የአፍሪካ ሞዛይክ የፋሽንና የባህል ትርኢት በሚቀጥለው አርብ ምሽት በሸራተን አዲስ የሚካሄድ ሲሆን በዝግጅቱ አለማቀፍ የፋሽን ሞዴሎችና ዲዛይነሮች ይሳተፋሉ፡፡ የአፍሪካን ሞዛይክ ዳይሬክተር አና ጌታነህ እንደገለፀችው፤ አስራ አምስት የውጪና የሀገር ውስጥ ዲዛይነሮች በሚሳተፉበት ትርኢት፤ እውቅ የዘርፉ  ባለሞያዎች ከኒውዮርክ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከሴኔጋል ይመጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጥ ሃያ ሞዴሎች የሚሳተፉበት የፋሽን ትርኢት ምሽት የመግቢያ ዋጋ 500 ብር ሲሆን ገቢው ከአዲስ አበባ 55 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አለልቱ ከተማ ለሚካሄደው የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት ይውላል ተብሏል፡፡ የአፍሪካ ሞዛይክ የፋሽንና የባህል ትርኢት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የአሁኑ ለአስራ አራተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡

         የዛሬ ሣምንት ቅዳሜ ነው፡፡ አብዛኛውን ቅዳሜዎቼን እንደማሣልፋቸው ሁሉ የዕለቱን ጋዜጦችና መጽሔቶች ሰብስቤ፣ ዘወትር መልካም ቡና ከማገኝበት  ቤት ተቀምጫለሁ፡፡
በወፍ በረር የማያቸውን አይቼ በዕለቱ የወጣውን ሳምንታዊውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ መመልከት ጀመርኩኝና… ገጽ 11 ላይ ደረስኩ፡፡ “ቅኔን ሳያውቁ ቅኔን መፍታት ታላቅ ድፍረት” ይላል - የጽሑፉ ርዕስ፡፡ ፀሐፊው በጋዜጣው ላይ በተገለፀው ስማቸው “ጵርስፎራ ዘዋሸራ” ይባላሉ፡፡ የስማቸው የቃሉ የትመጣ… ከግሪክ ሲሆን ቁርባን እንደማለት ነው፡፡ በሌላ ፍችውም ምዕመናን የሚጥሉት መባኔ ማለት ነው፡፡  
ወደ ውስጥ ከመጓዜ በፊት እንደዚህ በሽፍን ስም ሃሳብን መግለጽ ለምን አስፈለገ ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ ሁለት መልሶች ወደ ህሊናዬ መጡ፡፡ አንደኛው እውነተኛ ፍርሃት ነው፡፡ አንዳንዴ እውነተኛ አስተያየት (ሂስን) መቀበል የማይችሉ ሰዎች፤ ፀሐፊው ላይ አጉል ጥላቻ እንዳያተርፉ… ሊናገሩ የፈለጉትንም በቅንነትና በእውነት ለመግለጽ ስለማይደፍሩ ሲሆን ሁለተኛው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ደረት የማያቀና፣ ዐይን የማያስገልጥ፣ ገበሬ አስደንግጥ ሃሳብ ከሆነ፣ በራስ ላለማፈር በህዝብም ዘንድ ላለመናቅ፣ የድንገቴው ስም መልካም ግርዶሽ ይሆናል፡፡ ግዳይ በማይጥል ሃሳብ መፎከር አይቻልምና፡፡
ቡናዬን እየተጐነጨሁ ጵርስፎራ ዘዋሸራ፤ “ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት፤ ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታትና ሊቃውንት” በሚል ራሴ ያዘጋጀሁት መጽሐፍ ላይ የሰጡትን አስተያየት ደጋግሜ አነበብሁት፡፡ እናም አዘንኩ -ለ “ጵርስፎራ ዘዋሸራ፡፡”
ፀሐፊው ልጅ ይሁኑ አዋቂ፣ ምሁር ይሁኑ ሰነፍ ለማወቅ አቃተኝ፡፡ ጽሑፋቸው እንደ ሊቅ ይጀምራል፡፡ ነገር ግን ያሳዝናል… እንደ መሃይም ይፈጽማል፡፡ የሂስ ይዞታቸው ልኩን በጠበቀ ሁኔታ እንደ አዋቂ ይንደረደራል፡፡ ምን ያደርጋል… ሃሳባቸው ብዙም ሳይዘልቅ በሂስ እንዳልተነሳ በግለ ሂስ ጭቃ ላይ ይተኛል፡፡
ጵርስፎራ ለማሄስ የገለጡትን መጽሐፍ፤ መንገድ ላይ መፃሕፍትን ገረፈ ገረፍ እንደሚያደርግ ሰው እንኳ የተመለከቱት አይመስለኝም፡፡ የገዛ ጽሑፋቸው እንደሚነግረንም መጽሐፉን ለመግዛት ሲሉ ያቋረጡትን ፀሎት ለመጨረስ አስበው ይሆናል፡፡ መጽሐፉን ያገኙበትን አጋጣሚ ሲተርኩልንም እንዲህ ይላሉ:-
“…ሰሞኑን ከዋሸራ ማርያም ተነስቼ ወደ ባሕር ዳር የምሄድበት ጉዳይ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ባሕር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ለፀሎት እንደቆምኩ አንድ መጽሐፍ አዟሪ የታላቁን የቅኔ ፈላስፋ የተዋነይን ስም የያዘ መጽሐፍ አሳየኝ፡፡ ወዲያው ከፀሎቴ ተናጠብኩና መጽሐፉን ተቀብዬ በዓይነ ገመድ አየት አየት አደረግሁት፡፡ የዋሸራ ሰው ደግሞ ከገንዘብ ይልቅ ለቅኔ ስሱ ስለሆነ ዋጋው ስንት ነው ብዬ መጽሐፍ አዝዋሪውን ጠየቅሁት…”
ጵርስፎራ እንዲህ ናቸው፡፡ ፀሎት አቋርጠው በተስኪያን በር ላይ መጽሐፍ የሚመለከቱ፣ መንገድ ለተመለከቱት የወፍ በረር ምልከታ ሂስ ለመስጠት የሚተጉ፣ በአመክንዮ ሳይሆን በጉንጭ አልፋ ክርክር የሚያምኑ የሚመስሉ፣ ልብ ብለው ላላስተዋሉት ጉዳይ ብዕር የሚያነሱ፣ ለማረም ሳይሆን ለማማረር፣ ለማስገንዘብ ሳይሆን ለመሳደብ ዕንቅልፍ ለምኔ ያሉ፤ ከሚበጀው ይልቅ የማይበጀውን ለመናገር የሚታትሩ፡፡
“ለምሳሌ አንዲት ባለ ሁለት ቤት ጉባዔ ቃና ቅኔ በአንድ ገጽ ላይ ሰፍራ፣ ሌላው ወረቀት ባዶ ነው፡፡ በሚቀጥለው ገጽ ግን አቶ ኤፍሬም የቅኔያቱን ሰማዊ ፍቺ ወደ ግጥም ቀይሮ፤ ከባለቅኔው እሳቤ ውጭ ቃላት ደርድሮ ገጹን ለመሙላት ሞክሯል” (አጽንኦት የራሴ)
እዚህ ጋ ነው እንግዲህ አቶ ጵርስፎራ፤ የቁልቁለት መንገዳቸውን የሚጀምሩት፡፡ እዚህ ላይ ጀምሮ ነው እንደ ምሁር አንኳኩተው እንደ ወገበ - ነጭ የሚዘጉት፡፡ እንግዲህ ፀሐፊው እንደሚናገሩት ከሆነ፤ እኔ የተረጐምኩት የቅኔያቱን ሰማዊ ፍች ነው፡፡ ነገር ግን ወርቁ ምን እንደነበር አያሳዩንም አያብራሩልንም፡፡ ሃሳባቸው ምስክር አልባ ነው። እንዲሁም ለእርሳቸው አስተውሎት፤ የእኔ ትርጉም ከባለ ቅኔው እሳቤ ውጭ ነው፡፡ አሁንም አይገልፁልንም… ባለ ቅኔው ምን ሊል እንደፈለገና እኔ የቱ ጋ ውሉን እንደሳትኩ።  እኔ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የፀሐፊውን ምሁራዊነት የተጠራጠርኩት።
ያለ አስረጅ ያለ ምሥክር እንኳን የመጽሐፍ ሂስ ወንጀልም ተቀባይነት የለውም (አስመ ስምዓ ክልዔቱ ወሠለስቱ እሙን ውእቱ) ነውና ነገሩ፡፡ “እኔ የቅኔ እውቀት አለኝና እናንተ (አንባቢያን) እውቀቱ ስለሌላችሁ ስሙኝ፤ ልክ ነኝ” አይሠራም፡፡ አሁን ያለው ዘመን የማደናገር ሳይሆን የመማማር ነውና፡፡
አሁንም ፀሐፊ ጵርስፎራ ላልገባቸውና በማያገባቸው ሌላ ስህተት ውስጥ ወድቀው እናገኛቸዋለን፡፡ ማስረጃ ከራሳቸው ጽሑፍ፡- “የመጽሐፉ ርዕስ “ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሊቃውንት’ ይላል፡፡ አሳታሚው “ሻማ ቡክስ” ነው። የመጽሐፉ ገጽ 190 ሲሆን ቅኔያቱ ሁለት ሦስት እየሆኑ በየገጹ ቢስተናገዱ ኖሮ መጽሐፉ ከ50 እና 60 ገጽ አይበልጥም ነበር፡፡ ስለዚህ አንባቢው ለዚህ መጽሐፍ 100 ብር የሚከፍለው ለባዶው ወረቀት ጭምር ነው፡፡…”
ምናልባት ጵርስፎራ ስለ መጽሐፉ ህትመት ሁኔታ ባያውቁ ነው እንጂ መጽሐፉ እርሳቸው እንደሚሉት ሁለትና ሦስት ሆኖ አጥሮ ቢታተም ጥቅሙ ለእኔ እንጂ ለማንም አልነበረም፡፡ የመጽሐፉ ገጽ በበዛ ቁጥር ምን እንደሚያስከትል አታሚና አሳታሚ ያውቁታል፡፡ ነገር ግን አንድ ሥራ ከገንዘብ አኳያ ብቻ ሳይሆን ከውበት (Aesthetics) ጭምር በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባ ፀሐፊው የዘነጉት ይመስለኛል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ግን በመንገድ ላይ የገረፍ ገረፍ ንባብ ይህን ሁሉ ማለታቸው ነው፡፡
ፀሐፊው በድጋሚ እኔ ቅኔያቱን የተረጐምኩት ከፋንታሲ አኳያ እንጂ የባለቅኔዎቹን ሃሳብ እንደሳትሁ ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ሃሳባቸው ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያግዝ ምንም ዐይነት አስረጅ ሐተታ (ገለፃ) አላቀረቡልንም፡፡
“የተዋነይን ሁለት መስመር ጉባዔ ቃና ሲተረጉም ከተዋነይ መንፈስና ዕሳቤ ውጭ ነው” ይላሉ፡፡ ነገር ግን እንዴት የሚለውን አያብራሩም፡፡ ቢያንስ እርሳቸው የሚያውቁትን የተዋነይን እሳቤ አይነግሩንም፡፡ እጅግ ያሳፍራል፡፡ ትክክል አለመሆኔንና በውርስ ትርጉም ስም እንደቀለድኩ ይገልፁና… ወርቁ ያልተነጠረበት ሠፈፉ ብቻ የሚታይበት አንድ ሥራ ለመጥቀስ ይሞክራሉ፡፡ (ገጽ 64፤ የቅኔ ቁጥር 21)
“ሙሌ በታቦር እመ ትሬዒ ደመና
ኢይሞስልከ እስኩ ዘይወር ድ መና
ረደተ መና ጥዑም አምጣነ ተርፈ በሊና” …የሚለውን ኤፍሬም ሰሙን እንጂ ወርቁን አላገኘውም እንዲሁ ቅኔውን ግጥም አደረገው ይላሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም አብራርተው አይነግሩንም፡፡ ቢያንስ ባለቅኔው ሊናገር የፈለገው “ወርቁ” ይሄ ነው አይሉም፡፡
“ኤፍሬም በመሰለው ግጥም ቢያደርገውም የራሱ ምስጢር አለው…” ምሥጢሩ ምንድነው? ቄሱም ዝም እርሳቸውም ዝም!! እኔ ግን ዝም አልልም፡፡ “አሜን የመሃይም ወግ ነውና” እንዳለ ባለ ቅኔ፡፡ እኔ እንዲህ ነበር የተረጐምኩት:-
አደራ ሙሴ ሆይ
ታቦር ተራራ ላይ ደመና ከታየህ
በፍፁም አይደለም ከግብጽ ስትወጣ እስራኤልን ይዘህ
መንገድ የበላኸው “መና” እንዳይመስልህ
ሕዝብህን ስትመራ
ያኔ በየሥፍራው
ሲዘንብ የነበረው ያ ጣፋጩ መና
አሁን ከዚህ የለም ቀርቷልና ሲና፡፡
ታላቁ የፊክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን እውቀትና ጥበብን ቀላልና ግልጽ አድርጐ መስጠት  እንደሚገባ እንዲህ ይናገራል:- “If you can’t explain it simply, you don’t understand it well enough” (ነገሩን ግልፅና ቀላል አድርገህ ማሣየት ካልቻልህ፣ ነገሩ በደንብ አልገባህም ማለት ነው፡፡) የዋሸራው ጵርስፎራ፤ ይሄ መንገድ ሣይጎረብጣቸው አይቀርም፡፡ እኔ መስማት የምፈልገውን ለምን አላሉም እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ራሳቸው የገባቸው የመሠላቸውን እንዴት መግለጽ አልቻሉም፡፡ ሊተቹ የፈለጉትን እንዴት ማሳየት ተሳናቸው ማለቴ ነው፡፡ ብዙም ሣይረፍድ ግን “ጵርስፎራ” ሃሣባቸውን መግለፅ ያልቻሉበት ምክንያት መገለጥ ይጀምራል፤ በራሳቸው ልሣን:-
…“ቅኔ በስማበለው አይታወቅም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ቤተልሔም አካባቢ የሚንገላወደው ሰሞነኛ አማርኛ ግጥም መግጠምና ቃላት መደርደር የቻለ ሁሉ ባለ ቅኔ ይሆን ነበር…፡፡”
“የሠው ልጅ አንደበቱ በተከፈተ ቁጥር ማንነቱ ይታያል፡፡” ይላሉ አባ ባህርይ፡፡ ጵርስፎራ እንዲህ ናቸው። በግዕዝ ከሚፃፍና ከሚባል ቅኔ በቀር በአማርኛ የተፃፉም ሆኑ የሚፃፉ ግጥሞች ለእርሳቸው ቁብ አይሠጣቸውም፡፡ ምናልባትም በአማርኛ የተፃፉ ግጥሞች በሙሉ ለእርሳቸው ቁምነገር አይደሉም፡፡ በአማርኛ ግጥም ላይ ታላላቁን ሚና የተጫወቱት ታላላቆቹ ሠዎች ሣይቀሩ ጉዳያቸው አይደሉም። በግዕዝ ብቻ ከተሠራ ሥራ በቀር … በአማርኛም ሆነ በሌላ ቋንቋ የተፃፉ ቅኔያት ቅኔያት አይደሉም፡፡ መቼም ይህን የመሠለ አስተያየት ከሊቅ አፍ የሚወጣ አይመሥለኝም፡፡
የአቶ ጵርስፎራ ታላቁ ማንነት መጉላት የሚጀምረው ከእኔ በላይ ማንም የለም በሚመሥለው ገለፃቸው፤ ከአስተያየት ይልቅ ሥድብ ላይ መንጠላጠል ሲጀምሩ ነው፡፡
“በአቶ ኤፍሬም ሥዩም ሥራ ላይ በእጅጉ ያሳፈረኝ ደግሞ የአቶ በላይ መኮንን ምሥክርነት ነው፡፡ አቶ የምለው ‘ሊቀ ህሩያን’ የተሰኘውን ማዕረግ የትኛው ሕጋዊ አካል እንደሠጣቸው ስለማላውቅ ነው፡፡”
አቶ ጵርስፎራ እስካሁን ሲንደረደሩ የነበሩት እዚህ ጋ ለመድረስ ሣይሆን አይቀርም፡፡ ቤተስኪያን ደጅ ላይ ቆመው ፀሎት ሢያደርሱ የነበሩት ሠው አልመስልህ አሉኝ፡፡ ምክንያቱም ፀሐይ የሞቃቸውን ሀገር ያወቃቸውን ታላቁን ሊቅ መሣደብና መዛለፍ ከፀሎተኛ አይጠበቅምና። የተነሡለትንም ዓላማ ዘንግቶ፣ በክፉ ቅናት በመነሣሣት የግል ቂምንና ጥላቻን ማንፀባረቅ ቢያስገምት እንጂ አያስደንቅምና፡፡
“በገፅ 164 ላይ የተጠቀሠው ጉባዔ ቃና ሥሙ በትክክል አልተጠቀሠም፤ የታላቁ ሊቅ የመሪ ጌታ ስመኝ ነው” ላሉት ሃሣቡን እንደሃሣብ ብሠማዎትም እውነት ነው ብዬ ለመቀበል ግን እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ ይህንን ቅኔ ያገኘሁት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባሣተመው የግዕዝ ቅኔያት ስብስብ ውስጥ ነውና፡፡
ይህም ሥህተት ሆኖ ከተገኘ ሥህተትነቱ የእኔ ሣይሆን የተቋሙ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ሀሣብዎትን ሲቋጩ ጥበቡ አባ አጋር የተቀኟትን ቅኔ አሥቀምጠዋል፡፡ ቅኔዋ በዲያቆናት ላይ የተሰነዘረች ዘለፋ ብትመሥልም አብዛኛው የዚህ ጋዜጣ አንባቢ እንደ እርስዎ የግዕዝ እውቀት ላይኖረው ስለሚችል ትርጉሙን እኔ ልተባበርዎት፡፡ እግረ መንገዴንም የእርስዎን ማንነት ሠዎች በቅኔዋ ውስጥ እንዲረዱልኝ ብዬ ነው፡፡  እናም የሸለሙኝን ዘለፋ እንዲህ ተርጉሜዋለሁ:-  
መወድስ
የመስከረም በሬ ዲያቆን ደርሦ የሚያገሳ፤
ውሻ መክፈልት እስመ ለከርሡ ሰጠጠ፣
ወለድማሁ አቢይ ውዊረ ጋዘና መለጦ፤
መሪር ልሳነዚአሁ እስመ ከነ ግብጦ፡፡
ወቃለ መምህር ለእመ ለሞኢ
ፈሪ ዲያቆን በረዊጽ ያመልጦ፡፡
ለዲያቆን ሂ ፀረ ተማሪ እንተ ያገንብጥ ቂጦ፤
ኤርትራ ቤተልሔም ከመፈርኦን ትውህጠ፡፡
አመኒ ነፀረ ዓይነዚአሁ ገልብጦ
መክፈልት ገለሞታ ለልበዚአሁ ትመስጦ፡፡
***
ትርጉሙ እነሆ:-
አበባው ሲፈካ
ጨፌው ሲያቆጠቁጥ
ሣርና ቅጠሉን ሲበላ እንደዋለ ሢግጥና ሲውጥ፤
የመስከረም በሬ የማንነቱ አምሳል
የሆነ ይህ ዲያቆን እኔ ማነኝ?... ይላል፡፡
ይኸው ተመልከቱት
ሆዱ-አምላኩም አይደል
መክፈልትን ማጋበስ ከርሡን ገልብጦታል
ቦርጩ ምን ያህላል? …
ይኸው …
ሌላው … ሌላው ቀርቶ …
ካፉ … ሚወጣው ቃል እንደምን ያስጠላል
ከኮሦ ከግብጦ በዕጥፍ ይመራል፡፡
አዎን ለዚህ ዲያቆን
ከተጋስኩ በቀር መች ዕውቀት ዘልቆታል
ፀጉሩን ዕንኳ ሣይቀር የኩነኔ ሸክም መልጦ ጨርሦታል።
እንዴት ያሣዝናል?
