Saturday, 24 January 2015 12:46

የጉዞ ማስታወሻዬ

ከውሃ ወደ ውሃ - ከአሶሳ ወደ ካይሮ

         (ካለፈው የቀጠለ)
አሶሳ ስንደርስ እንዲህ ሆነላችሁ፡፡
አንድ ሆቴል ሄድን፡፡ ማረፊያችሁ እዚህ አደለም ተባለ፡፡ እርስ በርስ፤ የራስ ግምትም ተጨምሮበት፣ ስም ሊስት የያዙ ሁለት ሶስት ሰዎች ይታያሉ፤ እነሱን እየተከተሉ “ስሜ አለ ወይ?” እያሉ መጠየቅ ግድ ሆነ፡፡ ሁሉም የሚያውቀውንና አስተባባሪ ሊሆን ይችላል የሚለውን ሰው ይጠይቃል፡፡ ግራ ይገባል፡፡
ብቻ በመጨረሻ “ባምቡ ሆቴል ኑ ተብላችኋል” የሚለው ድምፅ በረከተና ወደ ባምቡ ሄድን፡፡ ደግነቱ አሶሳ ዐርበ - ጠባብ ናትና ከዚያች እዚያች እንደ መራመድ ነው ከሆቴል ሆቴል መሄድ፡፡ ባምቡ ሆቴል ደረስን፡፡ አስተባባሪው ልጅ ያውቀኛል፡፡ ከእኔ ጋር ያሉት እሱን ያውቁታል፡፡ “ሻንጣችሁን ሪሴፕሺን አስቀምጡና ምሳ ትበላላችሁ! ምሳው ላይ ስለመኝታችሁ እንነጋገራለን!” አለን፡፡ ቢያንስ መመሪያ ብጤ አግኝተናል አሁን፡፡ አበሻ ትንሽ እፎይ ሲል ብሶቱንም፣ ጨዋታውንም፣ ጉርምርምታውንም አንዴ ጠረጴዛው ላይ መዘርገፍ ይወዳል፡፡ ከምግቡ ጋር ነገር ማላመጥ ይቀናዋል፡፡  
“ይሄን ሁሉ ሰው ጠርተው ፕሮግራሙን ማሳወቅ እንኳ እንዴት ያቅታቸዋል?” አለ አንዱ፡፡ “ይሄ ሰው መናቅ ነው - የሰው ዋጋ አለማወቅ! ብቻ የጋበዘኝን ሰው ላግኘው!” አለ ሌላው፡፡ ብሶት ወዲያው ተቀጣጠለ፡፡
ቀጥሎ ያበሻ First Aid (የመጀመሪያ እርዳታ) ከንፈር እየመጠጡ “እምጥ… እምጥ” ማለት ነው፡፡ ትንሽ ሲሻሻል አስተያየት፣ አንዳንዴም ፍልስፍና ብጤ ይጨመርበታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሶስት ፈርጅ ያለው ነው ያበሻ አስተያየት፡-
“ዎ መንግስት ቤትኮ ይሄው ነው፡፡ ባለፈውም እንደዚሁ ተጫውተውብናል” አለ አንደኛው፡፡ ይሄንን “የትላንት ምሬት” በሉት፡፡ ቀጠለ ሌላኛው፡፡ “አሁንም‘ኮ ምንም ያሉን ነገር የለም፡፡ ብሉና እንወያያለን ነው የተባልነው!” አለ፡፡ የዛሬ ምሬት በሉት ይሄንን፡፡
ሦስተኛው ሰው፡- “ገና ምን አይታችሁ - ምስቅልቅላችንን ነው የሚያወጡት!” ይላል፡፡
ይሄ እንግዲህ የነገ ጉዳይ ነው፡፡ ትላንተኛነት…ዛሬኝነት…ነገኛነት! ትላንት፣ ዛሬና ነገን ምሬትና ብሶት ካፈሰሱባቸው በኋላ አንዱ ማስታመሚያ ሀሳብ ያቀርባል፡-
“ግን‘ኮ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ገና አዳጊ ክልል ነው - አትፈረዱበት”
ከአዲሳባው ዝግጅት ኮሚቴ ወደ ክልሉ መጣ ማለት ነው የቅንብር ችግሩ!
የጉዞ አስተባባሪው መጥቶ “እስቲ ትንሽ ቆዩ የናንተ አፍሪካ ሆቴል ሳይሆን አይቀርም” አለን፡፡ እንግዲህ ከቆየን ማወራረጃ ቢራ እንዘዝ ተባባልን፡፡ ከዩኒቨርሲቲው መምህር ወዳጄ ጋር ቢራ ልናዝ ተስማማን፡፡ አሁን እንግዲህ ወደ 10 ሰዓት ሆኗል - ከሰዓት፡፡ አስተናጋጇን “ቢራ እባክሽ” አልኳት
አስተናጋጇም “ቢራ በጀታችሁ ውስጥ አልተያዘም፡፡ ለስላሳና አምቦሃ ነው የሚቻለው” አለችን፡፡
“ይሁን እንከፍላለን - ብቻ ቶሎ አምጪው” አልናት፡፡
በዚህ ማህል ከእኛው ጋር ከመጡት ውስጥ አንዷ ታዋቂ ሴት መጣችና
“ነቢይ፤ የት ያዛችሁ አልጋ?” አለችን፡፡
“የትም” አልኳት፡፡
“እኔ እደዚህ ያለው የመንግስት ጉዞ ላይ እናቴ፣ ፊት የመቀመጫዬን ብዬ፤ ክፍሌን ይዤ መጣሁ” አለች፡፡
እኔ በሆዴ ትንሽ አማኋት፡-
“ይቺ ልዩ አስተያየት የሚደረግላት፣ ከመንግሥት ጉዞ ሁሌ አይቀሬ ከሚባሉት ተጓዦች ውስጥ ሳትሆን አትቀርም፡፡ እንጂ ከአገር ሰው ማህል ብቻዋን እንዴት አልጋ ይሰጣታል?” አልኩ፡፡
በመጨረሻ ከየት እንደተሰማ ባላውቅም አንድ መልዕክት በተደጋጋሚ ተነገረ፡-
“አርቲስቶች በሙሉ ሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ነው የምታርፉት”
“ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ደሞ የት ነው?” አልን፡፡
“ከዚህ አንድ 10ኪ.ሜ ገደማ ነው!”
“ገጠር ሊወስዱን ነዋ! ገና ምን አይታችሁ እነዚህ ሰዎች …” አለ ሌላው የነገ ስጋት ያለው አርቲስት፡፡
ሁሌም የሚገርመኝ ክፉም ደግም ጎን ያለው አንድ ነገር፤ ይሄ ተጓዦችን ከከተማ ወጣ አድርጎ የማሸግ የአፍሪካ ፈሊጥ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ አጋጥሞኛል፡፡ ዛምቢያ አጋጥሞኛል፡፡ ኬንያ አጋጥሞኛል .. ይገርመኛል! ፈረንጆች “a letter in a mail - box” የሚሉት አገላለፅ አላቸው፡፡ ከአንድ የፖስታ ሳጥን ወደ ባለቤቱ አንደሚወሰድ ደብዳቤ መሆን፤ ማለታቸው ነው፡፡ ፖስታው በገዛ ፈቃዱ ከሳጥኑ መውጣት እንደማይችል ሁሉ እኛም ያለፈቃዳችን ከከተማው ርቀን ልናድር ነው፡፡ ለጥናትና ምርምር አሊያም ለወርክሾፕ መጥተን ቢሆን እንኳ ጥናቱን ወይ ወርክሾፑን ስንወያይ ይመሻልና የበለጠ በትናንሽ ቡድን እናበስለዋለን - ይህ በጎ ጎኑ ነው፡፡
ለማንኛውም ወደ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ግቢ ገባን፡፡ ቡናና ፈንዲሻ የገቢ ተባልን፡፡ ቦታ ተደለደልን፡፡ እኔ መጀመሪያ የተመደብኩት 10 ሰው የሚይዝ ባለሁለት ድርብ አልጋ ያለው ክፍል ነበር፡፡ በኋላ ግን ዘነበ ኦላን አገኘሁትና “የእኛ ክፍል 4 ሰው የሚይዝ ቀለል ያለ ክፍል ነው፤ ለምን አትመጣም?” አለኝ፡፡ ሄጄ አየሁት፡፡ ዕውነትም ከባለ አስሩ ይሻለኛል፡፡ ክፍል ለወጥኩ፡፡ ተጣጠብንና ንፋስ ለመቀበል ስንወጣ፤ ዘነበ እዚህ አገር ወዳጆች አሉኝ - እነሱጋ ነገ መሄድ እንችላለን” አለኝ፡፡ “የአሶሳን ህይወት አጣጥሞ ለማወቅ ወደ  አገሬው ብቅ ማለትና ቤተሰብ ማየት ጥሩ ነው” አልኩኝ፡፡ ቀጥሎም “እዚህ አገር፤ ብርሃነ መስቀል ረዳ ያቋቋመው ላይብረሪ (መጽሐፍት ቤት) እንዳለ ታውቃለህ?” አለኝ፡፡ (ብርሃነ መስቀል እንግዲህ ኢህአፓን ከመሠረቱት ሰዎች አንዱ ነው፡፡)
“ኧረ ባክህ?”
“አዎ ሥዩም ወልዴ “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” ብሎ በፃፈው መጽሐፉ ላይ የጠቀሰው‘ኮ ነው?” አለኝ አጠናክሮ፡፡ የሥዩምን መጽሐፍ በቅርብ ነው ያነበብኩት፡፡ ይሄን ጉዳይ በትናንሽ ቡድን ሌላ ጊዜ እናየዋለን፡፡
ከዘነበ ዎላ ጋር መጽሐፍት ቤቱን ሄደን ልንጐበኘው ዕቅድ አወጣን፡፡ ብርሃነ መስቀልን ደርግ ጽ/ቤት እሥር ቤት ውስጥ አግኝቼው ስለነበር የጓደኛዬን መጽሐፍት ቤት እንደማይ ሁሉ ህዋሴን ነዘረኝ፡፡ አንድም የዚያን ትውልድ ጥንካሬና ለአገር አሳቢነት ያሳያል የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ሊሆን ይችላል - ለራስ ሲቆርሱ አያሣንሱ አደለ፡፡
በሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ግቢ እኛ የተመደብንበት ንፍቀ - ክበብ ዙሪያ ነው፡፡ ዙሪያውን ክፍሎች አሉ፡፡ መካከል ላይ ቅርንጫፉ የተንዘረፈፈ ዛፍ አለ፡፡ የዛፉ ጥላ አንዳች ቀዝቃዛ ድባብ ፈጥሯል፡፡ ጥላው ላይ ዙሪያውን ፍራሽ ተነጥፏል፡፡ ዋና ዋና ሰዎች ተቀምጠዋል:- ንዋይ ደበበ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኪሮስ ሃ/ሥላሴ፣ ቢንያም ሃ/ሥላሴ፣ ኩራባቸው ደነቀ፣ ኃይሉ ፀጋዬ፣ እመቤት ወ/ገብርኤል፣ ቶማስ ቶራ፣ አስቴር ከበደ፣ ስማቸውን የማላስታውሳቸው ሁለት ሶማሌዎች አሉ፡፡ ጨዋታው ደርቷል…አርዕስት ይነሳል አርዕስት ይጣላል… ውይይቱ ሞቋል፡፡ ንዋይ በሰፊው ይጫወታል፡፡ በተለይ አንዱ አባል “ንዋይ አየር ወለድ ነበርክ የሚባለው ዕውነት ነወይ?” ሲል በድንገት ጠየቀው፡፡ ንዋይ ታሪኩን አስረዳን፡፡ ማብራራቱን የወደደው ይመስላል፡፡ አምስት ሆነው ከቀይ ሽብር ሽሽት ከሻሸመኔ መጥተው ደብረዘይት አየር ወለድ እንዴት እንደገቡ፣ በኋላ ግን እዚያም አሳሳቢ ሁኔታ በመፈጠሩ እንደገና መውጣታቸውንና ንዋይና አንዱ ጓደኛው ወደ አዋሳ እንደሄዱ፤ ሌሎቹ ሦስቱ ግን አዋሳ አንመለስም ብለው ወደ ናዝሬት/አዳማ እንደሄዱና እዚያው እንደሞቱ በሚያስደንቅ ስሜታዊነት ገለፀልን፡፡ ውይይቱ እንዳማረበት መሸ፡፡
አመሻሽ ላይ የተወሰንን ሰዎች አዋሳን በምሽት እንያት ብለን ከባኮው ወጥተን ወደ ከተማ ሄድን፡፡
በመጀመሪያ ባምቡ ሄድን፡፡ አዋሳ የቀርክሃ አገር ናት፡፡ ቀርክሃ ሆቴል እንዳይሉት ምን እንዳገዳቸው እንጃ፡፡ ቅንጭብ፣ ቃጫ፣ ቁርቁራ፣ ቆንጥር፣ ምናምን ሆቴል፤ አይበሉት እንጂ ቀርክሃ እኮ ቆንጆ ስም ነበረ አልኩኝ በሆዴ፡፡
ባምቡ ሆቴል ግቢ ዛፉ ስር አያሌ ሰው ታድሟል፡፡ አብዛኛው ባለሥልጣን እዚያው እንደሚያርፍም ጠርጥሬያለሁ፡፡ እኛ “ሥራ አመራር” ራት ቢኖረንም እዚህ ብንበላስ ብለን እንደዘበት ብንጠይቅ፤ ከቢፌው ምግብ አመጡልንና በላን፡፡ ከዚያ በየቡና ቤቶቹ ዘወር ዘወር አልን፡፡
ያየነው ቡና ቤት ሁሉ፤ እንደአብዛኛው የደቡብ ቡና ቤት ሁሉ፤ ከፊት ለፊት ዛፍ የከበበው፣ በረንዳውም ሆነ ግቢው ጨለምለም ያለ፣ ብዙ ሰው እጭለማው ጋ የሚስተናገድበት፣ ዋናው ውስጠኛው ቡና ቤት ግን ሰፊና ፏ ያለ መብራት ያለው ነው፡፡ በሁለት ሦስት ቀናት የበለጠ እናየዋለን ተባብለን ቢራ ቀማምሰን ወደማደሪያችን ሄድን፡፡
ነገ ወደግድቡ ጉዞ ነው፡፡ ፊታችንን ወደ ነገ አዙረን ተኛን!
መቼም መፃፍ ለምንጽፈው ነገር ፍቅርን መግለፅ ነው፡፡ ነጋና ከጠዋቱ 11፡30 ወደ ግድቡ ለመሄድ ተነሳን፡፡ ይመጣል የተባለው አውቶቡስ አልመጣም፡፡ አንድ ሌላ አውቶብስ ግን ግቢ ገብቷል፡፡ ስንጠይቅ “ይሄ የአርቲስቶች አይደለም የሥራ አመራሮች ነው” አለን ሹፌሩ፡፡ አልገባኝም፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነ ኃላፊ ስለሌለ ማንንም መጠየቅ ስለማልችል መጠርጠር ነው፡፡ “የአርቲስቶች ባስ” ባይገባኝም ተቀበልኩት፡፡
“ምናልባት እስክስታ እየወረደ የሚወስደን ይሆናል” ብዬ ጐኔ ላለ አንድ ሰው ነገርኩትና ተሳስቀን ጥበቃችንን ቀጠልን፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የዚያው አውቶብስ ተሳፊሪዎች “ባዶውን ከሚሄድ ለምን ከኛ ጋር አትሄዱም” አሉን፡፡ ሳስበው ካውቶብስ አውቶብስ የምናማርጥበት አይደለም - በተገኘው መሄድ ይሻላል አልኩኝ፡፡ ቅርቤ ያለውን ኃይሉ ፀጋዬን ጠራሁት፡፡ ኃይሉ ያገሬ የናዝሬት ልጅ ነው - አዲሳባም አትገናኙ ቢለን ነው እንጂ እንቀራረባለን፡፡
ፀሐፌ - ተውኔት መንግሥቱ ለማ እንዲህ ይሉናል “ባለ ካባ እና ባለደባ” ላይ፡፡
(በቴያትሩ ላይ ተዋናይ ስለነበርኩኝ አስታውሰዋለሁ)
አንዱ ገፀ - ባህሪ ሌላውን፤
“የት ነህ ያለኸው?” ይለዋል፡፡
“እዚሁ - አዲሳባ!” ይላል ያኛው፡፡
“ታዲያ እንዴት አንገናኝም?” ይለዋል፡፡
“አዲሳባ በመስፋፋቷ ሳይሆን ይቀራል? እኩሬ ውስጥ ያሉ አሣዎች በየጊዜው ስለሚተላለፉ ይተያያሉ፤ ይገናኛሉ፡፡ እባህር ውስጥ ሲገቡ ግን ያ ሁሉ ይቀራል” የእኔና የኃይሉም ነገር እንደዚያ ነው፡፡ ለማንኛውም ዛሬ ተገናኝተናል፡፡ አብረንም ተቀምጠናል፡፡
እንግዲህ ወደ ግድቡ አመራን፡፡ ትንሽ ትንሽ ሐሜታ አልጠፋንም፡፡ “አርቲስቱ አንድ ላይ ለመሆን ለምን ይፈልጋል? ሁሌም በየሥራ መስኩ ይገናኛል፡፡ ዛሬ እንኳ ነጠልጠል ቢል ምናለበት፡፡ ሌላ አመለካከት፣ ከሌላ ህይወት ጋር ቢቀላቀልኮ ቢያንስ ለውጥ ይሆንለት ነበር፡፡ Landscape ይፈጠርለታል - የተለየ አስተሳሰብ፣ የተለየ ንፍቀ - ክበብ! ሁሌ የሚገርመኝ የአበሻም የቤት ጣጣ ነው! አገር ውስጥም ሆነ ውጪ አገር ሰብሰብ የማለት ሁኔታ ሲገኝ እንደገና እኛው የምንተዋወቀው ሰዎች ተገናኝተን ጥግ መያዝ ነው ሥራችን! (ማሽሟቀቅ” ይለዋል ባሴ ሀብቴ ነብሱን ይማረውና!)
ወደ ግድቡ ስናመራ ከንጋቱ 11፡30 ግድም አንድ አስገራሚ ነገር አየን! ከእኛ በስተግራ ባለው የሰማይ አድማስ ጨረቃ የብርቱካን አሎሎ መስላ ቁልቁል ወደተራራዎቹ ትወርዳለች፡፡ በስተቀኝ ባለው የሰማይ አድማስ ደግሞ ሌላ ዱባ - አከል ፖም መስላ ፀሐይ ሽቅብ ወደ ላይ ትመጣለች፡፡ አንዷ ከኛ ዐይን ሽሽት ከተራራው ጀርባ በመሽቆልቆል ላይ ያለች፣ አንዷ ደሞ  ወደ እኛ ዐይን ለመግባት መሰላል እየወጣች ያለች ትመስላለች! እኔና ኃይሉ ዐይናችንን ማመን አቅቶናል፡፡ እኔ፤ አንድም በገጣሚ ዐይን፣ አንድም በሰዓሊ ዐይን አንድም እንዲያው በአዘቦት ዐይን ሳይ፤ እንዲህ ያለ ጨረቃና ፀሐይ ሲተያዩ ማየት አጋጥሞኝ አያውቅምና ነብሴን ሰርቆታል!
ወዴት ትወጫለሽ አለቻት ጨረቃ
እኔ ሰው አይቼ ታዝቤ ሳበቃ
ፀሐይም መለሰች፤ ትላንት ያየሽውስ  መቼ አለና ዛሬ
ኑሮ ተለዋዋጭ፤ ቶሎ እማይጨበጥ፤ ዛሬ ሰው ነገ አውሬ!
ያሰኘኝ ነው!!
ነብሳችን በተፈጥሮ እንደተሸነፈች ከወዲሁ ገብቶናል፡፡
ሰማይ ላይ አውሮፕላን ውስጥ ሆነን እኔና ኃይሉ ዐባይን ስናይ ያን የተልባ እባብ የመሰለ ጉዞውን አይተን ስለነበር እጅግ አድርገን አድንቀናል፡፡ አሁን በዐይናችን ልናየው በእጃችን ልንዳስሰው ነው፡፡ ዳቡስ የተባለው ወንዝ ዋናው የዐባይ መጋቢ ነው፡፡
ስለሌሎቹም ወንዞች አውቶብሱ ውስጥ የነበሩ ጐበዝ ጐበዝ የውሃ ሙያ ሰዎች ገለፃ ካረጉልን በኋላ የዐባይ ግጥሜን እንዳጠነክረው ሀሳብ ፈነጠቀብኝ:-
“…ዳቡስ የመጋቢ ንጉሥ
በጐርፍ እንዳትሌት ሲፈስስ
ላንተው ውሃ ዳስ ሲቀይስ፡፡
ግልገል ጐጆህን ሲቀልስ
ዴዴሣ ዳልጋው ሲያገሳ
ዲንደር ጅረቱን ሲያስነሳ
ባሮ - ውሃ አነባበሮ
መንፈሱን ላንተው ገብሮ
ፊንጫና የማዶ ጉደር
ኦሮሚያ ቤኒሻንጉል፣ ድግስ ጭነው ውሃ ግብር
ተስማምተው ላንተ ለማደር
ሸለቆ ግልገል ኮርማ ኃይል
አንድም ድፍርስ አንድም ጠለል
እንደ አገር ህብር የህዝብ ወኪል
እንደራሴ ሆነው በእኩል
አቢይ ዐባይ ነብሰ ጡር ማይ
የጥንተ - ታሪክ ውል አዋይ!
ተትረፍረፍ ፍሰስ እንደልብ፣ እንካ ኮርቻ ግድብ!
ሰው የሚያለማ እጅ ጥበብ
ዐባይ ዐቢይ ፍኖተ ማይ
ዛሬስ ፍሰስ እትብትህ ላይ!
በተርባይን ተርብ ጥንስስ
አገርክን ሻማ ሸማ አልብስ!!”
የትልቁ ዐባይ ግጥሜ አንድ አንጓ ነው፡፡
ግድቡ ግድም የደረስነው በርሃብ ተከበን ነው ለማለት ይቻላል፡፡
ግቢው ስንደርስ ማንም የመንገድ መሪ የለንም፡፡ ወዴት እንደምንሄድ የነገረን የለም፡፡
ቀጥሎ ምን እንደሚደረግ አናውቅም Disorganization ቅጥ የለሽ አመራር ዓይነት ነው የሚል ስሜት ሁላችንም ላይ ሰፍሯል፡፡ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እህል ባልቀመሰ አንጀት ላይ ወዴት እንደምንሄድ አለማወቅ መራር ነው፡፡ አንድ አውቶብሱ ውስጥ ያለ ሰው፤
“ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄድ የብሔር ብሔረሰብ በዓል የተሻለ አመራር እንዴት አይኖረውም?” አለ፡፡
አንድ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኢትዮጵያ ውስጥ ፒኤችዲውን ሊሠራ ከእንግሊዝ የመጣ “በእኛ ትምህርት አንድ ፖሊሲ አለ” አለና ጀመረ፡፡   
በግል እንተዋወቃለን!
“አንድ ተማሪ አንዴ ስህተት ሠርቶ 12 ከ20 ሊያገኝ ይችላል፡፡ ወይም ከ10 በታች አግኝቶ ይወድቃል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ያነሰ ነው መውደቅ ያለበት 16 ከ20፤ 17 ከ20 እያለ ማሻሻል ይጠበቅበታል!”
ግድቡን አየነው!
ሰማይን ሊውጥ አፉን የከፈተ፣ ከፈፋ ፈፋ እያዛጋ የሚመስል ግዙፍ ጉድጓድ ነው፡፡ በቴሌቪዥን እንደምናየው ትንሽ አይደለም፡፡ ትልቅነቱና በውስጡ ያሉት ተርባይኖች (16) ጥርስና ላንቃው ይመስላሉ! ረሀባችንን ገዛው መሰለኝ - ለጥቂት ጊዜ ግድቡን ብቻ እንድናስብ ሆንን!
ዞሮ ዞሮ ወደምሣ መሄድ ነበረብን - ደክሞናል - ፀሐዩ በርትቷል!!
(ይቀጥላል)


