ለአጭር ጊዜ ታምሞ ባለፈው ረቡዕ በተወለደ በ44 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አርቲስት ፈለቀ ጣሴ፤ከትላንት በስቲያ በደብረሊባኖስ ገዳም፣ ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት የቀብር ሥነሥርዓቱ ተፈፅሟል፡፡ በአዲስ ከተማ ት/ቤት ለመጀመርያ ጊዜ ከትያትር ጋር የተዋወቀው አርቲስት ፈለቀ፤ በኋላም የአርቲስት ተስፋዬ አበበ ትያትር ክበብን ተቀላቅሏል፡፡ አርቲስቱ በሀገር ፍቅር ትያትር - የጣር ሳቅ፣ የቀለጠው መንደር፣ ጥምዝ፣ የወፍ ጎጆ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ እንዲሁም በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ - ቀስተ ደመና፣ የክፉ ቀን ደራሽ፣ የደም ቀለበት፣ ማዶ ለማዶ፣ ፍለጋ፣ ጣይቱ፣ ምርጫው፣ ሶስና እና የታፈኑ ጩኸቶች በተባሉ ትያትሮች ላይ ተውኗል፡፡ ሰርፕራይዝ እና ጥቁር ነጥብ በተሰኙ ፊልሞችም ላይ መስራቱ ይታወቃል፡፡

በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማና አካባቢዋ የሥነጽሑፍ አፍቃሪያን የተቋቋመው “ሆራቡላ ሥነጽሑፍ ማሕበር” 20ኛ የስነጽሑፍ ዝግጅቱን የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 7፡30 በከተማው ሕይወት ሲኒማ ትንሿ አዳራሽ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ “የብዕር አዝመራ” በሚል ርእስ በሚቀርበው ዝግጅት፤ የማሕበሩ አባላት የግጥም፣ መነባንብ፣ ጭውውት እና ሌሎች ኪነጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዝነኛው የፊልም ተዋናይ ግሩም ኤርምያስ፤የህይወትና የሙያ ተመክሮውን ለማህበሩ አባላት እንደሚያካፍል ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ1940ዎቹ የተመሠረተው ጐንደር ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን የ60ኛ አመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ለአንድ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርስቲው ዘንድሮ ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በተጨማሪ በዓሉን ምክንያት በማድረግ 3ሺ የቀድሞ ተማሪዎችንም በድጋሚ ያስመርቃል ተብሏል፡፡ ዩኒቨርስቲው በማስገንባት ላይ ያለውን ሆስፒታልም በሰኔ ወር እንደሚያስመርቅ ታውቋል፡፡ በታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም በይፋ የተከፈተው የዩኒቨርስቲው ክብረ በአል የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡበት ሲሆን ክብረ በአሉ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡ ዩኒቨርስቲው ባካሄደው የ6 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር ላይ ከ2000 በላይ የተሳተፉ ሲሆን የሆቴልና ቱሪዝም ተማሪዎች ለቡርባክስ ህዝቦች መታሰቢያ ያደረጉትን የአዝማሪ ቅኝት አቅርበዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው ከመንግስት ጋር በመሆን በማስገንባት ላይ ያለው ባለ አንድ ሺ መኝታ ሪፈራል ሆስፒታል በሰኔ ወር እንደሚመረቅ ተነግሯል፡፡

The secret በተሰኘው የመጀመሪያ መጽሐፏ ከፍተኛ ዝናን የተቀዳጀችው አውስትራሊያዊ ደራሲ ርሆንዳ ባይርኔ The hero በሚል ያወጣችው ሦስተኛ መጽሐፏ “ጀግና” ተብሎ ወደ አማርኛ ተተረጐመ፡፡ መጽሐፉን የተረጐመው ብርሃኑ በላቸው ነው፡፡ “እያንዳንዳችን ወደዚህች ምድር የመጣነው በየራሳችን መንገድ ራሳችንንና ዓለምን የማበልጸግ ዓላማ ይዘን ነው” የሚለው መጽሐፉ፤ “አንተም ልዩ ነህና ለስኬት ተዘጋጅ” ይላል፡፡ 182 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ በ40.50 እየተሸጠ ነው፡፡

በገጣሚ ሲሳይ ታደሰ /ዘ-ለገሐሬ/ የተፃፉ የግጥም ስብስቦችን የያዘው ‹‹ለፍቅራችሁ›› የተሰኘ የግጥም መድብል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ 106 ግጥሞችን ያካተተው መድበሉ፤ “ለፍቅራችሁ” የሚል ርዕስ የተሰጠው መጽሐፉ ለህትመት እንዲበቃ ያገዙትን ሁሉ ለማመስገን እንደሆነ ገጣሚው ገልጿል፡፡ የግጥሙ መድበል ለአገር ውስጥ በ30 ብር፤ ለውጭ ደግሞ በ15 ዶላር ይሸጣል፡፡

Saturday, 11 January 2014 12:18

በፍቅር የወደቁ ገጣሚያን!

            ጀምስ ኢ.ሚለርና በርኒስ ሎቲ እንዲህ ይላሉ: “Poetry is simply a deep kind of pleasure – like roses, or music, or love” ገጣሚ ስንኝ ከመቋጠሩ በፊት ነፍሱ ከሆነ ነገር ጋር በፍቅር ወድቃ፣ በባህር መዋኘት፣ በአየር መንሣፈፍ አለባት፡፡ ቫዛር ሚላር የተሰኘችው አሜሪካዊ ገጣሚት ይህንን ሃሳብ ስታጎላ “poets have been in love with any number of things.” ትላለች፡፡ ለምሣሌ ቬሊ ከዘማሪዋ ወፍ ጋር በፍቅር እንደወደቀ ነው፡፡ የልቡ ኳስ በቅኔ የሚሞላው፤ የአይኑ ጉንጮች በእምባ የሚጠረዙት፣ የነፍሱ ዋሽንት የሚጠዘጠዘው እርሷን ሲያይ ነው፡፡ ጡቶችዋ ደረትዋ ላይ ዘውድ የደፋ ኮረዳ፣ አይኖችዋ እሣት የሚወረውሩ ሸጋ ከምታስደነግጠው ይልቅ በወፍዋ ሕይወት ይማረካል፡፡ ከአይኑ ሥር የሚፈስስ ፏፏቴ መዐዛና ውበታቸውን አንድ ላይ ከሚወረውሩት አበቦች ይልቅ ወፊቷ ታውረገርገዋለች፡፡ ቲ. ኤስ. ኢሊየት ደግሞ የካቶሊክ መነኮሳትን ሲያይ ይነዝረዋል፡፡ አይኖቹ ይፍለቀለቃሉ፣ ልቡ ቃላት ታዘንባለች፡፡ ሩፐርት ብሩክስ ራሱን “ታላቅ አፍቃሪ” የሚለውም ለዚህ ነው፡፡ ገጣሚ አፍቃሪ ነው፡፡ ስሜቱ እንደ ብይ የምትንከባለልበት የንፋስ ባሪያ ነው፡፡ ስለ ገጣሚ አፍቃሪነት ሳስብ የከበደች ተክለአብ ግጥም ትዝ አለኝ፡፡