ምክንያቱም
ለእውቀት ባዶ ነውና ለቅኔና ለዜማ
ፈርቶ መሸሽ ይቀናዋል የመምህርን ቃል ሢሠማ
በርግጥ ለዚህ ዲያቆን
እውቀትን የሚሻ
የቆሎ ተማሪ ጥንትም ጠላቱ ነው
ሥለዚህም …
ፈሪው ዲያቆን
ተማሪውን ባየ ቁጥር ቂጡን አገላብጦ መሸሽ ነው ሚቀናው፡፡
ሥለ-ፈራም …
ከመቅደስ በአፍዐ ቤተ-ልሄም አንድ ራሡን ይደብቃል
አንድ ራሡን ይሸሽጋል፡፡
ያሳዝናል …!!
ታድያ ግና የሚገርመው
ለዚህ ፈሪ ሰነፍ ዲያቆን… ታላቅ ዕውቀት የሚመሥለው
እንደ ገለሞታ እንደ ቡና ቤት ሴት
ሁሉ እንደሚተኛት …
ዐይኑን ከፍቶ መመኘት ነው… ማሥተዋል ነው የዘኬን ቤት
የሠማንያ ያርባ መክፈልት፡፡
እንግዲህ ይህ ነው… ጵርስፎራ ዘዋሸራን እንደ ሊቅ አንኳኩቶ እንደ ሰነፍ ዘግቶ ያሰኛቸው፡፡ ምክንያቱም የሠውዬው የፅሁፋቸው ትልቁ አላማ (motif) ልክ አለመሆኔን ማረጋገጥ ብቻ ነበርና፡፡ ልክ እንዳልሆንኩ ብቻ። ለካ ፊሪሳውያን … ዘንድሮም አሉ፤ ካባቸውን አውልቀው። ሱፍ አጥልቀው፡፡ ሳምሶናይት አንጠልጥለው… አለ ያገሬ ሠው፡፡


Published in ጥበብ
Sunday, 05 January 2014 00:00

ከልሂቁ አንደበት…

የህይወት  ትርጉም
የህይወት ትርጉም ምንድርነው? የሰው ልጅም ሆነ ማንኛውም ፍጥረት የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ፣ ወደ ኃይማኖተኝነት ፅንፍ ሊመራ ይችላል፡፡ ግን አለመጠየቅስ ይቻላልን? ጥያቄው ተጠይቋል እንበል፤እኔ ብሆን መላሹ…አንድ ለራሱ ህይወት ላቅ ያለ ስፍራ የሚሰጥ፣ ሆኖም ግን ለመሰሉ ሰውና ለሌሎች ፍጥረታት ቦታ የማይሰጥ ሰው፤ ችግሩ እሱ ደስተኛ ያለመሆኑ ብቻ አይደለም፤ መልሶ እርሱ ራሱ ለህይወትም እንኳ አለመመቸቱም እንጂ፡፡
እውነተኛው የሰብአዊነት ዋጋ
የሰው ልጅ ትክክለኛ የማንነት ደረጃውን ለመገንዘብ ሲሻ፤ ትኩረት ሊያደርግበት የሚገባው ቀዳሚው ጉዳይ፤ በመላ ስሜቱና የማመዛዘን አቅሙ ሁሉ፤ ምን ያህል ራሱን ከገዛ ራሱ ተፅእኖ በማላቀቅ ነፃነትን እንደተጎናፀፈ ማረጋገጡ ላይ ነው፡፡  
ቅዱስ እና እርኩስ
እውነት ነው ፤ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ፤ ለሰው ፍጥረት ሁሉ የሚበጁና የሰው ልጆችን ህይወት ከፍ ያደረጉ ተግባራትን ያከናወኑ ከሌሎች ይበልጥ ይወደዱ ዘንድ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ስለ እኒህ ሰዎች ማንነት ጥያቄ ቢያቀርብ የሚያገኘው ውጤት ያልጠበቀውን ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ደግሞ ይኼ ጉዳይ በፖለቲከኞችና የሀይማኖት መሪዎች ላይ ሲሰላ ባብዛኛው ግራ መጋባትን የሚፈጥር ሆኖ ይገኛል፤ካከናወኑት ተግባር መልካሙ ወይስ ጎጂው ነገር ነው የሚያመዝነው? በሚለው የዘወትር አፍርሳታ፡፡ በበኩሌ ግን፤በፅኑ የማምነውና ትልቁን ቦታ የምሰጠውም፤በግሉ ከፍ ያለ ተግባር ከፈፀመው ሰው ይልቅ፤ ሰዎች በራሳቸው ከፍ ያሉ ተግባራትን ማከናወን የሚችሉበትን መንገድ የማመቻቸት ከፍ ያለ ምግባር ላከናወነው ሰው ነው፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ፤ ሰዎቹ፤ በሚያከናውኑት  ከፍ ያለ ተግባር ሂደት እነርሱ ራሳቸው ከፍ ከፍ ይላሉና፡፡
ስለ ሀብት
በፍጹም ልቤ የማምነው ነገር ቢኖር፤ በአለም ላይ ያለ የቱንም አይነት ባለፀግነት፤ የሰብአዊነትን ደረጃ አንዲትም ስንዝርኳ ወደፊት ማስኬድ አለማስቻሉን ነው፡፡ ምንም ያህል  ህይወቱን በስራ ጠምዶ ለመኖር በቆረጠ ታታሪ ሰው እጅ ላይ ያለ ሀብትም ቢሆን እንኳን። የታላላቆቹን ንፁኃኑን ህይወት በተምሳሌትነት የወሰድን እንደሁ፤ፊታችን ድቅን የሚለው የለጋስነታቸው ገድል ነው፡፡ የገንዘብ ጉጉት፤ በራስ ወዳድነት እና ልጓም አልባ ልቅነት ህይወትን ያውካል፡፡
እስቲ አስቡት፣ ሙሴ  ኢየሱስ ወይስ ጋንዲ፤ ማንኛቸው ናቸው የካርኒጌን የገንዘብ ሰንዱቅ አንጠልጥለው ሲዞሩ የኖሩ?  
የምስራች ለሀያሲው!
አንዱ ሰው፤ በጥልቅ ቅኝት በቃተተ ነፍሱ፤በረቂቅ መንፈሱ፤ኖሮ፤በገበረው ሥጋ እና ደሙ፤ ጠምቆ፤ እነሆኝ ያለውን ወይን ፤ የጣዕሙን ልኬት፤ ሌላው ሰው፤ በግል አይኖቹ ቀንብቦ አይቶ፤ የዘመኑን ትኩሳት ተለኩሶ፣ ዳስሶ፣ አሽትቶ፣ ቀምሶ ባላጣጣመው ስሜቱ፤ብቻ በገነፈለ ብዕሩ፤ለምርኩዝነት ባጌጡ ልጥልጥ ሀረጋት ወይም ለዝረራ በተመላለጡ ዘርዛራ ቃላት መዘርዘሩ - ደስ አይልም? እና ይኼስ፤ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ!›› ለማለት በቂ ምክንያት አይሆንምን?
መማር እና ነፃ አስተሳሰብ
አንድን ሰው ማስተማር ብቻውን በቂ አይደለም። ክህሎቱን በውስጡ አስርፆና ከነፍሱ አዋህዶ አንዳች አይነት የራሱን ማንነት ማዳበር ካልቻለ፤ ሰውየው በተማረው ሞያ፣ ልክ እንደ ተንቀሳቃሽ ማሽን ሊያገለግል ይችላል፡፡ አንድ ተማሪ፤ የዕለት ተዕለት ኑሮን በስክነት አስተውሎ፤ በራሱ የማመዛዘንና የመረዳት ባህሪን፤ ከገሀድ እውነታዎች መጋፈጥንና ለጤናማ ማህበራዊ ህይወት ፍሰት ጉልህ ድርሻ ያላቸውን መልካም ስነ ምግባራት ካላካበተ፤ ከማንነቱ ጋ ባግባቡ የተሰናሰለ ህልውና ያለው ሰውነቱን ካጣ፤በዚያ፡ ልምድ በቀሰመበት ሞያው እንደሰለጠነ ውሻ ለመሆን ይቀርባል፡፡ የሰው ልጆችን ውስጣዊ ግፊቶች፤ግራ መጋባቶች፤ የስቃይና መከራ ውጣ ውረዶች ሲረዳ ብቻ ነው፤ በቅርብ አብረውት ካሉትም ሆነ ከሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ጋ በቅጡ መግባባት የሚችለው፡፡
እኒህን መሰል ዘላቂ ውርሶች ለአዲሱ ትውልድ ማቀበል የሚቻለው ደግሞ በትምህርት ቤት የመማሪያ መጻሕፍት አማካኝነት  አይደለም ፤ በዘርፈ ብዙ የሰው ለሰው ግንኙነቶች እንጂ፡፡ ባህልን መጠበቅ የሚባለው አንደምታም ይኸው ነው፡፡ እኔም ላሰምርበት የምሻው፤ ከማንኛውም ነገር ሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው፤ ዋናው እና ሁነኛው ጉዳይ፤ ‹‹ሰብአዊነት›› መሆኑን ነው፤ ከዚያ ውጪ የታሪክም ሆነ የፍልስፍና… ትምህርቶች ብቻቸውን ምንም የማይፈይዱ ደረቅ ዕውቀቶች ይሆናሉና፡፡
በተለይም፤ የፉክክር መንፈስ የተጠናወታቸውና ባፋጣኝ ጥቅም ላይ የሚውሉ የለብ ለብ የሞያ ስልጠናዎች፤ በሺህ ዘመናት የተገነቡትን ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚንዱ አደጋዎች ናቸው፡፡ ልዩ ስልጠናዎችም ቢሆኑ፡፡
ሌላው፤ አዲሱ ትውልድ ንቁና ዕድገት አምጪ  ዜጋ እንዲሆን የምንረዳው፤ ከምንም አይነት ተፅዕኖዎች የፀዳ አመለካከት ያለውና በጥልቅ መርማሪ፤ በነፃነት ሀሳቡን ገላጭ እንዲሆን በማብቃት  ነው፡፡ ባንድ ጊዜ ይሄንንም ያንንም በማግበስበስ ስር በማይሰድዱ እውቀቶች በመጠቅጠቅ ማጨናነቅና አዳሩን ብዙ ውጤት እንዲያስመዘግብ ጫና ማድረግ ትርፉ አስመሳይነትን ማከናነብ ነው፡፡ ያልሆነውን መስሎ እንዲገኝ ማድረግ።         የትምህርት ለዛና ወጉ የሚጣፍጠው፤ ከቀረበው ገበታ አማርጠው ሲያጣጥሙት እንጂ፤ የግድ ሲጋ ቱት አይደለምና፡፡
የዘመኑ መልዕክት
ዘመናችን፤ በርካታ የአዳዲስ ግኝቶች ፈልሳፊ ባለ አዕምሮዎች የሞሉበት ነው፡፡ ግኝቶቹም ህይወታችንን ቀሊል አድርገውልናል፡፡ ብዙ ድካም ሳያስፈልግ ውቅያኖስ እናቋርጣለን፡፡ በሰማይ እንበርራለን፡፡ የኤሌክትሪክ ሞገዶችን በመጠቀም ብቻ መልዕክቶችንና ዜናዎችን ከምድር አፅናፍ ወደ አፅናፍ መቀባበል ችለናል፡፡
ግን ደግሞ፤ የምርቶች ግብይት፤ ስርጭትና ክፍፍል በስርአት የተደራጀና በፍትሀዊነት የተማከለ አይደለምና፤ ሰዉ ሁሉ፤ በድንገት ከኢኮኖሚ ኡደቱ ተሽቀንጥሮ እንዳይገለል በስጋት ተወጥሯል፡፡ የሚፈልገውን ያገኝ ዘንድ እየቋመጠ ፍዳውን ይበላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ በአለም ዙሪያ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች፤ ባልተጠበቀ ጊዜና ሁኔታ ይገዳደላሉ፡፡
በዚህም የተነሳ ስለ መጪው ጊዜ የሚያስብ ሁሉ በፍርሀትና ሽብር ይናጣል፡፡ የዚህም መንስኤ ሀቁ ፤ የትየለሌ ቁጥር ያለው ‹‹የመንጋው ህዝብ›› የአዕምሮ ደረጃና ባህሪ፤ለንፅፅር በማይቀርብ ሁኔታ፤ለማህበረሰቡ ጠቃሚ ነገር ከሚፈይዱት ከጥቂቶቹ የአእምሮ ደረጃና ባህሪ ያሽቆለቆለ በመሆኑ ነው፡፡
አዲሱ ትውልድ፤ ይህን መልዕክት የሚያነብበው፤ በአጉል የበላይነት ስሜት ተኮፍሶ ሳይሆን፤የተጠቀሰውን ጉድለት ለመሙላት በሚችለው አቅሙ ተማምኖና ለተግባር የተነሳሳ ወኔው በሚፈጥረው እውነተኛ በራስ መተማመን ውስጥ ሆኖ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  

Published in ጥበብ

በዕውቋ ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ተፅፎ የተዘጋጀው “ቀሚስ የለበስኩለት” የተሰኘ ፊልም በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽና በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች  ይመረቃል፡፡ የድራማ ዘውግ ባለው  የ1፡40 ደቂቃ ፊልም ላይ፤ ድምፃዊቷ ዘሪቱ ከበደ፣ የንግድ ም/ቤት ፕሬዚዳንቷ ሙሉ ሰለሞን፣ የጃኖ ባንዱ ድምፃዊ ዲበኩሉ ታፈሰ፣ ሙዚቀኛው ሄኖክ መሐሪ፣ ይስሃቅ ዘለቀና ሌሎችም እንደተወኑበት ታውቋል፡፡ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት የፈጀ ሲሆን ቀረፃውን “የሳቢሳ ፊልሞች” እንዳከናወነው ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ ልደቱ ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁማ!
እንግዲህ የበዓል ሰሞን አይደል… ያው ያለው “ፏ!” ይላል የሌለው “ዷ!” ይላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን ስሙኝማ…እሷዬዋ የዓመት ፈቃድ ነገር ወጣችና ሰው ሳያያት ከረምረም ብላ ትመጣለች፡፡ እናላችሁ… ስትመጣ ‘የቅቤ ቅል’ መስላ፣ ተመችቷት ነበር፡፡
ታዲያላችሁ… ወዳጆቿ “እንዴት ነው ነገሩ እንዲህ ያማረብሽ፣ ምን ተገኘ?” ምናምን ይሏታል፡፡ እሷም ከሀብታም ዘመዶቿ ዘንድ እንደ ከረመች ትነግራቸውና…ልጄ፣ “ከሀብታም መጠጋት ነው የሚያዋጣው…” ትላለች፡፡ እነሱም “ሀብታም ምን ያደርግልሻል፣ ይልቅ ከቢጤዎችሽ ከእኛ ጋር መሆኑ ነው የሚያዋጣው…” ምናምን አይነት ‘የክብር ማስጠበቂያ’ ክርክር ያመጣሉ፡፡
እሷም እነሱ ቤት የምታገኘውንና ሀብታም ቤት የምታገኘውን ልዩነት ስትነግራቸው ምን ብትል ጥሩ ነው… “ከሀብታም ቤት ጥብስ፣ ከድሀ ቤት ጥቅስ አይጠፋም፡፡”
የእውነት እኮ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ጥቅስን የመሰለ ‘ቀን አሳላፊ’ አለ እንዴ! ልክ ነዋ…ኪሳችን ተራግፎ ውስጡን ብል ሲበላው፣ “እንዴት አደራችሁ” ለማለት ሂሳብ የምንጠየቅ እየመሰለን ስንሳቀቅ፣ ዕድሜ ለጥቅስና ለተረት…ምን እንል መሰላችሁ…“ያጣም ያገኝና ያገኘም ያጣና፣  ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!” አለቀ፡፡ በተረት መልክ የመጣ ‘ፓራሲታሞል’ በሉት! የዚችኛዋ ተረት ኮሚክነቷ ምን መሰላችሁ…ይኸው “…ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!”  ስንል ስንት ዘመናችን ሆኖ…አለ አይደል…. የምንታዘበው እስኪመጣ ገና እየጠበቅን ነው!
ልጄ እንደ ዘንድሮ ከሆነ…አይደለም ቁልቁል መውረድ፣ ላይ የወጣው ሁሉ “ባትጋሩኝ!” እያለ ‘ገዢ መሬቱን’ እያጠናከረ ‘በእኛ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት’… ከተረታችን ጋር ረስተውናል፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን አንድ የምትገርመኝ ተረት አለች…“ሀብታም ለሰጠ የድሀ እንትን አበጠ” ምናምን የምትል፡፡ አሁን…ጭንቅላት፣ ትከሻ፣ አንገት የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎች እያሉ…አለ አይደል… እዛ ድረስ ‘ቁልቁል’ መውረድ ለምን አስፈለገ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“ያጣም ያገኝና…” የሚለውን ለመሞከር ችግሩ ምን መሰላችሁ…መሰላሉ የለማ! ‘ብልጦቹ’ መሰላሉን ከወጡበት በኋለ  ገፍተው ከመሬት ያጋድሙታል መሰለኝ፣ መሰላል አጥቶ የሚንከራተት መአት ነው፡፡ በእርግጥ ሲወረድ በምን እንደሚወረድ ራሱን የቻለ ጥያቄ ቢሆንም ገና ለገና ስለ‘መውረድ’ አይወራም፣ እዚህ አገር እኮ ያለውም የሌለውም ኑሮን በኪሎ ሜትር ማስላት ትቶ በሚሊ ሜትር እየደመረና እየቀነሰ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንዳወራነው አንዳንዴ ሰዉን ስታዩት “ነገ” የሚባል ነገር የሌለ ነው የሚመስለው፡፡
“መሰላሉን ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ…” ምናምን የሚል ዘፈን ይቀናበርልንና በየኤፍ.ኤሙ. ኮምፐልሰሪ ምናምን ነገር ይሁንልን፡፡ (ልክ ነዋ… ኤፍ.ኤሞችን ስናዳምጥ አንዳንድ ጊዜ ዘፈኖች ብቻ ሳይሆኑ ዘፋኞቹም ‘ቢያንስ አንዴ’ እንዲሰሙ ሰርኩላር ነገር ያለ እየመሰለን ቸግሮናላ!)