Published in ባህል
Saturday, 24 January 2015 12:44

የአዘቦት ቀን ጀግኖች

የ14 ዓመቱ ኮሊን ስሚዝ በደረሰበት የመኪና አደጋ መላ ሰውነቱ በድን (ፓላራይዝድ) ከሆነ በኋላ ሃኪሞች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የማጠናቀቅ ዕድሉ 20 በመቶ እንደሆነ አርድተውት ነበር፡፡ ኮሌጅ ገብቶ መማርማ እርሳው ነበር ያሉት፡፡ ሆኖም ከ8 ዓመት በኋላ ቢኤ ድግሪውን በኮሙኒኬሽን ከሃይ ፖይንት ዩኒቨርስቲ ለማግኘት ቻለ፡፡ ኮሊን ፈጽሞ የማይታሰበውን ማሳካት የቻለው በዕድሜ 50 ዓመት በሚበልጡትና ጨርሶ በማያቃቸው ደግ አዛውንት እርዳታ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም እንዳጋጣሚ ሆኖ ጡረተኛው ኧርነስት ግሪኒና ባለቤታቸው ካትሪን፣ ኮሊንስና ወላጆቹ በሚያመልኩበት በኖርዝ ካሮሊና በሚገኘው የአሼቦሮ ባፕቲስት ቤ/ክርስቲያን ያመልኩ ነበር፡፡ በእርግጥ እኒህ ቤተሰቦች ትውውቅ አልነበራቸውም፡፡ ምክንያቱም የግሪን ቤተሰብ ወደ አካባቢው ከመጣ ዘጠኝ ወር ያህል ቢሆነው ነው፡፡ ሆኖም ኧርነስት በወሬ ወሬ ኮሊን ስለደረሰበት አደጋና ወላጆቹ የሙሉ ጊዜ እንክብካቤ ሊያደርጉለት አለመቻላቸውን ሰሙ፡፡ ይሄ ለእሳቸው የተላከ ጥሪ መስሎ ታያቸው፡፡
“ፈጣሪ እንድረዳው መራኝ” ይላሉ - ኧርነስት ግሪኒ፡፡ እናም በነበራቸው ትርፍ ጊዜ ኮሊንስን ሊረዱት ቆርጠው ተነሱ፡፡
መጀመሪያ የኮሊንን ቤተሰብ በመቅረብ፣ እነሱ ወደ ሥራ በሚሄዱ ወቅት ልጃቸውን ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ የኮሊን ወላጆች አላቅማሙም፡፡ እርዳታውን በደስታ ተቀበሉ፡፡ አሁን 23ኛ ዓመት እድሜው ላይ የሚገኘው ኮሊን፤ እንዴት ጨርሶ የማላውቀው ሰው እኔን ለመርዳት መላ ህይወቱን እርግፍ አድርጐ እንደተወ ልረዳ አልቻልኩም ነበር ብሏል፡፡
አዛውንቱ ኧርነስት በቀጥታ ወደ እርዳታ አልገቡም፡፡ መጀመሪያ ለኮሊን እንዴት እርዳታ ማድረግ እንደሚችሉ መጠነኛ ስልጠና ወሰዱ፡፡ ከዚያም ወላጆቹ የሥራ ቀናቸውን በሚጀምሩበት አንድ ሰኞ ማለዳ ላይ እነኮሊን ቤት ከተፍ አሉ፡፡ ኮሊንን ከአልጋ ሲነሳ፣ ሲለባብስና ሲተጣጠብ ያግዙትም ጀመር፡፡ ቁርሱንም ሲመገብ እንዲሁ ይረዱታል፡፡ ከዚህም በላይ በራሳቸው መኪና ት/ቤት ያደርሱታል፡፡ በየቀኑ 9 ሰዓት ላይ ደግሞ ወደ ቤት ይመልሱታል፡፡ ወላጆቹ ከስራ እስኪመለሱም ወይ እሳቸው አሊያም ባለቤታቸው እያጫወቱ ይጠብቁታል፡፡
በዚያ ሰዓት ውስጥ ከኮሊን ጋር ብዙ ያወጉ እንደነበር ኧርነስት ያስታውሳሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ በመሃላቸው የነበረው የዕድሜ ልዩነት ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ በሁለት ትውልዶች መካከል የሚከሰት ልዩነት ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዳቸው ራፕ ሲወዱ ሌላኛቸው ምርጫቸው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ተቻችሎ መኖርን ተማሩ፡፡
“አዛውንቶች ዕድሜያቸው የገፋ እኛ ማለት ናቸው” የሚለው ኮሊን፤ “ድንቅ ታሪክ ያላቸው የእኛው ዓይነት ሰዎች” ሲል ይገልፃቸዋል፡፡
አንዳንድ ቀናት ከሌሎቹ የተሻሉ ነበሩ፡፡ “ምንም ነገር ራሱን ችሎ ማከናወን ስለማይችል ብዙ ሊያደክም ይችላል” ይላሉ ኧርነስት፡፡ ነገር ግን ፈታኝ ጊዜያትን ለማለፍ ያስቻለው የራሱ የኮሊን ጠንካራ ቁርጠኝነት መሆኑን ኧርነስት ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ኮሊን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከቀሩት የክፍል ጓደኞቹ ጋር በአጥጋቢ ውጤት አጠናቆ በአቅራቢያቸው በሚገኘው ሃይ ፓይንት ዩኒቨርስቲ ለመግባት ቻለ፡፡ በእያንዳንዱ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ኧርነስት ከአጠገቡ አይለዩም ነበር፡፡ “የመጀመሪያው ዓመት አስደሳች ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ - ኧርነስት፡፡ “ኮሊን ከሌላው ጐልቶ መታየት አይፈልግም ነበር” ግን ደግሞ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ ይጠቀም ነበር - አስተማሪ ሲያስተምር ማስታወሻ ይይዛል፤ ብዙ ጊዜም ክፍል ውስጥ አስተያየት ይሰጥ ነበር፡፡
በምረቃ ቀን ታዲያ ኮሊን ብቻ አልነበረም ዲግሪውን የተቀበለው፡፡ አዛውንቱ ኧርነስትም ላከናወኑት ሰብዓዊ ተግባር ዩኒቨርሲቲው የክብር ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡ ያልጠበቁት ስለነበር ትንግርት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ኮሊን ግን ጨርሶ አልተገረመም፡፡ “ኧርነስት ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት መለኮታዊ ምሳሌ የሚሆኑ ሰው ናቸው - ዝምተኛና ትሁት” በማለት ይገልፃቸዋል፡፡
ኮሊን ዛሬ በዚያው ሃይ ፖይንት ዩኒቨርሲቲ፣ የቅርጫት ኳስ ረዳት አሰልጣኝ ሲሆን ዕውቅና በተሰጠው ልዩ የእንክብካቤ ባለሙያ በየቀኑ ድጋፍ ያገኛል፡፡ አዛውንቱ ኧርነስትም አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከቤተሰባቸው ጋር ያሳልፋሉ፡፡
አሁን ሁለቱ የተለያየ ትውልድ ጓደኛሞች እምብዛም አይገናኙም፡፡ “ነገር ግን ኮሊንና እኔ ሁልጊዜም ግንኙነታችን ይቀጥላል” ይላሉ - ኧርነስት፡፡ ኮሊንም በዚህ ይስማማል፡፡ “በቀን ከ14-16 ሰዓታት አንድ ላይ ነበር የምናሳልፈው” ሲል ያስታውሳል፡፡ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን አስቸጋሪ ፈተናን በጋራ ተወጥተዋል፡፡ ለዚያም ነው የአዘቦት ቀን ጀግኖች የሚባሉት፡፡
(ሪደር ዳይጀስት - የፌብሯሪ 2015 እትም)

