አንድነትን ለመሰለል ኢህአዴግ ጊዜ የሚያጠፋ አይመስለኝም
ፓርቲው ኢንጂነር ግዛቸውን በመምረጡ አትርፏል ባይ ነኝ…
አንድነት ፓርቲ በቅርቡ መንግሥት ሆኖ እቺን አገር ይመራል…
በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተቀበሉት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፤ ወደ ፖለቲካው የገቡት የመኢአድ ፓርቲ የጂማ አስተባባሪ በመሆን ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም የተመሠረተው ብርሃን ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ፓርቲው ከአንድነት ፓርቲ ጋር ውህደት ከፈጠረም በኋላ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆነው የሰሩት ኢንጂነር ዘለቀ፤ ከፓርቲው አመራሮች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ራሳቸውን ከሃላፊነት አግልለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በቅርቡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ ኢንጂነር ዘለቀን የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ ሹመታቸውን ተከትሎም በአንዳንድ አመራሮች ተቃውሞ እንደተነሳ ሲገለፅ ሰንብቷል፡፡ የኢንጂነር ዘለቀ ምን ይላሉ? አዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲን በአዲሱ ሹመታቸውና በፖለቲካ ህይወታቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

 ጥያቄዬን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በሰሩበት “ብርሃን ለአንድነት ለዲሞክራሲ” ፓርቲ ልጀምርና ፓርቲው መቼ ተቋቋመ? እንዴትስ በምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንትነት ተመረጡ? ብርሃን ለአንድነት ለዴሞክራሲ (ብርሃን) ፓርቲ የተመሰረተው በ2000 ዓ.ም ነው፡፡ ምርጫ ሲካሄድም እንዳልሽው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው መርጠውኛል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ከነበረብኝ የስራ ጫና የተነሳ ሃላፊነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ነገር ግን “መስራት አለብህ” የሚል ጫና ስለመጣ በሃላፊነት መስራት ጀመርኩኝ። በአንድ ፓርቲ ውስጥ ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመመረጥ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ልምድ ያካበተ መሆንን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ እስቲ ስለፖለቲካ ልምድዎ ትንሽ ያጫውቱኝ? ከብርሃን በፊት በመላው አማራ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ውስጥ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ውስጥም ጅማ ውስጥ እሰራ ስለነበረ በፖለቲካው ልምድ ስላለኝ ነው የተመረጥኩት። ምንም እንኳ ሃላፊነቱን በጫና ብቀበልም ብርሃን ብዙ የተማርኩበት ፓርቲ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ከሁለት አመት በፊት በዲአፍሪክ ሆቴል ውህደት መፍጠራችሁ ይታወቃል፡፡ ውህደቱ ያስፈለገው ለምንድን ነው? በፓርቲያችን እና በእኛም አመራሮቹ ፓርቲዎች ተበታትነው መስራታቸው ውጤት አያመጣም የሚል እምነት ስለነበረ፣ ተነሳሽነቱን ወስደን የእንዋሀድ ጥያቄ አቀረብን፡፡ በደብዳቤ ከጠየቅናቸው በርካታ ፓርቲዎች ውስጥ አንድነትና መኢአድ ጥያቄውን ተቀበሉ፡፡

ከዚህ በኋላ የሶስትዮሽ ውይይት ማድረግ ጀመርን፡ በዚህ ሂደት ላይ መኢአድ፤ አንድነት ከመድረክ አባልነቱ ከወጣ እንደሚዋሃድ አስታወቀ፡፡ በወቅቱ የመኢአድ ጥያቄ የውህደትን ፋይዳ የሚቃረን እንደሆነ አመንን፡፡ የተነሳንበት አላማ የተበታተነ ሃይል፣ እውቀት፣ አባል… ይዘን ከምንታገል እውቀታችንን፣ ገንዘባችንንና አባላትን በአንድ አደራጅተን የተሻለ አቅም እንፍጠር የሚል ስለነበር የመኢአድን “አንድነት ከመድረክ ይውጣ” ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ከአንድነት ጋር ውህደቱን ልንፈጽም ችለናል፡፡ ከአንድነት ጋር ውህደት በፈፀማችሁበት ዕለት ፓርቲው አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ባደረገው ምርጫ ከዶ/ር ነጋሶ ጋር ተፎካክረው ነበር፡፡ አሸንፋለሁ የሚል እምነት ነበርዎ? በወቅቱ ሁለቱ ፓርቲዎች ሲዋሀዱ “ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እፈልጋለሁ የሚል ራሱን በእጩነት ያቅርብ፣ በጥቆማ መሆኑ ይቅር” የሚል ነገር ነበር፡፡

እኔ በብርሃን በኩል ራሴን አቀረብኩኝ፡፡ በእርግጥ ከልምድም ከምንም አኳያ ፕሬዚዳንት ሆኜ ፓርቲውን ለመምራት አቅሙ አልነበረኝም፡፡ ታዲያ ለምን በውድድሩ ተሳተፉ? ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ነው የተወዳደርኩት፡፡ በወቅቱ ሰዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ ባይችሉም እንኳን በዚያ ውድድር መውደቅ ማለት ራሱ ማሸነፍ እንደሆነ ለማሳየት ነበር የተወዳደርኩት፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው በዶ/ር ነጋሶ ከተሸነፉ በኋላ በፓርቲው ውስጥ የተሰጥዎ ሃላፊነትዎት ምን ነበር? የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ በዚህም ሃላፊነት ከአንድ አመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሃላፊነት በተጨማሪ በፓርቲው ውስጥ አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን አምጥቻለሁ፡፡ ለምሳሌ? በተለይ በአንድነት አባላት ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሰርቼአለሁ፡፡ ለምሳሌ ፓርቲው የፋይናንስ ችግር ነበረበት፡፡

ገንዘብ የለኝም ብሎ በቀጥታ ከመናገርና እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ የአንድነትን የአምስት አመቱን ስትራቴጂክ እቅድ ለአባላት ለማሳወቅ፣ ከየክልሉና ከየገጠሩ የሚመጡ አባላት ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ በቢሮ ውስጥ ሰሌን አንጥፈን በመተኛት፣ አባላት ስለፓርቲው እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው በጣም ሰርተናል፡፡ እነዚህ አባላት በራሳቸው አበል መጡ፤ እኛም የተወሰነ ድጐማ አደረግንና በትንሽ ወጪ በርካታ ስራ ሰራን። አስቢው ለአባላት አበል እንክፈል፣ አልቤርጐ እንከራይ ብንል ፓርቲው ገንዘብ የለውም፡፡ ግን ገንዘብ የለም ብሎ ከመቀመጥ በእነዚህ ስልቶች አባላትን በማሳወቅና በማንቃት የተሻለ የትግል ውጤት ማምጣት ይቻላል በሚል ይህን ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ በእርስዎ ስልት ምን ውጤት መጣ? እውነት ለመናገር በፊት ሳይከፈለን አንሰራም የሚሉ ሰዎች ወደየመጡበት ከተመለሱ በኋላ በራሳቸው ተነሳሽነት፣ በራሳቸው ገንዘብ እየተንቀሳቀሱ፣ በየክልሉ ከ27 በላይ ቢሮዎች እስከመክፈት ደርሰው ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ውጤት ይመስለኛል፡፡ በዚሁ ሃላፊነት ላይ እያሉ ከፓርቲው አመራሮች ጋር ተጋጭተው በርካታ ችግሮች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ በየጋዜጣው እስከመወቃቀስና እስከ መዘላለፍ ደርሳችሁ ነበር፡፡ የግጭቱ መንስኤ ምን ነበር? እውነት ለመናገር ያ ያለፈ ጉዳይ ስለሆነ አሁን ላለንበት ጊዜ ጠቃሚ አይደለም፡፡ መንስኤው ላልሽው በወቅቱ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኔ የመስራት አቅም እንደሌለኝ ይናገሩ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በዛን ወቅት የመስራት አቅም እንዳለኝ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ግለሰቦችና በፓርቲው ውስጥ ያሉ የሚዲያ አካላት ነገሩን ወደ ሌላ ለማዞርና ሌሎች ሰዎችን ለማጥቃት በሞከሩበት ስልት ሊያጠቁኝ ሞክረው ነበር፡፡ ሊሳካላቸው አልቻለም እንጂ፡፡ “ሌሎችን ለማጥቃት በሞከሩበት ስልት” ያሉትን ሊያብራሩት ይችላሉ? ለምሳሌ “እገሌ ኢህአዴግ ነው” በሚል ታፔላ እየለጠፉ ብዙ ለዚህች አገር ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ባልዋሉበት እየዋሉ፣ አንዳንዶቹ ተሰብረው አንዳንዶቹ ደግሞ “አልሰበርም” ብለው እየተለመጡና እየጐበጡ ትግላቸውን የቀጠሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ አንቺ ጋዜጠኛ ነሽ፤ አንዱ ተነስቶ ኢህአዴግ ናት ቢልሽ በየሄድሽበት ሁሉ ስራሽ ላይ እንቅፋት ይፈጠራል፡፡ “ይቺማ በቃ ኢህአዴግ ናት፤ አቃጣሪ ናት” እየተባልሽ ስራሽንና አካሄድሽን ያበላሹብኛል፡፡ እኔም በዚህ መንገድ ነው ጥቃት የተቃጣብኝ፡፡

ግን እኔ ኢህአዴግ ሆንኩም አልሆንኩም ያንን ስም ሲሰጡኝ መነሻቸው ምንድነው? በእንቅስቃሴሽ፣ በጥንካሬሽና በአካሄድሽ የምትበልጫቸውና እነሱን የምትሸፍኛቸው ሲመስላቸው ከመሬት ተነስተው ስም ይሰጡሻል። በእኛም ፓርቲ ውስጥ ራሳቸውን ጋዜጠኞች ነን ብለው የሰየሙ ሁለት ግለሰቦች፣ እኔን “ኢህአዴግ ነው” እስከማለትና ፌስ ቡክ ላይ እስከ መለጠፍ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ አልተቀበላቸውም፡፡ አንደኛ አሁን በፖለቲካው ህዝቡ በጣም እየነቃ ያለበት ጊዜ በመሆኑ፣ እንዲህ አይነቱ ፍረጃና አካሄድ ውጤት አልባ መሆኑን የተረዱት ይመስለኛል፡፡ በእኔ በኩል ደግሞ እነዛን ሰዎች ከሃላፊነቴ ሳልለቅ ውስጥ ሆኜ የበለጠ መታገል እችል እንደነበር የተማርኩበት ነው፡፡ በወቅቱ እኔ ከሚባለው ውንጀላ ንፁህ መሆኔን ለማሳየት ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እኔን እዚያው አፍነው ለማስቀረት ጥረው ነበር፡፡ ከጥረታቸው መካከል ለጋዜጠኞች እየደወሉ “ዘለቀን ኢንተርቪው አታድርጉ” የሚለው ይገኝበታል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች፣ የእነዚህን ግለሰቦች ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተፈጠረውን ነገር እንድናገርና እውነቱ እንዲወጣ እድል ሰጥተውኛል፤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በወቅቱ በተነሳው አለመግባባት እርስዎ በፈቃዴ ሃላፊነቴን ለቅቄያለሁ ቢሉም የፓርቲው አመራሮች ግን በዲሲፒሊን ጉድለት እንዳሰናበቱዎት የሚያሳይ ደብዳቤ እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡ የትኛውን እንመን? አንቺ የምትይውን ደብዳቤ እኔ አላየሁትም፤ አልደረሰኝምም፡፡ ከተሰናበትኩ መቼም ደብዳቤው መድረስ ያለበት ለእኔና ለእኔ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ደብዳቤ ሲቀበል ፈርሞ ነው፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን አላየሁትም፤ አልደረሰኝም፡፡ ባላየሁት ደብዳቤ ላይ ከዚህ በላይ መልስ መስጠት አልችልም፡፡ እርግጥ ከሁለቱም ወገን ራስን ለማዳን የሚደረጉ ጥረቶች ነበሩ፡፡ ራስን ለማዳን ሲሉ? ከፓርቲው ወገን ግለሰቦቹ ራሳቸው ትክክል እንደሆኑ ለማሳየት በርካታ ጥረት አድርገዋል። በእኔም በኩል ትክክል መሆኔን ለማሳየት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ አሸናፊውን የምታይው ነው፡፡ ግን እኮ ለዚህ ሁሉ ግጭት መንስኤ የሆነውን አስኳል ጉዳይ በግልፅ አልነገሩኝም፡፡ “ስራዬ ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው ፈረጁኝ” ብቻ ነው ያሉኝ… ለምን መሰለሽ ያልነገርኩሽ… አሁን ላይ ስለማይጠቅም ነው፡፡ ነገሩ አለፈና የግለሰቦች ሃሳብ የግለሰቦች ሆኖ ቀረ፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ደግሞ በአሁኑ ምርጫ ፍትሀዊ ውሳኔ ሰጥተውበታል።

ስለዚህ ወደኋላ ተመልሶ ነገር ማነቃነቁ አላስፈለገኝም፡፡ ይህ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ህዝቡ የማወቅ መብት ያለው አይመስልዎትም? ጠቃሚ ነገር ስለሌለው ምንም አይሰራም። አሁን ከእነዛ ግለሰቦችና ከእኔ የትኛው ትክክል እንደሆነ የፓርቲው አባላት ፍርድ ስለሰጡበት ማንሳት ጠቃሚ አይደለም፡፡ የፓርቲው አባላት ነገሩን በሰከነ ሁኔታ ይከታተሉ ነበር፣ ያጤኑ ነበር፣ ያነብቡ ነበር፡፡ አባላት እድሉን ሲያገኙ በምርጫው ወቅት ማን ትክክል እንደሆነ አውቀው፣ አሁን ፋይሉ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል፡፡ ይሄ ደግሞ ይግባኝ የለውም፡፡ እርስዎ ላይ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች አንዱ ቀደም ሲል እርስዎ እንደገለፁት “የፖለቲካ ብስለት የለውም” የሚል ሲሆን ሁለተኛው “አንድነትን ተጠቅሞ የራሱን ቢዝነስ ያጧጡፋል፤ ከፓርቲው ምስጢሮችን ለኢህአዴግ ያሾልካል፣ በአጠቃላይ ኢ/ር ዘለቀ ኢህአዴግ አንድነትን እንዲሰልል የላከው ነው” የሚሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ ውንጀላዎች ዙርያ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ዌል… ይህንን ያልሽውን ሁሉ ግለሰቦች ሚሊዮን ጊዜ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በመረጃ አስደግፎ የሚያቀርብ የለም፡፡ አንደኛ እኔ ኢህአዴግ ለመሆን በአንድነት ፓርቲ በኩል ማለፍ አያስፈልገኝም፡፡ ኢህአዴግ ለመሆን የተዘጋ በር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከእኛ ጋር የነበሩ በእውቀትም በችሎታም ከእኛ በታች የነበሩ ናቸው ኢህአዴግ ሆነው እላይ ተሰቅለው ያሉት፡፡