“ጣት ወዳጁን ሲያጣ” ከሚለው ግጥሟ ጥቂት ስንኞችን እወስዳለሁ፡፡ ከበደች ጥልቅ ሃሳብ፣ ውብ ስንኞች በእርጋታ የሚያፈስስ ብዕር ያላት የግጥም እመቤት ናት፡፡ “ካንጀት ከወደደ ካደነቀ ዓለምን እንደ ቀሳሚ ንብ ባበባ እንዳረፈ ከቀሰመ ፍቅርን፣ ይጽፍ ነበር ብዕር የውበት ውዳሴን የተፈጥሮ ትንግርት የዓለም ቡራኬን የዓለም ሱታፌን፡፡ በጥዑመ ቃሉ ጣዕም እየሰጠ በኪነት ልሳኑ ልብ እየመሰጠ ወዶ እያስወደደ ቤተ ፍቅር አንፆ ጥቅረ - ላህይ ገልሶ የራሱን አፍቅሮት ባንባቢው አሥርፆ የውበት ዐይኑንም ለሌላው ለግሶ፣ እዩት ይል ነበር ያልታየውን ዳሶ እንዲህ እንዳሁኑ ብዕር እንደዋዛ ተዘንግቶ ሳይቀር ጣት ወዳጁን አጥቶ መሬት ሳይቆረቁር የብሶት ተካፋይ ንፁህ ብራና አጥቶ---” ከበደች የጥበብ ፍቅሯን የምትገልጥበትን ብዕር በሶማሊያ እሥር ቤት ተነጥቃ የፃፈችው ነው፤ የልብዋ ንዝረት፣ የውስጧ ስብራት ድምጽም በስንኞችዋ ይደመጣል፡፡ ኋላ ላይ በአሜሪካ ታዋቂ ገጣሚ የሆነው፣ ነገር ግን በአሥራ ሦስት ዓመቱ በኒውዮርክ ጐዳና የወደቀው ግሪጐሪ ኮርሶ፤ ከልጅነቱ ሶስቱን ዓመታት በእሥር ቤት ስላሳለፈ ፍቅሩ ለሰው ልጆች ይመስላል፡፡ ታዲያ የልቡ ክንፎች ለሰው ልጆች እየተርገበገቡ በሚከንፍበት የዓለም አድማስ ላይ ከሌሎች ነገሮች ጋር በፍቅር የወደቁ ገጣሚያንን ለመተቸት ይቃጣዋል፡፡

ከሰው ልጆች ይልቅ ከዛፍና ሌሎች ግኡዝ ነገሮች ጋር ፍቅር የወደቁ ገጣሚያን ለርሱ ፌዘኞች ናቸው፡፡ ግሪጐሪስ ኮርሶ፤ ግጥም የሰው ልጅ ፀሐይ ናት ባይ ነው፡፡ “The poets cries for a change in society, not for himself but for all peoples” ገጣሚ የሰው ልጆች ጠበቃ፣ የለውጥ ሃዋርያ ነው የሚል ይመስላል፡፡ ገብረክርስቶስ ደስታ ደግሞ በሀገር ፍቅር የተለከፈ ነው፡፡ ለእርሱ ግጥም ማለት የሀገር ሙዚቃ ነፍስና ውበት ነው፡፡ ገብሬ ሲጽፍ ትንሹን ያገዝፋል፣ ረቂቁን ያጎላል፡፡ ጠላውን፣ ሽሮውን ፣ በርበሬውን ፣ ጮማውን፣ ጠጁን ሲተርክ--- ሀገርን ለማስታወስ፣ ትዝታውን ለማቅለም አስቦ ነው፡፡ ስለ ፆታ ፍቅርም ይጽፋል፡፡ ግን እንደሀገር እየነደደ አይደለም፡፡ ለነገሩ ፍቅርስ ያለሀገር ምን ዋጋ አለው? እሣት ያለ ምድጃ ማለት አይደል! “ወጡ ቀለም ሆኖ እንጀራው ብራና ይድረሰኝ ደብዳቤ ተርቤያለሁና ይሽተተኝ ቁሌቱ የቅመም ሽንኩርቱ በርበሬው ይበተን ንፋስ ይዞት ይምጣ በዝናብ ላኩልን ጠላውን ልጠጣ ልስከር በፊልተሩ! ይረሳኝ ችግሩ…” የገብረክርስቶስ ግጥሞች ከሀገር ናፍቆት የተወለዱ ናቸው፡፡ የሀሣቡ ሀውልት ዞሮ ዞሮ ሀገር ላይ ነው፡፡ ልቡ የተሠረቀው በሀበሻዊ ባህሎች ነው - በምግቡ፣ መጠጡና የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ጭምር፡፡