Published in ህብረተሰብ

“መልካ ኢትዮጵያ” ሥራ ከጀመረ ወደ 10 ዓመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ በአካባቢ ተቆርቋሪዎች፣ በህግ ባለሙያዎችና ሌሎች  የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በብዝሃ ህይወት ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዝሃ ህይወት የተጋረጠበትን የመመናመን አደጋ ለአዲሱ ትውልድ ለማስገንዘብ በትጋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም የድርጅቱ መስራች፣ አባልና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚሊዮን በላይ ይናገራሉ፡፡ ብዝሃ ህይወትና ባህል ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ለአርሶ አደሮችና ተማሪዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወንን ነው ይላሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በ “መልካ ኢትዮጵያ” አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ዓላማና ስኬቶች ዙሪያ ከዶ/ር ሚሊዮን በላይ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

“መልካ ኢትዮጵያ” ዋና ትኩረቱ አድርጎ የሚሰራው ምንድን ነው?
“መልካ ኢትዮጵያ” በዋናነት በሶስት ጉዳዮች ላይ ይንቀሳቀሳል፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ባህላችን እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ አዲሱ ትውልድ መቶ በመቶ ባህሉን አያውቅም ባይባልም የቀድሞውን ትውልድ ያህል ግንዛቤ አለው ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ ደግሞ ለአገሪቱ አደጋ ነው፡፡
ብዝሃ ህይወትና ባህል ምንድነው የሚያገናኛቸው?
ቀላል ምሳሌ ልስጥሽ፡፡ ወደ ጉራጌ አካባቢዎች ብትሄጂ፣ ከመቶ በላይ የኮባ ዝርያዎች ታገኛለሽ፡፡ ወደ ሰሜን ብታመሪ፣ ወረኢሉ አካባቢ ከመቶ በላይ የስንዴ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ይህ በምርምር የተገኘው ነው፡፡ የአማራው ሰው ከመቶ በላይ የኮባ ዝርያ መኖሩን አያውቅም፤ ምክንያቱም ከዚያ ባህል አልወጣምና፡፡ የጉራጌው ተወላጅም እንዲሁ በአማራ አካባቢ ከመቶ በላይ የስንዴ ዝርያ መኖሩን አይገነዘብም፡፡ ለምን? ከአማራ አካባቢና ባህል ስላልወጣ ነው፡፡ የከተማ ልጅ አማራም ጉራጌም አካባቢ ቢሄድ፣ እነዚህን የኮባና ስንዴ ዝርያዎች አያውቃቸውም፡፡ ለምን ያልሽ እንደሆነ፣ ባህሉን ስለማያውቀው… በቃ!
ወደ ሼካ ሄደሽ ከአንድ የአካባቢው ሽማግሌ ጋር ወደ ጫካ ብትዘልቂ፣ እያንዳንዱ ዛፍና ቅጠል ለምን ለምን እንደሚያገለግል፣ ስሩ ነው ቅጠሉ መድኀኒት የሚሆነው፣ የትኛው ቅጠል የትኛውን ህመም ያድናል…? የሚለውን ተንትነው ያብራሩልሻል፡፡ ከአካባቢው ባህልና አገር በቀል  ዕውቀት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ዘፈኖች፣ ተረቶችና ስነ-ቃሎች ሰብስበሽ ብትመረምሪያቸው፣ በውስጣቸው በርካታ ብዝሃ ህይወት ታገኛለሽ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፣ ስለ ስራስር መድሃኒትነት፣ ስለ አየሩ፣ ስለ ጋራ ሸንተረሩ፣ ስለ እርሻ፣ ስለ ግብርና፣ ስለ እንስሳት፣ በአጠቃላይ ስለ ብዝሃ ህይወት ብዙ ነገር ይዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሸረሸረና እየጠፋ ያለው ደግሞ ይህ ባህልና እውቀት ነው፡፡ እኛም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች የምንሰራው ይህን እየተሸረሸረ የመጣ የብዝሃ ህይወትና የባህል ጉዳይ ለመታደግ ነው፡፡
ለብዝሃ ህይወትና ለባህሉ መሸርሸር ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?
አንደኛ የከተማ መስፋፋት ነው፡፡ ከተሞች በተስፋፉ ቁጥር ከተማ ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገው እውቀት ብዙ ከባህል ጋር የተቆራኘ ሳይሆን ከመዘመን ጋር የተያያዘና ይበልጥ ከቴክኖሎጂው ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ከተሞች ሲስፋፉ የእርሻና የገጠር መሬቶችን እየወሰዱና እያጣበቡ ነው፡፡ መሬቱ በጠበበ ቁጥር ደግሞ የሚዘራውና የሚተከለው ብዝሃ ህይወት እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ከተሞች በተስፋፉ ቁጥር የገጠር ወጣቶችና ታዳጊዎች ወደ ከተማ ስለሚፈልሱ ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ይቋረጥና የተበረዘና የተከለሰ የከተማ ባህል ውስጥ በማደግ፣ ከወላጆቻቸው የሚያገኙትን ባህልና እውቀት ያጣሉ፡፡ ይህ አንዱ ነው፡፡ ሌላው የእርሻ ስርአታችን ነው፡፡ በፊት ስትዘሪና ስታመርቺ የነበረውን ትተሽ ወደ ሌላ ነገር ስትገቢ የብዝሃ ህይወት ሃብት ይጠፋል፤ ስለ ብዝሃ ህይወት የነበረሽም እውቀት አብሮ ይጠፋል፡፡ ሚዲያውም ለብዝሃ ህይወትና ለባህል መሸርሸር በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ሚዲያው … እንዴት?
በአሁኑ ወቅት በየገጠሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን… ዲሽን ጨምሮ ተስፋፍቷል፡፡ ይሄ ልጆች ከሽማግሌ አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ጋር ያላቸውን የውይይት፣ የምክር፣ የተረት መስሚያና የባህል ጉዳይን መወያያ ጊዜ በእጅጉ ይሻማል፡፡ የወላጅና የልጆች የግንኙነት ጊዜ ይቀራል ወይም ይጣበባል፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው ተረትና ምክር ይልቅ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ላይ ያተኩራሉ፡፡ በዚህም ስለ ብዝሃ ህይወትና ባህል ያላቸው እውቀት ይጠፋል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ አንድ ተማሪ አዲስ አበባ፣ ሆለታ ወይም ሆሳዕና… ብቻ የፈለገበት ቦታ ይማር (ጋናም ይሂድ) ቋንቋው ይገናኛል ወይም ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው፡፡ ስርዓተ ትምህርቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ ልጆች ት/ቤት ውስጥ ፊዚክሱን፣ ሳይንሱን፣ ሂሳቡን እንጂ የራሳቸውን ባህል አይማሩም፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ትምህርት ላይ ነው፡፡ ሲመለሱም በጥናት ላይ ይጠመዳሉ፡፡ ስርዓተ ትምህርቱም ሲቀረፅ አካባቢን ያማከለ አይደለም፡፡ በእንግሊዝኛው “De contextualized” ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት የአካባቢው እውቀት እና ባህል ይሸረሸራል፡፡ ከዚያ በኋላ ልጆች፤ ወላጆቻቸው እውቀት ያላቸው አይመስላቸውም፡፡ የእነሱን ምክር እንደ ኋላቀር መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ለብዝሃ ህይወትና ለባህል መሸርሸር አስተዋፅዋቸው የጐላ ነው፡፡
እነዚህ በችግርነት የተነሱት ጉዳዮች በአኗኗራችን፣ በስነ ምህዳር ስርዓት ወይም በምግብ ዋስትናችን ላይ በተጨባጭ ያመጡት ጉዳት ምንድን ነው?
በአኗኗራችን ላይ ያመጣው አንዱና ተጨባጩ ችግር አዲሱ ትውልድ ነባራዊውን ምግብ መመገብ እየተወ ነው፡፡ ታዲያ ነባራዊ ምግቡን መተው ምን ጉዳት አለው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ መልስ ለማግኘት በየገጠሩ አካባቢ ያሉ ክሊኒኮችን መጐብኘት በቂ ነው፡፡ ነባር የአመጋገብ ስርዓታችን ስለተቀየረ፣ በአገራችን በፊት ላልነበሩ አዳዲስ በሽታዎች እየተጋለጥን እንገኛለን፡፡ ወደፊት ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን እያጣን እንሄዳለን፡፡ ለምሳሌ ጤፍ ከዛሬ 20 እና 30 አመት በፊት ከውጭ የመጡ ተመራማሪዎች፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጤፍ የሚባለው ምግብ ጥሩ ስላልሆነ መቀየር አለበት ብለው ነበር፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ የማያድገው ተጫዎቾቹ ጤፍ ስለሚበሉ ነው እስከመባል ደርሶ ነበር፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ግን ጤፍ “ኪኒዋ” የሚባል ከላቲን አሜሪካ የሚመጣ የእህል ዘር አለ፡፡ እሱ ዘር አንደኛ የጤና ዘር ተብሎ ነበር የሚጠራው፡፡ አሁን ጤፍ ኪኒዋን እየተገዳደረና “The best seed” እየተባለ መጥቷል፤ በምግብ ዘይቱ ማለት ነው፡፡ በመሰረቱ “ግሎቲን” የሚባለው አለርጂ አምጪ ንጥረ ነገር በጤፍ ውስጥ የለም፡፡ ብዙ ልጆች ለግሎቲን አለርጂ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ጤፍ በምግብ ዘይቱ ከስንዴ፣ ከገብስ፣ ከሩዝ እና ከሌሎችም እንደሚበልጥ ተረጋግጧል፡፡ እንደ ጤፍ ጥናት ቢደረግባቸው የምግብ ጥራታቸው የላቀና ለጤና ተስማሚ የሆኑ በእጃችን ላይ ያሉ በርካታ ነባር ዘሮች አሉን፡፡ ወጣቱ ይህን ምግብ ትቶ በኬሚካል የታሸገ፣ አዳዲስ የተዳቀለ ምግብ በሚመገብበት ጊዜ ለጤና ችግር ይጋለጥና አምራች ዜጋ መሆኑ ይቀራል፡፡ ይሄ ሁሉ በአኗኗር፣ በምግብ ዋስትናም ሆነ በስነ ምህዳር ስርዓት ላይ መዛባትን መፍጠሩ ግልፅ ነው፡፡
“መልካ” በአራቱ ክልሎች እየሰራ ያለው የአድቮኬሲ ስራ ነው --- የትኛው ዘርፍ ላይ ነው ትኩረቱ?
“መልካ” --አንደኛ፤ አገሪቱን ሁሉ ማዳረስ ባንችልም በተመረጡ ነገር ግን በርካታ የነባር ዘር ዝርያ ባላቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት እነዚህ ያሉት ዝርያዎች ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ይሰራል፡፡ ሁለተኛ፤ የጠፉና ለመጥፋት የተቃረቡ ነባር ዝርያዎች ካሉ፣ ከአርሶ አደሮች በማፈላለግ እንዲያወጡና እንዲያባዙ ድጋፍና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ያከናውናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ገበሬዎች ዝም ብሎ ጉዳዩ ስለሚገባቸውና ስለሚያሳስባቸው ዘሩን ቋጥረው ያስቀምጡታል፡፡ ሶስተኛ፤ በእነዚህ ነባር ዝርያዎች ዙሪያ አዲሱ ትውልድ እውቀቱ እንዲሰርፅና ስለ ብዝሃ ህይወትና ስለ ባህል አውቆ እንዲያድግ እንዲሁም ለነባር ዝርያዎቹ ጥበቃ እንዲያደርግ የሚያስችላቸውን የእውቀት ስንቅ ማስታጠቅ ነው፡፡ አራተኛው እነዚህ ነባርና ውድ ዝርያዎች የሚቀመጡበት የዘር ባንክ መስራት አንዱ የመልካ ኢትዮጵያ ስራ ነው፡፡
አምስተኛው፤ ገበሬዎችን ያማከለ ምርምር እየተካሄደ ነው፡፡ ገበሬው ዘሩን ከዘራ በኋላ አገር በቀል እውቀቱን እና ሳይንሱን እንዴት አዋህዶ ምርታማ ይሁን በሚለው ላይ ምርምር ያካሂዳል፡፡ ምክንያቱም ሳይንሱንም መተው አይቻልም፡፡ አሁን ችግሩ አገር በቀል እውቀቱን ጥሎ ሳይንሱን ብቻ በተጋነነ ሁኔታ መከተሉ ነው፡፡ አርሶ አደሩ የለመድከውን ትተህ በሳይንስ ተመራ ስትይው፣ ችግር ውስጥ ይገባል፤ አለመደውማ! አሁን የህብረተሰቡ ሳይንቲስቶች ይመጣሉ፣ አርሶ አደሩን ያገኛሉ፤ አብረው ዘር ይዘሩና በዚያው ላይ ስልጠና ይሰጧቸዋል፡፡ ገበሬው በእውቀት እንዲበለጽግ የተለያዩ ስልጠናዎችን እናዘጋጃለን፡፡ ሌላው እርሻ ሲባል ሰው የሚገባው ዘር የሚዘራበት ቦታ ብቻ ነው፤ ነገር ግን በዙሪያው ያለው ሳር፣ ዛፍ እና ሌሎች አይታዩም፡፡ አፈር እንዳይሸረሸር ለመጠበቅ በእርሻው ዙሪያ ያሉ ዛፎች፣ ሳሮች… ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአበባ ዘሮችን የሚያራቡት እነ ቢራቢሮ እንዳይጠፉ ግንዛቤ እንሰጣለን፡፡ ይህን ሁሉ ነው መልካ የሚያከናውነው፡፡
መልካ ባለፉት 10 ዓመታት ምን ውጤት አስመዘገበ?
10 ዓመት የሞላቸውም ያልሞላቸውም ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ 10 ዓመት ከሞላቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ወጣቶች ላይ የምንሰራው ነው፡፡ ወጣቶችን ጫካ እንወስዳለን፤ ጫካ ውስጥ ለአምስት ቀናት ከሽማግሌዎች ጋር እንዲቀመጡ እናደርጋለን፡፡ በነዚህ ቀናት ውስጥ የተለያዩ ዕውቀቶችን ከሽማግሌዎች እንዲቀስሙ ይደረጋሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ ተረት ይነግሯቸዋል፤ ስለ እያንዳንዱ ዛፍና ጠቀሜታው ስለሚያወሯቸው ከባህል ጋር ይገናኛሉ፤ ከደኑ ጋርም እንዲሁ፡፡ ወጣቶቹ “ዛፍ አትቁረጡ፤ በረሃማነት ይመጣል” ከሚለው ባሻገር በአምስቱ ቀናት ጫካ ውስጥ ሲኖሩ ስለ አካባቢ የሚገነዘቡት ነገር አለ፡፡ እነዚህ ልጆች አሁን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡
 በ10 ዓመታት ውስጥ ብዙ መጥፎ ባህሪ የነበራቸው ልጆች ተለውጠው ጥሩ አመለካከት ይዘዋል፡፡ አካባቢያቸውን በራሳቸው ተነሳሽነት የመጠበቅና የመንከባከብ ልምድ አዳብረዋል፤ ይህ ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች የባህል መነቃቃቶች ታይተዋል፡፡ አሁን ባሌ አካባቢ በሰራነው ስራ ከፍተኛ የባህል መነቃቃት አለ፡፡ ስለ ህብረተሰባቸውና ስለ አካባቢያቸው እንዲሁም ስለ ነባር የዘር ዝርያዎቻቸው ያላቸው እውቀት በመጨመሩ፣ ለነዚህ ዝርያዎች ያላቸው ክብርና የሚያደርጉት ጥበቃ የውጤታችን ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) Education for Sustainable Development የሚባል ፕሮግራም አለ፡፡ ይህ ፕሮጀክታችን በዚህ ፕሮግራም እንደ ምርጥ ተምሳሌትነት ተወስዷል፡፡ ይሄም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ “teach a man to fish” በሚል ፕሮግራም ተወዳድረን አሸንፈናል፡፡ (አሳ አትስጠው፤ አሳ እንዴት እንደሚያጠምድ አስተምረው እንደማለት ነው፡፡)
እርስዎ እንዴት በአካባቢና በብዝሃ ህይወት ላይ ሊያተኩሩ ቻሉ? አስተዳደግና የትምህርት ዝግጅትዎ ከዚህ ጉዳይ ጋር ይያያዛል?
ተወልጄ ያደግሁት መርካቶ ነው፡፡ ነገር ግን ት/ቤት ሲዘጋ ክረምቱን አያቶቼን ጥየቃ ወደ ክፍለ ሀገር እወጣ ነበር፡፡ መርካቶ ካሮትና የተለያዩ የአትክልት አይነቶች እንድገዛ እላክ ስለነበር፣ ያም ተፅዕኖ ይኑረው አላውቅም፤ የተማርኩት ግን ባዮሎጂ ነው፤ የባዮሎጂ መምህርም ነበርኩኝ፡፡ አስተማሪ ሆኜ ግንደበረት ስሄድ የሚያምር ገጠር ነበር፡፡ ከዚያ ወሊሶ ስመደብ የአካባቢ ጥበቃ ክበብ አቋቋምኩኝ፡፡ ይህ ክበብ በአገሪቱ ከነበሩ ክበቦች ትልቁና ብዙ ስራ የሰራ ነው፡፡ “ኢንስቲትዩት ኦፍ ሰስቴይኔብል ዴቨሎፕመንት” የሚባል ድርጅት ውስጥ መስራቴም ወደዚህ ጉዳይ እንድገባና እንድቆረቆር ያደረገኝ ይመስለኛል፡፡ አሁን በምሰራው ስራም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡       