ሌላው አንድነት ምን የሚሰለል ምስጢር አለው? እስቲ ንገሪኝ... አንድነት እኮ ግልጽ ፓርቲ ነው፤ ዲሞክራት ነው፡፡ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን በግልፅ የሚያከናውን ፓርቲ ነው፡፡ ይህንን ፓርቲ ለመሰለል ኢህአዴግም ጊዜ የሚያጠፋ አይመስለኝም፡፡ ይህንን እንደተልዕኮ ተቀብሎ ጊዜውን የሚያጠፋ የዋህ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሚሰለለው እኮ መሳሪያ ታጥቆ በጦርነት የሚታገል ሲሆን ነው፡፡ ዛሬ ይህን አወድማለሁ፣ ነገ እዚህ ቦታ ላይ ጥቃት እሰነዝራለሁ፣ መንግስትን በማሸበር ስልጣን እነጥቃለሁ፤ የሚል ፓርቲ ሲሆን ነው የሚሰለለው፡፡ አንድነት በሰላማዊ ትግል የሚጓዝ፣ በግልጽ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው፡፡ ምን ምስጢር አለውና ይሰለላል? እርስዎ ይህን ይበሉ እንጂ አንዳንድ ወገኖች ግን “መንግስት በተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ ሰላዮችን በመመደብ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን ለመታገል የሚነድፏቸውን ምርጥ ምርጥ ስልቶች ቀድሞ በማወቅ እነዛን ስልቶች ያደናቅፋል፣ መንገድ ይዘጋል” በማለት ይከራከራሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ? የትግል ስልቶች ይነደፋሉ፤ ልክ ነው፡፡ ግን በምስጢር የሚያዙ አይደሉም፡፡ አንድነት በጋዜጣ ይጽፈዋል ብሮሸር ይበትናል፣ ለአባላት በተለያዩ መንገዶች እንዲደርሳቸው ይደረጋል፣ ለተለያዩ ሚዲያዎች በጋዜጣዊ መግለጫና በቃለ ምልልስ ይፋ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ምንም የሚደበቅና ለስለላ የሚያበቃ ነገር የለም፡፡ ምንም አይነት ድርጅታዊ ምስጢር የለም እያሉኝ ነው? ምንም ምስጢር የለም፤ ሁሉም ግልጽና ክፍት ነው፡፡ ለምሳሌ ፓርቲው የአምስት አመት እቅድና ስትራቴጂ አለው፡፡ ይህንን በመጽሐፍ መልክ አውጥተን ሸጠነዋል፡፡ ለአባላት በትነናል። አደረጃጀታችን ከማንም የተሰወረ አይደለም። አባላት መታወቂያ ተሰጥቷቸው በግልጽ በአንድነት አባልነታቸው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ድሮ አባላት አባልነታቸውን ይደብቁ ነበር፤ አሁን ያ ነገር የለም፡፡

አንድነት እኮ በቀጣይ መንግስት ሊሆን የሚችል ነው። ስለዚህ ዛሬ ትንንሽ ነገሮችን ደብቆ የሚንቀሳቀስ ትንሽ ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡ ከሳምንት በፊት ስለተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ እና ምርጫ ከማንሳታችን በፊት ከፓርቲው ለምን ያህል ጊዜ ተገልለው ቆዩ? ከፓርቲው እንቅስቃሴ ለአንድም ቀን ገለል ብዬ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባል ነኝ፡፡ በወቅቱ ራሴን ያገለልኩት ሊቀመንበሩ ከሰጡኝ ሃላፊነት እንጂ ህዝቡ ከሰጠኝ ስልጣን ራሴን ላገልል አልችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ለአንድ ቀንም ቢሆን አልተገለልኩም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ “የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት” የሚል ንቅናቄ ፓርቲው ሲያካሂድ፣ በጥሬ ገንዘብ 15ሺህ ብር፣ መኪናዬንና ሹፌሬን በመስጠት፣ እንዲሁም ለንቅናቄው ለሚሄዱት ሰዎች አበል እና መሰል ድጋፎችን በማድረግ ከአዲስ አበባ እስከ ባሌ ድረስ ንቅናቄናው እንዲካሄድና ሰላማዊ ሰልፉ እንዲደረግ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤና ወርሃዊ ጉባኤ ላይ እገኛለሁ፣ በመዋጮ እሳተፋለሁ፣ ፓርቲዬን በተመለከተ በጋዜጣ ላይ እጽፋለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ስታይው አንድም ቀን ከአባልነት ሃላፊነቴ ገሸሽ ብዬ አላውቅም፡፡ የኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የፓርቲው ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ከሚደመጡት አስተያየቶች መካከል “ፓርቲው ኢ/ሩን መምረጡ ኪሳራ ነው” የሚለው ጐላ ይላል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? በመጀመሪያ የኢ/ር ግዛቸውን መመረጥ ኪሳራ ነው የሚል ካለ ትርፍና ኪሳራን የማያውቅ ነው ብዬ እደመድማለሁ፡፡ እንደውም አንድነት ፓርቲ ኢ/ሩን በመምረጡ አትርፏል ባይ ነኝ፡፡ የአንድነት አባላት እውነት ለመናገር ሁሉን የሚያውቁ ሚዛኖች ናቸው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና በምን ጊዜ ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ከሁለት አመት በፊት እኔ ተወዳድሬ ነበረ፡፡

በዛን ወቅት እኔ በነበረኝ አቅም አንድነትን መሸከም እንደማልችል ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ነጋሶን መረጡ፡፡ በጣም ትክክል ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሶስት ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው፣ አቶ ግርማ ሰይፉና አቶ ተክሌ ማለት ነው፡፡ አቶ ተክሌ ኢ/ር ግዛቸው ለውድድር መቅረባቸውን ሲያውቅ ራሱን አገለለ፡፡ ይህን ያደረገው በፖለቲካ ልምድ፣ በትምህርት፣ በእድሜና በአጠቃላይ ብቃት እርሳቸው ፓርቲውን ቢመሩ ይሻላል በሚል ነው። ከዚያ በኋላ በኢ/ር እና በአቶ ግርማ መካከል ፉክክሩ ተካሄደ፡፡ አቶ ግርማ ወጣት የሚባል ባይሆንም እድሜው ከኢ/ር ግዛቸው በታች ነው፡፡ ነገር ግን ያገኘውን ድምጽ ስትመለከቺ ኢ/ር ግዛቸው ካገኙት ጋር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ይህ የሆነው ህዝቡ ፓርቲውን በአሁኑ ሰዓት ማን የመምራት ብቃት አለው የሚለውን መዝኖ በሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ትክክለኛ ውሳኔና ፍትሀዊ ምርጫ ነው። ኢህአዴግም ልክ እንደ አንድነት ለህዝቡ እድል ቢሰጠው የሚመራውን በትክክል ይመርጥ ነበር፡፡

በበኩሌ ኢህአዴግ ከአንድነት መማር ያለበት ነገር አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው የመረጧቸው የካቢኔ አባላት ለቦታው ይመጥናሉ ብለው ያምናሉ? በትክክል! አንዳቸውም የካቢኔ አባላት ያለቦታቸው አልተቀመጡም፡፡ ልብ ብለሽ ከሆነ ኢ/ሩ የመረጧቸው የካቢኔ አባላት እኛም ወጣት የምንባል ከሆነ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፣ የበፊቶቹን አብዛኞቹን አባላት አልመረጧቸውም፡፡ ይህን ስትመለከቺ በአሁኑ ሰዓት አንድነት አትርፏል ትያለሽ፡፡ በእርግጥ ይህን ኪሳራ ብለው የሚያስወሩ ከሁለት የማይበልጡ አባላት ይኖራሉ፡፡ አንደኛ ትርፍና ኪሳራን በውል ለይተው የማያውቁ ናቸው፡፡ ሁለተኛው አንድነት አሁን ያለበት ሁኔታ በእርግጥም ያስፈራል፡፡ ለምን ብትይ… ብዙ የተንኮል ፖለቲከኞች የሌሉበት፣ ለስራ ብቻ የሚተጉ የተመረጡበት በመሆኑ ወቅቱ የአንድነት ትንሳኤ ነው፡፡ ትንሽ የሚያሳስበኝ ኢ/ር ግዛቸው አሁን ከመረጧቸው ሰዎች ጋር እኩል ሮጠው ይችላሉ ወይ የሚለው ነው። ለምን? ከእርሳቸው በዕድሜ በጣም የሚያንሱትን መርጠዋልና እነርሱ በጣም የፈጠኑባቸው እንደሆነ፣ እኩል ለመሮጥ ዝግጁ ናቸው ወይ? ስል አስባለሁ፡፡ በእርግጥ ኢ/ር የማስተባበር ብቃትና ልምድ ያላቸው በመሆኑ ያን ያህል ችግር አይገጥማቸውም የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በመረጡት ካቢኔ ውስጥ እመረጣለሁ ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ ከተመረጡስ በኋላ ምን ተሰማዎት? እውነት ለመናገር አልጠበቅሁም ነበር፡፡ በመጀመሪያ አንድ ነገር ልንገርሽ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ከዚህ ትምህርት ይወስዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እዚህ በቅርብ ያሉ የአንድነት አባላት “ዘለቀ አንድነትን ተሳድቧል” ብለው አጋነው ለማቅረብ ሞክረዋል። አባላቱ ግን እኔ አንድነትን እንዳልተሳደብኩ፣ ችግሩ ከግለሰቦች ጋር ብቻ እንደነበር የገለጽኩትን በትክክል ተረድተውታል፡፡ ወደ ብሔራዊ ም/ቤት የምትገቢው በውድድር ተመርጠሽ እንጂ በፍላጐት ብቻ አይደለም፡፡ እኔ በመጀመሪያ ተመዝግቤ ተወዳድሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ስራ አስፈፃሚ እሆናለሁ ብዬ ሳይሆን ለብሔራዊ ም/ቤት አባልነት ነው የተወዳደርኩት፡፡ 17ኛው ወይም 18ኛ ተራ ቁጥር ላይ ነበር ስሜ የተመዘገበው፡፡

አባላቱ ግን ዘጠነኛ ቁጥር ላይ ነው ያመጡኝ፡፡ 217 ድምጽ ነው ያገኘሁት፡፡ ያኔ እኔ አንድነትን ማገልገል እንደምችል አባላቱ እምነት ጣሉብኝ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢ/ር የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አድርገው መረጡኝ፡፡ ትምህርትዎ ሲቪል ምህንድስና ይመስለኛል፡፡ አሁን ከተሰጠዎት ሃላፊነት ጋር ግንኙነት የለውም። ትንሽ አይከብድም? በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ጥናትና የውጭ ግንኙነት ሳይንስ ትምህርቴን በማጠናቀቄ ከተሰጠኝ ሃላፊነት ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ በዚሁ ትምህርት ውስጥ ዲፕሎማሲ ላይ የሚያተኩር ኮርስም ስለወሰድኩ ለቦታው እመጥናለሁ ብዬ አስባለሁ። አብዛኛው የውጭ ግንኙነት ስራዎች በሳይንሳዊ መንገድ ስለሚሰሩና በዘርፉም ስለተማርኩ ውጤታማ ስራ እሰራለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በምርጫው ወቅት የነበረው ድባብ ምን ይመስላል? በተለይ እርሶ የካቢኔ አባል ሆነው ሲመረጡ ተቃውሞ እንደነበር ሰምቼአለሁ… ከጠቅላላው ጉባኤው ልጀምርልሽ፡፡ እኔ ወደ ስብሰባው ስገባ “አንተን በማየታችን ደስተኞች ነን” ብለውኛል፡፡ አንዳንዶቹ መድረክ ላይ ንግግር እየተደረገ ሁሉ ያንን ጥሰው መጥተው ሰላምታ ሲሰጡኝ ነበር፡፡ ያኔ የአንድነት አባላት አሁንም ከጐኔ መሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡ ወደ ምክር ቤት ስንመጣ ግን ከሶስት ያልበለጡ ሰዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አንደኛው “ዘለቀ ልምድ ስለሌለው ስራውን አይችለውም” የሚል አስተያየት ሰጡ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ልምድ እድሜ የሚመስላቸው አሉ።