“እንደገና” የሚለው ግጥሙ እንዲህ ይላል: “ይናፍቀኝ ነበር … ዞሮ ዞሮ ከቤት ይላል የኛ ተረት፡፡ አቧራው ፀሐዩ ይናፍቀኝ ነበር፤ አፈሩ ጠጠሩ ይናፍቀኝ ነበር፡፡ የመንደር ጭስ ማታ … ይናፍቀኝ ነበር የሣር ቤት ጥቀርሻው መደቡ ምሰሶው፣ ማገሩ ግድግዳው፣ አጥሩና ጥሻው፡፡ የፈራረሰ ካብ … ቀጭን ጠባብ መንገድ በመንደር የሚሮጥ ቅጠል የሸፈነው፣ ሣር ያለባበሰው፤ እነዚህ፤ እነዚህ፤ ይናፍቁኝ ነበር፡፡ የተቆላ ቡና፤ የሚወቀጥ ቡና፤ የጐረቤት ሱፍ አልቦ ሁለተኛ፤ የተረጨ ቆሎ የሚያርቅ መጋኛ፤ የሚጨሰው ዕጣን … እንጀራ በመሶብ የፈሰሰበት ያገልግል እንጀራ የሚቧጠጥ ፍትፍት፣ የክክ ወጥ የሽሮ፣ የሥጋ የዶሮ፡፡ ሀገርን የሠራባቸው ጡቦች ይገርማሉ፡፡ ሳር ቤቱ ከነጥቀርሻው መደቡና ምሠሦው ፣ የድንጋዩ ካብ፤ የተቆላው ቡና፣ የአገልግሉ እንጀራ --- እነዚህ የተዳፈኑ ትዝታን የመፈንቀል አቅማቸው ብርቱ ነው፡፡ የነፍስን ምሠሦ ይነቀንቃል፡፡ እውነትም ቫዛር ሚለር እንዳለችው፤ ገብሬ ባንድ ነገር በፍቅር ወድቋል - በሀገር! ይሄን ሁሉ ያመጣነው ግጥም ያለ ፍቅር የሚፃፍ ጥበብ አይደለም ለማለት ነው፡፡

መጀመሪያ ስሜታችን መግለብለብ፣እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል መንደድ፣ ከዚያም እንደ ግራር ከሠል ትርክክ ያለ ፍም መፍጠር አለበት፡፡ እንደ ገብረክርስቶስ ከሀገር ጋር ፍቅር የወደቅ፣ እንደ ቬሊ ከወፍ ጋር የሚበርሩ ያሉትን ያህል፣ ከተፈጥሮ ጋር የተሣሠሩ፣ ከባህርና ሀይቅ ጋር በልባቸው ተቃቅፈው የሚኖሩና የሚፅፉ ሞልተዋል፡፡ የተቃራኒ ፆታ ፍቅር እንደ ቤንዚን እሣት ቦግ እያለ ድንገት የሚጠፋባቸውም፣ የተሰጥዖው ሃይል ካላቸው አንዱ የፍቅር ወደብ ላይ አርፈው፣ ግጥም ማፍሰሳቸው አይቀርም፡፡ ግጥም በውስጡ ፍቅር ያቀፈ እንቁላል ነው፡፡ ፍቅር ማለት ጠንካራ ንፋስ፣ ጣፋጭ ዜማ፣ የማይቋረጥ ሣቅ … የሚያፍን ደስታ ሣይሆን ይቀራል? እንደየ ትርጉሙና እንደየዐውዱ ---- ማን ያውቃል? የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ማን ያውቃል? በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ የተከበበ የሰው ልጅ ከመልሱ ይልቅ ጥያቄው ላይ ተንጠልጥሎ እየተወዛወዘ አይደል የሚኖር? …

Published in ጥበብ

በአስፋው መኮንን የተፃፈውና አስቂኝ፣ ቀልዶችና ቁምነገሮች የተካተቱበት መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በአገራችን በቃል የሚነገሩ በርካታ አዝናኝና ቁም ነገር አስተማሪ ቀልዶች ቢኖሩም ብዙዎቹ በመፃህፍት ተፅፈው ስለማይቀመጡ የሚረሱና የሚደበዝዙ ይሆናሉ፤ ስለዚህም መመዝገብ አለባቸው ብሏል አዘጋጁ፡፡ በ158 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

Saturday, 11 January 2014 12:11

“አለሁ ---- አልሞትኩም”

ረቡዕ ማታ በዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ላይ “አርቲስት ፈለቀ አበበ አረፈ” በሚል በስህተት በተነበበ ዜና እረፍት

ምክንያት አርቲስቱ፣ ቤተሰቦቹ፣ጓደኞቹና አድናቂዎቹ እስከ ሀሙስ እለት ተረብሸው ነበር፡፡ በርካቶች ዜናውን ባለማመን

ነገሩን ለማረጋገጥ አርቲስት ፈለቀ አበበ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ሲደውሉ ማምሸታቸውንና መዋላቸውን አርቲስቱ

ገልጿል፡፡ በስህተት ከተሰራጨው ዜና እረፍት በኋላ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ ስለተፈጠረበት ስሜትና አጠቃላይ

ሁኔታ ከጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር  አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

የሞትህን ዜና በምን ሁኔታ ሰማህ?
ረቡዕ ወደ ማታ ቤት ቁጭ ብዬ እየሰራሁ ሳለሁ፣ ባልተለመደ መልኩ ስልኮች በተከታታይ መደወል ጀመሩ፡፡ አስደንጋጭ

ነበር፡፡ ብቻ የሆነ ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡
ዜና እረፍትህን ሰምተው መደወላቸውን እንዴት አወቅህ?
አንዱን ጓደኛዬን በድፍረት ጠየቅሁት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፍጥነት በተከታታይ ሲደወል ለእኔ የተለመደ አይደለም፡፡

“ምንድን ነው ነገሩ? አካባቢው ላይ የተፈጠረ ነገር አለ እንዴ? ብዙ ሰው በተከታታይ እየደወለልኝ ነው” ብዬ

ስጠይቅ፤“አይ ሞተሀል ተብሎ በሬዲዮ ተነግሮ ነው” ሲለኝ ክው ብዬ ደነገጥኩኝ፡፡ ደግሞ ያስታውቃል፤ አንዳንዶቹ ልክ

ስልኬን አንስቼ “ሀሎ” ስላቸው ቶሎ ይዘጉታል። ብቻ መኖሬን ነው ማወቅ የሚፈልጉት፡፡ እንደዚህ ካደረጉት ውስጥ

ጓደኛዬ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ አንዱ ነው፡፡ አማኑኤል መሀሪ እንዲሁም ቤተሰቦቼም ድምፄን ሰምተው ብቻ ስልክ

ዘግተዋል፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤተሰቦቼም ይደወል ነበር፡፡ ከውጭ አገር ሁሉ የስልክ ጋጋታው ሊያቆም አልቻለም፡፡
ሲደውሉልህ የሰዎች ስሜት እንዴት ነበር?
በጣም ህመም የሆነብኝ እሱ ነው፤ በጣም የሚያለቅሱና ኡኡ የሚሉ ነበሩ (ለቅሶ…) በጣም ያሳዝናሉ፤ እኔም አብሬያቸው