Published in ህብረተሰብ

እንዴት ከረማችሁሳ!
በዓላቱ በሰላም አለፉ! በበዓላት ቀናት የሚታይብንን ፈገግታና ደስታ ለሁለም ቀናት ያድርግልንማ!
ስሙኝማ…ህዝቤ ይገለብጠው የለ እንዴ! መቼም ‘አንደኛ’ የምንወጣባቸው ነገሮች እየበዙ አይደል…ከዚህ በፊት እንዳወራነው ትንሽ ቆይቶ በ‘ሲፑም’ ዓለምን ባናስከነዳ ምን አለ በሉኝ፡፡ (“ልጆቼን የማበላው አጣሁ፡፡ ወር ላይ የምመልስልህ አንድ ሁለት መቶ ብር አበድረኝ…” የሚለው ሰው አዲስ ‘ብራንድ’ ቢራ በመጣ ቁጥር “…ተጋፍቶ የሚጠጣው ከየት አምጥቶ ነው!” ምናምን አይነት ጥያቄ መጠየቅ ትተናል፡፡ ልክ ነዋ…አይደለም እኛ ሳይንስም እኮ ገና ያልደረሰባቸው ብዙ ነገሮች አሉ!)
ይቺ ከተማ እኮ እንደ ድሮ በልደታና በአቦ ሳይሆን…ወሩን ሁሉ ‘ሲፕ’ ቤቶቹ ጢም እያሉ የሚጠጣባት ከተማ ሆናለች!
ስሙኝማ…መቼም ‘የቢራዎች ፍልሚያ’ እየተጧጧፈ ነው፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን አለ በሉኝ የቢራ ዋጋ ‘እንደዛኛው ዘመን’ በጠርሙስ ብር ከስሙኒ ምናምን ባይገባ፡፡ አሀ…እነኚህ አዳዲስ የሚባሉት ፋብሪካዎች ሁሉ ገበያ ሲገቡ እንዴት አድርገን ነው ያንን ሁሉ ጠጥተን የምንጨርሰው!)
አሁን፣ አሁን አብዛኞቹ ዝግጅቶች ስፖንሰር የሚደረጉትና፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚተላለፉት አብዛኞቹ ማስታወቂያዎች የቢራዎቹ ናቸው፡፡ እሰይ… እንኳንም ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን እንደዚሀ ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች በዙልንማ! ግን አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ሲበዙ… አለ አይደል…እነኚህ ነገሮች በአእምሮ ያልበሰሉት ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች ያሳስባችኋል፡፡ አለ አይደል… ‘ቢራ መጠጣት’ አይነት ነገሮች ‘የደስታ ጥግ’ ተደርገው ሲቀርቡ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናት አእምሮ ላይ የተሳሰቱ መደምደሚያዎች እንዳይፈጥሩ የማስታወቂያዎቹ አቀራረብ ይታሰብባቸውማ! ስልጣኔያችን በዝቶ  የሰማንያ ምናምን ዓመት አያትም፣ የዘጠኝ ዓመት የልጅ ልጅም እኩል ቁጭ ብለው እስከ እኩለ ሌሊት ቴሌቪዥን የሚያዩባት አገር መሆኗ አይረሳማ፡፡
እኔ የምለው…የቢራን ነገር ካነሳን አይቀር… ‘ከ18 ዓመት በታች የማይሸጥ’ የሚለው የሆነ ነገር የሚጎድለው አይመስላችሁም! አለ አይደል…ማተኮር ያለበት ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች… እነሱ ገዙትም ማንም ገዛው ‘መጠጣት እንደማይችሉ’ ነው፡፡ እናላችሁ…በዚህ በበዓላት ሰሞን በከተማው ብዙ ቦታዎች ያያነው ነገር ቢኖር አሥራዎቹን ያላገመሱ ልጆች ተሰብስበው ሲጠጡ ነው…ያውም አላፊ አግዳሚው እያያቸው! በቀደም ሰብሰብ ብለው ‘የሎዋን ሲገጩ’ ያየናቸው ታዳጊዎች… አለ አይደል… የሁሉም ታላቅ የሆነችው አሥራ አምስት ዓመት ቢሆናት ነው፡፡
እኔ የምለው…የዘንድሮ ወላጅ…አለ አይደል…የሆነ ‘ፈርስት አሜንድመንት’ ምናምን ነገር ያለው ይመስላል፡፡ የልጆቻቸውን ነፃነት ምናምን የሚገድብ ህግ ‘ማውጣት’ አይችሉማ! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን…አለ አይደል…ዘንድሮ በርከት ያሉ ወላጆች በልጆቻቸው አስተዳደግ ላይ ያላቸው አዎንታዊ ተሳትፎ እየቀነሰ ነው ይባላል፡፡ በቃ… የሚበሉትና የሚጠጡት ካቀረቡላቸው፣ ካሽቀረቀሯቸው፣ ለፈለጉት ነገር ሁሉ ገንዘብ ከሰጧቸው የወላጅነት ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን የተወጡ ይመስላቸዋል፡፡
ስሙኝማ…የተሳትፎ ነገር ካነሳን አይቀር…“በስፖርት ዋናው ነገር መሳተፉ ነው”… የምትባል ነገር አለች፡፡ ይሄ እንግዲህ ያኔ ስፖርት ፈረንካ በማያመጣበት ዘመን ነው፡፡ ዘንድሮ…ልጄ…ያውም በጦቢያ ኳስ… “እከሌ አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ብር ተሸጠ…” የሚባልበት ዘመን ደረስን አይደል! (እንትና… እስቲ የእግር ኳስ ‘ኤጀንትነት’ ምናምን ሞክርማ፡፡ “ምናለ አንድዬ እንደው አንድ ጊዜ ገንዘቡን ዝርግፍ ቢያደርግልኝ…” ስትል የከረምከው ሊሳካልህ ይችላላ!)
ስሙኝማ…የእግር ኳስ ነገር ከተነሳ አንድ ግርም የሚለኝ ነገር አለ…እግር ኳስ ተጫዋቾች ሜዳ ሲገቡ ሲጸልዩ ታዩዋቸዋላችሁ፡፡ የምር…‘ለውሳኔ’ እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሀ…ሁሉም… “ዛሬማ ጉድ አታደርገኝም!” እያለ የሚገባ ከሆነ ለማን ‘ሊፈረድ’ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ገና ሜዳ ሲገባ አራት፣ አምስት ጊዜ የሚያማትበው ተጫዋች ሀያ ደቂቃ ሳይሞላ የተጋጣሚውን ተጫዋች እግር ‘ቀልጥሞ’ ቀይ ካርዱን ይከናነባል፡፡ እኔ የምለው…“እንደው ደህና አድርጌ የምቀለጥመው እግር አመቻችትሀ አቅርብልኝ…” ብለው ነው እንዴ የሚለማመኑት!
እናላችሁ…ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ስንኮርጅ እንኳን አያምርብንም፡፡ ‘ሰለጠኑ’ ብለን እየኮረጅናቸው ያሉ አገሮች እኮ ወጣቶቻቸውን ለመከላከል መአት ‘መጠበቂያ’ ህጎች አሏቸው፡፡ ህጎች በወረቀት የሰፈሩ ብቻ ሳይሆኑ በተግባርም የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ “አሥራ ስምንት ዓመት ላልሞላቸው ታዳጊዎች መጠጥ አቅርበሀል…” ተብሎ የተጠየቀ ሰው አለ!  “ዕድሜሀ ሳይደርስ መጠጥ ስትጠጣ ተደርሶብሀል…” ተብሎ የተጠየቀ ታዳጊ አለ!
እናላችሁ…የአሥራ አምስት ዓመት ህጻናት የአስተማሪዎቻቸውን ‘የበጀት ጉድለት የሚሞሉባት’ አገር እየሆነች ነው፡፡
ለሁሉም ወላጆች በዓለም ቆንጆዎቹ ልጆች የእነሱ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ እናማ…የሚያጠፉት ይወደድላቸዋል፡፡ የሌላ ሰው ልጅ ሲያጠፋ ግን... አለ አይደል… “ምናለ ቢቆነጥጡት! ምናምን ይባላል፡፡ የራሳቸው ልጆች ሲያጠፉ ግን...“ቢያጠፋስ ምናለበት፣ ልጅ አይደለም እንዴ…” ምናምን ይባላል፡፡ እናማ…ዘንድሮ ነገሮችን የእኛ ልጆች ሲፈጽሟቸውና የሌሎች ልጆች ሲፈጽሟቸው የሚሰጣቸው ትርጉሞች የተለያዩ  ናቸው፡፡
ክብርና ምስጋና ልጆቻቸውን በተገቢው ስነ ስርአት ላሳደጉና ለሚያሳድጉ ወላጆች!
ስሙኝማ…መቼም በምንም ባህል ስለ አማቶች መአት ነገር ይባላል፡፡ እንደውም ከብዙ ትዳሮች መፍረስ ጀርባ ‘የአማቶች እጅ’ አለበት ይባላል፡፡ ባህር ማዶ ያሉት ወገኖቻችን ግን ከአማቶች ጋር ፍቅር የያዛቸው ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ…ስንትና ስንት እናቶች ወልድው፣ አሳድገው፣ “ያውልህ ውሰዳት…” ብለው ሰጥተው በማረፊያቸው ጊዜ እንደገና የልጅ ልጅ “አሳድጉ…” እየተባሉ አይደል እንዴ የሚሄዱት!
የአማቶች ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ…
ሰውየው ለጓደኛው እያማከረው ነው፡፡
“እባክህ ጭንቀት ይዞኛል፡፡”
“ምነው፣ ደህና አይደለህም እንዴ!”
“እኛ በሌለንበት አማቴን ጠላፊዎች ወሰዷት፡፡ 30,000 ዶላር ክፈሉ አሉን፡፡”
“አሀ… 30,000 ዶላር ከየት አመጣለሁ ብለህ ነው የተጨነክኸው!”
“እሱ አይደለም ያስጨነቀኝ፡፡”
“ታዲያ ምንድነው?”
“ገንዘቡን ካልከፈላችሁ መልሰን ቤት እናመጣታለን ስላሉኝ ነው፡፡”
አሪፍ አይደል! ስለ አማቶች ጭማሪ…
ባል ሆዬ ከሚስቱ ተጣልቶ ለጓደኛው እያማከረው ነው፡፡ “እናቴ ቤት እሄዳለሁ አለችኝ፡፡ እኔም… ዛቻ ነው፣ ቃል መግባትሽ ነው ብዬ ጠየቅኋት፣” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም “ምን ልዩነት አለው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ባል ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ወደ እናቷ ተመልሳ የምትሄድ ከሆነ ይህ ቃል መግባት ማለት ነው፡፡ እናቷን እኛ ቤት የምታመጣ ከሆነ ግን ዛቻ ነው…”  አለና አረፈው፡፡
የአማቶች መብት አስጠባቂ ማህበር ነገር ይቋቋምልንማ!
እናላችሁ…ስለ ልጆች አስተዳደግ የምር መታሰብ ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለ ልጆቹ መጻኢ ህይወትና ስለነገው ህብረተሰብም ማሰቡ መልካም ነው፡፡ ልጆችን የሚያሳስቱ ነገሮች እየተበራከቱ ባሉበት ሰዓት ወላጆች ከልጆቻቸው ትንሽ ሻል ብለው ማሰብ የሚኖርባቸው አይመስላችሁም!
ይቺን ስሙኝማ…ህጻናት ወንድምና እህት እየተጫወቱ ነው፡፡ እናማ… እህትየው ብቻ ነች የምትጮኸው፡፡ ወንድሟ ምንም ነገር አይተነፍስም፡፡ እናትየውም… “ማሚቱ፣ አንቺ ብቻ ለምን ትጮሂያለሽ! እሱም አንዳንዴ ይናገር እንጂ…” ትላታለች፡፡ ህጻኗ ምን ብትል ጥሩ ነው… “እኔ አንቺ ነኝ፣ እሱ ደግሞ አባዬ ነው…”  ብላት አረፈች፡፡ በቃ ለእሷ የእናት ሥራ አባት ላይ መጮህ፣ የአባት ሥራ ደግሞ ዝም ብሎ ማዳመጥ ሆኗላ! አባት እኮ ዝም ብሎ የሚያዳምጥ እያስመሰለ በሆዱ ይሄኔ ስንትና ስንት እርግማን አውርዶባታል! “እኔ ሚስት አገባሁ ብዬ… ለካስ ያገባሁት ምላስና ሰንበር ነው!” ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ….
እኔ የምለው…“አጅሬ፣ እያስመሰልክ የልብህን ትናገራለህ!” ያላችሁኝ ወዳጆቼ…አልገባኝም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ…“እንደ ሰዉ አንተም ታስመስላለህ…” “አስመሳይ ነህ…” ምናምን እያላችሁኝ ከሆነ… አለ አይደል…እስቲ ‘ስታተሴን’ መለስ ብዬ አየዋለሁ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ወይ ‘ማስመሰል!’
እናማ…ልጆች ወደተሳሳተ መንገድ ከመሄድ የሚጠብቃቸው ህጎች በተግባር ላይ ይዋሉማ! “ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ…” የሚሉ አይነት ህጎች ‘ባዶ ቃላት’ መሆናቸው ቢበቃ አሪፍ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