እንዲህ አይነት አስተያየት የሚሰጡ ትልልቅ ሰዎች ግን በእድሜ እንጂ በስራ ልምድ አይበልጡኝም፡፡ እኔ ስለ ሥራ ልምዴ ልንገርሽ፣ በአበባ አምራችነቱ ሁለተኛ የሆነውንና ዝዋይ የሚገኘውን የሆላንዱን “ሼር” የተባለ አበባ አምራች ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ አድርጌዋለሁ፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ለአራት አመታት ከሰባት ሺህ በላይ ሰራተኛ ስመራ፣ አንድ ሰራተኛ ለአንድም ቀን ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ አያውቅም፡፡ ለዚህም ድርጅቱ ዝዋይ ላይ በስሜ ትምህርት ቤት ሰርቷል፡፡ በአስተማሪነት በሰራሁበት ጊዜም ዩኒት መሪ ሆኜ ስሰራ፣ በአመራር ብቃት የወርቅ ተሸላሚ ሆኜ ነው የወጣሁት፡፡ ይህን “ሊሙ ገነት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት” ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጅማም በካቶሊክ ትምህርት ቤት አስተምሬያለሁ፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ ኮሙዩኒቲ ስኩልም አስተምሬያለሁ፡፡ በየሰራሁባቸው ቦታዎች ሁሉ በጥሩ የአመራር ብቃት ተሸልሜ ነው የምወጣው፡፡ እንደነገርኩሽ ዝዋይ ያለው የ”ሼር ኢትዮጵያ” ት/ቤት በስሜ ነው የሚጠራው - “ዘለቀ ት/ቤት” ይባላል፡፡ ይሄ ትልቅ ሽልማት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄንን ብዙ አውርቼው አላውቅም፡፡ ለምን ያልሽ እንደሆነ ሰው አሁን እየሰራ ባለው እንጂ ድሮ በሰራው ብቻ መመዘን አለበት ብዬ ስለማላምን ነው። እንግዲህ ተቃውሞ የተባለው አንድ ሶስት ሰዎች ሊቃወሙ ሞክረዋል፤ ግን የተቀበላቸው የለም፡፡ ነገር ግን በርካታ የአንድነት አባላት በእርስዎ የሃላፊነት ሹመት ደስተኞች እንዳልሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው… ብዙ ተቃውሞ አለ የሚባለው ሃሰት ነው፤ ከሶስት አይበልጡም፡፡ አንዱ ተቃዋሚ ከዚህ በፊት የኔን ገጽታ ለማበላሸት ሞክሮ ያልተሳካለት ስለነበር፣ አሁን ሃላፊነት ላይ ስቀመጥ በድንጋጤ የተናገረው ነው፡፡ እውነታው ይሄው ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሌላውን አባላትን አነጋግረሽ ድረሽበት፡፡ በሚቀጥለው አመት አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

ፓርቲው ለመወዳደር ሃሳብ ያለው ይመስልዎታል? ሃሳብ ያለው ይመስልዎታል ሳይሆን በደንብ ይሳተፋል፡፡ አንድነት በትክክል ይሳተፋል፡፡ እርስዎ በፖለቲካው ውስጥ እያሉ አንድነት ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ የመንግስት ሥልጣን የሚይዝ ይመስልዎታል? በትክክል! በምርጫው የምንወዳደረውም እኮ ለማሸነፍና አገር ለመምራት ነው፡፡ ደግሞም እሩቅ ሳትሄጂ አንድነት በቅርቡ መንግስት ሆኖ ይህቺን አገር ይመራል፡፡ በውስጥ አደረጃጀት፣ በአባላት ጥንካሬና በአጠቃላይ ሁኔታ በጥሩ አቋም ላይ በመሆኑ መንግስት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመጨረሻ? በመጨረሻ የአንድነት አባላት በእኔ እምነት ጥለው ድምፃቸውን ስለሰጡኝ እንዲሁም የፓርቲው ሊቀመንበር ችሎታና ብቃት አለው ብለው ሃላፊነት ስለሰጡኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እኔም ሃላፊነቴን በብቃት ለመወጣት ከወዲሁ በትጋት ስራዬን ጀምሬያለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Saturday, 11 January 2014 11:02

ወንዝ ለወንዝ መማማል…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለመውሊድ በዓል በሠላም አደረሳችሁ፡፡ በዛ ሰሞን አንድ ወዳጃችን አንድ ዝግጅት ላይ የሆነች ሴት ትጠራዋለች፡፡ ሴትዮ ስላላወቃት ለጊዜው ግራ ይገባዋል፡፡ ከዛ ትዝ ሲለው በደንብ የሚያውቃት ሴት ነች፡፡ አራት አምስት ዓመታት ገደማ አይቷት አያውቅም። “ወደ ፎርቲው እየተንደረደረች ነበር፡፡ አሁን ግን ሃያ መጀመሪያ ሆናለች!” ወዳጃችን ግራ የገባው ወጣት መሆኗ ሳይሆን ገጽታዋ ላይ ያየባት ለውጥ ነው፡፡ “አፍንጫዋና ጡቶቿ የእሷ እንዳልሆኑ እወራረዳለሁ!” ነው ያለው፡፡ ስሙኝማ…መቼም ከፈረደባቸው ‘ፈረንጆች የማንኮርጀው’ ነገር የለም አይደል…የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና እየተለመደ ነው ይባላል፡፡ (የኩረጃ ነገር ከተነሳ ‘ታንክስ ጊቪንግ’ እንኳን ሲኮረጅ!) እናላችሁ…ሰዎች ራሳቸውን ለመለወጥ መከራቸውን እያዩ ነው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…የ54 ዓመቷ ሴት የልብ ድካም ይገጥማትና ሆስፒታል ትገባላችኋለች፡፡ እናላችሁ… ገና በቀዶ ጥገናው ጠረዼዛ ላይ እያለች እግዚአብሔር ያናገራት ይመስላታል፡፡

እሷም… “እግዚአብሔርዬ፣ አበቃልኝ ማለት ነው?” ስትል ትጠይቃለች፡፡ እግዚአብሔርም… “አይዞሽ፣ አላበቃም፣” ይላታል። “ገና ሌላ 43 ዓመት ከሁለት ወር ከስምንት ቀን ትኖሪያለሽ፡፡” ሴትየዋም ደስ ይላትና ተሽሏት ስትወጣላችሁ… “ይሄ ሁሉ ዓመት ከቀረኝማ…” ትልና ራሷን ወጣት ለማድረግ ትወስናለች፡፡ ፊቷ በቀዶ ጥገና ተለወጠ፣ አፍንጫዋ ሰልካካ ሆነ፣ ጡቶቿ ከጉች፣ ጉችነትም አልፈው ለመወንጨፍ የተዘጋጁ የአሜሪካ ‘ፓትሪዮት’ ሚሳይሎችን መሰሉ። “ዋ! አንድ ነገር ካላደረግሽ ተወርውሬ መሬቱ ላይ ለሽ ልል ነው!” የሚል ይመስል የነበረው ቦርጯ ድራሹ ጠፋ። የጸጉሯ ቀለምና ዞማነት ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ተለወጠና እነኚህ የሻምፑ ማስታወቂያዎች ላይ የምናያቸውን ሴቶች ‘ጸጉር’ መሰለ፡፡ ብቻ…ምን አለፋችሁ “ፏ!” አለችላችሁ፡፡ ታዲያችሁ…አንድ ቀን የመጨረሻውን የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና አካሂዳ ከሆስፒታል እየወጣች ነበር፡፡ እናማ… ከየት መጣ የማይባል አምቡላንስ መኪና ይገጫትና በዛው ይቺን ዓለም ትሰናበታለች፡፡

እግዚአብሔር ፊትም ስትደርስ እየተንዘፈዘፈች… “ገና 43 ዓመት አለሽ ብለኸኝ አልነበረም እንዴ! ታዲያ መኪና ሲገጨኝ ለምንድነው ያላዳንከኝ!” ትላለች፡፡ እግዚአብሔርም ትኩር ብሎ ካያት በኋላ ምን አላት መሰላችሁ… “ጉድ! ጉድ! አንቺው ነሽ እንዴ! እኔ ታዲያ ምን ላድርግ፣ ሌላ ሰው መሰልሽኛ!” ዘንድሮ እኛ ዘንድ መልክን መለወጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር ሌላ ሰው የመምሰል ፉክክር ‘ብሔራዊ ስፖርት’ ነገር ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ እና የብዙዎቻችንን እውነተኛ ባህሪይ ለማወቅ ‘መፋቅ’ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ሆኗል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ብዙ ቃለ መጠይቆችን ነገሬ ብላችሁልኛል…ተጠያቂዎቹ ሌላ ሰው ለመምስል የሚያደርጉት ሙከራ…ምን አለፋችሁ…“ሰዉ ሁሉ ምን ነካው!” ያሰኛል፡፡ ከየሁለትና ከየሦስት ቃሉ በኋላ “እ…” እያሉ መጎተት የአዋቂነት ‘ግሪን ካርድ’ የሚመስለን መአት ነን፡፡ በነገራችን ላይ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “እ…” እየረዘመችና እየበዛች በሄደች ቁጥር ችግሩ የሽለላ ሳይሆን የሆድ ቁርጠት ሊሆን ይችላል! ቂ…ቂ…ቂ…. ልክ ነዋ! ስንት መሸለያ መንገድ እያለ፣ እዚቹ ከተማችን ውስጥ ስንት ‘ፈልሰው የመጡ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ስንት የሽለላ አይነቶች እያሉ አታሳቁና! እናማ…“እ…” ማለት የምታበዙ ሰዎች… አለ አይደል… “አድናቂው ነኝ!” ከማለት ይልቅ… “ሰውየው ምን ያምጥብናል! መጸዳጃ ቤት እንኳን ቢያጣ የሆነ ሰንሰል ምናምን ጀርባ አይሄድም እንዴ!” እንደምንል ይጻፍልን፡፡ እናማ…በምኑም በምናምኑም ሌላ ሰው ለመሆን የምንሞክር…አለ አይደል… በኋላ “እኔ ምን ላድርግ፣ ሌላ ሰው መሰልሽ/ከኛ!” ነገር እንዳይመጣብንማ! ችግሩ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ሰዉ ሁሉ አትኩሮቱ እኛ ላይ ያለ ይመስለናል፡፡ በመንገድ ስንሄድ፣ በሬስቱራንት ስንመገብ፣ ‘በግሮሰሪ’ ስንጨልጥ፣ ሲኒማ ቤት ስንገባ፣ ሚኒባስ ስንሳፈር…ምን አለፋችሁ… ሰዉ ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ ስለእኛ የሚያስብ ይመስለናል፡፡ አንዱ ያለውን ስሙኝማ… “በሀያዎቹ ዕድሜያችን ዓለም ስለእኛ ምንም ያስብ ምን ጉዳያችን አይደለም፡፡ በሠላሳዎቹ ዕድሜያችን “ሰዎች ምን ይሉን ይሆን!”” ብለን መከራ እንበላለን፡፡ በአርባዎቹ ዕድሜያችን ግን ማንም ሰው ስለእኛ ይቺን ታክል ጉዳዩ እንዳይደለ ይገባናል፡፡

እናላችሁ…ብዙዎቻችን ሰዉ ስለ እኛ ብቻ የሚጨነቅ እየመሰለን የሆነ ዓለም ፈጥረናል፡፡ በእርግጥ መፋጠጥ በጣም በዝቷል፡፡ በየቦታው ዓይኑን ተክሎ ሰው ላይ የሚያፈጥ መአት ነው፡፡ ግን ምን መሰላችሁ… እንደዛ አይነት ሰዎች የሚያፈጡት ሁሉም ‘ጸጉረ’ ልውጥ ላይ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… አሀ፣ እሱ የማያውቀው ሰው ሁሉ ለእሱ ‘ጸጉረ ልውጥ’ ነዋ! እናላችሁ…በሚዲያ ቀርቦ ልክ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እየተጣሉበት ያለ የምጣኔ ሀብት ጠቢብ ይመስል…ቦሶቻችንን መስሎ “የህዝቡ ኑሮ በጣም ተሻሽሏል…” ምናምን ነገር ሲል… የለየለት ቅሽምና ነው። ልከ ነዋ… “እንዴት ነው የሰዉ ኑሮ የተሻሸለው?” ብትሉት… አለ አይደል… ምን የሚል መሰላችሁ… “የቦሌን መንገድ እንዴት እንደሚያምር አላየኸውም!” ይላችኋል፡፡ የምር ግን…ቆዳችንን ገፈን የ‘ቦሶቻችንን ቆዳ’ ካላጠለቅን የሚሉ፣ በእከሌ ፓርቲ ጠበል ለመጠቀም ‘ሰልፍ የሚይዙ’…ምን አለፋችሁ፣ የባህሪይ ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ’ ራሳችን ላይ የምናካሂድ ሰዎች በዝተናል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የሂሳብ ሊቅ፣ አካውንታንትና ኤኮኖሚስት ለአንድ ክፍት የሥራ ቦታ ይወዳደራሉ፡፡

ቃለ መጠይቅ አድራጊው የሂሳብ ሊቁን ይጠራውና እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” “አራት፣” ይላል የሂሳብ ሊቁ፡፡ ጠያቂውም ““በትክክል አራት!” ሲል ደግሞ ይጠይቀዋል፡፡ “አዎን፣ በትክክል አራት፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ጠያቂው አካውንታንቱን ይጠራና ያንኑ ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” “በጥቅሉ አራት ነው፡፡ አሥር ከመቶ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል፡፡ ግን በጥቅሉ አራት ነው፡፡” ጠያቂው ኤኮኖሚስቱን ያስገባና “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ኤኮኖሚስቱ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ?” እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኛ ዘንድ የቁጥርና የመቶኛ መአት እየተደረደ…አለ አይደል… “አላወቃችሁ ሆናችሁ ነው እንጂ፣ ዲታ ሆናችኋል…” አይነት ነገር የምንባለው “ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ?” በሚለው ስሌት ነው እንዴ! ስሙኝማ…ልክ እኮ ጓደኛ “ስንት ልስጥህ?” እንደሚለው ቁጥርን “ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ?” አይነት ኮሚክ ነገር ነው፡፡ መቼም ቁጥሮች እንዲሀ አገር መከራቸውን ያዩበት ቦታ ያለ አይመስለኝም— “ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” ከሚለው ጀምሮ፡፡ እና…በተለይ ተቋሟት ሁሉ ነገራቸው የቁጥር ጨዋታ ሆኗል፡፡ ችግሩ… “ስንት እንዲሆንላችሁ ትፈልጋላችሁ?” የሚለን መጥፋቱ ነው፡ ያኔ እቅጯን እንልና…ምን አለፋችሁ የየድርጅቱ የፋይናንስ መምሪያዎች ያሉ ሁሉ ‘ላይ ቤታቸው’ ያለ ቡሎን ሁሉ አንድ በአንድ ወልቆ ያልቅ ነበር! ይቺን ስሙኝማ…የአእምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ነው፡፡