አለቅስ ነበር (ረጅም ለቅሶ)…
ሬዲዮ ጣቢያው ጋ አልደወልክም ?
ትንሽ ቆይቶ--- ከዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ደወሉልኝ፡፡ “በስህተት ነው ፈለቀ አበበ ሞተ ያልነው፤ የሞተው ግን አርቲስት

ፈለቀ ጣሴ ነው፤ አንተ በጣም ታዋቂ ስለሆንክ ፈለቀ ስንል አፋችን ላይ የገባው የአንተ አባት ስም ነው” አሉኝ፡፡ ነገር

ግን ሰው በጣም ያለቅሳል፤ በጣም ያሳዝናል፡፡
ይቅርታ ጠየቁ ወይስ----
እኔን በግሌ ይቅርታ ጠይቀውኛል፡፡ አድማጮችን ይቅርታ ይጠይቁ አይጠይቁ አላውቅሁም፡፡ ነገር ግን በነገሩ በጣም

አዝኛለሁ፡፡ ማንም ከሞት አይቀርም ግን እንዲህ ቀላል የሚመስሉ ስህተቶች ከባድ ጉዳት ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ በድንጋጤ

ልቡ ቀጥ የሚል ቤተሰብ፤ ወዳጅ ዘመድ ይኖራል፤ መሞት አለ --- ስንት ነገር አለ፡፡
በዚህ ድንገተኛ ክስተት ምን ተረዳህ?
እንዴ… በጣም በጣም ተገረምኩ እንጂ! ይህን ያህል ሰው ይወደኛል ወይ ነው ያልኩት፡፡ በጣም ደነቀኝ፡፡
ዜና እረፍትህ ከተነገረ ጀምሮ ምን ያህል ሰው ደውሎልሀል?
ከ500 በላይ ስልክ ተደውሏል፤ በግምት ወደ 600 ሳይጠጋ አይቀርም፡፡
ከዚህ በስህተት ከተሰራጨ ዜና እረፍት መልካም አጋጣሚ የምትለው ነገር አለ?
 እንደውም በጣም እድለኛ ነኝ አልኩኝ፡፡ በቁሜ ይህን ያህል ሰው እንደሚወደኝ ማየት ችያለሁ፡፡ ግርምቴ እስካሁን

አልቆመም፡፡
ከዚህ በፊት ያልሞተ ሰው ሞተ ተብሎ የተነገረበትን አጋጣሚ ታውቅ ነበር?
ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹን የሰማኋቸው ዛሬ (ሐሙስ ማለቱ ነው) ነው፡፡ ለምሳሌ ጥላሁን ጉግሳ የሚባል

ሌላ አርቲስት ሲሞት፣ በስም መመሳሰል በህይወት ያለው ጥላሁን የመሰለበት አጋጣሚ  ትዝ ይለኛል፡፡ ሌላ ጊዜ

በቴሌቪዥን አርቲስት ሲራክ ታደሰ ሲሞት፣ የአርቲስት አለሙ ገ/አብን ፎቶ ማሳየታቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ያጋጥማል ነገር

ግን ሰው የሚያለቅሰው… መንገድ ላይ ሲያዩኝ የሚሆኑት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል፡፡
አሁን እንዴት ነው ስልኩ ቀነሰ? አንተስ ተረጋጋህ?
ያው እየተረጋጋሁ ነው፡፡ አንድ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፡፡ የህይወት እስትንፋስን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡

የምንኖረውም እግዚአብሔር የፈቀደልንን ያህል ነው፡፡ ማናችንም ከተቆረጠልን ቀን አናልፍም፡፡ ግን እዛው ቤቴ ውስጥ

ቁጭ ብዬ፤ “አሁንስ ለመኖሬ ምን ማረጋገጫ አለ” ብዬ መፈላሰፍ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ “ኦኬ በቃ አለሁ ማለት ነው…”

ማለት ጀመርኩኝ፡፡ አንዳንዶች እኮ “እርግጠኛ ነህ ፈለቀ ነህ የምታናግረኝ” ብለውኛል፡፡ ስለሞት ብዙ ነገር ነው

ያሰብኩት፡፡ ከምንወለድበት ቀን ይልቅ የሞት ቀን ይሻላል የሚለውንም አሰብኩኝ፡፡ እንደውም የአዲስ አድማስ ባለቤትና

መሥራች አሰፋ ጎሳዬ  ሲሞት አዲስ አድማስ ግቢ ሆኜ  የፃፍኩት ግጥም ነበር፡፡
ትዝ ይልሃል ---ምን የሚል ነው?
ቢርቅም አይጠፋም ይልቃል ከሽቶ
በሰው ልብ ይኖራል ከመቃብር ሸሽቶ፡፡   የሚል ነበር፡፡ አየሽ --- በዚህ አጋጣሚ ያየሁት የሰው ፍቅር፤ የበለጠ

የምሰራበትና መልካም ያልሆኑ ነገሮች ካሉኝም ለማሻሻልና ጥሩ ለማድረግ የምተጋበት ነገር ተፈጥሯል፡፡ የበለጠ መልካም

ሆኜ እንዳልፍ የሚያደርግ ጥሪም ነው፡፡ ደጋግሜ የምነግርሽ… ሰው ለእኔ የሆነው ነገር ገርሞኛል… እንዲህ ነው ወይ

የምትወዱኝ ነው ያልኩት፡፡
አንዳንዴ ሞት የሚያናድደው ከሞትክ በኋላ ሰው ለአንተ ያለውን ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ማየት ባለመቻሉ  ነው አይደለ?
እውነት ነው፡፡ እህቴም እንደዚህ ነው ያለችው፡፡ እህቴ ምስጢር ደምሴ ስትነግረኝ፤ መንግስቱ የተባለ ደራሲ “ሞቻለሁ”

ብሎ ቀጨኔ መድሀኒዓለም ሰው ተሰብስቦ ዋይ ዋይ ሲል፣ እሱ ተደብቆ ማን ቀብር እንደመጣና እንዳልመጣ፣ ማን ከልቡ

እንዳዘነና እንዳላዘነ ይመለከት ነበር፡፡ ይሄ ይገርማል። እሱ አስቦበትና ተዘጋጅቶ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው

ሌሎች በፈጠሩት ስህተት፣ የህዝቡን ፍቅር አይቼበታለሁ፡፡ እኔ ልሳቀቅ፣ እኔ ልደንግጥላቸው (ለቅሶ…)
የሞትህ ዜና ሲነገር ስራ ላይ እንደነበርክ ነግረኸኛል፡፡ ምን እየሰራህ ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱሱን ዮሐንስ ራዕይን በትረካ መልክ ለማቅረብ  እየተረጐምኩ ነበር፡፡ በመተርጐም ላይ ሳለሁ ነው ስልኩ

በተደጋጋሚ መደወል የጀመረው። ሀሙስ ጠዋት ከቤት ስወጣ ገርጂ አካባቢ “ዊሽ ስቱዲዮ” የሚባል ፎቶ ቤት አለ፤ ፎቶ

ሲያነሱኝ አየሁ፡፡
ለምን እንደሆነ አልጠየቅሃቸውም?
አልጠየቅኳቸውም፡፡ እነሱ ማታ ሞቷል መባሉን ሰምተው አድረው ኖሮ፣ ፎቶ ካነሱኝ በኋላ “Fele this morning”

ብለው ፌስ ቡክ ላይ ፖስት አድርገውኝ አየሁ፡፡ ሌላም ሰው “Still alive” ብሎ ፖስት አድርጓል --- እና የሚገርም

ነው፡፡
እና አሁን ምን ትላለህ?
አለሁ አልሞትኩም፤ ፈጣሪ እስከፈቀደልኝ እኖራለሁ፡፡ የሞተውን ወዳጃችንን ፈለቀ ጣሴንም ነፍሱን ይማርልን፡፡ ማርክ

ትዌይን  ያለውን እናስታውስና እንጨርስ፤ “ሞቴን በተመለከተ የወጣው ዘገባ ያለቅጥ  ተጋንኗል” እናም አልሞትኩም።

በዚህ አጋጣሚ አንዱ ጓደኛዬ መኪና እየነዳ “ፈለቀ አበበ ሞተ” ሲባል በድንጋጤ መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት

ከመስመር ወጥቶ ሊጋጭ ለትንሽ ነው የተረፈው፡፡ እህቴም ቀድማ አልሰማችም እንጂ በልብ ድካም ትሞት ነበር፡፡

ስለዚህ ጋዜጠኝነት ትልቅና የተከበረ ሞያ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊያዝና ሊከበር ይገባል እንጂ በቸልታ የሚሰራበት

አለመሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እኔም እወዳችኋለሁ፤ ስለተጨነቃችሁ

ስላዘናችሁልኝ አከብራችኋለሁ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡  

Published in ጥበብ
Saturday, 11 January 2014 12:09

የመሳሳም ጥበብ

የኔ ውድ…

ባልሽ ጥሎሽ ስለሄደ አለም ጨለመብሽ አይደል?... የምታደርጊው ግራ ቢገባሽ፣ ነጋ ጠባ ተንሰቅስቀሽ ታለቅሻለሽ አይደል?... የኔ ምስኪን… አልቅሰሽ አልወጣልሽ ቢል፣ ዙሪያው ገደል ቢሆንብሽ፣ መላ ቅጡ ቢጠፋሽ… እኔን አሮጊቷን አክስትሽን “ምን ይሻለኛልይሆን?” ብለሽ፣ ምክር እንድለግስሽ ጠየቅሽኝ፡፡ አይ አንቺ!... ‘አክስቴ በፍቅር ጉዳይ ላይ ጥልቅ እውቀት አላት’ ብለሽ በማሰብ ነው አይደል፣ ምክሬን ፍለጋ ወደ እኔ የላክሽብኝ?... እውነቴን ልንገርሽ… የምታስቢውን ያህል ሁነኛ መፍትሄ ልሰጥሽ እችል እንደሆን አላውቅም፡፡ እርግጥ ሌሎችን የማፍቀርን ወይም ራስን ተፈቃሪ የማድረግን ጥበብ ጭራሽ የማላውቅ ፍጹም መሃይም ሰው አይደለሁም፡፡ አየሽ የኔ ውድ… አንቺ በተወሰነ ደረጃ ይጎድልሻል ብዪ የማስበው፣ ራስን ተፈቃሪ የማድረግ ጥበብ ነው፡፡ ልክድሽ አልፈልግም፣ እኔም በአንቺ እድሜ እንዲህ ነበርኩ፡፡ በአጠቃላይ አንቺ ማለት ለባለቤትሽ ትኩረት፣ ፍቅር፣ መሳሳምና መደባበስ እንደሆንሽ ነግረሽኛል፡፡ የችግሩ ዋነኛው ምንጭ ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደሚመስለኝ ባልሽን በወጣ በገባ ቁጥር ትስሚዋለሽ፡፡ የኔ ውድ፣ እኛ እኮ… በአለም ላይ አቻ የሌለውን ታላቅ ሃይል ነው በእጆቻችን የያዝነው፡፡ ይህ ሃይል ፍቅር ይባላል፡፡ ወንድ በአካላዊ ጥንካሬ የታደለ በመሆኑ፣ ሃይል መጠቀምንም ያዘወትራል። ሴት ደግሞ በተራዋ ውበትን ታድላለች፡፡ አቅፋ እየደባበሰች ነው የምታሸንፈው፡፡