  በመላው አሜሪካ ያሉ ተማሪዎች ባርነት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተወገደ ችግር መሆኑን ይማራሉ፡፡ ይሁንና በሚያሳዝን መልኩ፣ ከ150 ዓመታት በኋላ ዛሬም ችግሩ ሥር እንደሰደደ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በእርግጥ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚል ስሙንና መልኩን የቀየረ ቢሆንም፤ በአሜሪካና በመላው ዓለም አስከፊና የሰው ልጆችን መሠረታዊ ክብር የሚያዋርድ ወንጀል ሆኗል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ጃንዋሪ 2015 ብሔራዊ የባርነትና የህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚወገዝበት ወር እንዲሆን አውጀዋል፡፡ አሜሪካ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን ለህግ የምታቀርብ ሲሆን፤ የችግሩ ሰለባዎችንም ከችግሩ እንዲያገግሙና መልሰው እንዲቋቋሙ ትረዳለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥታችን የጤና ባለሙያዎች፣ የበረራ ሠራተኞችና ሌሎች በግሉ ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎች የህገወጥ ዝውውር ሰለባዎችን በተሻለ መልኩ መለየትና መርዳት የሚችሉበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮችና የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሥራት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስወገድ ዙሪያ የሚደረጉ ጥረቶችን ትደግፋለች፡፡ በዚህ ረገድ የህገ ወጥ ዝውውር ሰለባዎችን ለመጠበቅ፣ ወንጀሉን ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን በመደገፍና ተጎጂዎችን አቋቁሞ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ዙሪያ ከእነዚህ አጋር ድርጅቶች ጋር እንሠራለን፡፡
ዘመናዊ ባርነት በዓለማችን ላይ በየትኛውም ሥፍራ ሊከሰት የሚችል በመሆኑ መንግሥታት፣ የንግድ ድርጅቶችና ደንበኞቻቸው ችግሩን የመከላከል የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማሠማራት፣ ህገወጦች 150 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ህገ ወጥ አሠራር ትርፍ እንደሚያገኙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ መግታት የሸማቾችንም የነቃ ተሳትፎና የግሉን ዘርፍ መሪዎች አጋርነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-“እያንዳንዱ ዜጋ ችግሩን በማጋለጥና የሚለብሰው ልብስ፣ የሚበላው ምግብና ማናቸውም ለሽያጭ የሚቀርቡለት ሸቀጦች ከጉልበት ብዝበዛ በፀዳ መንገድ መመረታቸውን ማረጋገጥ ይችላል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የንግድና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች መሪዎችም የአቅርቦት ሰንሰለቶቻቸው ከጉልበት ብዝበዛ መፅዳታቸውን በማረጋገጥ ባርነትንና ግዞትን መከላከል እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በአሜሪካም ሆነ በዓለም ዙሪያ ከምንጩ ለማድረቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም የአሜሪካ መንግሥት፣ ከወርልድ ቪዥንና ከሜኖናይት የኢኮኖሚ ዕድገት አጋሮች ጋር በመተባበር “የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመዋጋት የተቀናጁ ኢትዮጵያውያን” በተሰኘ ፕሮጀክት በኩል ለጉልበት ብዝበዛና ለህገ ወጥ ዝውውር ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ሰፋ ያለ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማስቻል ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለህገ ወጥ ዝውውር ሊጋለጡ ይችላሉ ለተባሉ ህፃናት ቤተሰቦችም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር አቶ አብዱልፋታህ አብዱላሂ ሐሰን ጋር በመሆን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በተጓዝኩበት ወቅት ፕሮጀክቱ ህገ ወጥ ዝውውርን ከመዋጋት አኳያ እያበረከተ ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ባየሁትም አኩሪ ሥራ የተደነቅሁ ሲሆን፤ኢትዮጵያና አሜሪካ አስከፊ የሆነውን የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን በጋራ በመዋጋት ያሳዩት ቁርጠኝነት በአርአያነት የሚጠቀስ እንደሆነም ተረድቻለሁ፡፡
በሌላም በኩል የአሜሪካ መንግሥት የህገወጥ ዝውውርን ችግር ከምንጩ ለማድረቅ ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(IOM) ጋር በመተባበር “የማህበረሰብ ውይይት” የተሰኘ ፕሮግራም ያዘጋጃል፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ በታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ህገ ወጥ ዝውውርን በመከላከል ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የማህበረሰብ ውይይት ፕሮግራም እያንዳንዱ ማህበረሰብ አባላቱና ነዋሪዎች ለችግሩ እንዳይጋለጡ በማስተማር የህገወጥ ዝውውር ሰለባዎች እንዳይሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ዘመናዊ ባርነት በአሜሪካና ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አጋር ሀገራት የተንሰራፋና ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ያለ ችግር ሆኗል፡፡ ይሁንና ቀጣይነት ባላቸው የተቀናጁ ጥረቶች ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን በመዋጋት ብቻ ሳይሆን ችግሩንም ከምንጩ በማድረቅ ተጨባጭነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንደምንችል እንተማመናለን፡፡

Published in ህብረተሰብ

አንድ አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ውብ ልዕልት ነበረች አሉ - ሁሉም የሚያደንቃት ናት፡፡ ግን ማንም ላግባሽ ያላት የለም፡፡ ንጉሡ አባቷ ተስፋ በመቁረጥ አፖሎ የተባለው አምላክ ዘንድ ሄደና አማከረው፡፡ አፖሎም፤ ሳይክ (Psyche) ልዕልቲቱ ወደ ተራራ መውጣት አለባት፡፡ የሐዘን ልብስም ትልበስ፡፡ እዚያም ብቻዋን ትተው፡፡ ቀኑ ከመንጋቱ በፊት አንድ እባብ ይመጣል፡፡ ያገኛታል፡፡ ያገባታልም፡፡”
ንጉሱ ታዘዘው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ልዕልቲቱ ባሏን ልታይ ስትጠብቅ ቆየች፡፡
የሞት ያህል በሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ በአሰቃቂ ቅዝቃዜ በድና መጠበቋን ቀጠለች! በመጨረሻ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
ስትነቃ በአንዳች ቆንጆ ቤተ መንግስት ውስጥ ንግሥት ሆና ራሷን አገኘች! በየማታው ባሏ ይመጣል፡፡ ኢሮስ ይባላል፡፡ ይገናኛታል (ፍቅር ይሰራሉ)፡፡ ግን አንድ ቃል ኪዳን አስገብቷታል፡- “ሳይክ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፡፡ ግን ፊቴን መልኬን አታይም፡፡ ሳታይኝ ሙሉ በሙሉ ልታምኚኝ! ይገባል፡፡” ወጣቷ ያላትን ፈፅማ ለረዥም ጊዜ በደስታ ኖረች፡፡
ምቾት አላት፡፡ መወደድ አላት፡፡ ደስተኛ ናት፡፡ በየማታው ከሚጎበኛት ሰው ጋር ፍቅር ይዟታል! ግን አንዳንዴ ከእባብ ጋር የተጋባች የተጋባች ይመስላታል! አንድ ጧት ማለዳ ላይ፤ ባሏ ተኝቶ ሳለ ፋኖሱን ለኮሰችና ባሏን ኢሮስን መልኩን አየችው፡፡ ወደር የሌለው ቁንጅና ያለው ወንድ ነው፡፡ ከጎና ተኝቷል፡፡ የፋኖሱ ብርሃን ቀሰቀሰው፡፡
ያፈቀራት ሴት፤ አንድዬ አደራውን አለማክበሯን አይቶ ኢሮስ ላንዴም ለሁሌም ተሰወረ፡፡ ልዕልቲቱ ባለ በሌለ ኃይሏ ፍቅረኛዋን ዳግም ለመመለስ ስትፍረመረም አፍሮዳይት የተባለች የባሏን እናት አግኝታ ጥፋቷን አምና ለመነቻት፡፡ ከእንግዲህ ብዙ ልትፈፅማቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አውቃ፣ ተቀብላ ልትኖር ቃል ገባች፡፡
ምራቷ ግን በልዕልት ውበት ቅናት ይዟት ኖሮ፤ የሁለቱን ፍቅረኞች ዳግም መገናኘት ለመቀልበስ/ ለማነቀፍ ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ልዕልት ሳይክ፤ በተቀበለችው የቤት ስራ መሰረት አንድ ሳጥን ከፈተች፡፡ ለካ ያ ሳጥን ከባድ እንቅልፍ የሚያስወስድ አስማታዊ ሚስጥር ኖሮታል፡፡ ድብን አድርጎ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
መቼም ሳይደግስ አይጣላምና ኢሮስ ደግሞ ከባድ ፍቅር ይዞት ኖሮ እጅግ አድርጐ ተፀፅቷል፡፡ እንደምንም ብሎ ወደ ቤተመንግስቱ ህንፃ ገብቶ ሚስቱን በቀስቱ ጫፍ ጭሮ ቀሰቀሳት፡፡ “በማወቅ ጉጉትሽ ምክንያት ሞት አፋፍ ደርሰሽ ተመለስሽ” አላት፡፡ ዕውቀት ስር መጠለል ሽተሽ ግንኙነታችንን ገሥሠሽ አጠፋሽ! ቃልኪዳንሽን ሰበርሽ! ሆኖም በፍቅር ዓለም ምንም ነገር ለዘለዓለም አይጠፋም፡፡
ባልና ሚስቱ በዚህ ዕምነት ተይዘው/ተጠርንፈው ወደ ዚዑስ ሄዱ፡፡ ፍቅራቸው ከእንግዲህ እንዳይጠፋ ለመኑ፡፡ ዚዑስ ከብዙ ክርክርና ሙግት በኋላ የአፍሮዳይትን ምክር አገኘ፡፡ ከዚያን ቀን ወዲህ ሳይክ (የአንጎላችን አላዋቂ (unconscious) ግን አመክኖአዊ ወገን) እና ኢሮስ (ፍቅር) በደስታና በተድላ ለዘለዓለም ኖሩ!”
በዚህ ታሪክ መሰረት፤ “ይህንን የማይቀበሉና አስማታዊና ሚስጥራዊ ለሆነው የሰው - ልጅ ግንኙነት ማብራሪያ ለማግኘት የሚሹ ሁሉ፤ እንደሳይክ የህይወትን ምርጥ ክፍል ያጣሉ!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ሳይክ፤ በሆዷ እንዲህ አለች፡-
“አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ እነቃለሁ! የምፈልገው አንድ ነገር፤ ጊዜ ብቻ ነው!”
*          *          *
በዓለማዊው ህይወታችን ሳያዩ ማመን ከባድ ነው፡፡ ባሌ እባብ ሊሆን ይችላል ብሎ መኖርም ከባድ ነው! እርግጥ፤ “አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ እነቃለሁ” ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ግን ድካም አለበት፡፡ በቀስት ተጭሮ እንደመንቃት ቀላል አይደለም፡፡ ቃልኪዳንን መጠበቁን ይጠይቃል፡፡ ለማወቅ ጉጉት ለከት ማበጀትም ይፈታተናል፡፡ በልጦ መገኘትን ጠንቅቆ መቻል እንደው ያለጥረት የሚገኝ፣ ክብሪት እንደመጫርም የቀለለ፣ የዘፈቀደ ነገር አይደለም፡፡ በሀገራችን ተፎካካሪን በልጦ መገኘት እጅግ አዳጋች፣ የቋጥኛማ ተራራ ያህል የማይዘለቅ ችግር ሆኖ ከቆየ ሰነባብቷል፡፡ አንድ ፀሃፊ እንዳለው፤ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ ዘውድ በኪሱ ይዞ ስለሚዞር “ውይይቱም፣ ድርድሩም፣ ፉክክሩም ሌላውን በማጥፋት ወይም በመጥለፍ ላይ የተመሰረተ ይሆንና ጤናማ ጉዞ አይሆንም፡፡ ጥንትም እንደዚያው ነበር፤ አሁንም ቅኝቱን አልቀየረም፡፡ በዚህ ቅኝት ላይ የመከፋፈል ዜማ ሲጨመርበት ለባላንጣ ሲሳይ የመሆን አባዜ ይከተላል፡፡ ማ ለምን ይህን አደረገ? ምን እየተጠቀመብኝ ነው? ብሎ ማሰብ ያባት ነው!
ተፈጥሮውን ማሳየት የሚበጀው / የሚያዋጣው አንዳንዴ ብቻ ነው፡፡ ከተቻለ ቃናውን ዝቅ ማድረግ መማር አለብህ… ስትጀምር ብዙ ሳትጮህ መጀመር ነው፤ አዋጪው፡፡ የውድድር ዘዴ! “ከጥበብ ሁሉ ከባዱ ደደብነትህን መቼ እንደምትጠቀምበት ማወቅ ነው!” ይላሉ አዋቂ ፀሀፍት፡፡ ብዙ ከመንጫጫት፣ ሰብሰብ ብሎ የማሰብ፣ የማስተዋል ክህሎት ሊኖር ይገባል፡፡ ከተመክሮ ሁሉ ጥንቃቄን የሚፈልግ ተመክሮ የትግል ተመክሮ ነው፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ጊዜ ኖሮ በቂ ዝግጅት ማጣት አንድም ንዝህላልነት፣ አንድም አቅለ-ቢስ መሆን ነው ከማለት በስተቀር ምን ትርጓሜ ይኖረዋል? ራስን ለክፍፍል ማጋለጥ፣ የራስን ችግር ራስ አለመፍታት፣ የተፎካካሪን ስልትና ስትራቴጂ አለማስላት፣ የህዝብንና የሀገርን ፍላጐት አለማስቀደም፣ የመንገዶችን ኮረኮንችና ሊሾነት አለመለየት አባዜዎች ሁሌ እንደተፈታተኑን አሉ፡፡ ጠንካራነትን ብቻ ሳይሆን ደካማነትንም መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡
”ደካማ ከሆንክ በማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ለክብርህ ብለህ አትዋጋ፡፡ ይልቁንም ማፈግፈግን እወቅ፡፡ ማፈግፈግ ጊዜ መግዛት ነው፡፡ ማገገሚያ ነው፡፡ ቁስልህን ማከሚያና ባላንጣህን ማዳከሚያ ነው፡፡ ቁልፉ ነገር ማፈግፈግን የኅይል ማፍሪያ መሳሪያ ማድረጉ ነው!”
ጉዞን በረዥሙ ማቀድ ሌላው የብልህነት ስልት ነው፡፡ “ዛሬ ካልተሳካ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው! አጓጉል ፍዘትም ስስ ብልት መስጠት ነው፡፡ ፖለቲካ ማመዛዘንን፣ ጊዜ-መግዛትንና ፍጥነትን መሰረት የሚያደርግ “ሸቃባ ሚዛን” ነው ይባላል፡፡ ይሄን ልብ ማለት ግድ ነው፡፡ “ታሪክ ባሸናፊዎች የሚፃፍ ተረት ነው!” የሚባለውንም አለመርሳት ነው፡፡
ታዲያ ፀጋዬ ገ/መድህን በሼክስፒሩ ሐምሌት እንደሚለን፡-
“…ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም”
የሚለውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ሁሉም መስዋእትነት ይጠይቃል፡፡ መስዋእትነት እንደ ዴሞክራሲ ሁሉ ገጠመኝ አይደለም፡፡ ቀድመው መሰረትና እሳቤ የሚያበጁለት ነው፡፡
“አንተኛም ካላችሁ እንገንድሰው
መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው!” እያልን የምናላዝንበትም ከቶ አይደለም፡፡ ሂደት ነው፡፡ መቀጠል አለበት፡፡ ዝምታ እንኳ መስዋእትነት የሚጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ ትግል በጥበብ የተሞላ መንገድ ነው! ካልበሰሉ በድፍረት ብቻ የሚወጡት የወጣት ስሜታዊነት ዘመቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እንደ ፋሽን በወረት የሚያሸበርቁበት የገና ዛፍም አይደለም፡፡ ከጀመሩ በኋላ “ፉርሽ ባትሉኝ!” የሚባልበት ጨዋታም አይደለም! “ሰይ ብል ባንከረባብት” እያሉ ያሹትን የሚያጭዱበት ቁማርም መሆን የለበትም! “አርፋ ስጠኝ”፣ “አቫንስ ስጠኝ” እያሉ የሚጠባበቁበት አይደለም፡፡ ትግል መሰረቱ የፖለቲካ ክህሎት ነው፡፡ ያልተነገረ ያልተሰማ ነገር የለም፡፡ ከአንጃ እስከ ዋና መስመር፣ ከቀኝና ግራ መንገደኛ እስከ አምስተኛ-ረድፈኛ፣ ከውጪ ወራሪ እስከ ውስጥ ቦርቧሪ፣ ከአናርኪስት እስከ ዘውድ-ናፋቂ፣ ከገንጣይ-አስገንጣይ እስከ በታኝ-ከፋፋይ፣ ከጠባብ እስከ ትምክህተኛ፣ ከአኢወማ እስከ ሊግ፣ ከአንጋፋው ፎረም እስከ ብላቴናው ፎረም…” ስርዝ የኔ ድልዝ ያንተ፣ እመጫት የሷ፣ ሆያ-ሆዬ የሰፊው ህዝብ ስንባባል በኖርንበት አገር ትግል “ሁለት አንድ ዐይናዎች ተጋብተው ሁለት ዐይን ያለው ልጅ ወለዱ፡፡ ምነው ቢሉ፣ አንዱን ከእናቱ አንዱን ከአባቱ!” ብለው የሚገላገሉት አይደለም!? “ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ” የሚባለው ተወዶ አይደለም፡፡ እሙናዊውን ዓለም እናጢን! ሁሌ ልጅ አንሁት - ልብ-እንግዛ!!