አንድ ቀን…አንዱ በሽተኛ “እኔ ናፖሊኦን ነኝ! እኔ ናፖሊኦን ነኝ!” እያለ ይጮሀል፡፡ ሌላኛው በሽተኛም… “ናፖሊኦን መሆንህን በምን አወቅህ?” ይለዋል፡፡ ያኛውም “እግዚአብሔር ነግሮኝ ነው፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ይሄኔ ጎን ካለው ክፍል ምን የሚል ድምጽ ተሰማ መሰላችሁ… “ውሸቱን ነው፣ እኔ አልነገርኩትም!” እናላችሁ…መልክን በመለወጥም ሆነ፣ እውነተኛ መረጃዎችን በመለወጥ ነገሮችን…ሌላ ለማስመሰል መሞከር ቀሺም ነው፡፡ ‘መፋቅ’ የማያስፈልገው እውነተኛ ባህሪይ፣ ለማረጋገጥ እንደ ዘይት ጉድጓድ ጥልቅ ቁፋሮ የማያስፈልገው እውነተኛ መረጃ…እየናፈቁን ነው። መፋፋቅ ሲበዛ ያለመተማመን በዛ ማለት ነው፡፡ ያለመተማመን ደግሞ ወንዝ ለወንዝ መማማል ይሆናል፡፡ ወንዝ ለወንዝ ከማማል ይሰውረንማ! ድፍን አገር ‘ወንዝ ለወንዝ መማማል’ ደረጃ ሲደርስ አሪፍ አይደለም፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ከእለታት አንድ ቀን አንድ እረኛ ከብቶቹን ወደ ቤቱ እየነዳ ሳለ ወደ በረታቸው መቃረባቸውን በማሰብ ለመዝናናት ወደኋላ ይቀራል፡፡ ሳያስበው ግን በድንገት አንድ ተኩላ ይመጣበታል፡፡ ሮጦ በማያመልጥበት ርቀት ላይ በመሆኑ ባለበት ቆሞ ይቀራል፡፡ ተኩላውም፤ “እንዴት ብትደፍረኝ ነው፤ በእኔ ግዛት፣ በዚህ ምሽት፣ ያለ ፍርሃት እየተዝናናህ ያገኘሁህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ እረኛውም፤ “አያ ተኩላ፤ ብዙ ጊዜ ከብቶቼን እየነዳሁ ስሄድ ታየኛለህ፡፡ እስከዛሬም በጠላትነት ተያይተን አናውቅም፡፡ ስለዚህ በድፍረት ሳይሆን በፍቅር ተሳስበን እንተላለፋለን እንጂ በክፉ አንተያይም በሚል እሳቤ ነው ዘና ብዬ ወደ ቤቴ የምሄደው” አለው፡፡ ተኩላም፤ ነገር ፈልጐ ልጁን መብላት አስቦ ኖሮ፤ “በጭራሽ የንቀት ነው፡፡ ምናልባትም ውሾችህንና ጌታህን ተማምነህ ይሆናል፡፡ ማናቸውንም እንደማልፈራቸው ዛሬ አሳይሃለሁ!” እረኛው በሌላ መንገድ ሊያሸንፈው እንደማይችል ተገንዝቦ፤ “አያ ተኩላ፤ እራትህ ልሆን እንደምችል አውቄያለሁ፡፡

ላመልጥህም እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ ውሾቼም ሆኑ ጌታዬ እንደማያድኑኝም ተገንዝቤያለሁ፡፡ ስለዚህ አንድ ውለታ ብቻ ዋልልኝ፡፡ ከእንግዲህ ዕድሜዬ በጣም አጭር ናትና ተደስቼ እንድሞት ዕድል ሰጠኝ፡፡” ተኩላውም፤ ልጁ ለመበላት ዝግጁ መሆኑ ደስ አለውና፤ “ከመበላትህ በፊት የሚያስደስትህ ምን እንደሆነ ንገረኝና በቀላሉ ላደርገው የምችለው ነገር ከሆነ አደርግልሃለሁ” አለ፡፡ እረኛውም፤ “እባክህ ዋሽንት ንፋልኝ፡፡ ጥሩ ዜማ ሰምቼ ለመሞት እፈልጋለሁ” ሲል ለመነው፡፡ አያ ተኩላም ከእራት በፊት ሙዚቃ መጫወት የሚከፋ ነገር አይደለም ብሎ በማሰብ የእረኛውን ዋሽንት ተቀብሎ መጫወት ጀመረ፡፡ እረኛውም መደነስ ቀጠለ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የዋሽንቱን ድምጽ የሰሙ ውሾች፤ “በጭለማ ዋሽንት ማን ሊጫወት ይችላል? ከየት በኩል ነው ድምፁ የሚመጣው?” ተባባሉና ሙዚቃውን ወደሰሙበት አቅጣጫ ሲመጡ፤ አያ ተኩላ ዋሽንት ይጫወታል፡፡ ትንሹ እረኛ ይደንሳል፡፡ ሳያመነቱ ተኩላውን ለመያዝ እየሮጡ መጡበት፡፡ ተኩላው ዋሽንቱን ወርውሮ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ እየሮጠ ሳለ ግን ወደ ልጁ ዘወር ብሎ፤ “ዋና ሥራዬ ልኳንዳ ቤት ነው፡፡ ያገኘሁትን ሥጋ አርጄ መብላት ሲገባኝ እኔን ብሎ ሙዚቃ ተጨዋች! ዋጋዬን አገኘሁ!” እያለ ሩጫውን ቀጠለ፡፡

                                                             * * *

ያለሙያ መግባት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አገኘን የምንለውን ድል በአግባቡ ካልተጠቀምንበትና በዚያ ተኩራርተን ትርፍ መንገድ እንሂድ ካልን የጥፋተኝነታችንን ያህል ኪሣራውን መክፈል ግዴታችን ይሆናል፡፡ ፖለቲከኛው ባለሙያው ሥራ ውስጥ ተሸብልቆ ከገባ፣ ባለሙያ ባንድ ጀንበር ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ ከተፈጠመ፤ ጉዟችን የእውር የድንብር ነው የሚሆነው፡፡ በእጃችን ያለውን ሙያ ትተን የማያገባን ሥር ውስጥ ገብተን መቧቸር ከሁለት ያጣ ያደርገናል። የሰለጠንበት ሙያ ሌላ፤ የምንሠራው ሥራ ሌላ ከሆነ፤ ከሁለት ያጣ እንሆናለን፡፡ የራሳችንንም ሥራ አልሠራን፤ ሌሎችም ሥራ እንዳይሠሩ አደረግን፡፡ የሀገራችን አንዱ ችግር ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ አለመቀመጡ ነው (The right man at the right place እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ)፡፡ ወይ በዘመድ፣ ወይ በታሪክ አጋጣሚ፣ አሊያም በዕድል ያለሙያችን የተቀመጥንበት ቦታ ከልማቱ ጥፋቱ ይበዛል፡፡ ሁሉ በጄ፣ ሁሉ በደጄ ማለታችን አይቀርምና ከእኛ በላይ የሚያውቅን ሰው አላግባብ ማጐሳቆላችን፣ “እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ፣ እኔ ያልኩትን ብቻ ፈጽሙ” ወደሚል ግትርነት ማዘንበላችን አይቀሬ ነው፡፡

“ወዳጄ እጅግ ብዙ ምክር ያዳምጣል፡፡ የማታ ማታ የሚሰማው ግን የራሱን ልቦና ነው” ይለናል ደራሲ፡፡ ያ ደግሞ ለለውጥ አያመችም፡፡ “እግዚአብሔር ሲምር ምክር ያስተምር” የሚለውን ያስዘነጋልና፡፡ የጋራ አገር እንዳለን እንዲሰማን ያስፈልጋል፡፡ በጋራ እንደግ ብሎ ልብን መክፈት ያስፈልጋል፡፡ አገር ጥቂቶች የሚለፉባት ሌሎች የሚያፌዙባት እንዳልሆነች መገንዘብ ይገባል፡፡ ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን “የአገሬ ሰው አብረን ወደላይ እንደግ ሲሉት፤ አሸብልቆ ወደታች ወደመሬት ማጐንቆል ይወዳል!” ይለናል፡፡ ቀጥሎም፤ “አንድም መንግሥት ማለት የአገሩ አዕምሮ እንጂ የልቡ ሮሮ አይደለም” ይለናል፡፡ ሀገራችንን በጋራ ዐይን እንያት፡፡ “ወዳጄ ልቤ ሆዬ የእኔ መከራ ያንተ መከራ አይደለምን?” እንባባል፡፡ (ብላቴን ጌታ ህሩይ እንዳሉት) የሀገርን አንድነት፣ የሀገርን ኢኮኖሚ፣ የሀገርን ባህል፤ ተጠንቅቆ ጠብቆ በቅጥ በቅጡ ለማቆየት፤ በፍቅርና በመተሳሰብ እንጂ “የራቀውን በመድፍ፣ የቀረበውን በሰይፍ” የምንልበት የምንበቃቀልበት፣ የምንጠፋፋበት ዓይነቱ ዘዴ፤ ቢያንስ ዘመናዊ አይደለም፡፡ “ጀግናን ዘገንኩና አፈር ብዬ ተውኩት”፣ እንዳለች ዕድሜዋን ትገፋለች አሉ የጐበዝ አገር እናት፡፡ ዛሬ፤ በዕውቀት ብርሃን የተጋ ዜጋ ያስፈልገናል፡፡

ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአተካሮና የውሃ ወቀጣ ባህልን ዘሎ ማሰብ የሚችል አዕምሮ ብቻ ነው የመፍጠር ክህሎትን የሚቀዳጅ፡፡ ነፃ አዕምሮ ነፃ አስተያየትን ይወልዳል፡፡ ማርክ ትዌን፤ “በእኛ አገር በእግዚሃር ደግነት ሦስት ወደር የሌላቸው ነገሮች ተሰጥተውናል:- የመናገር ነፃነት፣ የሀሳብ ነፃነት እና ሁለቱንም በተግባር ያለማዋል ኩራት” ይለናል። ስለማንነት ሲናገርም “ቦስተን ውስጥ ምን ያህል ዕውቀት አለው? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ኒውዮርክ ውስጥ ምን ያህል ዋጋ አለው? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ፊላዴልፊያ ውስጥ ወላጆቹ እነማናቸው? ተብሎ ይጠየቃል” ይላል፡፡ የትኛውን ነን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በተግባር የማንፈጽመውን አዋጅ ማወጅ፣ የማንከውነውን መመሪያ ማውጣት፣ በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ ፖለቲካ ማውራት፣ የሩቁን ትተን የዕለት የዕለቱን ብቻ እያወራን በአየር ላይ መኖር፤ “ያልወጋ ቀንድ ከጆሮ ይቆጠራል” የሚለው ትርጓሜ ነው የምንሆነው፡፡ መሠረት ያለው፣ ዕውቀትን የተንተራሰ ከወሬ ያለፈ ህብረተሰብ ለመገንባት ጥረት እናድርግ፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ጭቆና ትግልን ያጠነክራል እንጂ አይገድልም...
ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ የአንድ ወር ሥራ በቂ ነው….
ኢህአዴግ ሁልጊዜ የትግራይ ህዝብ በስጋት እንዲኖር ነው የሚፈልገው

 በቅርቡ ለፓርቲዎች የውህደት ጥያቄ አቅርባችኋል፡፡ ለየትኞቹ ፓርቲዎች ነው ጥያቄውን ያቀረባችሁት? መስፈርታችሁስ ምን ነበር? እኛ እንግዲህ ያሰብነው በመድረክ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፈፀም ነው፡፡ ግን ከመድረክ ውጪም ቢመጣ ችግር የለብንም፡፡ እንግዲህ በጠየቅናቸው ፓርቲዎች ሙሉ ፈቃደኝነት በቅርቡ ከግንባር ወደ ውህደት እንሄዳለን የሚል እምነት ነው ያለኝ። ጥያቄውን ለኦፌኮ፣ ለአንድነት እና ለደቡብ ህብረቶች አቅርበናል፡፡ እነሱም በጐ ምላሽ እየሰጡን ነው፡፡ ውህደት የተጠየቁት ፓርቲዎች የመድረክ አባል ከሆኑ ለምን ራሱን መድረክን አልጠየቃችሁም? ፓርቲዎቹን በተናጠል መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ሁለት አቅጣጫ ነው ያለው፡፡ እንዳልከው በቀጥታ መድረክንም መጠየቅ ይቻል ነበር፤ ግን በተናጠል የመጠየቁን መንገድ ነው የመረጥነው፡፡ ይሄን ጥያቄ ያነሳሁት “አረና በመድረክ ላይ እምነት የለውም” የሚሉ አስተያየቶች ስለሚሰነዘሩ ነው… በተናጠል መጠየቁን በመድረክ ህልውና ካለማመን የመጣ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ… እኛ እኮ ሁሉንም ነው የጠየቅነው፡፡ ነጥለን የተውነው ፓርቲ ቢኖር ሊያስብል ይችላል፡፡ ግን የጠየቅናቸው በአጠቃላይ በመድረክ ውስጥ ያሉትን ነው:- አረና፣ ኦፌኮ፣ አንድነት እና የደቡብ ህብረት፡፡ አረና ተነሳሽነቱን ወስዶ ነው የእንዋሃድ ጥያቄውን ያቀረበው፡፡

ስለዚህ መድረኩን አይፈልጉትም የሚያስብል ሁኔታ አይፈጥርም፡፡ ይሄኛውን መንገድ መምረጣችን ብዙም ችግር አለው ብዬ አላስብም፡፡ ለውህደቱ ጥያቄ መነሻችሁ ምንድን ነው? እንዴትስ ይሄኛውን ጊዜ መረጣችሁ? ምናልባት ምርጫውን አስባችሁ ይሆን? እኛ የተቋቋምነው በክልላዊ ፓርቲነት ነበር፡፡ ህወኃት ቅድሚያ ለትግሬነት ስለሚሰጥ ነው እኛም በክልላዊ ፓርቲነት የተቋቋምነው፡፡ በቀላሉ ተቀባይነትን ለማግኘት በመሻት ነው እንጂ የአረና የመጀመሪያ አላማው ሀገራዊ እሳቤን ያዘለ ነው፡፡ ክልላዊነታችን የአጀማመር ጉዳይ ነው እንጂ ለዘለቄታው ያነገብነው አላማ ሀገራዊነትን ነው፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፍጠራችንም ሀገራዊ አላማ አንግበው የሚታገሉ ፓርቲዎች፣ በትግራይ ህዝብ በቀላሉ ተሰሚነት እንዲያገኙም አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህች ሀገር ሁነኛ መፍትሄ የሚሆነው ትግራይ ለብቻው፣ ኦሮሞው ለብቻው፣ አማራው ለብቻው፣ ሌላውም ለብቻው ሊታገል ሳይሆን ሁሉም በአንድነት ተዋህዶ ተስማምቶ ሲታገል ነው፡፡