እናማ…እኛ ግን ጥቅስ መጥቀሳችንን፣ ተረት መተረታችንን እንቀጥላለን፡፡ ልክ ነዋ…ያለመሳቀቅ ልንጠቀምባቸው ከምንችልባቸው ነገሮች መሀል ዋናዎቹ ጥቅሶችና ተረቶች ናቸዋ! ለዛውም ቢሆን ‘ኤዲት’ የተደረጉትን!
እና እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ…የሆነ ዝም ያለ ነገር አልበዛባችሁም! ልክ ነዋ…የሚጮህ ነገር ቢኖር፣ ወይ አዲስ የመዝሙር አልበም ሲያስተዋውቁ፣ ወይ “ሎተሪ ግዙ” ስንባል፣ ወይ “ለአቶ እከሌ መታከሚያ የአቅማችሁን አዋጡ…” ምናምን ሲባል ነው፡፡ መአት የምንነጋርባቸው ከእለት ኑሯችን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን … ነገርዬው ማን ማንን አምኖ ይናገራል ነው ነገሩ፡፡ እንደ ድንገት አምልጦን ሹክ ያልነው ነገር፣ ዙሪያውን ተሽከርክሮ በመጨረሻ ለእኛው ሲነገረን… አለ አይደል…
“ተናግሮ አናገረኝ ይወደኝ ይመስል፣
ሄዶ ተናገረ የላኩት ይመስል”
ብለን እንተርታለን፡፡ አሁን ‘መተረት’ ባንወድ ኖሮ ይቺን ማደንዘዣ ከየት እናገኛት ነበር! እንኳንስ ቤታችን ጥቅስ አልጠፋ!
ያቺ የለመድናት…
“ከእንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ፣ ከአፍ የሚለቅም”
ብለን ተርተን ‘ጭጭ’ ነው፡፡ ምን ይደረግ…‘ሄዶ ተናጋሪ’ ሲበዛ ከቤታችን ‘የማይጠፋውን ጥቅስ’ ለቀም አድርገን ማስታገሻ እናደርገዋለን፡፡
“ዝምታ ለበግም አልበጃት
አሥራ ሁለት ሆነና አንድ ነብር ፈጃት”
የምትለው ተረት…አለ አይደል…የሆነ እርፍና ነገር ቢኖራትም ያለችው ግድግዳችን ላይ ሳትሆን እንጨት ሳጥናችን ውስጥ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…አለ አይደል… “የዛሬውን አያድርገውና…” እያልን በሉካንዳ በኩል ባለፍን ቁጥር በናፍቆት ‘ሽንጥና፣ ታናሽ’ ላይ ዓይኖቻችንን እንተክላለን፡፡ አሀ… መቶ ብር ሦስት ኪሎውን ‘ሻሽ የመሰለ’ ሥጋ ከፋሽኮ ቪኖ ጋር ገዝተን ለቡና ይተርፈን የነበረበት ጊዜ ትዝ ይለናላ! አሁንስ?…አሁንማ ፓሪስ የሚታየው የፒካሶ የስዕል ዓውደ ርዕይና ዶሮ ማነቂያ የሚታየው የሥጋ ‘ዓውደ ርዕይ’ አንድ ሆኖብናላ! ብናጉረመርም ምን ይፈረድብናል! ይሄኔ ነው ተረት የማስታገሻ ሚናዋን የምትወጣው…
“ቁርበት ምን ያንጓጓሃል ቢሉት ባያድለኝ ነው እንጂ የነጋሪት ወንድም ነበርኩ አለ”
የምንንጓጓ ቁርበት መሆናችንን ብቻ አትዩብና! የእውነት ግን እኮ ብዙዎቻችን የምር ቁርበቷን መስለናል! እነ እንትና…ምነው ደብዘዝ አላችሁብኝሳ! ችግር አለ እንዴ!
እናላችሁ… እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ…መቼም ሁልጊዜ እንደምንለው ዘንድሮ እርስ በእርስ መተማመን ቀንሶ የለ! እናላችሁ…አይደለም የማናወቀው ሰው ሲያደናቅፈው “እኔን ድፍት ያድርገኝ…” ምናምን ሊባል የቅርባችን ሰው እንኳን አደናቅፎት ሲንገዳገድ “አንተ ሰውዬ ጭራሽ ደንባራ ሆነህ ቀረኸው…” ምናምን መባባል እየለመደብን ነው፡፡ እናላችሁ…“እባክህ አንድ ችግር ገጥሞኝ…” ለሚለው ሰው እኔ ወንድምህ እያለሁ ምናምን ከማለት ይልቅ…ችግሩ ይጋባብን ይመስል እንሸሻለን፡፡ እናማ ዕድሜ ለ‘ተረት ወዳጅነታችን’… ተረት አናጣለትም…
“ውሀ ለሚወስደው ሰው በትርህን እንጂ እጅህን አትስጠው”
እንልና…በትርም ስሌለን “እንደ ፍጥርጥርህ…” ብለን እንተወዋለን፡፡
ስሙኝማ… የጥቅስ ነገር ካነሳን ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ በብዛት እናያለን፡፡ በእርግጥ መልካም ያልሆኑ በተለይ ሴቶች ላይ የሚጠነክሩ ጥቅሶች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሪፎች አሉ፡፡ አንድ ወዳጄ ያያት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ…“የከፋው ሲሞት፣ የደላው መች ቀረ፡፡” ይቺ ዝም ብላ የምትመስል ጥቅስ ውስጧ መአት ነገር አላት፡፡ ዘመናችንን የምታሳይ አይመስላችሁም! ‘ስለደላቸው’ ብቻ ሰማይን ለመርገጥ የሚቃጣቸው በበዙበት ዘመን…አሪፍ ጥቅስ ነች፡፡
እኔ የምለው…‘አንደርግራውንድ’ መነጣጠቅ እንዲህ ለየለት ማለት ነው! የምንሰማው እኮ አንዳንዴ…“እነ ስቴፈን ስፒልበርግ ስንት ታሪኮች አምልጧቸዋል…” ያሰኛል። ታዲያ…እንደው ተገኘ ተብሎ…አለ አይደል…ጨዋታው የፊፋንም፣ የካፍንም ሆነ የማንንም ህጎች የማያከብር ይሆንና ‘አራቱን ወር’ ሲደፍን ቁልጭ ነዋ! ይሄኔ ዕድሜ ለተረቶች ወዳጅነታችን…ህመም ማስታገሻ አናጣም…
“ለፍቅር ብተኛት ለጠብ አረገዘች”
እንላለን፡፡ ከዛ ጠብ ይመጣል፡፡ ሁለቱም “የመውደድ መድሃኒት…” ምናምን ሲሉ የቆዩትን “አንተ ነህ…” “አንቺ ነሽ…” ነገር ይመጣል፡፡ ይሄኔ ለተረትና ጥቅስ ምስጋና ይግባውና ምን ይላል መሰላችሁ…
“ያንቺን አትበይ ገንዘብ የለሽ
የሰው አትበይ ምግባር የለሽ”
እናላችሁ… እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…የሆነች እንትናዬን ‘ኪሶሎጂ ለማጦፍ’ ስትፈልጉ እንዲህ ትሏታላችሁ…“ሕይወት ምንድነች? ሕይወት ፍቅር ነች፡፡ ፍቅር ምንድነው? ፍቅር መሳሳም ነው፡፡ መሳሳም ምንድው? ጠጋ በዪኝና ምን እንደሆነ ላሳይሽ፡፡” አሪፍ አይደል! እኔም በ‘ፌስቡክ’ ያገኘሁትን ‘ሼር’ ላድርግ ብዬ ነው!
ሌላ ‘ሼር’ እንዳላደርጋችሁ ደግሞ አንድ ተረት ትዝ አለችኝ…
“ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡”
አለቀ፡፡
እናላችሁ…እንኳንም በእኛ ቤት ‘ጥቅስ’ አልጠፋ። የ‘ጥብሱ’ ያለመኖር ‘ወና ያደረገውን’ ባይሞላውም… ማስታገሻ ይሆነናላ!
መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

(ከተወካይ አሊያም የዙምራ ወራሽ፤ ነው ብዬ ካሰብኩት ከኑሩ ጋር ስለዙምራ የምናደርገው ውይይት ላይ ነበር ያለፈው የጉዞ ማስታወሻዬ የተቋረጠው ከዛው ልቀጥል)
“ስለ ዙምራ እስቲ ንገረኝ?”
“ዙምራ፤ ገና በልጅነቱ … ‘እያንዳንዱን ነገር እኔ እማየው ከተፈጥሮ ሥዕል ነው፡፡ ከዛ ተነስቼ ነው ሚዛኑን የማየው፡፡ አብዛኛውን ከወላጆቼ እወስዳለሁ፡፡ ይሄ የወንድ ሥራ ነው፣ ይሄ የሴት ሥራ ነው፣ ይሄ ወገን ነው፣ ይሄ ባዕድ ነው፣ የሚባለውን ነገር ከዚያው አያለሁ፡፡ ይሄ ነገር ምንጩ ምንድነው? ብዬ ከቤት ስወጣም የማየው የምሰማውም ያው ነው፡፡ ለምን የሚለው ጥያቄ በውስጤ እያደገ ነው የመጣው” ይላል፡፡ ይሄንን ነገር ለማጥናት እስከ 13 ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ ትላልቅ የሃይማኖት አባቶችን፣ ኦርቶዶክሶችን፣ ሙስሊሞችን ያነጋግር ነበር፡፡ ስለአመሠራረቱ አንተ ራስህ በአካል ከአንደበቱ ብተሰማው በጣም ጥሩ ነበር…” አለኝ ኑሩ፡፡
“እናትዬዋ ምን ዓይነት ሰው ነበሩ፤ አንተ ስትደርስባቸው?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“በዕድሜ በሰል ብላ ነው ያገኘሁዋት፡፡ በእርግጥ በአስተሳሰቡዋም ታላቅ ሰው ናት፡፡ ለሁሉም ሰው አክብሮት አላት፡፡ ትንሽ ትልቅ አትልም ትመክራለች፡፡ የእሱን የህይወት ታሪክ ስንጠይቃት፤ ለመግለጥ ትቸገራለች፡፡ ‘ከባድ ነው! ከወለድኳቸው ልጆች ሁሉ ከእርግዝና ጀምሮ ልዩ ነው፡፡ በእጅጉ ልዩ ነው! አወላለዱም ልዩ ነው’ አለች፡፡ የቤት ሥራዋን ሰርታ ወደ ጉልጓሎ ልትሄድ ነሐሴ 16 ቀን አካባቢ ነው፤ 64 ወይ 65 ዓ.ም ይመስለኛል፤ (ሌላ ሰው እንጠይቃለን መረጃውን ቆይ) የምታስጐበኘዋን ልጅ ጠርቼ ታብራራልሃለች አለ፡፡  
“መጀመሪያ የኅብረት ሥራ ማህበራቱን (ኮኦፕሬቲቮቹን) እንጨርስ” አልኩት፡፡
“ኮኦፐሬቲቮቹ እንዴት ተቋቋሙ? አየህ፤ ባህሉ እዚህጋ አለ፡፡ ኮኦፕሬቲቮቹ የሁሉም ናቸው፡፡ ገበሬ ማህበሩ፣ የአውራምባ ማህበረሰብ ከዛ የተውጣጣ ማህበር አለ… እናንተ የራሳችሁ ኮኦፕሬቲቭ አላችሁ ማለት ነው?” አልኩት፡፡
“አዎ” ይሄ አንድ አለ፡፡ ያካባቢው ቀበሌ የኅ/ሥ/ማህበር አለ በመመሪያ ደረጃ የሚፈቀደው ከአንድ ቀበሌ ላይ አንድ ኮኦፕሬቲቭ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን መመሪያ ነው በሚል የማህበረሰቡን እሴት መረበሽ የለብንም ከሚል፤ ታሰበበትና ከህጉ ወጣ ብለንም ቢሆን እንደዚህ ያለውን አስተሳሰብ ማጐልበት አለብን በሚል፤ ኮኦፕሬቲቩ ራሱን ችሎ ተቋቋመ። 2000 ዓ.ም ነው ዕውቅና ያገኘው፡፡ በክልሉ ፍትሕ ቢሮ፡፡ ከዚያ ኮኦፕሬቲቩ ተጠናከረ”
“ምን ይሠራል?”
“የዕደ ጥበባት ሥራዎች ይሠራል፡፡ ግብርናውንም ይሠራል፡፡ ወፍጮ፣ ሱቅ ላይም ይሠራል፡፡ ሻይ ቤት ምግብ ቤት፣ እንግዳ ማረፊያ ነገሮች አሉት፡፡ ምናልባትም ወደፊት የዘይት ሞተርም ይኖረዋል፡፡ ቦታው፣ አዳራሹ ተዘጋጅቷል፡፡ ሞተሩ ተገዝቷል፡፡”  
“ፈንዱን ከየት ታገኙታላችሁ”
“ለምሣሌ የዘይት ሞተሩን የገዛንበትን፣ ከህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት፤ ነው ያገኘነው፡፡ 50% የእኛን ጨምረን ማለት ነው፡፡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ የእኛው ነው፡፡ ሞተሩም የእኛ ብዙ ድርሻ አለበት፡፡ የእንግዳ መቀበያው በእኛው ነው የተገነባው” (ይህ guest room በቀን 100 ብር የሚያስከፍል ዘመናዊ ሽንት ቤትና መታጠቢያ ያለው ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ያረፈ 5ኛ ቀኑን የያዘ ፈረንጅ አለ፡፡) ማህበረሰቡ ከሚያመርተው፣ ከሚገበየው፣ ከሚሸጠው ነው፡፡”
“አሁን የምጐበኛቸው የሚፈተሉት፣ የሚሸመኑት ሁሉ ወደ ሽያጭ ይሄዳሉ ማለት ነው?”
“ይህ ዶኩሜንት የሂሳቡን ውጣ ውረድ ያሳይሃል፡፡ ኮሚቴ አለው። ማህበረሰቡ ለብቻ አለው፡፡ ግዢ አለው፡፡ ሽያጭ አለው፡፡ በየመልኩ በሂሳብ የተሠራ ነው፡፡ ወደ ክፍፍል ስንመጣ፤ ልናንቀሳቅሰው የምንችለው ምን ያህል ነው? የሚለው በኮኦፕሬቲቭ ህጉ መሠረት አለው፡፡ ያ ይወሰናል።”  
“ስሙ ማን ይባላል?”
“የአውራምባ ማህበረሰብ የገበሬዎችና ዕዳ ጥበብ ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበር”
“ከጄክዶ ጋር እንዴት ነው መጀመሪያ ግንኙነታችሁ?”
“ስንገናኝ አቶ ተስፋዬ፤ አቶ ሙሉጌታ (ኃላፊዎቹ) የማህበረሰቡን ሁኔታ በሚዲያም ሰምተው መጥተው ይጐበኙት ነበርና አንዳንድ ነገሮችን አብረን ብንሠራ፤ እኛ እምንሠራው አብዛኛው ነገር ከእናንተ ሥራ ይመሳሰላል የሚል ሃሳብ ነበር፡፡ በተለይ ወላጅ ያጡ ህፃናትን ከመደገፍ አኳያ ብንሠራ የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ተቆፍሮ አገልግሎት መስጠት ያልቻለም የጉድጓድ ውሃ አለ ስለሱም ተወያየን፡፡ ሁለት ሶስቴ ለጉብኝት ይመጡ ነበረ፡፡ በዚያው አጋጣሚ ግንኙነቱ ተጀመረ፡፡ ለጐበዝ ተማሪዎች የሚያስፈልጉ ድጋፎች ላይም ሃሳብ ቀረበ፡፡ የአንድ ዓመት ፕሮጄክት በዛ ሠራን፡፡ በደንብ አቀድን ተፈራረምን፡፡ ተጠናቀቀ በ2001 ዓ.ም. -በ2002 ገደማ!! በጠቅላላው በህፃናት፣ ከአረጋውያን ላይ በጣም አተኮርን፡፡ በመሠረቱ ከመረዳት፤ መርዳት ብንችል ነው ጥሩ እሚሆነው! … ስለዚህ ሠርተን እምንመልሰው ፈንድ ቢሆን በሚል የመጀመሪያው የ170,000 ብር ፕሮጀክት ሆነ፡፡ በሚቀጥለው የ300 መቶ ሺህ ብር፡፡ በዓመቱ ሠርተን መለስን፡፡ ከሞዴልም አኳያ ከአስተሳሰብም አኳያ በጣም የተመቸ ነበር-ለሁሉም፡፡ ለእነሱ በጣም ደስ አላቸው … ወለድም አላሰቡብንም፡፡ ሁለት ዙር ተሠራ፡፡ የዘይት ሞተሩ 3ኛ ዙር ነው፡፡
“እንዴት ዘላቂ ይሆናል የኮኦፕሬቲቩ አካሄድ ያሳድገዋል? ወይስ የማ/ሰቡ ባህላዊ አካሄድ?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“ዘላቂ ሊያደርገው የሚችለው የማ/ሰቡ አስተሳሰብ፤ ባህልና ዕድገት ነው ብዬ አስባለሁ … ኮኦፕሬቲቭ በህግ እሚመራ ነው፡፡ ህግ ሲለወጥ ይለወጣል፡፡ በእርግጥ እሱን መከተል ይቻላል ከተቻለ፡፡ መሠረተ ጉዳዩ ግን የማ/ሰቡ ጥንካሬ ነው፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት በደርግ ሥርዓት የተቋቋመ የህብረት ሥራ ማህበር ደርግ ሲበተን፤ አንድም የለም፡፡ ይህ ማ/ሰብ ግን በራሱ ፀንቶ ቀጥሏል-ተሸጋግሯል፡፡ ስለዚህም ማ/ሰቡ የራሱ ባህል፣ አኗኗር፣ ዕድገት፣ ለውጥ … ነው ያስቀጥለዋል ብዬ እማምነው፡፡
“ከኢየሩሣሌም ጋራስ ምን ያህል ትዘልቃላችሁ? ፈንዱ ሲያልቅ ያልቃል?”
“ያው እንግዲህ፣ በመሠረቱ በፈንድ ብቻ አይደለም፡፡ ያለን ትሥሥር ሂሳብ አሠራር፣ አያያዝ፣ ሪፖርት አጠቃቀም… የፕሮጀክት አነዳደፍ፣ ሪፖርት አደራረግ … ሰፊ ሥልጠና ነው የሰጡን በያመቱ! አክብረው ነው የሚጠሩን! … ከብዙ ሰዎች አገናኝተውናል፣ ብዙ አካባቢዎች ሄደን የልምድ ልውውጥ እንድናገኝ አድርገውናል … እስከ ድሬ ድረስ ተንቀሳቅሰናል … ናዝሬት፣ ቢሾፍቱ፣ ጐጃም ወዘተ … ልምዱ ውስጣችን ይቀጥላል፡፡ … ማ/ሰቡን ያከብራሉ … ሥርዓታችንን እንኳ ወደ ሌላ ለማስተላለፍ የእኛን ይሁንታ ነው የጠየቁት! … ትልቅ ድርጅት ነው እየሩሣሌም!...”