Published in ርዕሰ አንቀፅ

ጥንታዊውን ስልጣኔ ለማሻሻል በመጀመርያ ስልጣኔውን ማክበር፣ ማቆየት፣ መጠበቅና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

        ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ በነፃ አስተያየት አምዱ፣ ዮሐንስ ሰ. በተባሉ ግለሰብ ፀሐፊነት “እውን ኢትዮጵያ ልዩና ድንቅ አገር ናት?” በሚል ርዕስ ያወጣውን ሸንቋጭ ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ፣ ከፀሐፊው ጋር ያለኝን የሃሳብ ልዩነት ለማስቀመጥ ወደድኩ፡፡
ፀሐፊው በሉዐላዊነትና በምዕራባውያን አስተምህሮ ሊያጠምቁን በሞከሩበት ፅሁፋቸው፣ ለገና በዓል በተዘጋጀው የቲቪ ፕሮግራም አቶ ዳንኤል ክብረትና አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ በምዕራባውያን ባህል መወረራችንንና የሀገራችን ባህል እየተሸረሸረ መሆኑ አሳስቧቸው ያደረጉትን በቁጭት የተሞላ ንግግር ነው መነሻ ያደረጉት፡፡
“…ሸማ፣ የሳር ጐጆ፣ የበሬ እርሻ፣ እንስራ የመሳሰሉ ከሺ ዘመናት በፊት በታላቅ የፈጠራ ባህል አማካኝነት የተፈለሰፉና ከትውልድ ወደ ትውልድ በልማድ የወረስናቸውን ነገሮች እንደታቀፍን ቆመን እንደቀረንና ደንዝዘን እንደተቀመጥን…” ፀሃፊው ይነግሩናል፡፡
ለማድረግ ያልቻልነውን ነገር ሲገልፁም፤ “ከሸክላ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የብረት፣ የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ፣ ከጠላና ጠጅ አልፈን የወይን ጠጅና የቢራ ፋብሪካ መፍጠር አልቻልንም” ይሉናል፡፡ ዮሐንስ ሰ. ባነሱት ሃሳብ ላይ ያለኝን የተቃውሞ ሀሳብ እንዲያንጸባርቅልኝ ሶስት ሃይለ ቃላትን በማስቀመጥ እነሱን እያብራራሁ ልቀጥል
1ኛ - ጥንታዊውን ስልጣኔ ለማሻሻል በመጀመርያ ስልጣኔውን ማክበር፣ ማቆየት፣ መጠበቅና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ማለቴ … ከዘመናት በፊት በነበረው ስልጣኔ የተፈለሰፈውን ግኝት አክብረን ስናቆየውና ስንጠብቀው ነው ዛሬ ላይ ልንጠቀምበት የምንችለው፡፡ ያቆየነውን ደግሞ ስንጠቀምበት ነው ክፍተቶቹንና ችግሮቹን ልንለይ የምንችለው፡፡ ችግሮችን ከለየንና በጉድለቶቹ ምክንያት መጎዳታችን በግልጽ ሲታወቀን፣ ያኔ መፍትሄዎችን ወይም የተሻሻሉ ግኝቶችን እንፈጥራለን ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አክብሮ ማቆየት፣ መጠበቅና መጠቀምን፤ መጠቀም ደግሞ፤ ችግሮችን መለየትን፤ ከዚያም ችግር ብልሀትን ይወልዳል ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ እንኳን ልናሻሽላቸው በወጉ ከአባቶች ተቀብለን ልንጠቀምባቸውም ያልቻልናቸውን በባህል ወረራው የተነሳ እንደ ኪነ-ህንፃ፣ ስነ ክዋክብትና ህክምና ያሉ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ጥበቦች ስናስብ፣ ሁለቱ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን፤ ቀደምት ስልጣኔንና ባህልን የማቆየት የመጠበቁ ሃሳብ ላይ ሙጥኝ የማለታቸውን ተገቢነት እንረዳለን፡፡
2ኛ - ካላሻሻልነው አላስፈለገንም ማለት ነው፡
ዮሐንስ ሰ. በዚሁ ጋዜጣ ላይ ከዚህ ቀደም በታተመ ፅሁፋቸው፤ በንፋስ ሀይል የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ከውሃ አንፃር ውድ ስለሆነ ገና ለገና “የሰለጠኑት” አገሮች ስለተጠቀሙበት ብቻ በሚል ሀብት መባከን የለበትም፤ ቴክኖሎጂውም አያስፈልገንም እያሉ ሲሟገቱ ነበር፡፡ የዚህ ሙግታቸው አመክንዮ ‘ለአንድ ሀገር ስራ ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች በሀገሪቱ ምድር ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ ሊሆኑ ይገባል’ የሚል እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡
 ታድያ ይሄንን ውሃ የሚያነሳ መከራከርያ ለሳምንቱ ጽሁፋቸው ማጠንጠኛ ለማድረግ ለምን አልፈለጉም ወይም አልቻሉም?
የአንድ ማህበረሰብ የስልጣኔ ወይም የለውጥ ፍላጎት ከራሱ ከማህበረሰቡ ነው የሚመነጨውና ሊመነጭም የሚችለው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ችግርም በራሱ በማህበረሰቡ አረዳድ የተወሰነ እንጂ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል ሌላ አካል ሊወሰን አይገባም፡፡ ማህበረሰቡ ያሉበትን ችግሮች በመፍታት ሂደት አዳዲስ ግኝቶችን ሊፈጥር ወይም ያሉትን ሊያሻሽል የሚችለው ከችግሩ አስገዳጅነት በሚመጣ ተፈጥሯዊ ግፊት ነው፡፡
(“ችግር ብልሀትን ይወልዳል” እንደሚለው ነው ጥንታዊው ሀበሻ፡፡) ፈረንጆቹም “NECESSITY IS THE MOTHER OF INNOVATIONS” ይላሉ፡፡ /የእነሱ ነገር በአንድ በኩል የነፃ አስተሳሰብ አራማጅ ነን እያሉ፣ በሌላ በኩል የእኔ አውቅልሃለሁ አቀንቃኝ ሆነው ይገኛሉ እንጂ!
እኛ ኢትዮጵያውያን ከሺ ዓመታት በፊት የነበሩት አባቶቻችን የፈጠሩትን ጠቃሚ ነገሮች ጠብቀን አቆይተን እስከ ቅርብ ጊዜም (የባህል ወረራው በእጃችን ያለውን አጣጥሎብን የምዕራባውያንን ግሳንግስ ናፋቂ እስካደረገን ቀን ድረስ) ስንጠቀምባቸው ቆይተናል፡፡ ታድያ ከተጠቀምንባቸው ለምን አላሻሻልናቸውም? መልሱ በጣም ግልፅ እና አጭር ነው - ማሻሻል ስላላስፈለገን፡፡
እስቲ አስቡት … የሸማን ጥበብ ወዴት እናሳድገው? ወደ ሻማ? ከሸማ ወደ ሻማ? ቁልቁል ወደ ቴትሮን? ወደ ናይለን …ከዚያ ደግሞ 100% ጥጥ ፍለጋ መኳተን፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ እራሳችን ከአቅራቢያችን የተመረተውን ጥጥ በየቤታችን ፈትለን፣ ደውረንና ሸምነን ለሰውነት ተስማሚና ምቹ የሆነውን የጥበብ ልብስ መልበሱ ሳይጎረብጠንና ሳይረብሸን ሰው ስላደረገ ነው የምናሻሽለው ወይስ ለምን? ሌሎቹም ግኝቶች እንዲሁ ናቸው - አብዛኞቹ በቀላሉ በአቅራቢያችን የሚገኙ ወጪ ቆጣቢና ለከባቢ አየር ተስማሚ (friendly) ናቸው - ልክ እንደ የውሃ ግድብ ኃይል ማመንጫዎቹ፡፡ አቶ ዮሐንስ ሰ. በሸንቋጭ ፅሁፋቸው ጠላና ጠጅ ወደ ቢራ ፋብሪካ ማደግ እንደነበረባቸው ጠቁመውናል፡፡ ቢራ ፋብሪካ በቤት ውስጥ ከሚጠመቀው ጠላ ወይም ጠጅ የተሻሻለ መሆኑ ነው እንግዲህ እንደሳቸው አባባል፡፡ እንደመግዛትና እንደመጠጣት አቅማችን እያየን በየቤታችን ጠምቀንና ጥለን ከጉሽ እስከ ፊልተር፤ ከከረመ እስከ የተላሰ አማርጠን መጎንጨት እየቻልን ለምንድነው የተወሰኑ ካፒታሊስቶችን ብቻ ሊጠቅም የሚችል ፋብሪካ ከፍተን (ተከፍቶብን) ምላሳችን ካልለመደው ጎምዛዛ ቢራ ጋር በተፅዕኖ የምንጋተረው?
የገና ጨዋታንም መውሰድ ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ዮሐንስ ሰ. አጣጥለው እንዳቀረቡት የገና ጨዋታ መሯሯጥ ብቻ አይመስለኝም፡፡
የማራኪ ስፖርታዊ ጨዋታ መለኪያ ብለው ያቀረቡትም ምንም እንኳን ከኛ አንፃር የወጣ መለኪያ መሆኑ ቢያጠራጥርም የገና ጨዋታ ግን ሁሉንም የሚያሟላ ነው፡፡ የስፖርተኛው የአካልና የአእምሮ ብቃት የእንጨት ኳሱን ይዞ እየተታለለ ለመሮጥ በሚያደርገው ጥረት የሚለካ ሲሆን ለተመልካች አመቺነት ለሚለው ደግሞ ጨዋታው ከጎልፍና በተለይም ከማራቶን በተሻለ ለተመልካች አመቺ መሆኑ እሙን ነው፡፡
አቶ ዳንኤል ክብረት እንዳሉትም፤ የገና ጨዋታን ከገና በዐል ቀደም ብለን ጀምረን ፍፃሜውን የበዐሉ እለት አድርገን ብንጫወትና ከጨዋታው ሊገኙ በሚችሉ ጥቅሞች ሁሉ ብንጠቀም ደግሞ ማለፊያ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ስንጠቀምበት ነውና ክፍተቶቹን አይተን ልናሻሽለው የምንችለው፡፡ ተጠቅመንበት ካላሻሻልነው በበቂ አዝናንቶናል ማለት ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡
3ኛ - ወገኛ ነገር - የዮሐንስ ሰ. ነገር ወይስ የእኛ ነገር?
“… በአዲስ አበባ የሚኖር ደራሲ፣ ዘፋኝ ሙዚቀኛ ወይም ጋዜጠኛ ወደ ቆላማው አካባቢ … የሀመር ተወላጆች ወደሚኖሩበት ሄዶ አኗኗራቸውን ሲያደንቅ፣ ከተሜነትን ሲያንቋሽሸው ይቆይና ወደየከተማ ኑሮ ለመመለስ ይሮጣል፡፡” ይላሉ ዮሐንስ ሰ. በዚሁ ጽሁፋቸው፡፡ አትፍረዱባቸው፡፡ እርሳቸው ይህን ፅሁፍ የጻፉት በስጋና በአእምሮ ሆነው፣ እንደ ጥበበኞቹ እንደ ፍቅረማርቆስ ደስታ ወይም የጎሳዬን ኢቫንጋዲ ዜማ እንደ ፃፈ ደራሲ አሊያም ደግሞ እንደ ጥልቅ አሳቢዋ ድምፃዊ እጅጋየሁ ሽባባው በነፍስ ሆነው አይደለም ጉዳዩን ያጤኑት፡፡
ዮሐንስ ሰ. የወገኛ ነገር ሆኖባቸው ስልጡንና ዘመናዊ ለመባል (ታድያ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?) ከላይ የቀነጨብኳትን አንቀፅ በፅሁፋቸው ከማካተታቸው በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች እራሳቸውን ጠይቀው ቢሆን መልካም ነበር፡፡
ጠቢባኑ ለምን ይዋሻሉ? የዕለት እንጀራዋን ያሸነፈችውና ሙያዊ ነጻነቷን ያወጀችው ጂጂ፤ ናፈቀኝ እያለች የገጠሩን ህይወት ስታዳንቅና ‘ደህና ሁን ከተማ’ እያለች የከተሜን ህይወት ስታጣጥል ለነፍሷ የተገለጠላት አንዳች እውነት ከውስጧ ፈንቅሏት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ምክንያት ይኖራታል? እኛስ ታዳሚዎቹ እነኚህን የጥበብ ስራዎች ስንሰማ ወይ ስናነብ አንዳች ነገር ወደ ገጠሩ “ሂድ ሂድ/ ሂጂ ሂጂ” የሚለን ለነፍሳችን አንዳች የጥሪ ደወል ማቃጨል ቢችሉ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ታድያ ለምን ’ሂዱ ሂዱ’ የሚለንን ስሜት ተከትለን ወደ “አልሰለጠነው” ገጠር አልሄድንም? ካሉኝ ደግሞ ለዮሐንስ ሰ. አንድ ጥያቄ አለኝ፡- ገነት ለመግባት ሁሉም ይፈልጋል፤ ሁሉም ሊገባ ግን ይቻለዋል?
“ስልጡኑና ዘመናዊው” ዮሐንስ ሰ. እንዲህም ብለዋል፡፡ “… እንዴት ልብስ አለመልበስ እንደ ስልጣኔና እንደ ባህል ይቆጠራል? ባህል ማለት እኮ በሰፊው ስር ለመስደድ የበቃ የፈጠራ ውጤትና ስኬት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ልብስ መስራት እና መልበስ፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ እላቸዋለሁ …
ልብስ አለመልበስ እንደ ስልጣኔና እንደ ባህል ላይቆጠር ይችላል፤ ነገር ግን ምድር ካፈራቻቸው ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች የተቀመመ ሽቱ፣ እጣን፣ የጭቃ ቅባት ሰውነትን አስውቦ፣ በላዩ ላይ ደግሞ በልዩ እደ ጥበባዊ ክህሎት የተሰሩ የእግርና እጅ ጌጦች በራቁት ገላ ላይ ደርቦ ልብስ ሳይለብሱ፣ ልብስ ከለበሰው በላይ ውብና ጨዋ ሆኖ መታየት ባህልና ስልጣኔ ካልተባለ እራሱ ስልጣኔ ምንድነው?
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ ምሉዕ ነው፡፡ ከልዩ ልዩ ወረራዎችና ዝርፊያዎች ተከላክለንና ተንከባክበን ልናቆየው ብቻም ሳይሆን ልንጠቀምበትና ለልጅ ልጅም ልናስተላልፈው እንችላለን፡፡
ስልጣኔውና ባህሉ በራሱ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የመለወጥና የመሻሻል ተፈጥሯዊ ባህሪ ስላለው ለመሻሻል ነጋሪ አይፈልግም፡፡ ካልተሻሻለ አላስፈለገውም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ሀገር ልዩና ድንቅ ብቻ ሳትሆን የበቃችና የነቃች ሉዓላዊት ሀገር ነችና!