እኛ ኢህአዴግ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 ያስቀመጠውን የመገንጠል መብት እንቃወማለን፡፡ መነሻችን ለጊዜው ክልላዊ ይሁን እንጂ ይሄም ያስቀመጥነው አላማ ሀገራዊነት ነው፡፡ አረና በህወሐት ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በተፈጠረ የግለሰቦች ኩርፊያ የተመሰረተ እንጂ ከህወሓት የተለየ አጀንዳ የለውም የሚሉም አሉ፡፡ ይሄን እንዴት ያዩታል? ይሄን የሚለው ፓርቲው ውስጥ ያሉትን አባላት ማየት ያልቻለ ሰው ይመስለኛል፡፡ በሚዲያም ብዙ ጊዜ ወጣቶቹ አይወጡም፡፡ እኔ በፊት የህወሓት አባል አልነበርኩም፡፡ ብዙዎቹም አባል ያልነበሩ ናቸው፡፡ እነ አቶ ገብሩ ደግሞ ከህወሐት ጋር መሰረታዊ ልዩነት አላቸው፡፡ ያንን ልዩነታቸውን በግልፅ አስቀምጠው ነው የወጡት፡፡ ፓርቲ ያቋቋሙት ስላኮረፉ ነው ማለት ከባድ ነው፡፡ ስንት ሰዎች ናቸው ያኮረፉት? አቶ ገብሩ፣ ወ/ሮ አረጋሽና አቶ አውአሎም ናቸው፡፡ ግን እኮ እነዚህ ግለሰቦች ናቸው የፓርቲው ጠንሳሾችና መስራቾች። እነዚህ ሰዎች ደግሞ በኢህአዴግ የብሄር ፌደራሊዝም፣ የመሬት ፖሊሲና በመሳሰሉት የሚያምኑ ናቸው፡፡ በወቅቱ የልዩነታቸው አንዱ መነሻ በኤርትራ ላይ የተያዘው አቋም ነው፡፡

ፓርቲውን ካቋቋሙ በኋላ ከህወሓት ጋር ያላቸውን ልዩነት በነጥብ ማስቀመጥ ይቻላል? በመሰረቱ ከህወሓት ለመለየት ተብሎ የብሄር ፌደራሊዝም ትክክለኛ አይደለም፣ ከህወሐት ለመለየት ተብሎ የብሄር ብሄረሰብ መብት አይከበርም ማለት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለልዩነታችን መነሻ ከሆኑት መካከል ለምሳሌ የአሰብ ወደብ ጉዳይ አለ፡፡ በሰላማዊ መንገድ መንግሥት መቀየር በሚለውና በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ላይ ልዩነት አለን፡፡ ህወሓት ትልቁ የታገልንለት አላማ አንቀፅ 39 ነው ይላል፡፡ እሱ አንቀፅ ይሻሻል ሲባል ግን ህገ መንግሥቱ አይሻሻልም ይላል፡፡ ይሄ በፖለቲካ ስርአት ውስጥ ያልተለመደ ነው፡፡ እኛ ህገ መንግስቱ መሻሻል እንዳለበትና መሻሻልም እንደሚችል እናምናለን። በተቃራኒው ህወሐት ህገ መንግስቱ ፈፅሞ መሻሻል እንደማይችል ያምናል፡፡ በኢኮኖሚው አካሄድ ላይም ልዩነት አለን፡፡ እኛ ቅይጥ የሚለውን የኢኮኖሚ ስልት ሀገሪቱ መጠቀም አለባት እንላለን፡፡ እነሱ አንዱን መስክ መሪ፣ ሌላውን ተመሪ አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡ በመሬት ፖሊሲው ላይም ልዩነት አለን፡፡ እኛ መሬት የመንግስት ሆኖ ከግለሰቡ ጋርም የጋራ የሚሆንበት መንገድ አለ ብለን እናምናለን፡፡ በፖለቲካ አካሄዳችን ደግሞ የስልጣን ገደብ ሊኖር ይገባል እንላለን፡፡ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገር እየመራ የሚሞትበት ስርአት መቀጠል የለበትም ባይ ነን፡፡ በብሄር ፌደራሊዝም ላይ ያላችሁ አቋምስ? እኛ በብሄር ፌደራሊዝም አናምንም፤ ነገር ግን ፌደራሊዝም ለዚህች ሀገር ይጠቅማል የሚል እምነት አለን፡፡

ምን አይነት ፌደራሊዝም ይሁን በሚለው ጉዳይ አቋም ላይ አልደረስንም፤ ነገር ግን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እያዩ ማስተካከል ይቻላል የሚል እምነት አለን፡፡ በፕሮግራማችን ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ እንደሚጠቅም ያለጥርጥር አስቀምጠነዋል፡፡ የውህደት ጥያቄ ካቀረባችሁላቸው ፓርቲዎች መካከል የፌደራሊዝም አስፈላጊነት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው አሉ፡፡ ከነዚህ ፓርቲዎች ጋር ይህን አቋማችሁን እንዴት ነው የምታስታርቁት? በእርግጥ አንዳንዶች የሚያስቀምጧቸው ሃሳቦች አሉ፡፡ ይህን እንግዲህ ወደፊት በውይይት የምንፈታው ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ አንድነት የተወሰነ የሄደው ነገር አለ፡፡ የቡድንና የግለሰብ መብትን ሳይነጣጠሉ ማስከበር የሚለውን እንደተቀበሉ አውቃለሁ፡፡ ይህን ሲቀበሉ እስከምን ድረስ ነው የሚለው እንግዲህ ሌላ ውይይት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በቋንቋው የመፃፍ፣ የማንበብ፣ የመማር መብቱ ከተረጋገጠለት የቡድን እና የግል መብት የሚባለው ከዚህ በላይ ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ እንደ ግለሰብ መብቱ ይከበርለታል፡፡ እንደ ቡድንም እንግዲህ የዘር ልዩነት ሳይሆን የቋንቋ ልዩነት ብቻ ነው ሁላችንም ያለን፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው በቋንቋው ከተማረ፣ በቋንቋው መተዳደር ከቻለ፣ መብቱ ከተከበረለት ሌላ ምን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት በመድረክ ስብስብ ውስጥ በመካተታችሁ “የነፍጠኛ ስርአት አቀንቃኞችና ተላላኪዎች” በሚል ስትፈረጁ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ውህደት ካልፈፀምን እያላችሁ ነው፡፡

ውህደቱ ለበለጠ ፍረጃ አይዳርጋችሁም፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴያችሁ ላይስ ተፅእኖ አይፈጥርም? ከነፍጠኛ ስርአት ናፋቂዎች ጋር እየሰራችሁ ነው የሚባለውን እኛ ሚዲያ ባለማግኘታችን ነው እንጂ ማስረዳት እንችላለን፡፡ እኩል የሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ እድል ቢከፈት፣ በእርግጠኝነት የኛ ሃሳብ የበላይ ይሆን ነበር፡፡ ከአንድነት እና ከሌሎች ጋር መስራታችንን እንደ ነፍጠኛ ስርአት ናፋቂነት እየቆጠረ፣ እራሱ አማራውንና ኦሮሞውን እንወክለዋለን ከሚሉት ጋር እየሰራ፣ ራሱን ለትግራይ ህዝብ ታማኝ እንደሆነ አድርጐ ማቅረቡ ስህተት ነው፡፡ ይህን ስህተቱን ግን ሚዲያ በመከልከላችን ለህዝቡ ማስረዳት አልቻልንም፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ሲመሰረት ቅዠት ነው የተባለው አረና፤ ጫናውን ሁሉ ችሎ ዛሬ ተቀባይነትን በስፋት እያገኘ ነው፡፡ መጀመሪያ በክልሉ ግዙፍ ነኝ ከሚለው ህወሐት ጐን የሚቆም ተገዳዳሪ ፓርቲ ማፍራት መቻሉ ተረጋግጧል፡፡ አሁን ደግሞ ሀገራዊ ሆኖ የበለጠ ተወዳዳሪነቱ የሚጨምር መሆኑን አባሎቻችንን አሳምነን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እና ለውህደት ከጋበዝናቸው ፓርቲዎች ውስጥ ደግሞ እንዳለፉት ስርአቶች በቋንቋህ መናገር፣ መግባባት፣ መማር አትችልም የሚል አቋም ያላቸው የሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሃይላት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አስጊ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ይልቁኑ አስጊ የሚሆኑት ህወሐት እና ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ህወሐት ትግሉ መካን እንዲሆን ጠንክሮ እየሰራ ነው ብዬ አምናለሁ። የትግራይ ህዝብ በሌላው ተገዝቷል፣ በተራውም ገዝቶ ያውቃል፣ አሸንፎ ያውቃል፤ ተሸንፎም ያውቃል፤ ያ እንግዲህ በጦርነት የታየ ነው፡፡

ዛሬ ግን የሚያስፈልገው ሰላማዊ ትግል ነው ተብሎ እስከታመነበት ድረስ ለሰላማዊ ትግሉ በር የመክፈትና ሜዳ የማመቻቸት ተነሳሽነቱን ሊወስድ የሚገባው ህወሐት-ኢህአዴግ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉት የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፓርቲዎች የበለጠ ለዚህች ሀገር ስጋት የሚሆነው ኢህአዴግ ነው፡፡ የዚህች ሀገር ትልቁ ስጋት ኢህአዴግ ነው፡፡ ለትግራይ ህዝብ ይሄን ማስረዳትና ማሳመንም ቀላል ነው፡፡ በየመግለጫዎቻችሁ ኢህአዴግ አላፈናፍን ብሎ መንቀሳቀስ እንዳልቻላችሁ ትናገራላችሁ፡፡ በሌላ በኩል በትግራይ ህዝብ ሰፊ ተቀባይነት አግኝተናል ትላላችሁ፡፡ እንደውም በጥቂት ቀናት ቅስቀሳ ብቻ በምርጫ ኢህአዴግን ከስልጣን ልናወርደው እንችላለን ብላችኋል። እነዚህን ሃሳቦች እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው? እንግዲህ ኢህአዴግ ሁልጊዜ የትግራይ ህዝብ በስጋት እንዲኖር ነው የሚፈልገው፡፡ ከሌላው ህዝብ ተነጥሎ ፈርቶ እንዲኖር ነው የሚፈልገው፡፡ ኢህአዴግ ከሌለ የትግራይ ህዝብ እንደማይኖር አድርጐ ነው የሚቀሰቅሰው፡፡ በውስጥ ደግሞ የአረናን አባላት ለማጥላላት “አሸባሪ ናቸው፤ ከነፍጠኛ ጋር ነው የሚሰሩት፤ አኩርፈው ነው እንጂ የተለየ አጀንዳ የላቸውም” የመሳሰሉትን እያለ በፓርቲያችን ላይ ዘመቻውን ያጧጡፋል፡፡ ይህን አላምንም ያለውን ደግሞ በግልፅ ያስራል፡፡ አባሎቻችን በየጊዜው እየተሸበሩ ነው፡፡ ይታሠራሉ፣ ይገረፋሉ፣ አካላቸው ይጐድላል፡፡ ባስ ሲልም በ2002 ምርጫ ያጋጠሙ አይነት የአባላት ግድያ አለ፡፡ እኛ ግን ይህ በደል ስለደረሰብን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም፡፡

ትግሉን ወደፊት ማስኬድ ይህን መሰሉን ጭቆና ለማስቆም ብቸኛው አማራጫችን እንደሆነም እንገነዘባለን። በዚህ ስሌት ዱላው ሲበረታብን፣ እኛም እየበረታን ትግላችንን እናስቀጥላለን። ደርግም የወደቀው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ጭቆና ትግልን ያጠነክራል እንጂ ትግልን አይገድልም፡፡ ህዝቡም ይሄን ያውቃል፡፡ የትግራይ ህዝብ፤ ህወሓት ለትግሉ የተሠው ሠማዕታትን አላማ እንደካደ በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ የብሄር ተዋፅኦ ተመጣጣኝ እንዲሆን ተብለው ህወሓትን ባለመደገፋቸው ብቻ ከጦር ሠራዊት እንዲቀነሱ የተደረጉ አሉ፡፡ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የብሔር ተዋጽኦ ይኑር የሚለውን አትደግፉም ማለት ነው? በሠራዊት ግንባታው ላይ አሁንም የትግራይ ህዝብ ከከፈለው መስዋዕትነት አንፃር ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይሄን የምልህ እንደግለሰብ ባለኝ አቋም ነው እንጂ በፓርቲያችን የተያዘ አቋም አይደለም፡፡ በየግንባሩ ሲዋጉ የወደቁት ወንድሞቻችን አሉ፡፡ ሌላው በገበያ ላይ ተደብድቦ፣ ተገደሎ ህዝቡ የከፈለው መስዋዕትነት አለ፣ እንዲሁም በከተማ የነበረው ትግል አለ፡፡ እነዚህ መስዋዕትነቶች አጉል መቅረት የለባቸውም፤ ወደላቀ ደረጃ መሸጋገር አለባቸው፡፡ በእርግጥም ኢህአዴግ እንደሚለው የተመጣጠነ ሠራዊት ለመገንባት እነዚህን ለትግሉ መስዋዕት የሆኑ ወገኖችን መቀነስ ተገቢ አይደለም፡፡ በቀጥታ ነበር መቀጠል የነበረባቸው፡፡ ቅነሣው ሲካሄድ ደግሞ የእነሱ ታዛዥ ያልሆኑትንና በኤርትራ ላይ ከነሱ የተለየ አቋም ያላቸው ተመርጠው ነው፡፡ ለነገሩ አጠቃላይ የስርአቱ ስትራቴጂ የታዛዥነትን መንፈስ ማስረጽ ነው፡፡ ለነሱ ታዛዥ ያልሆነ ምክንያት ተፈልጐለት ይገለላል፡፡