ለእኛ ለሴቶች፣ ውበታችን በዋዛ የማይረታና የማይበገር መሳሪያችን ነው፡፡ ታዲያ ግን አጠቃቀሙን ካላወቅንበት ዋጋ የለውም፡፡ እኛ የአለሙ ሁሉ እመቤቶች መሆናችንን በሚገባ መረዳት አለብሽ!!... ከዘፍጥረት አንስቶ ያለውን የፍቅርን ታሪክ መናገር፣ የራሱን የሰው ልጅን ታሪክ መተረክ ማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከፍቅር ነው፡፡ ጥበባትም ሆኑ ታላላቅ ሁነቶች፣ ጦርነቶችም ሆኑ የነገስታት ውድቀቶች ሁሉም ፍቅር ነው መነሻቸው፡፡ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪኮችን ፈትሺ፣ ደሊላንና ዮዲትን ታገኛቸዋለሽ፡፡ በተረቶች ውስጥ እነ ሄለንን፣ በታሪክ ድርሳናት ደግሞ እነ ክሊዮፓትራን፣ ኸረ ስንቶችን!… ብዙ ብዙ ተጠቃሽ ሴቶችን እናገኛለን። እኛ ሴቶች ታላላቆችን አስገብረናል፣ በሃያላን ላይም ነግሰናል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ እንደ ንጉሳውያን ሁሉ፣ ተለሳልሶ የማስገበርን ጥበብ መጠቀም ግድ ይለናል። የኔ ውድ… ፍቅር የሚገነባው፣ ጎልተው ከማይታዩ ጥቃቅን ስሜቶች ነው፡፡ ፍቅር የሞትን ያህል ብርታት እንዳለው እናውቃለን፡፡

ያም ሆኖ ግን፣ እንደ ሸክላ በቀላሉ ተሰባሪ ነው፡፡ ተሰብሮ ለመድቀቅ ትንሽ ነገር ነው የሚበቃው፡፡ ፍቅር በትንሽ ነገር ሲሰበር፣ አይሆኑ ሆነን ልንነካክት እንገደዳለን፡፡ የታጠቅነው ሃይል ተሟጦ ያልቃል፡፡ ዳግም ነፍስ በማንዘራበት፣ አገግመን በማንነሳበት በአጉል ቀውስ ውስጥ እንወድቃለን፡፡ እኛ ሴቶች ራሳችንን በሌሎች ዘንድ ተፈቃሪ የማድረግ ታላቅ ሃይል ቢኖረንም፣ አንዲት ትንሽዪ ነገር ትጎድለናለች፡፡ ይህም ሌሎችን መንከባከብ የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች በተመለከተ ግንዛቤ አለመያዛችን ነው፡፡ ወንዶችን አጥብቀን ስንናፍቅና እኛነታችንን ሙሉ ለሙሉ ለእነሱ ስንሰጥ፣ ተሰባሪ መሆናችንን እንዘነጋለን፡፡ ይሄኔ ልቡን ገዝተነዋል ብለን የምናስበው ወንድ፣ የራሱ አለቃ ሆኖ ይቀራል፡፡ ለአድናቆት ብለን የምንሰነዝራቸውን ቃላት ከሞኝነት መቁጠር ይጀምራል፡፡ አደራሽን የኔ ውድ… ራሳችንን ከጥቃት የምንከላከልበት ጥሩር በወጉ ያልተሰራ መሆኑን ልብ በይ! እውነተኛው ሃይላችን የሚገለጠው መቼ እንደሆነ ታውቂያለሽ?... ስንስማቸውና ስንስማቸው ብቻ!... መሳማችንን እንዴት መጀመርና መጨረስ እንዳለብን በተረዳን ጊዜ፣ ያኔ የንግስትነትን ክብር እንቀዳጃለን፡፡ መሳሳምን እንደ መቅድም ውሰጂው፡፡ ግን እንደሚያስደስት ማራኪ መቅድም፡፡

ከዋናው ነገር የበለጠ ማራኪ የሆነ መቅድም፡፡ አለ አይደል… ሁሌም ደጋግመሽ ደጋግመሽ ብታነቢው እንደማትሰለችው መቅድም አስቢው፡፡ አንድ ሰው ምንም ያህል ቢጥመው፣ አንድን ሙሉ መጽሃፍ ሁሌም ደጋግሞ ሊያነበው አይችልም፡፡ የከናፍርት ግንኙነት ፍጹም ደስታንና ሰማያዊ ስሜትን ይጎናጸፉበት ዘንድ ለሰው ልጆች የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ የደስታ የላይኛው ጣራ ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡ አንድ ሰው በመሳሳም ብቻ፣ ከሚወደው ሰው ጋር የነፍስ ጥምረት የፈጠረ ያህል ጥልቅ ስሜት ሊሰማው የሚችልበት ጊዜ ያጋጥመዋል። ይህ ደግሞ ሁላችንም የምናልመው ነገር ነው - የልቦች ውህደት መፍጠር! “አስፈሪ ደስታ ነው መሳም፣ የሚወዱትን ማሻሸት ፍቅር ነፍሶችን ለማዋሃድ፣ የሚፈጽመው ከንቱ ኩሸት…” የሚሉት የፈረንሳዊው ባለቅኔ የሱሊ ፕሩዶም ስንኞች ትዝ ይሉሻል?... ለአፍታ ተቃቅፎ መተሻሸትና መሳሳም ብቻ፣ ጥንዶችን በአንድ የተዋሃዱ ያህል ጥልቅ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ አለሙን ሁሉ ቢገዙ፣ ሃብትን ሁሉ ቢይዙ የሚወዱትን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳም ሲጠጉ እንደሚፈጠረው የከንፈር መንቀጥቀጥ፣ ትንፋሽ ለትንፋሽ እንደመግጠም፣ ከንፈር ለከንፈር ተጎራርሶ በጸጥታ ተቃቅፎ እንደመቆየት ልብን የሚያጠፋና በደስታ የሚያጠምቅ ስሜት የሚያጎናጽፍ ነገር የለም፡፡