  • አቶ አስራት ጣሴ ብለው መድረኩን ረግጠው ወጥተዋል
  • በቦርዱ ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች በህግ ሊያስጠይቁ ይችላሉ ተብሏል
  • “መድረክ” የስነ ምግባር ደንቡን ልፈርም እችላለሁ ብሏል

   ፋና ብሮድካስቲንግ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ ሆቴል የግንቦቱን ምርጫ አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆኑ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን አሰራር ሲተቹ፣ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በፓርቲዎች ገንዘብ ክፍፍል ላይ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
“5ኛው ሃገራዊ አጠቃላይ ምርጫ ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የባለድርሻ አካላት ሚና” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ኢዴፓ፣ ኢህአዴግና መድረክ የሃገሪቱን የምርጫ ሂደት የዳሰሰ ነው ያሉትን ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
በፓርቲዎቹ የቀረበው ፅሁፍ ከተጠናቀቀ በኋላ በፅሁፉ ላይ አስተያየትና ጥያቄ እንዲያቀርቡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በተጋበዙበት ወቅት የአንድነት ፓርቲ ተወካይ አቶ አስራት ጣሴ፤ በምርጫ ቦርድና በውይይቱ አዘጋጆች ላይ ያላቸውን አስተያየት ከሰነዘሩ በኋላ ፓርቲያቸው በሁለት አመራሮች መወከሉን በመቃወም ጉባኤውን ጥለው ወጥተዋል፡፡
“አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ ፈፅሞ የኢትዮጵያን ምርጫ ማካሄድ አይችልም” ሲሉ ኃይለቃል የተናገሩት አቶ አስራት፤ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም፣ ተአማኒነት የለውም ብለዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ምርጫ ቦርድና ሬዲዮ ፋና በህጋዊ መንገድ የተመረጠን የአንድነት ፕሬዚዳንት ባለመቀበል ፓርቲውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉም ከሰዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩት አቶ አስራት፤ ምርጫን በሚያህል ጉዳይ ለምንድን ነው የምንቀልደው? በማለት ጉባኤውን ጠይቀዋል፡
በውይይት መድረኩ ላይ አስተያየት እንዲያቀርቡ እድሉ የተሰጣቸው በዲ-አፍሪክ ሆቴል ተደርጓል በተባለው የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በፕሬዚዳንትነት መመረጣቸውን የገለፁት አቶ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው፤ አቶ አስራት የሚያከብሯቸውና የሚያደንቋቸው የትግል አጋራቸው መሆናቸውን ጠቅሰው “እኔ የተመረጥኩት በ2004 ዓ.ም በፀደቀው የፓርቲው ደንብ ነው፤ እሳቸው ያሉበት አመራር ደግሞ በ2006 ወጥቷል በተባለውና ባልፀደቀው ደንብ ነው የተመረጡት” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በአሁን ሰዓት የአንድነት ህጋዊ አመራር ነን ብለን ነው የምንቀሳቀሰው በማለት አቶ ትዕግስቱ አክለዋል፡፡
የአቶ አስራት ጣሴ ጉባኤውን አቋርጦ መውጣት በመድረኩ አዘጋጆችና በአንዳንድ ተሳታፊ ፓርቲ አመራሮች የተተቸ ሲሆን የፋና ብሮድካስቲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዱ ይመስል ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግርም፤ ጣቢያው “ለድምፅ አልባዎች ድምፅ መሆን” የሚል አላማ እንዳለው ጠቁመው፣ በዚህ መሰረት የትኛውም ሚዲያ አክብሮ ሊያስተናግዳቸው ላልፈለጋቸው ለእነ አቶ ትዕግስቱ ሃሳባቸውን የሚገልፁበትን እድል እንዳመቻቸላቸውና በቀጣይም ይህን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ሌላው በውይይት መድረኩ ላይ ጎልቶ የወጣው በቅርቡ ዘጠኝ ፓርቲዎች “ትብብር” በሚል መደራጀታቸውን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ “አደረጃጀቱን አላውቀውም፤ ህጋዊ አይደለም” ማለቱን ተከትሎ የተከሰተው ውዝግብ ሲሆን የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ተወካዮች፤ ምርጫ ቦርድ በህግ ያልተሰጠውን ስልጣን ከየት አምጥቶ ነው ትብብሩ ህጋዊ አይደለም የሚለው? የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል - ቦርዱ በግንባር፣ በቅንጅት፣ በውህደት ደረጃ ያሉ አደረጃጀቶችን ብቻ የመቆጣጠር ስልጣን እንዳለው በመጥቀስ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌራ በበኩላቸው፤ “በህግ ያልተከለከለ ነገር እንደተፈቀደ ይቆጠራል” የሚለው አስተሳሰብ ጥያቄውን እንደፈጠረ ጠቅሰው፣ አደረጃጀቱ በትብብር ስም መግለጫ ማውጣት፣ ደብዳቤ መፃፍ አይቻልም ነው ያልነው እንጂ ፓርቲዎች መተባበራቸው አይጠላም ብለዋል፡፡
የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “በኢህአዴግ አይን ትብብር አይጠላም፤ ትብብሩ ለምን አላማ ነው? የሚለው ግን አጠያያቂ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም አቶ ደስታው ኢህአዴግ በዚህ ምርጫ በስነ ምግባር ተወዳድሮ አሸናፊ ለመሆን መዘጋጀቱን፣ ለአባላቱም ተከታታይ የስነ ምግባር ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ አንዳንድ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በቅርቡ በምርጫ ቦርድ ቀመር ወጥቶለት ለፓርቲዎች እንዲከፋፈል በተደረገው ገንዘብ ላይ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረንስ ም/ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው፤ ቦርዱ ለፓርቲዎች ያከፋፈለው ገንዘብ እንደሚያንስና ለምንም ስራ ሊያውሉት እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡ ለፓርቲዎች የተከፋፈለው ገንዘብ በግለሰብ ደረጃ ከ250-500 ብር ብቻ ሊደርስ የሚችል ነው ያሉት አቶ ሽፈራው፤ በዚህ ገንዘብ ምንም መንቀሳቀስ አይቻልም፣ ይታሰብበት ብለዋል፡፡ የኢትየጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ ምርጫውን የጋራ እናድርገው፣ ብሄራዊ መግባባት እንፍጠር ያሉ ሲሆን ሬዲዮ ፋና ይህን መሰሉን የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አድንቀዋል፡፡ የቅንጅት ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶም በሁሉም ፓርቲዎች መካከል መቻቻል እንዲኖርና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ “የስነ ምግባር ደንቡን ያልፈረሙ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመወያየት አለመቻላቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ፓርቲዎች አዋጅ ሆኖ የወጣን ህግ ፈርሙ መባላቸው ትክክል አይደለም፤ ፈርሙ ከተባለም መድረኩ እንዲስተካከል የሚፈልጋቸው አንቀፆች ከተስተካከሉ የስነ ምግባር ደንቡን እንፈርማለን” ብለዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉ የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች፤ መድረክና ሌሎች ፓርቲዎች ደንቡን ፈርመው እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ በበኩላቸው፤ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ በምርጫ ቦርድ ላይ የሚያቀርቡት በመረጃ ያልተደገፈ ውንጀላ በህግ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል አሳስበዋል፡፡ “ምርጫ ቦርድ ኢህአዴግ ነው፤ የሚለው ዘመቻ በህግ የሚያስጠይቅ ነው” ብለዋል፤ አቶ አስመለሽ፡፡
“ቦርዱ ኢህአዴግ ቢሆን ኖሮ ለፓርቲዎች ከሚሰጠው ገንዘብ ላይ ኢህአዴግ ማግኘት ከነበረበት 20 በመቶ አይቀንስም ነበር” ያሉት አቶ አስመላሽ፤ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ እነዚህ ውንጀላዎች መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በበኩላቸው፤ ቦርዱ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ አደረጃጀት ፈጥሮ፣ ለዓለም ተሞክሮ በሚሆን ደረጃ ነፃ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ገለልተኛ አይደለም የሚሉት ውንጀላዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡ በጉባኤው ላይ መንግስትን ወክለው ሃሳባቸውን የሰነዘሩት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እውነቱ ብላታ፤ የመወዳደሪያ ሜዳው ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል እንዲሆን መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም በውጭ ኃይሎች ምርጫው እንዳይረበሽ በንቃት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  