ወደ ወ/ሮ ጥሩ ሰው (አስጐብኚዬ ዞርኩኝና) “እስቲ ደግሞ አንቺ እምትይኝን በይኝ?” አልኳት፡፡ “ማነሽ? ምንድነሽ? የት ትደርሻለሽ? ጥሩ ሰው እስቲ አንድ በይኝ”
ሳቂታ ናት፡፡ ጠይም ናት፡፡ ጠይም ሳቅ ሳቀች፡፡
“ጥሩ ሰው ፈንቴ እባላለሁ፡፡ የሥራ ድርሻዬ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብዬ፣ ለምን ዓላማ እንደመጡ ጠይቄ ጉብኝት ካሉ ማስጐብኘት፣ የማ/ሰቡን ባህል ማስተዋወቅ፣ ከዶ/ር ዙምራም ጋር አገናኚኝ ካሉኝ ማገናኘት ነው፡፡”
“የማህ/ሰቡ በሩ ነሽ ማለት ነዋ!! …
ጥሩ ሰው የሳቅ ሰው ናት … የጠይም ቆንጆ ሳቋን ስቃ ነው ጥያቄዬን መመለስ የጀመረችው፡፡ አንደበተ-ስል ናት!
 “አባትሽ አቶ ፈንቴ አሉ? ምን ይሠራሉ?”
“አቶ ፈንቴን አላቃቸውም … የ19 ዓመት ልጅ ሆነሽ ነው አባትሽ የሞተ ትለኛለች እናቴ…
እናቴ እዚሁ ናት… ከነዙምራ ጋር መስራች ሆና ቆይታ እኔን እዚህ አሳደገችኝ”
“አንቺ አ.አ. መጥተሽ መኖር አትፈልጊም?” ሳቋን ለቀቀችው፡፡ “እዚሁ አዲሳባን መፍጠር ነው እምፈልገው! ጠንክረው ከሠሩ ዓለም የደረሰበት ቦታ ማ/ሰብን ማድረስ ይቻላል! … ቦታ ቢቀይሩ፣ የትም ቢደርሱ፤ ሰው የአስተሳሰብ ለውጥ ካላመጣ ባለበት ጠንክሮ መሥራት በታማኝነት! የትም ቦታ አዲሳባን መፍጠር ይቻላል!”
“የማ/ሰቡ ህግጋት ምንድናቸው?”
“ዋናውና ትልቁ ለሰው ልጆች ክብር መስጠት!! ከገንዘብ ይልቅ ትልቁ ሀብት፤ ሰው ነው፡፡ ገንዘብ ሁለተኛና ሰውን የሚደግፍ የሚገነባ ነው ሚሆነው! ሌላው የሰውን ልጆች በልዩነታቸው ሳይሆን ባንድነታቸው ነው ምናምነው! ነጭም እንሁን ጥቁር ያንድ ሐረግ ፍሬዎች ነን! እንጂ ያዳም ዘር አልተቀየረም ብሎ ሚያምን ማ/ሰብ ነው! በሥነ - ምግባሮች በኩልም መጥፎዎቹን አስወግደን፣ ጐጂና ጠቃሚ ብለን ጐጂዎቹን ላንመለስባቸው አስወግደን፣ ጠቃሚዎቹን በተግባር እየሠራን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ነው! ዙምራ የኛን ወላጆች ካገኘና ከመሠረተ ጀምሮ፤ ይህን አስተሳሰብ ተግባራዊ አድርገው እየቀጠሉት ነው የቆዩት፡፡ እኛም ያንኑ ይዘን ተመችቶን እያስፋፋነው ነው፡፡ ዓለም እንዲያውቀው፣ ሁሉን ባለበት እንዲኖረው ነው እምንፈልገው!”
“እንዴት ይሰፋል?”
“ሊሰፋ እሚችለው ስንወስደው ነው! ዙምራ ከኛ ወላጆች ጋር ሲመሠርት እሱ ከህፃንነቱ ጀምሮ ቢሆንም፤ ዓላማ የተማሩ ሰዎች እንዲያገኙት ነው የተነሳው፡፡ የተማሩ ሰዎች እነማናቸው፤ የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የቀለም ምሁሮች ናቸው፡፡ እነሱ ካገኙት ህዝባቸው የሚነሳው በነሱ ነው! በነሱ ጉያ ነው! …ሁሉም ወስዶ ሲያስፋፋው ዓለም አንድ ይሆናል ብለን እናስባለን!”
“እየዞረ ያስተምራል ዙምራ?”  
“ከህፃንነቱ ጀምሮ እየዞረ የሀሳቡ ተካፋይ ለማግኘት ይሞክር ነበረ! እናቱ እምትገልፅልን የ4 ዓመት ህፃን ሆኖ ጀምሮ በዚህ መሠረተ - ሀሳብ እንደተነሳ ነው! በ2 ዓመቱ እንዳዋቂ ይጠይቅ ነበር፡፡ በ4 ዓመቱ ስለ ሰው ልጅ መሠረታዊ ኑሮ ይጠይቅ ነበር፤ ነው እናቱ ምትለው! በ4 ዓመቱ ከተነሳባቸው ሀሳቦች 1ኛው የሴቶች እኩልነት ነው! አባቱ በናቱ ላይ በሚያሳድረው ጫና ተነስቶ ነው!
ሴት እናት ነች፤ ወንድ አባት ነው፤ አለቀ፡፡ እናቴና አባቴ እኩል መብት የማይኖራቸው ለምንድን ነው? የዱር ሥራ ላይ ገበሬዎች ናቸው … አብረው ሲሠሩ ውለው ማታ ላይ ሲመለሱ ያባት ሥራ ዱር ይቀራል፤ የእናት ሥራ ግን ቤት እንጀራ ትጋግራለች… ወጥ ትሠራለች፣ … ያ መቅረት አለበት፡፡ ወንዱም መሥራት አለበት!
ድንጋይና ድንጋይ ተፈጭቶ ቤት ተሰርቶ ቤተሰብ ታስተዳድራለች እናቲቱ፡፡ እሱ ቢፈልግ ይተኛል፣ ቢፈልግ ይቀመጣል፡፡ ሥራው ለምን የሷ ብቻ ይሆናል? ይላል ዙምራ! የቤቱ ሥራ ለእናቴ ብቻ የሆነበት ለምን ነው? ስለዚህ መጀመሪያ የሚያስፈልገው የሴቶች እኩልነት ነው” አለ፡፡
(2ኛው) የህፃናት መብት ነው! ህፃናት እግረ-ተከል ከሆኑ ጀምሮ አላቅማቸው ሥራ ይሰጣቸዋል፡፡ አቅማቸው አልችል ካለ ለምን አጠፋህ ለምን አበላሸህ? የስሜት ማውጫው ዱላ ነው! ለምን? ህፃናት ህይወት አደሉም ወይ? ያላቅማቸው ብትሩ ኬት መጣ? ነው! 3ኛው) በጤናም ሆነ በእርጅና የደከሙ ሰዎችን ሁሉም እያለፋቸው ይሄዳል፡፡ … ሌላው በልቶ፣ ጠጥቶ ሲሄድ ደካሞች ይወድቃሉ፡፡ ለሰው ደራሹ ሰው ነው፡፡ እኛም አንድ ቀን ያው ነን-ደጋፊ ያስፈልገናል፡፡ ደካሞችን ያንን ዕድል ለምን እናሳጣቸዋለን?
4ኛው) ሰውን ሰው ሲዋሸው፣ ሲቀጥፈው፣ ሲደበድበው፣ ሲገለው፣ አያለሁ እሰማለሁ … በጥቅሉ በራሳችን ላይ ሊሆን የማንፈልገውን በወገኖቻችን ላይ የምንፈፅመው ለምንድነው? ይህን ከሠራንስ ከእንስሶቹ በምን ተሻልን? ይህን አስተሳሰብ የአራት ዓመት ህፃን ሆኖ እንዳነሳው፤ እናቱ ለእኛ ታወራልን ነበር፡፡ እሱ ግን አላስታውስም ነው ሚለው። እስከ 88 ዓ.ም የዙምራ እናት ከእኛጋ ነበረች፡፡ አባቱ በህፃንነቱ ነው የሞቱት፡፡ የአካባቢው ሰው የ4 ዓመት ህፃን ሆኖ ይሄን ካሰበ ታሟል፣ አብዷል አለው፡፡ “የማይወጣ ጥጃ ከማሠሪያው ይታወቃል” እንዲሉ፤ ይህን አስተሳሰብ ካራመደ ነገ ምን እንደሚሠራ አናውቅም፤ እየተባለ ታሟል ይሉት ገቡ፡፡ እስከ 13 ዓመቱ እቤተሰቡ ጋር ይቆያል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ያለንበት ፎገራ ወረዳ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኝ ወረዳ እስቴ ነው፡፡ ዙምራ እስቴ ነው አገሩ፡፡ በ13 ዓመቱ የሀሳቡ ተካፋይ ለማግኘት ከአገር አገር መዞር ነው ያሰበው፡፡ የመጀመሪያው ጉዞዬ ከእስቴ ተነስቼ ወደ ጐጃም ለ5 ዓመታት ተጓዝኩ፡፡ ሰዎች በተሰበሰቡበት የማገኘውን አጋጣሚ 4ቱን መሠረተ - ሀሳብ አካፍላለሁ፡፡ ይህን ሳካፍላቸው እንደቤተሰቦቼ ዕብድ ነህ ጅል ነህ አላሉኝም፤ ይላል፡፡ ሀሳቤን በግርምት ይመለከቱታል፡፡ “እምትናገሪው ነገር መልካም ነው፤ ግን ማን ይወስደዋል ከማለት ውጪ የሚከተለኝ አላገኘሁም ይላል፡፡ የ13 ዓመት ልጅ በመሆኑ “አንቺ” ብለው ነው የሚጠሩት! … የሚቀበለኝ አላገኘሁም፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተሰብ ተመልሼ፣ እርሻ እያረስኩ፣ ባመቱ የማገኘውን ምርት፣ ለአካባቢው ደካሞች ባከፋፍል፣ አንድ የህሊና እረፍት አገኛለሁ ብዬ በማሰብ ወደ እስቴ ተመለስኩ፡፡ ፊት 13፣ በስደት 5 ዓመት፤ 18 ዓመት ሆኖታል፡፡ ቤተሰቡን ሄዶ ትዳር ልይዝ ነው፣ ሴት ፈልጉልኝ ሲላቸው፤ “በሽታው ለቆት ነው ትዳር ታሰበ” … “በሽታው ባይለቀው ኖሮ ትዳር አያስብም ነበር” -ይሉት ነበር፡፡ ሴቷን ፈልገው ትዳር ይመሰርታል … ትዳር መሥርቶ፣ ያርሳል ያመርታል … ምርቱን ግን ባካባቢው ለወደቁ ደካሞች ማከፋፈል ነው ያሰበው! የኔ ደስታዬ እሱ ነው፤ እሚለው ዙምራ! እሱን በማደርግ ጊዜ ቤተሰቦቼ “አይደለም እንዲያውም በሽታ ጨምሮ ነው የመጣው … አልበላም፣ አልጠጣም፣ አልታደለም … ‘የሱን ገንዘብ ዘመድ እንኳን አላገኘውም ለባዒድ ነው እሚሰጠው’ አሉኝ፤ አለ፡፡ እዚህ ላይ 5ኛ) ጥያቄ ያነሳው ዙምራ ‘ከሰው ልጆች ላይ ባዕድ የምትሉት የትኛውን ነው? ዘመድስ የምትሉት የትኛውን ነው? ብሎ ጠይቋል ቤተሰቡን፡፡ ከ7 ትውልድ በኋላ ያለው ባዕድ፣ ከዚያ በታች ወገን/ዘመድ ነው ብለውታል፡፡ ከ7 ትውልድ በኋላ ያለው ባዕድ ይሆናል ያለው ማነው? ንገሩኝ አላቸው፡፡ በእኔ በኩል ነጭ ጥቁር ማረግ የፈጣሪ አሠራር ነው፡፡ ሰዎች ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም፣ መሬትንም … ብንወስድ አንድ ቦታ ነጭ አንድ ቦታ ጥቁር፤ እሱን ለፈጣሪ እንተወውና ሰዎቹ ሁሉ ያንድ ፍሬ ሐረግ ፍሬዎች ነን! የእኔ ገንዘብ ለባዕድ ሳይሆን ለዘመዶች ነው እሚሄደው ይልና ይረዳና፤ ለሀሳብ ብቸኛ ነው-ብቻውን መኖር አይችልም-ከአገር አገር እንዲሁ በጋ በጋ ላይ ሲዘዋወር፤ ከዕለታት አንድ ቀን ከእስቴ ተነስቶ እዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎችን ያገኛል፡፡ ይህን ሀሳብ ሲያካፍላቸው፣ ስለተቀበሉት፡፡ እዚህ ቦታ ብመላለስ እቅዴ ይሳካል ሲል ለብዙ ዓመታት በተከታታይ በጋ በጋ ላይ እየተመላላሰ፤ በትክክል ሀሳቡን መቀበላቸውን ሲያረጋግጥ ነው በ64 ዓ.ም. መጥቶ እዚህ ከእኛ ወላጆች ጋ ሊኖር የቻለው፡፡ ሲመሠርቱም 4ቱን መርሆች ይዘው ነው፡፡ ሴት በሴትነቷ እናት ነች፣ ወንድ በወንድነቱ አባት ነው፡፡ የሥራን አጋርነት ፈጥረን መሄድ መቻል አለብን፡፡ ሴት የወንዱን ሥራ ብትሠራ ያባቷ ሥራ ነው፡፡ ወንድ የሴቷን ሥራ ቢሠራ የእናቱ ሥራ ነው። ችግሩ ምኑ ላይ ነው፡፡ በጋራ ስንኖር የጠብ ምንጭን ማስወገድ አለብን። የጠብ ምንጭን አስወግደን፣ ሰላምን ዘርግተን፣ ገነትን ፈጥረን መሄድ መቻል አለብን! ነው ያላቸው፡፡ በጋራ ማህበራዊ ኑሮ  ስንገባ መጀመሪያ መወገድ ያለበት ይሄ ነው! ጠብ እንዴት ይቀራል ብለህ አሰብክ? ተብሎ ሲጠየቅ፤ ለጠብ የሚያነሳሱ ሁለት ነገሮች ናቸው (1) መጥፎ አነጋገር (2) መጥፎ አሠራር፡፡ እነሱን ካስወገድናቸው ጠብ የለም፡፡ ስሙም የለም፡፡ ሥርም አይኖረውም፡፡ ለጠብ የሚያነሳሳን በሀሳብም፣ በአሠራርም ራስ ወዳድነት ሲበዛ ነው! መብት ለመብት ተከባብረን ከሄድን ጠብ የለም። ስምም አይኖረውም! እሺ ምድራዊ ገነትንስ እንዴት ነው መፍጠር የምንችለው? ብለውታል፡፡ ምድራዊ ገነትን እኛ የምንችለው ነው፡፡ ማንም ሰው መጥቶ እንዲፈጥርልን አንጠብቅም፡፡ ምድራዊ ገነት የሚፈጠረው አንድ ሰው ችግር ሲደርስበት ዝም ብለን መመልከት ሳይሆን፤ ሁላችንም እጃችንን አውጥተን የዛን ሰው ችግር መርዳት ማስወገድ ነው! (የጉዞዬ ማስታወሻ የመጨረሻውና ከዙምራ ጋር ያደረግሁት ውይይት ይቀጥላል)  

Published in ባህል

          የአፍሪካ ነባር ባህል፣ ባለፉት 25 አመታት ምን ያህል እንደተረዘ በግልፅ አየነው - በደቡብ ሱዳን። ተቀናቃኞቹ ወገኖች፣ ገና ተኩስ ከመጀመራቸው፣ በጦርነት የመቀጠል ፋታ አልተሰጣቸውም። በቃ፣ በድንበር መዋጋት ወይም እርስበርስ እንደልብ መፋጀት ከእንግዲህ ለአፍሪካዊያን አይፈቀድም ማለት ነው?
ድሮኮ እንዲህ አልነበረም። ግጭትን ከትውልድ ትውልድ ማውረስና ማሸጋገር የለመደ አህጉር፣ አሁን ጦርነት ተከልክሎ ምን ሊውጠው ነው? ቢያንስ ቢያንስ፣ አስር አመት ወይም ሃያ አመት መዋጋት ለአፍሪካ ብርቅ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ... እና ሌሎች ከደርዘን የሚበልጡ የአፍሪካ አገራትን መጥቀስ ይቻላል። አይገርምም? ዛሬ ከሶማሊያና ከኮንጎ በስተቀር፣ የያኔዎቹ የጦርነት አውድማዎች ከሞላ ጎደል ሰላም አግኝተዋል። የብዙዎቹ አገራት የእርስ በርስ ጦርነት እየከሰመ ጠፍቷል ወይም ረግቧል። በአንዱ ወይም በሌላው አገር አዲስ ግጭት ስንለኩስም፣ በጦርነት በርካታ ወራትና አመታት ሳይቆጠሩ ፍጅቱን በአጭሩ ለመቅጨት መሯሯጥ ተለምዷል።
አሁን አሁንማ፣ ፈፅሞ ለጦርነት ጊዜ የሚሰጠን ሰው እየጠፋ ነው። ደቡብ ሱዳንን ተመልከቱ። ለአዲስ ጦርነት የተነሳሱት ባላንጣዎች፤ የአንድ ሳምንት የውጊያ ጊዜ እንኳ አላገኙም። ከግራና ከቀኝ፣ ከጎረቤትና ከሩቅ፣ ከጓዳና ከአደባባይ... አለም ሁሉ “ተረጋጉ፣ እረፉ፣ አደብ ግዙ” እያለ ዘመተባቸው። “ጦርነት ካልቆመ እመጣላችኋለሁ” የሚል ማስፈራሪያ ከሰነዘረችው ከኡጋንዳ ጀምሮ እስከ አሜሪካ፣ ከአፍሪካ ህብረት እስከ ዩኤን፣ ከኢትዮጵያ እስከ ቻይና፣ ከኢጋድ እስከ አውሮፓ፣ በግልና በቡድን ድምፁን ያላሰማ የለም ማለት ይቻላል። እንደየዝንባሌው፣ ገሚሱ ሸምጋይና አደራዳሪ፣ አንዳንዱ ተቆጪና መካሪ፣ ሌላኛው ገላጋይና ሰላም አስከባሪ እየሆነ፣  አለማቀፉ ማህበረሰብ (አዳሜ በሙሉ) ከየአቅጣጫው ሲያጣድፋቸው፣ ደቡብ ሱዳኖች ሳይደነግጡ አይቀሩም።
በቃ፣ “እንደልብ መዋጋትና እድሜ ልክ መፋጀት ድሮ ቀረ!” ልንል ነው? ድሮ ድሮኮ፣ አፍሪካዊያን እንዳሻቸው በጦርነት ቢፋጁ ከልካይ አልነበራቸውም። ደግሞም አይገርምም። በብዙ የአፍሪካ አገራት፣ የአንዱ ጎሳ ተወላጆች፣ በሌላ ጎሳ ተወላጆች ላይ እየዘመቱ፣ ከብት መዝረፍና መንደር ማቃጠል፣ አካል መቁረጥና በጅምላ መግደል፣ ከጥንት ጀምሮ የተለመደ ነባር ባህል ነው። ስሙን እናሳምረው ካልን፣ “ቱባ ባህል” ልንለው እንችላለን - ለረዥም ዘመን ዛይበረዝና ሳይከለስ የዘለቀ! ጥንታዊው የጎሳ ዘመቻ፣ በሃያኛው ክፍለዘመንም ቢሆን፣ ከዘመኑ አኗኗር ጋር መልኩ ቢቀየርም ጨርሶ አልቀነሰም። እንዲያውም ይበልጥ ሲጧጧፍና ዘግናኝነቱ ሲብስበት ነው ያየነው። በቋንቋና በብሄረሰብ ወይም በፖለቲካ ድርጅት ተቧድኖ መጨፋጨፍ፣ የአፍሪካ መለያ ባህርይ እስከመሆን የደረሰው በ20ኛው ክፍለዘመን አይደል?