እኛ እንደ አቋም የግድ ከዚህኛው ብሔር ይሄን ያህል እያልን ቀመር ባናወጣለትም ሠራዊቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተዋጽኦ እንዲኖርበት እንፈልጋለን፡፡ የፓርቲያችሁ አንዳንድ አባላት የነበሩ ከሠላማዊ ትግል ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት ኤርትራ ሄደው ስልጠና እየወሰዱ ነው ይባላል? ይሄን መደበቅ አይቻልም፡፡ ከኛ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር የነበረ ጐይቶም በርሄ የሚባል ሰው የትኛውን ቡድን እንደተቀላቀለ ባላውቅም ወደ ኤርትራ እንደሄደ ይታወቃል፡፡ እኔ ይሄ አካሄድ ይጠቅማል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እዚሁ የኢህአዴግን ጫና ተቋቁሞ ትግል ማድረግ አሁንም ይቻላል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥም ሁሉም ክፉዎች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መጥበብ የሚያሳስባቸው ይኖራሉ የሚል ግምት ነው ያለኝ፡፡ የተከፈለውን መስዋዕትነት እና አሁን እየተደረገ ያለውን እያዩ የሚብከነከኑ የኢህአዴግ አባላት እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ መሣሪያ ማንሣትን አማራጭ የሚያደርጉ ወገኖች ተቀባይነት የላቸውም፤ ዞሮ ዞሮ በጠላት ሃይል ነው የሚደገፉት፡፡

የሠላማዊ ትግላችሁ እርምጃ ለውጤት ያበቃናል ብላችሁ ታምናላችሁ? ኢህአዴግ የፖለቲካ ሜዳውን ከከፈተው አሁን ያሉት ተቃዋሚዎች እንደሚያሸንፉት ጥርጥር የለውም፡፡ ህዝቡ ከሚገባው በላይ ኢህአዴግን ጠልቶታል ብዬ ነው የማስበው፡፡ የኢህአዴግ የመከፋፈል፣ አንድን ህዝብ አንዱ በጥርጣሬ አይን እንዲመለከተው የሚያደርገው ሁሉ በህዝቡ ተነቅቶበታል፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ወደ አንድ አቅጣጫ የመምጣት ሂደቱ አሁን ላይ የተሻለ ይመስላል፡፡ ተቃዋሚዎች ያለንን የፖሊሲ ልዩነት እያጠበብን፣ ወደ አንድ አቅጣጫ እየመጣን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለውጡ በዚህ ብቻ አይደለም የሚመጣው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥም ቅን አሣቢ የሆኑ፣ ለህዝብ የሚቆም ህሊና ያላቸው ወገኖች ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሸምቀቆው እየበረታ ሲሄድ “ይሄማ ትክክል አይደለም” ብለው የትግሉ አላማ መካዱን የሚያስታውሱ ሰዎች ይፈጠራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግን መቀየር አለበት። ህዝብ እየጠላው ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች በራሱ በኢህአዴግ ውስጥም እንዳሉ ጥርጥር የለኝም፡፡ መሠረታዊ ጥያቄው ኢህአዴግ እንዴት ስልጣን ይልቀቅ የሚለው ነው፡፡ በመሣሪያ ከሆነ ለሃገሪቱም ለሁላችንም ኪሣራ ነው፡፡ በሠላማዊ መንገድ ከሆነ ግን ለኢህአዴግም ወርቃማ ታሪክ፣ ለአገሪቱም ታላቅ ድል ነው፡፡ እኔ አቶ መለስ በስልጣን ላይ እያሉ በመሞታቸው በጣም ነው የማዝነው፡፡ በጣምም ይቆጨኛል፡፡ የትግሉ አላማ ይሄ አልነበረም፡፡ እሣቸው ግን የእነ አፄ ዮሐንስን፣ ሚኒልክን፣ ሃይለስላሴን ታሪክ ነው የደገሙት። አዲስ ነገር አላመጡም፡፡

ከስልጣኑ ገለል ብለው ህልፈታቸው ቢሆን ደስታዬ ነበር፡፡ በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ በጣም የተከበሩ የመሆን እድልም ያገኙ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ተምሮ ታሪኩን ላለማበላሸት መስራት አለበት እላለሁ፡፡ እሱም እንደመሪው ሞቴን በስልጣን ላይ ያድርገው ካለ፣ በገዛ እጁ ታሪኩን እንዳበላሸ እቆጥረዋለሁ። ራሱን ተቃዋሚ ሆኖ ለማየት መጓጓት እንዳለበት ይሠማኛል፡፡ ከኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ እንደሚጀምር ያያችሁት ፍንጭ ይኖር ይሆን በተለይ በህወሓት በኩል የመከፋፈል ነገር አለ ማለት ነው? ይፋ የወጣ ነገር ባይኖርም በግሌ ከአንዳንዶች ጋር ስንወያይ “አቶ መለስ በስልጣን ላይ ሙጭጭ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉ የትግሉ አላማን የሣተ ነው፤ በእርግጥም ከስልጣን ወርደው ህይወታቸው ቢያልፍ ለራሳቸውም ለሀገራቸውም ታሪክ ይሆን ነበር፡፡ የትግሉ ፍሬም ውጤቱ ያምር ነበር” እያሉ የሚቆጩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ የሚቆጩ ከሆነ፣ ህወሓት ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እንዳለ እንዲሞት አይፈልጉም ማለት ነው፡፡ እኔ በ2007 ምርጫ ኢህአዴግ በምርጫ ተሸንፎ በሠላም ከስልጣን ይለቃል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከለቀቀ በኋላ ደግሞ ሰዶ ማሳደድ ሣይሆን እንደማንኛውም ተቃዋሚ ሆኖ እናየዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንደምትሉት ግን ኢህአዴግን በምርጫ አሸንፎ ስልጣን መያዝ ቀላል ነው? በሚገባ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ዋናው የሠላማዊ ትግል መንገድ የተደላደለ ይሁን፣ ተቃዋሚዎችም ከልባቸው ከታገሉ በእርግጥም ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ የአንድ ወር ስራ በቂ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ውስጥም ሃገር ለመምራት፣ ሚኒስትር ለመሆን እና ህዝብን ለማስተዳደር አቅም ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እንኳን ህዝቡ ኢህአዴግም በሚገባ ይገነዘበዋል፡፡ ኢህአዴግ እኮ ውጤቱን የሚለካው ግሎባላይዜሽን ባመጣቸው ነገሮች ነው፡፡ ሞባይል ለገበሬው አከፋፈልኩ፣ መብራት አስገባሁ ነው የሚለው፡፡ አረና የግንቦት 20 በዓልን ያከብራል? ሠማዕታትንስ እንደ ህወሓት በየአመቱ ይዘክራል? ትግሉ የተጀመረበት የካቲት 11 እና ትግሉ ፍፃሜ ያገኘበት ግንቦት 20 በህወሓት ኢህአዴግ የሚከበሩ ናቸው፡፡ አረና እንደፓርቲ እስካሁን ግንቦት 20ን ለይቶ አክብሮ አያውቅም፡፡ ግን እንደ ግለሰብ የምኮራበት ሊሆን ይችላል፡፡ በግንቦት 20 ምክንያት ቀለበት መንገድ ተሠራ፣ በግንቦት 20 ምክንያት የባቡር ሃዲድ እየተሠራ ነው፣ የአባይ ግድብ የግንቦት 20 ፍሬ ነው ከተባልኩ ግን ፈጽሞ አልቀበለውም። በተለያዩ የቀደሙ መንግስታትም ቢሆን እነዚህን የመሠሉ የልማት አቅጣጫዎች ነበሩ፡፡

አሁን በዚህ ዘመን አፄዎቹ መሪ ቢሆኑም የሚሠሯቸውን ነው ኢህአዴግ እየሠራ ያለው፤ የተለየ ታሪክ አልፈጠረም፡፡ የግንቦት 20 ፍሬን በዚህ አይደለም የምለካው፡፡ ኢህአዴግ በሠላማዊ መንገድ ከስልጣን ሲወገድ ነው ትግሉ ፍሬ አፍርቷል የምለው፡፡ በሠላማዊ መንገድ ስልጣን ማሸጋገር ከተጀመረ የካቲት 11 እና ግንቦት 20 ልዩ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከመስከረም 2 የሚለዩብኝ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ግንቦት 20 ፍሬ አፍርቷል ብዬ አላምንም፡፡ ግን ሠላማዊ ሽግግር የሚደረግና የሠማዕታቱ ህልም የሚፈታ ከሆነና ግንቦት 20 ትልቅ በአል ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

በደሌ ለኮንሰርቶቹ 25 ሚ.ብር መድቦ ነበር ኮንሰርቶቹ ቢሰረዙም ውዝግቡ አልተቋጨም የቴዲ ደጋፊዎች የአፀፋ ዘመቻ ጀምረዋል

አለማቀፉ የኔዘርላንድ ኩባንያ ሄኒከን ከሚያስተዳድረው በደሌ ቢራ ጋር በመሆን በበርካታ ከተሞች ሊካሄዱ የነበሩ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርቶች ቢሰረዙም፣ ቴዲ አፍሮ በውላቸው መሰረት 4.5 ሚ. ብር እንደሚከፈለው ምንጮች ገለፁ፡፡ እስካሁን በአገር ውስጥ ከተካሄዱ ኮንሰርቶች በላቀና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በድሬዳዋ ተጀምሮ በርካታ ከተሞችን እንዲያዳርስ ታስቦ የተፈረመው የቴዲ አፍሮና የበደሌ ቢራ ስምምነት፤ በኢንተርኔት በተካሄደ የተቃውሞ ዘመቻ ታውኮ ነው ሳምንት ሳይሞላው የፈረሰው፡፡ ከ20ሺ በላይ ሰዎች በኢንተርኔት በተሰባሰበ ድምጽ ለተካሄደው የተቃውሞ ዘመቻና ውዝግብ እንደመነሻ ሆኖ የሚጠቀሰው ዐረፍተ ነገር “የአፄ ምኒልክ ጦርነቶች ቅዱስ ናቸው” የሚል አባባል ሲሆን፤ ቴዲ አፍሮ የኔ አባባል አይደለም በማለት ማስተባበሉ ይታወሳል፡፡ በምኒልክ ጦርነት ብዙ ሰው አልቋል በሚል የገፋው ተቃውሞ፤ በደሌ ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ጋር እንዳይተባበር ለሄኒከን ኩባንያ ጥያቄውን በማቅረብ እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡

የቀድሞ የአገሪቱ ነገሥታትን በተመለከተ፣ በተለይም በአፄ ምኒልክ ዙሪያ ከየአቅጣጫው “መልካም ወይም መጥፎ ናቸው” የሚባሉ የንጉሱ ድርጊቶች እየተጠቀሱ በተደጋጋሚ የፖለቲካ ጭቅጭቆች፤ መነሳታቸው አዲስ አይደለም፤ በአንድ በኩል ምኒልክ ለአገሪቱ ነፃነት፣ አንድነትና ሥልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ስልጣናቸውን ለማስፋፋት ባካሄዱት ጦርነት ግፍ ተፈጽሟል፤ ብዙ ህዝብ አልቋል ብለው የሚያወግዙም ጥቂት አይደሉም፡፡ በመሃል ደግሞ፣ በታሪክ የተከሰቱ ነገሮችን ወደኋላ ተመልሶ መለወጥ እንደማይቻል የሚገልፁ ወገኖች፤ መጥፎ ነገሮችን እያስተካከልን መልካም ነገሮች ላይ አተኩረን እየወረስን ማሳደግ አለብን በማለት ለማስታረቅ የሚሞክሩ አሉ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎችና ብሔረሰቦች የፈለቁ ጀግኖች ከአፄ ምኒልክ ጋር ለአገራቸው ነፃነትና ስልጣኔ ተጣጥረዋል በማለት ከአስታራቂዎቹ ወገን የተሰለፈው ቴዲ አፍሮ፤ የምኒልክን መቶኛ ሙት ዓመት በማስመልከት ለ“እንቁ” መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ ካለፈው ዘመን የሚወረሱ መልካም ታሪኮችን ጠቅሶ፣ የስህተቶችና የጥፋቶች መድሃኒት ፍቅር ነው በማለት የዘረዘራቸው ሃሳቦች ታትመው ወጥተዋል፡፡

“የአፄ ምኒልክ ጦርነቶች ቅዱስ ናቸው” የሚል ሃሳብ ግን እንዳልተናገረና በመጽሔቱ እንዳልታተመ በመጥቀስ ያስተባበለው ቴዲ አፍሮ፤ በኢንተርኔት የተሰራጨው አባባል እኔን አይወክልም ማለቱ ይታወሳል፡፡ የበደሌ ቢራ ባለቤት የሆነው የአለማችን ታዋቂ ቢራ አምራች ኩባንያ ሄኒከን፤ የበደሌ ቢራ ፋብሪካ እና የቴዲ አፍሮ ስምምነት እንዲሰረዝ የወሰነው፤ እንደብዙዎች ኩባንያዎች ሁሉ አደባባይ በወጣ ውስብስብ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ መዘፈቅ ባለመፈለጉ እንደሆነ ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ እነዚሁ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለፁት፤ በደሌ ቢራ “የፍቅር ጉዞ” በሚል ስያሜ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በበርካታ ከተሞች በተከታታይ ለሚካሄዱ ኮንሰርቶች 25ሚ. ብር ገደማ መድቦ ነበር፡፡ በደሌ 4.5 ሚ. ብር ለቴዲ አፍሮ ለመክፈል ተስማምቶ ውል ሲፈራረም 1.5 ሚ ብር የመጀመሪያ ክፍያ እንደፈፀመ የገለፁት እነዚሁ ምንጮች፤ በተለያዩ ከተሞች የሚቀርቡት ኮንሰርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ድምቀትን የተላበሱ ለማድረግ ከ20 ሚ. ብር በላይ ወጪ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ነበር ብለዋል፡፡ በደሌ ቢራ በራሱ መሪነት በሚያዘጋጃቸው ኮንሰርቶች ላይ፣ ከትኬት ሽያጭ የሚሰበሰበውን ገቢ ለበጐ አድራጐት ድርጅቶች ለመለገስ ሃሳብ እንደነበረውም ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡

በደሌ ከኮንሰርቶቹ ዝግጅት ራሱን ለማግለል ሲወስን፣ ቀደም ሲል የተፈራረመውን ውል በሚመለከት ከቴዲ አፍሮ ጋር ተደራድሮ የውል ማፍረሻ ስምምነት መፈራረሙንም ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡ የስምምነት ማፍረሻ ስምምነቱንና የክፍያውን መጠን በተመለከተ በደሌ እና ቴዲ አፍሮ ዝርዝር መግለጫ ካለመስጠታቸውም ባሻገር፣ ከሁሉም ወገኖች መረጃ ለማግኘት የተደረጉ ሙከራዎች አልተሳኩም። በድርድር የተቋጩ ጉዳዮች ላይ ተዋዋይ ወገኖች ጉዳዩን በተናጠል በይፋ ላለመግለጽ መስማማታቸው የተለመደ እንደሆነ ምንጮቹ ጠቅሰው፤ በደሌ የመጀመሪያ ክፍያውን ጨምሮ ለቴዲ አፍሮ 4.5 ሚ. ብር የሚከፍል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ብለዋል፡፡ በኢንተርኔት ሲካሄድ የነበረው ዘመቻ፣ የበደሌ እና የቴዲ አፍሮ የስምምነት ውል ከፈረሰ በኋላ ቢረግብም፤ ያንን ተከትለው የመጡ ሌሎች ዘመቻዎች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመቃወም የተጀመረው ዘመቻ፣ በተቃራኒ ኮንሰርቱን በመደገፍ ከተፈጠረው ሌላ ዘመቻ ጋር እንካ ሰላንቲያው ቀጥሏል፡፡ በቅርብ ጊዜ የሚካሄድ ኮንሰርት ባለመኖሩ ጭቅጭቁና ዘመቻው ምን ያህል የፌስቡክ ዕድምተኞችን ሳያሰለች ሊቀጥል እንደሚችል ገና አልታወቀም፡፡

Published in ዜና

            ሰማያዊ ፓርቲ፤ የምናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥልኝ አልፈቅድም ሲል ገለፀ፡፡ ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም፤ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ግንኙነት አላቸው፤ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ይሰራሉ” መባሉ በሰላማዊ ትግል የሚሳተፉ ፓርቲዎችን ለመወንጀል ያለመ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል አጣጥሎታል፡፡ “ዘጋቢ ፊልሙ፤ የፓርቲያችንን ከፍተኛ አመራሮችና የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ፎቶ እያሳየ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ይሰራሉ ማለቱን አጥብቀን እንቃወማለን” ያለው ፓርቲው፤ በህግ ስልጣን የተሰጠው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት “አሸባሪ” ብሎ ሳይፈርጀው ኢሳት ቴሌቪዥንን መጠቀም እንደሚያስከስስ እና ከአሸባሪዎች ጋር እንደመተባበር ተድርጐ መቅረቡ የዜጐችን መብት የሚጥስና ህገመንግስቱን የሚቃረን ነው ብሏል፡፡

“መንግስት የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን በቁጥጥር ስር በማዋሉና አንዳንድ የግል ጋዜጦችም በተጽእኖ ስር በመውደቃቸው፣ በአሸባሪነት እስካልተፈረጀ ድረስ በአማራጭነት በኢሳት ቴሌቪዥን እንናገራለን፤ ሃሳባችንንና ፕሮግራማችንን እናስተዋውቃለን፤ የደጋፊዎቻችንን ቁጥርም እናበዛለን” ያለው ፓርቲው፤ በኢሳት ቴሌቪዥን መናገር ያስከስሳል የሚለውን የመንግስት ማስፈራሪያ አንቀበለውም ሲል አጣጥሎታል፡፡ “የብሔራዊ ደህንነትና የፀረ ሽብር ግብረ - ሃይል አድርጐ ራሱን የሚጠራ አካል ይህን ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ብቃትም የህግ አግባብም የለውም” ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ይህ ራሱን ከህግ በላይ የሰቀለ አካል ያለ ምንም ገደብ ከሚሰራቸው ጥፋቶችና የመብት ጥሰቶች እንዲታቀብ እንጠይቃለን ብሏል፡፡ “የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ - ሃይል የሚሰራውን ስህተት ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተባባሪ ሆኖ እያገዘው ነው” ያለው ፓርቲው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለ ሰላማዊ ትግል፣ ስለፓርቲያቸው እንቅስቃሴና ስለ እቅዳቸው ለመግለጽ ኢሳትን እንደ አማራጭ እንዳይጠቀሙ ለማሸማቀቅና ከትግሉ ለማስወጣት የሚያደርገውን ጥረት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል፡፡

“መንግስት ከዚህ ቀደም በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩ ዜጐች ገና ሳይፈረድባቸው አሸባሪ እያለ ሲወነጅል በተደጋጋሚ ተቃውሟችንን አሰምተናል” ያለው ፓርቲው፤ ተፈርዶባቸው ከታሰሩ በኋላም መንግስት ያልተባለ ነገር እየጨመረ ነው ሲል ነቅፏል፡፡ ፓርቲው በዋቢነትም “ርዕዮት አለሙ የሽብር ድርጊት ልትፈጽም እንደተዘጋጀች እጮኛዋ ስለሺ ሀጐስ መስክሮባታል” ተብሎ በዘጋቢ ፊልሙ የተገለፀው ፈጽሞ ውሸትና መሰረተቢስ ውንጀላ በመሆኑ ፓርቲው እንደሚቃወመው ገልጿል፡፡ “ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና ሌሎች ባለስልጣናት ቃለ ምልልስ አድርገው ያውቃሉ፤ የኢሳት ጋዜጠኞች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች የመንግስት ባለስልጣናት ምላሽ ሲሰጡ ሰምተናል” ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ “ኢሳት አሸባሪ ከሆነና የአሸባሪ ልሳን ከሆነ ባለስልጣናቱ ለምን ቃለ -ምልልስ ያደርጋሉ፣ ለምንስ ምላሽ ይሰጣሉ?” ሲል ጠይቋል፡፡ “እስካሁን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኢሳትን አሸባሪ ብሎ አልፈረጀውም፤ ኢሳትም የግንቦት ሰባት ልሳን ነኝ ብሎ አያውቅም” ያለው ፓርቲው፤ በአገር ውስጥ ያሉ አማራጮች እስካልሰፉ ድረስ፣ በኢሳት የምንናገረው ስለ ሽብርና ለሽብርተኞች ግብአት እስካልዋለ ድረስ በአማራጭ ሚዲያነት እንጠቀመዋለን ብሏል፡፡ መንግስት በተለያየ መንገድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርሰውን ማሸማቀቅ እንዲያቆም በማሳሰብም፤ የሚናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥለት እንደማይፈቅድ ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ለሆኑት ለአቶ ሬድዋን ሁሴንና ለሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሽመልስ ከማል በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

Published in ዜና

ደቡብ ሱዳንን ለመገንጠል የትጥቅ ትግሉን የመሩት ጆን ጋራንግ ከሞቱ በኋላ፤ ስልጣኑን እያጠናከረ በመጣው የሳልቫ ኪር ቡድን እና ከስልጣን በተገለለው የሬክ ማቻር ቡድን መካከል በተፈጠረው ግጭት፣ ኢትዮጵያዊው አምባሳደር ስዩም መስፍን ከቻይና ተጠርተው እያደራደሩ ሲሆን ሰሜን ሱዳን እንደ ኡጋንዳ ወደ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አዘነበለች፡፡ ሳልቫ ኪር የዲንቃ ጐሳ ተወላጅ፣ ተቃዋሚያቸው ሬክ ማቻር ደግሞ የኑዌር ተወላጅ እንደመሆናቸው ግጭቱም የጐሳ ልዩነት የተራገበበት እንደሆነ ቢገለጽም የሟቹ መሪ የጆን ጋራንግ ሚስት እና ልጃቸውን ጨምሮ ከስልጣን የተገለሉ የዲንቃ ጐሳ ተወላጆች ከተቃዋሚው ወገን ጋር እንደተሰለፉ ታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ ምክትላቸው የነበሩት ሬክ ማቻርን ጨምሮ በርካታ የትጥቅ ትግል ዘመን አንጋፋ መሪዎችን ከስልጣን በማግለል፣ በትጥቅ ትግል ያልነበሩ ባለሙያዎችን መሾማቸው የእርስ በርስ ቅራኔን እንዳባባሰ ይገለፃል። በሌላ በኩል ሬክ ማቻር ያቀነበባበሩት መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ተከትሎ ግጭቱ ሲፈነዳ፤ የኑዌር ጐሳ ተወላጅነታቸውን ከሳልቫኪር የዲንቃ ጐሳ ተወላጅነት ጋር በማነፃፀር የእርስ በርስ ግጭቱ ጐሳን የተከተለ ነው በማለት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ነገር ግን፣ የሟቹ መሪ የጆን ጋራንግ ሚስትና ወንድ ልጃቸው እንደ ፕሬዚዳንቱ የዲንቃ ጐሳ ተወላጆች ቢሆኑም፤ ከተቃዋሚው ሬክ ማቻር ጐን እንደተሰለፉ ታውቋል፡፡ በአምባሳደር ስዩም አስታራቂነት በሚካሄደው ድርድር ላይ ሬክ ማቻርን በመወከል ከመጡት ተደራዳሪዎች መካከል አንዱ የጆን ጋራንግ ልጅ ናቸው ተብሏል፡፡

ሳልቫ ኪርን ለመደገፍ ጦራቸውን እንደላኩ ከሚነገርላቸው የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ለመነጋገር፣ ሬክ ማቻርን በመወከል ወደ ካምፓላ የተጓዙትም የጆን ጋራንግ ሚስት እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ድርድሩን ከምትመራው ኢትዮጵያ ጋር ኬንያ በድጋፍ ሰጪነት የተሰለፈች ሲሆን፤ ሰሜን ሱዳን ከኡጋንዳ በተቃራኒ ተቃዋሚውን ወገን ትደግፋለች ተብሎ ሲነገር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር በድንገት ወደ ጁባ በመሄድ ከሰሜን እና ከደቡብ ሱዳን በተውጣጣ ጦር የነዳጅ ማውጫ አካባቢዎችን እንዲጠብቅ ከሳልቫኪር ጋር መስማማታቸው የብዙዎችን ግምት የሚያፈርስ ሆኗል። በትጥቅ ትግሉ መሪዎች መካከል ፀብ በተነሳ ቁጥር ወደ አልበሽር በመሄድ ይጠለሉ የነበሩት ሬክ ማቻር፤ ሰሞኑን በተፈጠረው የአልበሽር የሳልቫ ኪር ሽርክና ቅር እንደተሰኙ ተገልጿል፡፡

ከድርድሩ ጐን ለጐን የኢጋድ አደራዳሪ በመሆን የተሾሙት አምባሳደር ስዩም መስፍን ሬክ ማቻር ለተኩስ አቁም ስምምነት ባቀረቡት ቅድመ ሁኔታ መሰረት ወደ ጁባ በመሄድ እስረኞችን አነጋግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው ግጭት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሠማርተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ንብረታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በጋምቤላ በኩል የገቡት ኢትዮጵያውያን፤ ጊዜያዊ መጠለያ ከቆዩ በኋላ ወደየአካባቢያቸው እየሄዱ ሲሆን በማላካ እና ናስራ በተባሉ የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች መጋዘኖች እንደተዘረፈባቸው እና ያልተዘረፉ መጋዘኖቻቸውንም ጥለዋቸው እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን አለመረጋጋት ምክንያት ብዙ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ጋምቤላ እየገቡ ሲሆን ቁጥራቸው ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ይገኛል፡፡

Published in ዜና

ሪፖርቱ የአደጋ ምልክት ነው ብለዋል

“በኢትዮጵያ የሚታተሙ ሰባት የግል መጽሔቶች የጽንፈኛ ፖለቲካ ልሳናት ሆነዋል፤ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ህዝቡ በስርአቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ ያደርጋሉ” ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ያሠሩት የጥናት ሰነድ አመለከተ። የመጽሔቶቹ አዘጋጆች በበኩላቸው፤ ሪፖርቱን ያጣጣሉ ሲሆን ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡ ተቋማቱ ያስጠኗቸው አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ ዕንቁና ሊያ መጽሔቶች ሲሆኑ ከመስከረም 1 ቀን እስከ ህዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ባወጧቸው ህትመቶች ላይ በተደረገ የአዝማሚያ ትንተና መሠረት፤ መጽሔቶቹ የግል መገናኛ ብዙሃን ሳይሆኑ የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት ሆነዋል ተብሏል፡፡ መጽሔቶቹ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ይዘት፣ ህዝቡ በስርአቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉና የቀለም አብዮት ባስተናገዱ አገሮች የታየውን ቅኝት የሚከተሉ ሆነው ይታያሉ ብሏል - የጥናት ሰነዱ፡፡ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ በረቡዕ እትሙ የጥናት ሰነዱን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ “የሁሉም ጽሑፎች ይዘት ያተኮረው አሉታዊ ጉዳዮችን በማራገብ፣ መረጃዎችን አዛብቶ በማቅረብ፣ መንግስት በልማት፣ በሰላምና በዲሞክራሲ መስኮች ያመጣቸው ለውጦች የሌሉ በማስመሰል እንዲሁም ህዝቡ ከችግር ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ላይ በማሾፍና በማንኳሰስ ነው” ብሏል፡፡

ሁሉም መጽሔቶች የጋራ የመረጃ ምንጮችን ይጠቀማሉ ያለው ሰነዱ፤ የኒዮሊበራል አክራሪ ሃይሎች ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች፤ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ እጅግ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው የድሮ ስርአት ናፋቂዎችና በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ሲል ዘርዝሯቸዋል፡፡ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ የወጣውን የጥናት ሪፖርት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የግል መጽሔቶች አዘጋጆች፤ “የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት ሆነዋል” በሚል የወጣውን ትንተና ያጣጣሉት ሲሆን ጥናቱ ከዚህ ቀደም በታየው ልምድ መሠረት ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በሪፖርቱ ከተካተቱት መጽሔቶች መካከል የእንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ኤልያስ ገብሩ፤ “ጥናቱ የግሉን ፕሬስ ሆን ብሎ ለማሸማቀቅ እና ለመወንጀል የወጣ ነው” ሲል ተችቶታል፡፡