ስለዚህ የኔ ውድ… መሳም ወንዶችን የምናሸንፍበት ጠንካራው መሳሪያችን እንደሆነ ልብ በይ!... አሳሳምሽ አሰልቺ እንዳይሆን ግን መጠንቀቅ አለብሽ፡፡ የመሳሳም ዋጋና የሚፈጥረው የእርካታ ስሜት አንጻራዊ እንደሆነ አትዘንጊ፡፡ በመሳሳም ውስጥ የሚፈጠረው ስሜት እንደ ሁኔታዎች፣ እንደነበረን የቀድሞ ግምት ወይም እንደምንጠብቀው ነገርና እንደ ውስጣችን ፍንጠዛ በየጊዜው የሚቀያየር ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ… ሌላኛው ገጣሚ ፍራንኮይስ ኮፔ የጻፋት አንዲት ስኝን አለች… የሁላችንን ልብ በስሜት የምታሞቅ ስንኝ… ገጣሚው በአንድ የክረምት ምሽት ቤቱ ውስጥ ቁጭ ብሎ ፍቅረኛውን በጉጉት ስለሚጠብቅ አንድ የናፈቀ አፍቃሪ ይነግረናል፡፡ በውስጡ ስለተፈጠረው ጭንቀት፣ ትዕግስት አጥቶ ስለመቅበጥበጡ፣ ‘ሳላያት ላድር ነው’ ብሎ በፍርሃት ስለመራዱ ይተርክልናል። በስተመጨረሻም ያቺ በጉጉት ስትጠበቅ የነበረች ተፈቃሪ ድንገት ከተፍ ማለቷን ይገልጽልናል፡፡ የሚወዳት ልጅ ትንፋሷ እየተቆራረጠ፣ በክረምቱ ምሽት የንፋስ ሽውታ ውስጥ በጥድፊያ ስትመጣ የተመለከተውና አቅፎ መሳም የጀመረው አፍቃሪ፣ ድንገት እንዲህ ብሎ በማጋነን ተናገረ ይለናል ገጣሚው ኮፔ… “ኤጭ!... የከናፍርቷ ጣዕም፣ በአይነ እርግቧ ውስጥ ጠፋ!...” እጅግ ድንቅ ስሜት፣ ውብ እይታ፣ ፍጹም የሆነ እውነታ የያዘ… ደስ የሚል ገለጻ ነው አይደል?... የሚወዱትን ሰው በድብቅ ለማግኘት የተጣደፉ፣ በፍቅር አቅላቸውን ስተው በወንዶች ክንድ ላይ የወደቁ ሴቶች ሁሉ፣ በአይነ እርግብ ውስጥ ተከልለው ያደረጓቸውን ጣፋጭ መሳሳሞች ጠንቅቀው አይረሷቸውም፡፡

ከዘመናት በኋላ ተመልሰው ባስታወሷቸው ቁጥርም በስሜት ይቃትታሉ፡፡ የሚስሟቸው ወንዶችስ?... እስኪ የዚህን ገጣሚ አፍቃሪ ገጸባህሪ ታሪክ ልብ ብለሽ አስቢው የኔ ውድ… ወጣቷ በሚያንቀጠቅጥ ውርጭ ውስጥ በፍጥነት እየተራመደች ወደ አፍቃሪዋ ትመጣለች… በቀዝቃዛ ትንፋሿ እንፋሎት የረጠበ፣ ጤዛ የቋጠረ አይነ እርግብ ተከናንባለች… መጣች ቀረች እያለ በር በሩን እያየ በጭንቀት ሲባዝን ያመሸው አፍቃሪ፣ ዱካዋን ሲሰማ በደስታ ይፈነጥዛል፡፡ ጨለማውን ሰንጥቃ የመጣችለትን ፍቅሩን ደጃፍ ድረስ ወጥቶ እየተፍለቀለቀ ይቀበላታል፡፡ በጥድፊያ በእቅፉ ውስጥ አስገብቶ በክንዶቹ ይጨምቃታል፡፡ እቅፍ አድርጎ እንደያዛት ጎምጅቶ ወደ ከናፍሯ ይሄዳል፡፡ ቀዝቃዛ ትንፋሿን በትኩስ ከናፍሩ ለብ ያደርገዋል። በዚህ መሃል… የአይነ እርግቧ ጤዛ ጺሞቹን ሲያረጥባቸው፣ አፍንጫ ቆርጦ የሚጥል ጠረን ከእሷ ገላ ላይ ተንኖ ድንገት ሲተነፍገው… ይሄ ሰው ምን ይሰማዋል?... ጓጉቶ የጠበቃትን የሚወዳትን ሴት ከናፍርት በወጉ ማጣጣም ይችላል?... በፍጹም!... የከናፍርቷን ጣዕም አይነ እርግቧ ይነጥቀዋል፡፡ ከቀዝቃዛ ትንፋሿ ይልቅ፣ አይነ እርግቧ የታጠበበት ኬሚካል መጥፎ ጠረን ጎልቶ ይሰማዋል፡፡ ይሄኔ ነው … “ኤጭ!... የከናፍርቷ ጣዕም፣ በአይነ እርግቧ ውስጥ ጠፋ!...” ያለው፡፡ ምን ማለቴ መሰለሽ… እንዲህ ያለው ፍቅር አሰጣጥ የሚኖረው ዋጋ በሁለቱ ተፋቃሪዎች ስምምነትና በውስጣቸው በሚፈጥረው ስሜት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ነገሩን እንዳናበላሸው መጠንቀቅ አለብን፡፡ የኔ ውድ… ቅልጥፍና የጎደለሽ ገልጃጃ ቢጤ መሆንሽን በተደጋጋሚ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ እርግጥ ይህ የአንቺ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች መሳሳም የሚባለውን ትልቅ ነገር፣ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ያለወቅቱ ይከውኑታል፡፡ ይህን በማድረጋቸውም በሚወዷቸው ወንዶች ላይ ያላቸውን የበላይነትና ስልጣን ያጣሉ፡፡

የትዳር አጋራቸው ወይም ፍቅረኛቸው ድካም ቢጤ እንደተሰማውና መንፈሱም አካሉም እረፍት እንደሚሻ እያወቁ፣ በውስጡ ያለውን ስሜት ከማጤን ይልቅ በጉትጎታ ለመደባበስና ፍቅር ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ እንዲስማቸው በመገፋፋትና በመለመን እንዲሁም ያለ ምክንያት በመደባበስ የበለጠ ያደክሙታል፡፡ ከልምዴ በመነሳት የምሰጥሽን ምክር በጥርጣሬ አትመልከቺው፡፡ የመጀመሪያው ነገር ፍቅረኛሽን ሰው በተሰበሰበበት በአደባባይ አትሳሚው፡፡ እንዲህ ያለው መሳሳም ጣዕም የለውም፡፡ ለራስሽ ስሜት ብቻ ተገዝተሽ በአደባባይ ብትስሚው፣ ሀፍረት ሊሰማውና ይቅር የማይሉት ቅያሜ ሊይዝብሽ ይችላል፡፡ ጥቅም የሌላቸው መሰል መሳሳሞች በመካከላችሁ ክፍተት ይፈጥራሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ አንቺም እንዲህ ስታደርጊ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ የሆነ ቀን አስደንጋጭ ነገር እንዳደረግሽ አስታውሳለሁ፡፡ ምናልባት አንቺ ትዝ ላይልሽ ይችላል፡፡ እኔ፣ አንቺና ባለቤትሽ አንድ ክፍል ውስጥ ነበርን፡፡ ከባለቤትሽ ጭኖች ላይ ቁጭ ብለሽ አሻግረሽ በሩቁ ከኔ ጋር ስታወሪ፣ እሱ እንደምንም እየተንጠራራ ከንፈርሽንና አንገት ስርሽን ይስም ነበር፡፡ በወሬያችን ተጠምደሽ ስለነበር፣ ሲስምሽ ከጉዳይ አልጣፍሽውም፡፡ ችላ ብለሽው ከኔ ጋር ስታወሪ ቆይተሽ፣ በመካከል ጥግ ላይ ወደነበረው ምድጃ ታያለሽ፡፡ አጥፍቼዋለሁ ያልሽው እሳት እንደገና ተያይዞ እየተንቀለቀለ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል... “እሳቱ!... እሳቱ!” እያልሽ መጮህ ጀመርሽ፡፡ ባልሽ ጩኸትሽን ሲሰማ በድንጋጤ ክው አለ፡፡