ኢትዮጵያ ውስጥ በእርስበርስ ጦርነት ከ150 ሺ ሰው በላይ፣ በኢትዮኤርትራ የድንበር ጦርነትም ከ70 ሺ ሰው በላይ አልቋል። በላይቤሪያ የሰባት አመታት ጦርነትም እንዲሁ 150 ሺ ሰው ሞቷል። የአፍሪካውያን የጦርነት ሱስና የፍጅት ባህል ባይቀየርም፤ ፍጅቱ እየበዛ የመጣው አለምክንያት አይደለም። ዛሬ በዘመናችን፣ እንደጥንቱ በጎራዴና በጦር ሳይሆን፣ በክላሺንኮቭና በታንክ ነው የሚጨፋጨፉት። አንጎላዊያን ለሃያ አመታት ባካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነት፣ የግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በሱዳን የዳርፉር ግዛት፣ በሁለት አመታት ግጭት ሰበብ ሁለት መቶ ሺ ሰዎች ሞተዋል። በሴራሊዮንም እንዲሁ፣ ከሞተው ህዝብ የማይተናነስ ቁጥር ያላቸው ሰዎች፣ በጭካኔ እጃቸው ተቆርጧል።
ታዲያ፣ ያ ሁሉ ሰው ያለቀው፣ “ሕዝቡን ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተናል” በሚሉ ሶሻሊስት መሪ፣ ወይም “ሕዝቡን ከአምባገነን መሪዎች ነፃ እናወጣለን” በሚሉ ሶሻሊስት አማፂዎችና አገር ወዳድ አርበኞች አማካኝነት ነው። እርስ በርስ ሲጨፋጨፉ፣ “አለማቀፉ ማህበረሰብ” ምን ይሰራ ነበር ትሉ ይሆናል። አንዳንዱ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ጦርነቱን ያባብሳል። አንዳንዱ፣ “እንደፍጥርጥራቸው” ብሎ አይቶ እንዳላየ ኑሮውን ይቀጥላል። ነገር ግን፣ ተግሳፅና ምክር ለመለገስ የተጣጣሩ አልነበሩም ማለት አይደለም። ገላጋይና አስታራቂ ለመሆን የሞከሩ አልጠፉም። ቢሆንም ሰሚ አላገኙም። እንዲያውም ስድብ ነው የተረፋቸው። “በውስጥ ጉዳያችን ላይ ጣልቃ አትግቡብን፤ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ናችሁ” ተብለው ይዘለፋሉ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ ዋነኛ መርህ “በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት” የሚል እንደነበረ አታስታውሱም? አፍሪካዊያን “ጣልቃ አትግቡብን” እያሉ የሚከራከሩት፤ እያንዳንዱ አገር የውስጥ ጉዳዩን በራሱ ምርጫ እየመራ ተከባብሮ ለመኖር በማሰብ እንዳይመስላችሁ። ያለከልካይ እርስ በርስ ለመተላለቅ ነው።
የአፍሪካዊያን እልቂት ከጣሪያ በላይ አልፎ አለምን ለማስደንገጥ የበቃው ግን፣ በሩዋንዳ ከዚያም በኮንጎ በተከሰቱ ዘግናኝ ጦርነቶችና ግጭቶች ነው። በአንድ አመት የእርስ በርስ ፍጅት ነው፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሩዋንዳዊያን የረገፉት። የኮንጎ ደግሞ የባሰ ነው። ጦርነትና ረሃብ ተደማምሮ፣ በአስር አመታት ውስጥ፣ 5.4 ሚሊዮን የኮንጎ ሰዎች መሞታቸውን አለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት ገልጿል።
ደግነቱ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ አፍሪካዊያን ጥንታዊ የጦርነት ሱሳቸውንና የፍጅት ባህላቸውን የሙጢኝ ይዘው መቀጠል አልቻሉም። ምክንያቱ ሚስጥር አይደለም፡፡ የጥንቱ የፍጅት ባህል እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሲቀላቀሉ ነው፤ አህጉሪቱ በደም የታጠበችው። በጥንቱ ዘመን፣ አፍሪካዊያን ብዙ ሰውዎችን የመግደል ፍላጎት እንጂ ብዙ ሰዎችን የመግደል አቅም አልነበራቸው። ሹል እንጨት ቀስሮ ለጦርነት የሚዘምት ተዋጊ፣ አገር ምድሩን የመጨፍጨፍ እድል አያገኝም። እንጨቱ ይዶለዱማል ወይም ይሰበራል። አልያም እያሳደደ ሲገድል ውሎ፣ አመሻሹ ላይ ደክሞት ይዝለፈለፋል። ባደክመው እንኳ ጊዜ አይበቃውም - እያንዳንዱን ሰው ማሳደድና በእንጨት መውጋት ከባድ ፈተና ነው። ክላሺንኮቭ ታጥቆ በእሩምታ ደርዘኖችን መረፍረፍ፣ በታንክ መንደሮችን ማረስ የቻለ ጊዜ ነው፤ ጥንታዊ የፍጅት ባህል ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ ጎልቶ መታየት የጀመረው። ጥንታዊ ባህልን ይዞ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው የአፍሪካ ሕዝብ፣ ብዙም በሕይወት የመቆየት እድል እንደሌለው በአህጉሪቱ ከተከሰቱ እልቂቶች መረዳት ይቻላል።
እናስ ምን ተሻለ? ያለከልካይ የመጨፋጨፍ ቱባ ባህል የግድ ተወግዶ፣ በምትኩ ተከባብሮ የመኖር ባህል መፈጠር አለበት። በዚህ ምክንያት፣ “ወግና ልማድ ተሻረ፤ ቱባ ባህል ተበረዘ” የሚል ቁጭት የሚያድርባቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆን? የሚኖሩ ከሆነ፤ “ነገር የተበላሸው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ነው” ማለታቸው አይቀርም። እውነትም፤ ኢትዮጵያንና ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ፣ በአህጉሪቱ አራት አቅጣጫዎች፣ የጥንቱን ባህል የሚቃረን የለውጥ አየር ከዳር እስከ ዳር የነፈሰው፣ ያኔ ነው። የለውጡ መጠንና የነፋሱ ጉልበት፣ እንደየአገሩ ሁኔታ ይለያያል። የአንዳንዶቹ ፈጣን ሲሆን፣ የሌሎቹ ዘገምተኛ ነው። ገሚሶቹ፣ በእመርታ ሲራመዱ፤ ገሚሶቹ ይንፏቀቃሉ። ከፊሎቹ ያለማቋረጥ ሲሻሻሉ፤ ከፊሎቹ መነሳትና መውደቅ ያበዛሉ። ጠንካራ መሠረት የተከሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከአፍታ እልልታ በኋላ ወደ ዋይታ የተመለሱም አሉ። ከጦርነት ለመላቀቅ ጊዜያዊ መፍትሄ ማበጀትና የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረም ብቻውን በቂ አይደለማ፤ ተከባብሮ ለመኖር ዘላቂ መላ መፍጠር ያስፈልጋል።
የሆነ ሆኖ፣ መጠኑና ደረጃው ቢለያይም፤ በ80ዎቹ ዓ.ም መግቢያ ግድም፣ በአዲስ የለውጥ ነፋስ ያልተነካ የአፍሪካ አገር የለም ማለት ይቻላል። በአፍሪካ የለውጥ አየር የነፈሰው፤ በራሺያ መሪነት አለምን ሲያተራምስ የነበረው የሶሻሊዝም ስርዓት በተፈረካከሰ ማግስት መሆኑ አይገርምም። ያው እንደምታውቁት፣ በሶሻሊዝም ስርዓት ተከባብሮ መኖር አይቻልም።
ሶሻሊዝም ማለት የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት ስለሆነ፤ የፈላጭ ቆራጭነትን ስልጣን ለመያዝ፣ የግድ መጠፋፋትና መፋጀት ያስፈልጋል። ብዙዎቹ የአፍሪካ መንግስታትና አማፂ ሃይሎች፣ ሶሻሊስት ለመሆን የተሯሯጡት ለምን ሆነና! ሶሻሊዝም ከጥንታዊው አፍሪካዊ የፍጅትና የጦርነት ባህል ጋር ይጣጣማላ። ደግነቱ፣ በ1980 ዓ.ም መፍረክረክ የጀመረው የሶሻሊዝም ስርዓት፣ በ1983 ዓ.ም ሶቭየት ዩኔን ስትበታተን ነው ተፈረካክሶ አበቃለት። ይሄው የለውጥ ነፋስ፣ አፍሪካን ለማዳረስ ጊዜ አልፈጀበትም። እንዴት በሉ።
ከዚያን ጊዜ በፊት፣ በአፍሪካ ለስም ያህል፣ የፓርቲዎች ፉክክርና የምርጫ ውድድር የሚያካሂዱ አገራት ከሁለትና ከሶስት አይበልጡም ነበር። አንዷ ቦትስዋና ናት። በተወሰነ ደረጃ ደግሞ፣ ሴኔጋል ትጠቀሳለች።
ሌሎቹ አገራት በሙሉ ማለት ይቻላል፤ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የነገሰባቸውና፣ “ተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም በእስር ወይም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው” የሚል ህግ ያወጁ፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ፣ ለበርካታ አመታት በእርስ በርስ ጦርነት የሚታመሱ አገራት ነበሩ። አማፂው ሃይል፣ በጦርነት አሸንፎ ስልጣን ሲቆናጠጥም፣ በተራው የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ስለሚያሰፍን ሌላ ዙር ጦርነት ይቀጣጠላል። ማብቂያ በሌለው የአምባገነንነትና የፍጅት አዙሪት ውስጥ በነበረችው አህጉር ላይ፣ አዲስ የለውጥ አየር ሲነፍስ ይታያችሁ። በጦርነት ብዛትና በአንድ ፓርቲ አገዛዝ የተጥለቀለቀችው አህጉር፣ በሰላም ድርድርና በአዳዲስ የህገመንግስት ረቂቆች ተጥለቀለቀች።
ለምሳሌ ለረዥም አመታት በአንጎላ፣ በሞዛምቢክና በኢትዮጵያ ሲካሄዱ የነበሩ ጦርነቶች እልባት ያገኙት በተመሳሳይ ጊዜ ነው። እነዚህ ሶስት የጦርነት አገራትን ጨምሮ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ናይጄሪያ፣ ኒጀር እና ዛምቢያ፣ ታንዛኒያና ኬኒያን…ምን አለፋችሁ? ከሰሃራ በታች፣ 25 ገደማ አገራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማቋቋም የሚፈቅድ ህገመንግስት ያዘጋጁትና ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ምርጫ ማካሄድ የጀመሩት ከ1982 እስከ 1987 ዓ.ም ባሉት አምስት አመታት ነው። በቃ፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው፣ የነፃነት ሜዳው ሰፊም ሆነ ጠባብ፣ የፖለቲካ ምርጫ የማያካሂድ አገር እንደ ነውረኛ መታየት የጀመረው። አሁን እንደ ኤርትራና ሱዋዚላድ ከአለም የተገለሉ አገራት ካልሆኑ በቀር፤ የአንድ ፓርቲና የአንድ ግለሰው አምባገነንነትን በአዋጅ የሚያሰፍን የአፍሪካ አገር የለም ማለት ይቻላል። ከዚሁ ጎንም ነው፤ “ያለከልካይ እንደልብ በእርስበርስ ጦርነት የመፋጀት ባህል” የተበረዘው።
የምታስታውሱ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሃያ አመታት ያህል፣ የእርስ በርስ ጦርነት ሲካሄድ፣ አለም “እሪ” አላለብንም። ሊያስቆመን አስቦ እጁን ያስገባ ማንም የለም። የሰላም አስከባሪ ሃይል ማሰማራትማ ጨርሶ አይታሰብም ነበር። ያለገላጋይ እስኪለይለት ድረስ መፋጀት ነው። ከ1980ዎቹ ዓ.ም ወዲህ፣ በተለይ ከርዋንዳው እልቂት በኋላ ግን፣ አዲስ ጦርነት በተቀሰቀሰ ቁጥር፣ አለም እሪ ይላል። ሳምንት ሳይሞላው፣ ጎረቤት አገራት አደራዳሪ ቡድን ያቋቁማሉ። የአፍሪካ ህብረት የአቋም መግለጫና ውሳኔ ያስተላልፋል። ዩኤን በበኩሉ፣ በኬንያና በሱዳን፣ በላይቤሪያና በርዋንዳ እንደታየው፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ያካሄዱ መሪዎች ላይ ምርመራ ለማካሄድና ወደ አለማቀፉ የወንጀል ፍ/ቤት ለመውሰድ ይዝታል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ በፊናቸው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ይከፍታሉ።
በዚህ መሃል፣ “አልደራደርም፤ እንዳሻኝ እዋጋለሁ፤ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብኝ” ለማለት የሚደፍር ማን ነው? ዋጋውን ያገኛታላ። ጎረቤት አገራት ጦር ይልካሉ። የምዕራብ አፍሪካ አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ላይቤሪያ አዝምተው አልነበር? ኢትዮጵያና ኬንያም፣ ጦራቸውን ወደ ሶማሊያ አስገብተዋል። አሜሪካና አውሮፓም፣ እንደሁኔታው፣ ሊቢያ ላይ እንዳደረጉት የጦር አውሮፕላን ይልካሉ። ወይም እንደ ፈረንሳይ እግረኛና ኮማንዶ ጦር ያዘምታሉ። የተባበሩት መንግስታት እንኳ፣ እንደድሮው፣ ሰላምን የሚጠብቅ (Peace Keeping) ታዛቢ ሃይልን አይደለም የሚያሰማራው። በእርግጥ ስሙ አልተለወጠም። ተግባሩ ሲታይ ግን፤ “ሰላም አስከባሪ ተዋጊ ሃይል” ብለን ልንጠራው እንችላለን። በኮንጎ፣ በሴራሊዮንና በላይቤሪያ እንዳየነው፤ የተባበሩት መንግስታት ጦር፣ ለእርቅ እምቢተኛ ሆነዋል የተባሉ አማፂ ቡድኖችን እያሳደደ ወግቷል። አንዳንዳችን አስሮ ለፍርድ አቅርቧል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ወደ ሶማሊያ የዘመተው የአፍሪካ ህብረት ጦርም፣ ከአልሸባብ ጋር ይዋጋል።
በአጭሩ፣ ጊዜው ተለውጧል። እንደ ድሮ አይደለም፣ ዛሬ “አለከልካይ መፋጀት ለአፍሪካዊያን አይፈቀድም” የሚል ስሜት በርክቷል። ይሄውና የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች፤ ገና ወደ ጦርነት በገቡ ሳምንት፣ በሰላም ጥሪ መውጪያ መግቢያ አጥተዋል።

        ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን የሚወክሉት 5 ብሄራዊ ቡድኖች ምን ውጤት እንደሚኖራቸው በርካታ ዘገባዎችና ትንተናዎች  እየተሰሩ ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫው የአፍሪካ ቡድኖች እንደልማዳቸው በተሳትፎ ብቻ ተወስነው እንደሚቀሩ ብዙዎች ቢገልፁም፤ አዲስ የውጤት ክብረወሰን ሊመዘገብ እንደሚችል የገመቱም ይገኛሉ፡፡  የምድብ ፉክክሩን በማለፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ለመግባት እድል የሚኖራቸው የአፍሪካ ቡድኖች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተተንብይዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚቀላቀል አፍሪካዊ ቡድንም ሊኖር እንደሚችልም ተገምቷል፡፡   
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለዋንጫ የተጫወቱ አገራት አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካን የወከሉ ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስም አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ከሌሎቹ አህጉራት በከፍተኛ ሁኔታ ይበልጣሉ። ከሁለቱ አህጉራት ውጭ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት ሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ሲሆኑ ሰሜንና መካከለኛው አሜሪካን የወከለችው አሜሪካ እና ኤሽያን የወከለችው ደቡብ ኮርያ ነበሩ፡፡
በዓለም ዋንጫ  መድረክ አፍሪካዊ ቡድኖች አንዳንድ አስደናቂ ውጤቶች ከማስመዝገብ ባሻገር፤ በጎል ደስታ አገላለፅ መላው ዓለም ከማስደመም እና ትልልቅ ተጨዋቾች በሚያገኙት የሚዲያ ትኩረት ከማነጋገር በቀር የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ ቡድኖችን የመፎካከር አቅም ሳይኖራቸው ቆይተዋል፡፡ በዓለም ዋንጫ መድረክ አንድም አፍሪካዊ  ቡድን ግማሽ ፍፃሜ ደርሶ አያውቅም፡፡ የአህጉሪቱን ከፍተኛ የዓለም ዋንጫ ውጤት ለሩብ ፍፃሜ መድረስ ሲሆን ይህ  3 ብሄራዊ ቡድኖች አስመዝግበዋል፡፡  በ1990 እኤአ ላይ ጣሊያን ባስተናገደችው 14ኛው ዓለም ዋንጫ ካሜሮን፤ በ2002 እኤአ ላይ ደቡብ ኮርያ እና ጃፓን ባዘጋጁት 17ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ሴኔጋል እንዲሁም በ2010 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ጋና  እስከ ሩብ ፍፃሜ መጓዝ ችለዋል፡፡
የአምስቱ አፍሪካ ቡድኖች ታሪክ፤ ብቃትና ግምት
ባለፉት 19 ዓለም ዋንጫዎች በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፈዴሬሽን አባል ከሆኑ 52 አገራት ለአንዴና ከዚያም በላይ 13 ብሄራዊ ቡድኖች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ከሰሜን አፍሪካ 5፣  ከምዕራብ አፍሪካ 7 ፤ እንዲሁም ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫ  ብዙ ጊዜ በመሳተፍ አንደኛ ደረጃ የወሰደችው 7 ጊዜ የተሳተፈችው ካሜሮን ናት፡፡ ናይጄርያ ለ5 ጊዜያት በመሳተፍ ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ፤ የሰሜን አፍሪካዎቹ ሞሮኮ ፣ቱኒዚያ እና አልጄርያ እያንዳንዳቸው ለ4 ጊዜያት በመካፈል፤ አይቬሪኮስት፣ጋና እና ደቡብ አፍሪካ እያንዳንዳቸው ለ3 ጊዜያት፤ ግብፅ ለሁለት ጊዜያት እንዲሁም ዛየር፡ አንጎላ፣ ሴኔጋል እና ቶጎ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በማስመዝገብ በተከታታይ ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡ የአፍሪካ ቡድኖች በ71 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከአውሮፓ ቡድኖች ጋር ተገናኝተው 15 ጊዜ ድል፣ 20 ጊዜ አቻ እንዲሁም 36 ጊዜ ሽንፈት አስመዝግበዋል። ከደቡብ አሜሪካ ጋር ቡድኖች  በ22 ጨዋታዎች ጋር ተገናኝተው 3 ጊዜ ድል ፣ 5 ጊዜ አቻ እንዲሁም 14 ጊዜ ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡ በ6 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከሰሜንና መካከለኛው አፍሪካ ቡድኖች ጋር ሲገናኙ 3 ድል፣ 2 አቻ እንዲሁም 1 ሽንፈት ውጤት ሲመዘገብላቸው፤ በ7 የዓለም ዋንጫ  ጨዋታዎች ከኤሽያ ቡድኖች ጋር ተገናኝተው 3 ጊዜ ድል፤ 3 ጊዜ አቻ እንዲሁም አንድ  ጊዜ ሽንፈት ነበራቸው፡፡  