የጥናቱ ምንጭ የሆኑት ሁለቱ ተቋማት የመንግስት እንደመሆናቸው ገለልተኛ ናቸው ለማለት እቸገራለሁ ብሏል አዘጋጁ። “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት” የሚለው አገላለጽ በየአስራ አምስት ቀኑ የምትወጣውን “ዕንቁ” መጽሔትን አይወክልም፤ እኛ ከጋዜጠኝነት መርህ አኳያ እንሠራለን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን አይደለንም፤ ልንሆንም አንችልም ብሏል - ዋና አዘጋጁ፡፡ “ነገር ግን መንግስት አካሄዱን እንዲያስተካክል በመረጃ ተደግፈን እንተቻለን፣ የምንሠራው ህግና ስርአቱን አክብረን ነው” ሲል ገልጿል፡፡ ሪፖርቱ ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት መሆኑን የጠቀሰው ዋና አዘጋጁ፤ በተለይ መጽሔታቸውን ከሽብርተኝነት ጋር ማያያዙና የአመጽ ጥሪ አቅራቢ እያለ መወንጀሉ በስራቸው ላይ ከባድ ስጋት እንደሚፈጥርባቸው ገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት ያቀርቡ የነበሩ ጋዜጦችም የዚህ መሰሉ ውንጀላ ሠለባ ከሆኑ በኋላ ነው የተዘጉት ያለው ኤልያስ፤ የአሁኑ ሪፖርትም በመጽሔቶቹ ላይ ትልቅ አደጋ እንደተደቀነ የሚያመላክት ነው ብሏል፡፡

ከሰላሳ በላይ ገፆች ያሉትን የጥናት ሪፖርት እንዳነበበ የገለፀው የ “ቆንጆ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ካሣ በበኩሉ፤ መንግስት በቀጣዩ ምርጫ መጽሔቶች ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ በመፍራቱ ነው እንዲህ ያለ ሪፖርት ያወጣው ሲል ተናግሯል፡፡ መጽሔታችን ሚዛናዊነትን ጠብቆ የጋዜጠኝነት ሚናውን እየተወጣ እንጂ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን አይደለም ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ መንግስት የግሉ ፕሬስ ስላልተመቸው በርግገው ከሃገር ይሰደዳሉ በሚል እምነት ነው ይሄን ያደረገው ብሏል፡፡ በተለይም የአጥኝዎችን ማንነት ስንመለከት ዋና ስራቸው ዜናዎችን መቀበልና ማሠራጨት እንጂ ጥናት እያጠኑና እያስጠኑ፣ ደረጃ እንዲመድቡ ወይም እገሌ መጽሔት ይሄን ያህል በመቶ ሽብርተኝነትን ቀስቅሷል፣ ይሄን ያህል በመቶ ደግሞ የኢኮኖሚ እድገቱን ክዷል በሚል መፈረጅ አይደለም ሲል ተችቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ጋዜጦች የከሰሙበትን መንገድ ሲያስታውስም፤ “ብዙውን ጊዜ በአዲስ ዘመን ላይ ትችቶች በተከታታይ ይቀርባሉ፣ በቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ይሰራበታል፤ ከዚያም የህዝብ አስተያየት ተብሎ ይሰበስብና ይወገዛል፤ በሂደትም መጽሔቶቹንና ጋዜጦቹን በተለያዩ ክሶች በማዳከም እንዲከስሙ ይደረጋል” ያለው ቴዎድሮስ፤ ይህ መሰሉ ልምድ ባለበት ሁኔታ የዚህ ሪፖርት መውጣት ከፍተኛ ስጋት ይፈጥርብናል ብሏል፡፡

“ጥናቱን ያደረጉት የመንግስት ተቋማት ምን ለማለት እንደፈለጉ ይገባናል፤ እዚህች ሃገር ላይ የፕሬስ ነፃነት እንዲኖር አይፈልግም” ያለው የሳምንታዊው ሎሚ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፤ የጥናቱ ሪፖርት በግል መጽሔቶቹ ላይ እርምጃ ሊወሰድ መታሰቡን የሚጠቁም ነው ብሏል። “መጽሔቶች የጽንፈኛ ፖለቲካ ልሣናት ናቸው የተባለው እንደልብ የምናገኛቸውን የመረጃ ምንጮች ስለምንጠቀም ነው” ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ቃለ መጠይቅ ለመስራት ስንሞክር አናገኛቸውም ብሏል፡፡ ጥናቱን የሠሩት ተቋማት እኛን ከመፈረጅ ይልቅ በማተሚያ ቤቶች ያለብንን ችግርና ወረቀት ከውጭ ሀገር ለማስመጣት ያለውን ፈተና ለምን አያጠኑም ሲልም ጠይቋል - ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፡፡ የሊያ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር መላኩ አማረ በበኩሉ፤ በጥናቱ የተገለፀው ፍረጃ የመጽሔታቸውን ባህሪ እንደማያንፀባርቅ ገልፆ፤ ከሪፖርቱ በተቃራኒው የህብረተሰቡ ልሣን በመሆን እየሠሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጥናቱ ሚዛናዊነት የጐደለው ነው ያለው መላኩ፤ ጥናቱ ተደረገ የተባለባቸውን ያለፉትን ሶስት ወራት የመጽሔቶች ህትመት እንዳየና ከተወነጀሉበት “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት” አስተሳሰብ የራቁ ጉዳዮችን ሲያነሱ እንደነበር ማረጋገጡን ገልጿል። የፕሬስ ትልቁ አላማው የፖለቲካ አስተሳሰብና የህዝቡን ሃሳብ በነፃነት ማንሸራሸርና ማስተላለፍ ነው ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ ሪፖርቱ ምናልባትም የመጽሔቶቹ ቀጣይ ህልውና ላይ ቀይ ምልክት የሚያበራ በመሆኑ አዘጋጆችን የበለጠ የሚያሸማቅቅና ሥጋት ላይ የሚጥል ነው ብሏል። “መንግስት ፕሬሶችን ለማጥፋት ሲፈልግ ቀይ መብራት የሚያሳየው አዲስ ዘመን ላይ በሚወጡ ትችቶች ነው” ያለው መላኩ፤ የረቡዕ እለቱን የጋዜጣውን እትም ለየት የሚያደርገው ርዕሰ አንቀፁም ጭምር የኛ ጉዳይ ላይ ማተኮሩ ነው ብሏል፡፡ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዮሐንስ ካሣሁን ስለጉዳዩ በሰጠው አስተያየት፤ “የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣን” የሚለው ፍረጃ ለእኛም አዲስና ያልጠበቅነው ስለሆነ ተገርመናል፤ እኛ የምንሠራው የጋዜጠኝነትን ሙያ እንጂ ሌላ አይደለም ብሏል። “ቀደም ባሉት የአዲስ ዘመን እትሞች ላይ ‘አዲስ ጉዳይ’ን የሚያብጠለጥሉ ጽሑፎች ሲስተናገዱ ተመልክተናል፡፡ እኛም ለትችቶቹ መልስ ስንሰጥ ከርመናል፡፡ ይሄኛውም ከዚያ የተለየ አይሆንም” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡ በመጽሔቶቹ ላይ የተደረገው ጥናት ያተኮረው “የመንግስት ኀላፊዎችን የግል ስብዕና የሚነኩ፣ የአመጽ ጥሪዎችን የሚያስተላልፉ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ፣ የፖለቲካ ስርአቱን የሚያጨልሙ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚክዱና ህገመንግስቱን የሚያጣጥሉ” በሚሉ ነጥቦች ላይ ሲሆን በተከታታይ ህትመቶች የተነሳበት ድግግሞሽም ሆነ በአንድ ህትመት የተለያዩ አምዶች የተነሳበት ብዛት በቁጥር መተንተኑ ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

ከመንግስት 20 ሚ.ብር ይጠብቃል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በ5000ሚ. ብር ባለ 16 ፎቅ ህንፃ ሊያስገነባ እንደሆነ የገለፀ ሲሆን የህንፃ ማስገንቢያውን ገንዘብ “አንድ ብር ለሰብአዊነት” በሚል ዘመቻ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰብ መሆኑን አስታውቋል፡፡ መንግስት በሦስት አመት ውስጥ 20ሚ. ብር ሊሰጣቸው ቃል እንደገባላቸው የገለፁት የማህበሩ ሃላፊዎች፤ ህብረተሰቡ ከአንድ ብር አንስቶ አቅሙ የፈቀደለትን በመለገስ ለህንፃው ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በያዝነው ዓመት 127 ሚ.ብር ከህብረተሰቡ ለማሰባሰብ መታቀዱን የጠቆሙት የማህበሩ ሃላፊዎች፤ ህንፃው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በማከራየት ለማህበሩ የገቢ ምንጭነት እንደሚያገለግል አስታውቀዋል፡፡ ለማህበሩ የህንፃ ግንባታ ከ1 ብር ጀምሮ እርዳታ ለሚያደርግ ህጋዊ ደረሰኝ እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡ በሰብዓዊ እርዳታና ድጋፎች ላይ የተሰማራው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፤ ከተቋቋመ 78 አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት እንዳሉት ይታወቃል፡፡

Published in ዜና

የህዝብ ፊርማ ይዘን በፍ/ቤት ክስ እንመሰርታለን ብሏል
የፀረ-ሽብር አዋጁን በመቃወም “የሚሊዮኖች ድምፅ” በሚል መርሃግብር የህዝብ ፊርማ ሲያሠባስብ የቆየው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ህጉን ለማሠረዝ የሚያስችል በቂ ድምፅ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ከ1ሚ. በላይ ፊርማ አሰባስቤአለሁ ያለው ፓርቲው፤ የህዝቡን ፊርማ በመያዝ ክስ እንደሚመሰርት ገልጿል፡፡
ፓርቲው ለ3 ወራት ባካሄደው ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ የፀረ ሽብር አዋጁን ለማሰረዝ የሚያስችል ድምጽ ማግኘቱን የገለፁት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ አሁንም ድረስ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በኦንላይን እየፈረሙ በመሆኑ አጠቃላይ የፈራሚዎቹን ቁጥር መግለጽ ቢያዳግትም፣ እስካሁን ከ1 ሚሊዮን በላይ ፊርማ መሰባሰቡን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ የተሰባሰበው የፊርማ ብዛት ፓርቲው ከገመተው በላይ ስኬት መቀዳጀቱን ይጠቁማል ያሉት ሃላፊው፤ በአጠቃላይ የተሰበሰበውን የፊርማ ብዛት ፓርቲያቸው በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
“አንድነት” ፓርቲ በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ያለው አቋም ሙሉ ለሙሉ ይሰረዝ የሚል እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ የተሰበሰበውን የህዝብ ፊርማ ለፍ/ቤት በማቅረብ፣ ህጉ ከህገመንግስቱ ጋር እንደሚጋጭና የዜጐችን መሠረታዊ መብት እንደሚጥስ በመጥቀስ ክስ እንመሠርታለን ብለዋል። ከፍ/ቤት ቀጥሎም ጉዳዩን ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ የገለፁት ሃላፊው፤ ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም በህዝብ ድምፅ ህግ የማሠረዝ እንቅስቃሴ ተሞክሮ ባያውቅም ፍ/ቤቶች እና  ምክር ቤቱ የፓርቲውንና የፈራሚውን ህዝብ ጥያቄ ተቀብለው ውሳኔ እንደሚሰጡ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐችን ድምፅ ዝም ብለን ሜዳ ላይ አንጥልም ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የፍ/ቤቶች ገለልተኝነት አጠያያቂ ከመሆኑ አንፃር ጥያቄው ተቀባይነት ባያገኝ እንኳን ህዝቡ የተሣተፈበት የፓርቲው የትግል አካል ተደርጐ ለታሪክ ተመዝግቦ ይቀመጣል ብለዋል፡፡
ህጉ ይሠረዝ የሚል አቋማቸው በመንግስት በኩል “ለሽብርተኝነት ድጋፍ ከመስጠት አይለይም” የሚል ትችት ማስከተሉን ያነሳንባቸው አቶ ዳንኤል በሰጡት ምላሽ፤ “የወንጀለኛ ህጉ አልበቃ ብሎ የፀረ-ሽብር ህግ ራሱን ችሎ የሚያስፈልግ ከሆነም ከውጭ የተቀዳ ሣይሆን ከፍተኛ የህግ ባለሙያዎች የተሣተፉበት እንዲሁም ህብረተሠቡ በየደረጃው ውይይት ያደረገበትና የመላውን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ ህግ ማውጣት ይቻላል” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡  ፓርቲያቸው በስራ ላይ ያለው የፀረ - ሽብር አዋጅ እንዲሠረዝ ጥብቅ አቋም የያዘበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ “ህጉ ከወጣ በኋላ በቀጥታ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ለማስፈራሪያና ለማጥቂያ በመዋሉ ነው” ብለዋል - ሃላፊው፡፡  
የፀረ - ሽብር ህጉን ለማሠረዝ የሚያስችል ድምጽ ማሠባሠብ መቻላችን አገሪቱ አቤቱታ ለማቅረብ ምቹ የዲሞክራሲ ቁመና ላይ መገኘቷን ፈፅሞ አያመለክትም ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ፓርቲያቸው የፀረ-ሽብር አዋጁን በተመለከተ ህጋዊ መነሻ ይዞ ለመላ ኢትዮጵያውያን በይፋ የተቃውሞ ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም ሠሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተላለፈ በሚገኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ “አንድነት ፀረ-ሠላም ለማድረግ መሞከሩ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ በ97 ምርጫ ትልቁ የኢህአዴግ አጀንዳ “ኢንተርሃሞይ” እንደነበር ያስታወሱት ሃላፊው፤ በ2002 ምርጫ “ተቃዋሚዎች አጀንዳ የላቸውም” ወደሚል ቅስቀሣ መቀየሩን ጠቁመው፤ ለቀጣዩ ዓመት ምርጫ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን “ፀረ-ሠላም ናቸው” የማለት እንቅስቃሴ  ከወዲሁ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲው፤ ከዚህ ቀደም ሠላማዊ ሠልፍ እንዳላደርግ እንቅፋት ሆነውብኛል ባላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ፖሊስ ላይ ክሡን ለመመስረት በዝግጅት ላይ እንደሆነ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡ በዛሬው እለት አዲስ በተመረጡት የፓርቲው ሊቀመንበር በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ይፋ የሚደረገው የፓርቲው ካቢኔ የመጀመሪያ ስራ፣ የፀረ - ሽብር አዋጁን ማሠረዝ እና ክስ የሚቀርብባቸው አካላት ላይ ክስ መመስረት እንደሚሆን ሃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡   

Published in ዜና
Page 10 of 14