Saturday, 24 January 2015 12:32

ካምፕ ቅየራ

ከማን፣ የትና መቼ እንደሰማሁት ባላስታውስም ውስጤ የቀረ አንድ አባባል አለ፡፡ “አቋሙን የማይቀይር ሬሳ  (የሞተ ሰው)  ብቻ ነው” የሚል፡፡ በዚህ ብሂል (ብሂል ከሆነ) በመርህ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ እስማማለሁ፡፡ በመርህ ማለቴ አቋምን ከመቀየር አስቀድሞ “መጠየቅ” ያለበት ነገር አለ ብዬ በማመኔ ነው፡፡ ይኸውም የተሟላና ተጠየቃዊ የሆነ ምክንያት ነው! አንድ ሰው ቀደም ሲል ሲያምንበት፣ ሲመሰክርለት፣ ሲያራምደውና ሲያድርለት  የነበረውን አመለካከትም እንበለው ርዕዮት… ሲቀይር፤ ቀይሮም ለሌላ አመለካከትና ርዕዮት ሲያድር፣ በዚህም ሌላ ካምፕ ውስጥ ሲገኝ፣ እጅጉን ተጠየቃዊ የሆነ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህን እስካደረገ ድረስ ይህ ሰው አቋሙን የቀየረው “ሰው” የመሆኑ ፀጋ የሰጠውን አቅም ተጠቅሞ ነውና ቅየራው ምናልባትም ያስመሰግነዋል እንጂ አያስከስሰውም፤ አያስወቅሰውምም፡፡ ደግሞም የሰው ልጅ በመኖር ውስጥ ሲያልፍ፣ በዚህም በዕውቀትና በልምድ ሲያድግና ሲበለፅግ ለነገሮች የነበረው አመለካከትና አስተሳሰብም አብሮ መለወጡና ማደጉ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በመሆኑም በአንድ ነገር ላይ የነበረውን የቀደመ አቋም ሊያሳድግና ሊያሻሽል ወይም ጭራሹኑ ሊለውጥና በሌላ ሊተካ ይችላል፡፡ ማንም በነበረበት ላይዘልቅና ላይገኝ ይችላል፡፡ ጥያቄው አለመገኘቱና አቋሙን መቀየሩ ሳይሆን ጥያቄው ቅያሬው ምክንያታዊነቱ ምን ያህል ተጠየቃዊነት ላይ የተመሰረተ ነው የሚለው ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ማለት አንድ ሰው፣ ሰው በመሆኑ ብቻ የፈለገውን የመከተልና ለፈለገው የመቆም መብቱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ እኔ እንዲህ አምናለሁ፡፡ አምኜም እጽፋለሁ፡፡ ያመኑትን መጻፍ መብት አይደል? ልቀጥል፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ በዚህችው በእኛይቱ ሀገር ቀላል ከሆኑ ነገሮች አንዱ ድንገት ካምፕ ቀይሮ መገኘት ይመስለኛል፡፡ “እኔ እንዲህ ነኝ፤ እንዲህ አምናለሁ፤ ለዚህ እታገላለሁ፤…” ሲል የነበረ ሰው፣ እኛም አምነነው “እውነት ነው፤ እሱ እንዲህ ነው፤” እያልን በጉልህ የመሰከርንለት ሰው ድንገት የኖረበትን ካምፕ ቀይሮ ሌላ ካምፕ ውስጥ ይገኛል፡፡
አምናችሁትና ተማምናችሁበት አብራችሁት መንገድ የጀመራችሁ ወዳጃችሁን ድንገት መንገድ ቀይሮ በተቃራኒው ጎዳና ላይ ታገኙታላችሁ፡፡
ተነፍገነዋል ያላችሁትን መብትና ነጻነት ለማስመለስ አብሯችሁ መክሮና አቋም ይዞ ሲታገል የነበረውን ጓዳችሁን ድንገት ካምፑን ቀይሮና ለምትታገሉት አድሮ ታገኙታላችሁ፡፡… ሊያውም እዚህ ግባ በማይባል “ቀሽም” ምክንያት፡፡ አውቃለሁ “ቀሽም ምክንያት” አልኩ እንጂ ያለ ምክንያት የሚፈጸምማ አንዳችም ነገር የለም፡፡ ጥያቄው የምክንያቱ ተጠየቃዊነት ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ይዘን ዘንድሮ የፋሽን ያህል በብርቱ የተያዘውን ካምፕ ቅየራ እንፈትሽ፡፡ ካምፕ ቅየራው የሚጠበቅም የማይጠበቅም አይነት ነው፡፡ ይህንን ያሰኘኝ የካምፕ ቀያሪዎቹ ማንነት ነው፡፡ ማንነት ስል አቅምና ሰብዕናንም ያጠቃልላል፡፡ ካምፕ ቀያሪዎቹ ግለሰቦች፤ ሀገሬው በየዋህነትም በሉት በ“ቲፎዞ” ግፊት… “ታላላቅ ሰዎች” ናቸው ብሎ የሚያደንቃቸውና የሚያከብራቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ካምፕ ቀያሪዎችን ልብ ብላችሁ አይታችኋቸው ከሆነ፣ አብዛኞቹ ካምፕ የቀየሩበትን ምክንያት በቅጡ ማስረዳት የሚችሉ አይደሉም፡፡ ለምን መሰላችሁ?
ሲጀመር በየትኛውም ካምፕ ውስጥ ለመገኘት አቅሙ ያላቸው አይደሉም፡፡ አቅም ስል ግለሰቦቹ በራሳቸው ሙያ ያላቸውን አቅምና ችሎታ ክጄ ወይንም ዘንግቼ አይደለም፡፡ ካምፑ የሚፈልገው አይነት አቅም የላቸውም እያልኩ ነው፡፡ ግን በተለያዩ “ከንቱ” ምክንያቶች ግፊት አንዱ ካምፕ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ወይ ስሜታዊ ሆነው፣ ወይ አደርባይነት አጥቅቷቸው (ይህ በራስ ካለመተማመን ይመነጫል)፣ ወይንም ደግሞ የማይገባና ያልደከሙበትን ጥቅም (ዝና፣ ገንዘብ) ሽተው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ምክንያቶቹ አቅምን የማይጠይቁ “ከንቱ” ምክንያቶች ናቸው፡፡
አሳዛኙ ነገር ካምፕ ቅየራው የግለሰቦቹን ማንነት ትዝብት ላይ ጥሎ ብቻ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ጉዳቱ የሀገርና የህዝብ ነው፡፡ እንዴት? እንዳለመታደል ሆኖ እነዚህ ካምፕ ቀያሪዎች በአብዛኛው በህዝብ “የሚታወቁ” አንዳንዶቹም (ጊዜውና ሚዲያው አብሮላቸው) ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ሳይገባቸው “የሚያደንቃቸው” ናቸው፡፡ እንግዲህ የጥፋቱ አስኳል ያለው እዚህ ጋ ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ ህዝብ የሚያደንቀውን ግለሰብ ያምናል፡፡ ባስ ሲልም ያ “ተደናቂ” ግለሰብ ሰው መሆኑና በዚህም የሰውን ባህሪይና ድክመት ተሸክሞ የሚኖር መሆኑ ይረሳል፡፡ በመሆኑም የሚያደርገው ነገር ሁሉ በአድናቂዎቹ መረዳት ትክክል ነው፡፡ የሚያደርገው ሁሉ! ከአለባበሱ እስከ አበላሉና አጠጣጡ፣ ከአነጋገሩ እስከ ሚያምንበትና እስከሚከተለው አስተሳሰብ ድረስ “ትክክል” ነው፡፡ ስለሆነም ተከታዩ ብዙ ነው፡፡ እናም ግለሰቡ ካምፕ ሲቀይር ይታመናል፡፡ ከመታመንም አልፎ “ትክክል ነው፤ አይቶት ነው፤ ገብቶት ነው …” ወዘተ የሚባል ምስክርነት በአድናቂዎቹ ተሰጥቶት ካምፕ ቅየራው ይሞገሳል፡፡
ለምን? ብሎ የሚጠይቅ ብዙም የለም፡፡ ግለሰቡ ለምን ይህን እንዳደረገ የሚጠይቅ የለም፡፡ ስለ አቅሙም ሆነ አቋሙ የሚሞግት የለም፡፡ በፊት ለምን እዚያ ካምፕ ነበረ? አሁን ለምን ካምፕ ቀየረ? የሚል የለም፡፡ ግለሰቡ ህዝብን ዋሽቶና አታሎ ራሱን በመጥቀሙ፣ በራሱ በህዝብ ሊገሰጽና ሊቀጣ ሲገባ ጭራሽ አበጀህ ተብሎ ይሞካሻል፡፡ ዜናው ከዳር ዳር ተዳርሶ ይወደሳል፡፡ ሰሞኑን እንኳን የሆነውን ልብ እንበል፡፡ “ዘይገርም” ነው!
ጥፋቱ በዚህ አይቆምም፡፡ የግለሰቡን ካምፕ መቀየር ተከትሎ አድናቂዎቹም በሏቸው ተከታዮቹ አብረውት ካምፕ ይቀይራሉ፡፡ ለምን? ሳይሉ፣ ሳይጠይቁ፣ ሳይገባቸው… ይከተሉታል፡፡ ተያይዞ መንጎድ ነው፡፡ የመንጋ ጉዞ!
የሚገርመው እነዚህ ካምፕ ቀያሪዎች ካምፕ ቅየራቸው የሚያቆም አይደለም፡፡ ዛሬ ቀይረው የሄዱበት ካምፕ ነገ ጊዜ ሲከዳው ደግሞ ተመልሰው ጥለውት የሄዱት ካምፕ ውስጥ ወይንም ሌላ ካምፕ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ በዚህ የካምፕ ቅየራ ሂደት ውስጥ ሁሌም ተጎጂው ይኸው መከረኛ ህዝብ ነው፡፡ እኔና እናንተ፡፡ እንዴት ካላችሁ እመለስበታለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ወደ እሱ ድምዳሜ የሚያደርሰኝን ሌላ ጉዳይ ላስቀድም፡፡
ካምፕ ቀያሪዎቹ ያለባቸውን ድክመት (የአቅም፣ የአቋም…) እንዲሁም ተገብቷቸውም ይሁን ሳይገባቸው በህዝብ ዘንድ ያገኙትን አድናቆት፣ ተሰሚነትና ቦታ በቅጡ የሚረዳው መንግስት የግለሰቦቹን ካምፕ ቅየራ ላልተገባና ብዙም ሩቅ ለማያስኬድ ፕሮፓጋንዳ ይጠቀምበታል፡፡
ምክንያቱም ግለሰቦቹ ከዓመታት በፊት ከእሱ በተቃራኒ የነበረ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ወደ እሱ ካምፕ መጥተዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም የነበራቸውን አመለካከትና “አሁን ያ አመለካከታቸው ስህተት መሆኑን አምነው መለወጣቸውን” ወዘተ አግንኖ ለህዝብ እያሳየ፣ የእሱን ትክክለኛነት ሊያሳይበት ይሞክራል፡፡
ታዲያ አንድ ነገር ልብ እንበል፡፡ ተቀብሏቸዋል ማለት አምኗቸዋል ወይም ያምናቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የተቀበላቸው የሚሰጡትን ጥቅም ስለሚያውቀው ብቻ ነው፡፡ እሱ ነኝ ለሚለው ትክክለኛነት “ቀሽም ማሳያ” ስለሆኑ ያደናግርባቸዋል፡፡ ደግሞም አቅማቸውን ያውቃል፡፡ ወይ ስሜታዊ ወይንም አድርባይ ናቸው፡፡
እንዳቅማቸው ይይዛቸዋል፡፡ የሚፈልጉትንም ያውቃል፡፡ ብዙዎቹ ያልደከሙበትንና የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት የሚሹ ናቸው፡፡ ሁሉ በእጁ ነውና ሞልቶ ከተትረፈረፈውና የህዝብ ነው ከሚለው “ጎተራው” በአይነት ይሰፍርላቸዋል፡፡ ምን ገዶት!
እንግዲህ በዚህ ሁሉ ማምታታት ውስጥ “ተጎጂው ህዝብ ነው” ማለቴ ለዚህ ነው፡፡ እንዴት? አንድ፦ ሲጀመርም የሚፈልጉትን ለማግኘት ካምፕ የሚቀይሩት ሰዎች የሚዋሹትና የሚያታልሉት አውቆም ይሁን ሳያውቅ የሚያከብራቸውንና የሚወዳቸውን ህዝብ ነው፡፡ ልብ በሉ! ለሚወዳቸው ህዝብ የሚሰጡት ምላሽ ውሸትና ማታለል ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ያለምክንያት “ተለውጠው ሊለውጡት” ይሻሉ፡፡ እውነት ለመናገር ከዚህስ በላይ በደል ምን አለ?
ሁለት፦ በተጨባጭ ለህዝቡ በሚሰራው ሳይሆን በየሚያጋጥመው ውሃ የማይቋጥር ክስተት ሁሉ ትክክለኛነቱን ለህዝብ ለማሳመን የሚደክመው መንግስትም ያገኘውን አግንኖና ሌላ ያልተገባ ትርጉም ሰጥቶ፣ በዚህም የማይጠቅም ትርፍ ለማግኘት ፕሮፓጋንዳውን የሚለቀው እዚሁ ህዝብ ላይ ነው፡፡ እኔና እናንተ ላይ፡፡
ትርፉ ተገቢና ዘላቂ ትርፍ ባይሆንም ሁለቱም አካላት ከዚህ አጉል ጨዋታ ማትረፋቸው አይቀርም፡፡ ካምፕ ቀያሪው ቀይሮ በሄደበት ካምፕ ውስጥ ሊያገኝ የፈለገውን ትርፍ ለጊዜውም ቢሆን (ማግኘት ከተባለ) ያገኛል፡፡ የካምፑ ባለቤትም የትናንት ተቃራኒው ዛሬ ወደ ካምፑ ስለመጣ (ምን ፈልጎ እንደመጣ ቢያውቀውም ቅሉ) ራሱን ትክክለኛ አድርጎ ለህዝብ ለማሳየት በመሞከር ያደናግርበታል፡፡ ወደ ካምፑ ያልመጡትንም ያጣጥልበታል፤ ያንኳስስበታል፡፡ በዚህም እሱም አጉል ትርፍ ያተርፋል፡፡ እናስ ማን ተጎዳ መልሱ አሻሚ አይደለም፡፡ “መጥኔ እንጂ ለዚህ ህዝብ!” አለ ገጣሚው፡፡
አስገራሚው ነገር ታዲያ በዚህ ጨዋታ ተጎጂ የሆነው ህዝብ ሳያውቀው ለራሱ መጎዳት አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ራሱ መሆኑ ነው፡፡ ይኸውም ምናልባትም ልክ ካልሆነና ከተዛባ የወል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡ ሲጀመር የምናደንቀውንና የምናከብረውን ግለሰብ፣ የምናደንቀውና የምናከብረው ተጨባጭና አሳማኝ ምክንያት ይዘን ሳይሆን “ቲፎዞ”ንና ሚዲያውን ተከትለን ነው፡፡ እውነት ብቃቱ ምን ላይ ነው? ምንስ ያህል ነው? ምንስ ሠርቶአል?... በማለት ጠይቀን አይደለም፡፡ ከዚያም አልፈን ግለሰቡን ከሙያው አውጥተን “ከሀሌ ኩሉ” (ሁሉን ቻይ፤ በሁሉ የተካነ…) አድርገን እናስበዋለን፡፡ሌላው ችግር ደግሞ ይህንን አደንቀዋለሁና አከብረዋለሁ የምንለውን ግለሰብ (ከሙያው ባለፈ) እንደ አንድ ሰው የመቁጠርም ሆነ ግለሰቡ የሰው ልጅ ሊኖርበት የሚችለው ድክመቶች እንዳሉት አናስብም፡፡ እንደ ፍፁም እንቆጥረዋለን፡፡ ግለሰቡ በጥቅም ሊዳኝ እንደሚችል፣ እንደ ማንኛውም ግለሰብም ሊዋሽም ሆነ የተለየ ዓላማ ሊኖረው እንደሚችል አናስብም፡፡  እጅጉን እናምነዋለን፡፡ ስለምናምነውና እንደ ፍፁም አዋቂ ስለምንቆጥረውም የሚያደርገውን ትክክል ነው ብለን እናጸድቅለታለን፡፡ ከዚያም አልፈን ድርጊቱን ጭራሽ አወድሰን እናራግብለታለን፡፡ የጨዋታው የመጨረሻ ተጎጂ እኛ መሆናችንን ልብ አንልም፡፡ “ራስ በገመዱት ጅራፍ መገረፍ” ይሉታል ይሄ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ ከዓመታት በፊት ያጫወተኝን ጠቅሼ ላብቃ፡፡ እዚሁ ከተማችን ውስጥ በሚገኝ አንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ በሚገኙ የሃይማኖቱ መሪዎች መካከል የአቋም ልዩነት ተነስቶ መሪዎቹ ለሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመከፈሉ ማዕከል በተቋሙ የመጨረሻ ዋናው ሰው ዙሪያ ነበር፡፡ ከፊሎቹ ከሳቸው ጋር ቆመዋል፡፡
 ከፊሎቹ ደግሞ እሳቸውን ተቃውመው፡፡ ታዲያ ተቃውመው የቆሙትን አካላት ከሚያስተባብሩት አባቶች አንዱ እንደ ትናንት ተቃውሞውን ሲመሩና ሲያስተባብሩ ውለውና አምሽተው ጠዋት ከተቃራኒው ጎራ ጋር ቆመው ተገኙ፡፡ ታዲያ በዚህ ቅጽበታዊ ካምፕ ቅየራ እጅጉን ያዘኑት ጓደኛቸው ምን አሏቸው መሰላችሁ? “ምልስ አፈር!”  መልካም ሰንበት!!




መንግስት መሰረተቢስ ውንጀላ ነው በሚል ያጣጥለዋል
የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የግል ሚዲያ ላይ የሚያደርገው የተራቀቀ ጫና፣ ሚዲያዎቹ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ በሚሰሩት ዘገባ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ምህዳሩን እያጠበበባቸው ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለጸ፡፡
መንግስት የግሉን ሚዲያ እንደ አንድ የታመነ የመረጃና የትንተና ምንጭ ሳይሆን እንደ ስጋት በመቁጠር የተጠና ጫና ያደርስበታል ያሉት የሂውማን ራይት ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ሚዲያው በመጪው ምርጫ ቁልፍ ሚና መጫወት ቢኖርበትም፣ በአንጻሩ ግን በርካታ የአገሪቱ ጋዜጠኞች ምርጫን በተመለከተ በሚያቀርቡት ዘገባ ለእስር እንዳረጋለን የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
መንግስት በአገሪቱ የግል ሚዲያ ላይ የሚያደርገው ጫና እየተባባሰ በመምጣቱ ባለፈው አመት ብቻ ስድስት የግል የህትመት ውጤቶች ተዘግተዋል፤ በ22 ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አሳታሚዎች ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ ከ30 በላይ ጋዜጠኞችም እስራትን በመፍራት አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት፡፡
“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም፣ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ጥሰት በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለው  ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ነጻ ዘገባን የሚያቀጭጩ ተግባራትን ሲፈጽም እንደቆየ ጠቅሶ፣ በእነዚህ አመታትም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው 19 ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና 60 ያህሉም መሰደዳቸውን ገልጿል፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች በስደትና በአገራቸው የሚገኙ ከ70 በላይ ጋዜጠኞችን አነጋግሬ ያዘጋጀሁት ነው ባለው በዚህ ሪፖርቱ፣ በአገሪቱ አብዛኞቹ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ ጥቂት የግል የህትመት ውጤቶችም እንዳይዘጉ በመስጋት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሲዘግቡ በአብዛኛው በራሳቸው ላይ ሳንሱር እንደሚያደርጉ ጠቁሟል፡፡መንግስት በበኩሉ፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸው የነፃነትና መብት ጥሰትን የተመለከተ ሪፖርቶች መሰረተ ቢስ እንደሆነ በመግለፅ በተደጋጋሚ ማጣጣሉ ይታወቃል፡፡

Published in ዜና
Page 7 of 18