በ20ኛው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ቡድኖች ያላቸው የፉክክር ደረጃ ከአውሮፓ እና ከደቡብ አሜሪካ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ግምት አግኝተዋል፡፡ በዚሁ ዓለም ዋንጫ አፍሪካዊ ቡድኖች የሌሉባቸው ሶስት ምድቦች ስፔን፣ ሆላንድ፣ ቺሊና አውስትራሊያ የሚገኙበት ምድብ 2፤ ኡራጋይ፣ ኮስታሪካ፣ እንግሊዝና ጣሊያን የሚገኙበት ምድብ 4 እንዲሁም ስዊዘርላንድ፣ ኤኳዶር፣ ፈረንሳይና እና ሆንዱራስ የሚገኙበት ምድብ 5 ናቸው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች በደቡብ አሜሪካ የተዘጋጀ ዓለም ዋንጫን የአውሮፓ ቡድን አሸንፎ አያውቅም በሚል ምክያት የአውሮፓን ሃያላን ከግምት ውጭ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የደቡብ አሜሪካ የአየር ሁኔታ እና ባህል ከአፍሪካ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን በመግለፅ አፍሪካን ከወከሉ አምስት ብሄራዊ ቡድኖች መካከል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚመዘገቡ ውጤቶችን ሊያሳኩ እንደሚችሉ ገልፀዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ናይጄርያ በአህጉሪቱ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለግማሽ ፍፃሜ የማለፍ እድል እንዳላት በሚል ተስፋ ማድረጉም አልቀረም። በአጠቃላይ ከአምስቱ የአፍሪካ ተወካዮች በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ውጤታማ እንደሚሆኑ ግምት ያገኙት በምርጥ ፕሮፌሽናሎች የተገነቡትና በወቅታዊ ብቃታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ያሉት ጋና እና አይቬሪኮስት ናቸው፡፡ ካሜሮን እና አልጄርያ ከተሳትፎ የማይዘል ውጤት እንደሚያገኙ ተጠብቋል፡፡ ታዋቂው የፈረንሳይ ተጨዋች እና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ማርሴይ ዴሳይ አይቬሪኮስት ሩብ ፍፃሜ እንደምትደርስ ሲገምት፤ የናይጄርያ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በበኩሉ የራሱ ቡድን በዓለም ዋንጫው ሩብ ፍፃሜ ለመድረስ ይታገላል ብሏል፡፡ የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ባለድል እንደሚሆኑ ግምት በመስጠት ይታወቅ የነበረው የብራዚሉ ፔሌ ነው፡፡ ፔሌ አፍሪካዊ ቡድን ዓለም ዋንጫን ማሸነፍ ይችላል ያለበት ይግዜ ተመን ከ10 ዓመት በላይ አልፎታል። የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ በሚኖራቸው ተሳትፎ እንደ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ቡድኖች ስኬት ለማግኘት የማይችሉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ያላቸው የተሳትፎ ኮታ ማነስ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ እግርኳስ ሰዎች አህጉሪቱ በዓለም ዋንጫ የሚኖራት የተሳትፎ ኮታ ጭማሪ ሊደረግበት ይገባል በሚል በፊፋ ላይ ግፊት እያሳደሩ ናቸው፡፡ 52 አገራት የሚያቅፈው የአፍሪካ አህጉር በዓለም ዋንጫ ያለው የተሳትፎ ኮታ 5 ሲሆን 53 አገራትን የሚያስባስበው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 13 ተሳታፊዎች አሉት፡፡ ይህ የተሳትፎ ኮታ ሚዛናዊ አይደለም በሚል እነ ሳሚ ኩፎር፤ ሳሙኤል ኤቶ እና ሌሎች የአፍሪካ እውቅ እግር ኳሰኞች አስተያየት ሰጥተዋል። በብዙዎቹ አስተያየቶች የአፍሪካ ቡድኖች ተሳትፎ በዓለም ዋንጫ ከ5 ወደ ሰባት ማደግ አለበት ተብሏል፡፡ ይህንኑ ሃሳብ ከደገፉ መካከል የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ሚሸል ፕላቲኒ ሲገኝበት በቀጣይ በ2018 እና በ2022 እኤአ ላይ በራሽያ እና በኳታር በሚደረጉት ዓለም ዋንጫዎች የአፍሪካ ኮታ ሊያድግ የሚችለው በ20ኛው ዓለም ዋንጫ በሚገኝ ውጤታማነት ነው፡፡ የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ስኬታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶችም መዘርዘር ይቻላል፡፡  በዓለም ዋንጫ ከመሳተፋቸው በፊት ባለው ጊዜ በቂ ዝግጅት አያደርጉም፤ በአውሮፓ እና በአገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን አቀናጅቶ ምርጥ ቡድን ለመስራት ይቸገራሉ፤ በየአገሮቻቸው ፌደሬሽኖች በዓለም ዋንጫ በሚገኝ ውጤት የሚሰጡ የቦነስ ክፍያዎች አለመኖር እና ማነስ እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሚነሱ ውዝግቦች መጠመዳቸው ትኩረት ያሳጣቸዋል፤ የብሄራዊ ቡድኖቹ አሰልጣኞች አገር በቀል መሆናቸው እና ዓለም አቀፍ ልምድ እና ተፎካካሪነት የሌላቸው መሆኑም ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡
የአረንጓዴዎቹ ንስሮች በረራ
የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነችው ናይጄርያ ብራዚል ላይ በታሪኳ ለ5ኛ ጊዜ ዓለም ዋንጫን ልትሳተፍ ነው፡፡ በ4 የዓለም ዋንጫዎች ላይ በነበራት የተሳትፎ ታሪክ 14 ጨዋታ አድርጋ 4 ድል፣ 2 አቻ 8 ሽንፈት የገጠማት ሲሆን 21 ጎሎች ተቆጥረውባት በተጋጣሚዎቿ ላይ 21 ጎሎችን አስመዝግባለች። በ4ቱ ዓለም ዋንጫዎች 14 ነጥብ በመሰብሰብ ከአፍሪካ በ3ኛ ደረጃ ከዓለም በ36ኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡     የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን ዓለም ዋንጫውን የምትሳተፈው ናይጄርያ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 35ኛ በአፍሪካ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የናይጄርያ ብሔራዊ ቡድን 362 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ ሲኖረው የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 18 ይደርሳል የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ እድሜ 24.10 ሲሆን በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 56 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ ናይጄርያ በምድብ 6  ከአርጀንቲና፤ ቦስኒያ ሄርዞጎቪና እና ኢራን ጋር ስትድለደል አረንጓዴዎቹ ንስሮች በስብስባቸው ወጣትነት መልካም ውጤት ለማግኘት የተገመቱ ናቸው፡፡
የወርቃማዎቹ ዝሆኖች  መጨረሻ
አይቬሪኮስት በ2 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ 6 ጨዋታ አድርጋ 2 ድል፣ 1 አቻና 3 የሽንፈት ውጤት ሲኖራት 9 ጎል ገብቶባት በተጋጣሚዎቿ ላይ ያስቆጠራቸቸው 9 ጎሎች ተመዝግቦላታል፡፡ በሁለቱ አለም ዋንጫዎች 7 ነጥብ ማግኘት የቻለችው አይቬሪኮስት በዚህ ስኬት ከአፍሪካ 8ኛ ደረጃ ሲሰጣት ከዓለም በ49ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የዝሆኖቹ  ወርቃማ ትውልድ በተከታታይ በተሳተፈባቸው 2 ዓለም ዋንጫዎች ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ምድቡን ማለፍ እንኳን ሳይችል ቀርቷል፡፡ ብራዚል ላይ በዓለም ዋንጫ በታሪክ 3ኛ ተሳትፎውን ያገኘው የዝሆኖቹ ወርቃማ ትውልድ  ለስኬት የመጨረሻ እድሉ ነው፡፡ አይቬሪኮስት በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 18ኛ በአፍሪካ 1ኛ ደረጃ ስትገኝ፤ 772 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ አላት፡፡ በብሐራዊ ቡድኑ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 25 አማካይ እድሜ 25 እንደሆነና አጠቃላይ  ስብስቡ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 135ሚሊዮን ፓውንድ ነው። የአይቬሪኮስት ብሄራዊ  ቡድን በምድብ 3 የተደለደለው ከኮሎምቢያ፤ ጃፓንና ግሪክ ጋር ነው፡፡
በተሳትፎ የማይበገሩት አንበሶች  
ካሜሮን በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የምትሳተፈው ለ7ኛ ጊዜ ሲሆን የአህገሪቱ ከፍተኛ የተሳትፎ ክብረወሰን ነው። አስቀድማ በተሳተፈችባቸው 6 የዓለም ዋንጫዎች 20 ጨዋታዎች አድርጋ 4 ድል 7 አቻ እና 9 የሽንፈት ውጤት ሲመዘገብላት በተጋጣሚዎቿ ላይ 17 ጎል አግብታ 34 ተቆጥሮባታል፡፡ በ6 ዓለም ዋንጫዎች ካሜሮን 19 ነጥብ በመሰብሰቧ ከዓለም 29ኛ ደረጃ ስታገኝ በዓለም ዋንጫ ከፍተኛውን ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ናት፡፡ ካሜሮን በ1990 እኤአ ላይ በጣሊያን ተደርጎ በነበረው ዓለም ዋንጫ ለሩብ ፍፃሜ በመድረስ የመጀመርያውን ከፍተኛ የአፍሪካ ቡድን የውጤት ክብረወሰን በማስመዝገብ ፈር ብትቀድም ይህን ስኬት መድገም ተስኗት ቆይቷል፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 51ኛ በአፍሪካ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የካሜሮን ቡድን ቡድን 498 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ አለው፡፡ ካሜሮን ያሏት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 28 ሲሆን የቡድኑ  አማካይ እድሜው 26 እንደሆነና አጠቃላይ ስብስቡ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 125 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን  በምድብ 1 ከብራዚል፤ ሜክሲኮ እና ክሮሽያ ጋር ተመድቧል፡፡  ቡድኑ ከጡረታ በተመለሰው፤ ከዓለማችን ምርጥ አጥቂዎች አንዱ በሆነውና ለአራት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች በነበረው ሳሙዔል ኤቶ የሚመራ ነው። የማይበገሩት አንበሶች በፈረንሳይ ሊግ በሚጫወቱ ምርጥ ተከላካዮች የተገነባ ቢሆንም በቡድኑ ተጨዋቾች መካከል ያለው መከፋፈል፤ ግጭት እና ከአቅም በታች የመጫወት አባዜ የ20ኛው ዓለም ዋንጫ ተሳትፎው ፈታኝ ሊሆንበት ይችላል፡፡
በሞት ምድብ ያሉት ጥቋቁር ክዋክብቶች
ጋና ባለፉት 2 የዓለም ዋንጫዎች ስታሳትፍ ባደረገቻቸው  9 ጨዋታዎች 4 ድል፣ 2 አቻ እና 3 ሽንፈት ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን በተጋጣሚዎቿ ላይ 9 አግብታ 10 ጎሎች አስተናግዳለች፡፡ በሁለቱ ዓለም ዋንጫዎች 14 ነጥብ መሰብሰብ የቻለችው ጋና በዓለም ዋንጫ ውጤቷ በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ሲሰጣት በዓለም 35ኛ ነች፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 24ኛ በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የጋና ብሄራዊ ቡድን 725 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ አለው፡፡ 34 ምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የሚያቅፈው ቡድኑ አማካይ እድሜ 25.20 ሲሆን አጠቃላይ ስብስቡ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 77 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ በነበረው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለመግባት ከፍተኛ እድል ይዛ ነበረ፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ታሳካዋለች ተብሎ ይገመታል፡፡ በከሞት ምድብ በተፈረጀው ምድብ 7 ከጀርመን፣ፖርቱጋልና አሜሪካ መገናኘቷ ትኩረት አግኝቷል፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን በወቅታዊ ብቃቱ የምርጥ አማካዮች እና አጥቂዎች ስብስቡ የተጠናከረ ነው፡፡
አልጄርያ ለሰሜን አፍሪካ ብቸኛ ተወካይ
ሰሜን አፍሪካን በብቸኛ የወከለችው አልጄርያ ከ20ኛው የዓለም ዋንጫ  በፊት አልጀሪያ በ3 የዓለም ዋንጫዎች ስትሳተፍ ባደረገቻቸው 9 ጨዋታዎች 2 ድል፣ 2 አቻ ና 5 የሽንፈት ውጤቶች ስታገኝ በተጋጣሚዎቿ ላይ 6 ጎል አግብታ በመረቧ ላይ 12 ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡  አልጄርያ አስቀድሞ በተሳተፈችባቸው 3 ዓለም ዋንጫዎች በሰበሰበችው 8 ነጥብ ከአፍሪካ ሰባተኛ ደረጃ ስተወስድ ከዓለም 47ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 34ኛ በአፍሪካ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የአልጄርያ ቡድን 300 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ ይዟል፡፡ የአልጄርያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 19 ሲሆን አማካይ እድሜ 26.8 የሆነና ድረገፅ አጠቃላይ የቡድን ስብስብ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 51.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ   ለ4ኛ ጊዜ ስትሳተፍ የተመደበችው ቀላል በተባለው ምድብ 8 ከቤልጅዬም፣ ደቡብ ኮርያ እና ራሽያ ጋር ነው፡፡ ከአራቱ የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ለአልጄርያ ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ዋና ጥንካሬዋ ተቀማጭነታቸውን በፈረንሳይ ያደረጉ ተጨዋቾችን በብዛት ያሰባሰበ ቡድን መያዟ ነው፡፡





          የልብ ሕመም፣ ካንሰር፣ ራስ ምታትና በርካታ የዕለት ተዕለት በሽታዎችን የሚከላከሉና የሚያሽሉ ተብለው በህክምና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የተረጋገጡ 12 ምርጥ ምግቦችን አስተዋውቃችኋለሁ።
ፊግስ:- ከበለስ ጋር የሚመሳሰል የፍራፍሬ ዓይነት ነው፡፡ እነዚህ ፍሬዎች እንደልብ አይገኙም እንጂ በውስጣቸው ካልሲየም የተባለውን ማዕድን የያዙ ናቸው። ፍሬዎቹ፣ ዕድሜን ተከትሎ የሚመጣውን የአጥንት መዳከም (Bone loss) ይከላከላሉ፡፡ ከፍተኛ አሰር (fibre) ስላላቸው፣ በደንዳኔ (Colon)፣ በጡትና በወንድ የዘር ፍሬ መንሳፈፊያ ፈሳሽ አመንጪ ዕጢ (Prostate) ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሳሉ፡፡
ያልተላጡ ትኩስ የፊግስ ፍሬዎችን ከትፈው ከአይብ ወይም ከሰላጣ ጋር ይመገቡ፡፡ እንዲሁም የደረቁ ፍሬዎችን የአትክልት ምግብ ላይ ጨምሮ መመገብ ይቻላል፡፡ በደንብ ያልበሰሉ ፍሬዎች ስለሚጐመዝዙ የበሰሉና ለስለስ ያሉትን ይምረጡ፡፡
ቀይ ስር፡- በንጥረ-ምግብ (Nutrient) የበለፀገው ቀይ ስር፤ ቀልጣፋና ፈጥኖ አሳቢ (Sharp mind) አዕምሮ እንዲኖረን ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ቀይ ስር፣ በማርጀት ላይ ባሉና  ቅልጥፍና በሌላቸው የአንጐል ክፍሎች ጭምር፣ የደም ዝውውር እንዲጨምር የሚያደርገውን ናትሪክ አሲድ (Nitric Acid) ያመርታል።
ስለዚህ ቀይ ስር ከትፈውና ጠብሰው ከእርጐ ጋር በመደባለቅ ወይም ጥሬ ቀይ ስር ልጠውና ከትፈው ከሰላጣ ጋር ይመገቡ፡፡ ሰውነት፣ በካንሰር እንዳይያዝ የሚረዳውን አንቲ ኦክሲደንት (Anti-oxident) በደንብ ማግኘት ከፈለጉ ግን ጥሬውን እንዲመገቡ ይመከራሉ፡፡
ትኩስ አጋም (Cranberries) እነዚህ ቀይ ወይም የቀይ ዳማ ፍሬዎች የሽንት ቧንቧ ሕመም (urinary tract infection) በማከም የሚስተካከላቸው የለም፡፡ የእነዚህ ትናንሽ ፍሬዎች ጐምዛዛ ጣዕምም፣የልብ ሕመምን ለመከላከል እንደሚረዳ ይታመናል፡፡ የአጋም ፍሬዎች LDL የተባለው አደገኛ ኮሌስትሮል ከኦክስጂን ጋር ተዋህዶ በደም ስር ግድግዳ ላይ እንዳይጣበቅ በሚያደርጉ anthocyanins፣ flavonols፣ እና Proanthocyanidins በተባሉ የአትክልት ኬሚካሎች የበለፀጉ ናቸው፡፡
ትኩስ ቀይ አጋም በጋለ መጥበሻ አመስ አመስ አድርገው፣ ከስጋ ወይም ከሙዝ፣ አናናስና ብርቱካን ሳላድ ጋር አደባልቀው ይመገቡ፡፡ ምክንያቱም የፍራፍሬዎቹ ጣፋጭነት የአጋሙን ጐምዛዛነት ይቀንሰዋል፡፡
የብርቱካን ልጣጭ (Orange Pith)፡- ብርቱካን በቫይታሚን ሲ የበለፀገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ብርቱካን ልጠው ቅርፊቱን (ልጣጩን) አይጣሉ። በቅርፊቱ የውስጠኛ ክፍል ተጣብቆ የሚገኘው ነጭ ለስላሳ ነገር (pith) ለጤና በእጅጉ ጠቃሚ ስለሆነ የቻሉትን ያህል ይመገቡ፡፡ መረር ቢልም አሰርና ኮለስትሮል ከደም ጋር እንዳይዋሃድ የሚያደርገውን አንቲኦክሲደንት (Antioxident) በብዛት ይዟል፡፡
የብርቱካን ቆዳ (ልጣጭ) ወይም የውስጡ ነጭ ለስላሳ (pith) ሲመገቡ፣ፀረ-ተባይ ያልተረጨበት የተፈጥሮ (Organic) ብርቱካን መሆኑን ያረጋግጡ።  
እንቁላል፡- እነዚህ የፕሮቲን ምንጮች ሌላም የጤና ጥቅም አላቸው፡፡ በእንቁላል ውስጥ የሚገኙት የብረትና የዚንክ ማዕድናት፣ ጤነኛ ፀጉርና ጥፍር እንዲኖረን ያደርጋሉ፡፡ እንዲሁም አስኳሉ ውስጥ የሚገኘው ለሲቲን (Iecithine) የተባለ ንጥረ-ቅመም፣ የተጐዱ የአንጐል ሕዋሳትን በሚጠግነውና ኮሌስትሮል ደም ስር ላይ ሳይጣበቅ በደም ውስጥ እንዲዘዋወር በሚያደርገው ኮሊን (Choline) በተባለ ማዕድን የበለፀገ ነው፡፡
የእንቁላልን አበላል ለመንገር መሞከር ምጥ ለእናቷ አስተማረች … ዓይነት ይሆናል፡፡ ነገር ግን እፍኝ ያህል ስፒናች ከእንቁላል ጋር ደባልቀው ወይም በአትክልት በተሞላ አትክልት አናት ላይ በደንብ ያልበሰለ (ለጋ) እንቁላል፣ ሰሊጥና የአኩሪ አተር ሾርባ ጨምረው ቢመገቡ፣ የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡
ሰሊጥ (Sesame seeds) የLDL (መጥፎ) ኮሌስትሮል መጠን ከፍተኛ የሆነባቸው ሰዎች፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሰሊጥን አይመገቡም ነበር፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ጥቂት ማንኪያ ሰሊጥ የበሉ ሰዎች የደም ኮሌስትሮላቸው 10 በመቶ መቀነሱን አንድ በቅርቡ የተካሄደ ጥናት አመልክቷል፡፡የተቆላ ሰሊጥ ከአጃ ጋር ደባልቃችሁ ወይም ያልበሰለ አትክልት፣ የሰሊጥ ፍሬ ወይም የሰሊጥ ዘይት ከሰሊጥ ቅቤ ጋር ደባልቃችሁ ተመገቡ፡፡
