲያነጋግሩን አባ ተክለ ማርያምን ለስብሰባ ጠርተን እግረ መንገዳችንን የገዳሙን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ እርሳቸው ያለ አግባብ የሚሰሯቸውን ስራዎች፣ እና አጠቃላይ ያለውን ችግር አስረዳናቸው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡

ይሁን እንጂ ለምን አካሄደን ተቃወማችሁ በሚል በግል እየጠሩ ማስፈራሪያና ዛቻ ያቀርቡብናል ለአንዳንዶቻችን ያለ አግባብ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተፅፎብናል ብዙዎችም ከስራ ተባረዋል ብለዋል የገዳሙ ሰራተኞች፡፡ አስተዳዳሪው ወደ ገዳሙ ተሹመው ከመጠ አንድ አመት ከስድስት ወር ቢሆናቸውም እስከዛሬ በቤተክርስቲያኑ አንድም ልማት እንዳላካሄዱ የገለፁት ቅሬታ አቅቢዎቹ ችግር አለ ይስተካከል በማለት ቅሬታ የሚያርበውን ሁሉ እንደጠላት በማየት ሊመደብ ወደማይገባው ቦታ ይመድባሉ፣ ከደረጃ ዝቅ ያደርጋሉም ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ ያለ አግባብ እየተመራች ነው ሰራተኞቹ እየተንገላቱ ነው በሚል ቅሬታ ያቀረበውና የቤ/ክርስቲያኑ ጉዳይ አስፈፃሚ የነበረውን መምህር ሰለሞን ተስፋዬን ከስራው አንስተው ሙያው ወደማይፈቅደው የገዳሙ ክሊኒክ እንደመደቡትና በዚህም ለገዳሙ የቦርድ ሊቀመንበር አመልክቶ ጉዳዩ እየታየ ባለበት ከስራ እንዳባረሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡

የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ተክለማሪያም በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው ሲመልሱም ሰራተኞቹ የደሞዝ ጥያቄ ባነሱ ጊዜ ባለፈው ሀምሌ ጨምረናልም ምግብ መጠለያና ሁሉን አሟልተን ይዘናችሁ እንዴት አሁን የጭማሪ ጥያቄ ታነሳላችሁ ብለናቸዋል ይላሉ፡፡ የመምህር ሰለሞንንን ከስራ መባረር በተመለከተም “ወደ ክሊኒኩ ያዛወርነው በእድገትና በሁለት እርከን የደሞዝ ጭማሪ ነው” ያሉት አስተዳዳሪው ጉዳዩን አምኖበት ስራውን ከተረከበ በኋላ ማንም ሳያውቅ ዘግቶ በመጥፋቱ ሊሰናበት ችሏል ብለዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን በተመለከተ ለአንድ ሰራተኛ መስጠቱን አምነው “ቤተክርስቲያኗ ሲኦል ናት” በሚል ለተናገረው ንግግር ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ የገዳሙ ክሊኒክ መካከለኛ ሆኖ ሳለ አልትራ ሳውንድ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ክልክል ነው በሚል ቅሬታ አቅራቢዎቹ የተናገሩ ሲሆን “በፊት እንጠቀም ነበር አሁን ተከልክለን አቁመናል” ብለዋል አባ ተክለማሪያም አምኜ፡፡ “የቤተክርስቲያኗን ስም ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እንዳሉ እናውቃለን” ያሉት አስተዳዳሪው በገዳሙ ያሉ እስረኞች በእንክብካቤ ተያዙ እንጂ በአንዳቸውም ላይ ጭቆናና እንግልት አላደረስንም ብለዋል፡፡

Published in ዜና
Page 13 of 14