በፍጥነት አፈፍ ብሎ በመነሳትም በሩጫ ወደ ምድጃው ሄዶ እሳቱን ለማጥፋት መጣደፍ ያዘ፡፡ እንደምንም ከወላፈኑ ጋር እየታገለ የፍም ጉማጆችን እየመዘዘ ማውጣት ጀመረ፡፡ አንቺ ታዲያ፣ በዚህ ጊዜ ባልሽን ተከትለሽው ወደ ምድጃው ሄደሽ ከንፈርሽን አሞጥሙጠሽ፣ “ሳመኝ!...” ስትይ እየተሞላቀቅሽ ጠየቅሽው፡፡ ባልሽ ከምድጃው በመዘዘው የፍም ጉማጅ እጆቹ እየተቃጠሉ እንደምንም ዘወር ብሎ አየሽ፡፡ አንቺ መች በዚህ በቃሽ!... በእሳት የሚለበለበውን ያንን ምስኪን ባልሽን፣ ጠምዝዘሽ ይዘሽ ልቡ እስኪጠፋ ሳምሽው፡፡ ይሄኔ በእጁ ይዞት የነበረውን ጉማጅ ጣለና በንዴትና በተስፋ መቁረጥ ተነፈሰ፡፡ በቁጣ ገንፍለሽ መሳምሽን አቋረጥሽና ባልሽን ገፋ አደረግሽው፡፡ ከዚያም… “አሳሳምህ እንዴት ነው የሚያስጠላው ባክህ!?” አልሽው በመጸየፍ እያየሽው፡፡ የኔ ውድ… እውነቴን ነው የምልሽ… በእንደዚህ አይነት ነገሮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ!... ልብ ባንለው እንጂ፣ አብዛኛዎቹ ሴቶች ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ለፍቅር ልፊያና ኩሸት የመምረጥ እንዲህ ያለ የቂል አመል አለብን። ፍቅረኛችን ወይም የትዳር አጋራችን በጥም ተቃጥሎ አንድ ብርጭቆ ውሃ በሚፈልግበት፣ ጫማውን ለማጥለቅ ባጎነበሰበት፣ ከረባቱን ለማሰር በሚጣደፍበት… በአጠቃላይ ምቹ ባልሆነበት አጣዳፊ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ነው፣ ለመሳምና ለመተሻሸት የምንፈልገው፡፡ ይህ ደግሞ የጀመረውን ነገር አቋርጦ ከእኛ ጋር እንዲላፋ ማስገደድ ነው፡፡ እንዲህ ስናደርግ ፊቱ ላይ የመሰላቸትና ምነው በተገላገልኳት የሚል ምሬት የወለደው ስሜት ሲፈጠር እናነባለን፡፡ የምልሽን ነገር ከከንቱ ትችት አትቁጠሪብኝ። የኔ ውድ… ፍቅር ስሱ ነው፡፡ ተራ የሚባል ነገር ፍቅርን ሊረብሸው፣ ተፈቃሪንም ሊያስቀይመው አቅም አለው፡፡

ሁሉም ነገር የሚመሰረተው በፍቅር አሰጣጣችን ላይ እንደሆነ እወቂ። ቦታውን ያልጠበቀ መሳሳም ፍቅርን ክፉኛ ሊጎዳው ይችላል፡፡ “ባሌ በማላውቀው ነገር ነው የራቀኝ፣ ለምን ትቶኝ እንደሄደ ምክንያቱን አላውቀውም!... ምን አስቀይሜው ይሆን ብዪ ባስብ ባስብ መልስ ላገኝ አልቻልኩም” ብለሽኛል፡፡ ምናልባትም ያን ቀን፣ “አሳሳምህ እንዴት ነው የሚያስጠላው ባክህ!?” ብለሽ በተናገርሽው ነገር ተቀይሞ ሊሆን ይችላል። በይ አንግዲህ የኔ ውድ… ምናልባት ባልሽ ተመልሶ የሚመጣ ከሆነ፣ የሰጠሁሽን ምክር ተቀብለሽ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሪ፡፡ አሮጊቷ አክስትሽ - ኮሌቴ፡፡

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 11 January 2014 12:06

የቀን ብዙ

አድረን ልንገናኝ….
ነግቶ ልትመጪልኝ….
ለአንድ ቀን ባጣሁሽ፣
በዚሁ ቀን ብቻ - ብዙ ቀን ናፈኩሽ፡፡

ማዕድኑ ሰው
እግዜር አመዛዝኖ፣
ከአፈሩ ዘግኖ፣
መሬት ላይ በትኖ…
‹‹ሰው ሁን›› ካለው ወዲህ…
መኖር ያልደፈረ…
መሞት ያልጀመረ…
ለአንዱም ያልበቃ፣
በአንዱም ያልነቃ፣
ስንት አለ ጥሬ ዕቃ!?

የሴት ልጅ ነኝ
የሴት ልጅ መባሌ - ቂም አያስይዘኝም፣
ምክንያቱም አባቴ - አላረገዘኝም፡፡
        በገጣሚ ሲሳይታደሰ /ዘ-ለገሐሬ/

Published in የግጥም ጥግ
Page 8 of 14