ሰናፍጭ (mustard)፡- ሰናፍጭ መፋጀቱ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ካንሰርን በሚከላከለውና  የልብ ሕመምን በሚያድነው፣ እንዲሁም ሴሎችን ከሚጐዱ ፍሪ ራዲካልስ (Free radicals) በሚከላከለውና የአካልን የበሽታ መከላከያ ሥርዓት በሚያነቃቃው Selenium በተባለ ንጥረ-ነገር የበለፀገ ነው፡፡  
የተጠበሰ አትክልት ላይ ሰናፍጭ በማድረግ ወይም የሰናፍጭ ዘይትና ኮምጣጤ አደባልቀው ሰላጣ ላይ በመጨመር ይመገቡ፡፡
የጠቦት ሥጋ፡- ከቀይ ሥጋ ሁሉ፣ የጠቦት ሥጋ የምግብ ይዘቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ደግሞ ከልብ በሽታና ከስትሮክ በሚከላከለው ኦሜጋ-3 (Omega-3) በተባለ ፋቲ አሲድ የበለፀገ ነው፡፡ በጠቦት ሥጋ ውስጥ የሚገኘው የብረት ማዕድንም ከሰውነታችን ጋር በቀላሉ ይዋሃዳል፡፡ ስለዚህም የደም ማነስ (anemia) ይከላከላል፣ የሰውነት ኃይልም ይጨምራል፡፡
ከጠቦቱ ጐንና ጐን (ወርች)፣ ከጭራው አካባቢ፣ ከጉበትና ከቁርጨምጭሚት መኻል ከሚገኝ ስፍራ ቀይ ሥጋ መርጠው ይቁረጡ፡፡ ሁሉም የቤተሰቡ አባል በሚሰበሰብበት ዕለት፣ ለእራት የጠቦት እግር ጠብሰው ያቅርቡ፡፡ እንዲሁም የተፈጨ የጠቦት ሥጋ በፒዛ ወይም በአትክልት አናት ጨምረው ይመገቡ፡፡
በጣም የቀዘቀዘ ብሮኮሊ (Frozen Broccoli) እንደ በረዶ የቀዘቀዘው የብሮኮሊ ዝርያ ከገበያ ከተገዛው ትኩስ ብሮኮሊ 35 በመቶ የበለጠ፣ በደም ውስጥ በመዘዋወር ጉዳት የሚያደርሰውን ፍሪ ራዲካልስ የሚዋጋውን ቤታ ካሮቲን የተባለ ንጥረ-ቅመም ይፈጥራል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ብሮኮሊ ውስጥ የሚገኘው ሰልፎራፎን (Sulforaphone) የተባለ ኬሚካል፤ ሳንባና የደም ስሮች (አርተሪስ) አመርቅዘው የማቃጠል ስሜት እንዳይፈጠር ይከላከላል፡፡ በቫይታሚን ሲ የበለፀገ መሆኑ ደግሞ ቆዳችን ጤናማ፣ ጠንካራና እንዲያንፀባርቅ የሚያደርገውን ኮላይጅን (collagen) የተባለ ንጥረ-ቅመም ለማምረት ይረዳል፡፡
 የሚፋጁት አትክልቶች (Chili):- ቃሪያና ሚጥሚጣ እንዲፋጁ (እንዲያቃጥሉ) የሚያደርገው ካፕሲያሲ (Capsaicin) የተባለው ኬሚካል፣ ደም ረግቶ ድንገተኛ የልብ በሽታና ስትሮክ እንዳይከሰት ሊረዳ ይችላል፡፡ በተጨማሪም፣ ቃሪያና ሚጥሚጣ መብላት፣ የአፍንጫና የጭንቅላት አጥንቶች ቧንቧ እንዳይጣበቁ ያደርጋል፤ የምግብ ስልቆጣንም እንዲፋጠን ይረዳል፡፡
ስለዚህ እነዚህን አትክልቶች ከትፎ እንቁላል፣ ሾርባና እና ሌሎች ምግቦች ውስጥ ጨምሮ መመገብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ኪዊ (kiwis) :- ይሄ አረንጓዴ ጣፋጭ ፍሬ ዓይን ጤናማ እንዲሆን የሚረዱትን ሉቲን (lutein) እና ዜዛንቲን (Zeaxanthin)  የተባሉ ኬሚካሎች ይዟል። የኪዊ ፍሬዎች፣ በቫይታሚን ሲ እና ኢ እንዲሁም በመጨረሻ ወደ ካንሰር ሊያደርስ የሚችለውን ፍሪ ራዲካልስ በሚዋጋው phytochemicals የበለፀጉ ናቸው።
የሾርባ ቅጠል(Celery leaves):- ሰዎች ብዙ ጊዜ አገዳውን ወስደው ቅጠሉን ይጥሉታል፡፡ ይሄ ግን ስህተት ነው፡፡ የሾርባ ቅጠል ከፍተኛ የምግብ ይዘት ያለው ከመሆኑም በላይ፣ ካልሲየም፣ አይረን፣ ፖታሲየም፣ ቤታ ካሮቲንና ቫይታሚን ሲ፣ ከአገዳው በላይ ይዟል፡፡ ስለዚህ እንደፓርሲሊ አድቀው በመክተፍ ምግቦች ላይ ነስንሰው ወይም ከሳላድ ጋር ደባልቀው ይመገቡ፡፡
ምንጭ፡- (Reader’s digest, March, 2013)

Published in ዋናው ጤና

ማማሟቂያ
አየለ ሞተ!... በድፍን ደብረ ማርቆስ ዝናው የናኘው ቀልደኛው፣ ተረበኛው፣ የቀን ሰራተኛው አየለ፤  ቋጠሮ ተሸክሞ ሲመላለስበት ከኖረው የከተማዋ ጎዳና ዳር ተፈጽሞ ተገኘ፡፡ ትናንት ቀልዱን ሰምተው ተንከትክተው የሳቁ፣ ዛሬ ጧት ሞቱን ሰምተው ተንሰቅስቀው አለቀሱ፡፡
ከጓደኞቹ ጋር መጠጥ ቢጤ እየቀማመሱ ሲጨዋወቱ አምሽተው፣  “በሉ ደህና እደሩ!” ተባብለው ተሰነባብተው ነበር፣ ሁሉም ወደ ማደሪያቸው ጉዞ የጀመሩት፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል፣ አየለ ደህና አላደረም፡፡ በእግሩ ላይ የነበረበት አካል ጉዳት ከስካሩ ጋር ተዳምሮ፣ ድንገት መዝነብ ከጀመረው ዶፍ ማምለጥ አላስቻለውም፡፡ ውሽንፍሩና ዶፉ ተባብረው ከመንገድ ዳር ካለ የጎርፍ መፍሰሻ ቱቦ ስር ጣሉት። ታግሎ የሚያመልጥበት እንጥፍጣፊ አቅም ያልነበረው አየለ ተሸነፈ።  ጨለማ ውስጥ እንደወደቀ ዶፍ ቀጠቀጠው፣ ጎርፍ አሰመጠው፡፡ ጧት ላይ አስከሬኑ ቱቦ ስር ደለል ሰርቶበት ተገኘ፡፡
የአየለ ሞት በመላ ደብረ ማርቆስ ተሰማ፡፡ ሁሉም ስለ አየለ አዘነ… እና ደሞ ተጨነቀ፡፡ ሃዘኑ ስለሞቱ፣ ጭንቀቱ ስለ ቀብሩ ነበር፡፡ በወግ በወግ አድርጎ የሚቀብረው የስጋ ዘመድ አልነበረውም፡፡ ዘመዱ ህዝቡ ነበር፡፡ በሸክም የሚያገኘው የማያወላዳ ገቢም የእድር አባል የሚያደርገው አልነበረም። በቅርብ የሚያውቁት ግለሰቦች አስከሬኑን አንስተው እንደሚሆን አድርገው ለመቅበር ወዲያ ወዲህ ማለት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው፣ የአየለን ሞት የሰሙ በከተማዋ የሚታወቁ ባለሃብቶች፣ ሟች በህይወት ሳለ የሰጣቸውን አደራ ይዘው ከያሉበት ብቅ ብቅ ያሉት፡፡
“እኔ ጋ 500 ብር አለው”፤“ይሄው… 350 ብር”፤“ለእኔ 150 ብር ነው የሰጠኝ… ይሄውላችሁ!” የሚለው የባለሃብቶች ያልተጠበቀ ንግግር ተደመጠ፡፡ አየለ ግን፣ አንድ ቀን ይህ እንደሚሆን ይጠብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን መታመሙ ወይም መሞቱ እንደማይቀር ያውቅ ነበር፡፡ “ቢያመኝ ጎረቤትን፣ ብሞትም መንግስትን ማስቸግር አልፈልግም!… ይህቺን ለክፉ ቀን አስቀምጡልኝ!” እያለ፣ ቋጠሮ ተሸክሞ የሚያገኘውን ገንዘብ በአደራ ያስቀምጥ ነበር፡፡ ይህን የሚያደርገው፣ ገንዘብ ይዞ መገኘትን የሚጠይቅ አንዳች አስቸገሪ ሁኔታ የሚከሰትበት ወሳኝ ወቅት ሊመጣ እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው፡፡ የአየለ ጥንቃቄና አርቆ አሳቢነት በወቅቱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የግርምቱ ሰበብ ሁለት ነው፡፡ አንድም እታመማለሁ ብሎ በማሰብ መታከሚያ ገንዘብ ማጠራቀሙ፣ ሁለትም ከእለት ወጪው ቆጥቦ ለክፉ ቀን የሚቀመጥ ገንዘብ ማግኘቱ፡፡
እንዲህ እንደ አየለ ቀድመው ያልተዘጋጁ ወይንም ለመዘጋጀት አቅም የሌላቸው ብዙዎች ግን፣ ለሚያጋጥማቸው ድንገተኛ የጤና እክል መታከሚያ የሚሆን ገንዘብ በማጣት ለከፋ ስቃይና ለሞት መዳረግ ዕጣቸው ነው፡፡ ከፍለው ይታከሙበት በቂ ገንዘብ አጥተው፣ ከጤና ተቋማት ደጃፍ ሳይደርሱ በህመም ሲሰቃዩ ቆይተው ለሞት የሚዳረጉ በርካቶች ናቸው፡፡
ከዕለት ተዕለት ኑሮ ተርፎ ድንገት ለሚከሰት የጤና እክል መታከሚያ ተብሎ የሚቀመጥ በቂ ገንዘብ የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል እምብዛም ነው፡፡ በህክምና ወጪ እጦት ተገቢውን ህክምና ማግኘት ተስኗቸው ለስቃይና ለሞት ከሚዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ በወርሃዊ ደመወዝ የሚተዳደሩ ተቀጣሪዎችና ጡረተኞች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡
በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት ለሚሰሩ ሰራተኞች ህክምና የሚውል የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ቅጽ በየቢሮው ሲዞር መመልከት የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ደመወዛቸው ቤተሰብ ከሚያስተዳድሩበት የወር ወጪ ተርፎ ለህክምና ክፍያ አልበቃ ብሏቸው፣ የመስሪያ ቤት ባልደረቦቻቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለመጠየቅ የሚገደዱ ታማሚ ሰራተኞች ብዙዎች ናቸው። ችግሩ ግን በዚህ መልኩ አስር አምስት ተብሎ የሚሰበሰበው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑና ለህክምና በቂ አለመሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ህመም እንደ ደመወዝ ወር ጠብቆ አይደለም የሚመጣው። ገንዘቡ የሚሰባሰበው ሰራተኛው ደመወዝ በሚቀበልበት ወቅት በመሆኑ፣ በተፈለገው ወቅት ደርሶ ታማሚውን የመታደግ ዕድሉ እምብዛም ነው፡፡
ድንገተኛ የጤና እክሎች ሲከሰቱ የሚፈጠረውን የህክምና ወጪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው፣ በችሮታ ላይ በተመሰረቱና አስተማማኝነት በሌላቸው መደበኛ ያልሆኑ መሰል የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለጊያ መንገዶች አይደለም፡፡
የማህበረሰቡ የመረዳዳት ባህል የሚገለጽባቸው እንደ እድር ያሉ ተቋማት ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ከሞት በኋላ እንጂ በህይወት እያሉ ድጋፍ ለማድረግ ትኩረት የሚሰጡ አይደሉም። ብዙዎቹ የማህበረሰብ ዕድሮች ዕድርተኞች በህይወት እያሉ ከሚገጥማቸው የጤና ችግር ለሚላቀቁበት የህክምና ወጪ ሳይሆን፣ ከሞቱ በኋላ ለሚመጣው ቀብራቸውና ለንፍሮ ግዢ ገንዘብ የሚያወጡ ናቸው፡፡
እርግጥ በአንዳንድ አገራት ዕድሮችን የመሳሰሉ የማህበረሰብ ተቋማትን የበለጠ በማደራጀት እንደ አማራጭ የጤና ፋይናንስ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡ እድሮችን እንደ አማራጭ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ፣ በአፍሪካ ደረጃ የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው ጋናን በመሳሰሉ ጥቂት አገራት አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም በአብዛኞቹ አገራት ይህ ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም፡፡ ጥናቱ እንደሚለው በእድሮች አማካይነት በተበጣጠሰ ሁኔታ የሚሰሩ መሰል የጤና መድህን ስራዎች ዘላቂነታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ አሰራሩ ከአባላት ቁጥርና ከመዋጮው ማነስ ጋር ተያይዞ በቂ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስችል ካለመሆኑም በላይ፣ ዕድሮች በተለያዩ ምክነያቶች የመፍረስ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የአማራጩን ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡
በአገራችንም ዕድሮችን እንደ አማራጭ መጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም በየካቲት ወር ዕድሮችን መሰረት ያደረገ የጤና መድህን አገልግሎት ለመዘርጋት ታስቦ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በጅማ ከተማ የተመረጡ 4 ቀበሌዎች ዙሪያ የተሰራው የናሙና ጥናት ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡ የከተማዋን ማህበረሰብ ፍላጎትና የዕቅዱን አዋጪነት ለመገምገም ታስቦ የተሰራውና፣  ‘የጅማ ከተማ ዕድሮችን በአማራጭ የጤና ክብካቤ አገልግሎት የፋይናንስ ምንጭነት መጠቀም’ የሚለው የዚህ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፣ ማህበረሰቡ በእድሮች አማካይነት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡ በዚህ የናሙና ጥናት ጥያቄ ከቀረበላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች 76.5 በመቶው  ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል። ቀደም ብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰራ ጥናትም በአገሪቱ የእድር አባል ከሆነው ቤተሰብ 94.7 በመቶ ያህሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት አለው፡፡
ችግሩ ግን፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ባልተደራጀ ሁኔታ የሚከናወነው ይህን መሰሉ አሰራር፣ ረጅም ርቀት የሚያስኬድና የህግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት ዜጎችን በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ የሚያደርግ አለመሆኑ ነው፡፡ ይልቁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ለሚታየው የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ፍላጎት በተደራጀ፣ መንግስታዊ እውቅና ባለው፣ የአገሪቱን የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ባማከለና ዜጎችን የበለጠ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ምላሽ መስጠት ተመራጭ ይሆናል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት ይህን መሰሉ ያልተደራጀና አስተማማኝ ያልሆነ አካሄድ ለዜጎች የጤና ወጪ ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የማይሰጥ መሆኑን በመገንዘብ ነው፣ አስተማማኝ የሆነና በአግባቡ የተደራጀ የጤና መድህን ዋስትና ስርዓትን ለመዘርጋት ከረጅም ዘመናት በፊት ጥረት ማድረግ የጀመሩት።
የማህበራዊ የጤና መድህን፣ ጅማሮና ተሞክሮ
 አውሮፓዊቷ ጀርመን የአለማችን ዘመናዊና አሃዳዊ ማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት መነሻ ናት፡፡ ጊዜው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1883 ዓ.ም፡፡ ከዚያ በፊት በአገሪቱ የነበሩትን የተበታተኑና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረቱ የመድህን ማህበራት ወደተቀናጀ፣ በማዕከላዊ መንግስት ወደሚደጎምና ወደሚመራ እንዲሁም ግዴታን መሰረት ወዳደረገ ስርዓት እንዲለወጥ ያደረገው፣ የአገሪቱ ቻንስለር የነበረው ኦቶቫን ቢስማርክ በወቅቱ ያወጣው ህግ ነበር፡፡
ጀርመንም ሆነ ሌሎች አገራት የጤና መድህን ስርዓቶቻቸውን አደረጃጀት በሂደት የማስተካከል እርምጃ ወስደዋል፡፡ ከተበታተኑና በፈቃደኝነት ላይ ከተመሰረቱ የማህበረሰብ መረዳጃ ማህበራትነት፣ ወደ አገር አቀፍና በማዕከላዊ መንግስት ህግ የተደገፉ ተቋማትነት በማሸጋገር ዜጎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡ የዚህን አሰራር ጠቀሜታ የተረዱት የተለያዩ የአፍሪካ አገራትም፣ ባለፉት 25 አመታት የተለያየ አደረጃጀት ያለው የጤና መድህን ዋስትና ለመዘርጋት ጥረት አድርገዋል፡፡
‘የማህበራዊ የጤና መድህን ስኬት፣ ውድቀትና መልካም ተሞክሮዎች በሰብ ሰሃራ የአፍሪካ አገራት’ በሚል ርዕስ ኤ.ኤም ስፒወርስና ግሪት ጃን ዲናት ለንባብ ያበቁት ጽሁፍ እንደሚያሳየው፣ በአፍሪካ አገራት በጤና ፋይናንስ ምንጭነት ከሚውሉት አማራጮች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ከታካሚዎች የሚገኝ ክፍያ ነው፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው፣ በሁሉም የአፍሪካ አገራት እ.ኤ.አ በ2007 ከወጣው የጤና ወጪ 50 በመቶው ከግል ምንጮች የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ወጪ 71 በመቶው የተገኘውም ታካሚዎች ከከፈሉት የህክምና ወጪ ነው፡፡ ይህም በታካሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር መሆኑን ጸሃፊዎቹ ይናገራሉ፡፡
ጋና፣ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራትም በዜጎቻቸው ላይ የሚደርሰውን የህክምና ወጪ ጫና ለማቃለልና የጤና አገልግታቸውን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ፣ ማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት ዘርግተው መተግበር ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ አገራቱ ስርዓቱን በመዘርጋታቸው፣ ዜጎቻቸው በተለይም ደግሞ ድሆች በከፍተኛ የህክምና ክፍያ ሳቢያ የተለየ የኑሮ ጫና እንዳያድርባቸው በማድረግ የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ከማዳረስ ባለፈ፣ የፋይናንስ አቅማቸውን በማሳደግ የጤና አገልግሎታቸውን ለማስፋፋት ችለዋል፡፡
አገራቱ የማህበራዊ የጤና መድህንን ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት የሰጡት፣ አሰራሩ ዜጎች ድንገት ከሚከሰቱ በሽታዎች ለመዳን ጥሪታቸውን አሟጠው በሚያፈሱት ያልታሰበ የህክምና ወጪ ሳቢያ ለከፋ የኑሮ ቀውስና ለድህነት እንዳይዳረጉ የሚያስችል መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡
በህክምና ወጪ ለድህነት መዳረግ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአለም አገራት ችግር ነው፡፡ ጥሪታቸውን አሟጠው ለህክምና ወጪ በማዋል ለኑሮ ቀውስና ለከፋ ድህነት የሚዳረጉ የተለያዩ የአለም አገራት ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ በ2012 ብቻ ለራሳቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው ህክምና ከፍተኛ ወጪ በማውጣታቸው ሳቢያ ለከፋ ድህነት የተዳረጉ የተለያዩ አለም አገራት ዜጎች ቁጥር ከ150 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ አገራት ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ሁነኛ መላ ያሉት የጤና መድህን ስርዓት መዘርጋትን ነው፡፡
ማህበራዊ የጤና መድህን ለምን?
ማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት፣ ተጠቃሚው በጤና ተቋማት አገልግሎት በሚሻበት ወቅት አብዛኛውን ከኪስ የሚከፈል ወጪ በመቀነስ ጥራት ያለውና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያገኝ የማድረግ አላማ ያለውና፣ በመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችን የሚያቅፍ ትርፍን መሰረት ያላደረገ የመድህን ስርአት ነው፡፡
የማህበራዊ ጤና መድህን ስርአትን መዘርጋት፣ የአገራትን አጠቃላይ የጤና ዘርፍ ልማት በማፋጠንና የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የስርአቱ ተጠቃሚ የሆኑ አገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡ የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች፣ የጤና አገልግሎት ክፍያ የሚከፍሉት አገልግሎት በሚፈልጉበት ወቅት ሳይሆን ቀደም ብሎ በተተመነ ሂሳብ መሰረት በየጊዜው በመሆኑ የክፍያ ጫና አይኖርባቸውም፡፡ ክፍያው ለህመም ተጋላጭነትን ሳይሆን ገቢን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሀብታሙ ድሃውን፣ ጤነኛው በአንጻራዊ ደረጃ ታማሚውን እንዲደግፈው በማስቻል የጤና ወጪን ጫና በመቀነስ ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ የመክፈል አቅምን መሰረት ሳያደርግ ሁሉም ተጠቃሚ እንደየ ፍላጎቱ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆንም ያስችላል፡፡
መደጋገፍን፣ፍትሃዊነትና አሳታፊነት አመላካች መርሆዎቹ ያደረገው ይህ የጤና መድህን አይነት፣ በአባላት መካከል አንድነትንና መተባበርን በመፍጠር፤ ያለው የሌለውን፣ ጤነኛው ታማሚውን የሚደጉምበትና፤ ሁሉም የመድህን ስርአቱ አባል እንደ ገቢው መጠን ከፍሎ፣ እንደ መዋጮው ሳይሆን እንደ ህመሙ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው፡፡ ግለሰቦች ወይም ቤተሰቦች አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ ወይም ክፍያ አማካይነት የጤና መታወክ በሚድረስባቸው ጊዜ ከሚያጋጥማቸው ያልታሰበ ከፍተኛ የህክምና ወጪ የሚድኑበት ከመሆኑም በላይ፣ አባላት ገንዘባቸውን የሚያዋጡ በመሆናቸው የመድህኑን አሰራር በባለቤትነት እንዲመሩና እንዲከታተሉ ዕድል የሚፈጥር ስልት ነው፡፡
አሰራሩ የጤና አገልግሎት ገዢውንና አገልግሎት ሰጪውን (የጤና ተቋማትን) በመለያየት ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመደራደር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና የተሸለ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማግኘት ያስችላል፣ ተጠያቂነትንም ያጎለብታል፡፡ የማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት ለጤና አገልግሎት የሚውለውን ፋይናንስ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ህብረተሰቡ በታክስ መልክ ከሚጠየቅ ይልቅ በጤና መድህን ስርዓት ለአገልግሎቱ እንዲከፍል መጠየቁ፣ የባለቤትነት መንፈስ በመፍጠር ገንዘቡን ለማዋጣት የበለጠ ፈቃደኛ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አሰራሩ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታክስን የመሰብሰብ ውሱን አቅም ላላቸው አገራት ተመራጭ ነው፡፡
 እኛስ የት ጋ ነን?
በአገሪችን የጤና ዘርፍ ልማትና የጤና አገልግሎት አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑ ይነገራል - የጤና ፋይናንስ ስልት ውስንነት፡፡ በኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር የፖሊሲ፣ ፕላንና ፋይናንስ ጄኔራል ዳይሬክቶሬት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ለአገሪቱ የጤና ዘርፍ የሚያስፈልገው ፋይናንስ ከመንግስት (31 በመቶ)፣ በአገልግሎት ወቅት በቀጥታ ከተጠቃሚዎች ከሚሰበሰብ  ክፍያ (30 በመቶ)፣ ከልማት አጋሮች (37 በመቶ)ና ከመድህንና ከሌሎች የግል ምንጮች (2 በመቶ) የሚሸፈን ነው፡፡
ይህም ለጤናው ዘርፍ የሚውለው ወጪ አነስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ፣  በአገልግሎት ወቅት ከተጠቃሚዎች ከሚገኘው ክፍያ የሚሸፈነው ወጪ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ፣ በተጠቃሚዎች በተለይም በድሆች ላይ የተለየ ጫና ስለሚያሳድር የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ለማዳረስ አስቸጋሪ መሆኑን ያመላክታል፡፡ በጤና ፋይናንስ ላይ በሚታየው ውስንነትና በሌሎች ምክነያቶች በአገሪቱ ያለው የጤና አገልግሎት አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ፣ በህብረተሰቡ የጤንነት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ማድረጉና በአገሪቱ ጤና ነክ የልማት ግቦች አፈጻጸም ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡
ከአገሪቱ ጠቅላላ የጤና ወጪ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ተጠቃሚዎች በአገልግሎት ወቅት በሚከፍሉት ክፍያ የሚሸፈን መሆኑ፣ የአከፋፈል ስርዓቱ ከፍትሃዊነት አንጻር የራሱ የሆነ ችግር ያለበት መሆኑን ያሳያል፡፡ ሃብታሙም ሆነ ድሃው ለጤና የሚከፍሉት ክፍያ የገቢ መጠናቸውን ያገናዘበ ሳይሆን እኩል ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም። ተጠቃሚዎች ለጤና አገልግሎት ክፍያ የሚፈጽሙት አገልግሎቱን በሚያገኙበት ጊዜ መሆኑ፣ በተጠቃሚዎች ላይ ጫና የሚያሳድርና አገልግሎቱን ለማግኘት የሚያዳግት፣ በተለይ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን ደግሞ ገንዘባቸውን በማሟጠጥ ወደ ከፋ ድህነት እንዲገቡ የሚያደርግ ነው። ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችም የየራሳቸው ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡  ለዚህ ነው፣ መንግስት አገሪቱ የጤና ግቦቿን ለማሳካት የጤና ፋይናንስ ስልቷን ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎትን ለመጠቀም በሚገፋፋና በሚያስችል መልኩ መቃኘት እንደሚኖርባት ድምዳሜ ላይ የደረሰው፡፡ የጤና መድህንን እንደ አንድ የፋይናንስ ምንጭ በመጠቀምና በአገሪቱ የጤና ዘርፍ  የሚስተዋለውን የገንዘብ ጉድለት በመሙላት የጤና አገልግሎቱን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግም ትኩረት የሰጠው፡፡
መንግስት በአገሪቱ የጤና መድህንን በመዘርጋትና የጤና ፋይናንስ አከፋፈልን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና መተሳሰብን የሚያጎለብት እንዲሆን፣ የጤና አገልግሎት ሽፋንን እንዲስፋፋና ተጠቃሚነትም እንዲጨምር በማድረግ የአገሪቱን ዜጎች የጤንነት ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አስፈላጊ ህጋዊ ማዕቀፎችንና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ፈጥሯል። የጤና አገልግሎት ሽፋን መስፋፋት ለአገሪቱ የተቀላጠፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ በመንግስትና በተጠቃሚው ህብረተሰብ መካከል ወጪን መጋራት ወሳኝ ሆኖ በመገኘቱ፣የማህበራዊ ጤና መድህን በአባላት መካከል መደጋገፍን በመፍጠር ፍትሃዊና የተሸለ የጤና አገልግሎትን ለማጎልበት የሚረዳ ቀጣይነት ያለው የጤና ፋይናንስ ማሰባሰቢያ ስልት በመሆኑ፣  የማህበራዊ ጤና መድህን በአዋጅ ቁጥር 690/2002 በነሃሴ 2002 በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ ውሏል፡፡
የጤና መድህን ስርዓቱን በአግባቡ የሚያስፈጽም ተቋም መገንባት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 191/2003 ባወጣው የማቋቋሚያ ደንብ  የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲን ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። የጤና መድህን ስርዓቱን የማስፈጸም አላማ ይዞ የተነሳው ኤጀንሲው፣  ተጠሪነቱን ለሚንስትሩ በማድረግ ከተቋቋመ ጀምሮ ባሉትአመታት ተቋማዊ አቅሙን የማደራጀትና ስርአቱን በአግባቡ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኤጀንሲው በአገሪቱ ሊዘረጉ ከታቀዱት የጤና መድህን ስርዓቶች አንዱ የሆነውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በ13 ወረዳዎች የሙከራ ትግበራ አስጀምሯል። ከመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ ውጭ ያሉትንና ቋሚ ገቢ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በቤተሰብ መዋጮና ከክፍያ ነጻ በሆነ አሰራር የጤና መድህን ስርዓቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ መረጃ እንዲኖረውና ጠቀሜታውን በመገንዘብ ለእቅዱ ተፈጻሚነት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት በመስራት ላይ የሚገኘው ኤጀንሲው፣ መገናኛ ብዙሃን ስለ ጤና መድህን ተገቢውን መረጃ ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ማሰራጨት የሚችሉት፣ ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸው ነው በሚል እሳቤም ለጋዜጠኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ኤጀንሲው በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ የማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት አባላት የሚሆኑት፣ 3 ወርና ከዚያ በላይ የአገልግሎት ዘመን ያላቸው ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች፣ 10ና ከዚያ በላይ የሰራተኞች ቁጥር ባላቸው የግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ሁሉም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እና የጡረታ ባለመብቶች ናቸው፡፡
በማህበራዊ የጤና መድህን አዋጅ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ማንኛውም አሰሪ ሰራተኞቹን፣ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ደግሞ ሁሉንም የጡረታ ባለመብቶችን ለማህበራዊ የጤና መድህን በኤጀንሲው ዘንድ ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡ ኤጀንሲው በበኩሉ የአባላትን አመዘጋገብ በተመለከተ በሚያወጣቸው የራሱ መመሪያዎችን ተፈጻሚ ያደርጋል፡፡
ስርአቱ የአባላት መዋጮን፣ የአሰሪዎች መዋጮን፣ ከኢንቨስትመንት የሚገኝ ገቢን እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ምንጮችን የፋይናንስ ምንጩ በማድረግ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ የስርአቱ ተጠቃሚዎች አባላትና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ፣ ይህም ከ18 አመታት በታች የሆኑ ልጆች፣ ቤተሰብ፣ ባል ወይም ሚስትን ያጠቃልላል፡፡
 የማህበራዊ ጤና መድህን አባላት በየወሩ ከሚያገኙት ደመወዝ ወይም የጡረታ አበል በመቶኛ ተሰልቶ የሚከፍሉት መዋጮ  የአረቦን ክፍያ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አሰሪዎችም አባል በሆኑ ሰራተኞቻቸው ስም ከደመወዝ በመቶኛ የሚሰላ ገንዘብ ለመድህኑ ያዋጣሉ፡፡ የመዋጮው መጠን ከአገር አገር የሚለያይ ሲሆን፣ በአገራችንም ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባና ተመጣጣኝ የሆነ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት፣ ሰራተኞች ከደመወዛቸው 3 በመቶ ሲከፍሉ፣ አሰሪዎች ደግሞ ለሰራተኞቻቸው 3 በመቶ ያዋጣሉ። ጡረተኞች በበኩላቸው የጡረታ አበላቸውን 1 በመቶ ሲያዋጡ፣ መንግስትም ለጡረተኞች 1 በመቶ የሚከፍል ይሆናል፡፡
በአገሪቱ የማህበራዊ የጤና መድህን የሚሸፈኑ አገልግሎቶች ዋነኛ በሚባሉ የህብረተሰቡ የጤና ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉና አባላቱ የሚፈልጓቸው እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በየደረጃው ከሚገኙት የጤና ተቋማት ጋር በተጣጣመ መንገድ በጤና መድህኑ ሊሸፈኑ የሚገባቸው አገልግሎቶች የጥቅም ፓኬጅ በጥናት ላይ ተመስርቶ ተዘጋጅቷል፡፡ የጥቅም ማዕቀፉ በመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ማዕቀፍ (basic health service package) የተካተቱትን የፈውስ ህክምናዎችና ለህይወት አስጊ የሆኑ ህመሞችንና ጉዳቶችን ለማከም በየደረጃው ባሉ የጤና ተቋማት የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን ያካትታል።  
ማንኛውም የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት ተጠቃሚ የተመላላሽ ህክምና፣ የተኝቶ ህክምና፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ህክምናና በህክምና ባለሙያዎች የታዘዙ የምርመራ አገልግሎቶችና በኤጀንሲው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱትን መድሃኒቶች ማግኘት ይችላል። በማዕቀፉ ውስጥ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ተብለው የተካተቱት የጤና ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም ተላላፊና ተላላፊ በሽታዎች፣ የደም ግፊት፣ የልብ ችግር፣ የስኳር በሽታ፣ የካንሰር፣ የአእምሮ በሽታና የድንገተኛ በሽታ ህክምናዎች ናቸው፡፡
የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት ማስፈጸሚያ ደንብ፣ በማዕቀፉ የማይካተቱ ብሎ ካስቀመጣቸው አገልግሎቶች መካከል፣ ከአገር ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ህክምና፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በማህበራዊ ብጥብጥ፣ በወረርሽኝና ከፍተኛ አደጋ ባላቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ለሚደርሱ አደጋዎች የሚደረጉ ህክምናዎችና አደገኛ እጾችን በመውሰድ ለተከሰተ ጉዳት ወይም ለሱስ ተገዢነት የሚደረግ ህክምና ይጠቀሳሉ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፣ በየጊዜው የሚደረጉ ከህመም ጋር ያልተያያዙ የጤንነት ሁኔታ ምርመራዎች፣ የስራ ላይ ጉዳቶች፣ የትራፊክ አደጋዎችና በሌላ የህግ ሽፋን የተሰጣቸው ሌሎች አደጋዎች፣ ለውበት ሲባል የሚደረጉ ቀዶ ጥገናዎች፣ የአካል ቀዶ ማዛወር፣ ድንገተኛ የኩላሊት ስራ ማቆምን ለመታደግ ከሚሰጥ ህክምና ውጭ የሚደረግ የዲያሊሲስ ህክምናዎችም በአገልግሎቱ አይካተቱም፡፡
የአይን መነጽርና ኮንታክት ሌንስ፣ በሰው ሰራሽ ዘዴ ከአካል ውጭ ለማስጸነስ የሚደረግ ህክምና፣ ሰውሰራሽ አካል መተካት፣ ሰውሰራሽ ጥርስ ማስተካከልና በኢንፌክሽን ምክነያት የሚደረግ የሩት ካናል ህክምናን ሳይጨምር ሌላ ማናቸውም የሩት ካናል ህክምና፣ የመስማት ሃይልን የሚያግዙ መሳሪያዎች ወዘተ… የመድህን አባሉ የማያገኛቸው አገልግሎቶች ናቸው። በሌሎች ህጎች የተሸፈኑ እንዲሁም ያለክፍያ ለሁሉም ዜጎች እኩል የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችም በማዕቀፉ አይካተቱም፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ በመጪው ጥር ወር የማህበራዊ ጤና መድህንና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግና፣ አባላቱ በመላ በአገሪቱ በሚገኙ 123 የመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ዕቅድ ይዞ ሲሰራ ቢቆይም፣ ሁሉም ክልሎች እኩል ወደስራ መግባት ባለመቻላቸው፣  ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል፡፡  
እርግጥም ይሄን አገራዊ ተልዕኮ ማስጀመር ቅንጅትን የሚሻ ትልቅ የቤትስራ ነውና፣ ተጨማሪ ጊዜ ወስዶ በወጉ ለመዘጋጀትና ወደ ስራ ለመግባት ትኩረት መሰጠቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

Published in ዋናው ጤና
Page 12 of 14